የገንዘብ ፍቅር እና ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ የሰጠው ዐደራ 6፡1-21

፩. የቤተ ክርስቲያን መሪ ሠራተኞች (ባሪዎች) ከአሠሪዎቻቸው (ከጌቶቻቸው) ጋር ተገቢው ግንኙነት እንዲኖራቸው መርዳት አለባቸው (1ኛ ጢሞ. 6፡1-2)።

በታሪክ ውስጥ እጅግ አስቸጋሪ ከነበሩት ውስጥ አንዱ በሠራተኞችና አሠሪዎቻቸው መካከል ያለውን ችግር ለመፍታት ቤተ ክርስቲያን ሊኖራት የሚገባውን ሚና መወሰኑ ነው። በጳውሎስ ዘመን ይህ ግንኙነት በአብዛኛው በባሪያና በጌታ መካከል የሚታይ ነበር። በመጀመሪያው ምእተ ዓመት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ባሪያዎች ነበሩ። ሃብታሞችና ነጋዴዎችም የባሪያ አሳዳሪዎች ነበሩ። ከቀድሞዎቹ አማኞች አብዛኞቹ ባሪያዎች ነበሩ። እንደ ፊልሞናና አናሲሞስ ባሪያውም ጌታውም ክርስቲያኖች የሆኑበት አጋጣሚዎችም ነበሩ። በዚህ ሰዎችን በባርነት በማሳደሩ አስከፊ ተግባር የክርስቲያኖች ምላሽ ምን ሊሆን ይገባል? ክርስቲያን የሆኑ ባሮች ነፃ ለመውጣት መታገል ያስፈልጋቸዋል? ለክርስቲያኖች ባሪያ ማሳደሩ ስሕተት ነው? የትኞቹም የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች የባሪያ አሳዳሪነትን ተግባር ለማስወገድ ቀጥተኛ የሆነ አሳብ አላቀረቡም። ነገር ግን ሰዎች ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት በቤተ ክርስቲያን እኩል እንደሆኑ በመግለጽ የባሪያ አሳዳሪነትን ልምምድ አለመደገፋቸውን አሳይተዋል። ሰዎች ሁሉ ሰብአዊ ክብራቸው ተጠብቆ ሊኖሩ ይገባልና። እንደ አለመታደል ሆኖ በታሪክ ሁሉ ክርስቲያኖች የባሪያ አሳዳሪነት ምን ያህል አስከፊ እንደሆነ ሳይገነዘቡ ቆይተዋል። በምዕራቡ ዓለም፥ ክርስቲያኖች እስከ ዛሬ አንድ መቶ ዓመታት ድረስ ባሪያዎች ነበሩዋቸው። ዛሬም እንኳን በአንዳንድ የዓለም ክፍሎች የባሪያ አሳዳሪነት እንደ ቀጠለ ይገኛል።

ጳውሎስ ጢሞቴዎስ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ክርስቲያን ባሪያዎች በባሪያ አሳዳሪነት ሥርዓት ላይ እንዳያምጹ እንዲነግሯቸው አሳስቧል። ይልቁንም ጌቶቻቸውን ማክበርና ማገልገል ነበረባቸው። ጌታቸው አማኝ ስለሆነ ብቻ የተለየ አያያዝ ወይም አነስተኛ ሥራ እንዲሰጣቸው መጠየቅ አያስፈልጋቸውም ነበር። ነገር ግን በሥራቸው በጌታ ወንድማቸው የሆነውን ሰው እንደሚረዱት በማሰብ፥ የበለጠ ተግተው ሊሠሩ ይገባ ነበር። ምንም እንኳ ዛሬ በብዙ አገሮች ባሪያ አሳዳሪነት ባይኖርም፥ ከዚህ ግንኙነት የመነጩትን መርሆዎች ለሠራተኛና አሠሪ መጠቀም ይቻላል። ክርስቲያን ሠራተኛ አሠሪውን ማክበር ይኖርበታል። ምንም እንኳ አሠሪው ራስ ወዳድና የማይመች ቢሆንም ይህንኑ ማድረግ ይኖርበታል። መጽሐፍ ቅዱስ እንድ ሠራተኛ አሠሪውን እንዲቀናቀን፥ እንዲቃወም ወይም እንዲጠላ አይፈቀድለትም። እንዲሁም አሠሪው አማኝ በመሆኑ ብቻ ሠራተኛው የተለየ አስተያየት እንዲደረግለት ወይም የሥራ ጫና እንዲቀነስለት መጠበቅ የለበትም። ነገር ግን በጌታ ወንድሙ የሆነውን አሠሪውን ለመርዳት የበለጠ ተግቶ መሥራት ይችላል። ሰዓቱን ጠብቆ ተግባሩን የማያከናውን ሰነፍ ሠራተኛ የክርስቶስን ስም ያሰድባል። እግዚአብሔር ልጆቹ ተግተው እንዲሠሩና የሥራ ሰዓታቸውን እንዳያዛንፉ፥ ብሎም አሠሪያቸውን እንዲያከብሩ ይፈልጋል። አሠሪያቸው ክርስቲያን ቢሆንም ባይሆንም ይህንኑ ማድረግ ይኖርባቸዋል።

በተጨማሪም እግዚአብሔር አሠሪዎች ሠራተኞቻቸው በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠሩ ሰዎች መሆናቸውን እንዲገነዘቡ ይፈልጋል። ሠራተኛው አማኝ ከሆነ ደግሞ ሁለቱም የአንድ መለኮታዊ ቤተሰብ አባላት መሆናቸውን መገንዘቡ ተገቢ ነው። ስለሆነም እግዚአብሔር አሠሪው ሠራተኞቹ ያለ አድልዎና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ማስተዳደር ይኖርበታል። ሠራተኞቹ ቤተሰባቸውን ማስተዳደር ይችሉ ዘንድ ተመጣጣኝ ክፍያ ሊደረግላቸው ይገባል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ክርስቲያን ሠራተኞች ለአሠሪዎቻቸው እንዲህ ዓይነት አመለካከት ያላቸው ይመስልሃል? ለምን? የጳውሎስን ትምህርት ከተከተሉ የሥራቸው ሁኔታ እንዴት እንደሚለወጥ ግለጽ። ለ) አብዛኞቹ ክርስቲያን አሠሪዎች መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውን አመለካከት የሚከተሉ ይመስልሃል? ለምን? እግዚአብሔር በሚፈልገው መንገድ ሠራተኞቻቸውን ለመርዳት ባህሪያቸው እንዴት ሊለወጥ እንደሚገባ ግለጽ።

፪. የቤተ ክርስቲያን መሪ ለሆነው ጢሞቴዎስ የተሰጠ የግል ምክር (1ኛ ጢሞ. 6፡3-21)

ጳውሎስ በመልእክቱ ማጠቃለያ ላይ ጢሞቴዎስን እንደ ምሳሌ በመውሰድ፥ ብዙውን ጊዜ መሪዎች በግላዊ ሕይወታቸው የሚሸነፉባቸውን ነገሮች ይጠቁማል። ሁሉም የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እነዚህን አስቸጋሪ ነገሮች በመረዳት ሕይወታቸውን በጥንቃቄ መጠበቅ ይኖርባቸዋል። ይህም የክርስቶስን ስም እንዳያሰድቡ ይረዳቸዋል።

 1. ጢሞቴዎስ ራሱን ከገንዘብ ፍቅር መጠበቅ አለበት (1ኛ ጢሞ. 6፡3-10)።

ጳውሎስ ይህንኑ ስለ ገንዘብ የሚኖር የተሳሳተ አመለካከት ማብራራት የጀመረው አሁንም ስለ ሐሰተኛ አስተማሪዎች በመጥቀስ ነው። ጳውሎስ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የሐሰተኛ አስተማሪዎችን ባሕርያት በመረዳት ቤተ ክርስቲያናቸውን ሊጠብቁ የሚችሉባቸው በርካታ መንገዶች እንዳሉ ያስረዳል። በመጀመሪያ፥ ሐሰተኛ አስተማሪዎች ሐሰተኛ አስተምህሮዎችን ያቀርባሉ። ማለትም ሚዛናዊ ያልሆኑና መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያስተምራቸው እውነቶች ሁሉ ጋር የማይጣጣሙ አሳቦችን ከእግዚአብሔር ቃል እያወጡ ያስተምራሉ። ሁለተኛ፥ ክርስቲያኖች የእግዚአብሔርን ቃል በማጣቀስ መሳሳታቸውን በሚያሳዩዋቸው ጊዜ ለመቀበል ፈቃደኞች አይሆኑም። ብዙውን ጊዜ ሐሰተኛ አስተማሪዎች እናውቃለን በሚሉት አሳብ ስለሚኩራሩ የሌሎችን ትምህርት ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ለመቀበል አይፈልጉም። ሦስተኛ፥ አንድነትን ከማበረታታት ይልቅ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሰዎችን ይከፋፍላሉ። አራተኛ፥ ሐሰተኛ አስተማሪዎች የሌሎችን መልካም ስም ያጎድፋሉ፤ በተለይም ከትምህርታቸው ጋር የማይስማሙትን የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ስም ለማጥፋት ይጣጣራሉ። አምስተኛ፥ ለገንዘብና ለግል ጥቅማ ጥቅሞች ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው። ሐሰተኛ አስተማሪዎች መሪዎች ለመሆን ይፈልጋሉ። በዚህም የገንዘብ ወይም በሰዎች የመከበር ጥቅም ለማግኘት ይሻሉ።

የውይይት ጥያቄ፡- በቤተ ክርስቲያንህ ላይ ችግር ያስከተሉትን አንዳንድ የሐሰት አስተማሪዎች ግለጽ። እነዚህ ባሕርያት በምን መልኩ ተገልጸዋል?

ጳውሎስ የገንዘብ ፈተና ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ ተገንዝቧል። በተለይም ገንዘብ እየተከፈላቸው ለሚያገለግሉ መሪዎች ይህ ከባድ ፈተና ነበር። ጳውሎስ ይህን ሲል ገንዘብና ብልጽግና ክፉ ነው ማለቱ አይደለም። ነገር ግን ገንዘብን ከመጠን በላይ መሻት ለመንፈሳዊ ዕድገታችንና አገልግሎታችን አደገኛ መሆኑን ያስተምራል። አንድ ጊዜ ምን ያህል ገንዘብ ቢኖርህ ያረካሃል የሚል ጥያቄ ብዙ ሚሊዮን ብሮች ለነበሩት ግለሰብ ቀርቦለት ነበር። ሀብታሙም ሰውዬ፥ አንድ ሚሊዮን ቢጨመርልኝ ሲል መልሷል። የሰው ልጅ እግዚአብሔር ምንም ያህል ቢባርከውም ሌላ ነገር ለመጨመር ይፈልጋል።

ከዚሁ በተቃራኒ ጳውሎስ ጢሞቴዎስና የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በሙሉ ፈሪሃ እግዚአብሔር ያለበትን እርካታ ንብረታቸው እንዲያደርጉ አሳስቧል። ፈሪሃ እግዚአብሔራዊ ሕይወት እንዲኖረን መጣር አለብን። መሪዎች ባላቸው ነገር መርካትን መማር አለባቸው። ሁልጊዜም ተጨማሪ ሀብት ለማግኘት መጣሩ ሞኝነት ነው። ምክንያቱም የኋላ ኋላ በምንሞትበት ጊዜ አንድም ነገር ይዘን አንሄድምና፡፡ የገንዘብ ፍቅር ደግሞ ለሌሎች ኃጢአቶች ይመራል። ገንዘብ ያላቸውም ሰዎች ለኩራት ኃጢአት ቅርብ ናቸው። አንድ ሰው ቶሎ ገንዘብ ለማካበት በሚፈልግበት ጊዜ ጉቦ ለመስጠት ወይም ለማጭበርበር ይገደዳል። የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ከመባ ወይም ከውጪ ድርጅቶችና ለልማት ከሚመጣ ገንዘብ ለመስረቅ ይፈተናሉ። የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ባላቸው መርካትና እግዚአብሔር የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ እንደሚያሟላላቸው መተማመን አለባቸው። እግዚአብሔር ለሰጣቸው በረከቶች ሊያመሰግኑትና እነዚህኑ በረከቶች እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ ለመጠቀም መጣር አለባቸው (1ኛ ጢሞ. 6፡17-19)።

የውይይት ጥያቄ፡– የገንዘብ ፍቅር የቤተ ክርስቲያንን መሪ ሕይወት ሲያበላሽ ያየህበትን ሁኔታ ግለጽ።

 1. ጢሞቴዎስ ሕይወቱንና እምነቱን በመጠበቅ በእግዚአብሔርና በሰዎች ፊት በንጽሕና መመላለስ ይኖርበታል (1ኛ ጢሞ. 6፡11-21)።

ለመሪዎች ሁለተኛው ዋንኛ ፈተና ወሲባዊ ንጽሕና ነው። በመሆኑም ጳውሎስ ጢሞቴዎስ በዚህ ረገድ ሕይወቱን በንጽሕና እንዲጠበቅ ያዝዘዋል። የትኛውም ክፉ ነገር በተለይም የወሲብ ኃጢአት ለሕይወቱ አደገኛ ስለሆነ በተቻለው አቅም መሸሽ ይኖርበታል። በተቃራኒው ጢሞቴዎስ ጽድቅን፥ ፈሪሃ እግዚአብሔርን፥ እምነትን፥ ፍቅርን፥ ትዕግሥትንና ገርነትን እንዲከተል ተናግሯል። በየዕለቱ እነዚህ ባሕሪያት በሕይወቱ ውስጥ እያደጉ እንዲሄዱ ማድረግ ያስፈልገዋል። ጳውሎስ ጢሞቴዎስ በውሸት እውቀት ከተባለ ለዓለም ከሚመች ከከንቱ መለፍለፍና መከራከር በመራቅ ጊዜውን በአግባቡ እንዲጠቀም ይመክረዋል። አንድ ቀን በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት በመቅረብ ሕይወቱን ስለመራበት መንገድ እንደሚገመገምም ያስጠነቅቀዋል። ጢሞቴዎስ በዚያን ጊዜ ለማፈር አይፈልግም ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በመንፈሳዊ ሕይወታችው ለማደግ ቢፈልጉና ክርስቶስ አመራራቸውንም ሆነ ሕይወታቸውን እንደሚገመግማቸው ቢያስታውሱ፥ የመሪነት አገልግሎታቸው እንዴት የሚለወጥ ይመስልሃል? ለ) አሁኑኑ በክርስቶስ ፊት ቀርበህ ብትገመግም የምታፍርባቸው ጉዳዮች ምን ምንድን ናቸው? ስለ እነዚህ ጉዳዮች ንስሐ በመግባት መንገድህን ቀይር። መንፈስ ቅዱስ እንዲቀድስህና እግዚአብሔርን ሚያስደስት ሕይወት እንዲኖርህ እንዲያግዝህ ጸልይ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

መሪ አድልዎ በሌለው ሁኔታ በሚያገለግልበት ጊዜ የቤተ ክርስቲያኒቱ አባላት ሊያከብሩት ይገባል (1ኛ ጢሞ. 5፡17-25)

የቤተ ክርስቲያን መሪነት ከባድ አገልግሎት ነው። ደመወዙ በጣም ዝቅተኛ ከመሆኑም በላይ፥ ብዙ የቤተ ክርስቲያን ምእመናን ፍላጎታቸው በማይሟላበት ጊዜ ያጉረመርማሉ። መሪው በአማኞች መካከል የሚከሰቱትን ስሜትን የሚጎዱ ነገሮችና ፀቦች የማስተካከል ኃላፊነት አለበት። ከቤተሰቡ ጋር የሚያሳልፈው በቂ ጊዜም አይኖረውም። ጳውሎስ በማስተማርና በመስበክ የሚተጉ መሪዎች እጥፍ ክብር እንደሚገባቸው ገልጾአል። የቤተ ክርስቲያን ምእመናን መሪዎቻቸውን በማክበር አገልግሎታቸውን ቀለል ሊያደርጉላቸው ይገባል። በተጨማሪም ጳውሎስ ለጠቅላላው ቡድን ጥቅም በመሥዋዕትነት ለሚያገለግሉት መሪዎች ምእመናን የገንዘብ ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባም ያስተምራል። መሪው በሚገባ ለመምራት፥ ለመስበክና ለማስተማር የሚችለው ለአገልግሎቱ በቂ ጊዜ ሲሰጥ ነው። ብዙ ጊዜ ሌላ ሥራ ወይም ንግድ ከሌለው፥ የገንዘብ ችግር ይገጥመዋል። በመሆኑም አገልጋዩ ኑሮን ለመምራት ባለመቻሉ፥ ቤተሰቡን የሚያስተዳድርበት ገንዘብ በማጣቱ ተጨማሪ ሸክም እንዳያድርበት፥ ቤተ ክርስቲያን ደመወዝ ልትከፍለው ይገባል። አገልጋዩ በቂ ደመወዝ የሚያገኝ ከሆነ፥ ስለ ገንዘብ ከማሰብ ተላቅቆ በአገልግሎቱ ላይ ሊያተኩር ይችላል። ለመሪነት፥ ለስብከትና ለማስተማር አገልግሎት ሙሉ ጊዜያቸውን ለሚሰጡት ሰዎች በቂ ደመወዝ የማትከፍል ቤተ ክርስቲያን፥ የመጽሐፍ ቅዱስን ትእዛዝ ትጥሳለች። ደመወዝ ሳይከፍሉ መሪዎች በነፃ ጊዜያቸውን እንዲሰጡ የሚያደርጉ አብያተ ክርስቲያናት ብዙውን ጊዜ የኋላ ኋላ ቤተ ክርስቲያኒቱን ይጎዳሉ። ቁልፍ መሪዎች ለመተዳደሪያ የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ ለማግኘት ወዲያ ወዲህ ለማለት የሚገደዱ ከሆነ፥ ሙሉ ለሙሉ ራሳቸውን ለአገልግሎት ሊሰጡ አይችሉም። ተገቢው አሠራር ለአብያተ ክርስቲያናት ለመሪዎች ደመወዝ መክፈል ቢሆንም፥ መሪዎች እንደ ጳውሎስ ጊዜያቸውን በነፃ ለመለገስ የሚፈቅዱባቸው አጋጣሚዎችም ሊኖሩ ይችላሉ (1ኛ ቆሮ. 9፡6-18)። ይሁንና፥ ይህ የአገልጋዩ የግል ምርጫ እንጂ ቤተ ክርስቲያን በግዳጅ የምታስፈጽመው ሊሆን አይችልም።

ጳውሎስ ጢሞቴዎስ ቤተ ክርስቲያንን ስለሚመራበት ሁኔታ አንዳንድ የምክር ቃሎችን ሰጥቷል፡–

ሀ) ምእመናን ወይም መሪዎች የፈጸሟቸውና በጠቅላላው የቤተ ክርስቲያን ማኅበረሰብ ላይ ተጽዕኖ ያስከተሉ ታላላቅ ኃጢአቶች በምእመናን ሁሉ ፊት ቀርበው እልባት ሊያገኙ ይገባል። ይህም ቤተ ክርስቲያኒቱን በንጽሕና ለመጠበቅ ይረዳል። ጳውሎስ አንድ ሰው እንደ ክፉ አሳብ ያሉ ድብቅ ኃጢአቶች በሚኖሩት ጊዜ ሁሉ ቤተ ክርስቲያን ፊት እየተነሣ ኃጢአቱን መናዘዝ አለበት ማለቱ አይደለም። ነገር ግን በአንድ አማኝ ወይም መሪ ሕይወት ውስጥ የዐመፅ መንፈስ ሲኖርና ይህም ዐመፅ ያስከተለው ኃጢአት በአማኞች ሁሉ ዘንድ በሚታወቅበት ጊዜ፥ መፍትሔውም ምእመናንን ባሳተፈ መልኩ እልባት ማግኘት እንዳለበት ይናገራል። የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ግለሰቡን በይፋ ሊገልጹት ይገባል። በመሆኑም በምእመናን ፊት ቀርቦ ንስሐ መግባት አለበት። ንስሐ ካልገባ፥ ውሳኔው የቤተ ክርስቲያኒቱ ምእመናን የሚሰጡት ይሆናል። እንዲህ ዓይነቱን ኃጢአት በዚህ ዓይነት መንገድ ማስተናገዱ፥ ሦስት ዐበይት ውጤቶችን ያስከትላል።

በመጀመሪያ፥ ቤተ ክርስቲያን በቤተሰብ ወይም በጓደኛሞች የአስተሳሰብ መሥመር አትከፋፈልም። ነገሮች በምሥጢር በሚያዙበት ጊዜ፥ የቤተ ክርስቲያን አባላት የተሳሳተ መረጃ ይደርሳቸዋል። ይህም እንደ ተሳሳተ ውሳኔ ይቆጠራል። በይፋ በሚታይበት ጊዜ ግን ክፍፍልን መፍጠር አዝማሚያው አናሳ ይሆናል።

ሁለተኛ፡ ግለሰቡ የኃጢአትን አደገኛነት እንዲገነዘብና ራሱን ዝቅ አድርጎ ንስሐ እንዲገባ ይረዳዋል።

ሦስተኛ፥ ሰዎች ለኃጢአት ፍትሐዊና ግልጽ እልባት እንደሚሰጥ ሲገነዘቡ በግድየለሽነት የኃጢአትን አመለካከት ከመያዝ ይቆጠባሉ። ምንም እንኳን በብዙ ባህሎች ውስጥ ኃጢአቱን በማጋለጥ አንድን ሰው ማሳፈሩ ትክክል ባይሆንም፥ መጽሐፍ ቅዱሳዊው መንገድ ግልጽ ተጋፍጦና ኑዛዜ የሚካተትበት ነው። ይህም ኃጢአትን ትኩረት ሰጥቶ ለማስወገድና በክርስቶስ አካል ውስጥ ቅድስናን ለማስፈን ይረዳል። ዛሬ በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ኃጢአት የበረከተው በግልጽ ለመጋፈጥና ለመናዘዝ ባለመፈለጋችን ይሆን?

(ማስታወሻ፡ ይህ መመሪያ በማቴዎስ 18፡15-17 የቀረቡትን በቅድሚያ ከተከተልን በኋላ ልንከተለው የሚገባ ቀጣይ እርምጃ ነው።)

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በቅርብ ጊዜ በቤተ ክርስቲያንህ ይፋዊ ተግሣጽ፥ ይፋዊ ኑዛዜ ወይም ውሳኔ የተሰጠው መቼ ነው? ለ) በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ብዙ ኃጢአቶች በግልጽ የማይታዩት ለምን ይመስልሃል? ሐ) በቤተ ክርስቲያን ላይ ተጽዕኖ ያስከተለው ኃጢአት ከመደበቅና ይፋዊ እልባት ካለመስጠት የመነጩት አሉታዊ ነገሮች ምን ምንድን ናቸው? መ) አንድ የቤተ ክርስቲያንህ አባል በባህላችን እንዲህ ዓይነት ነገር አናደርግም ቢል ምን ዓይነት ምላሽ ትሰጠዋለህ? መጽሐፍ ቅዱሳዊ ዕገዳዎች ከባህል የበለጠ አስፈላጊነት የሚኖራቸው ይመስልሃል? ለምን? ሠ) እግዚአብሔር በሰዎች ሕይወት ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ በመሥራት ምእመናን ንስሐ እንዲገቡና ለጽድቅ እንዲጠሙ ያሳስባቸው ዘንድ በጸሎት ጠይቅ።

ለ) የቤተ ክርስቲያን መሪ አድልዎ በሌለበት ሁኔታ አገልግሎቱን ማካሄድ አለበት። አንድ ሰው መሪ በሚሆንበት ጊዜ፥ ቤተሰቡ ጠቅላላው የቤተ ክርስቲያን ምእመናን የሚገኙበት ቡድን ይሆናል። ስለሆነም ጓደኞቹን፥ ሥጋዊ ቤተሰቡን፥ የጎሳውን አባላት የሚያስተናግድበትን መንገድ የቤተ ክርስቲያን አባላት በእኩልነት እንደሚያይ የሚያንጸባርቅ መሆን አለበት። የቤተ ክርስቲያን መሪዎች አድልዎ በማስፈጸም ለቤተሰቦቻቸው፥ ለወዳጆቻቸውና ለጎሳቸው አባላት የተለየ ጥቅማ ጥቅም በሚያስገኙበት ወቅት በእግዚአብሔር ቤተሰብ ውስጥ ከፍተኛ ችግር ይፈጠራል። መሪዎች ልጆቻቸውን የቤተ ክርስቲያን ኳየር ውስጥ በማስገባት፥ ወዳጆቻቸውን ቤተ ክርስቲያን እስፖንሰር ወደምታደርገው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት በመላክ ወይም የጎሳ አባሎቻቸውን ለሽምግልና በማስመረጥ አድልዎ ሊፈጽሙ ይችላሉ። በዚህም ረገድ ከባህላችን ይልቅ መጽሐፍ ቅዱሳዊው አሠራር ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል።

ሐ) የቤተ ክርስቲያን መሪ በችኮላ የመሪነትን ኃላፊነት ለሰዎች መስጠት የለበትም። የቀድሞዋ ቤተ ክርስቲያን በሰዎች ላይ መቼ እጇን እንደምትጭንና ይህም ምን እንደሚያመለክት አልተገለጸም። አንዳንድ ምሁራን እንደሚያስቡት ይህ የሚሆነው አንድ ሽማግሌ ንስሐ ገብቶ ወደ ቤተ ክርስቲያን ኅብረት በሚመለስበት ጊዜ ነው ይላሉ። በዚህ ጊዜ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ከራሱ ላይ እጆቻቸውን ጭነው በመጸለይ ወደ ቤተ ክርስቲያን ኅብረት ይመልሱታል። ጳውሎስ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ኃጢአት የፈጸመውን ሰው አመራር ከመመለሳቸው በፊት ንስሐ መግባቱን ማረጋገጥ እንዳለባቸው ያሳስባል። ንስሐ የልብንና የተግባርን ለውጥ የሚያመለክት እንጂ፥ በቀላሉ ይቅርታ መጠየቅን ብቻ የሚያመለክት መሆን የለበትም።

ይሁንና፥ እጅን መጫን አንድን መሪ ወይም ሽማግሌ ለአገልግሎት የማቆምን ልምምድ ይመስላል። ለምሳሌ ጳውሎስና በርናባስ ለወንጌል መልእክተኝነት አገልግሎት በተለዩ ጊዜ መሪዎች እጆቻቸውን ጭነው ጸልየውላቸዋል (የሐዋ. 13፡3)። ጳውሎስ ጢሞቴዎስ ሰዎችን በችኮላ ለመሪነት እንዳይቀበል የሚያሳስበው ይመስላል። ይህ አንድን ሰው ለመሪነት ከመወከሉ በፊት፥ ሕይወቱን መመርመርና መንፈሳዊነቱ፥ ብስለቱና ንጽሕናው ለመሪነት የሚያበቃው መሆኑን ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው። ይህ መሪም ለአገልግሎት መሾም የሚጀምረው ሰዎች ለአዲሱ ሽማግሌ እንዲጸልዩና እጆቻቸውን እንዲጭኑበት በማድረግ ነበር። እንደ ጢሞቴዎስ ያለ መሪ በአዲሱ መሪ ላይ እጁን በሚጭንበት ጊዜ የግለሰቡ ሕይወት ተጨምሮ ለዚሁ አገልግሎት ብቁ ሆኖ መገኘቱን ማረጋገጡ ነበር። ይህንን በችኮላ ማከናወኑ ትክክለኛ ያልሆኑ መሪዎችን ወደ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት መጋበዝ ይሆናል። አንድን ሰው በችኮላ መሾም ወይም በኃጢአት ውስጥ የሚኖር ግለሰብን ለመሪነት አገልግሎት መቀበል ማለት ቤተ ክርስቲያንን ወደ ኃጢአት መምራት ማለት ነው። ይህ ማለት ደግሞ የግለሰቡ ክፉ አመራርና ኃጢአት ተካፋይ መሆን ነው። እግዚአብሔር እጁን በመጫን የሾመውን ግለሰብ ቤተ ክርስቲያንን ባለመጠበቁ በኃላፊነት ይጠይቀዋል።

የውይይት ጥያቄ፡- እነዚህን የጳውሎስ ማስጠንቀቂያዎች አብያተ ክርስቲያናት ሊያጤኗቸውና ተግባራዊ ሊያደርጓቸው የሚገባው ለምንድን ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የቤተ ክርስቲያን መሪ ቤተ ክርስቲያን መበለቶችን የምትረዳበትን መንገድ ማዘጋጀት ይኖርበታል (1ኛ ጢሞ. 5፡1-16)

ጳውሎስ አንድ የቤተ ክርስቲያን መሪ ራሱንና ምእመናኑን እንዴት ከሐሰተኛ ትምህርት እንደሚጠብቅ ካብራራ በኋላ፥ በዝርዝር ጉዳዮች ላይ ያተኩራል። እነዚህም ዝርዝር ጉዳዮች ቤተ ክርስቲያን በማኅበረሰብ ውስጥ መልካም ምሳሌና ምስክርነት እንድትሰጥ የሚያግዛት ናቸው።

1) መሪዎች ከሁሉም የማኅበረ ምእመናን አባላት ጋር በሚያደርጓቸው ግንኙነቶች ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው። መሪዎች ብዙ ትምህርት ቢኖራቸው እንኳን፥ በዕድሜ የሚበልጧቸውን ሰዎች ማክበር አለባቸው። ከቅንዓትና ጥርጣሬ ርቀው፥ የዕድሜ እኩዮቻቸውን እንደ ወንድሞቻቸውና እኅቶቻቸው መቁጠር አለባቸው። ከተቃራኒ ጾታ ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት፥ አንድ መሪ ቤተሰባዊ ዝምድና ማድረግ አለበት። ይህም መሪው በኃጢአት እንዳይወድቅ ወይም ደግሞ ሌሎች ሰዎች የተሳሳተ ግምት እንዳይሰጡት ይረዳዋል።

2) መሪዎች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚገኙትን መበለቶች በጥንቃቄ መንከባከብ አለባቸው። በጥንት ማኅበረሰቦች ውስጥ፥ መበለቶች ብዙ ችግሮች ነበሩባቸው። መበለቶች የቤተሰቡ አካል ስለማይሆኑ፥ ወላጆቻቸው ከሞቱ በኋላ ከወንድሞቻቸውና ከእኅቶቻቸው ምንም ዓይነት እርዳታ አያገኙም ነበር። የሞቱ ባሎቻቸውም ዘመዶች አያስጠጓቸውም ነበር። መበለቶች ብዙውን ጊዜ ትናንሽ ልጆቻቸውን የሚንከባከቡበትን መንገድ አያገኙም ነበር። እነዚህ ሰዎች ምንም ዓይነት መብት ስላልነበራቸው መሬታቸውን፥ ቤታቸውን የመነጠቅ አደጋ ይደርስባቸው ነበር። በብሉይ ኪዳን ዘመን እግዚአብሔር መበለቶችን ስለመንከባከብ ልዩ ትእዛዝ ሰጥቷል። ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ መበለቶችን ስለ መንከባከብ የሚከተለውን አዟል።

ሀ) አማኝ የሆኑ የቤተሰብ አባላት የቤተ ክርስቲያንን እርዳታ ከመጠበቅ ይልቅ መበለት የሆኑ ዘመዶቻቸውን ፍላጎቶች ማሟላት ያስፈልጋቸው ነበር። መበለት የሆነች ዘመዱን ወይም እናቱን ለመንከባከብ የማይፈልግ ሰው ከክርስቲያናዊ ባህሪ ውጪ እየተመላለሰ መሆኑ ተገልጾአል። እንዲህ ዓይነቱ ሰው ‘ከዓለማዊ የከፋ በመሆኑ’፥ የቤተ ክርስቲያን የቅጣት እርምጃ ሊወሰድበት ይገባል። ከቤተሰብ አባሎቿ መካከል ረዳት የለሸ መበለት መኖሯን የምታውቅ ሴት በራስ ወዳድነት የእርዳታ እጆቿን ከመሰብሰብ ወይም ቤተ ክርስቲያን እንድትረዳት ከመጠበቅ ይልቅ መበለቷን መንከባከብ ይገባታል።

ለ) ቤተ ክርስቲያን ምንም ዓይነት ረዳት የሌላቸውን ክርስቲያን ሴቶች የመንከባከብ ኃላፊነት አለባት።

ሐ) በቤተ ክርስቲያን መዝገብ ውስጥ ሰፍረው እርዳታ ሊያገኙ የሚችሉት ያረጁ (ከ 60 ዓመት በላይ) እና ረዳት የለሽ የሆኑ መበለቶች ብቻ ሊሆኑ ይገባል። ጳውሎስ እዚህ ጋ ለማስተላለፍ የፈለገው መልእክት ቤተ ክርስቲያን ወጣት ሴቶች ለችግር እንዳይጋለጡ ወይም በወሲብ ኃጢአት እንዳይወድቁ እንደገና የሚያገቡበትን መንገድ ማመቻቸት እንዳለባት ነው። በዕድሜ የገፉ መበለቶች ወጣት ሴቶችን በመርዳት በመንፈሳዊነት እንዲያድጉና ለምሳሌያዊነት የሚበቁ እናቶችና ሚስቶች እንዲሆኑ መርዳት አለባቸው። እነዚህ በዕድሜ የገፉ መበለቶች በችግር ውስጥ ያሉትን ሰዎች በመርዳቱ ተግባር ላይ ማተኮር ይኖርባቸዋል። የተመቻቸ ሕይወት ከመፈለግ ወይም ባሎቻቸውን በማጣታቸው ከማጉረምረም ይልቅ በተለያዩ ጉዳቶችና ችግር ውስጥ ያሉትን ሰዎች በመርዳቱ ላይ አጽንኦት መስጠት ያስፈልጋቸዋል።

መ) ወጣት መበለቶች እርዳታ የሚያገኙ መበለቶች መዝገብ ውስጥ መስፈር የለባቸውም። መበለቶች በቤተ ክርስቲያን መዝገብ ውስጥ ሰፍረው እርዳታ ከሚያገኙባቸው መንገዶች አንዱ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለማገልገል መሐላ መፈጸማቸው ሳይሆን አይቀርም። (ድሆች ሳይሠሩ እርዳታ ማግኘት እንደሌለባቸው ከብሉይ ኪዳንና ከጥንታዊ ቤተ ክርስቲያን ምሳሌነት እንረዳለን) ሙሉ ለሙሉ ክርስቶስን ለማገልገል ይችሉ ዘንድ ከእንግዲህ ላለማግባት ቃል ይገባሉ። ነገር ግን እንደገና የማግባትና ከባል-አልባነት ነቀፋ የመላቀቅ ፍላጎት አለባቸው። በመሆኑም ቃል ኪዳናቸውን አፍርሰው ያገባሉ። ወይም ደግሞ ከአንዱ ቤት ወደ ሌላው ቤት እየዞሩ ሰው በማማትና ውጤታማ ተግባር ባለማከናወን ለስንፍና ይጋለጣሉ። ስለሆነም፥ ጳውሎስ ወጣት ሴቶች እንዲያገቡ፥ ልጆች እንዲወልዱና የቤት እመቤትነትን ተግባር እንዲወጡ አዝዟል።

ጳውሎስ ሚስቶቻቸው የሞቱባቸው ሰዎች ስለሚረዱበት መንገድ የሰጠው ማብራሪያ የለም። ስለሆነም እንደገና የማግባት ወይም በቤተሰቦቻቸው የመረዳት ግዴታ ይኖርባቸዋል ማለት ነው።

ከዚህ ትምህርት ውስጥ ቤተ ክርስቲያን ከማኅበረ ምእመናኑ መካከል ችግር ያለባቸውን ሰዎች የመርዳት ኃላፊነት እንዳለባት የሚያስገነዝብ መሠረታዊ አሳብ እንመለከታለን። ቤተ ክርስቲያን ድሆችን ማለትም ወላጅ የሌላቸውን ልጆች፥ መበለቶች፥ ሥራ የሌላቸውን፥ ወዘተ… የመርዳት ኃላፊነት የለብኝም ልትል አትችልም። እነዚህ መመሪያዎችና በ1ኛ ተሰሎንቄ ውስጥ የሚገኙ ሌሎች ምንባቦች እንደሚያሳዩት፥

ሀ) አንድ አማኝ በመጀመሪያ የራሱን ፍላጎቶች ለማሟላት መሻት አለበት። ለቤተ ክርስቲያን ሸክም ላለመሆን ሲሉ ከደረጃቸውም ዝቅ ብለው እንኳን የራሳቸውን ገቢ የሚያገኙበትን መንገድ መፈለግ ይኖርባቸዋል። ቤተ ክርስቲያን ሥራ የሚያገኙበትን መንገድ በመፈለግ ወይም ሥልጠና በመስጠት ድሆችን መርዳት ትችላለች። ነገር ግን ለመሥራት የማይፈልጉትን ድሆች ለረጅም ጊዜ ገንዘብ እየሰጠች ማኖር የለባትም። ብዙውን ጊዜ ለድሆች ገንዘብን መስጠቱ የጥገኝነትን መንፈስ ስለሚያበረታታ ጎጂ ነው። በመሆኑም ገንዘብ ከመስጠት ይልቅ የሥራ ዕድል መፍጠር ጠቃሚ ነው።

ለ) ዝምድና ያላቸው ሰዎች የተራራቀ ቢሆንም እንኳን የቤተ ክርስቲያንን እርዳታ ከመጠበቅ ይልቅ ለቤተሰባቸው አባላት እርዳታ ማድረግ ይኖርባቸዋል። ስለሆነም ዕጓለ ማውታዎችን፥ ድሆችን፥ መበለቶችን መርዳቱ በቀዳሚነት የዘመዶቻቸው ተግባር ይሆናል።

ሐ) ስለሆነም ቤተ ክርስቲያን ረዳት ለሌላቸው ቤተሰብ ትሆንላቸዋለች ማለት ነው። በቤተ ክርስቲያን ይህንኑ ተግባር የምታከናውንበት መንገድ ከባህል ባህል ይለያያል። በመሆኑም ዕጓለ ማውታዎችን በአማኝ ቤተሰቦች ውስጥ ማኖር፥ ለመበለቶች እርዳታ ማድረግና ሥራ ለሌላቸው ድሆች ጊዜያዊ መፍትሔዎችን መስጠት ቤተ ክርስቲያን ከምታከናውናቸው ተግባራት ጥቂቶቹ ሊሆኑ ይችላሉ። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚገኙ ቤተሰቦች ራስ ወዳድነትን በማስወገድ ለሥጋዊ ቤተሰቦቻቸው የሚያደርጉትን ያህል እንክብካቤ ለመንፈሳዊ ቤተሰቦቻቸውም ሊያደርጉ ይገባል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ቤተ ክርስቲያንህ የድሆችን፥ የዕጓለ ማውታዎችንና የመበለቶችን ፍላጎቶች ለማሟላት ምን እያደረገች ነው? ለ) ቤተ ክርስቲያንህ ይህንኑ ተግባር በአጥጋቢ ሁኔታ እንድትወጣ ክርስቶስ ወይም ጳውሎስን ምን ዓይነት ትእዛዛትን የሚሰጡ ይመስልሃል?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

መሪ ሐሰተኛ ትምህርቶችን ሊከላከልና የእምነትን እውነት ሊጠብቅ ይገባዋል (1ኛ ጢሞ. 4፡1-16)

ብዙውን ጊዜ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እንዴት መልካም መሪዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ይሠለጥናሉ። ስለ ጊዜ አጠቃቀም፥ ኃላፊነትንና ሥልጣንን ለሌሎች ስለ መወከል፥ መልካም አደረጃጀትና ስለ መመሥረት፡ ግልጽ የሥራ ድርሻን መግለጫ ስለማዘጋጀትና ስለ ሌሎችም ተመሳሳይ ጉዳዮች ይማራሉ። እነዚህ ሁሉ የሥልጠና ሀሳቦች ጥሩዎች ናቸው። ይሁንና የትኞቹም የአመራርን ችግር ሊቀርፉ አይችሉም። መጽሐፍ ቅዱስ የአመራር መሠረቱ የሰው ልብ እንደሆነ ይናገራል። አንድ ሰው ጥሩ ልብ እስከሌለው ድረስ ምንም ያህል የአመራርና የአስተዳደር ችሎታ ቢኖረው፥ ፍጻሜው የእግዚአብሔርን ቤት ማፍረስ እንጂ መገንባት ሊሆን አይችልም። ነገር ግን ልቡ ከእግዚአብሔር ጋር ከተቃኘና እግዚአብሔርን የሚታዘዝ ሕይወት ካለው፥ ለውጤታማ አስተዳደር የሚያስፈልጉ ብቃቶች ሁሉ ባይኖሩትም እንኳን እግዚአብሔር ይህን ሰው ይጠቀምበታል። መጽሐፍ ቅዱስ በቀዳሚነት ልባችንና ባሕሪያችን ከእግዚአብሔር ጋር መስማማት እንዳለበት ያስተምረናል። ከዚያ በኋላ የአመራርን ችሎታ ልንማር እንችላለን። ወይም መልካም መሪዎችና ቤተ ክርስቲያንን የምንገነባ መሪዎች እንድንሆን ያስችለናል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ስጦታ ኖሯቸው መንፈሳዊነት የጎደላቸው ሰዎች ቤተ ክርስቲያንን ሲጎዱ የተመለከትክበትን ሁኔታ ግለጽ። ለ) ብዙም የመሪነት ስጦታ የሌለውና ለእግዚአብሔር በመገዛቱ ምክንያት ቤተ ክርስቲያንና ለመገንባት በመሣሪያነት ያገለገለ መሪ አጋጥሞህ ያውቃል? ሁኔታውን ግለጽ። ሐ) መጽሐፍ ቅዱስ የጊዜ አጠቃቀም፥ ኃላፊነትና ሥልጣንን መወከል፥ ወዘተ… ካሉት የአመራር ጉዳዮች በላይ በመንፈሳዊነት፥ ከቅድስና፥ በትሕትና፥ ራስን በመቆጣጠርና እነዚህን በመሳሰሉት ባሕርያት ላይ ትኩረት የሚያደርገው ለምን ይመስልሃል?

ሐዋርያው ጳውሎስ ጢሞቴዎስ በኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መንፈሳዊ መሪዎችን ስለሚመርጥበት ሁኔታ ምክር እየሰጠው ነበር። ጳውሎስ እንደ የቤተ ክርስቲያን መሪ ሊያከናውናቸው የሚገባውን የሥራ ዝርዝሮች አላሰፈረም። ነገር ግን መሪነት ከልብ እንደሚመነጭ መሪዎችን በመምረጡ ረገድ እጅግ አስፈላጊው ነገር ልባቸውና ባሕሪያቸው ትክክል መሆኑን ማረጋገጥ መሆኑን ያስረዳል። መሪዎች መንፈሳዊነትን የተላበሱ፥ በእምነታቸው የበሰሉ፥ የተቀደሱና ከሌሎች ሰዎች ጋር አብረው እንዲሠሩ የሚያስችል ባህሪ ያላቸው ሊሆኑ ይገባል። ነገር ግን ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔርን የምታስከብር ተቋም ትሆን ዘንድ መሪዎች ሊኖሩዋቸው የሚገቧቸውን የተለያዩ ነገሮች ዘርዝሯል። ጳውሎስ ጢሞቴዎስ የመሪነትን ባህሪ ስለሚያንጸባርቅበት ሁኔታ ሲያስተምር፥ እግዚአብሔር ከሌሎች መሪዎች ምን እንደሚጠብቅ እግረ መንገዱን ማስተማሩ ነበር። ጳውሎስ ካነሣቸው ነጥቦች መካከል የሚከተሉት ይገኙባቸዋል።

ከኋለኛው ዘመን ባሕርያት እንዱ የሐሰት አስተማሪዎች መብዛት እንደሚሆንና ይህም ብዙ አማኞች እምነታቸውን እንዲተዉ የሚያደርግ መሆኑን መንፈስ ቅዱስ ለጳውሎስ ገልጾለት ነበር። በአዲስ ኪዳን ውስጥ፥ የኋለኛው ዘመን የሚለው ሐረግ ከክርስቶስ የመጀመሪያው መምጣት ጀምሮ ዳግም እስከሚመለስበት ጊዜ ድረስ ያለውን ያጠቃልላል። ስለሆነም ጳውሎስም ሆነ እኛ በዚሁ የኋለኛ ዘመን ውስጥ እንኖራለን።

ከመጀመሪያው ጀምሮ የቤተ ክርስቲያን ራስ ምታት ከሆኑት ነገሮች መካከል በዋናነት የሐሰት ትምህርት ይጠቀሳል። ጳውሎስ መልካምና መንፈሳዊ መስለው ከሚቀርቡት ከእነዚህ የሐሰት ትምህርቶች በስተጀርባ አሳሳች መናፍስቶችና የአጋንንት ትምህርቶች መኖራችውን ገልፆአል። በእያንዳንዱ ትውልድ ውስጥ ሰይጣን እውነትን የሚያዛቡትን አስመሳይ ክርስቲያኖች ይጠቀማል። ጳውሎስ እነዚህ የሐሰት አስተማሪዎች መንፈሳዊያን መስለው ቢቀርቡም፥ ሕሊናቸው እንደጠፋና የሰይጣንን ውሸቶች እንደሚያሰራጩ አስረድቷል። ስለሆነም ጳውሎስ ጢሞቴዎስና በየትውልዱ የሚገኙ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እውነትን ለይተው በማወቅ የሐሰት ትምህርቶችን እንዲከላከሉ ያስጠነቅቃቸዋል።

በጳውሎስ ዘመን፥ በስፋት የሚታየው ዋንኛው የሐሰት ትምህርት ሰዎች ድነትን (ደኅንነት) ለማግኘት ወይም ለበለጠ መንፈሳዊነትን ለመላበስ የተወሰኑ ሕግጋትን መጠበቅ እንዳለባቸው የሚያስተምር ነበር። እነዚህ ሕግጋት ብሉይ ኪዳንንና ሌሎችም ሕጎችን ከሚያስተምሩ አይሁዶች ወይም ከሌሎች አስተማሪዎች መምጣታቸው አልተገለጸም። ምናልባትም እነዚህ ትምህርቶች በዓለም ውስጥ የሚገኙ ነገሮች ክፉዎች እንደሆኑ በማስተማር ሰዎች ሥጋቸውን በመጨቆን የተወሰኑ ምግቦችን እንዳይመገቡ፥ ብዙም ቁሳዊ ምቾቶችን እንዳይጠቀሙ፥ እንዳይጋቡ፥ ወዘተ.. ከሚከለክሉ አሕዛብ የመጡ ሊሆኑ ይችላሉ። ሰይጣን እነዚህን የሐሰት አስተማሪዎች በመጠቀም፥ ሰዎች እውነተኛ መንፈሳዊነትን በማያስገኙ ነገሮች ላይ እንዲያተኩሩ ያደርግ ነበር። ሰዎች በፍቅር፥ ቅድስና፥ ትሕትናን፥ ታዛዥነት፥ ወዘተ… ላይ እንዲያተኩሩ ከማድረግ ይልቅ፥ እነዚህ የሐሰት አስተማሪዎች በውጫዊ ሕግጋት ላይ ያተኩሩ ነበር። ከእነዚህ ሕግጋት መካከል አንዳንዶቹ በእግዚአብሔር የተፈቀዱ ቢሆኑም እውነተኛ መንፈሳዊነትን የማያንጸባርቁ ነበሩ። ለምሳሌ፥ ያህል፥ ወሲብን መፈጸም ትክክል እንዳልሆነና ለክርስቶስ ሳያገቡ መኖር እንደሚሻል በማሰብ፥ መጋባት ተገቢ አይደለም ብለው ያስተምሩ ነበር። ሰዎች እንደ ሥጋ ያሉትን የተወሰኑ ምግቦች እንዳይመገቡ ይከላከሉ ነበር። ምናልባት እነዚህ ሰዎች የከለከሉት ብሉይ ኪዳን ሰዎች እንዳይመገቡ የከለከለውን ሥጋ ሳይሆን አይቀርም። ጳውሎስ ግን እግዚአብሔር አንዳንድ ልምምድ እስካልከለከለ ድረስ፥ በትክክለኛ አነሣሽ ምክንያት፥ እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ይህንኑ ልምምድ ማከናወን እንደሚቻል ገልጾአል። የእነዚህ ሰዎች ትምህርት በእግዚአብሔር ጸጋ፥ ክርስቲያን ለእግዚአብሔር ባለው ፍቅር፥ እንዲሁም በመንፈሳዊ ባሕርይ ላይ አያተኩርም ነበር። ይህ ዛሬ ብዙ ሰዎች ለእግዚአብሔርና ለሰዎች ከሚኖረን ፍቅር ይልቅ ስላላመጠጣን ወይም ስላለመደነስ አጽንኦት ሰጥተው ከሚያስተምሩበት ሁኔታ ጋር ተመሳሳይ ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በአዲስ ኪዳን ውስጥ በግልጽ ያልተከለከሉና ኢትዮጵያውያን የማያደርጓቸው ነገሮች ወይም የማይመገቧቸው ምግቦች ምን ምንድን ናቸው? ለ) እነዚህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ ነገሮች በመንፈሳዊነት ላይ የሚያስከትሉት ተጽዕኖ ምንድን ነው? ሐ) በእነዚህ ውጫዊ ነገሮች ላይ ትኩረት መስጠቱ እግዚአብሔርና ሰዎችን እንደ ማፍቀር ካሉት እጅግ ጠቃሚ ነገሮች የሚያርቀን እንዴት ነው? መ) ብዙ ሰዎች በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ከልባቸው ይልቅ በውጫዊ ነገሮች ላይ ስለሚያተኩሩባቸው ሁኔታዎች ግለጽ።

አንድ መሪ እነዚህን የሐሰት ትምህርቶች በሚመለከትበት ጊዜ ያለው ኃላፊነት ምንድን ነው? ጳውሎስ መሪዎች ሊያደርጓቸው ይገባል የሚላቸውን አያሌ ነጥቦች ዘርዝሯል።

ሀ) መሪዎች ሐሰተኛ የሆነውን ነገር በሚሰሙበት ጊዜ ለይተው ለማወቅ ይችሉ ዘንድ እውነትን ማወቅ አለባቸው፡፡ ከዚያ በኋላ ለምእመኖቻቸው በመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ መሠረት የተሳሳተው ነገር ምን እንደሆነ ሊያብራሩ ይችላሉ። ከቤተ ክርስቲያን መሪዎች ዐበይት ተግባራት መካከል አንዱ የወንጌሉን እውነት መጠበቅ ነው። መሪዎች ቤተ ክርስቲያንን ከሐሰት ትምህርቶች መከላከል አለባቸው። ይህንንም ማድረግ የሚቻልበት ብቸኛው መንገድ እውነትን በማወቅ ነው። እግዚአብሔር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያስተማረውን እውነት ካላወቅንና ስሕተት የሆነውን ነገር ለይቶ ከሚያሳየን መንፈስ ቅዱስ ጋር በቅርብ ተጣምረን ካልተመላለስን፥ እውነትን ልንጠብቅ አንችልም። ከዚህም የተነሣ ብዙውን ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የተቀላቀለበትን የሰይጣንን ውሸት እናምናለን።

የቤተ ክርስቲያን መሪዎች አንድን አዲስ ትምህርት በሚሰሙበት ጊዜ ሊያደርጓቸው የሚገቧቸው ሦስት አማራጮች አሉ። በመጀመሪያ፥ ከዚህ በፊት ሰምተው የማያውቁት በመሆኑ ምክንያት ሊቃወሙት ይችላሉ። ብዙ መሪዎች በባህላዊ ግንዛቤያቸው ላይ በመንተራስ አዲስ የሆነውን ሁሉ ይቃወማሉ። ይህ ቤተ ክርስቲያኒቱን ከሐሰተኛ ትምህርት ቢከላከልም፥ መንፈስ ቅዱስ ወደ ቤተ ክርስቲያኒቱ ለማምጣት የሚፈልገውን አዲስ እውነትም የሚከላከል በመሆኑ ተመራጭነት አይኖረውም። ይህም አባሎቻቸው መጽሐፍ ቅዱስ በሚያስተምረው እውነት ሥር ነፃ ሆነው እንዳይመላለሱና ሰው ሠራሽ ሕግጋትን እንዲከተሉ ያደርጋል። ሁለተኛ፥ የመጣውን አዲስ ትምህርትም የሚቀበሉ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችም አሉ። አዲስና ሰዎችን የሚያስደስት እስከሆነ ድረስ፥ ትክክል መሆን አለበት ብለው ያስባሉ። ከዚህም የተነሣ፥ ብዙ የሐሰት ትምህርቶች ወደ እነዚሁ አብያተ ክርስቲያናት እየጎረፉ በመምጣት ሰዎችን ከእውነት ያስታሉ። ሦስተኛ፥ ብቸኛው መጽሐፍ ቅዱሳዊ አማራጭ ያቀረበውን ትምህርት በመጽሐፍ ቅዱስ እውነት መገምገም ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቱን የሚደግፍ ከሆነ፥ በአዲስ መንገድ ቢቀርብም እንኳን ልንቀበለው ይገባል። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ ከሚደግፈው ውጪ ከሆነ፥ መቀበል የለብንም። ሰዎች ሐሰተኛ ትምህርት እንዳይቀበሉ መናገር ብቻ ሳይሆን መቀበል የለባቸውም የምንልባቸውን ምክንያቶችም ማብራራት አለብን። ይህም ማለት የሐሰት ትምህርቶችን ነቅለን ለማውጣትና እግዚአብሔር የሰጠንን መንጋ ለመጠበቅ እንድንችል በማይለወጠው የእግዚአብሔር ቃል እያደግን መሄድ አለብን ማለት ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- በቅርቡ ወደ ቤተ ክርስቲያንህ የመጣ አዲስ ትምህርት ምንድን ነው? ሀ) ይህ ትምህርት ከላይ በቀረቡ ሦስት መንገዶች ሊስተናገድ የሚችልበትን ሁኔታ ግለጽ። ለ) የቤተ ክርስቲያንህ መሪዎች አዳዲስ ትምህርቶችን ወይም የአምልኮ ልምምዶችን ስለሚያስተናግዱበት ሁኔታ ምን ትመክራቸዋለህ?

ለ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ጎጂ የሆነውንና ሊወገድ የሚገባውን፥ እንዲሁም ጉዳት የሚያስከትለውንና ጠቃሚ ያልሆነውን ትምህርት ለይተው ማውጣት ይኖርባቸዋል። ጳውሎስ ጢሞቴዎስ ዘላለማዊ ምልከታዎች የሌሏቸውን ትምህርቶች ከመከታተል እንዲቆጠብ ይመክረዋል። እነዚህ ትምህርቶች የሰው ልጅ እእምሮ የፈጠራቸው ከንቱ አሳቦች ብቻ ናቸው። ጳውሎስ እነዚህን ተረትና መጨረሻ የሌለው የትውልድ ታሪክ ሲል ይጠራል።

ሐ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ደክመው በኃጢአት እንዳይወድቁ ባለማቋረጥ መንፈሳዊ ሕይወታቸውን ማጠናከር ይኖርባቸዋል። ጳውሎስ ይህንን እውነት በስፖርታዊ ምሳሌ ያብራራዋል። እንድ ሰው የሩጫ ውድድር ከማካሄዱ በፊት፥ ሰውነቱን ለማጠናከር ብርቱ ልምምድ ማድረግ ይኖርበታል። የማሸነፍ ዕድል የሚኖረው ከዚህ በኋላ ብቻ ይሆናል። ሰውነትን ለመቆጣጠር መማሩ አስፈላጊ ይሆናል። ይህ ግን እንደ መንፈሳዊነት፥ ጸሎት፥ ጾም፥ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን በቃል ማጥናት፥ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፥ ምስክርነት የሚሰጡትን ያህል መንፈሳዊ በረከት የሚያስገኝ አይደለም። እነዚህ ነገሮች አንድ መንፈሳዊ መሪ በሕይወቱ እንዲጠናከርና ውጤታማ እንዲሆን በማድረግ በሐሰተኛ ትምህርት እንዳይታለል ይረዱታል። በመሆኑም በከርስቶስ የፍርድ ወንበር በሚቀርብበት ጊዜ መሪው ለኀፍረት አይዳረግም። ብዙውን ጊዜ አንድ መሪ ለሐሰት ትምህርት፥ የወሲብ ኃጢአት፥ ወይም ለሌላ ኃጢአት የሚሸነፈው ከመንፈሳዊ ልምምዶች በሚርቅበት ጊዜ ነው።

መ) አንድ መሪ በቃሉ ብቻ ሳይሆን በምሳሌነቱ ጭምር መምራት አለበት። ጳውሎስ ጢሞቴዎስ በንግግር፥ በሕይወት፥ በፍቅር፥ በእምነትና በንጽህና ለምእመናን ምሳሌ እንዲሆንላቸው አሳስቦታል። ብዙውን ጊዜ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች የሚያስተምሩትን ሕይወት አይኖሩም። ምእመናን የጸሎት ሰዎች እንዲሆኑ እያስተማሩ፥ እነርሱ ራሳቸው ብዙም አይጸልዩም። ምእመናን ለእግዚአብሔር አሥራት እንዲሰጡ እያስተማሩ፥ ራሳቸው ግን አሥራት አይከፍሉም። የአንድ መሪ ትልቁ ስብከት የሚናገረው ሳይሆን በሕይወቱ ኖሮ የሚያሳየው ነው። ብዙ ሰዎች የመሪን ምሳሌነት ይከተላሉ። እርሱ በቅድስና የሚመላለስ ከሆነ እነርሱም በቅድስና ይመላለሳሉ። መሪው ለመንፈሳዊ ሕይወቱ ግድ የለሽ ከሆነ፥ እነርሱም ለከርስቶስ የቆራጥነት ሕይወት አይኖሩም።

ሠ) የቤተ ክርስቲያን መሪ በእግዚአብሔር ቃል ላይ እንጂ በራሱ ሐሳብ ላይ ትኩረት መስጠት የለበትም። ጳውሎስ ጢሞቴዎስ ቅዱሳት መጻሕፍትን በማንበብ፥ በመስበክና በማስተማር እንዲተጋ መክሮታል። ብዙውን ጊዜ መሪዎች የገዛ ሐሳባቸውን ይሰብካሉ። ከመድረክ የሚሰበከው ቃል ደግሞ ተያያዥነት የለውም። የተለያዩ መሪዎች በሚወዷቸው ርእሰ ጉዳዮች ላይ ይሰብካሉ። በየሰንበቱ የሚጋበዙ አገልጋዮች ተመሳሳይ እውነቶችን ይናገራሉ። ከዚህም የተነሣ ምእመናን ስለ እግዚአብሔር ቃል የሚኖራቸው ዕውቀት የተወሰነ ይሆናል። ይህንን ለማስወገድ፥ ጳውሎስ ጢሞቴዎስ መጽሐፍ ቅዱስን ባለማቋረጥ እንዲያጠናና ይሄኑ ለምእመናን እንዲያስተምር ነግሮታል። የእግዚአብሔርን ቃል ሙሉ በሙሉ ካላወቅን የሐሰተኛ ሐሳቦችን ለማሸነፍና እግዚአብሔር የሚፈልግብንን ዓይነት ክርስቲያኖች ለመሆን አንችልም። የእግዚአብሔር ቃል በሙላት የምናውቀው ደግሞ መሪዎች በጥንቃቄ ተዘጋጅተው የእግዚአብሔርን ቃል ከዳር እስከ ዳር ሲያስተምሩን ነው።

ረ) መሪዎች የገዛ የራሳቸውን ሕይወት በጥንቃቄ መጠበቅ አለባቸው። ሰይጣን አንድን መሪ በሐሰተኛ ትምህርት ወይም በወሲብ ኃጢአት ለመጣል ከቻለ፥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ብዙ ችግሮችን ሊፈጥር እንደሚችል ያውቃል። ስለሆነም መሪዎች ከምእመናን የበለጠ የሰይጣን ፈተናዎችና ጥቃቶች ዒላማዎች ናቸው። በመሆኑም መሪዎች በኃጢአት እንዳይወድቁና ለክርስቶስ ለመኖር መልካም ምሳሌዎች ይሆኑ ዘንድ ሕይወታቸውን በጥንቃቄ መጠበቅ ይኖርባቸዋል። በዚህም ጊዜ የራሳቸውን ሕይወት መጠበቅ ብቻ ሳይሆን፥ የቤተ ክርስቲያናቸው ምእመናን እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ እንዲኖሩ ይረዷቸዋል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ጳውሎስ ከሰጣቸው ምክሮች መካከል በተለይ ለቤተ ክርስቲያን መሪዎች አስፈላጊ የሆኑት የትኞቹ ናቸው? ለ) ለማሸነፍ ከባድ የሆኑብህ የትኞቹ ነጥቦች ናቸው? ሐ) መሪዎቻችን የጳውሎስን ትምህርቶች ተቀብለው ቢለወጡ በአብያተ ክርስቲያኖቻችን ውስጥ ምን ዓይነት ለውጥ ይከሰታል?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የቤተ ክርስቲያን መሪ ቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎችና ዲያቆናትን በጥንቃቄ እንደሚመርጡ ሊረዳቸው ይገባል (1ኛ ጢሞ. 3፡1-16)

የአንድ መሪ መንፈሳዊ ሕይወት ለቤተ ክርስቲያን በጣም አስፈላጊ መሆኑን ቀደም ብለን ተመልከተናል። ትክክለኛ ያልሆኑ መሪዎች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሥልጣን መያዛቸው ወይም አንድ መሪ በኃጢአት መውደቁ፥ ቤተ ክርስቲያንንና ምስክርነቷን እጅግ ይጎዳል። ስለሆነም ጳውሎስ በ1ኛ ጢሞቴዎስ ውስጥ ስለ መሪዎችና የብቃት መመዘኛዎቻቸው በሰፊው ጽፎአል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በአንድ ወረቀት ላይ ሦስት አምዶችን አዘጋጅ። የመጀመሪያውን አምድ ‹ሽማግሌዎችን፥ ሁለተኛውን ‹ዲያቆናትን፥ ሦስተኛውን ‹ቤተ ክርስቲያናችን› ብለህ ሰይም። በእነዚሁ አምዶች ውስጥ በ1ኛ ጢሞቴዎስ 3 እና ቲቶ 1 ለሽማግሌዎችና ዲያቆናት የተሰጡትን የብቃት መለኪያዎች ዘርዝር። የመጨረሻው እምድ የምትሞላውን አሳብ ለማግኘት በቅርቡ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሽማግሌዎች የተመረጡበትን ሁኔታ አስብ። እነዚህ መሪዎች የተመረጡበት ምክንያት ምን እንደሆነ የምታስበውን በዚህ አምድ ውስጥ አስፍር። ለ) ጳውሎስ በዘረዘራቸው የብቃት መመዘኛዎች መካከል የምትመለከታቸው አንድነቶችና ልዩነቶች ምን ምንድን ናቸው?

በአዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሁለት ዓይነት ዐበይት የመሪነት ዓይነቶች ነበሩ። ከእነዚህም መካከል የመጀመሪያዎቹ በቀዳሚነት የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሲሆኑ፥ ሽማግሌዎች (የሐዋ. 20፡17) መጋቢዎች ወይም ኤጲስ ቆጶሳት (1ኛ ጢሞ. 3፡1) ወይም እረኞች (1ኛ ጴጥ. 5፡1-4) ተብለው ይጠራሉ። በአዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስንት ሽማግሌዎች በአንድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንደሚያገለግሉ ወይም እንዴት እንደሚመረጡ አልተጠቀሰም። አገልግሎቱ የሕይወት ዘመን ወይም በተወሰነ ጊዜ ውስጥ የሚቀያየሩበት መሆኑም አልተጠቀሰም። ጳጳስ ወይም ኤጲስ ቆጶስ የሚለው ቃል ከግሪክ ቋንቋ የተገኘ ሲሆን፥ የአንድ ቤተ ክርስቲያን ወይም የመንግሥታዊ ድርጅት መሪ የሆነን ሰው ያመለክታል። ይህም ፕሬዚዳንት ወይም ዋና ጸሐፊ ከሚለው የዘመናችን አገላለጽ ጋር ተቀራራቢ ነው። ሽማግሌ የሚለው ቃል ከአይሁዳውያን ባህል የተወሰደ ሲሆን፥ የማኅበረሰብ ወይም እንደ ምኩራብ ያለ ድርጅት መሪዎችን ያመለክታል (የሐዋ. 20፡17፤ 28፤ ቲቶ 1፡5-7፤ 1ኛ ጴጥ. 5፡1-2) ሽማግሌዎች፥ ዲያቆናትና እረኞች የሚሉ ቃላት ተመሳሳይነታቸውን በሚያመለክት ሁኔታ ቦታ ተቀያይረው ማገልገላቸውን ያሳያሉ።) ሽማግሌዎች ቤተ ክርስቲያኒቱን በማስተዳደር አጠቃላይ ተግባር ላይ ላቅ ያለ ኃላፊነት ነበራቸው። በመሆኑም የጸሎትና የትምህርት መንፈሳዊ አገልግሎቶችን፥ ብሎም ለምእመናን የመጋቢነት አገልግሎት በመስጠቱ ተግባራት ላይ ያተኩራሉ።

ሁለተኛው የመሪዎች ዓይነት ‘ዲያቆናት’ በመባል ይታወቅ ነበር። ዲያቆን የሚለው ቃል ከግሪክ ቋንቋ የተወሰደ ሲሆን፥ አገልጋይ ወይም አስተናጋጅ የሚል ፍቺ ይሰጣል። ይህ የአገልግሎት ዘርፍ መጀመሪያ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተመሠረተው በሐዋርያት ሥራ 6፡1-6 በቀድሞይቱ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ዲያቆናት ሐዋርያትን ለማገልገል በተመረጡበት ወቅት ነበር። ዲያቆናት በሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ መመረጥ እለመመረጣቸውን ባናውቅም፥ ቤተ ክርስቲያን የተወሰነ ዕድገት በምታሳይበት ጊዜ ዲያቆናት ሽማግሌዎችን ለማገዝ ይመረጡ የነበረ ይመስላል። ሽማግሌዎች መንፈሳዊ አገልግሎቶችን ሲወጡ፥ ዲያቆናት ደግሞ ድሆችን እንደ መንከባከብ ያሉትን ተግባራዊ አገልግሎቶች ያከናውኑ ነበር።

ብዙ ሰዎች በመሪነት ለማገልገል አይፈልጉም። ምንም ዓይነት ኃላፊነት ሳይሸከሙ ተራ የቤተ ክርስቲያን አባል ሆነው ማምለኩ ቀላል መስሎ ይታያቸዋል። የቤተ ክርስቲያን መሪነት ትንሽ ደመወዝ እያገኙ ብዙ ጊዜ ማጥፋትንና ለልብ ስብራት መዳረግን የሚያካትት ተግባር ነው። መሪዎች ለመሆን የሚፈልጉ ሰዎች ደግሞ ይህን ስፍራ የሚፈልጉት ትክክለኛ ላልሆኑ ምክንያቶች ነው። ጥሩ ደመወዝ የሚያገኙበት ከሆነ ብሩን ወይም ደግሞ ከመሪነት የሚመጣውን ክብር ይፈልጋሉ። ጳውሎስ ግን የመሪነት ጥሪ ወይም ፍላጎት በአንድ ሰው ልብ ውስጥ ማደሩ መልካም እንደሆነ ይናገራል። በተለይም ደግሞ ግለሰቡ ይህ አገልግሎት በእርሱና በቤተሰቡ ላይ የሚያስከትለውን ችግር የሚገነዘብ ከሆነ ለመሪነት አገልግሎት መጠራቱ ነው። የቤተ ክርስቲያን መሪ መሆን በእግዚአብሔር ዓይኖች ፊት ክቡር ተግባር ነው። እግዚአብሔር በስጦታዎች ያበለጸገውና የጠራው ሰው በአመራር አላገለግልም ማለቱ ተገቢ አይሆንም።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) አንድ ሰው በመሪነት አገልግሎት ላይ ለመሠማራት የሚፈልግባቸው የተሳሳቱ ምክንያቶች ምንድን ናቸው? ለ) አንድ ሰው መሪነትን ሊፈልግ የሚገባቸው ትክክለኛ ምከንያቶች ምን ምንድን ናቸው? ሐ) ብዙ ክርስቲያኖች በመሪነት ለማገልገል የማይፈልጉበት ምክንያቶች ምን ምንድን ናቸው?

ለሽምግልና ወይም ለድቁና አገልግሎት የሚያስፈልጉትን የብቃት መመዘኛዎች ጠለቅ ብለን ስንመረምር የሚከተሉትን እውነቶች እንመለከታለን።

 1. ለሽምግልናና ለድቁና የሚያስፈልጉ አብዛኞቹ መመዘኛዎች ተመሳሳይ ናቸው። ከዋነኛ ልዩነቶች አንዱ ሽማግሌ የማስተማርና መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነትን ለማኅበረ ምእመናን የማስተላለፍ ችሎታ ሊኖረው የሚገባ መሆኑ ነው።
 2. አብዛኞቹ የመሪነት ብቃቶች ከባህሪ ጋር የተያያዙ ናቸው። ጳውሎስ በመሪነት የሚያገለግሉ ሰዎች እንደ ራስን መግዛት፥ የዋህነት፥ ቅድስና፥ ከነቀፋ ነፃ መሆንና የመሳሰሉትን ውስጣዊ ብቃቶች ሊያሟሉ እንደሚገባ ያስተምራል። ይህ ዛሬ ትኩረት ከምንሰጥባቸው እንደ ትምህርት፥ ሀብት፥ ጥሩ ሥራ፥ ከጥሩ ጎሳ መወለድ፥ እና ከመሳሰሉት ውጫዊ ብቃቶች የተለየ ነው።
 3. ሌላው ብዙ ጊዜ ተደጋግሞ የሚጠቀሰው ከሌሎች ሰዎች ጋር የሚደረገውን ግንኙነት የሚመለከት ነው። አንድ መሪ እንግዳ ተቀባይ፥ በውጪ ባሉት ዘንድ መልካም ስም ያለው፥ የአንዲት ሚስት ባልና ቤተሰቡን በአግባቡ የሚያስተዳድር መሆን ይኖርበታል። በዚህ ክፍል ውስጥ የተጠቀሱት አብዛኞቹ ባህሪዎች አንድ ሰው ከሌሎች ጋር መልካም ግንኙነት ማድረግ መቻሉን የሚያመለክቱ ናቸው።
 4. ከመሪ የሚጠበቀው ዋናው ብቃት ለማስተማር መቻሉ ነው።
 5. ዋንኛው የአመራር ብቃት መለኪያ አንድ ሰው የራሱን ቤተሰብ ማስተዳደር መቻሉ ነው።
 6. የመሪዎች ሚስቶች ባህሪም እንዲሁ አስፈላጊ መሆኑ ተጠቅሷል። የመሪዎች ሚስቶች የተከበሩ፥ አንደበታቸውን የሚገዙና ከሀሜት የሚርቁ፥ እንዲሁም በሁሉም ነገር እምነት የሚጣልባቸው መሆን አለባቸው።

የውይይት ጥያቄ፡- እነዚህን ባሕርያት ከልስ። ሀ) እያንዳንዱ ባሕሪ ለአንድ መሪ አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው? ለ) አንድ መሪ ከእነዚህ ባሕርያት አንዱን በሚያጣበት ጊዜ ምን ይከሰታል? ሐ) ከእነዚህ ባሕርያት የሚጎድልህ የትኛው ነው? ለመሪነት ብቁ ትሆን ዘንድ ይህንኑ ባሕሪ ለማሳደግ ምን ማድረግ ይኖርብሃል።

(ማስታወሻ፥ ምንም እንኳ ጳውሎስ በዚህ ስፍራ ትኩረት የሰጠው ለመሪዎች ቢሆንም፥ እነዚህ ባሕርያት ለክርስቲያኖች ሁሉ አስፈላጊ መሆናቸውን ከሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች እንመለከታለን። እነዚህ ባሕርያት የመንፈሳዊ ሰው መገለጫዎች ናቸው። ጳውሎስ እየተናገረ ያለው ሁሉም የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እነዚህን ባሕርያት በመያዝ መንፈሳዊ ሞዴሎች እንዲሆኑና ክርስቲያኖችም ይህንኑ ሕይወት ለመኖር መጣር እንደሚገባቸው ነው።)

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የቤተ ክርስቲያን መሪ፣ ሴቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ምሳሌያዊ ሕይወት እንዲኖሩ መርዳት አለበት (1ኛ ጢሞ. 2፡9-15)

ክርስቶስን መከተል ጸሎታችንን ብቻ ሳይሆን የዕለት ዕለት አኗኗራችንንም ጭምር ይቀይራል። ከእነዚህም መካከል አለባበሳችንና አኳኋናችን ሁለቱ ናቸው። እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባቦች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ብዙ ክርክር አስነሥተዋል። አንዳንድ አማኞች ጳውሎስ ይህንን ምንባብ የጻፈው በመጀመሪያው ምእተ ዓመት ውስጥ ከነበረችው ቤተ ክርስቲያን አማኞች የተወሰኑት ችግሮች እንደሆነና በተለይም በሴቶች አገልግሎት ላይ የተጣለው እገዳ ከዘመናችን ጋር ቀጥተኛ ተዛማጅነት እንደማይኖረው ይናገራሉ። ሌሎች አማኞች ደግሞ እነዚህ የሴቶችን ሚና የሚመለከቱ ምንባቦች በሁሉም ዘመን በሚኖሩ ክርስቲያኖች ሴቶች ላይ ተፈጻሚነት እንደሚኖራቸው ይናገራሉ። እውነቱ እንግዲህ በእነዚህ ሁለት አክራሪ ጫፎች መካከል እንደሚገኝ ግልጽ ነው።

ይህንን ምንባብ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ካሉት ሌሎች ምንባቦች ጋር አዛምዶ መመልከቱ ጠቃሚ ነው። ለምሳሌ ያህል ጳውሎስ በሌላ ስፍራ ሴቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሊጸልዩና ትንቢት ሊናገሩ እንደሚችሉ ይናገራል (1ኛ ቆሮ. 15)፡፡ ስለሆነም ጳውሎስ ሴቶች ሙሉ በሙሉ ዝም እንዲሉና በክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የፍጹም ተገዢነት ስፍራ እንዲኖራቸው እየተናገረ አለመሆኑ ግልጽ ነው። እንዲያውም ጳውሎስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሴቶችና ወንዶች እኩል መሆናቸውን ያስተምራል (ገላ. 3፡28)፡፡ ስለሆነም እነዚህን ጥቅሶች ብቻ በመውሰድ ሴቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዳያገለግሉ መከላከሉ ተገቢ አይሆንም። በሌላ በኩል፥ ጳውሎስ አዳምንና ሄዋንን የክርክሩ መነሻ መሠረት ማድረጉ እነዚህ እገዳዎች (ወይም የቀረቡት መርሆች) ዓለማቀፋዊና ለሁሉም ዘመን የሚያገለግሉ እንጂ ለጳውሎስ ዘመን ብቻ የታሰቡ እንዳልሆኑ የሚያመለክት ይመስላል።

ጳውሎስ እነዚህን ትእዛዛት የሰጠው ለምን እንደሆነ ማወቁ ይህንን ምንባብ በሚገባ እንድንረዳ ያግዘናል። እነዚህን ትእዛዛት ለመረዳት በኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተከሰቱትን ችግሮች ማወቁ ጠቃሚ ቢሆንም፥ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ግን ሰፍሮ አንመለከትም። በጳውሎስ ዘመን ሴቶች ምንም ዓይነት መብት አልነበራቸውም። በአመዛኙ የወንዶች ንብረት ተደርገው ይወሰዱ ነበር። አይሁዶች በፈለጉት ጊዜ ሚስቶቻቸውን መፍታት ይችሉ ነበር። አንዳንድ አሕዛብ ሴቶች ቤት ውስጥ እንዲቀመጡና ወደ ውጭ ከወጡም ሁልጊዜም ፊታቸውን እንዲሸፍኑ ያስገድዱ ነበር። በእንዲህ ዓይነቱ ጨቋኝ ማኅበረሰብ ውስጥ ወንጌሉ ሴቶች ከወንዶች ጋር እኩል መሆናቸውን ያስተምር ጀመር። በክርስቶስ አካል ውስጥ ማንም ከማንም አይበልጥም። ምክንያቱ በወንዶችና በሴቶች መካከል ልዩነት የለምና (ገላ. 3፡28)። ሴቶች በክርስቶስ ባመኑ ጊዜ ባገኙት በዚሁ አዲስ ነጻነት ደስ ይሰኙ ጀመር። ይህ ደግሞ ሴቶች አንዳንድ አምልኮን የሚረብሹና የክርስቶስን ስም የሚያሰድቡ አለአግባብ ልምምዶችን እንዲያካሂዱ አደረጋቸው። ይህም ለወንጌሉ እንቅፋት ሆነ። በመሆኑም ጳውሎስ በአያሌ መልእክቶች ውስጥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሴቶች አገልግሎት ምን መሆን እንዳለበት ግልጽ አድርጎ ያስቀምጣል። ምንባቡን ለመተርጎምና ለማዛመድ አስቸጋሪ ያደረገው በጳውሎስ ጽሑፍ ውስጥ ምን ያህሉ በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ የሚያመለክት እንደነበር ለመለየት አለመቻሉ ነው። በመሆኑም በዘመናት ሁሉ የሚሆነውና ለሁሉም ባህሎች የሚዛመደው ምን ያህሉ እንደሆነ ለማወቅ ያስቸግራል። በ1ኛ ጢሞቴዎስ ውስጥ ጳውሎስ ዛሬ ከሕይወታችን ጋር ልናዛምዳቸው የሚገቡትን አያሌ ጠቃሚ እውነቶች አስተምሯል፡

ሀ) ሴቶች በውጫዊ ውበታቸው ወይም በወንዶች ዘንድ ማራኪነታቸውን በሚጨምሩ ነገሮች ላይ ብቻ ሳይሆን፥ በመንፈሳዊ ውበታቸውም ላይ አጽንኦት መስጠት ይኖርባቸዋል። ጳውሎስ ይህን ሲል ሴቶች ጌጣ ጌጦችን መጠቀማቸውን ወይም ፀጉራቸውን ማሳመራቸውን መቃወሙ አልነበረም፡፡ ይልቁንም ጳውሎስ በሰዎች አመለካከት ላይ ያተኩራል። ሴቶች ውበታቸውን እያዩ ለመኩራራት በማሰብ ጌጣ ጌጦችን፥ የፀጉር አሠራሮችን ወይም ልብሶችን መጠቀማቸው ትክክል አይደለም፡፡ እንዲሁም ደግሞ ሴቶች የወንዶችን ወሲባዊ ስሜት ለመቀስቀስ ጌጣ ጌጦችንና ልብሶችን መጠቀማቸው ተገቢ አይሆንም። ውጫዊ ውበት የእግዚአብሔር ስጦታ ቢሆንም፥ ዋንኛ አስፈላጊ ነገር አይደለም። እግዚአብሔር የሚያየው ልባችንን ነው። እርሱ በአኗኗራችን እንድናስከብረው ይፈልጋል። እግዚአብሔርን የምናስከብረው ደግሞ መንፈሳዊ ባህሪያችንንና እኗኗራችንን በማስተካከል ነው። ሌሎች ሲቸገሩ አይተን በምንረዳቸው ጊዜ እግዚአብሔርን እናከብራለን። ከወንጌሉ ጋር በማይፋታ ወይም ሰዎችን ወደ ኃጢአት በማይገፋ መንገድ በመልበስና በማጋጊያጥ እግዚአብሔርን እናስከብራለን።

ለ) ሴቶች ከወንዶች የበለጠ ሥልጣን ካልያዝን ማለት የለባቸውም፡፡ ጳውሎስ ሰዎች ለአምልኮ በሚሰበሰቡበት ሁኔታ ላይ ያተኩራል። እዚህ ላይ ጳውሎስ የሚናገረው ስለ ሁሉም ሁኔታዎች አይደለም። ለምሳሌ፥ ሴቶች በሥራ ቦታ ላይ የወንዶች አለቆች ሊሆኑ ይችላሉ። አማኞች ይህንን እገዳ የሚረዱት በተለያዩ መንገዶች ነው። አንዳንድ ምሁራን ጳውሎስ ይህንን ክፍል የጻፈው ያልተማሩና ያልሠለጠኑ ሴቶች ከወንዶች ጋር እኩል እንደ መሆናችን መጠን እኛም የማስተማር መብት አለን በማለታቸው ሳይሆን እንዳልቀረ ይናገራሉ። ይህን አቋም የሚያራምዱ ሰዎች ጳውሎስ የሚናገረው ስላልተማሩ ሴቶች ነው ሲሉ ያስረዳሉ። ጳውሎስ ሴቶች እንዲያስተምሩ ያልፈቀደው እንደ ዛሬው ሴቶች ከወንዶች እኩል ወይም በላይ በተማሩበት ሁኔታ ውስጥ ሳይሆን ምንም ትምህርት ያላገኙ ሴቶች በነበሩበት በጥንታዊው ማኅበረሰብ ውስጥ ብቻ እንደሆነ እነዚሁ ምሁራን ያስተምራሉ። ሌሎች ምሁራን ደግሞ ጳውሎስ የሚናገረው ስለ አመራር ሥልጣን እንደሆነ ያስረዳሉ። በመሆኑም ጳውሎስ ሴቶች ከወንዶች በላይ ሆነው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መሾም እንደሌለባቸው ያስተማረ መሆኑን ይናገራሉ። ስለሆነም ሴቶች የልጆች ወይም የሴቶች አስተማሪዎች፥ መጋቢዎችና ሽማግሌዎች ሊሆኑ ቢችሉም፥ የወንዶች ሽማግሌዎች ወይም መጋቢዎች ሊሆኑ እንደማይችሉ ይናገራሉ።

በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እግዚአብሔር ሴቶችን ከወንዶች እኩል እንደሚያያቸው እውነት ነው። ነገር ግን እኩልነት ማለት የግድ የሥልጣን መዋቅር አይኖርም ማለት አይደለም። አዲስ ኪዳን እግዚአብሔር በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የአመራርን ሥልጣንና ኃላፊነት ለወንዶች እንደሰጠ ያስተምራል። ጳውሎስ በሌሎች ስፍራዎች እንደሚያስተምረው የተለያዩ የሥልጣን ደረጃዎች አሉ። ይህም በሥላሴ ውስጥ እኩልነትና የተለያየ የሥልጣን ደረጃ እንዳለ በሚያመለክት ምሳሌ ተብራርቷል። እግዚአብሔር አብ ከኢየሱስ ክርስቶስ በላይ ነው። አብና ወልድ ደግሞ ከመንፈስ ቅዱስ በላይ ናቸው (1ኛ ቆሮ. 11፡3)፡፡ (ማስታወሻ፡- እግዚአብሔር ሥልጣንን ለማገልገል እንጂ ሌሎችን በጭካኔ ለመግዛት አለመጠቀሙ፥ ወንዶች በሴቶች ወይም ሽማግሌዎች በቤተ ክርስቲያን ላይ ምን ዓይነት ሥልጣን ሊኖራቸው እንደሚገባ የሚያመለክት ነው። የተሰጣቸው ሥልጣን ሌሎችን የማገልገል እንጂ የመግዛት ወይም የመጨቆን አይደለም።) ጳውሎስ ሴቶች በወንዶች ላይ ሥልጣን ሊኖራቸው አይገባም የሚለውን አሳብ ለማስደገፍ በፍጥረት ውስጥ የታየውን የእግዚአብሔርን ዕቅድ ይጠቅሳል። እግዚአብሔር አዳምን መጀመሪያ ሔዋንን ደግሞ ቀጥሎ መፍጠሩ ወንድ በሴት ላይ ሥልጣን እንዳለው ያሳያል። ሴት ከወንድ ቀድማ በኃጢአት መውደቋ ይህንኑ ያጠናክራል።

ይህ ማለት ሴቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ምንም ዓይነት ሥልጣን እንደማይኖራቸው ወይም ሊያስተምሩ እንደማይችሉ ያሳያልን? ይህ ክፍል ሴቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሥልጣን ስፍራ በመያዝ እንደ ሽማግሌ የምእመናንን መንፈሳዊ ሕይወት መንከባከብ እንደሌለባት የሚያስተምር ይመስላል። እንዲሁም ደግሞ ሴቶች ወንዶች እንዴት ሊመላለሱ እንደሚገባ በሥልጣን ሊያዙ በሚችሉበት የማስተማር አገልግሎት ላይ ሊቀመጡ እንደማይገባ የሚያስተምርም ይመስላል። ነገር ግን ይህ እገዳ ሴቶች በልጆች ወይም በሴቶች ላይ የመሪነት ሥልጣን እንዳይኖራቸው አያስተምርም (ቲቶ 2፡3-4 አንብቡ።) (ለምሳሌ፥ የሰንበት ትምህርት ቤቶች፥ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መሪዎች፥ የሴቶች አገልግሎት ዳይሬክተሮች፥ ወዘተ…) እግዚአብሔር ለሴቶች የትንቢት ስጦታ መስጠቱ (1ኛ ቆሮ. 11፡5 አንብብ።) ሴቶች የእግዚአብሔርን ቃል የማስተማር ስጦታ ሊኖራቸው እንደሚችል ያሳያል። ይህ ግን በቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ሥልጣን ሥር መከናወን አለበት።

ሐ) የሴቶች ቀዳማዊ ሚና መንፈሳዊ እናትነት ነው። ጳውሎስ ሴት በምትወልድበት ጊዜ መንፈሳዊ ደኅንነትን አገኘች የሚል አሳብ እንደማያስተላልፍ ከሌሎቹ የአዲስ ኪዳን ክፍሎች መረዳት ይቻላል። እንደዚያ ከሆነማ መንፈሳዊ ደኅንነት ሴቶች በሥራ የሚያገኙት መሆኑ ነው። ልጅ ያልወለዱ ሴቶችና ወንዶች ደግሞ የመዳን ተስፋ አይኖራቸውም። በአዲስ ኪዳን ውስጥ መንፈሳዊ ደኅንነት ሁልጊዜም በኢየሱስ ክርስቶስ በምናምንበት ጊዜ ከእግዚአብሔር የምንቀበለው ስጦታ መሆኑ ተገልጾአል። ይህን ለመረዳት የሚያስቸግር ጥቅስ ለማብራራት አያሌ አማራጮች ቀርበዋል።

 1. ጳውሎስ በዚህ ስፍራ መዳን የሚለውን ቃል የሚጠቀመው የተሟላን ሕይወት ለማመልከት ነው። እርካታና የተሟላ ሕይወት ሴቶች የወንዶችን ዓይነት ሥራ በመሥራት ወይም ደግሞ የወንዶችን ያህል ሥልጣን በመያዝ እኩል መሆናቸውን በማወጃቸው አይደለም። ነገር ግን እርካታና የተሟላ ሕይወት የሚመጣው አንዲት ሴት እግዚአብሔር ያዘጋጀላትን ዕቅድ ተግባራዊ ስታደርግ ነው። ይህም በቤተሰብ ውስጥ የእናትነት ሚናዋን መጫወት ነው። ይህንን ሚና ተግባራዊ በምታደርግበት ጊዜ በግሪክ ማኅበረሰብ ውስጥ የነበሩት ሴቶች የሚፈጽሙትን ዓይነት ኃጢአት ከመፈጸም ትድናለች።
 2. ጳውሎስ መጀመሪያ በሴቶች ላይ የተጣለውን የመጀመሪያውን እርግማን ይጠቅሳል (ዘፍጥ. 3፡16)። ክርስቲያን መሆን ሴቶች ልጅ በሚወልዱበት ጊዜ የሚሰማቸውን የምጥ ጣር ሥቃይ አያስወግድም። ክርስቶስ እስከሚመለስ ድረስ እርግማኑ ይቀጥላል። ነገር ግን ይህ ማለት ሴቶች ከእግዚአብሔር ፍርድ ድነው መንፈሳዊ ድነትን (ደኅንነትን) አያገኙም ማለት አይደለም። ሴቶች በክርስቶስ በማመን እንደ ወንዶች ሁሉ ድነትን ሊወርሱ ይችላሉ።
 3. ጳውሎላ አጽንኦት የሰጠው ልጅን በመውለድ ላይ ሳይሆን፥ አንዲት የተለየች ሴት በወለደችው ልጅ ላይ ነው። ድነት ወደ ዓለም የመጣው ማርያም የተባለች ሴት በወለደችው ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ነው። ማርያም እግዚአብሔር የሰጣትን ኃላፊነት ባትወጣ ኖሮ ሴቶችም ሆኑ ዓለም በሙሉ ደኅንነትን አያገኙም ነበር። ነገር ግን ማርያም የድርሻዋን ስለተወጣች እግዚአብሔር በልጁ በኩል ደኅንነትን ወደ ዓለም አመጣ (ዘፍጥ. 3፡15)።
 4. ጳውሎስ መዳን የሚለውን ቃል የተጠቀመው ሴቶች ልጅ በሚወልዱበት ጊዜ ለሥጋዊ ጉዳት አለመጋለጣቸውን ለማመልከት ነው። ስለሆነም አንዲት ሴት በመንፈሳዊ ሕይወቷ ብቻ ሳይሆን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከወንዶች ጋር ባላት ግንኙነትም እግዚአብሔርን በምታስከብርበት ጊዜ፥ እግዚአብሔር ያቺን ሴት ልጅ በመውለዱ አደገኛ ሂደት ውስጥ ከአደጋ ይጠብቃታል።

የዚህ መጽሐፍ ጸሐፊ እንደሚያስበው፥ የመጀመሪያው ወይም ሁለተኛው አመለካከት ሊሆን የሚችል ይመስላል።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

አንድ መሪ ምእመናን የጸሎት ሰዎች እንዲሆኑ ያስተምራል (1ኛ ጢሞ.2፡1-8)

የቤተ ክርስቲያን መሪ ለራሱ ሕይወት ብቻ ሳይሆን፥ የጠቅላላዋን ቤተ ክርስቲያን አገልግሎቶች ለማሳደግ ከእግዚአብሔር ዘንድ ኃላፊነትን የተቀበለ ሰው ነው። ጳውሎስ እግዚአብሔርን የሚፈራ የቤተ ክርስቲያን መሪ በጥንቃቄ ሊያከናውናቸው የሚገባውን አንዳንድ የአገልግሎት ክፍሎች ጠቃቅሷል። ይህም የክርስቶስ አካል እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድና በማኅበረሰብ ውስጥም መልካም ምስክርነትን በሚያንጸባርቅ መልኩ እንድትንቀሳቀስ ያስችላል። ጳውሎስ ብዙ ነገሮችን ማካተት ቢችልም፥ በሚከተሉት ነጥቦች ላይ ብቻ ያተኩራል።

የእግዚአብሔር ሕዝብ የሚጸልይ ሕዝብ ሊሆን ይገባል። ጸሎት ለተቀደሰ አኗኗር ኃይልን ይሰጣል። ጸሎት በሆነ ምሥጢራዊ መንገድ የእግዚአብሔር ኃይል በቤተ ክርስቲያንና በማኅበረሰባችን ውስጥ እንዲሠራ ያንቀሳቅሰዋል። ጳውሎስ በተጨማሪም የክርስቲያኖች የጸሎት አመለካከት ወይም ባህሪ ወሳኝ እንደሆነ ይናገራል። ይህም የጸሎት አመለካከት አማኞች በሚጠይቁት ነገር ውስጥ የሚታይ ነው። እንደ ብዙዎቻችን የኤፌሶን ክርስቲያኖች የራስ ወዳድነት ጸሎቶችን ይጸልዩ እንደነበር አይጠረጠርም። «ጌታ ሆይ፥ ባርከኝ»፥ «ጌታ ሆይ፥ ቤተ ክርስቲያናችንን ባርክ» የሚለው ነበር የዘወትር ጸሎታቸው ጳውሎስ ክርስቲያኖች ከቤተ ክርስቲያኖች ውጪ ላሉት ዓለማውያንና ለሌሎች ክርስቲያኖችም መጸለይ እንዳለባቸው ለጢሞቴዎስ አስረድቷል። ክርስቲያኖች ለመንግሥት መሪዎችም መጸለይ አለባቸው። እንደ ዛሬዎቹ የመንግሥት መሪዎች ሁሉ በጳውሎስ ዘመን የነበሩት ባለሥልጣናትም ስደትን በክርስቲያኖች ላይ ያመጡ ነበር። ጳውሎስ ይህን መልእክት የጻፈው ለሁለት ዓመታት በሮም እስር ቤት ውስጥ ቆይቶ እንደተፈታ ነበር። ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ደግሞ ተመልሶ ይታሠርና በሮማውያን ይገደል ነበር። ይሁን እንጂ ጳውሎስ ክርስቲያኖች የመንግሥት ባለሥልጣናትን እንደ ጠላት በመቁጠር እንዳይጠሏቸው መክሯል። አሳዳጆችም ቢሆኑ ይህን ማድረጉ ተገቢ አልነበረም። ለምን? ሁለት ጉልህ ምክንያቶች ሊጠቀሱ ይችላሉ። የመጀመሪያው፥ መንግሥት መሪዎች በማኅበረሰብ ውስጥ መረጋጋትን ለማምጣት እግዚአብሔር የሚጠቀምባቸው መሠረታዊ መሣሪያዎች ናቸው። የመረጋጋት መኖር ደግሞ ክርስቲያኖች ፈሪሃ እግዚአብሔርን የተላበሰ የቅድስና ሕይወት እንዲኖሩ ይረዳቸዋል። ሁለተኛ፥ የተረጋጋ መንግሥት በሚኖርበት ጊዜ ወንጌል በቀላሉ ሊስፋፋ ይችላል። እግዚአብሔር ሰዎች ሁሉ የክርስቶስን ወንጌል ሰምተው እንዲድኑ ይፈልጋል፡፡ ልጆቹም ኢየሱስ ክርስቶስ በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ብቸኛው አማላጅ እንደሆነ እንዲናገሩ ይፈልጋል። ከሌሎች ሃይማኖቶች የሚመጣ ምንም ዓይነት ተስፋ ሊኖር አይችልም። ይህም ማለት እያንዳንዱ ቤተ ክርስቲያን ለሰዎች ሁሉ ወንጌልን የምትሰብክበት መንገድ እንዲከፈትላት መጸለይ አለባት ማለት ነው። እግዚአብሔር ጸሎታችንን የሚመልስበት ዋናው መንገድ ደግሞ እንደ ጳውሎስ ያሉትን ሰዎች በመጥራትና መልካሙን የምስራች ላልዳኑት ሰዎች እንዲያውጁ በመላክ ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የቤተ ክርስቲያንህን ተለምዷዊ ጸሎቶች አጢን። እነዚህ ጸሎቶች በቤተ ክርስቲያኒቱ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ ናቸው? ወይስ ከቤተ ክርስቲያን ውጪ ያሉትንና የመንግሥት ባለሥልጣናትን የሚያካትቱ ናቸው? ለ) ቤተ ክርስቲያንህ ለመንግሥት ባለሥልጣናት የምትጸልየው ምን ያህል ነው? ሐ) ቤተ ክርስቲያንህ በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኙና ወንጌልን ላልሰሙ የተለያዩ የሕዝብ ቡድኖች (ለምሳሌ፥ ለሙስሊሞች፥ ለዘላኖች፥ ወዘተ…) የምትጸልየው ምን ያህል ነው? መ) ይህ ስለ ጸሎት የተሰጠው ትምህርት ቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ተቀባይነትን እንዲያገኝ ምን ልታደርግ ትችላለህ?

ጳውሎስ አማኞች ከተቀደሰ ሕይወት የመነጨ ጸሎት እንዲያቀርቡ ያሳስባቸዋል። ዋናው ነገር በጸሎታችን ውስጥ የምንጠቀምባቸው ቃላት፥ ድምፃችንን ምን ያህል ከፍ ማድረጋችን ወይም በክርስቶስ ስም እያልን መደጋገማችን ላይሆን፥ ንጹሐን መሆናችን ነው። ጳውሎስ በምንጸልይበት ጊዜ እጆቻችን ንጹሐን ሊሆኑ እንደሚገባ ይናገራል። (አይሁዶች ብዙውን ጊዜ በሚጸልዩበት ወቅት እጆቻቸውን ወደ ሰማይ ያነሱ ነበር።) በሚጸልይ ሰው ሕይወት ውስጥም ሆነ በአማኞች መካከል ንስሐ ያልተገባ ኃጢአት፥ ክፍፍል፥ ቁጣና ክርክር ሊኖር አይገባም። እነዚህ ነገሮች የጸሎትን ውጤታማነት ይቀንሳሉና።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ለጳውሎስ የተሰጠው የጌታ ጸጋ (1ኛ ጢሞ. 1፡12-20)

አብዛኛቹ ሐሰተኛ ትምህርቶች የሚመጡት አንድን መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት ነጥሎ ከማስተማር ነው። ብዙውን ጊዜ ሰይጣን በትንሽ እምነት ላይ በማተኮር መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን እንድንዘነጋ ለማድረግ ይሞክራል። በኤፌሶን ቤተ ክርስቲያንም የተከሰተው ይኸው ነበር። በመሆኑም ጳውሎስ የራሱን ሕይወት በምሳሌነት በመጥቀስ፥ መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ምን እንደሆነ ለጢሞቴዎስ ያስገነዝበዋል። እጅግ ጠቃሚውና አስፈላጊው እውነት የእግዚአብሔር አስደናቂ ጸጋ ነው። ይህ ጸጋ እንደ ጳውሎስ ያለውን በጣም ክፉ ሰው ወስዶ በክርስቶስ እንዲያምን ከማድረጉም በላይ፥ አገልጋዩ እንዲሆን ሾሞታል። (ጳውሎስ ደኅንነትን ከማግኘቱ በፊት አማኞችን ያስርና ይገድል የነበረ ነፍሰ ገዳይ መሆኑ ይታወቃል።) በጳውሎስ ላይ የነበረው ክፋት በሰዎችም ሁሉ ላይ የነበረ መሆኑ ግልጽ ነው። በምናደርጋቸው ነገሮች፥ በምንጠብቃቸው ሕግጋት ወይም እግዚአብሔርን ለማገልገል በምናከናውናቸው ተግባራት ላይ ትኩረት ማድረግ የለብንም። ብዙ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እንደዚህ ዓይነት ዝንባሌ አላቸው። ይልቁንም በሕይወታችን ውስጥ በተገለጸው የእግዚአብሔር አስደናቂ ጸጋና ምሕረት ላይ አጽንኦት ልንሰጥ ይገባል። ዋናው ነገር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ የቀረበው መሠረታዊ ወንጌል እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ስለማያስተምራቸው እውነቶች የድምዳሜ አሳብ ማበጀት ወይም ደስ በሚያሰኙን የተወሰኑ እውነቶች ላይ ማተኮር አይደለም። ማተኮር ያለብን ግልጽና ጠቃሚ በሆነው መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት ላይ እንጂ፥ ግልጽ ባልሆነውና መንፈሳዊ ጠቀሜታ በሌለው አሳብ ላይ መሆን የለበትም። እንደ አለመታደል ሆኖ ግን የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የዚህን ተቃራኒ እርምጃ ይወስዳሉ። በመሆኑም የወንጌልን እውነታዎች የሚያፋልሱትን የሐሰት አስተማሪዎች እየታገሱ እንደ መጠጣት፥ የሕፃናት ጥምቀት ወይም የጌታ ራት አወሳሰድ የመሳሰሉትን ልምምዶች ከእነርሱ በተለየ መንገድ የሚያከናውኑትን ክርስቲያኖች አጥብቀው ይቃወማሉ።

ጢሞቴዎስ ዓይናፋርና ሐሰተኛ ትምህርት የሚያቀርቡትን ሰዎች ለመጋፈጥ ያልደፈረ ይመስላል። ጳውሎስ ግን እንዲጋደል ይነግረዋል። የሐሰተኛ አስተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዲያቀርቡ በመፍቀድ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ሰይጣን እንዲያጠፋ ከመፍቀድ ይልቅ፥ ጢሞቴዎስ የማጥቃት እርምጃ እንዲወስድ ተነግሮታል። የሚዋጋውም በሁለት መንገዶች ነው። በመጀመሪያ፥ ግላዊ ውጊያ ማካሄድ ነበረበት። ይኸውም እውነትን አምኖ በንጽሕና ይመላለስ ዘንድ ሕይወቱንና ምስክርነቱን መጠበቅ እንዳለበት የሚያስገነዝብ ነው። ሁለተኛ፥ ሐሰተኛ ትምህርትን የሚያስፋፉ ሰዎችን በመከላከልና ምእመናን እውነትን እንዲከተሉ በማድረግ የአደባባይ ውጊያ ማካሄድ ነበረበት። የትንቢት ስጦታው የእግዚአብሔርን ፈቃድና እውነትን እንዲያውቅ ያስችለው ነበር። ሰዎችን ፈርቶ ስጦታውን መደበቁ ወይም አለመጠቀሙ ትክክል አልነበረም። ጳውሎስ ጢሞቴዎስ ራሱንና ቤተ ክርስቲያኒቱን ለመከላከል አለመጣሩ እምነትን ሊያፈራርስ የሚችል አደገኛ ነገር መሆኑን አስገንዝቧል። ጳውሎስ ከእምነታቸው የወደቁትን ሁለት ሰዎች ይጠቅላል። እነዚህም ሄሜኔዎስና እስክንድሮስ ናቸው። ምንም እንኳን በእምነት ላይ ያሉ ቢሆኑም፥ ስድብን ለማቆም ይማሩ ዘንድ ለሰይጣን አሳልፎ ሰጣቸው። እነዚህ ሰዎች ምን ዓይነት ኃጢአት እንደ ፈጸሙ አናውቅም። ምናልባትም የሐሰት ትምህርት እያስፋፉ ወይም በኃጢአት እየተመላለሱ ይሆናል።

ለሰይጣን አሳልፎ መስጠት ማለት ምን ማለት ነው? ይህ ጳውሎስ የቤተ ክርስቲያንን የሥነ ሥርዓት እርምጃ ለመግለጽ የሚጠቀምበት ቃል ነው። አንድ ሰው በተለይም በመሪነት የሚያገለግል ግለሰብ በዐመፃ መንፈስ ተነሣሥቶ መንፈሳዊ ሕይወት ላለመኖር ወይም እውነትን ላለመከተል በሚመርጥበት ጊዜ ጳውሎስ የቤተ ክርስቲያን የቅጣት እርምጃ ይወስድበት ነበር። ይህንንም የሚያደርገው ከአማኞች ኅብረት ግለሰቡን በማግለል ነበር። ጳውሎስ የአማኞች ኅብረት አካል መሆኑ ከሰይጣን ቀጥተኛ ጥቃቶች እንደሚከላከል ያውቅ ነበር። ምክንያቱም በዚህ ኅብረት ውስጥ ክርስቶስ በተለየ ሁኔታ ይኖራልና። ከዚህ የአማኞች ኅብረትና ከመንፈስ ቅዱስ ጥበቃ ውጪ መሆኑ ሰውዬውን ለሰይጣን ጥቃት ያጋልጠዋል። ይህ ግን ሰይጣን ሰውዬውን ወደ ጠለቀ ኃጢአት እንዲመራው ለማድረግ የታሰበ አልነበረም። ይልቁንም ሰይጣን አካላዊ ጤናውን ወይም በዐመፀኛነቱ ከቀጠለ ሞትን በማስከተል ከኃጢአቱ ንስሐ እንዲገባ ያደርገዋል ከሚል አሳብ የመነጨ ነበር። በመሆኑም ጳውሎስ እነዚህ ሰዎች ከቤተ ክርስቲያን ኅብረት ወጥተው እንዲቀጡ አዟል። ይህም በ1ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 5 ውስጥ ከተጠቀሰውና በኃጢአት ውስጥ ከሚኖር ግለሰብ ሕይወት ጋር የሚመሳሰል ነበር። ጳውሎስ ይህንን ያደረገው ኃጢአት የሠራውን ግለሰብ ለመቅጣት ብቻ አልነበረም። ሌሎች አማኞች በእግዚአብሔር ላይ ዐመፅ እንዳይፈጽሙና የቤተ ክርስቲያንን ንጽሕና እንዲጠብቁ ለማስጠንቀቅ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ለቤተ ክርስቲያን በዐመፀኝነት መንፈስ ተነሣሥተው ከኃጢአት ወይም ከሐሰተኛ ትምህርት ለመመለስ የማይፈልጉትን ሰዎች መቅጣት አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው? ለ) ቤተ ክርስቲያንህ አማኞችን የቀጣችበትን ሁኔታ ግለጽ። ሐ) ዓላማቸው ምን ነበር? መቅጣት ወይስ ማስተማር? መ) በቤተ ክርስቲያን ቅጣት ውስጥ ትክክለኛ ምክንያት አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ጳውሎስ ጢሞቴዎስ በሕጎች ላይ ባለማተኮር የወንጌሉን እውነት እንዲጠብቅ ያስጠነቅቀዋል (1ኛ ጢሞ. 1፡1-11)

ለ20 ዓመታት የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌ ሆኖ አገልግሏል። ሚስቱ መልካም መንፈሳዊት ሴት ስትሆን፥ ልጆቹም በእግዚአብሔር እውነት ይጓዙ ነበር። በተለይም ኮሚኒዝም በሥልጣን ላይ በነበረበት ወቅት እግዚአብሔር ስንታየሁን በብዙ መንገዶች ተጠቅሞበታል። የኋላ የኋላ ግን በመንፈሳዊ ዕድገትና ባሕርያት ላይ ከማተኮር ይልቅ ሕይወቱ እያዘቀዘቀ እንዲሄድ አድርጓል። አንድ ቀን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እየሠራ እያለ አንዲት ቆንጆ ወጣት ስለ ግል ጉዳይዋ ልታማክረው መጣች። ስንታየሁ ከተለያዩ ውይይቶች በኋላ ከዚህች ልጅ ጋር ወሲባዊ ኃጢአት ፈጸመ። ከዚህም የተነሣ ሚስቱን ፈታ። ከቤተ ክርስቲያን መሪነቱም ወረደ። ከዚያ በኋላ እንደ ማንኛውም ዓለማዊ ሰው ይኖር ጀመር።

በላይነሽ በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ የታወቀች ሴት ነበረች። የቤተ ክርስቲያኒቱ የጸሎት ቡድን መሪ ከመሆኗም በላይ፥ የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያንና የቀጠና የሴቶች ማኅበር መሪም ነበረች። አንድ ቀን ባሏ ከፍተኛ ደመወዝ በሚከፍል መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት (መያድ) ውስጥ ሥራ አገኘ። ብዙም ሳይቆይ እርሷም በዚሁ ድርጅት ውስጥ ተቀጠረች። ነገር ግን ከሥራው ጋር በተያያዘ እርሷና ባለቤቷ ሊወስኑዋቸው የሚገቡ ነገሮች ተከትለው መጡ። ድርጅቱ እርሱን በሰሜን ኢትዮጵያ እርሷን ደግሞ በደቡብ ኢትዮጵያ ውስጥ መደባቸው። ለእነዚህ ሰዎች ቤተሰባቸው ሥራው ከሚያስገኘው ገንዘብ የበለጠ አስፈላጊ ነበር? እርሱ ሁለት ትልልቅ ልጆችን እርሷ ደግሞ ሁለት ትንንሽ ልጆችን ይዘው በተለያዩ ቦታዎች መኖር ጀመሩ። እርስ በርሳቸው ብዙም ሳይገናኙ በሚያገኙዋቸው ገንዘብና ጥቅማ ጥቅሞች መደሰታቸውን ቀጠሉ። መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ብዙ ገንዘብ ቢከፍሉም ከሠራተኞቻቸው ብዙ ሥራ ይጠብቃሉ። በመሆኑም በላይነሽ ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ወይም የጸሎት ስብሰባዎች ለመሄድ የምትችልበትን ጊዜ ልታገኝ አልቻለችም። ብዙውን ጊዜ እሑድ እሑድ ቀን ስብሰባዎች ይካሄዳሉ። ይህም ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዳትሄድ ከለከላት። ከሁለት ልጆቹ ጋር በሰሜን የሚኖረው ባለቤቷ ምግብ የምታዘጋጅላቸው ሠራተኛ ቀጠረ። የኋላ ኋላ ግን ከዚህችው ሠራተኛ ጋር አብሮ ይተኛ ጀመር። ምንም እንኳ ሥራው፥ ገንዘቡና ተራርቆ መኖሩ ከእግዚአብሔር ጋር የነበራቸውን ግንኙነት የሚቀንስና እነርሱንም የሚያራርቃቸው መሆኑን ቢገነዘቡም፥ ገንዘብ የሚያስገኘውን ጥቅም ለማጣት አልፈለጉም። ከዚህም የተነሣ ብዙም ሳይቆይ መንፈሳዊ ሕይወታቸው በጽኑ ተጎዳ።

ሙሉጌታ ለረጅም ጊዜያት የቤተ ክርስቲያን መሪ ሆኖ ሲያገለግል ቆይቷል። ምንም እንኳን ሙሉጌታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቡድን አባል ቢሆንም፥ የእግዚአብሔርን ቃል ለማጥናት ወይም እውነትን በማወቅ ለማደግ ጊዜ አልወሰደም። ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሚያስተምርበት ጊዜ ሁሉ ስለ ደኅንነት ወይም አንድ ሰው ጥሩ ክርስቲያን ለመሆን ሊያደርጋቸው ስለሚገቡ ነገሮች ከመናገር የበለጠ አሳብ አያቀርብም። አንድ ቀን አንድ ሐሰተኛ አስተማሪ ወደ እነ ሙሉጌታ ቤተ ክርስቲያን መጥቶ መጽሐፍ ቅዱስ የሥላሴን አስተምህሮ እንደማያስተምር ገለጸ። ይህ ሰው በብሉይ ኪዳን ዘመን አብ፥ በምድር ላይ በነበረ ጊዜ ደግሞ ወልድና አሁን ደግሞ በሰዎች ልብ ውስጥ መንፈስ ቅዱስ ሆኖ የሚኖር አንድ አምላክ ብቻ እንዳለ አስተማረ። ይህ ግለሰብ የተወሰኑ ጥቅሶችን ያለ አውዳቸው ከመጽሐፍ ቅዱስ ፈልቅቆ በማውጣት ሙሉጌታ እውነተኛ ክርስቲያን አለመሆኑን አሳየው። በመሆኑም ሙሉጌታ የቀድሞ አሳቡን ለውጦ ወደ ሌላ ቤተ ክርስቲያን ተዛወረ። ይህም ከእውነት ወደ ሐሰተኛ ትምህርት እንዲቅበዘበዝ አደረገው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እነዚህ ሁሉ መሪዎች እግዚአብሔር ለሕይወታቸው ካቀደው ዓላማ እንዲኮበልሉ ያደረጋቸው ችግር ምን ነበር? በቤተ ክርስቲያንህ እነዚህን ሦስት ችግሮች እንዴት እንደተመለከትህ ግለጽ። ለ) ለቤተ ክርስቲያን መሪዎች ከእነዚህ ሦስት ችግሮች መራቅ እጅግ አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው?

የጢሞቴዎስ መጽሐፍ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ለክርስቶስ ውጤታማ አገልግሎት ይሰጡ ዘንድ ሕይወታቸውን በጥንቃቄ እንዲጠብቁ ያስጠነቅቃቸዋል። የወሲብ ሕይወታችንን በመጠበቅ ንጹሐን ሆነን መመላለስ ይኖርብናል። ለእግዚአብሔር ከምናገለግለው አገልግሎት ወይም ከቤተሰባችን እንዳይበልጥብን የገንዘብ ፍቅር ራሳችንን መጠበቅ አለብን። ከሐሰት ትምህርቶችም ራሳችንንና የቤተ ክርስቲያናችንን ምእመናን መጠበቅ ይኖርብናል። እነዚህ ሦስት ችግሮች ዛሬ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ባለማቋረጥ የሚጋፈጧቸው ችግሮች ናቸው። ጳውሎስ በዚህ የጢሞቴዎስ መልእክት ውስጥ ጢሞቴዎስና የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በሙሉ ልባቸውን እንዲጠብቁ፥ ሕይወታቸውን እንዲጠብቁና እምነታቸውን በንጽሕና እንዲይዙ ያስጠነቅቃል።

ጳውሎስ ከሮም እስር ቤት ከተፈታ በኋላ በአውሮፓና በእስያ ውስጥ የሚገኙትን አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት የጎበኘ ይመስላል። በዚህም ጊዜ ጢሞቴዎስና ቲቶ አብረውት ይጓዙ ነበር። ጳውሎስ የቆጵሮስን ቤተ ክርስቲያን እንዲመሠርትና አንዳንድ ችግሮቻቸውን በማስወገድ ረገድ ይረዳቸው ዘንድ ቲቶን እዚያው ተወው። የኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን የምትጋፈጣቸውን ችግሮች ለማስተካከልም ጢሞቴዎስን በኤፌሶን አቆየው። ጳውሎስ ቶሎ ወደ ኤፌሶን ለመመለስ እያሰበ ሳይሆን አይቀርም ወደ መቄዶኒያ የሄደው። ጳውሎስ እንዳሰበው በፍጥነት ባለመመለሱና ጢሞቴዎስም ወደ መቄዶኒያ ለመሄድ እያቀደ በመሆኑ፥ ጳውሎስ ይህንኑ የ1ኛ ጢሞቴዎስ መልእክት በመጻፍ ጢሞቴዎስ በኤፌሶን መሥራቱን እንዲቀጥል ይነግረዋል። በተጨማሪም ጳውሎስ በዚህ መልእክቱ ውስጥ የጢሞቴዎስ አገልግሎት በኤፌሶን ምን መሆን እንዳለበት ያብራራል። በዚህ መልእክት ውስጥ አንዳንድ ጠቃሚ ትምህርቶች ቀርበዋል። እነዚህም ሁሉም የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በጥንቃቄ ሊያጤኗቸውና ሊከተሏቸው የሚገቡ ናቸው።

ሰይጣን የቤተ ክርስቲያን ጠንካራው ጠላት ሲሆን፥ ቤተ ክርስቲያን ውጤታማነቷን እንድታጣና እንድትጠፋ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋል። ሰይጣን ቤተ ክርስቲያንን ከሚዋጋባቸው ቀዳማይ መንገዶች አንዱ መሪዎቿን ማጥቃት ነው። ቤተ ክርስቲያን ከመሪዋ መንፈሳዊ ሕይወት አልፋ ልታድግ አትችልም። መሪዎች መንፈሳዊ ምስክርነታቸውን ካጡ፥ ሕይወታቸው ከቆሸሸ፥ እምነታቸውን ካመቻመቹ፡ ሰይጣን መሪውን ብቻ ሳይሆን ቤተ ክርስቲያኒቱንም አሸንፎአል ማለት ነው። በተጨማሪም አምልኮ፥ መሪዎቹን በሚመርጡበት ሁኔታ፥ እርስ በርሳቸው በሚዛመዱባቸው መንገዶች ቤተ ክርስቲያንን ለማጥቃት ይሞክራል። ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ እንድትንቀሳቀስ ከተፈለገ፥ በአግባቡ የተመረጡ መሪዎች፥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለድሆች እንክብካቤ የተወጠነ ዕቅድና በማኅበረሰብ ውስጥ መልካም ምስክርነት ያለው የአባላት አኗኗር ወሳኝ ነው። ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ የሰጠው ምክር እነዚህን ነጥቦች ይዳስሳል።

በአብዛኛቹ መልእክቶቹ እንደተለመደው፥ ጳውሎስ ይህንን መልእክት በእግዚአብሔር ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ በማለት ይጀምራል። ጳውሎስ ጢሞቴዎስ የኤፌሶን ቤተ ክርስቲያንን ለመምራት የሚጠቀምበትን ደብዳቤ ሲጽፍ በሐዋርያዊ ሥልጣኑ ላይ አጽንኦት ሰጥቷል። ዛሬ ይህንን እውነት የማንቀበል ከሆነ ይህ የጳውሎስን የሐዋርያነት ሥልጣን ብቻ ሳይሆን እነዚህን ቃላት የጻፈውን የመንፈስ ቅዱስ ሥልጣንም ቸል እያልን ነው ማለት ነው።

ጳውሎስ ጢሞቴዎስ ለሁለት ዓይነት ትምህርቶች ጥንቃቄ እንዲያደርግ በመምከር ይጀምራል። በመጀመሪያ፥ ተረቶችና ፍፃሜ የሌላቸው የትውልድ ታሪኮች ነበሩ እነዚህ ነገሮች ምን እንደሚያካትቱና የሚያስተምሯቸው ደግሞ አይሁዶች ወይም አሕዛብ መሆናቸውን መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ አይጠቅስም። ነገር ግን እነዚህ ነገሮች ምንም ዓይነት መንፈሳዊ ለውጥ የማያስከትሉ ሥነ መለኮታዊ ወይም ምሁራዊ ክርክሮች ሳይሆኑ አይቀሩም። ይህ ቤተ ክርስቲያንን ከማነጽና መንፈሳዊ ዕድገትን ከማምጣት ይልቅ የሚከፋፍሉ ሥነ መለኮታዊ ጉዳዮችን ለምንከታተል ሰዎች ጠንካራ ማስጠንቀቂያ ነው። ስለ እነዚህ ደቃቅ አስተምህሮዎች መከራከሩ ብዙውን ጊዜ ከንቱ ድካም ነው። ውጤቱም ክርስቶስን የማያስከብር ክፍፍል በክርስቲያኖች መካከል ማስከተል ነው። ጳውሎስ ጢሞቴዎስ የንጹሕ ልብ፥ የፍቅር፥ የመልካም ሕሊናና የእውነተኛ እምነት ምንጭ በሆኑት የእግዚአብሔር ቃል እውነቶች ላይ እንዲያተኩር ያሳስሰዋል።

ሁለተኛ፥ በግልጽ ከእውነት ያፈነገጡና ሰዎችን ከቤተ ክርስቲያን የሚያስኮበልሉ ትምህርቶች ነበሩ። ጳውሎስ በሁሉም መልእክቶቹ ውስጥ ማለት ይቻላል ሰይጣን ሰዎችን ከቤተ ክርስቲያን ለማስኮብለል የሚጠቀምባቸውን የተለያዩ የሐሰት ትምህርቶች የሚመለከት ትምህርት ያቀርባል። ጳውሎስ ባለማቋረጥ ከእነዚህ የሐሰት ትምህርቶች ጋር መዋጋትና ለእውነት መጋደል ከነበረበት፥ ዛሬም የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በአብያተ ክርስቲያኖቻችን ተመሳሳይ ሁኔታዎች እንደሚኖሩ መገንዘብ ይኖርባቸዋል። ጳውሎስ ጢሞቴዎስ በኤፌሶን እንዲቆይ የፈለገበት ዋነኛው ምክንያት በዚያች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አንዳንድ ሰዎች ሐሰተኛ አስተምህሮዎችን ያስፋፉ የነበሩ መሆናቸው ነበር። ከእነዚህም የሐሰት ትምህርቶች አንዱ ስለ ሕግ የተሳሳተ ግንዛቤ መያዝ ነበር። ጳውሎስ በአግባቡ ከተጠቀሙበት የብሉይ ኪዳን ሕግ መልካም መሆኑን ያምናል። ሕግ የተሰጠው ደኅንነትን ለማስገኘት ወይም የመንፈሳዊነት ማረጋገጫ እንዲሆን አልነበረም። ይልቁንም ሕግ የተሰጠው የሰዎችን የልብ ክፋት ለመቆጣጠርና ፈሪሀ እግዚአብሔር የሌላቸውን ተግባራት ለመገደብ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ሰይጣን በእነዚህ ሁለት ዓይነት የተሳሳቱ ትምህርቶች እማካኝነት ቤተ ክርስቲያንን ሲያጠቃ የተመለከትከው እንዴት ነው? ለ) በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሚዛናዊነቱን የጠበቀ ትምህርት እንዲሰጥ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ምን ሊያደርጉ ይችላሉ?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የ1ኛ ጢሞቴዎስ መዋቅር እና አስተዋጽኦ

የ1ኛ ጢሞቴዎስ መዋቅር

1ኛ ጢሞቴዎስ መልእክት በዋነኛነት ልምድ ያካበተ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ገና ወጣት ለሆነ አገልጋይ ያስተላለፈው ምክር ነው። ጳውሎስ መንፈሳዊ ልጁና ወጣት የቤተ ክርስቲያን መሪ የሆነው ጢሞቴዎስ ንጹሕ ሕይወት ለመምራትና ቤተ ክርስቲያኒቱንም በንጽሕና ለመጠበቅ ይችል ዘንድ ሊያውቃቸው የሚገባቸውን አንዳንድ ነገሮች ያስገነዝበዋል። ምንም እንኳ በመጽሐፉ ውስጥ ግልጽ የሆነ አስተዋጽኦ ባንመለከትም፥ ጠቅለል ባለ መልኩ በሦስት ዐበይት ክፍሎች ሊከፈል ይችላል።

1) የቤተ ክርስቲያን መሪ ለሆነው ጢሞቴዎስ የተሰጠ የግል ምክር (1ኛ ጢሞ. 1)። ጳውሎስ ጢሞቴዎስ እውነተኛውን የእምነት ትምህርት ትቶ ሐሰተኛ ትምህርቶችን እንዳይከተል ወይም ክርስቶስን ከማመን ወደ ኋላ እንዳይመለስ ያስጠነቅቀዋል። በሐሰተኛ ወይም ትርጉም በሌላችው ትምህርቶች ተወስደው እምነታቸውን የጎዱ ሌሎች የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ነበሩ። በሕይወታቸው እግዚአብሔርን የማያስከብሩና እምነታቸው የፈረሰባቸው አገልጋዮችም እንዲሁ ነበሩ።

2) የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ስለሚያስተዳድርበት ሁኔታ የተሰጠ ምክር (1ኛ ጢሞ. 2፡1-6፡2)። ጳውሎስ ጢሞቴዎስ እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ ቤተ ክርስቲያንን እንዴት እንደሚያስተዳድር ይመክረዋል። በዚህ ክፍል ውስጥ ጳውሎስ ስለ ጸሎት ተገቢ አለባበስ፥ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን ስለ መምረጥ፥ የሐሰተኛ አስተማሪዎችን ስለ መቋቋም፥ መበለቶችን መንከባከብና ስለ ባሮች ትኩረት ሰጥቶ አስተምሯል።

3) የቤተ ክርስቲያን መሪ ለሆነው ጢሞቴዎስ የተሰጠ የግል ምክር (1ኛ ጢሞ. 6፡3-21)። ጳውሎስ አሁንም የቤተ ክርስቲያንን መሪ ውጤታማነት ሊያጠፉት ስለሚችሉት ነገሮች ጢሞቴዎስን በማስጠንቀቅ የመጀመሪያ መልእክቱን ይደመድማል። በገንዘብ ፍቅር እንዳይነደፍና ሕይወቱን በእግዚአብሔር ዓይኖች ፊት በንጽሕና እንዲጠብቅ ይነግረዋል።

የ1ኛ ጢሞቴዎስ አስተዋጽኦ

 1. የቤተ ክርስቲያን መሪ ለሆነው ጢሞቴዎስ የተሰጠ የግል ምክር (1ኛ ጢሞ. 1)።

ሀ) ጳውሎስ ጢሞቴዎስ የወንጌልን እውነት እንዲጠብቅ ያስጠነቅቀዋል (1ኛ ጢሞ. 1፡1-11)።

ለ) ጳውሎስ ወንጌሉ ክርስቶስ ለኃጢአተኞች ካለው ፍቅር እንደሚመነጭ የራሱን የግል ተሞክሮ በመግለጽ ያብራራል (1ኛ ጢሞ. 1፡12-17)።

ሐ) ጳውሎስ ጢሞቴዎስ በኃጢአት እንዳይወድቅ ትምህርቱንና የግል ሕይወቱን ንጽሕና እንዲጠበቅ ይመክረዋል (1ኛ ጢሞ. 1፡18-21)።

 1. የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ስለ ማስተዳደር የተሰጠ ምክር (1ኛ ጢሞ. 2፡1-6፡2)።

ሀ) አንድ የቤተ ክርስቲያን መሪ ምእመናን የጸሎት ሰዎች እንዲሆኑ ያስተምራል (1ኛ ጢሞ. 2፡1-8)።

ለ) የቤተ ክርስቲያን መሪ ሴቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ምሳሌያዊ ሕይወት እንዲኖሩ ይረዳቸዋል (1ኛ ጢሞ. 2፡9-15)።

ሐ) የቤተ ክርስቲያን መሪ ምእመናን ሽማግሌዎችንና ዲያቆናትን በጥንቃቄ እንዲመርጡ ይረዳቸዋል (1ኛ ጢሞ. 3)።

መ) የቤተ ክርስቲያን መሪ የሐሰት አስተማሪዎችን ለመከላከል የእምነትን እውነት ይጠብቃል (1ኛ ጢሞ. 4)።

ሠ) የቤተ ክርስቲያን መሪ ቤተ ክርስቲያኒቱ መበለቶችን የምትንከባከብበትን መንገድ እንድታዘጋጅ ይረዳል (1ኛ ጢሞ. 5፡1-16)።

ረ) የቤተ ክርስቲያን መሪ ያለ አድልዎ በሚያበረክተው አገልግሎት በምእመናን ሊከበር ይገባዋል (1ኛ ጢሞ. 5፡17-24)።

ሰ) የቤተ ክርስቲያን መሪ ሠራተኞች (ባሪያዎች) ከአሠሪዎቻቸው (ከጌቶቻቸው) ጋር ተገቢ ግንኙነት እንዲኖራቸው ይረዳል (1ኛ ጢሞ. 6፡1-2)።

 1. የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ለሆነው ጢሞቴዎስ የተሰጠ ግላዊ ምክር (1ኛ ጢሞ. 6፡3-21)

ሀ) ጢሞቴዎስ ራሱን ከገንዘብ ፍቅር ማራቅ ያስፈልገው ነበር (1ኛ ጢሞ. 6፡3-10)

ለ) ጢሞቴዎስ በሰዎች ሁሉ ፊትና በእግዚአብሔር ንጹሕ ሆኖ ለመገኘት ይችል ዘንድ ሕይወቱንና እምነቱን መጠበቅ ያስፈልገው ነበር (1ኛ ጢሞ. 6፡11-21)።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)