የዘላለም ሕይወት እንዳልዎት እርግጠኛ ነዎት?

በመጀመሪያ እንኳን ወደዚህ የደህንነት ትምህረት ጥናት መጡ እያልን መጽፍ ቅዱስ ለማጥናት ላደረጉት ቆራጥ ውሳኔ ልናደንቅዎ እንወዳለን፡፡  ይህ ‹የደኅንነት ትምህርት› ኮርስ የዘላለም ሕወትዎን በተመለከተ ወሰኝ ርእሰ ጉዳይ መሆኑን ልብ ይበሉ፡፡ በዚህ ጥናት ውስጥ የቀረቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች እርሶ ወደ መንግስተ ሰማይ ለሚያደርጉት የጉዞ መሰናዶ በእጅጉ እንደሚጠቅሞዎት እናምናለን፡፡ በዚህ ኮርስ ውስጥ የቀረቡ ሃሳቦች የእኛን አስተሳሰብና ግምት የያዙ ሳይሆኑ በቀጥታ መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን የሚናገሩ ናቸው፡፡ መጽሐፍ ቅዱሱ ሲናገር ልንናገር፣ ዝም ሲል ደግሞ ዝም ልንል ግድ ነውና፡፡ የምናደርጋቸውን ነገሮች ሁሉ በመጽሐፍ ቅዱስ መሰረት ልናደርጋቸው፣ በጽሐፉ በስማቸው የሚጠራቸውንም በግልጽ ልንጠራቸው ይገባል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ከሚለው የነሰ፣ የበዛ፣ ወይም የተለየ ነገር ሁሉ የስህተት ትንህርት ነው፡፡

ከእግዚአብሔር ቃል እውቀት ማነስ የተነሳ በተፈጠሩት በርካታ ሃይማኖቶች ምክኒያት በአለም ሕዝቦች መካከል ከፍተኛ ግራ በጋባት ይስተዋላል፡፡ በአሁኑ ሰአት በአለማችን ላይ የተለያየ አስተምህሮዎች፣ የስነ መለኮት ምልከታዎች እና አስተሳሰቦች ያልዋቸው ከ 600 በላይ ቤተ እምነቶች ይገኛሉ፡፡ በእነዚህ በርካታ እምነቶች ‹የእመን› ጥያቄ የሚቀርብላቸው የአለማችን ሰዎች ምን እና ማንን ማመን እንዳለባቸው ለመወሰን ግራ ተጋብተዋል፡፡ አዳኛችን የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ በፈቃዱ በከፈለው ስቃይና ሞት ለኃጢአታችን ይቅርታ የሚያስፈልገውን ሁሉ አቅርቦልናል፡፡ በፍርድ ቀን ከሰይጣንና ከመላእክቱ ጋር ወደ ወደ ዘላለም እቶን እሳት መጣል አይገባንም፡፡ እናም ለመዳን የወንጌልን እውነት መታዘዝ ይኖርብናል፡፡ ወንጌል ምንድን ነው? ለመዳን ምን ማድረግ ይኖርብኛል? በዚህ ጥናት ውስጥ እግዚአብሔር በሰማይ ያዘጋጀልንን የዘላለም ሕይወት ስጦታ ለመውረስ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ማድረግ እንዳለብን የሚናገረውን አብረን እናያለን፡፡

ከመጽሐፍ ቅዱስ የተወሰዱ ጥቅሶች በሙሉ ጠመም/ዘመም ባለ የፊደል አጻጻፍና ደማቅ ሆነው የቀረቡ ሲሆን ለእነዚህ ጥቅሶች ልብዎንና አእምሮዎን ሊከፍቱ ይገባል፡፡ እግዚአብሔር በእነዚህ ቃሎች ውስጥ ምን ሊያስተላልፍ እንደፈለገ መግለጥ የዚህ ኮርስ ዋነኛ አላማ ነው፡፡ ከመጽሐፍ ቅዱስ የተወሰዱትን እነዚህን ጥቅሶችን ሲያነቡ ለተሰመረባቸው ቃላት ልዩ ትኩረት እንዲሰጡ እናሳስባለን፡፡

“የዘላለም ሕይወት እንዳልዎት እርግጠኛ ነዎት?” የሚለው ይህ ኮርስ በ10 ትምህርቶች የተከፋፈለ ነው፡፡ ከእያንዳንዱ ትምህርት በኋላ የምርጫ እና የእውነት/ውሸት ጥያቄዎች ቀርበዋል፡፡ የጥያቄዎቹን ትክክለኛ መልሶች ከጥያቄዎቹ ጋር በቀረቡት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ውስጥ ያገኙዋቸዋል፡፡ ይህን ኮርስ ማጥናት በዘላለም ሕይወትዎ ላይ ታላቅ ሚና እንዲጫወት የዘወትር ጸሎታችን ነው፡፡ ማነኛውም ጥያቄ ሆነ አስተያየት ቢኖርዎ ለመምህሮ ያሳውቁ ወይም በሚከተለው አድራሻ ቢልኩልን ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ቃል እንገባለን፡፡

መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የሕይወትዎ ጌታ በማድረግ ቀሪው ዘመንዎን ለመኖር ወስነው ከሆነ፣ ይህንን ሊንክ በመጫን ስምዎንና የኢ-ሜይል አድናሻዎን ይላኩልንና፣ ለመንፈሳዊ ሕይወት እድገትዎ የሚቻለንን ሁሉ እገዛ እናደርግሎታለን።

ከዘላለም ሞት ፍርድ ለመዳን ምን ማድረግ አለብኝ?

ሞትን የማይፈራ ማን ይሆን? ሞት በሰው ልጆች ሕይወት ፊት የተደቀነ ትልቅ ጠላት ነው። ሰው ብዙ ነገር ሊያሸንፍ ይችል ይሆናል። ሞትን ማሸነፍ ግን የማይታሰብ ትግል ነው። ብርቱዎች፣ ጀግኖች፣ መሪዎች፣ ፖለቲከኞች፣ ሳይንቲስቶች ሁሉ የዚህ የሞት ሰይፍ ሰለባ ናቸው። ሞት ትንሽ ትልቅ ሳይል፣ ጥቁር ነጭ ሳይለይ፣ የተማረ መሃይም ሳያስቀር ሁሉን እያጨደ፣ ሁሉን እየከመረ፣ በሁሉ ላይ ነግሶ ዘመን ጠግቧል።

ብዙዎች የሚያውቁት ሞት፣ ነፍስ ከስጋ ተለይታ የምትሄድበትን የመጀመሪያ ሞት ነው። ሞት ይህ ብቻ ቢሆን ሃላፊነት የጎደላቸው፣ ኢሞራላውያን፣ እንዳሰኛቸው የፈቀዱትን እና የወደዱትን ሁሉ እያደረጉ የኖሩ ምግባረ ብልሹዎች፣ እግዚአብሔር የለም ብለው በድፍረት የተናገሩ መናፍቃን ሁሉ ከህሊና ክስ ነጽተው በሰላም ወጥተው ባደሩ ነበር። የክርስቲያኖችም የትንሳኤ ስብከት ከንቱ ድካም ነበር። ሆኖም እውነታው አይደለም። ከሞት በኋላ ሌላ ሞት አለ። ከመጀመሪያው ሞት በኋላ ሁለተኛው ሞት አለ። ከአካላዊው ሞት በኋላ መንፈሳዊው ሞት አለ።

ከሁሉ በላይ የሚያሰጋው ሞት ይህ ሞት ነው። ምክንያቱም ይህ ሞት እንደ አካላዊው ሞት ጊዚያዊ አይደለም። ይህ ሞት ዘላለማዊ ነው። ይህ ሞት ከመኖር ወደ አለመኖር መቀየር ማለትም ጨርሶ መጥፋት ሳይሆን ከእግዚአብሔር ተለይቶ አሳቱ በማይጠፋበት  የስቃይ ስፍራ መኖር ማለት ነው፣ ‘‘እንግዲህ እንክርዳድ ተለቅሞ በእሳት እንደሚቃጠል፥ በዓለም መጨረሻ እንዲሁ ይሆናል። የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል፥ ከመንግሥቱም እንቅፋትን ሁሉ ዓመፃንም የሚያደርጉትን ይለቅማሉ፥ ወደ እቶነ እሳትም ይጥሉአቸዋል፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል’’ (ማቴዎስ 1340-42)

መንፈሳዊ የሆነውን ይህን ሞት መጽሐፍ ቅዱስ ሁለተኛው ሞት እያለ ይጠራዋል፣ ‘‘ሞትና ሲኦልም በእሳት ባሕር ውስጥ ተጣሉ። ይህም የእሳት ባሕር ሁለተኛው ሞት ነው’’ (ዮሐንስ ራዕይ 2014) ‘‘ዳሩ ግን የሚፈሩና የማያምኑ የርኵሳንም የነፍሰ ገዳዮችም የሴሰኛዎችም የአስማተኛዎችም ጣዖትንም የሚያመልኩ የሐሰተኛዎችም ሁሉ ዕድላቸው በዲንና በእሳት በሚቃጠል ባሕር ነው፤ ይኸውም ሁለተኛው ሞት ነው’’ (የዮሐንስ ራዕይ 218)

ለመሆኑ ከዚህ ሁለተኛ ሞት እንዴት ማምለጥ እንችላለን? ከሲኦል እሳት፣ ከዚህ የስቃይ ስፍራ የሚድኑት እነማን ናቸው? ምን ባደርግ ነው ከዘላለም ሞት የምድነው?

ከአዳም ውድቀት ጀምሮ በሰው ላይ ተነጣጥራ ያለችው የእግዚአብሔር ቁጣ መብረጃዋ አንድ ነገር ብቻ ነው። የእግዚአብሔር ቁጣ የእግዚአብሔርን ፍትህ ያሳያል። የእግዚአብሔር ፍትህ ደግሞ የእኛን ሞት ይጠይቃል (ሮሜ 6፡23)። የእግዚአብሔር ፍትህ የሃጢአተኛውን ሞት ይሻል (ዕብራውያን 9፡22)። ሁላችን ሃጢአትን ስላደረግን ለዚህ ሞት (የእግዚአብሔር ቁጣ ውጤት) ተዘጋጅቶልናል (ሮሜ 6፡23)። ሃጢአትን ያላደረገ በዚህ ምድር ላይ ስለሌለ (መክብብ 7፡20፤ 1ዮሐንስ 1፡8፤ ሮሜ 3፡10-18) ከዚህ ፍርድ ስር ያልሆነ ሰው በምድር ላይ የለም።

ሆኖም ግን፣ ከዚህ ፍርድ ስር መሆናችን ያሳዘነው እግዚአብሔር የራሱን ፍትሃዊ ፍርድ ራሱ ሊቀበልልን ወሰነ። በዚህም ምክንያት ሁላችን ከምንሞት አንድ ልጁ በእኛ ፈንታ እንዲሞት ፈቀደ (የሐንስ 11፡50-52)።  ይህ ቅዱስ ልጁ፣ ኢየሱስ ይባላል። ኢየሱስ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ ነው (ዮሐንስ 1፡29)። እግዚአብሔር በእኛ ላይ ሊያፈሰው የነበረውን ቁጣ በልጁ በኢያሱስ ላይ አፈሰሰው። ኢየሱስ በእኛ ሞት ፈንታ ሞተልን። በዚህ ምትክ ሞት ምክንያት በኢየሱስ ሞት እና ትንሳኤ የሚያምኑ ሁሉ ከእግዚአብሔር ቁጣ እንዲተርፉ ሆነ። እግዚአብሔር፣ በኢየሱስ ሞትና እና ትንሳኤ ያመኑትን ሁሉ፥ ከሞት ፍርድ ያድናቸዋል (1ተሰሎንቄ 4፡14)። ‘‘በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም’’ (ዮሐንስ  3፥36)።

በልጁ ሞት እና ትንሳኤ ማመን ማለት፣ የእርሱ ሞት እግዚአብሔር በእኔ ላይ የነበረውን ቁጣ እንዲያነሳና ከእኔ ጋር ሰላም እንዲያርግ (ሮሜ 5፡1) አድርጎታል ብሎ ማመን ነው። በልጁ የሚያምን ከእንግዲህ የእግዚአብሔር ቁጣ በእርሱ ላይ የለበትም (ዮሐንስ  3፥36)። የእግዚአብሔር ጠላት (ሮሜ 5፡10) ሳይሆን ወዳጅ ሆኗል። የኢየሱስ የሚያምን ሰው የኢየሱስ ሞት ለእግዚአብሔር ቁጣ በቂ ምላሽ እንደሰጠ ያምናል። ተጨማሪ የማምለጫ ስልቶችንም አይቀየስም። የእግዚአብሔር የድነት መንገድ  (ዮሐንስ 14፡6) በቂ እና ፍጹም እንደሆነ ያምናልና።

ከእግዚአብሔር ቁጣ ለመትረፍ የሚበጁ ሌሎች አማራጮች ሁሉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደሉም። በራስዎ ‘‘መልካም’’ ምግባር ወይም ስራ እግዚአብሔርን ደስ አሰኝተው ከእግዚአብሔር ቁጣ ለመትረፍ እንደሚችሉ ያስቡ ይሆን? ‘‘የተቀደሱ’’ ቦታዎች ላይ በመሄድ ከእግዚአብሔር ፍርድ የሚያመልጡ ይመስሎታል? ሃይማኖታዊ ክብረ በአላትን አዘውትረው በመጠበቅ ከቁጣው የሚሸሸጉ ይመስሎታል? የፓስተር ወይም የጳጳስ ልጅ ወይም ዘመድ በመሆንዎ የእግዚአብሔርን ፍረድ ሊያጣምምሙ የሚችሉ ይመስሎታል? ቁጣውን ለማፍሰስ በገዛ ፃድቅ ልጁ ላይ እንኳ ያልራራ (ሮሜ 8፡34)፣ ለእርሶ ጽድቅ ያውም ደግሞ የመርገም ጨርቅ ለሆነ ጽድቅዎ የሚራራ ይመስሎታል (ሮሜ 10፡2-3)? ገዳም በመግባትዎ፣ ለድሆች በመመጽወትዎ፣ ሳያጓድሉ በመጾምዎ እና በመፀለዮ፣ አዘውትረው ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሄድዎ ምክንያት እግዚአብሔርን ከቁጣው የሚመልሱት ይመስሎታል? እንዲህ የሚያስቡ ከሆነ እንግዲያው ክርስቶስ በከንቱ ሞተ (ገላቲያ 2፡21)። እነዚህ መልካም ነገሮች ሁሉ ከዚህ ከእግዚአብሔር ቁጣ በክርስቶስ ሞት አማካኝነት ያመለጠ አማኝ ሁሉ ሊያፈራቸው የሚጠበቁ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ (ገላትያ 5፡20) ናቸው። እናም የሚናቁ አይደሉም። ነገር ግን፣ ከእግዚአብሔር ፍርድ የማምለጫ አቋራጮች አይደሉም። ከእግዚአብሔር ቁጣ እና ፍርድ ማምለጥ የሚቻልበት ሌላ አማራጭ ቢኖር ኖሮ እግዚአብሔር ፃድቅ እና አንድያ ልጁን ለሃጢአተኞች ሞት ተላልፎ እንዲሰጥ የሚፈቅድ የመስሎታል?ቅዱስ ጳውሎስ የሰው ልጅ እንዴት ከእግዚአብሔር ቁጣ ሊድን እንደሚችል የተናገረውን ተናግረን እናጠናቅ፣ ‘‘ይልቁንስ እንግዲህ አሁን በደሙ ከጸደቅን በእርሱ ከቍጣው እንድናለን (ሮሜ 5፡9)’’።

መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የሕይወትዎ ጌታ በማድረግ ቀሪው ዘመንዎን ለመኖር ወስነው ከሆነ፣ ይህንን ሊንክ በመጫን ስምዎንና የኢ-ሜይል አድናሻዎን ይላኩልንና፣ ለመንፈሳዊ ሕይወት እድገትዎ የሚቻለንን ሁሉ እገዛ እናደርግሎታለን።

 

ታላቁ የእግዚአብሔር የቁጣ ቀን መጥቶአል፤ ማንስ ሊቆም ይችላል? ራዕይ 6፡17

የሰው ልጅ የፈጣሪውን ትዕዛዝ በገዛ ፈቃዱ ከተላለፈባት እለት ጀምሮ ቅዱስ የሆነው ፈጣሪ፣ ከእርሱ ክብር በጎደለው (ሮሜ 3፡22-23) ፍጡሩ ላይ ተቆጥቷል። ይህ ቁጣ ሃጢአተኞችን ሁሉ ሊበላ ያለ ቁጣ ነው። እውነትን በዓመፃ በከለከሉ ሰዎች በኃጢአተኝነታቸውና በዓመፃቸው ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር ቍጣ ከሰማይ የሚገለጥበት ጊዜ ደርሷል (ሮሜ 1፥18)። ቅዱስ ዮሐንስ በራዕዩ ላይ የእግዚአብሔር የቁጣ ጽዋዎች ሞልተው በምድር ላይ የሚፈሱበት ሰአት እንዳለ ገልጿል (ራእይ 16፥1፤ ራእይ 15፥7)።

ይህ የእግዚአብሔር ቁጣ ለተወሰኑ ሰዎች ብቻ የተጠበቀ አይደለም። ለተወሰነ የሃይማኖት ተከታዮች፣ ለተወሰኑ ዘሮች ወይም ነገዶች፣ ወይም ለተወሰኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ብቻ ወይም የቆዳ ቀለም ላላቸው የተጠበቀም አይደለም። ለእርሱ በማይታዘዙ ሰዎች ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር ቁጣ ይመጣል (ኤፌሶን 5፥6፤ ቆላስይስ 3፥6)።

የእግዚአብሔር ቁጣ ሕይወታችንን ለዘላለም ከእግዚአብሔር ቅድስና ለይቶ በዘላለም እሳት ውስጥ የሚያኖር ቁጣ ነው። ይህ ቁጣ ከምናስበው በላይ ብርቱ ነው (ራእይ 19፥15)።

ይህ ታላቅ የእግዚአብሔር ቁጣ ንስሃ በማይገቡ ሰዎች ላይ እንደነደደ እስከ ፍርድ ቀን ድረስ እንደሚቆይ ጳውሎስ በ ሮሜ 2፥5 እንዲህ በማለት ያሳየናል፣ ‘‘ነገር ግን እንደ ጥንካሬህና ንስሐ እንደማይገባ ልብህ የእግዚአብሔር ቅን ፍርድ በሚገለጥበት በቍጣ ቀን ቍጣን በራስህ ላይ ታከማቻለህ።’’

‘‘ታዲያ፣ እንዴት ከዚህ የእግዚአብሔር ቁጣ ልተርፍ እችላለው?’’ መልሱን ሐዋሪያው ቅዱስ ዮሐንስ እንዲህ ሲል ያሳውቀናል፣  ‘‘በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም’’ (ዮሐንስ  3፥36)።

ከአዳም ውድቀት ጀምሮ በሰው ላይ ተነጣጥራ ያለችው የእግዚአብሔር ቁጣ መብረጃዋ አንድ ነገር ብቻ ነው። የእግዚአብሔር ቁጣ የእግዚአብሔርን ፍትህ ያሳያል። የእግዚአብሔር ፍትህ ደግሞ የእኛን ሞት ይጠይቃል (ሮሜ 6፡23)። የእግዚአብሔር ፍትህ የሃጢአተኛውን ሞት ይሻል (ዕብራውያን 9፡22)። ሁላችን ሃጢአትን ስላደረግን ለዚህ ሞት (የእግዚአብሔር ቁጣ ውጤት) ተዘጋጅቶልናል (ሮሜ 6፡23)። ሃጢአትን ያላደረገ በዚህ ምድር ላይ ስለሌለ (መክብብ 7፡20፤ 1ዮሐንስ 1፡8፤ ሮሜ 3፡10-18) ከዚህ ፍርድ ስር ያልሆነ ሰው በምድር ላይ የለም።

ሆኖም ግን፣ ከዚህ ፍርድ ስር መሆናችን ያሳዘነው እግዚአብሔር የራሱን ፍትሃዊ ፍርድ ራሱ ሊቀበልልን ወሰነ። በዚህም ምክንያት ሁላችን ከምንሞት አንድ ልጁ በእኛ ፈንታ እንዲሞት ፈቀደ (የሐንስ 11፡50-52)።  ይህ ቅዱስ ልጁ፣ ኢየሱስ ይባላል። ኢየሱስ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ ነው (ዮሐንስ 1፡29)። እግዚአብሔር በእኛ ላይ ሊያፈሰው የነበረውን ቁጣ በልጁ በኢያሱስ ላይ አፈሰሰው። ኢየሱስ በእኛ ሞት ፈንታ ሞተልን። በዚህ ምትክ ሞት ምክንያት በኢየሱስ ሞት እና ትንሳኤ የሚያምኑ ሁሉ ከእግዚአብሔር ቁጣ እንዲተርፉ ሆነ። እግዚአብሔር፣ በኢየሱስ ሞትና እና ትንሳኤ ያመኑትን ሁሉ፥ ከሞት ፍርድ ያድናቸዋል (1ተሰሎንቄ 4፡14)። ‘‘በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም’’ (ዮሐንስ  3፥36)።

በልጁ ሞት እና ትንሳኤ ማመን ማለት፣ የእርሱ ሞት እግዚአብሔር በእኔ ላይ የነበረውን ቁጣ እንዲያነሳና ከእኔ ጋር ሰላም እንዲያርግ (ሮሜ 5፡1) አድርጎታል ብሎ ማመን ነው። በልጁ የሚያምን ከእንግዲህ የእግዚአብሔር ቁጣ በእርሱ ላይ የለበትም (ዮሐንስ  3፥36)። የእግዚአብሔር ጠላት (ሮሜ 5፡10) ሳይሆን ወዳጅ ሆኗል። የኢየሱስ የሚያምን ሰው የኢየሱስ ሞት ለእግዚአብሔር ቁጣ በቂ ምላሽ እንደሰጠ ያምናል። ተጨማሪ የማምለጫ ስልቶችንም አይቀየስም። የእግዚአብሔር የድነት መንገድ  (ዮሐንስ 14፡6) በቂ እና ፍጹም እንደሆነ ያምናልና።

ከእግዚአብሔር ቁጣ ለመትረፍ የሚበጁ ሌሎች አማራጮች ሁሉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደሉም። በራስዎ ‘‘መልካም’’ ምግባር ወይም ስራ እግዚአብሔርን ደስ አሰኝተው ከእግዚአብሔር ቁጣ ለመትረፍ እንደሚችሉ ያስቡ ይሆን? ‘‘የተቀደሱ’’ ቦታዎች ላይ በመሄድ ከእግዚአብሔር ፍርድ የሚያመልጡ ይመስሎታል? ሃይማኖታዊ ክብረ በአላትን አዘውትረው በመጠበቅ ከቁጣው የሚሸሸጉ ይመስሎታል? የፓስተር ወይም የጳጳስ ልጅ ወይም ዘመድ በመሆንዎ የእግዚአብሔርን ፍረድ ሊያጣምምሙ የሚችሉ ይመስሎታል? ቁጣውን ለማፍሰስ በገዛ ፃድቅ ልጁ ላይ እንኳ ያልራራ (ሮሜ 8፡34)፣ ለእርሶ ጽድቅ ያውም ደግሞ የመርገም ጨርቅ ለሆነ ጽድቅዎ የሚራራ ይመስሎታል (ሮሜ 10፡2-3)? ገዳም በመግባትዎ፣ ለድሆች በመመጽወትዎ፣ ሳያጓድሉ በመጾምዎ እና በመፀለዮ፣ አዘውትረው ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሄድዎ ምክንያት እግዚአብሔርን ከቁጣው የሚመልሱት ይመስሎታል? እንዲህ የሚያስቡ ከሆነ እንግዲያው ክርስቶስ በከንቱ ሞተ (ገላቲያ 2፡21)። እነዚህ መልካም ነገሮች ሁሉ ከዚህ ከእግዚአብሔር ቁጣ በክርስቶስ ሞት አማካኝነት ያመለጠ አማኝ ሁሉ ሊያፈራቸው የሚጠበቁ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ (ገላትያ 5፡20) ናቸው። እናም የሚናቁ አይደሉም። ነገር ግን፣ ከእግዚአብሔር ፍርድ የማምለጫ አቋራጮች አይደሉም። ከእግዚአብሔር ቁጣ እና ፍርድ ማምለጥ የሚቻልበት ሌላ አማራጭ ቢኖር ኖሮ እግዚአብሔር ፃድቅ እና አንድያ ልጁን ለሃጢአተኞች ሞት ተላልፎ እንዲሰጥ የሚፈቅድ የመስሎታል?ቅዱስ ጳውሎስ የሰው ልጅ እንዴት ከእግዚአብሔር ቁጣ ሊድን እንደሚችል የተናገረውን ተናግረን እናጠናቅ፣ ‘‘ይልቁንስ እንግዲህ አሁን በደሙ ከጸደቅን በእርሱ ከቍጣው እንድናለን (ሮሜ 5፡9)’’።

መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የሕይወትዎ ጌታ በማድረግ ቀሪው ዘመንዎን ለመኖር ወስነው ከሆነ፣ ይህንን ሊንክ በመጫን ስምዎንና የኢ-ሜይል አድናሻዎን ይላኩልንና፣ ለመንፈሳዊ ሕይወት እድገትዎ የሚቻለንን ሁሉ እገዛ እናደርግሎታለን።

ዳግም ልደት ማለት ምን ማለት ነው?

ዳግም ልደት ከክርስትና ዋነኛ ትምህርቶች መካከል አንዱ ነው። የሰው ልጅ ሁለት ልደቶች አሉት። አንደኛው ከስጋ ፈቃድ በሩካቤ ከአባት እና ከእናት የሚያገኘው ስጋዊ ልደት ሲሆን ሁለተኛ ደግሞ ኢየሱስን በማመን እና በመቀበል የሚያገኘው መንፈሳዊ ልደት ነው፣ ‘‘ለተቀበሉት ሁሉ ግንበስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም’’ (ዮሐንስ ወንጌል 1፡12-13)።

ያለዚህ ልደት ሰው የእግዚአብሔርን መንግስት ሊወርስ አይችልም። ሰው በስጋ ልደቱ የሰው ልጅ እንደሚባል፣ በመንፈስ ልደቱ ደግሞ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል። ስጋ እና ደም የእግዚአብሔርን መንግስት ሊወርሱ አይችሉም፣ የእግዚአብሔር ልጆች ግን የእግዚአብሔርን መንግስት ሊወርሱ ይችላሉ። የመጀመሪያውን ልደት ብቻ ያገኙ፣ የእግዚአብሔር መንፈስ በውስጣቸው የለምና ስጋ እና ደም ብቻ ተብለው ይጠራሉ። እነዚህ ሰዎች የእግዚአብሔርን መንግስት ሊወርሱ አይችሉም፣ ‘‘ሥጋና ደም የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊወርሱ አይችሉም፥ የሚበሰብሰውም የማይበሰብሰውን አይወርስም’’ (1ቆሮንቶስ 15፥50)።

የመጀመሪያውን ልደት ብቻ ያገኙ ፍጥረታዊ ሰዎች ይባላሉ። አካላቸው ደግሞ ፍጥረታዊ አካል ይባላል (1ቆሮንቶስ15፡46)። እነዚህ ሰዎች መንፈሳዊ የሆነውን የእግዚአብሔርን ነገር ሊያስተውሉ አይችሉም ‘‘ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም፤ በመንፈስም የሚመረመር ስለ ሆነ ሊያውቀው አይችልም’’ (1ቆሮንቶስ 2፡14)።

የመጀመሪያውን ልደት በመወለድ እንዳገኘነው፣ ሁለተኛውንም ልደት በመወለድ እናገኘዋለን። የመጀመሪያውን ስጋዊ ልደት ስጋዊ ከሆኑ ቤተሰቦቻችን እናዳገኘነው ሁለተኛውን ልደት ደግሞ መንፈሳዊ ከሆነው አባታችን በመወለድ የምናገኘው ይሆናል። የመጀመሪያውን ልደት መልካም ሰው በመሆን፣ ምጽዋት በመስጠት፣ በመፀለይ እና በመጾም እናዳላገኘነው፣ ሁለተኛውንም ልደት በእነዚህ መንገዶች አናገኘውም። የቤተሰቦቻችን ልጅ ለመሆን የከፈልነው ክፍያም ሆነ አስተዋጽዎ እንደሌለ ሁሉ፣ የእግዚአብሔር ልጅ ለመሆንም የምናዋጣው መዋጮ የለም።

የእግዚአብሔር ልጅ ለመሆን ከእኛ የሚጠበቀው አንድ ነገር ብቻ ነው። ይኸውም፣ በኢየሱስ ማመን እና እርሱን መቀበል፣ ‘‘ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም’’ (ዮሐንስ ወንጌል 1፡12-13)። ‘‘በእምነት በኩል ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁና’’ (ገላቲያ 3፡26)።

የሰው ልጅ ሁለተኛውን ልደት ካላገኘ ወይም ዳግም ካልተወለደ የእግዚአብሔርን መንግስት ሊወርስ አይችልም፣ ‘‘ኢየሱስም መለሰ፥ እንዲህ ሲል፦ እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም። ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፥ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነው’’ (የዮሐንስ ወንጌል 3፡5-6)። ምንም ይስራ ምን፣ ከስጋ የተወለደ ስጋ ነው። ስጋ እና ደም ደግሞ የእግዚአብሔርን መንግስት ሊወርሱ አይችሉም። የተፈጥሯዊ ሰው መልካምነት እስከ አለም ዳርቻ ቢሰማም እንኳ፣ ከስጋ ከተወለደ ስጋ ብቻ ነው። ድርጊቱ ምንም ያህል የተከበረ፣ አንቱ የተባለ እና የተመሰከረለት ቢሆን፣ ተፈጥሮውን አይቀይርለትም። ሃይማኖተኛ ቢሆን፣ አዘውትሮ ረዥም ፀሎት ቢያደርግ (ማቴዎስ 23፡14) በሳምንት ሁለት ጊዜ ቢጾም ሳያጓድል ለእግዚአብሔር አስራት ቢያወጣ (ሉቃስ 18፡12)፣ ቀማኛ፣ ዓመፀኛ አመንዝራ ባይሆን (ሉቃስ 18፡11)፣ በሌላ አባባል በሰፈሩ የተመሰከረለት የሞራል ሰው ቢሆን፣ ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር ያው ስጋዊ፣ ያው ፍጥረታዊ ብቻ ነው። በእግዚአብሔር መንግስትም እድል ፈንታ የለውም። ዳግም ልደት የእግዚአብሔር ምህረት ውጤት እንጂ የእኛ መልካም ስራ ውጤት አይደለም። ‘‘እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን እንጂ፥ እኛ ስላደረግነው በጽድቅ ስለ ነበረው ሥራ አይደለም’’ (ቲቶ 3፡5)። በመልካም ስራ ተፈጥሯችን አይቀየርም። መልካም ስራችን በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት የሚኖረው ከአዲሱ ተፈጥሯችን ሲመነጭ ብቻ ነው።

ዳግም ልደት ሰው በእግዚአብሔር መንፈስ ዳግም ሲፈጠር ወይም ሲለወጥ የሚከናወን መንፈሳዊ ድርጊት ሲሆን ይህም ድርጊት ሰው ከእግዚአብሔር መለኮታዊ ባሕሪይ ተካፋይ እንዲሆን ያስችለዋል፣ ‘‘ስለ ክፉ ምኞት በዓለም ካለው ጥፋት አምልጣችሁ ከመለኮት ባሕርይ ተካፋዮች በተስፋ ቃል እንድትሆኑ፥ በእነዚያ ክብርና በጎነት የተከበረና እጅግ ታላቅ የሆነ ተስፋን ሰጠን’’ (2ጴጥሮስ 1፡4)።

ኢየሱስን በማመን እና በመቀበል የተገኘው ልጅነት (ዮሐንስ 1፡12)፣ እግዚአብሔርን አባት ብለን እንድንጠራው እና የእግዚአብሔር ወራሾች እንድንሆን መብትን አስገኝቶልናል፣ ‘‘በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመሩ ሁሉ እነዚህ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸውና። አባ አባት ብለን የምንጮኽበትን የልጅነት መንፈስ ተቀበላችሁ እንጂ እንደገና ለፍርሃት የባርነትን መንፈስ አልተቀበላችሁምና። የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ያ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ይመሰክራል። ልጆች ከሆንን ወራሾች ደግሞ ነን፤ ማለት የእግዚአብሔር ወራሾች ነን፥ አብረንም ደግሞ እንድንከበር አብረን መከራ ብንቀበል ከክርስቶስ ጋር አብረን ወራሾች ነን’’ (ሮሜ 8፡14-17)።

በመጀመሪያው ልደት ከቤተሰቦቻችን (ከፊተኛው አዳም)  የወረስነው ተፈጠሮ፣ አዳማዊ ተፈጥሮ ወይም አሮጌው ሰው ይባላል። በዳግም ልደት ኢየሱስን በማመን ከእግዚአብሔር ያገኘነው አዲሱ ተፈጥሮ ደግሞ አዲሱ ሰው ይባላል፣ ‘‘እርስ በርሳችሁ ውሸት አትነጋገሩ፥ አሮጌውን ሰው ከሥራው ጋር ገፋችሁታልና፥ የፈጠረውንም ምሳሌ እንዲመስል እውቀትን ለማግኘት የሚታደሰውን አዲሱን ሰው ለብሳችሁታል’’ (ቆላሲያስ 3፡9-10)። ‘‘ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል’’ (2ቆሮንቶስ 5፡17)።

ኢየሱስን አምኖ የተቀበለ ሰው፣ በዳግም ልደት ሌላ አዲስ ተፈጥሮ ስለሚኖረው የሁለት ተፈጥሮዎች ባለቤት ይሆናል ማለት ነው። በዳግም ልደት አዲስ ተፈጥሮን እናገኛለን እንጂ የቀድሞውን አሮጌ ተፈጥሮ አናጣም። አሮጌው ተፈጥሮ እስከሞታችን ከእኛ ጋር ይኖራል። እነዚህ ሁለት ተፈጥሮዎች በባህሪይ ተቃራኒ በመሆናቸው እርስ በእርሳቸው ይቀዋወማሉ፣ ‘‘5፥17 ሥጋ በመንፈስ ላይ መንፈስም በሥጋ ላይ ይመኛልና፥ እነዚህም እርስ በርሳቸው ይቀዋወማሉ …’’ (ገላቲያ 5፡17)። ዳግም የተወለደ ሰው በፊተኛው እና እግዚአብሔርን በማያከብረው ስጋዊ ወይም አሮጌ ተፈጥሮ ቁጥጥር ስር እንዳይሆን በእግዚአብሔር ቃል እውቀት እለት እለት መታደስ ይኖርበታል። የአዲሱ ተፈጥሮ ምግብ የእግዚአብሔር ቃል ነው (ማቴዎስ 4፡4)። የአሮጌውን ተፈጥሮ ፍላጎት እንቢ እያልን የአዲሱን ተፈጥሮ ፈቃድ እየተቀበልን የምንጓዘው ጉዞ የቅድስና ጉዞ ይባላል፣ ‘‘ፊተኛ ኑሮአችሁን እያሰባችሁ እንደሚያታልል ምኞት የሚጠፋውን አሮጌውን ሰው አስወግዱ፥ በአእምሮአችሁም መንፈስ ታደሱ፥ ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ።

ሰው በአሮጌው ተፈጥሮ እግዚአብሔርን ደስ ማሰኝት ስለማይችል ዳግም ልደት ያስፈልገዋል፣ ‘‘እነሆ፥ በዓመፃ ተፀነስሁ፥ እናቴም በኃጢአት ወለደችኝ (መዝሙር 51፡5)። ‘‘የሰው ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ እጅግም ክፉ ነው ማንስ ያውቀዋል? (ኤርሚያስ 17፡9።) ‘‘ስለ ሥጋ ማሰብ በእግዚአብሔር ዘንድ ጥል ነውና፤ ለእግዚአብሔር ሕግ አይገዛምና፥ መገዛትም ተስኖታል፤ በሥጋ ያሉትም እግዚአብሔርን ደስ ሊያሰኙት አይችሉም’’ (ሮሜ 8፡16-17)። ‘‘በእነዚህም ልጆች መካከል እኛ ሁላችን ደግሞ፥ የሥጋችንንና የልቡናችንን ፈቃድ እያደረግን፥ በሥጋችን ምኞት በፊት እንኖር ነበርን እንደ ሌሎቹም ደግሞ ከፍጥረታችን የቁጣ ልጆች ነበርን’’ (ኤፌሶን 2፡3)።

ዳግመኛ ልደት ያገኘ ሰው ምልክቶች ምንድን ናቸው? ዳግም የተወለደ ሰው ከሃጢአት ልምምድ ነፃ የወጣ ነው (ሮሜ 6፡14-23)። ዳግም የተወለደ ሰው የእግዚአብሔርን መንፈስ ምሪት ለመቀበል እና ለመታዘዝ መሻት ይኖረዋል (ሮሜ 8፡13-14)። ዳግም የተወለደ ሰው የጽድቅ ሕይወት ይኖረዋል (1ዮሐንስ 2፡29)። ዳግም የተወለደ ሰው ሌሎችን ይወዳል (1ዮሐንስ 4፡7)። ዳግም የተወለደ ሰው ከሃጢአት ሕይወት ይርቃል (1ዮሐንስ 3፡9፤ 5፡18)። ዳግም የተወለደ ሰው አለምን መውደድ ይተዋል (1ዮሐንስ 2፡15-16)።

ኢየሱስን በማመን እና በመቀበል ይህን ዳግም ልደት ለማግኘት የሚሹ ከሆነ ይህን ሊንክ በመጫን፣ ኢየሱሰን መቀበል መጽሐፍ ቅዱሳዊ ወይስ መናፍቃዊ የሚለውን ትምህርት እንዲያነቡ በትህትና እንጠይቆታለን። የመዳን ቀን አሁን ነው (2ቆሮንቶስ 6፡2)፣ ለነገ ቀጠሮ አይስጡ። ነገ የእርሶ አይደለምና።

መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የሕይወትዎ ጌታ በማድረግ ቀሪው ዘመንዎን ለመኖር ወስነው ከሆነ፣ ይህንን ሊንክ በመጫን ስምዎንና የኢ-ሜይል አድናሻዎን ይላኩልንና፣ ለመንፈሳዊ ሕይወት እድገትዎ የሚቻለንን ሁሉ እገዛ እናደርግሎታለን።

የዘላለም ሕይወት፣ የእግዚአብሔር ታላቁ ስጦታ

የዘላለም ሕይወትን የማገኘው እንዴት ነው?

የዘላለም ሕይወትን እንዳገኝ የየትኛው ቤተ ክርስቲያን አባል መሆን አለብኝ የሚል ጥያቄ ያስጨንቆታል? የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ከእኔ የሚጠበቀውስ ምን ይሆን በሚል ሃሳብ ተወዛግበው ያውቃሉ? እርሶ ሃጢአተኛ በመሆኖ እና እግዚአብሔር ደግሞ ፍጹም ፃድቅ ስለሆነ የዘላለም ሕይወት ሊደረስበት የማይቻል እና የተወሰኑ ሰዎች ብቻ የሚያገኙት እንደሆነስ አስበው ያውቃሉ? ከእነዚህ ጥያቄዎች አንዱ የሚመለከትዎ ከሆነ ምላሹን እነሆ።

የዘላለም ሕይወት የሚለው ሃሳብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከ38 ጊዜ በላይ ተጠቅሷል። በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ ባለው አገባብ (አውድ) መሰረት የዘላለም ሕይወት ማለት የሰው ልጅ በሰማያዊ ስፍራ በእግዚአብሔር መንግስት ውስጥ በተድላና በደስታ የሚኖረውን ቁጥር አልባ የሕይወት ዘመን ያመለክታል።

የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ላይ ካመፀበት ወቅት (ዘፍጥረት 3፡6) ጀምሮ፣ በሰራው ሃጢአት ምክንያት የተፈረደበትን ሞት (ሮሜ 6፡23) እየጠበቀ፣ ሕይወቱ ከስጋው የምትለይበትን ቅንጭብጫቢ እድሜዎች እየቆጠረ፣ በተስፋቢስነት የሚኖር ምስኪን ፍጥረት ነው። ከዚህ ውድቀት በኋላ የሰው ልጅ የሃጢአት ባሪያ ሆነ። ይህንን እውነት ቅዱስ ዮሐንስ እንዲህ በማለት ይገልፀዋል ‘‘ኢየሱስ መለሰ፥ እንዲህ ሲል፦ እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ኃጢአት የሚያደርግ ሁሉ የኃጢአት ባርያ ነው።’’ (ዮሐንስ 8፡34፤ ሮሜ 6፡17-18፤ ሮሜ 6፡20)።

የእግዚአብሔር ልጅ በመሆን ከዚህ እስራት የተፈታ ካልሆነ በቀር የሃጢአት ባሪያ የሆነ ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት ደርሻ እንደማይኖረው  የእግዚአብሔር ቃል በሚከተለው መንገድ ማስረጃ ይሰጠናል፣ ‘‘ባርያም ለዘላለም በቤት አይኖርም፤ ልጁ ለዘላለም ይኖራል’’ (ዮሐንስ 8፡35)።

መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ልጅ የሃጢአት ባርያ መሆኑን ብቻ ሳይሆን፣ ለምን የሃጢአት ባሪያ እንደሆነም ይነግረናል። የሃጢአት ደራሲ ዲያብሎስ ነው (1ዮሐንስ 3፡8)። ሃጢአትን ያደረግነው በዚህ እርኩስ ፍጥረት ስር ስለተገዛን እነደሆነ ዮሐንስ በቁጥር 8 ላይ ይነግረናል። በዚህ መሰረት የሰው ልጅ የሃጢአት ባሪያ የሆነው በቅዱስ አምላኩ ትዕዛዝ ላይ አምጾ የዲያብሎስን ውሸት ለማድመጥ በመረጠ ወቅት (ዘፍጥረት 3፡1-8) እንደሆነ እንረዳለን።

የዘላለም ሕይወት ማለት ከዚህ ባርነት ነፃ መውጣት ማለት ነው። የዘላለም ሕይወት የሚያገኙት እነማን ናቸው ብሎ መጠየቅ በሌላ አነጋገር ከዚህ እስር እና ባርነት ነፃ የሆኑት እነማን ናቸው ማለት ነው።

በዚህ ባርነት ውስጥ ያለ ሰው የሚያፈራው መልካም ነገር ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት አፀያፊ ነው (ሮሜ 8፡8)። የሚያፈሩት ፍሬ፣ የልጅ ሳይሆን የባሪያ ፍሬ ነውና በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ ሊኖረው አይችልም። ከባርነት ሳይወጡ፣ በሃይማኖተኝነት በመነሳሳት፣ መልካም ስራ በመስራት፣ እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት መሞከር ይቻላል። ሙከራው ግን ፍሬ ቢስ ነው። እግዚአብሔር በዚህ ደስ አይሰኝምና። የዘላለም ሕይወት የስራ ጉዳይ ሳይሆን የተፈጥሮ ጉዳይ ነው። የፍሬ ጉዳይ ሳይሆን የዛፍ ጉዳይ ነው። ከእሾህ ዛፍ የበለስ ፍሬ እንደማይቆረጥ ሁሉ ከአጣጥ ቍጥቋጦም የወይን ፍሬ አይለቀምም። ሁለቱንም አንድ የሚያደርጋቸው ነገር ቢኖር፣ ፍሬ ማፍራቸው ነው። የሚያለያያቸው ደግሞ የፍሬው አይነት ነው። በዲያብሎስ እና በሃጢአት ባርነት ስር ያለ ሰውም ሆነ ነፃ የወጣ፣ ሁለቱም ፍሬ ያፈራሉ። ስራ ይሰራሉ። ጥያቄው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘው ፍሬ የቱ ነው የሚለው ነው።  በባርነት ስር ሆነው እግዚአብሔር በፍሬያችን ደስ በማሰኘት የዘላለም ሕይወት እናገኛል ስለሚሉ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ግልጽ መልዕክት አለው፣ ‘‘በሥጋ ያሉትም እግዚአብሔርን ደስ ሊያሰኙት አይችሉም’’ (ሮሜ 8፡8)። መጀመሪያ ፍሬው ሳይሆን ግንዱ መቀየር አለበት። ግንዱ ከተቀየረ ፍሬው መልካም ይሆናል። ስለዚህ የዘላልም ሕይወት ከተፈጥሯችን እንጂ ከመልካም ምግባሮቻችን ጋር ምንም ግንኙነት የለውም። የግንድ ለውጥ ያደረገ፣ (የተፈጥሮ ለውጥ ያደረገ) የግንዱ ሕይወት ውጤት የሆነውን ፍሬ ማፍራቱ አይቀርምና።

በዚህ ምድር ላይ አፋቸውን ሞልተው ‘‘እግዚአብሔር የለም’’ የሚሉ ነገር ግን በሕይወታቸው በሚያደርጉት ሰናይ ምግባር አለምን ያስደመሙ በርካታ ሰዎች መኖራቸውን ታሪክ ለሚያገላብጥ እና አካባቢውን በትኩረት ለሚቃኝ ሰው እንግዳ ነገር አይደለም። እነዚህ ሰዎች በሚያደርጉት ልግስና፣ ታማኝነት፣ ታታሪነት በርካታ ተከታዮችን ለማፍራት የቻሉ መሆናቸውንም መዘንጋት የለብንም። አንዳንዶቹ ስለያዙት መልካም አላማ መሳካት ሲሉ ራሳቸውን ለሞት አደጋ እንኳ አሳልፈው ሰጥተዋል፣ እየሰጡም ነው። የዘላልም ሕይወት ጉዳይ የተፈጥሮ ጉዳይ ሳይሆን የመልካም ምግባር ጉዳይ ቢሆን ኖሮ እነዚህን ሰዎች በመንግስተ ሰማይ ባገኘናቸው ነበር። በዚህ ምድር ላይ ላበረከቱት መልካም ተጽዕኖ አክብሮት ቢኖረኝም፣ የዘላለም ሕይወት ተካፋዮች ስለመሆናቸው ግን ተስፋ ልንሰጣቸው አልችልም። ስለዚህ ስለዘላለማዊ ሕይወት ተገቢው ጥያቄ – ‘‘ምን ሰርቻለው?’’ ሳይሆን፣ ‘‘ከዚህ የዲያብሎስ እስራት ተፈትቻለው ወይ?’’፣ ‘‘ከሃጢአት ባርነት ነፃ ወጥቻለው ወይ’’፣ ‘‘ባሪያ ሳይሆን ልጅ ሆኛለው ወይ?’’ የሚለው ይሆናል።

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጅ የሚያስፈልገውን አርነት የሚያውቅ አምላክ ነውና በምድር ላይ በነበረ ጊዜ ይህንን የአርነት ስብከት መስበክ ጀመረ። ለዚህ የኢየሱስ ስብከት፣ ትምህርቱን የተቃወሙ አንዳንድ አይሁድ የሰጡትን ምላሽ እንመልከት። ኢየሱስም፣ ‘‘እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል አላቸው። እነርሱም መልሰው። የአብርሃም ዘር ነን ለአንድም ስንኳ ከቶ ባሪያዎች አልሆንም፤ አንተ፣ አርነት ትወጣላችሁ እንዴት ትላለህ? አሉት። ኢየሱስ መለሰ፥ እንዲህ ሲል፦ እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ኃጢአት የሚያደርግ ሁሉ የኃጢአት ባርያ ነው። ባርያም ለዘላለም በቤት አይኖርምልጁ ለዘላለም ይኖራል። እንግዲህ ልጁ አርነት ቢያወጣችሁ በእውነት አርነት ትወጣላችሁ። …እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ’’ (ዮሐንስ 8፡32-44፣)።

የዘላለም ሕይወትን የሚሰጥ ማን ነው?

የዘላለም ሕይወት ከእግዚአብሔር የሚሰጠን እና እኛ የምንቀበለው ውድ ስጦታ ነው። የሰው ልጅ በራሱ ማንነት እና ጥረት ሊያገኛት ስላልቻለ፣ እግዚአብሔር እንዲሁ በነፃ፣ ለሚቀበላት ሁሉ ሊሰጣት ወዷል። በዘላለም ሕይወት ውስጥ የእግዚአብሔር ድርሻ መስጠት ሲሆን የእኔ እና የእርሶ ድርሻ ደግሞ በእምነት መቀበል ነው።

የዮሐንስ ወንጌል 10፥28 ‘‘እኔም የዘላለም ሕይወትን እሰጣቸዋለሁ፥ ለዘላለምም አይጠፉም፥ ከእጄም ማንም አይነጥቃቸውም።’’

የዮሐንስ ወንጌል 17፥1-2 ‘‘ኢየሱስም ይህን ተናግሮ ወደ ሰማይ ዓይኖቹን አነሣና እንዲህ አለ፦ አባት ሆይ፥ ሰዓቱ ደርሶአል፤ ልጅህ ያከብርህ ዘንድ፥ በሥጋም ሁሉ ላይ ሥልጣን እንደ ሰጠኸው፥ ለሰጠኸው ሁሉ የዘላለምን ሕይወት ይሰጣቸው ዘንድ ልጅህን አክብረው።’’

1ኛ የዮሐንስ መልእክት 2፥25 ‘‘እርሱም የሰጠን ተስፋ ይህ የዘላለም ሕይወት ነው።’’

1ኛ የዮሐንስ መልእክት 5፥11 ‘‘እግዚአብሔርም የዘላለምን ሕይወት እንደ ሰጠን ይህም ሕይወት በልጁ እንዳለ ምስክሩ ይህ ነው።’’

ወደ ሮሜ ሰዎች 6፥23 ‘‘የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የዘላለም ሕይወት ነው።’’

የዮሐንስ ወንጌል 5፥39 ‘‘እናንተ በመጻሕፍት የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ይመስላችኋልና እነርሱን ትመረምራላችሁ፤ እነርሱም ስለ እኔ የሚመሰክሩ ናቸው፤’’

የዘላለም ሕይወት ያላቸው እነማን ናቸው?

ከዚህ የሃጢአት ባርነት ነፃ የሚያወጣኝ ማን ነው? ከዲያብሎስ አገዛዝ የሚታደገኝ ማነው? ማነው ይህን አጋንንታዊ አሮጌ ተፈጥሮ ሽሮ የእግዚአብሔር ልጅ የሚያደርገኝ? ማነው የዘላልም ሕይወት የሚሰጠኝ? መልሱ አጭር ነው፣ ኢየሱስ ብቻ። ይህ የኔ አስተያየት አይደለም። የዘላለም ሕይወት የሚለው ቃል ተጠቅሶ በምናገኘው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ሁሉ የዚያ ስጦታ ምክንያት ኢየሱስ እንደሆነ ይናገራል።

የዘላለም ሕይወት ያላቸው ከሃጢአት ባርነት ነፃ የወጡ ናቸው። ‘‘አሁን ግን ከኃጢአት አርነት ወጥታችሁ ለእግዚአብሔርም ተገዝታችሁ፥ ልትቀደሱ ፍሬ አላችሁ፤ መጨረሻውም የዘላለም ሕይወት ነው’’ (ወደ ሮሜ ሰዎች 6፥22)። ከዚህ ሞት እና ሃጢአት ባርነት ነፃ ለመውጣት  ነፃ አውጪ ያስፈልጋል (ሮሜ 8፡2)። ያ ነፃ አውጪ ኢየሱስ ነው (ዮሐንስ ወንጌል 8፡36፤ 1ዮሐንስ መልዕክት 3፡8፤ ሉቃስ 4፡17-20)። ከዚህ ባርነት በመልካም ምግባሮቻችን ማምለጥ የምንችል ቢሆን ኖሮ የኢየሱስ ነፃ አውጪነት ባላስፈለገም ነበር። ከዚህ ባርነት ነፃ የሚያወጣን ክርስቶስ እንደሆነ ካመንን የዘላለም ሕይወት የእኛ ናት።

የዘላለም ሕይወት ራሱ ኢየሱስ ነው። ‘‘የእግዚአብሔርም ልጅ እንደ መጣ፥ እውነተኛም የሆነውን እናውቅ ዘንድ ልቡናን እንደ ሰጠን እናውቃለን፤ እውነተኛም በሆነው በእርሱ አለን፥ እርሱም ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነውእርሱ እውነተኛ አምላክና የዘላለም ሕይወት ነው’’ (1ኛ የዮሐንስ መልእክት 5፥20)። የዘላለም ሕይወት የሚገኘው በኢየሱስ ውስጥ ነው፣ ‘‘እግዚአብሔርም የዘላለምን ሕይወት እንደ ሰጠን ይህም ሕይወት በልጁ እንዳለ ምስክሩ ይህ ነው’’ (1ኛ የዮሐንስ መልእክት 5፥11)። ይህን ዘላለማዊ ሕይወት፣ ኢየሱስን ስንቀበል ገንዘባችን (የራሳችን) እናደርጋለን። የዘላለም ሕይወት ያላቸውም ኢየሱስ ያላቸው ብቻ ናቸው። የዘላለም ሕይወት፣ ኢየሱስ በሌለበት የለችምና ኢየሱስ የሌለው የዘላለም ሕይወት የለውም፣ ‘‘ልጁ ያለው ሕይወት አለው፤ የእግዚአብሔር ልጅ የሌለው ሕይወት የለውም’’ (1ኛ የዮሐንስ መልእክት 5፥12)።

ይህ ሕይወት ያላቸው – የዚህ እምነት ተከታይ ናቸው፣ ወይም ረጅም ዘመን የቆየው የዚህ እምነት አባላት ናቸው፣ ወይም፣ ባማረ እና በተዋበ ካቴድራል ውስጥ እግዚአብሔር የሚያመልኩት የዚህ እምነት ተከታዮች ናቸው፣ ወዘተ አይልም። ይህ ሕይወት ያላቸው ልጁ ኢየሱስ ያላቸው ሁሉ ናቸው። እናም የትኛውን እምነት ብከተል ነው የዘላልም ሕይወት ያለኝ የሚል ጭንቀት ካለብዎ፣ መልሱ አጭር ነው በስጋ የተገለጠውን (1ጢሞቴዎስ 3፡16)፣ ሰውም (ማቴዎስ 16፡13) እግዚአብሔርም (ዮሐንስ 1፡1፤ 1ኛ የዮሐንስ መልእክት 5፥20) የሆነውን ለእርሶ ሃጢአት ቤዛ የሆነውን የሞተውን ከዛም በ3ኛው ቀን ከሙታን መካከል የተነሳውን ኢየሱስን የሚያምኑ እና ቃሉን የሚከተሉ (ዮሐንስ 5፥24) ከሆኑ የዘላልም ሕይወት እንዳሎ መጽሐፍ ቅዱስ ያረጋግጥሎታል። ቅዱሱ መጽሐፍ ካረጋገጠልዎ፣ የሰው ማረጋገጫ የግድ አያስፈልጎትም። የምሁራን፣ የሊቃውንት፣ የጳጳሳት፣ የፓስተሮች ይሁንታ አያሻዎትም። እርሱ ካለ፣ አለ ነው። የእርሶ ድርሻ፣ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም እንዳለችው አሜን፣ ‘‘እንደ ቃልህ ይሁንልኝ’’ (ሉቃስ 1፡38) ማለት ብቻ ነው።

የዘላለም ሕይወት ለማግኘት የእኔ ድርሻ ምንድን ነው?

አንድ ነገር ለማግኘት ልፉት እና ድካም ግድ በሆነባት አለም ውስጥ፣ በፀጋ ስለተገለጠው የእግዚአብሔር ነፃ ስጦታ ማውራት እጅግ አስቸጋሪ ይሆናል። በመልፋት እና በመድከም የላቡን ዋጋ በመቀበል ለኖረ ሰራተኛ፣ ነፃ ስጦታ ድካሙ ካስገኘችለት በላይ ደሞዝ እንዳላት ቢነገረው ዜናውን የጅል ወሬ አድርጎ መቁጠሩ የሚጠበቅ ነው። እግዚአብሔር ግን ይህንን የአለም ጥበብ እና ስርአት ሊያዋርድ በስብከት ሞኝነት የሚያምኑትን ያድን በጎ ፈቃዱ ሆነ (1ቆሮንቶስ 1፡19-21)። ያለስራ ሃጢአተኛውን በሚያፀድቅ ያመነን ሰው እግዚአብሔር በዘላለም ሕይወት ሊያኖር ቢወድ (ሮሜ 4፡5)፣ እንዲህ አይሁን ለማለት እኛ ማን ነን? በውስጣችሁ ያለው ግንድ (የወደቀው ተፈጥሯችን ማለት ነው) የሞተ ስለሆነ የምታፈሩትም ፍሬ የሞተ ነውና በእናንተ ስራ አልከብርም። መልካም ምግባራችሁ ሳይቀር የመርገም ጨርቅ ስለሆነ በፊቴ አስነዋሪ ነው። በመሆኑም የገዛ እጄ መድሃኒት አዘጋጅታለች። በእኔ ስጦታ እንጂ በእናንተ ስራ የዘላለምን ሕይወት አታገኙም (ኤፌሶን 2፡8-9) ቢል፣ ከእግዚአብሔር ጋር የሚከራከር ማን ነው? የዘላለም ሕይወት እግዚአብሔር በላከው በኢየሱስ ለሚያምኑ እና ቃሉን ለሚከተሉ ሁሉ የተዘጋጀች ነፃ ስጦታ ነች። የሚቀበላት ያገኛታል፤ የሚያቃልላት ወይም በሌላ መንገድ ሊያገኛት የሚሻት ሁሉ ያጣታል። የዘላለምን ሕይወት መቀበል የሚሹ ሰዎች ድርሻ ምን እንደሆነ ከዚህ በታች በቀረቡት ጥቅሶች ውስጥ እንመልከት፡-

የዮሐንስ ወንጌል 3፥14-15 ‘‘ሙሴም በምድረ በዳ እባብን እንደ ሰቀለ እንዲሁ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ የሰው ልጅ ይሰቀል ይገባዋል።’’

(የዮሐንስ ወንጌል 3፥16) ‘‘በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።’’

ለዘላለም ሕይወት ተዘጃግተዋል? እንግዲያው በሐዋሪያት ዘመን እንደነበሩ ብልህ ሰዎች ያድርጉ። ለመሆኑ እነዚህ ሰዎች ምን አደረጉ? ‘‘አሕዛብም ሰምተው ደስ አላቸው የእግዚአብሔርንም ቃል አከበሩ፥ ለዘላለም ሕይወትም የተዘጋጁ ሁሉ አመኑ’’ (የሐዋርያት ሥራ 13፥48)።

የዮሐንስ ወንጌል 3፥36 ‘‘በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም።’’

የዮሐንስ ወንጌል 6፥40 ‘‘ልጅንም አይቶ በእርሱ የሚያምን  ሁሉ የዘላለም ሕይወትን እንዲያገኝ የአባቴ ፈቃድ ይህ ነው፥ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ።’’

የዮሐንስ ወንጌል 6፥47 ‘‘እውነት እውነት እላችኋለሁ በእኔ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው።’’

የዮሐንስ ወንጌል 17፥3 ‘‘እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት።’’

1ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 1፥16 ‘‘ስለዚህ ግን፥ የዘላለምን ሕይወት ለማግኘት በእርሱ ያምኑ ዘንድ ላላቸው ሰዎች ምሳሌ እንድሆን፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ዋና በምሆን በእኔ ላይ ትዕግስቱን ሁሉ ያሳይ ዘንድ፥ ምህረትን አገኘሁ።’’

ቲቶ 3፡6-7 ‘‘ያን መንፈስም፥ በጸጋው ጸድቀን በዘላለም ሕይወት ተስፋ ወራሾች እንድንሆን፥ በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በእኛ ላይ አትርፎ አፈሰሰው።’’

1ኛ የዮሐንስ መልእክት 1፥2 ‘‘ሕይወትም ተገለጠ አይተንማል እንመሰክርማለን፥ ከአብ ዘንድ የነበረውንም ለእኛም የተገለጠውን የዘላለምን ሕይወት እናወራላችኋለን፤’’

1ኛ የዮሐንስ መልእክት 5፥13 ‘‘የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ታውቁ ዘንድ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ለምታምኑ ይህን ጽፌላችኋለሁ።’’

የዮሐንስ ወንጌል 5፥24‘‘እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ቃሌን የሚሰማ የላከኝንም የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፥ ከሞትም ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም።’’

የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ሌሎች አማራጭ መንገዶች ይኖሩ ይሆን?

ወደ ዘላለም ሕይወት የሚያደርሰው መንገድ አንድ ነው። እርሱም ኢየሱስ ነው (ዮሐንስ 14፡6)። መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ መንገድ እንዲህ ይላል፣ ‘‘ወደ ዘላለም ሕይወት የሚወስደውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት ስትጠባበቁ በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችሁን ጠብቁ’’ (ይሁዳ 1፡21)።

ይህንን ዘላለማዊ ሕይወት በራሴ መንገድ ለማግኘት እጥራለው፣ ወደዚህ ዘላለማዊ ሕይወት የሚያደርሱ ሌሎች አማራጭ መንገዶች አሉኝ፣ ሃይማኖቴ የዘላለም ሕይወት መንገዴ ነው፣ ወዘተ ብለን ይህን ሕይወት ለምንገፋ ሐዋሪያው ጳውሎስ እና በርናባስ የሚከተለውን ይመክሩናል፣ ‘‘ጳውሎስና በርናባስም ገልጠው፣ የእግዚአብሔር ቃል አስቀድሞ ለእናንተ ይነገር ዘንድ ያስፈልጋል፤ ከገፋችሁትና የዘላለም ሕይወት እንዳይገባችሁ በራሳችሁ ከፈረዳችሁ ግን፥ እነሆ፥ ወደ አሕዛብ ዘወር እንላለን’’ (የሐዋርያት ሥራ 13፥46)።

በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ ሌላ አማራጭ የሚፈልግ ደግሞ የእግዚአብሔር ቁጣ በእርሱ ላይ ይሆናል፣ ሕይወትንም አያይም። ‘‘በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም’’ (የዮሐንስ ወንጌል 3፥36)።

መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የሕይወትዎ ጌታ በማድረግ ቀሪው ዘመንዎን ለመኖር ወስነው ከሆነ፣ ይህንን ሊንክ በመጫን ስምዎንና የኢ-ሜይል አድናሻዎን ይላኩልንና፣ ለመንፈሳዊ ሕይወት እድገትዎ የሚቻለንን ሁሉ እገዛ እናደርግሎታለን።

ከሞት ፍርድ ለመዳን ምን ማድረግ አለብኝ?

ከድረ-ገጽ ላይ ያገኘሁትን የሞት ስታስቲካዊ መረጃ ላስቀድም። ለመሆኑ በዚህ አለም ላይ በእያንዳንዷ ሰከንድ 1.78 ሰው፣ በአንድ ደቂቃ 107 ሰው፣ በአንድ ሰዓት 6390 ሰው፣ በአንድ ቀን 153000 ሰው፣ በአመት ደግሞ 56 ሚሊዮን ያህል ሰው እንደሚሞት ያውቃሉ? ይህ ሞት አካላዊ ሞት ነው። ከዚህ ሞት የሚቀር ከመካከላችን አንድም የለም። ከአዳም የተገኝ ሰው ሁሉ ይህን አካላዊ ሞት መቅመሱ አይቀሬ ነው።

ሞት አካላዊ ብቻ አለመሆኑ ደግሞ ይህን አስደንጋጭ ዜና አሰቃቂ እንዲሆን ያደርገዋል። በሕይወት እያሉ ስለሞቱ ሰዎች ሰምተው ያውቃሉ? ከሞት በኋላ ስላለው ሁለተኛው ሞትስ (የዮሐንስ ራእይ 21፡8)? ከዚህ በታች ባሉት ጥቂት አንቀጾች ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህኛው የሞት አይነት ምን እንደሚል እናጠናለን።

ሞት መቼ መጣ?

የሰው ልጅ በፍጹም ተድላና ደስታ በዔድን ገነት ይኖር ነበር። ፈጣሪም ሰውን አንድ ነገር እንዲያደርግ አዘዘው፤ እንዲህ ሲል፣ ‘‘… መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህ…’’ (ኦሪት ዘፍጥረት 2፥17)። ሌላው ባላንጣው ደግሞ እንዲህ ሲል ሃሳብ አቀረበለት፣ ‘‘…ሞትን አትሞቱም’’ (ኦሪት ዘፍጥረት 3፥4)። ባልዘራው፣ ባላጨደው እና ባልሰበሰበው ፍሬ ደስ እንዲሰኝ፣ ያማረ እና የተዋበ የአትክልት ስፍራ የሰጠውን ፈጣሪውን መስማት ያልወደደው የሰው ልጅ፣ ኋላ ረግጦ ለሚገዛው ሰይጣን ፈቃድ አደረ። ‘‘ስለዚህ ምክንያት ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት፥ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ’’ (ወደ ሮሜ ሰዎች 5፥12)። ሞት ሕግን በመተላለፋችን ምክንያት ወደ አለም ገባ (ሮሜ. 7፡9)። በአዳም መተላለፍ ምክንያት ሞት በሰው ልጆች ሁሉ ላይ ሰለጠነ (ሮሜ 5፡7)። ሞት ለሃጢአታችን የተከፈለን ምንዳ (ደሞዝ) ነው (ሮሜ 6፡23)። በዚህም ምክንያት ሞት የሰው ልጅ ጠላት ሆነ (1ቆሮ. 15፡26)።

ወደ ሮሜ ሰዎች 7፥9 እኔም ዱሮ ያለ ሕግ ሕያው ነበርሁ፤ ትእዛዝ በመጣች ጊዜ ግን ኃጢአት ሕያው ሆነ እኔም ሞትሁ፤

ወደ ሮሜ ሰዎች 5፥17 በአንዱም በደል ሞት በአንዱ በኩል ከነገሠ፥ ይልቁን የጸጋን ብዛትና የጽድቅን ስጦታ ብዛት የሚቀበሉ በአንዱ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በሕይወት ይነግሣሉ።

ወደ ሮሜ ሰዎች 6፥23 የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የዘላለም ሕይወት ነው።

1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 15፥26 የኋለኛው ጠላት የሚሻረው ሞት ነው፤

ቀዳሚ አባታችን አዳም በበደለው በደል እና እኛም ራሳችንን ካወቅንበት ደቂቃ ጀምሮ እግዚአብሔርን ስለበደልን የበደላችን ደሞዝ የሆነው ሞት ደጃችንን እያንኳኳ በሰረገላው ይዞን ሊነጉድ የመጨረሻዋን እስትንፋሳችንን እየጠበቀ ነው። ይህ ቅስበታዊ ስጋዊ ሞት ወደ ቀጣዩ እና ዘላለማዊ ሞት የሚያሻግረን ድልድይ ነው። ቅስበታዊው ሞት የሚያስፈራ ከሆነ፣ ዘላለማዊውማ እንዴት አብልጦ አያስፈራ!!! ‘‘ሞትና ሲኦልም በእሳት ባሕር ውስጥ ተጣሉ። ይህም የእሳት ባሕር ሁለተኛው ሞት ነው’’ (የዮሐንስ ራእይ 20፥14)።

እግዚአብሔርን ባለመታዘዛችን እና ፈቃዱን ባለማድረጋችን ምክንያት አሁን በሕይወት ሳለን እንኳ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ሙታን እያለ ይጠራናል። በሕይወት እያለን በሁለተኛው ሞት ፍርድ ስር መሆናችን የሚያሳዩ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችም አሉ። እስቲ ለአብነት የተወሰኑትን እንመልከት፡-

ወደ ኤፌሶን ሰዎች 2፥1-2 በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ሙታን ነበራችሁ፤ በእነርሱም፥ በዚህ ዓለም እንዳለው ኑሮ፥ በማይታዘዙትም ልጆች ላይ አሁን ለሚሠራው መንፈስ አለቃ እንደ ሆነው በአየር ላይ ሥልጣን እንዳለው አለቃ ፈቃድ፥ በፊት ተመላለሳችሁባቸው።

ወደ ኤፌሶን ሰዎች 2፥5 ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ በበደላችን ሙታን እንኳ በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ሕይወት ሰጠን፥ በጸጋ ድናችኋልና፥

ወደ ኤፌሶን ሰዎች 5፥14 ስለዚህ፦ አንተ የምትተኛ ንቃ ከሙታንም ተነሣ ክርስቶስም ያበራልሃል ይላል።

ወደ ቆላስይስ ሰዎች 2፥13 እናንተም በበደላችሁና ሥጋችሁን ባለመገረዝ ሙታን በሆናችሁ ጊዜ፥ ከእርሱ ጋር ሕይወትን ሰጣችሁ። በደላችሁን ሁሉ ይቅር አላችሁ። (ይህ የስጋ ግርዘት ሳይሆን መንፈሳዊውን የልብ ግርዘት ነው ሮሜ 2፡29)

የሞት መፍትሄ ምንድን  ነው?

ከአዳም ውድቀት ጀምሮ እስከ ኢየሱስ መምጣት፣ ሞት በሰው ልጆች ላይ ስልጣን ነበረው። ሞት ድል የተነሳበት ብስራት የተነገረው ኢየሱስ ይህችን ምድር ሲረግጥ ነው። የሞት መውጊያ የተወሰደው፣ ሙታኑን ሲቀበል የነበረው ሲኦል የደነገጠው፣ ኢየሱስ በመስቀል ላይ ሞትን፣ በሞቱ ሲቀጣ ነው። ‘‘ሞት ሆይ፥ መውጊያህ የት አለ? ሲኦል ሆይ፥ ድል መንሣትህ የት አለ?’’ (1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 15፥55)። ከሞት ጋር ታግሎ ያሸነፈ የለም፣ ሞትን ገጥሞ ድል የነሳ የለም። የሲኦልን ድንፋታን ፀጥ ያሰኘ የለም። ኢየሱስ ብቻ ይህን አድርጓል። ‘‘ሞት በሰው በኩል ስለ መጣ ትንሣኤ ሙታን በሰው በኩል ሆኖአልና’’ (1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 15፥21)። ያም ሰው ኢየሱስ ይባላል።

ቅዱሳን ብለን የምንጠራቸው አንዳቸው ሳይቀሩ በሞት የተሸነፉ ናቸው። ማንም ከማንም ሳይለይ ሰው የሆነ ሁሉ ከሞት በታች ነበር። ሞት ገዝቷቸው ነበር። ከአንዱ በቀር። ኢየሱስን ግን ሞት አልቻለውም። የመቃብር ደጅ አፍኖ ሊያስቀረው አልደፈረም። እርሱ ብቻ ከሙታን መካከል አልተገኘም፣ ሕያው ነውና።  ‘‘…ሕያውን ከሙታን መካከል ስለ ምን ትፈልጋላችሁ? ተነሥቶአል እንጂ በዚህ የለም’’ (የሉቃስ ወንጌል 24፥5)።

ከዚህ ሞት ማን ሊድን ይችላል?

እግዚአብሔር በሞት ጥላ የሚሄደውን ሰው ተመልክቶ ዝም የሚል ልብ ስለሌለው፣ አንድ ልጁን በመላክ በሞት የተገዛውን ፍጥረቱን ሊያድን ወደደ። እናም በጨለማ የተቀመጠው ሕዝብ ታላቅ ብርሃን ያይ ዘንድ፥ በሞት አገርና ጥላ የተቀመጡትም ብርሃንን ይመለከቱ ዘንድ (የማቴዎስ ወንጌል4፥14-16) ሙታን ሁሉ የእግዚአብሔርን ልጅ ድምፅ የሚሰሙበት ሰዓት መጣ (የዮሐንስ ወንጌል 5፥25)። ዘመኑ ሲደርስ እግዚአብሔር ልጁን ወደ ምድር ላከ። የልጁም ብርሃን  በጨለማና በሞት ጥላ ተቀምጠው ለነበሩት ሁሉ አበራ (የሉቃስ ወንጌል 1፥7)።

የሚሰሙትም ሁሉ፣ ቃሉን የሚጠብቁቱ ከዚህ ሞት አምልጠው በሕይወት እንዲኖሩ የእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ሆነ (የዮሐንስ ወንጌል 5፥25)። ‘‘እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ቃሌን የሚሰማ የላከኝንም የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፥ ከሞትም ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም’’ (የዮሐንስ ወንጌል 5፥24)። ‘‘እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ሙታን የእግዚአብሔርን ልጅ ድምፅ የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል እርሱም አሁን ነው፤ የሚሰሙትም በሕይወት ይኖራሉ’’ (የዮሐንስ ወንጌል 5፥25)። ‘‘እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ቃሌን የሚጠብቅ ቢኖር ለዘላለም ሞትን አያይም’’ (የዮሐንስ ወንጌል 8፥51)።

ኢየሱስ ሃጢአትን ስላላደረገ ሊሞት ባላተገባው ነበር። እኛ ግን፣ ሁላችን ሃጢአት ስላደረግን (ሮሜ 3፡23) በሞት ልንቀጣ ይገባናል (ሮሜ 6፡23)። ሆኖም፣ ሁላችን ይህን ሞት ከምንሞት (ዮሐንስ ወንጌል 11፡50-51) ኢየሱስ የእኛን ሞት ሊሞት ወደደ፣ ‘‘መሞትን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ለኃጢአት ሞቶአልና፤ …’’ እናም የኢያሱስ ሞት ስለሃጢአታችን የተደረገ የእኛ ሞት ምትክ ነው (ወደ ሮሜ ሰዎች 6፥10)። በእርሱ ሞት እኛ የእግዚአብሔርን ይቅርታ አግኝተናል፣ ‘‘ጠላቶች ሳለን ከእግዚአብሔር ጋር በልጁ ሞት ከታረቅን፥ ይልቁንም ከታረቅን በኋላ በሕይወቱ እንድናለን’’ (ወደ ሮሜ ሰዎች 5፥10)። የኢየሱስ ሞት ምትክ ሞት ብቻ ሳይሆን እኛ ሁላችን ከእርሱ ጋር ሆነን ለሃጢአት እንድንሞት ያደረገ ሞትም ጭምር ነው፡-

‘‘ነገር ግን ከክርስቶስ ጋር ከሞትን ከእርሱ ጋር ደግሞ በሕይወት እንድንኖር እናምናለን (ወደ ሮሜ ሰዎች 6፥7-8)።

‘‘ቃሉ የታመነ ነው እንዲህ የሚለው። ከእርሱ ጋር ከሞትን፥ ከእርሱ ጋር ደግሞ በሕይወት እንኖራለን (2ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 2፥11)።

‘‘ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር፥ እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ’’ (1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 2፥24)።

‘‘ከእንግዲህስ ወዲያ ለኃጢአት እንዳንገዛ የኃጢአት ሥጋ ይሻር ዘንድ አሮጌው ሰዋችን ከእርሱ ጋር እንደ ተሰቀለ እናውቃለን፤ የሞተስ ከኃጢአቱ ጸድቋልና።ነገር ግን ከክርስቶስ ጋር ሞትን ከእርሱ ጋር ደግሞ በሕይወት እንድንኖር እናምናለን፤ ክርስቶስ ከሙታን ተነሥቶ ወደ ፊት እንዳይሞት ሞትም ወደ ፊት እንዳይገዛው እናውቃለንና። መሞትን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ለኃጢአት ሞቶአልና፤ በሕይወት መኖርን ግን ለእግዚአብሔር ይኖራል። እንዲሁም እናንተ ደግሞ ለኃጢአት እንደ ሞታችሁ፥ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ሆናችሁ ለእግዚአብሔር ሕያዋን እንደ ሆናችሁ ራሳችሁን ቁጠሩ’’ (ሮሜ 6፡6-11)።

‘‘ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ’’ (ገላቲያ 6፡14)።

ኢየሱስ የሞት መፍትሄ ነው። ከሃጢአት እና ከሞት ፍርድ ነፃ እንድንሆን አድርጎናል፣ ‘‘በክርስቶስ ኢየሱስ ያለው የሕይወት መንፈስ ሕግ ከኃጢአትና ከሞት ሕግ አርነት አውጥቶኛልና’’ (ወደ ሮሜ ሰዎች 8፥2)።

ከሞት ለመዳን የእኔስ ድርሻ ምንድን ነው?

ኢየሱስ ቅጣቴን ሁሉ ከተቀበለልኝ እና ሞቴን ከሞተልኝ፣ የእኔ ድራሻ ምን ሊሆን ነው? የሚል ጥያቄ ካለዎ፣ ምላሹ እነሆ ፡- ለበደላችን የእኛን ሞት በሞተውና እኛን ስለማጽደቅ በሶስተኛው ቀን ከሙታን መካከል በተነሳው በኢየሱስ የሚያምን ሰው ሁሉ ከአሰቃቂው ሁለተኛ ሞት ነፃ ነው። ከሞት ፍርሃት ድኗል። ከሞት ፍርድ በኢየሱስ አምልጧል። ማስረጃዎቹን ከዚህ በታች ይመልከቱ፡-

የዮሐንስ ወንጌል 11፥25 ኢየሱስም፦ ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤

የዮሐንስ ወንጌል 11፥26 ሕያው የሆነም የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘላለም አይሞትም፤ ይህን ታምኚያለሽን? አላት።

ወደ ሮሜ ሰዎች 8፥11 ነገር ግን ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው የእርሱ መንፈስ በእናንተ ዘንድ ቢኖር፥ ክርስቶስ ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው እርሱ በእናንተ በሚኖረው በመንፈሱ፥ ለሚሞተው ሰውነታችሁ ደግሞ ሕይወትን ይሰጠዋል።

ወደ ሮሜ ሰዎች 10፥9 ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህና፤

ወደ ቆላስይስ ሰዎች 2፥13 እናንተም በበደላችሁና ሥጋችሁን ባለመገረዝ ሙታን በሆናችሁ ጊዜ፥ ከእርሱ ጋር ሕይወትን ሰጣችሁ። በደላችሁን ሁሉ ይቅር አላችሁ

የዮሐንስ ራእይ 14፥13 ከሰማይም። ከእንግዲህ ወዲህ በጌታ የሚሞቱ ሙታን ብፁዓን ናቸው። መንፈስ። አዎን፥ ከድካማቸው ያርፉ ዘንድ፥ ሥራቸውም ይከተላቸዋል ይላል ብለህ ጻፍ የሚል ድምፅ ሰማሁ።

ወደ ኤፌሶን ሰዎች 5፥14 ስለዚህ፦ አንተ የምትተኛ ንቃ ከሙታንም ተነሣ ክርስቶስም ያበራልሃል ይላል።

ማጠቃለያ

ከዘላለማዊው የሞት ፍርድ ለመዳን ልናደርግ የምንችለው አንድም ነገር የለም። ጾምና ፀሎታችን፣ ሃይማኖታዊ ስርአቶቻችን፣ ሞራላዊ ድርጊቶቻችን ሁሉ ከሞት አያስመልጡንም። በሕይወት ዘመናችን ሁሉ ያለማቋረጥ ብንፀልይ፣ ያለመታከት ብንጾም፣ ሃብታችንን ሁሉ ሸጠን ለድሆች ብንመፀውት፣ ሞት አይፈራንም። ሞት የሚፈራው ኢየሱስን ብቻ ነው። ድል የነሳውም እሱ ብቻ ነው። እነዚህ መልካም ምግባራት ሁሉ በኢየሱስ በማመን ከሞት ያመለጡ አማኞች እንዲያደርጓቸው የሚጠበቁ ናቸው እንጂ የሞት ማምለጫዎች አይደሉም። ከሁለተኛው ሞት ለመዳን ይሻሉ? እንግዲያው ኢየሱስ ሞትዎን እንደሞተልዎት፣ ቅጣትዎን እንደተቀጣልዎት በልብዎ ይመኑ፤ ያመኑትን ያን እውነት በአፍዎ ይመስክሩ። አለቀ። ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ ከሆኑ የሚከተለውን አይነት ፀሎት ያድርጉ።

“ ጌታ ኢየሱስ ሆይ፣ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆንክ አምናለው። ስለሃጢአቴ በመስቀል ላይ በእኔ ፈንታ ስለሞትክልኝ አመሰግንሃለው። እባክህ፣ ሃጢአቶቼን ሁሉ ይቅር በለኝና የዘለዓለምን ሕይወት ስጠኝ። ወደ ሕይወቴ እና ወደ ልቤ አዳኜና ጌታዬ ሆነህ እንድትመጣ እለምንሃለው። በቀሪው ዘመኔ ሁሉ ላገለግልህ እወዳለሁ፤ አሜን።”

መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የሕይወትዎ ጌታ በማድረግ ቀሪው ዘመንዎን ለመኖር ወስነው ከሆነ፣ ይህንን ሊንክ በመጫን ስምዎንና የኢ-ሜይል አድናሻዎን ይላኩልንና፣ ለመንፈሳዊ ሕይወት እድገትዎ የሚቻለንን ሁሉ እገዛ እናደርግሎታለን።

 

ኢየሱስን መቀበል – መጽሐፍ ቅዱሳዊ ወይስ መናፍቃዊ?

እስቲ ለአፍታ በቡድ ማሰብ ትተን በግላችን፣ ለግላችን እናስብ። ሰከን ባለ ስሜት መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረንን ቃል እንመርምር። ለማሸነፍ ወይም ለመሸነፍ ሳይሆን ለማወቅ ቃሉን እንመርምር። ‘‘የትኛው ቡድን እንዲህ ያምናል?፣ የትኛውስ እንዲህ አያምንም?’’ የሚለውን ውጤት አልባ ክርክር ወደጎን ትተን ‘‘መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ ያለው እውነት፣ የትኛው ነው?’’ በሚል መንፈስ ርዕሰ ጉዳዩን እንመርምር።

ለመሆኑ ኢየሱስን መቀበል መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው ወይ? መቀበል የሚለው ቃል – ይሁንልኝ፣ አሜን፣ እስማማለው፣ ይህንኑ አረጋግጣለው፣ የራሴ አድርጌዋለሁ፣ እወስዳለሁ፣ ወዘተ የሚሉ ትርጉሞች አሉት። እነዚህን ትርጉሞች ከሚከተሉት የእግዚአብሔር ቃል ላይ እንፈልግ፡-

ማቴዎስ 10፡14 ከማይቀበላችሁም ቃላችሁንም ከማይሰሙ ሁሉ፥ ከዚያ ቤት ወይም ከዚያች ከተማ ስትወጡ የእግራችሁን ትቢያ አራግፉ።

ማቴዎስ 10፡41 ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ይወስዳል፥ ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል።

ማርቆስ 6፡11 ከማይቀበሉአችሁና ከማይሰሙአችሁ ስፍራ ሁሉ፥ ከዚያ ወጥታችሁ ምስክር ይሆንባቸው ዘንድ ከእግራችሁ በታች ያለውን ትቢያ አራግፉ። እውነት እላችኋለሁ፥ ከዚያች ከተማ ይልቅ ለሰዶምና ለገሞራ በፍርድ ቀን ይቀልላቸዋል አላቸው።

ሉቃስ 9፡5 ማናቸውም የማይቀበሉአችሁ ቢሆኑ፥ ከዚያ ከተማ ወጥታችሁ ምስክር እንዲሆንባቸው ከእግራችሁ ትቢያ አራግፉ።

ዮሐንስ 3፡11 እውነት እውነት እልሃለሁ፥ የምናውቀውን እንናገራለን ያየነውንም እንመሰክራለን፥ ምስክራችንንም አትቀበሉትም

ዮሐንስ 3፡32 ያየውንና የሰማውንም ይህን ይመሰክራል፥ ምስክሩንም የሚቀበለው የለም።

ዮሐንስ 3፡33 ምስክሩን የተቀበለ እግዚአብሔር እውነተኛ እንደ ሆነ አተመ።

ከላይ በቀረቡት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ውስጥ፣ ‘መቀበል’ ማለት ምን ማለት እንደሆነ መጠነኛ ግንዛቤ ከማግኘታችን በተጨማሪ ቃሉ ለመጽሐፍ ቅዱስ እንግዳ እንዳልሆነ የተረዳን ይመስለኛል። በመቀጠል ኢየሱስን መቀበል መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሆን አለመሆኑን ከመመርመራችን አስቀድሞ፣ መጽሐፍ ቅዱስ – የእግዚአብሔርን ቃል (መልዕክት) ስለ መቀበል እና መንፈስ ቅዱስን ስለ መቀበል የሚናገረውን በቅደም ተከተል እንመልከት፡-

የእግዚአብሔርን ቃል መቀበል

የሐዋርያት ሥራ 2፡41 ቃሉንም የተቀበሉ ተጠመቁ፥ በዚያም ቀን ሦስት ሺህ የሚያህል ነፍስ ተጨመሩ፤

የሐዋርያት ሥራ 8፡14 በኢየሩሳሌምም የነበሩት ሐዋርያት የሰማርያ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል እንደተቀበሉ ሰምተው ጴጥሮስንና ዮሐንስን ሰደዱላቸው።

ዮሐንስ 17፡8 የሰጠኸኝን ቃል ሰጥቻቸዋለሁና፤ እነርሱም ተቀበሉት፥ ከአንተም ዘንድ እንደ ወጣሁ በእውነት አወቁ፥ አንተም እንደ ላክኸኝ አመኑ።

ዮሐንስ 12፡48 የሚጥለኝ ቃሌንም የማይቀበለው እርሱ የሚፈርድበት አለው፤ እኔ የተናገርሁት ቃል እርሱ በመጨረሻው ቀን ይፈርድበታል።

የሐዋርያት ሥራ 11፡1 ሐዋርያትና በይሁዳም የነበሩት ወንድሞች አሕዛብ ደግሞ የእግዚአብሔርን ቃል እንደ ተቀበሉ ሰሙ።

የሐዋርያት ሥራ 17፡11 እነዚህም በተሰሎንቄ ከሚኖሩት ይልቅ ልበ ሰፊዎች ነበሩና። ነገሩ እንደዚሁ ይሆንን? ብለው ዕለት ዕለት መጻሕፍትን እየመረመሩ ቃሉን በሙሉ ፈቃድ ተቀበሉ

1ቆሮንቶስ 15፡1 ወንድሞች ሆይ፥ የሰበክሁላችሁን ደግሞም የተቀበላችሁትን በእርሱም ደግሞ የቆማችሁበትን በእርሱም ደግሞ የምትድኑበትን ወንጌል አሳስባችኋለሁ፤

2ቆሮንቶስ 11፡4 የሚመጣውም ያልሰበክነውን ሌላ ኢየሱስ ቢሰብክ፥ ወይም ያላገኛችሁትን ልዩ መንፈስ ወይም ያልተቀበላችሁትን ልዩ ወንጌል ብታገኙ፥ በመልካም ትታገሡታላችሁ።

ገላቲያ 1፡9 አስቀድመን እንዳልን እንዲሁ አሁን ሁለተኛ እላለሁ፥ ከተቀበላችሁት የተለየውን ማንም ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን።

1ተሰሎንቄ 1፡6 ደግሞ እናንተ ቃሉን በብዙ መከራ ከመንፈስ ቅዱስ ደስታ ጋር ተቀብላችሁ፥ እኛንና ጌታን የምትመስሉ ሆናችሁ፤

1ተሰሎንቄ 2፡13 ስለዚህም የመልእክትን ቃል እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ከእኛ በተቀበላችሁ ጊዜ፥ በእውነት እንዳለ በእናንተ በምታምኑ ደግሞ እንደሚሠራ እንደ እግዚአብሔር ቃል እንጂ እንደ ሰው ቃል አድርጋችሁ ስላልተቀበላችሁት፥ እኛ ደግሞ እግዚአብሔርን ሳናቋርጥ እናመሰግናለን።

ያዕቆብ 1፡21 ስለዚህ ርኵሰትን ሁሉ የክፋትንም ትርፍ አስወግዳችሁ፥ ነፍሳችሁን ማዳን የሚችለውን በውስጣችሁም የተተከለውን ቃል በየዋህነት ተቀበሉ

የሐዋርያት ሥራ 22፡18 እርሱም፦ ፍጠን ከኢየሩሳሌምም ቶሎ ውጣ፥ ስለ እኔ የምትመሰክረውን አይቀበሉህምና ሲለኝ አየሁት።

2ዮሐንስ 1፡10 ማንም ወደ እናንተ ቢመጣ ይህንም ትምህርት ባያመጣ በቤታችሁ አትቀበሉት ሰላምም አትበሉት፤

መንፈስ ቅዱስን መቀበል

ዮሐንስ 7፡39 ይህን ግን በእርሱ የሚያምኑ ሊቀበሉት ስላላቸው ስለ መንፈስ ተናገረ፤ ኢየሱስ ገና ስላልከበረ መንፈስ ገና አልወረደም ነበርና።

ዮሐንስ 14፡17 እርሱም ዓለም የማያየውና የማያውቀው ስለ ሆነ ሊቀበለው የማይቻለው የእውነት መንፈስ ነው፤ ነገር ግን ከእናንተ ዘንድ ስለሚኖር በውሥጣችሁም ስለሚሆን እናንተ ታውቃላችሁ።

የሐዋርያት ሥራ 8፡15 እነርሱም በወረዱ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን ይቀበሉ ዘንድ ጸለዩላቸው፤

የሐዋርያት ሥራ 8፡17 በዚያን ጊዜ እጃቸውን ጫኑባቸው መንፈስ ቅዱስንም ተቀበሉ

የሐዋርያት ሥራ 8፡19 እጄን የምጭንበት ሁሉ መንፈስ ቅዱስን ይቀበል ዘንድ ለእኔ ደግሞ ይህን ሥልጣን ስጡኝ አለ።

የሐዋርያት ሥራ 10፡47 በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ መልሶ፦ እነዚህ እንደ እኛ ደግሞ መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉ እንዳይጠመቁ ውኃን ይከለክላቸው ዘንድ የሚችል ማን ነው? አለ።

የሐዋርያት ሥራ 19፡2 አንዳንድ ደቀ መዛሙርትንም አገኘ። ባመናችሁ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን ተቀበላችሁን? አላቸው። እርሱም፦ አልተቀበልንም መንፈስ ቅዱስ እንዳለ ስንኳ አልሰማንም አሉት።

ሮሜ 8፡15 አባ አባት ብለን የምንጮኽበትን የልጅነት መንፈስ ተቀበላችሁ እንጂ እንደገና ለፍርሃት የባርነትን መንፈስ አልተቀበላችሁምና

1ቆሮንቶስ 2፡12 እኛ ግን ከእግዚአብሔር እንዲያው የተሰጠንን እናውቅ ዘንድ ከእግዚአብሔር የሆነውን መንፈስ እንጂ የዓለምን መንፈስ አልተቀበልንም

1ቆሮንቶስ 2፡14 ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም፤ በመንፈስም የሚመረመር ስለ ሆነ ሊያውቀው አይችልም።

ገላቲያ 3፡14 የመንፈስን ተስፋ በእምነት እንድንቀበል፥ የአብርሃም በረከት ወደ አሕዛብ በኢየሱስ ክርስቶስ ይደርስላቸው ዘንድ።

1ዮሐንስ 2፡27 እናንተስ ከእርሱ የተቀበላችሁት ቅባት በእናንተ ይኖራል፥ ማንም ሊያስተምራችሁ አያስፈልጋችሁም፤ ነገር ግን የእርሱ ቅባት ስለ ሁሉ እንደሚያስተምራችሁ፥ እውነተኛም እንደ ሆነ ውሸትም እንዳልሆነ፥ እናንተንም እንዳስተማራችሁ፥ በእርሱ ኑሩ።

የሐዋርያት ሥራ 2፡38 ጴጥሮስም፦ ንስሐ ግቡ፥ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ

የእግዚአብሔርን ቃል ወይም መልዕክት መቀበል እንዲሁም መንፈስ ቅዱስን መቀበል መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነታ እንደሆነ በበርካታ ማጣቀሻዎች ለማረጋገጥ የቻልን ይመስለኛል። መንፈስ ቅዱስ፣ ከስላሴ አንዱ መሆኑን እና አምላክነት የባሕሪዩ እንደሆነ በስላሴ ትምህረት ለሚያምኑ ሁሉ እንግዳ ሃሳብ አይደለም። ይህን አምላክ እያንዳንዳችን መቀበል እንዳለብን በማያወላዳ መልኩ ከጥቅሶቹ መገንዘብ ከቻልን፣ እግዚአብሔር ወልድን፣ ማለትም ኢየሱስን መቀበል እንዲሁ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ ልንገምት እንችል ይሆናል። ሆኖም ግን ግምታችንን ለጊዜው ወደጎን እናድርግና፣ እውነታውን ከቅዱሱ መጽሐፍ እንመርምር፡-

ኢየሱስን መቀበል

ቆላስያስ 2፡6 እንግዲህ ጌታን ክርስቶስ ኢየሱስን እንደ ተቀበላችሁት በእርሱ ተመላለሱ።

ዮሐንስ 1፡11-12 የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፥ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትምለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤

ማቴዎስ 10፡40 እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላልእኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል።

ማርቆስ 9፡37 እንደዚህ ካሉ ሕፃናት አንዱን በስሜ የሚቀበል ሁሉ እኔን ይቀበላልየሚቀበለኝም ሁሉ የላከኝን እንጂ እኔን አይቀበልም አላቸው።

ዮሐንስ 5፡43 እኔ በአባቴ ስም መጥቻለሁ አልተቀበላችሁኝምም፤ ሌላው በራሱ ስም ቢመጣ እርሱን ትቀበሉታላችሁ።

ዮሐንስ 13፡20 እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ማናቸውን የምልከውን የሚቀበል እኔን ይቀበላልእኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል።

ከላይ በቀረቡት ማስረጃዎች መሰረት ኢየሱስን መቀበል፣ መናፍቃዊ ሃሳብ ሳይሆን መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሆኑን የተገነዘብን ይመስለኛል። ‘‘እናም ኢየሱስን ተቀብያለሁ ወይ?’’ ‘‘መንፈስ ቅዱስንስ ተቀብያለሁ ወይ?’’ ‘‘እውነተኛ ወንጌል ተቀብያለሁ ወይ?’’ ብሎ ራስን መጠየቅ ተገቢ ከመሆኑ በላይ ራሳችንን ልንጠይቅ ከሚገቡን ጥያቄዎች መካከል ዋነኛዎቹ ናቸው። ክቡሩን አምላክ፣ መድሃኔዓለም ክርስቶስን ያልተቀበልን ማንን ልንቀበል ነው? ይህን የእግዚአብሔር ልጅ ያልተቀበሉት አይሁድ (ዮሐንስ 1፡11-12) ከእግዚአብሔር ፍርድ ስር ከሆኑ፣ ልጁን ያልተቀበልን እኛ ከዚህ ፍርድ እንዴት ልናመልጥ እንችላለን? የተቀበሉቱ ግን፣ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚል የእግዚአብሔር ልጆች እንዲሆኑ ስልጣን ተሰጧቸዋል። የእግዚአብሔር ልጆች ከሆንን ደግሞ የመንግስቱ ወራሾች ነን (ሮሜ 8፡17)። እናም፣ ፍርድን ከመቀበል ኢየሱስን ተቀብለን በእርሱ እንመላለስ (ቆላሲያስ 2፡6)። የአውሬውን ቁጥር ከመቀበል (ራዕይ 14፡9-10፤ ራዕይ 14፡ 11፤ ራዕይ 20፡4) ኢየሱስን ተቀብለን የእግዚአብሔር ልጆች እንሁን (ዮሐንስ 1፡11-12)።

መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የሕይወትዎ ጌታ በማድረግ ቀሪው ዘመንዎን ለመኖር ወስነው ከሆነ፣ ይህንን ሊንክ በመጫን ስምዎንና የኢ-ሜይል አድናሻዎን ይላኩልንና፣ ለመንፈሳዊ ሕይወት እድገትዎ የሚቻለንን ሁሉ እገዛ እናደርግሎታለን።