የ1ኛ ጢሞቴዎስ ልዩ ባሕርያት

1) የ1ኛ ጢሞቴዎስ መልእክት ለጢሞቴዎስ የግል ምክሮችን የሚለግስና ለቤተ ክርስቲያንም የሚያገለግል መልእክት ነው። ይህ ቀደም ሲል ከተመለከትናቸውና ጳውሎስ ለአብያተ ክርስቲያናት ወይም ለተወሰኑ እማኞች ቡድን ከላካቸው መልእክቶች የተለየ ነው። ለምሳሌ ያህል፥ ጳውሎስ ከሰጣቸው ምክሮች አንዳንዶቹ የጢሞቴዎስን ግላዊ ሁኔታ ያገናዘቡ ነበሩ። ጳውሎስ ጢሞቴዎስን ልጄ እያለ በመጥራት (1ኛ ጢሞ. 1፡18)፥ በልጅነቱ የበታችነት ስሜት እንዳይሰማው (1ኛ ጢሞ. 4፡12)፥ እንዲሁም ላለበት በሽታ ጥቂት የወይን ጠጅ እንዲጠጣ ይመክረዋል (1ኛ ጢሞ. 4፡23)። ነገር ግን በዚህ መልእክት ውስጥ የሚገኙ አብዛኞቹ ጉዳዮች ጢሞቴዎስ በኤፌሶን ከተማ ቤተ ክርስቲያንን በሚገባ እንዲያደራጅ የሚያሳስቡ ነበሩ። ይህ መልእክት ምናልባትም ጢሞቴዎስ እንደ መመሪያ ሊከተለውና ከእርሱ በኋላ የሚመጡ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችም በዚሁ መንገድ ቤተ ክርስቲያንን እንዲመሠርቱ የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም።

2) የ1ኛ ጢሞቴዎስና የቲቶ መልእክቶች የቀድሞዎቹ አብያተ ክርስቲያናት እንዴት ይደራጁ እንደነበር ያስገነዝቡናል። ምንም እንኳን በሐዋርያት ሥራ ውስጥ ዲያቆናትና ሽማግሌዎች የተጠቀሱ ቢሆንም፥ ሽማግሌዎች በተወሰኑ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ማገልገላቸውን ወይም ዲያቆናት በተወሰኑ ቦታዎች ብቻ መገኘታቸውን በዝርዝር እንመለከትም። የጢሞቴዎስ መልእክት በአዲስ ኪዳን ዘመን የተለመደው የቤተ ክርስቲያን አመራር ዲያቆናትንና ሽማግሌዎችን እንደሚያካትት ያብራራል። እነዚህ መሪዎች እንዴት እንደሚመረጡ ግን የተገለጸ ነገር የለም። በሐዋርያት ይሆን የሚሾሙት? ወይስ በምእመናን ይመረጡ ነበር? ይህም አንድ ዓይነት የአመራር መዋቅር መርጠን በአዲስ ኪዳን ልናስደግፈው እንደማንችል ያስገነዝባል። ጳውሎስ ለአገልግሎቱ ስለሚያስፈልግ ውጫዊ የብቃት መለኪያም የገለጸው ነገር የለም። የቀድሞይቱ ቤተ ክርስቲያን ትኩረት የምትሰጠው በውስጣዊ ብቃቶች ላይ ነበር። ከዚህም የተነሣ በባሪያና ጨዋ፥ ማንበብ በሚችልና በማይችል፥ ወይም በሀብታምና ድሃ መካከል ልዩነት አይደረግም ነበር። ሁለቱም ውስጣዊ ብቃቶችን ካሟሉ በመሪነት ሊያገለግሉ ይችሉ ነበር። ሌላው በጳውሎስ መልእክቶች ውስጥ የሽማግሌ አገልግሎት ከዲያቆን የሚለይባቸው ነጥቦች ሰፍረው አንመለከትም።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በቤተ ክርስቲያንህ ሽማግሌዎችን ወይም ዲያቆናትን ለመምረጥ በዋናነት የሚወሰዱ ብቃቶች ምን ምንድን ናቸው? ትኩረት የሚሰጠው እንደ ታዋቂነት፥ ትምህርት፥ ሀብት፥ መልካም ቤተሰባዊ ሥረ መሠረት ላሉት ውጫዊ ብቃቶች ነው ወይስ እንደ የጸሎት ሕይወት፥ የማስተማር ችሎታ፥ መንፈሳዊነት፥ ላሉ መንፈሳዊ ብቃቶች ነው? ለ) ብዙ መሪዎች ከመንፈሳዊ ብስለታቸው ይልቅ በጎሳቸው፥ በቤተሰባቸው ወይም በትምህርት ደረጃቸው ምክንያት የሚመረጡት ለምንድን ነው? ሐ) ይህ ቅድሚያ ስለምንሰጣቸው ነገሮች ምን ያሳያል?

3) ጳውሎስ ሰዎች ሊያምኑት፥ ሊጠብቁትና ለሌሎች ሊያስተላልፉ ስለሚገባው ወንጌል አጽንኦት ሰጥቶ ይናገራል። ጳውሎስ ጢሞቴዎስ አዲሱን ትውልድ ለማስደሰት አዳዲስ መረጃዎችን እንዲፈጥር አይጠብቅበትም ነበር። ይልቁንም ጢሞቴዎስ ብዙ ጊዜ ጳውሎስ ወንጌል ሲሰብክ ስለሰማ ይህንኑ እውነት በጥንቃቄ ለሌሎች እንዲያስተላልፍ ይፈልጋል (1ኛ ጢሞ. 1፡3-11)። ምንም እንኳን ወንጌሉን የምንሰብክበት መንገድ ከባህል ባህል ወይም ከትውልድ ትውልድ ሊለያይ ቢችልም፥ የወንጌሉ አስኳል ይዘት መለወጥ የለበትም። ሁልጊዜም ወንጌሉ ክርስቶስ ብቸኛው የመዳን መንገድ መሆኑን፥ ለኃጢአታችን መሞቱንና ሰው ድነትን (ደኅንነትን) የሚያገኘው በክርስቶስ በማመን መሆኑን አጽንቶ መናገር አለበት። ሰባኪው ጢሞቴዎስ፥ ጳውሎስ ወይም ዛሬ ያለነው እኛ ብንሆን ወይም ሰውዬው በቻይና፥ ዩናይትድ ስቴትስ፥ ወይም በኢትዮጵያ ውስጥ ቢኖር ይህ የመልእክት አስኳል መለወጥ የለበትም። ኃይማኖቶች ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ይመራሉ የሚለው ዓይነት የትኛውም የወንጌሉን አስኳል የሚለውጥ ትምህርት ወንጌሉን በመለወጥ ከእግዚአብሔር ስለሚያርቀን ሐሰተኛነቱ ሊገለጥ ይገባል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እያንዳንዱ ክርስቲያን የወንጌልን ምንነት በግልጽ መገንዘቡ አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው? ለ) ሐሰተኛ አስተማሪዎች በኢትዮጵያ ውስጥ የወንጌሉን አስኳል እንዴት እንደሚለውጡ ምሳሌዎችን ዘርዝር።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የ1ኛ ጢሞቴዎስ ዓላማ

1) በኤፌሶን ጳውሎስ የሰጠውን ኃላፊነት ለማሟላት ደፋ ቀና ይል ለነበረው ጢሞቴዎስ ሥልጣንን ለመስጠት። ጢሞቴዎስ ሐዋርያ ባለመሆኑ የጳውሎስ ዓይነት ሥልጣን አልነበረውም። ስለሆነም ትምህርቱን ተቀባይነት ያለው ለማድረግ ጳውሎስ የጻፈለትን ደብዳቤ ለአብያተ ክርስቲያናቱ ማሳየት ይችል ነበር።

2) በኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሐሰት ትምህርት በመስፋፋት ላይ ነበር። በመሆኑም ጳውሎስ ጢሞቴዎስ እነዚህን የሐሰት ትምህርቶች እንዲከላከል አዞታል (1ኛ ጢሞ. 1፡3-20)። እነዚህ የሐሰት አስተማሪዎች እነማን እንደሆኑ በግልጽ አልተጠቀሰም። ምናልባትም እነዚህ ሰዎች ክርስቲያኖች ሊጠብቋቸው ይገባል የሚሏቸውን አንዳንድ የብሉይ ኪዳን ትምህርቶች የሚያስተምሩ አይሁዶች ሳይሆኑ አይቀሩም። ምናልባትም ደግሞ እነዚህ የሐሰት አስተማሪዎች የቀድሞዎቹ የኖስቲሲዝም ገጽታዎችን የሚያንጸባርቁ ሊሆኑ ይችላሉ። እነዚህ የኖስቲሲዝም እስተማሪዎች ከክፉ ሥጋቸው ለመገላገል የሚፈልጉ ክርስቲያኖች ሥጋቸውን እንዲጨቁኑና ከተወሰኑ ነገሮች እንዲርቁ ያስተምሩ ነበር (1ኛ ጢሞ. 4፡1-8፥ 6፡3-5፥ 20-21)። እነዚህ ሐሰተኛ አስተማሪዎች ብሉይ ኪዳንን በተሳሳተ መንገድ ይተረጉሙ ስለነበር ጳውሎስ ጢሞቴዎስ ሕጉን ማለትም ብሉይ ኪዳንን በጥንቃቄ እንዲያጠናና እንዲገነዘብ አስጠንቅቆታል (1ኛ ጢሞ. 1፡8-11)።

3) ጳውሎስ 1ኛ ጢሞቴዎስን የጻፈው ጢሞቴዎስ ቤተ ክርስቲያንን ስለሚያስተዳድርበት መንገድ መመሪያዎችን ለመስጠት ነበር። በመሆኑም የሚከተሉትን ጉዳዮች ሲዳስስ እንመለከታለን። ሀ) የጉባዔ አምልኮ (1ኛ ጢሞ. 2፡1-8)፥ ለ) ብዙ ሕዝብ በተሰበሰበበት የአምልኮ ቦታ የሴቶች ሚና ምን መሆን እንዳለበት (1ኛ ጢሞ. 2፡9-15)፤ ሐ) ለመበለቶችና ላላገቡ ሴቶች ሊደረግ ስለሚገባው እንክብካቤ (1ኛ ጢሞ. 5)፥ እና መ) ለሽምግልናና ለዲቁና የሚመረጡ ሰዎች ሊያሟሉ ስለሚገባቸው ብቃቶች ጳውሎስ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥቷል (1ኛ ጢሞ. 3፡1-13)።

4) ጢሞቴዎስ ሀ) ስደትን የማይፈራ፥ ለ) ንጹሕ ሥነ ምግባራዊ ሕይወት የሚመራና፥ ሐ) ጥንቃቄ የተሞላበትን የገንዘብ አያያዝ የሚከተል ታማኝ የወንጌል አገልጋይ እንዲሆን ለማበረታታት።

የውይይት ጥያቄ፡- እነዚህ ዕበይት ትምህርቶች ለቤተ ክርስቲያንህ ለምን እንደሚያስፈልጉ አብራራ። የ1ኛ ጢሞቴዎስ መጽሐፍ ለዲያቆናትና ለሽማግሌዎች ዛሬ ጠቃሚ የሚሆንበትን መንገድ ግለጽ?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የ1ኛ ጢሞቴዎስ በማን ተጻፈ፣ ለማን ተጻፈ፣ መቼና የት ተጻፈ

የ1ኛ ጢሞቴዎስ ጸሐፊ

የውይይት ጥያቄ፡- 1ኛ ጢሞቴዎስ 1፡1-2 አንብብ። ሀ) የመልእክቱ ጸሐፊ ማን ነው? ራሱን እንዴት ይገልጻል? ይህ ገለጻ ከሌሎች መግቢያዎች ጋር ምን ዓይነት ተመሳሳይነት ወይም ልዩነት እንዳለው ግለጽ (ለምሳሌ፥ ሮሜ 1፡1፤ ገላ. 1፡1፥ 1ኛ ቆሮ. 1፡1) ለ) የመልእክቱ ተቀባይ ማን ነበር? የተገለጸውስ እንዴት ነው?

ጳውሎስ እንደ ሌሎቹ መልእክቶቹ ሁሉ የዚህ መልእክት ጸሐፊ መሆኑን ሲገልጽ፥ «መድኃኒታችን እግዚአብሔር ተስፋችንም ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳዘዘው ትእዛዝ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነው ጳውሎስ» በማለት ገልጾአል። ምንም እንኳ ጳውሎስ የሚጽፈው በኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዲያገለግል ለላከው የቅርብ ጓደኛው ቢሆንም፥ ለጢሞቴዎስ ሐዋርያነቱን ለማስገንዘብ ፈልጓል። ምናልባትም ጳውሎስ ይህንን ያደረገው የጢሞቴዎስ አገልግሎት በቤተ ክርስቲያን አሠራር ላይ ተጽዕኖ እንደሚያስከትል ስለተገነዘበ ሳይሆን አይቀርም። የኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን ጢሞቴዎስ የራሱን ሕግጋት እየፈጠረ ሳይሆን ነገር ግን የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ከሆነውና በሥልጣን ቃል ከሚናገረው ጳውሎስ እንደተቀበለ ለማስገንዘብ ይፈልጋል።

የጳውሎስ መግቢያ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይም ያተኩራል። ጳውሎስ የኢየሱስ ክርስቶስ ተወካይ ወይም ሐዋርያ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፥ ሥልጣኑም የሚመጣው ተስፋችን ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ጳውሎስ በዚህ ጊዜ ወደ ሕይወቱ ፍጻሜ እየተቃረበ ነበር። በመሆኑም አሳቡ ይበልጥ በሰማያዊ መንግሥት ላይ ያተኮረ ይመስላል። የዘላለም ሕይወት ተስፋ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እንደ ተመሠረተ ተረድቶ ነበር። ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ካለው ግንኙነት የተነሣ እንዲሁም እግዚአብሔር አብ አዳኙ በመሆኑ ጳውሎስ ኢየሱስ ክርስቶስ በሰማይ የሚያዘጋጅለትን በረከት ለማግኘት ሙሉ ዋስትና ወይም ተስፋ ነበረው።

ጳውሎስ መልእክቱን የጻፈው ለማን ነበር።

ይህ መልእክት የተጻፈው የጳውሎስ የእምነት ልጁ ለነበረው ለጢሞቴዎስ ነበር። ከ15 ዓመታት ለሚልቁ ጊዜያት ጢሞቴዎስ ከጳውሎስ ጋር የቅርብ ጓደኛ ሆነው አገልግለዋል። ምናልባትም ግንኙነታቸው የተጀመረው በጳውሎስ የመጀመሪያው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞ ወቅት ሳይሆን አይቀርም። ከሁለተኛው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞ በኋላ ግን ጢሞቴዎስ በአብዛኛው በጳውሎስ አገልግሎት ላይ ተካፋይ ሆኖ ሠርቷል።

ጢምቴዎስ ያደገው ልስጥራ በምትባል ከተማ ነበር። አባቱ የግሪክ ሰው ነበር። በልጅነቱ ግን አይሁዳዊያን የሆኑት እናቱ ኤውንቄ እና አያቱ ሎይድ ብሉይ ኪዳንን በጥንቃቄ ያስተማሩት ይመስላል (የሐዋ. 16፡1)፡፡ ግሪኮች ግርዘት ያልሠለጠኑ ሰዎች ልማድ ነው ብለው ያስቡ ስለነበር፥ ግሪካዊ አባቱ ምናልባትም ጢሞቴዎስ በአይሁዳውያን ልማድ እንዳይገረዝ ሳይከለክለው አልቀረም። ጳውሎስ ወደ ልስጥራ በመጣ ጊዜ ጢሞቴዎስን ወደ ክርስቶስ የመራው ይመስላል። ይህም የሆነው በጳውሎስ የመጀመሪያው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞ መጨረሻ አካባቢ ነበር። ጳውሎስ ባልነበረበት አንድ ወይም ሁለት ዓመታት ውስጥ ጢሞቴዎስ ከክርስቶስ ጋር ባለው ግንኙነት አድጎ በአካባቢው ክርስቲያኖች ዘንድ የታወቀ ሆነ። ጳውሎስ በሁለተኛው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞው አካባቢ ወደ ልስጥራ ሲመጣ (50 ዓ.ም)፥ በዚህ ወጣት ልጅ ሁኔታ ተማረከ። በመሆኑም ጢሞቴዎስ የሁለተኛው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞው አጋዥ ሆኖ ከእርሱ ጋር እንዲሠራና እንዲሠለጥን ጋበዘው። ጳውሎስ ጢሞቴዎስን የመረጠው እግዚአብሔር ከሰጠው ትንቢት የተነሣ ሳይሆን አይቀርም (1ኛ ጢሞ. 1፡18፤ 4፡14)።

ጳውሎስ ልስጥራን ለቅቆ ከመሄዱ በፊት ሁለት ነገሮችን አከናውኗል። በመጀመሪያ፥ ጢሞቴዎስን አስገረዘው። ለምን ነበር ይህን ያደረገው? ጳውሎስ ጢሞቴዎስን የገረዘው ግርዘት በጢሞቴዎስ ደኅንነት ላይ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ እንዳለ በማመኑ ምክንያት አልነበረም። ቀደም ሲል ጳውሎስ በእናቱም በአባቱም ግሪክ የነበረው ቲቶ እንዳይገረዝ መከልከሉንና ግርዘት ለደኅንነት አስፈላጊ አለመሆኑን የሚገልጽ መልእክት ለገላትያ ሰዎች መላኩን ተመልክተናል። ነገር ግን ጳውሎስ የወንጌሉን እውነተኝነት በማይነካ መልኩ ቃሉን ሰምተው የሚድኑ ሰዎች እንዳይሰናከሉ መርዳት አስፈላጊ መሆኑን ያምን ነበር። በከተማይቱ ውስጥ ጳውሎስ በዋናነት የሚያገለግለው አይሁዶችን ስለሆነና ጢሞቴዎስም ከፊል አይሁድ ስለነበረ፥ አይሁዶችን ለመድረስ እንቅፋት ሊሆን የሚችለውን ነገር ለማስወገድ ሲል ጢሞቴዎስን ገረዘው። ሁለተኛ፥ ጳውሎስ እጆቹን በመጫንና በመጸለይ ጢሞቴዎስን ለአገልግሎት ላከው። እግዚአብሔር ለጢሞቴዎስ ልዩ መንፈሳዊ ስጦታ የሰጠው በዚህ ጊዜ ነበር (1ኛ ጢሞ. 4፡14፤ 2ኛ ጢሞ. 1፡6)።

ጢሞቴዎስ ለቀጣይ 15 ዓመታት የጳውሎስ የአገልግሎት ባልደረባ ሆኖ ሠርቷል። ይህንንም ያደረገው በሁለተኛና በሦስተኛ የወንጌል መልእክተኝነት አገልግሎት ላይ፥ እንዲሁም ጳውሎስ በሮም ታሥሮ በነበረበት ወቅት ነበር። ጢሞቴዎስ ከጳውሎስ ጋር የነበረ ቢሆንም፥ ጳውሎስ ወደ ተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት እየላከው ክርስቲያኖችን ያበረታታና ያነቃቃቸው ነበር። በዓመታት ውስጥ በጳውሎስና በጢሞቴዎስ መካከል ጠንካራ ግንኙነት ተመሥርቷል። ይህም በጳውሎስና በሌሎች አገልጋዮች መካከል ከነበረው ግንኙነት ሁሉ የጠነከረ ነበር። ጳውሎስ ከአብራኩ የወጡ ሥጋዊ ልጆች ስላልነበሩት፥ ጢሞቴዎስ ልክ እንደ ልጁ ሆነለት።

ጢሞቴዎስ እንደ ሐዋርያ የተቆጠረ አገልጋይ አልነበረም። ወይም ደግሞ የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን መጋቢ አልነበረም። ይልቁንም ጢሞቴዎስ የጳውሎስ አጋዥ ነበር። ብዙውን ጊዜ የጳውሎስ ልዩ ተወካይ በመሆን ወደ ተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት እየሄደ ችግሮችን ይፈታ ነበር። ስለሆነም አብያተ ክርስቲያናት ጳውሎስን እንደሚቀበሉት ሁሉ ጢሞቴዎስንም መቀበልና ማክበር ነበረባቸው (1ኛ ቆሮ. 16፡10-11)። ይህ መልእክት በተጻፈበት ወቅት ጢሞቴዎስ በኤፌሶን ከተማ ውስጥ ነበር። ምክንያቱም ጳውሎስ ጢሞቴዎስ በዚያ ያለችውን ቤተ ክርስቲያን እንዲያደራጅና የተወሰኑ አመራሮችን እንዲሰጥ ልኮት ነበር።

ጳውሎስ 1ኛ ጢሞቴዎስን በጻፈበት ወቅት ምናልባትም 60 ዓመታት ያለፉት አዛውንት ሳይሆን አልቀረም። ጢሞቴዎስ ደግሞ በ30ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ ነበር። በጥንታዊ ማኅበረሰቦች ዘንድ እንደ ወጣት መቆጠሩ የማይቀር ነበር። ምንም እንኳን ጢሞቴዎስ መንፈሳዊና እግዚአብሔር በስጦታ ያበለፀገው አገልጋይ ቢሆንም፥ ዝምተኛና ዓይናፋር የነበረ ይመስላል። ስለሆነ ጳውሎስ እንዳይፈራ ወይም እንዳያፍር ያበረታታዋል (1ኛ ቆሮ. 16፡10፤ 1ኛ ጢሞ. 4፡12፤ 2ኛ ጢሞ. 1፡7-8)። ጳውሎስ በሕይወቱ መጨረሻ አካባቢ ጢሞቴዎስ በወንጌሉና በጳውሎስ መታሠር ስላፈረ ገሥጾታል (2ኛ ጢሞ. 1፡8)።

ጳውሎስ ከመሠዋቱ ጥቂት ቀደም ብሎ፥ ሁለት የቅርብ ጓደኞቹ ማለትም ጢሞቴዎስና ዮሐንስ ማርቆስ ወደ እርሱ እንዲመጡ ጠይቋቸዋል (2ኛ ጢሞ. 4፡9)። ጢሞቴዎስ የጳውሎስ አንገት በሮማ ወታደሮች ከመቀላቱ በፊት መድረስ አለመድረሱን በመጽሐፍ ቅዱስ አልጠቀሰም። አንዳንድ ምሁራን እንደሚያስቡት ጢሞቴዎስ ሮም ከተማ በደረሰ ጊዜ ለእሥራት የተዳረገ ሲሆን በኋላ ግን ተፈትቷል (ዕብ. 13፡23)። የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከጳውሎስ ሞት በኋላ ስለነበረው የጢሞቴዎስ ሁኔታ ብዙም የሚያስረዳው ነገር የለውም። አንደኛው ታሪክ እንደሚለው ጢሞቴዎስ በመጀመሪያው ምእተ ዓመት መጨረሻ አካባቢ በመሥዋዕትነት ተገድሏል።

1ኛ ጢሞቴዎስ የተጻበፈት ዘመንና ቦታ

የውይይት ጥያቄ፡- የሐዋ. 28፡30-31 እንብብ። የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ታሪክ በሚጠናቀቅበት ጊዜ ጳውሎስ የት ነበር?

የሐዋርያት ሥራ በሚጠናቀቅበት ጊዜ ጳውሎስ በሮም ከተማ ታሥሮ ነበር። ሉቃስ እንደሚነግረን ጳውሎስ በዚያ ከተማ ውስጥ ለሁለት ዓመታት ያህል ታስሮ ቆይቷል። ሉቃስ ጳውሎስ በቅርብ ጊዜ ይፈታል የሚል ግምት የነበረው ይመስላል። የጥንታዊቷ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ የሚጠናቀቀው በዚሁ ስፍራ ነው። ለመሆኑ ጳውሎስ ከእሥራቱ ተፈትቶ ነበር? ወይስ በዚሁ ጊዜ ነበር የተገደለው? በጥንታዊ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ እርስ በርሳቸው የሚጋጩ ዘገባዎች በመገኘታቸው ምክንያት ምሁራን በእነዚህ ጥያቄዎች ላይ ይከራከራሉ። ምናልባትም ጳውሎስ በዚህ ጊዜ ተፈትቶ ሊሆን ይችላል? እንደዚያ ከሆነ ደግሞ እራተኛው የወንጌል መልእክተኝነት አገልግሎት ወደሚባለው ሌላ የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞ ሳይሄድ አይቀርም። አንዳንድ ምሁራን ጳውሎስ ከመጀመሪያው እሥራቱ በ62 ዓመተ ምሕረት እንደ ተፈታ ይናገራሉ። ጳውሎስ ወደ ስፔን ለመሄድ እንደሚፈልግ በመግለጽ ለሮሜ ከጻፈው መልእክት ለመረዳት እንደሚቻለው፥ ምናልባትም ጳውሎስ ወደ ስፔን ሄዶ ሊሆን ይችላል። ከዚያም ወደ ኋላ ወደ ምሥራቅ ተጓዘ። በ65 ዓ.ም አካባቢ ወደ ቀርጤስ ሄደ (ቲቶ 1፡5)። እዚያ ነበር ቲቶን ለአገልግሎት ትቶት የተመለሰው። ከዚያም ወደ ኤፌሶን ተጓዘ (1ኛ ጢሞ. 1፡3)። ይህ የሆነው በ66 ዓ.ም አካባቢ ሲሆን፥ ጢሞቴዎስን በዚያ ቤተ ክርስቲያን እንዲመሠርት መድቦታል። ከዚያም ጳውሎስ በ66 ዓ.ም አካባቢ ወደ ፊልጵስዩስ ሄደ (1ኛ ጢሞ. 1፡3)። ቀጥሎም ከ66-67 ባለው ጊዜ ኒቃፖሊስ ወደምትባል ከተማ ሄደ (ቲቶ 3፡12)። ከዚያ በኋላ ታስሮ ወደ ሮም ተመለሰ። በእሥር ቤት ውስጥ ከቆየ በኋላ ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ የሞት ቅጣት ተፈረደበት። ለሮም ዜጋ በሚፈጽመው የሞት ቅጣት መሠረት፥ አንገቱ በሰይፍ ተቀላ።

ጳውሎስ ወደ ኤፌሶን በደረሰ ጊዜ ጢሞቴዎስን የቤተ ክርስቲያኒቱ ኃላፊ አድርጎ ከሾመው በኋላ ወደ መቄዶኒያ ተጓዘ (1ኛ ጢሞ. 1፡3)። ምናልባትም የጢሞቴዎስ አገልግሎት ከቤተ ክርስቲያን ወደ ቤተ ክርስቲያን እየተጓዘ የሚያከናውነው የመጋቢነት ኃላፊነት ሳይሆን አይቀርም። ጳውሎስ ምናልባትም በፍጥነት ወደ ኤፌሶን እንደሚመላስ ሳያስብ አልቀረም። ነገር ግን ቶሎ ለመመለስ ባለመቻሉ ከመቄዶኒያ ሆኖ 1ኛ ጢሞቴዎስን ጻፈ። ይህም የ1ኛ ጢሞቴዎስ መልእክት ጢሞቴዎስ ሽማግሌዎችን ስለሚመርጥበትና ሌሎች የቤተ ክርስቲያኒቱን ጉዳዮች ስለሚያከናውንበት መንገድ መመሪያ የሚሰጥ መልእክት ነበር። ምናልባትም ይህ መልእክት የተጻፈው ከ66-67 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ሳይሆን አይቀርም። (ማስታወሻ፡ ጳውሎስ በ64 ዓ.ም እንደ ሞተ የሚያስቡ ሌሎች ምሁራን 1ኛ ጢሞቴዎስ በ63 ዓ.ም ሳይጻፍ አይቀርም ይላሉ።)

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የ1ኛ ጢሞቴዎስ መግቢያ

ሙላቱ የአንዲት ቤተ ክርስቲያን አባል ሲሆን፥ በመልካም መንፈሳዊ ሕይወቱ ይታወቃል። ዲያቆን ሆኖ የሚያገለግለው ይህ ወንድም የቤተ ክርስቲያኒቱ ዕለታዊ ተግባራት በትክክል መከናወናቸውን ለማረጋገጥ በሚያደርገው ጥረት የታማኝነትን አገልግሎት ያበረክታል። በየእሁድ ቤተ ክርስቲያኑን ለማጽዳት፥ ወንበሮችን ለማስተካከል፥ ወዘተ… በማለዳ ከቤተ ክርስቲያን ግቢ ይደርሳል። ሙላቱ ቤተሰቡን አፍቃሪ፥ ተንከባካቢና በመልካም ሥነ ሥርዓት የሚያስተዳድር ሰው ነበር። በሥራ ቦታም እውነተኛ ሰው በመሆኑ ተለይቶ ይታወቃል። አንድ ቀን ከሽማግሌዎቹ አንዱ ወደ እርሱ መጥቶ በሽምግልና ለመመረጥ ፈቃደኛ ይሆን እንደሆነ ጠየቀው። ሙላቱ ለዚህ ጥያቄ ምን እንደሚመልስ አላወቀም ነበር። ቀደም ሲል በትሕትናቸው የሚያውቃቸው መሪዎች በሙሉ ይህን ሥልጣን ካገኙ በኋላ በትዕቢት ሲነፉ ታዝቧል። በመሪነት አገልግሎት ውስጥ የሰዎችን ባሕሪ የሚያበላሽ አንድ ችግር እንዳለ ተገንዝቧል። በመሆኑም ለእግዚአብሔር የነበረውን ታላቅ ፍቅር የሚያበላሽ ሁኔታ እንዲፈጠር እልፈለገም። በሽምግልና ተመርጦ እያገለገለ ንጹሕ ሕይወት ሊመራ ይችል ይሆን? ሙስናን በሚያይበት ጊዜ ሌሎችን ሽማግሌዎች ቢቃወምስ? የቤተ ክርስቲያኒቱን ምእመናን በራስ ወዳድነት ፍላጎት ተነሣስቶ እንደሚያገለግል በማሰብ ስሙን ያጠፉበት ይሆን?

የውይይት ጥያቄ፡– ሀ) ብዙ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ለሽምግልና ከተመረጡ በኋላ መንፈሳዊ ባሕርያቸውን፥ አገልጋይ ሆነው የመሥራት ፍላጎታቸውንና ለሌሎች ሰዎች የነበራቸውን አክብሮት የሚያጡበትን ሁኔታ የሚያስረዱ ምሳሌዎች ስጥ። ለ) በአመራር ስፍራ ላይ ከመሆን ይልቅ ንጹህ ባህሪና መልካም ስም ይዞ መኖር የበለጠ አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው? ሐ) ብዙውን ጊዜ ሥልጣንን ማግኘት መሪዎችን ወደ ትዕቢት የሚመራቸው ለምንድን ነው?

እንደ አለመታደል ሆኖ ብዙ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች መሪነትን ልክ ዓለማውያን በሚመለከቱበት መንገድ ይገነዘባሉ። መሪ ወይም ሽማግሌ መሆን ተጨማሪ ክብርና ጥቅማ ጥቅሞችን ያስገኛል። ከዚህም የተነሣ ብዙ ሰዎች ለራስ ወዳድነት ዓላማዎች ሲሉ መሪነትን ይፈልጋሉ። ይህንኑ የመሪነት ሥልጣን ካገኙ በኋላ ወንበራቸውን ይዘው ለመቆየትና ሰዎችን በአምባገነንነት ለማዘዝ ይፈልጋሉ። የዚህ ዓይነቱ አመራር ደግሞ ለሥልጣን የሚደረጉ ሽኩቻዎችን፥ የገንዘብ ስርቆትን፥ ሙስናንና የምእመናንን ክብር ማጣትን ያስከትላል። ከዚህም የተነሣ ብዙ ሰዎች እንደ ሙላቱ ያለኝን መልካም ሕይወት ያበላሽብኛል በሚል ከአመራር ይሸሻሉ።

አዲስ ኪዳን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለ መሪነት ከዓለማዊ አሠራር የተለየ መሆን እንዳለበት ያስረዳል። አመለካከታችን ሌሎችን እንጂ ራሳችንን ወይም ቤተሰቦቻችንን ወይም የጎሳ አባሎቻችንን በማገልገሉ ላይ አጽንኦት ሊሰጥ አይገባም። ብቃቶቻችንም ከዓለም የብቃት መለኪያዎች የተለዩ መሆን አለባቸው። በመሆኑም ትኩረት ሊሰጥ የሚገባው በትምህርት ላይ ሳይሆን በመንፈሳዊነት ላይ ሊሆን ይገባል። የክርስቲያኖች የአመራር መንገድም መለየት ይኖርበታል። ይኸውም ቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔር እንጂ የእኛ እንዳልሆነች በመገንዘብ በትሕትና መከናወን አለበት። ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ እንደ አሕዛብ ተከታዮቻቸውን እንዳይመሩ አዟቸዋል። አሕዛብ በጭፍሮቻቸው ላይ ጌቶች ለመሆን ይፈልጉ ነበር (ማር. 10፡35-45)።

የ1ኛና የ2ኛ ጢሞቴዎስ እንዲሁም የቲቶ መልእክቶች ስለ አመራር ብዙ ነገሮችን ያስተምራሉ። እንደውም የመጋቢነት ትምህርቶች በመባል ይታወቃሉ። እነዚህ መልእክቶች ጳውሎስ ለሁለት የቅርብ ጓደኞቹ ማለትም ለጢሞቴዎስና ቲቶ የነበረውን የመጋቢነት ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን፥ መጋቢያን እንዴት ቤተ ክርስቲያናቸውን ሊንከባከቡ እንደሚገባ ያስተምራሉ። እነዚህ መልእክቶች የተጻፉት የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ለነበሩ ግለሰቦች እንጂ ለአብያተ ክርስቲያናት አልነበረም።

የውይይት ጥያቄ፡- ስለ 1ኛና 2ኛ ጢሞቴዎስ ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት አንብብ። ስለ ጸሐፊው፥ መልእክቱን ስለሚቀበሉት ሰዎችና ስለ መልእክቶቹ ዓላማ ከመዝገበ ቃላቱ ያገኘኸውን ጠቅለል አድርህ ጻፍ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)