1ኛ ዮሐ 5፡1-21

፩. እውነተኛ አማኞች እና አስተማሪዎች ከክርስቶስ ጋር ትክክለኛ ግንኙነት ይኖራቸዋል (1ኛ ዮሐ 5፡1-12)

አብዛኞቹ እውነቶች እንዳልተበጠሰ ሰንሰለት ናቸው። እግዚአብሔር አብን ለመውደድ ከፈለግህ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን እና እርሱንም መውደድ ይኖርብሃል። ወልድን በማመን ለአብ ያለህን ፍቅር ትገልጻለህ። በወልድ ማመንህን እና ለእርሱ ያለህን ፍቅር ደግሞ ሰዎችን በመውደድ እና የእርሱን ትእዛዛት በመፈጸም ታሳያለህ። ዓለምን ለማሸነፍ የሚያስችልህ ኃይል የሚፈልቀው ከዚሁ የማይበጠስ ሰንሰለት ውስጥ ነው። ከዚህ ሰንሰለት ውስጥ አንደኛው መገጣጠሚያ ቢበጠስ፥ ችግሮች መከሰት ይጀምራሉ። እግዚአብሔር አብን ባንወደው ወይም ባናምነው፥ በክርስቶስ ባናምን፥ ወይም በፍቅር ባንመላለስ፥ በእምነታችን ውስጥ አንድ ችግር እንደ ተከሰተ ከእነዚህ ሁሉ መረጃ ዎች መመልከት ይቻላል።

የውይይት ጥያቄ፡– ሀ) ከእነዚህ የሰንሰለቱ መገጣጠሚያዎች አንዱ ብዙ ወንጌል አማኝ ክርስቲያኖች የሚሸነፉባቸው የትኞቹ ናቸው? ለ) «ኢየሱስ ብቻ» የሚሉ የእምነት ክፍሎች የሚሸነፉት የትኛውን እውነት በመሳሳታቸው ነው?

ዮሐንስ የሚከላከለው ሐሰተኛ ትምህርት ኖስቲሲዝም በመባል ይታወቃል። ኖስቲሲዝም ክርስቶስ ፍጹም አምላክ ወይም ፍጹም ሰው እንዳልሆነ ያስተምራል። ነገር ግን ዮሐንስ ክርስቶስ ፍጹም ሰውና ፍጹም አምላክ ነው የሚሉት ሁለቱም አሳቦች ወሳኝ መሆናቸውን ይናገራል። ዮሐንስ አማኞች ክርስቶስ አምላክ እንደሆነ እንዲያምኑ፥ «ኢየሱስም የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ከሚያምን በቀር ዓለምን የሚያሸንፍ ማን ነው?» ሲል ይጠይቃል። ዮሐንስ በተጨማሪም አማኞች በክርስቶስ ፍጹም ሰብአዊነት እንዲያምኑ ያበረታታል። ዮሐንስ ይህን እውነት የገለጸው ክርስቶስ በመንፈስ፥ በውኃና በደም እንደ መጣ በመመልከት ነው። (ዮሐንስ ምናልባት በሁለት ወይም በሦስት ምስክሮች ነገር እንደሚጸና የሚናገረውን የብሉይ ኪዳን ግንዛቤ እየተጠቀመ ይሆናል። እነዚህም ሦስት ምስክሮች ክርስቶስ ሰው መሆኑን እንደሚያመለክቱ ያስረዳል።)

እነዚህን ጥቅሶች ለመረዳት ሐሰተኛ አስተማሪዎቹ ሲያስተላልፉ የነበረውን መልእክት መረዳቱ ጠቃሚ ነው። እነዚህ ሰዎች መለኮታዊ መንፈስ የሆነው ክርስቶስ በጥምቀት ጊዜ በሰብአዊው ኢየሱስ ላይ እንደ ወረደ እና ከመስቀል ላይ ሞቱ በፊት ተመልሶ እንደ ሄደ ይናገራሉ። በመስቀል ላይ የሞተው ሰብአዊው ኢየሱስ ብቻ ነው ሲሉ ያስተምራሉ። ዮሐንስ ይህንን ትምህርት በመቃወም ክርስቶስ ከጥምቀቱ እስከ ሞቱ ድረስ አምላክም ሰውም እንደ ነበር ያስረዳል። ለዚህም ሦስት ነገሮችን በምስክርነት ይጠቅሳል።

ሀ) ውኃ፡- ምሁራን ዮሐንስ ውኃ ሲል ምን ማለቱ እንደሆነ ይከራከራሉ? አንዳንዶች ይህ የክርስቶስን ሥጋዊ ውልደት ያሳያል ይላሉ። ይህም ሕጻኑ በእናቱ ማሕጸን ውስጥ ሳለ የሚኖርበትና በሚወለድበት ጊዜ የሚፈሰው ውኃ ነው ይላሉ። ሌሎች ደግሞ ይህ ኢየሱስ በተሰቀለ ጊዜ ወታደሮች ጎኑን በጦር ሲወጉ የፈሰሰውን ውኃና ደም ያመለክታል ይላሉ ( ዮሐ. 19፡34)። ዮሐንስ የሚናገረው ክርስቶስ በውኃ መጠመቁን ለማመልከት ይመስላል። በዚያን ጊዜ፥ እግዚአብሔር አብ ክርስቶስ የእርሱ ልጅ መሆኑን የገለጸ ሲሆን፥ እንደ ሰው ይፋዊ አገልግሎቱን ጀምሯል። ስለሆነም ክርስቶስ በተጠመቀ ጊዜ ፍጹም ሰውና ፍጹም አምላክ መሆኑ ታይቷል።

ለ) ደም፡- ይህ የከርስቶስን ሥጋዊ ሞት ያመለክታል። ክርስቶስ በጥምቀት ጊዜ በኢየሱስ ላይ የወረደ እና ከስቅለት በፊት የሄደ መንፈስ ብቻ አይደለም። ድነት (ደኅንነት) ሊገኝ የሚችለው የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሲሆን ብቻ ነው። ክርስቶስ እንደ ሰውና አምላክ መሞቱን የሚያረጋግጠው ደሙን በመስቀል ላይ ማፍሰሱ ነው። ዮሐንስ ክርስቶስ በተሰቀለበት ስፍራ ስለነበር፥ የክርስቶስን ደም እንደ ተመለከተ ገልጾአል።

ሐ) መንፈስ፡– ክርስቶስ በተጠመቀ ጊዜ፥ መንፈስ ቅዱስ በእርሱ ላይ ወረደ። ኢየሱስ መንፈስ ቅዱስን መቀበል የሚያስፈልገው እንደ ሰው ብቻ ነበር። እንደ አምላክ፥ ኢየሱስ የመንፈስ ቅዱስን ዓይነት ኃይል ነበረው። ስለሆነም መንፈስ ቅዱስ ወደ ክርስቶስ መምጣቱ አምላክ ብቻ ሳይሆን ፍጹም ሰው ጭምር እንደ ነበር ያመለክታል። ይኸው መንፈስ ቅዱስ ክርስቶስ ፍጹም አምላክና ሰው መሆኑን በመጽሐፍ ቅዱስ አማካይነት መመስከሩን ይቀጥላል። በአማኞች ልብ ውስጥ ይህንኑ ምስክርነት ይሰጣል።

ኢየሱስ ፍጹም ሰውና ፍጹም አምላክ መሆኑን የማያምን ማንም ቢሆን ከእግዚአብሔር ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የለውም። ዮሐንስ እንደሚያስረዳው፥ ድነት (ደኅንነት) በጠባቡ በር የሚገባበት ነው። ይህም እምነታችንን የምናሳድርበትን ቁርጥ ያለ ግንዛቤ ይጠይቃል። ስለሆነም ዮሐንስ ድነትን (እርሱ የዘላለም ሕይወት የሚለውን) የሚያገኙት በክርስቶስ የሚያምኑ ሰዎች ብቻ መሆናቸውን ይናገራል (እነዚህም ሰዎች ክርስቶስ ሰው ሆኖ ለሰው ልጆች ኃጢአት በመስቀል ላይ እንደ ሞተ የእግዚአብሔር መለኮታዊ ልጅ አድርገው ሊቀበሉት ይገባል።) ይህን እውነት ለማመን የማይፈልግ ወይም የሚያዛባ ማንም ቢሆን የዘላለም ሕይወት የሌለው እና የእግዚአብሔር ልጅ የመሆን ሥልጣን ያላገኘ መሆኑ ተገልጾአል።

የውይይት ጥያቄ፡- ዮሐንስ ሰዎች የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ክርስቶስ ማን እንደሆነ በግልጽ ሊገነዘቡ እንደሚገባ ያስረዳል። ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚገኙ ሌሎች ሐሰተኛ ትምህርቶች ምን ምን ናቸው? እነዚህ ትምህርቶች ከመጽሐፍ ቅዱስ ዐበይት ትምህርቶች ጋር የሚቃረኑበትን እና አቀንቃኞቹም ድነትን አግኝተው በመንፈስ ቅዱስ እንዳልተሞሉ የሚያሳዩበትን ሁኔታ ግለጽ።

፪. እውነተኛ አስተማሪዎች እና አማኞች የእግዚአብሔር ልጆች መሆናቸውን ያውቃሉ። ይህንንም በተቀደሰ አኗኗር ያሳያሉ (1ኛ ዮሐ 5፡13-21)

ዮሐንስ አማኞች ሊያስታውሷቸውና ተግባራዊ ሊያደርጓቸው የሚገባቸውን አንዳንድ ቁልፍ እውነቶች በመዘርዝር መልእክቱን ይደመድማል።

ሀ) ሰው ድነትና የዘላለም ሕይወት ሊያገኝ የሚችለው በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ብቻ ነው። ከዚህ ውጪ ሌላ መንገድ የለም።

ለ) እግዚአብሔር ጸሎታችንን እንደሚመልስ በድፍረት የምንተማመነው የእግዚአብሔርን ፍቃድ ስናውቅ እና እንደ ፈቃዱ ስንጸልይ ነው። ይህም ከእግዚአብሔር ጋር የቅርብ ግንኙነት ሊኖረን እንደሚገባ ያሳያል። አንዳንድ ክርስቲያኖች እግዚአብሔርን የፈለግነውን ነገር ልንጠይቀው እንደምንችል እና እርሱም የጠየቅነውን ሁሉ የመስጠት ግዴታ እንዳለበት ያስባሉ። እነዚህ ሰዎች እንደ ኢሳ. 45፡11 ያሉትንና «ጠይቁ ይሰጣችኋል» (ማቴ. 7፡7-8) የሚሉትን ጥቅሶች በተሳሳተ መንገድ ይተረጉማሉ። በእነርሱ አስተሳሰብ ማድረግ ያለብን ነገር ቢኖር እግዚአብሔር አንድን ነገር እንዲሰጠን በተደጋጋሚ መጠየቅ እንደሆነና እርሱም በዚህ ጊዜ ሊሰጠን እንደሚገደድ ያስባሉ። (ማስታወሻ፡ የኢሳይያስ 45፡11 የአማርኛው ትርጉም ይህን ያህል ጥሩ አይደለም። ትክክለኛው ትርጉም «እዘዙኝ» የሚል ሳይሆን፥ «ስለ እጆቼ ሥራ ታዙኛችሁ?» የሚል ነው።) አንዳንድ ሰዎች «ፈቃድህ ከሆነ» ብሎ መጸለይ ጥርጣሬን ያሳያል ይላሉ። ይህ እርግጥ አንዳንድ ጊዜ ጥርጣሬን ሊያሳይ ይችላል። ነገር ግን ክርስቶስ በማቴ. 6፡10 እንዳስተማረው እና ወደ መስቀል ሞት ከመሄዱ በፊት እንደ ጸለየው (ሉቃስ 22፡42)፥ ለጸሎት ወደ እግዚአብሔር በምንቀርብበት ጊዜ ፈቃዳችንን ከመሻት ይልቅ ለእርሱ ፈቃድ የመገዛት ባህሪ ሊኖረን ይገባል። መጽሐፍ ቅዱስን ብንመለከት፥ እግዚአብሔርን ምንም ነገር እንዲያደርግ ልናዘው አንችልም። እርሱ ፈጣሪያችን ነው፥ እኛም ፍጥረቱ ነን (ኢሳ. 45፡12)። እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ በልባችን ኃጢአትና፥ ራስ ወዳድነት እስካለ ድረስ ጸሎታችን እንደማይመለስ ይናገራል (ያዕ. 4፡1-3)።

እግዚአብሔር ጸሎታችንን እንደሚመልስ የምንተማመነው እንዴት ነው? ዮሐንስ በሁኔታው ውስጥ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ካወቅን እግዚአብሔር ጸሎታችን ይመልሳል ብለን ልንተማመን እንደምንችል ይናገራል። መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ነገር ሊሰጠን በግልጽ ተስፋ ከገባልንና እግዚአብሔርም ለዚያ ሁኔታ የሚፈልገው ይህንኑ እንደሆነ ካወቅን፥ በልበ ሙሉነት ልንጸልይ እንችላለን። ነገር ግን እግዚአብሔር በአንድ ሁኔታ ውስጥ ምን እንደሚፈልግ ካላወቅን፥ ልክ ክርስቶስ በጌቴሴማኒ እንደ ጸለየው «የእኔ ፈቃድ ሳይሆን የአንተ ፈቃድ ይፈጸም» በሚል የትሕትና መንፈስ መጸለይ ይኖርብናል።

ሐ) እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ለመጸለይ ምሳሌ የሚሆነን በኃጢአት፥ በተለይም ባለማመን ኃጢአት ለሚቅበዘበዙ ሰዎች አማኞች የሚቀርበው ጸሎት ይሆናል። እግዚአብሔር የራሳችን ፍላጎቶች እንዲያሟላ ብቻ ሳይሆን፥ በሌሎች ሰዎችም ሕይወት እንዲሠራ መጸለይ ይኖርብናል። ዮሐንስ «ሞት የሚገባው ኃጢአት» ሲል ምን ማለቱ እንደሆነ ምሁራን ይከራከራሉ። ምክንያቱም ዮሐንስ ስለ ምን ኃጢአት እንደሚናገር አያብራራም። ዮሐንስ የሚናገረው ስለ ዘላለማዊ ሕይወት (ድነት (ደኅንነት) ወይም ስለ ሥጋዊ ሕይወት መሆኑ አልተገለጸም። በማርቆስ 3፡28-29 እንደ ተገለጻው ስለማይሰረይ ኃጢአት ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚከተሉትን ነገሮች ልንማር እንችላለን፡

 1. መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ሰው በክርስቶስ ለማመን ፈልጎ አንድ ኃጢአት ከመፈጸሙ የተነሣ ተቀባይነትን ያጣበትን ሁኔታ አይገልጽልንም። ስለሆነም፥ አንድ ሰው በሕይወት ዘመኑ ንስሐ ከገባ እግዚአብሔር ይቅር የማይለው ኃጢአት አይኖርም።
 2. በአዲስ ኪዳን ትምህርት መሠረት፥ አንድ ሰው ከሞተ በኋላ ወደ ሲኦል የሚወርደው በኢየሱስ ክርስቶስ ካላመነ ብቻ ነው።
 3. መጸለይ የማይቻልበት ኃጢአት አንድ ሰው ክርስቶስ በሥጋ የተገለጠ የእግዚአብሔር ልጅና የድነት (ደኅንነት) መንገድ መሆኑን ሳያምን የሞተ እንደሆነ ይመስላል። ሰውየው ከሞተ በኋላ እግዚአብሔር ምሕረት እንዲያደርግለትና እንዲያድነው መጸለይ አይኖርብንም።
 4. አንዳንድ ምሁራን ዮሐንስ የሚናገረው ስለ መንፈሳዊ ሞት ሳይሆን፥ ስለ ሥጋዊ ሞት ነው ይላሉ። በመሆኑም አንድ ሰው ብዙ ልመና እየተደረገለት ለክርስቶስ ጀርባውን ሰጥቶ ሐሰተኛ ትምህርትን ቢከተል፥ ወይም የእግዚአብሔር ፈቃድ አለመሆኑን እያወቀ በኃጢአት ቢመላለስ፥ እግዚአብሔር በሥጋዊ ሞት እንደሚቀጣው ይናገራሉ። ይህም እግዚአብሔር ሐናንያንና ሰጲራን (የሐዋ. 5)፥ እንዲሁም አንዳንድ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችን እንደ ቀጣ ማለት ነው (1ኛ ቆሮ. 11፡30)። እንዲህ ዓይነት ሰው በሚታመምበት ጊዜ እግዚአብሔር እንዲለውጠው ከመጠየቅ ይልቅ ኃጢአቱን እንዲናዘዝ መጠየቅ ይኖርብናል።

መ. ዮሐንስ ዐቢይ ትምህርቱን አማኞች ሊያደርጓቸው ይገባል ባላቸው ሦስት ነገሮች ይደመድማል። በመጀመሪያ፥ የእግዚአብሔር ልጅ የሆነ ማንኛውም ሰው በልማድ ኃጢአት ውስጥ አይኖርም። ከእግዚአብሔር የተወለዱ ሰዎች ኃጢአትን ሊያሸንፉ ይችላሉ። እግዚአብሔርም ከዲያብሎስ ይጠብቀናል። ሁለተኛ፥ በክርስቶስ የምናምን ሰዎች የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ማወቅ ይኖርብናል። ነገር ግን በክርስቶስ የማያምኑና የሚያሳድዱ፥ ሰዎች በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ያሉ ናቸው። ሦስተኛ፥ የእግዚአብሔር መለኮታዊ ልጅ የሆነው ክርስቶስ በሥጋ እንደ ተገለጠ ማወቅ አለብን። እርሱ እውነተኛ አምላክና የዘላለም ሕይወት ምንጭ ነው።

ሠ. አማኞች እንደ መሆናችን፥ ሕይወታችንን ከጣዖት አምልኮ መጠበቅ አለብን ምንም እንኳን ዮሐንስ ይህን ሲል ከእንጨትና ድንጋይ የተሠሩትን ጣዖታት ማመልከቱ ሊሆን ቢችልም፥ በአእምሮ ውስጥ ከዚህ የሰፋ አሳብ ሊኖር ይችላል። ከእግዚአብሔር በላይ የምወደው ማንኛውም ነገር ጣዖት ነው። ቤተሰባችንን፥ ሀብታችንን፥ ትምህርታችንን፥ ሥራችንን ከእግዚአብሔር አብልጠን ከወደድን፥ ያ ነገር ጣዖታችን ነው ማለት ነው። አንድን ነገር ከእግዚአብሔር አብልጠን መውደዳችንና ከዚህም የተነሣ ጣዖት እንደሆነብን በምን እናውቃለን? እግዚአብሔርን በእነዚያ ነገሮች ዙሪያ መታዘዝ አለመታዘዛችንን ራሳችንን ጠይቀን መረዳት አለብን። ለአንዲት ዓለማዊ ልጅ ያለን ፍቅር እንድናገባት የሚያስገድደን ከሆነ፥ ጣዖታችን ሆናለች ማለት ነው። ገንዘብ የማግኘት ፍላጎታችን ጉቦ እንድንሰጥ ካስገደደን፥ ገንዘብ ጠዖታችን ሆኗል ማለት ነው። በትምህርትና በደረጃ ከፍ የማለት ፍላጎታችን በፈተና ላይ እንድናጭበረብር ካደረገን፥ ትምህርት ጣዖታችን ሆኗል ማለት ነው። ዮሐንስ ልባችንን በመመርመር ከእግዚአብሔር አብልጠን የምንወደው ነገር እንዳለ እንድንመለከት ያስጠነቅቀናል።

ከአብዛኞቹ መልእክቶች በተቃራኒ፥ ዮሐንስ መልእክቱን የሚጨርሰው በስንብት ሰላምታ፥ የሰዎችን ሰላምታ በማስተላለፍ ወይም በቡራኬ አይደለም። ዮሐንስ ኃይለኛ መልእክቱን የሚደመድመው በዚህ ትእዛዝ ነው፣ “ልጆች ሆይ፥ ከጣዖታት ራሳችሁን ጠብቁ።”

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በአንድ አማኝ ሕይወት ውስጥ ጣዖታት ሊሆኑ የሚችሉትን ሌሎች ነገሮች ዘርዝር። ለ) ሕይወትህን መርምር። በሕይወትህ ውስጥ ጣዖት አለን? ከሆነ፥ የጣዖት አምላኪነት ኃጢአትህን ተናዘዝና ክርስቶስን በሙሉ ልብህ ወደ ማፍቀር ተመለስ። ሐ) ከ1ኛ ዮሐንስ ጥናት ያገኘሃቸው አስፈላጊ ትምህርቶች ምን ምን ናቸው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

1ኛ ዮሐ 4፡1-21

፩. እውነተኛ አስተማሪዎችና አማኞች በተለይ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ አስተምህሮን ይከተላሉ (1ኛ ዮሐ 4፡1-8)

“ወዳጆች ሆይ፥ መንፈስን ሁሉ አትመኑ። ነገር ግን መናፍስት ከእግዚአብሔር ሆነው እንደሆነ መርምሩ ብዙዎች ሐሰተኞች ነቢያት ወደ ዓለም መጥተዋል” (1ኛ ዮሐ 4፡1)። ብዙውን ጊዜ ጥያቄ ማንሣት ወይም አንድን ነገር መገምገም የዐመፀኝነት ወይም የእምነት ማጣት ምልክት ነው ብለን እናስባለን። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ነገር ከእግዚአብሔር ወይም ከሰይጣን መሆኑን ለማወቅ በሚገባ እንድንገመግም፥ እንድንፈትን በተደጋጋሚ ያዝዘናል። ይህ ትእዛዝ የተሰጠው ለቤተ ክርስቲያን መሪዎች ብቻ አይደለም። አማኞች ሁሉ ከቤተ ክርስቲያን ስብከት፥ ከጓደኞቻቸው፥ ከካሴቶችና ከቪዲዮዎች፥ ከመጻሕፍት፥ ወዘተ.. የሚተላለፈውን መልእክት የመገምገም ኃላፊነት አለባቸው። አንድ ሰው ሐሰተኛ ትምህርት በሚያምንበት ጊዜ፥ የኋላ ኋላ ኃላፊነትን የሚወስደው ራሱ ነው። ምንም እንኳን እግዚአብሔር የቤተ ክርስቲያን መሪዎች መንጋውን ባያስተምሩ ወይ ባይጠብቁ በኃላፊነት የሚጠይቃቸው ቢሆንም፥ ነገሮችን የመገምገም የመጨረሻው ኃላፊነት የሚውለው በእያንዳንዱ ግለሰብ ላይ ነው። ለመሆኑ አንድ ነገር ከእግዚአብሔር ወይም ከሰይጣን መሆኑን ለማወቅ የምንመረምረው ወይም የምንገመግመው እንዴት ነው? ይህ የዮሐንስ መልእክት የመጨረሻው ክፍል ይህን በተመለከተ አንዳንድ አሳቦችን ይሰጠናል።

ሀ) አንድ ሰው ከእግዚአብሔር መሆኑን ያለመሆኑን የምንገመግመው ያቀረበው ትምህርት ከእግዚአብሔር ቃል ጋር መስማማት ያለመስማማቱን በመመልከት ነው። በዮሐንስ ዘመን፥ የክርስቶስን ማንነት የሚጠራጠር ሐሰተኛ ትምህርት ተሰጥቶ ነበር። ይህ ሐሰተኛ ትምህርት ክርስቶስ ፍጹም አምላክ አይደለም ብሎ ያስተምር ነበር። ሌሎች ደግሞ ፍጹም ሰው አይደለም ብለው ያስተምሩ ነበር። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ የቀረበውን ትምህርት የሚቃረን መልእክት የሚያቀርብ ማንኛውም ሰው ይህንኑ አሳብ ያገኘው ከክርስቶስ ተቃዋሚዎች ሁሉ በስተጀርባ ከሚሠራው ሰይጣን ነው። (በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የቀረበውን ግልጽ ትምህርት ከሚጻረሩ አሳቦች መካከል የሚከተሉት ለአብነት ሊጠቀሱ ይችላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ስሕተት የሌለው የእግዚአብሔር ቃል አለመሆኑን፥ ክርስቶስ ብቸኛ አዳኝ ሰውና አምላክ አለመሆኑን፥ ብሎም የሥላሴ አለመኖርን፥ በተጨማሪም ድነት (ደኅንነት)፥ በልሳን መናገር፥ በጥምቀት ወይም አንዳች ተግባር በማከናወን መሆኑን፥ የመጽሐፍ ቅዱስን ግልጽ መልእክቶች በመጻረር ማስተማር ነው።)

ለ) የግለሰቡን ባህሪ በማጥናት ለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን መሪዎችና ለእግዚአብሔር ቃል እውነት የሚሰጡትን ግምት በመገምገም አንድ ሰው ከእግዚአብሔር እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ እንለያለን። ዮሐንስ ከእግዚአብሔር የተወለዱ ሰዎች «እኛን» ይሰሙናል ይላል። ይህም ዮሐንስን እና ሐዋርያትን፥ እንዲሁም መንፈስ ቅዱስ የመረጣቸውን መሪዎች የሚያመለክት ነው። ከክርስቶስ ወደ ሐዋርያት፥ ከዚያም በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ሁሉ እያለፈ እስከ ዛሬ የደረሰ የእውነት መሥመር አለ። ይህም እውነት በአዲስ ኪዳን ውስጥ የሚገኝ ነው። አንድ ነገር እውነት ወይም ውሸት መሆኑን ለመገምገም ትልቁ ምንጭ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። እግዚአብሔር በተጨማሪም የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እውነትን እንዲጠብቁ ኀላፊነት ሰጥቷቸዋል። ይህም ማለት የቤተ ክርስቲያኑ ልጆች የእግዚአብሔርን ቃል በማጥናት እና የእግዚአብሔርን እውነት በማወቅ ራሳቸውን በጥንቃቄ እንዲዘጋጁ ማድረግ አለበት ማለት ነው። ቃሉን ካላጠኑ፥ እግዚአብሔር የሰጣቸውን ይህን ወሳኝ አገልግሎት ሊያከናውኑ አይችሉም። በተጨማሪም፥ ይህ ማለት የቤተ ክርስቲያን አባላት እውነት ናቸው ብለው የሚያስቧቸውን አዳዲስ ትምህርት በሳል መንፈሳዊ መሪዎችን ሳያማክሩ መቀበል የለባቸውም ማለት ነው። መሪዎቻችንን እና መሪዎቻችን አንድ ትምህርት ከእግዚአብሔር ቃል ጋር መስማማት ያለመስማማቱን እንዲመረምሩ ኃይል የሚሰጣቸውን መንፈስ ቅዱስ ማክበር ይኖርብናል። ሽማግሌዎቹ ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል በግልጽ እስካልጣሱ ድረስ አባላት በመሪዎች ላይ ማመጻቸው የእግዚአብሔር ፈቃድ አይደለም።

፪. እውነተኛ አስተማሪዎች እና አማኞች ሌሎች አማኞችን በመውደድ ለእግዚአብሔር ያላቸውን ፍቅር ያሳያሉ (1ኛ ዮሐ. 4፡9-21)

ሐሰተኛ አስተማሪዎች ብዙውን ጊዜ ከሚታወቁባቸው መንገዶች አንዱ ከትምህርታቸው የተነሣ በአማኞች ኅብረት ውስጥ የሚከሰተውን ሁኔታ በመመልከት ነው። ብዙውን ጊዜ እነዚህ ሐሰተኛ አስተማሪዎች ስለ ሌሎች ወይም ስለ ክርስቲያናዊ አንድነት ግድ የላቸውም። የሚያሳስባቸው ሕዝቡ ትምህርታቸውን መቀበሉ ብቻ ነው። በመሆኑም ዮሐንስ፥ ሐሰተኛ አስተማሪዎችን ለይተን ከምናወቅባቸው ዐበይት መንገዶች አንዱ ከራሳቸው ይልቅ ሌሎች የተሻለ መንገድ እንዲያስቡ በማሰብ በፍቅር እና በርኅራኄ የተሞላ ሕይወት መምራታቸውን ማጤን እንደሆነ ይናገራል። እነዚህ ሰዎች በአማኞች መካከል ከትችት ይልቅ የፍቅርን እና የመቀባበልን መንፈስ እየፈጠሩ ናቸው? ከእግዚአብሔር ከተላኩ፥ ከትምህርታቸውና ከተግባራቸው በስተጀርባ ፍቅር ማቆጥቆጥ አለበት። ትምህርታቸው ከመንፈስ ቅዱስ ከሆነ በአማኞች መካከል ከክፍፍል ይልቅ ፍቅር እና አንድነትን ማስፋፋት ይኖርበታል።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ተስፋን በከርስቶስ ዳግም ምጽአት ላይ መጣል እና እርስ በእርስ መዋደድ (1ኛ ዮሐ. 2፡28-3፡24)

፩. የእግዚአብሔር ልጆች ተስፋችንን በከርስቶስ ዳግም ምጽእት ላይ መጣል አለብን። ይህም ወደ ጽድቅ ኑሮ ይመራናል (1ኛ ዮሐ. 2፡28-3፡10)።

ዓለም ሰዎች መሆናችንን ብቻ ትገነዘባለች። ነገር ግን እኛ ማን ነን? ዮሐንስ የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ይናገራል። ለመቼውም ቢሆን ይህንን ታላቅ እውነት መዘንጋት የለብንም። ምንም እንኳን ዛሬ ብዙም የተለየን መስለን ባንታይም፥ ወደፊት እጅግ የተለየን ሰዎች እንሆናለን። ዮሐንስ አማኞች ስለ ወደፊቱ እንዲያስቡና የክርስቶስን ዳግም ምጽአት በናፍቆት እንዲጠባበቁ ያበረታታል። ወደፊትን አሻግረን የምንመለከትና ዳግም ለሚመለሰው ክርስቶስ ክብርን በሚያመጣ መልኩ ሕይወታችንን የምንመራ ከሆነ ሁለት ነገሮች ይፈጸማሉ። በመጀመሪያ፥ የክርስቶስ ዳግም ምጽአት ፍርሀትን ወይም ኀፍረትን ሳይሆን፥ ልበ ሙሉነትን ያጎናጽፈናል። ሁለተኛ፥ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ስለሆነና እኛም የእግዚአብሔር ልጆች ስለሆንን (ከእግዚአብሔር ስለተወለድን)፥ እርስ በርሳችን እንመሳሰላለን። ክርስቶስ ዳግም ሲመለስ፥ እኛም እንደ እርሱ እንሆናለን። ዮሐንስ ይህን ሲል ውጫዊ መልካችንን ማለቱ ሳይሆን፥ ልባችንንና ባህሪያችንን ማመልከቱ ነው። በጽድቅ ለመኖር ስንሻ እዚሁ በምድር ላይ የለውጥን ሂደት እንጀምራለን። ይህም ለውጥ ክርስቶስ ዳግም ሲመለስና ሙሉ በሙሉ እርሱን ስንመስል የተሟላ ይሆናል።

ነገር ግን በዚያን ጊዜ ክርስቶስን እንመስል ዘንድ አሁን መለወጥ ይኖርብናል። የልማድ ኃጢአት መፈጸማችንን ማቆም አለብን። ባለማቋረጥ ኃጢአት እየፈጸመ የሚኖር ሰው የእግዚአብሔር ልጅ አለመሆኑን ያረጋግጣል። እንዲህ ዓይነቱ ሰው የሰይጣን ተከታይ ነው። ይህም ከሰይጣን ጎን በመሰለፍ የክርስቶስን ቅጣት እንዲቀበሉ ያደርጋቸዋል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የክርስቶስን ዳግም ምጽአት መጠባበቅ ዛሬ በቅድስና እንድንመላለስ የሚያግዘን እንዴት ነው? ለ) አንድ ቀን ክርስቶስን እንደምንመስልና ከኃጢአት ባህሪ ነፃ እንደምንወጣ ማወቃችን እንዴት እንደሚያበረታታን ግለጽ።

፪. የእግዚአብሔር ልጆች እርስ በርሳቸው በመዋደድ አንድነትን ይጠብቃሉ (1ኛ ዮሐ 3፡11-24)።

በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በመሪዎችም ሆነ በታዋቂ አባላት መካከል ተቃራኒ አሳቦች በሚሰነዘሩበት ጊዜ በአብዛኛው የስሜት መጎዳቶችና ክፍፍሎች ይከሰታሉ። ሰዎች በአንድ ጉዳይ ላይ መስማማት በማይችሉበት ጊዜ ክፍፍል ይፈጠራል። ከዚያም አንዱ ሌላውን መተቸት ይጀምራል። ትክክል ያልሆኑ መነሻ አሳቦችንም መገመት ይጀምራል። በዚህም ጊዜ ቤተሰቦችና ጓደኞች ከሚደግፉት ወገን ጎን በመሰለፍ ክፍፍልን ያስከትላሉ። ብዙም ሳይቆይ ጠቅላላይቱ ቤተ ክርስቲያን በተከፋፈሉት ሰዎች ትሞላለች። ብዙውን ጊዜ እንደዚህ ዓይነቱ ሁኔታ በሚከሰትበት ጊዜ ክፍፍሉ ከመንሥኤ ጉዳዩ እልፍ ብሎ የክፍፍሉን ተሳታፊዎች የሚመለከት ይሆናል። ይህ በትንሹ እስያ ውስጥ በነበሩት አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ የተከሰተ ይመስላል። መሪዎች በተለያዩ ጉዳዮች ላይ አለመስማማት ሲጀምሩ፥ የቃላት ጦርነት ገጠሙ። ብዙም ሳይቆይ ከፍተኛ የሆኑ ክፍፍሎች ተከሰቱ።

ተቃራኒ አሳቦች በሚኖሩበት ጊዜ (በተለይም ሐሰተኛ ትምህርት ወይም አዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ወደ ቤተ ክርስቲያን በሚመጣበት ጊዜ)። ሰይጣን ክፍፍልን ለማምጣት ይሞክራል። ይህን በሚያደርግበት ጊዜ የተባበረች ቤተ ክርስቲያን ጠንካራ በመሆንዋ ሊያሸንፋት አይችልም። የተከፋፈለች ቤተ ክርስቲያን ደካማ ስለሆነች፥ ሰይጣን ብዙ ሰዎችን በግጭቱ አማካይነት ሊያጠፋ ይችላል። ስለሆነም፥ ስለ ሐሰተኛ ትምህርት በሚጽፍበት ጊዜ፥ ዮሐንስ የፍቅርን ጉዳይ ያነሣል። ዮሐንስ ፍቅርን ከጥላቻ ጋር ሲያነጻጽር እንመለከታለን። ጥላቻ የቃየልን መንገድ ይከተላል። ቃየል በወንድሙ ላይ ስለቀናና እግዚአብሔርን በልቡ ለማዳመጥ ስላልፈለገ፥ ወንድሙን አቤልን ገድሎታል። በተመሳሳይ ሁኔታ፥ እግዚአብሔርን ለመስማት የማይፈልጉ ዓለማውያን እማኞችን በመጥላት ያሳድዷቸዋል። ይህም አንዳንድ ጊዜ እማኞችን እንዲገድሉ ያደርጋቸዋል። ነገር ግን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ትዕቢትና ቅንአት አማኞች የሌሎች አማኞችን ዝና፥ አገልግሎት፥ ግንኙነት፥ ወዘተ… እንዲገድሉ ማድረጉ የበለጠ አሳዛኝ ነው።

የእግዚአብሔር ልጆች እግዚአብሔርን መምሰል ይኖርባቸዋል። በማንስማማበት ጊዜ እንኳን እርስ በርሳችን መዋደድ ይኖርብናል። ፍቅር እሳትን እንደሚያጠፋ ውኃ ነው። ፍቅር የትዕቢትና የራስ ወዳድነት ተቃራኒ በመሆኑ፥ የጥላቻን ሥር ያጠፋዋል። ዮሐንስ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን በምሳሌነት ይጠቅሳል። አምላክ የነበረው ክርስቶስ ከፍቅሩ የተነሣ ሁሉንም በረከት ትቶ ስለ እኛ ሞቷል። በትሕትናና ሌሎችን በማገልገሉ ረገድ ክርስቶስን መምሰል ይኖርብናል። ይህ ፍቅር እራሱን በተለያዩ መንገዶች ይገልጻል። በመጀመሪያ፥ አንድ ግለሰብ በእምነት ወንድሙ ለሆነው ሰው ሕይወቱን አሳልፎ በሚሰጥበት ጊዜ ፍቅር ይገለጣል። ምንም እንኳን ይህ ለሌላ ሰው ብሎ መሞትን የሚያመለክት ቢሆንም፥ ዮሐንስ በተምሳሌትነት የሚናገረው ለሌላው ሰው ስንል ለዝናችን፥ ለአሳባችን ወይም ለምንመርጠው ነገር ስለመሞታችን ነው። ዋነኛው እውነት ግልጽ በማይሆንበት ሁኔታ ውስጥ በምንሆንበት ጊዜ፥ ከእነርሱ ጋር ባልስማማም እንኳን እነ እገሌን ለመርዳት ምን ማድረግ አለብኝ? የሚለው ጥያቄ ቀዳሚውን ስፍራ ሊይዝ ይገባዋል። ሁለተኛ፥ ፍቅር ለመኖር የሚያስፈልጓቸው ነገሮች የሌላቸውን ሰዎች ለመርዳት የሚችልበትን መንገድ በመፈለግ ራሱን ይገልጻል። የእነዚህ ሰዎች ችግር እንደ ገንዘብ፥ ምግብ ወይም ሥራ ዓይነት ቁሳዊ ነገር ሊሆን ይችላል። ወይም እንደ ጓደኝነትና ተቀባይነት ያለ ስሜታዊ ጉዳይ ሊሆን ይችላል። ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉት ሰዎች የተለያዩ ፍላጎቶች አሏቸው። ፍቅር በሚኖርበት ጊዜ የቤተ ክርስቲያን አባላት እርስ በርሳቸው ይረዳዳሉ።

የክርስቲያኖች እርስ በርስ መዋደድ እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ፥ ዮሐንስ በሐሰተኛ አስተማሪዎችና በራሳችን እምነት እውነተኛነት መካከል ለመለየት ከሚያስችሉ መንገዶች ይህ ዋነኛው እንደሆነ ይናገራል። ሰዎችን የማንወድ ከሆነ፥ የፍቅር አምላክ የሆነው እግዚአብሔር ከልባችን ውስጥ መኖሩ አጠራጣሪ ይሆናል። የፍቅር ሕይወት ሁለት ነገሮችን ያደርጋል። በመጀመሪያ፥ እውነተኛ ፍቅር የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ለልባችን ያረጋግጥልናል። እንደሚገባን ሰዎችን ልንወድ የምንችለው በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ብቻ ነውና። ሁለተኛ፥ በሕይወታችን ውስጥ ያለ ፍቅር ከእግዚአብሔር ጋር ትክክለኛ ግንኙነት እንዳለንና ከዚህም የተነሣ እግዚአብሔር ጸሎታችን እንደሚመልስ ያሳያል። (ማስታወሻ፡ በፍቅር ቁጥጥር ሥር የዋለ ሕይወት ብዙውን ጊዜ የሚጸልየው ከራስ ይልቅ ለሌሎች ነው፡፡ ከዚህም የተነሣ፥ እግዚአብሔር እነዚህን ጸሎቶች ለመመለስ ደስ ይሰኛል። ነገር ግን ብዙውን ጊዜ ለግል ፍላጎቶቻችን የምንጸልይ ከሆነ፥ ጸሎቶቻችን ራስ ወዳድነት ያጠቃቸዋል። እግዚአብሔርም በአብዛኛው እነዚህን ጸሎቶች አይመልስም።)

ዮሐንስ እግዚአብሔር የአማኞችን ጸሎት የሚመልሰው አራት ነገሮች ከተሟሉ እንደሆነ ይናገራል፡- ሀ) በክርስቶስ በማመን ግላዊ ግንኙነትን መመሥረት፥ ለ) ክርስቶስ ለሰጠን ትእዛዛት መታዘዝ፥ ሐ) ሌሎችን የምናገለግልበት የፍቅር ሕይወት እና መ) ከክርስቶስ ጋር የሚደረግ ሕያውና የጥገኝነት ግንኙነት። የተሟሟቀ የጥገኝነት ግንኙነት እንዳለ የምናውቀው መንፈስ ቅዱስ በሕይወታችን ውስጥ ስላለና ለመንፈሳችን ስለሚመሰክር ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በራስህ ቤተ ክርስቲያን ወይም አንተ በምታውቀው ሌላ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተከሰተን አንድ አለመግባባት አስብ። አለመስማማቱን የፈጠረው መሠረታዊ ችግር ምን ነበር? ለ) ሰዎች ስለ እርስ በርሳቸው በሚነጋገሩበት ወቅት ጥላቻና ግድያ የተከሰተው እንዴት ነበር? ይህ ሁኔታ አለመግባባቱን እንዴት እንዳባባሰው ግለጽ። ሐ) በዚህ ሁኔታ ውስጥ እውነተኛ ፍቅር ቢኖር ኖሮ የተለያዩ ሰዎች የሰጡት ምላሽ እንዴት የተለየ ሊሆን ይችል ነበር? መ) እነዚህ ጥቅሶች እምብዛም ፍቅር ስለማይታይባቸው አብያተ ክርስቲያኖቻችን የሚያስተላልፉአቸው ጠንካራ ማስጠንቀቂያዎች ምንድን ናቸው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የእግዚአብሔር ልጆች የሰይጣንን ውሸት ከማመን ይልቅ እውነትን መጠበቅ ይኖርባቸዋል (1ኛ ዮሐ 2፡18-27)።

ምንም እንኳ ይህ የ1ኛ ዮሐንስ መልእክት ክፍል እንዴት ለእግዚአብሔር መኖር እንዳለብን የሚያመለክት ተግባራዊ ትምህርት ቢሆንም፥ ቀዳሚ ትኩረቱ ግን በሐሰተኛ ትምህርቶች በምንከበብበት ጊዜ እንዴት ለእውነት መኖር እንዳለብን ማሳየት ነው።

ዮሐንስ በመጨረሻው ሰዓት ወይም ክርስቶስ ሊመለስ ሲል ከሚከሰቱት ነገሮች አንዱ የሐሰተኛ ትምህርቶች መበራከት መሆኑን ይናገራል። ዮሐንስ ሁለት ዓይነት የክርስቶስ ተቃዋሚዎች (ሐሳዊ መሲሆች) እንዳሉ ይገልጻል። የመጀመሪያው፥ የክርስቶስ ተቃዋሚ ነው። ዮሐንስ ይህን ሲል ክርስቶስ ሊመለስ ሲል ዓለምን ለመግዛትና የእግዚአብሔርን ሕዝብ ለማጥፋት ሰይጣን የሚሾመውን ዋነኛ ክፉ የዓለም ገዢ ማለቱ ነው (ራእይ 13፡1-8)። ሁለተኛ፥ ሌሎች ብዙ የክርስቶስ ተቃዋሚዎች ይኖራሉ። ይህ በሰይጣን ኃይል እውነትን የሚዋጉትን ሁሉ ያጠቃልላል። ይህም ሐሰተኛ አስተማሪን ሊያመለክት ይችላል። ዮሐንስ በጠቀሰው ምሳሌ ውስጥ ይህንን መመልከት ይቻላል። ወይም ደግሞ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ለማጥፋት የሚጥረውን የፖለቲካ መሪ ሊያመለክት ይችላል። ለምሳሌ ያህል፥ ሙሶሎኒ የክርስቶስ ተቃዋሚ ነው ማለት ይቻላል። ሰዎች ከርስቶስን ሳይሆን የክርስቶስን ተቃዋሚ እንደሚከተሉ የሚያሳየው ምንድን ነው?

ሀ) ከእውነተኛ አማኞች መለየታቸው። ከሐሰተኛ አስተማሪዎች የተነሣ አንዳንድ ሰዎች ቤተ ክርስቲያንን የለቀቁ ይመስላል። ዮሐንስ እነዚህ ሰዎች የለቀቁት ቀድሞውንም የሚያድን እምነት ስላልነበራቸውና የክርስቶስ አካል ባለመሆናቸው ነው ይላል።

ለ) እነዚህ ሰዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የማይስማማ የተሳሳተ ትምህርት ያስተምሩ ነበር። በዮሐንስ ዘመን ክርስቶስ በሥጋ የተገለጠ አምላክ መሆኑን ክደዋል። ዮሐንስ እንዲህ ዓይነቱን መሠረታዊ እውነት መካድ ክርስቶስን ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔር አብንም መካዳቸውን የሚያረጋግጥ መሆኑን ይናገራል። በዛሬው ዘመናችን እነዚህ መሠረታዊ እውነቶች እንደ ሥላሴ፥ የድነት መንገድ (በጥረታችን የእግዚአብሔርን ሞገስ የምናገኝበት ሳይሆን ዳሩ ግን በክርስቶስ በማመን የምንቀበለው የእግዚአብሔር ስጦታ)፥ ድነት የሚገኘው በክርስቶስ ብቻ ወይም በሌሎች ሃይማኖቶች ጭምር የሚሉ ይሆናሉ። ሐሰተኛ ትምህርት በሚገጥመን ጊዜ ምላሻችን ምን ይሆናል? በመጀመሪያ፥ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ሁሉ ውስጥ አልፈው ወደ እኛ በደረሱት የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ላይ አጽንኦት መስጠት ይኖርብናል። እነዚህ እውነቶች በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ይገኛሉ። ሁለተኛ፥ መንፈስ ቅዱስን መተማመን አለብን። በግል፥ በተለይም በክርስቶስ አካል ውስጥ መንፈስ ቅዱስ ሰዎች ከእውነት ወደ ሰይጣን ውሸቶች የሚቅበዘበዙባቸውን መንገዶች ለአማኞች ይገልጻል።

(ማስታወሻ፡- አንዳንድ ጊዜ ክርስቲያኖች ዮሐንስ በዚህ ስፍራ መንፈስ ቅዱስ ያስተምራቸዋል ሲል ምን ማለቱ እንደሆነ በትክክል ሳይረዱ ይቀራሉ። ዮሐንስ ይህን ሊል በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አስተማሪዎች አያስፈልጉንም ማለቱ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪዎች የሚያስፈልጉ መሆናቸውን በተደጋጋሚ ይገልጻል። እንዲያውም፥ ይህ መንፈስ ቅዱስ አንዳንድ አማኞች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዲያገለግሉ የሚሰጣቸው ቁልፍ መንፈሳዊ ስጦታ ነው (ማቴ. 28፡20፤ 1ኛ ቆሮ. 12፡28፥ ኤፌ. 4፡11፤ ቆላ. 3፡16)። ስለሆነም፥ እግዚአብሔር በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እውነትን እንዲያስተምሩ፥ በስጦታዎች ያበለጸጋቸውን ሰዎች ማዳመጥ ይኖርብናል። ይህ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የለብንም ማለትም አይደለም። ይህም የእግዚአብሔርን እውነት እንጂ ከመንፈስ ቅዱስ እንዲመጣ የሚያስቡትን የራሳቸውን አሳብ እንዳያስተምሩ ይረዳቸዋል (2ኛ ጢሞ. 3፡16-17)።

ይህ ክፍል የተመሠረተው ሐሰተኛ አስተማሪዎች በሚያስተምሩት አሳብ ላይ ነው። እነዚህ ሰዎች ሐዋርያት ወይም መንፈስ ቅዱስ ከሚያስተምረው የበለጠ ልዩ ምሥጢራዊ እውቀት እንዳላቸው ይናገሩ ነበር። ዮሐንስ በሚጽፍላቸው ክርስቲያኖች ለማስተማር የፈለጉት ይህንኑ ምሥጢራዊ እውቀት ነበር። እግዚአብሔር ከገለጠው ውጭ ክርስቲያኖች የሆነ ምሥጢራዊ እውቀት መሻት የለባቸውም። አማኞች በልባችን ውስጥ መንፈስ ቅዱስ አለን። እርሱም ወደ እውነት ሁሉ ይመራናል። መንፈስ ቅዱስ ሁሉን አማኞችን ለማስተማር የሚጠቀምበት ዋነኛው መሣሪያ ደግሞ የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ አንድን አዲስ ነገር ከመፈለግ ይልቅ መንፈስ ቅዱስ ከጻፈው መጽሐፍ ውስጥ እንዲያስተምረን መፍቀድ አለብን። ሁሉም አማኝ የሚያስተምረው መንፈስ ቅዱስ በውስጡ እንዳደረበት ቢታወቅም፥ ሰይጣን አንድን አማኝ በቀላሉ ሊያስት ስለሚችል መንፈስ ቅዱስ በአማኞች መካከል የሚሰጠውን ትምህርት መከታተሉ ጠቃሚ ነው። አማኞች መንፈስ ቅዱስ እያስተማራቸውና ወደ እውነት ሁሉ እየመራቸው እንዳለ የሚያውቁት የመንፈስ ኅብረት ሲኖራቸውና የእግዚአብሔርን ቃል በተሟሟቀ ሁኔታ በሚያጠኑበት ጊዜ ነው። የእግዚአብሔርን ቃል በጥንቃቄ በምታጠና ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያላስቀመጠው አሳብ ክፍፍል በሚፈጥርበት ጊዜ፥ ይህ በተለምዶ ከመንፈስ ቅዱስ ስለማይሆን ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ሐሰተኛ አስተማሪዎች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ክፍፍል ሲፈጥሩ የተመለከትክበትን ሁኔታ ግለጽ። ለ) ዮሐ 17 አንብብ። በዚህ ክፍል ውስጥ ክርስቶስ የጸለየውና ዛሬም መንፈስ ቅዱስ ሕይወታችንን ሊያዛምድበት የሚፈልገው እውነት ምንድን ነው? ሐ) አንዳንድ ክርስቲያኖች መንፈስ ቅዱስ በውስጣቸው ስላለ ሰዎች እንዲያስተምሯቸው ወይም የእግዚአብሔርን ቃል መማር እንደማያስፈልጋቸው ሲናገሩ ሰምተህ ታውቃለህ? ይህ ጤናማ አመለካከት ነው? ለምን? መ) 2ኛ ጴጥ. 1፡20-21፤ 2ኛ ጢሞ. 3፡16–17 አንብብ። እነዚህ ጥቅሶች መንፈስ ቅዱስ መጽሐፍ ቅዱስን እንደ ጻፈ ብቻ ሳይሆን፥ መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ሰዎችን ለማረም፥ ለመገሠጽ፥ እና በጽድቅ ለማሠልጠን፥ ወዘተ… የሚጠቀምበት መሣሪያ መሆኑንም ያስረዳሉ። መንፈስ ቅዱስና መጽሐፍ ቅዱስ በስሕተት እንዳንወድቅ እውነትን በማስተማሩ በኩል ለእኛ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ምንድን ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት ማድረግ ሌሎች አማኞችን መውደድን እና የዓለምን የአኗኗር ዘይቤ አለመውደድን ይጠይቃል (1ኛ ዮሐ 2፡7-17)

፩. ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት ማድረግ ሌሎች አማኞችን መውደድን ይጠይቃል (1ኛ ዮሐ 2፡7-14)

የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ከምናሳይባቸው መንገዶች አንዱ ከሌሎች አማኞች ጋር ያለን ግንኙነት ነው። በቤተሰብ ውስጥ የሁለት ልጆች መጣላት የተቀሩትን የቤተሰብ አባላት እንደሚነካ ሁሉ፥ በአማኞች መካከል የሚካሄድ ጸብ ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸውን ግንኙነት ይጎዳዋል። ዮሐንስ በአማኞች መካከል ያለውን ግንኙነት «ፍቅር» በሚል ቃል ይገልጸዋል። ዮሐንስ ይህን ሲል ስለ ስሜታዊ ፍቅር መናገሩ ብቻ አይደለም፥ ወይም በአማኞች መካከል ሊኖር ስለሚገባ መልካም ስሜት ብቻ መናገሩ አይደለም። ይልቁንም ከፍቅር የሚመነጩትን ተግባራት ለማመልከት ይፈልጋል። እነዚህም ተግባራት በአሳብ ወይም በተግባር የተከናወኑትን በደሎች ይቅር ማለት ሊያካትቱ ይችላሉ፥ ወይም ደግሞ በችግር ውስጥ ያሉትን መርዳትን ሊያመለክቱ ይችላሉ። ዮሐንስ በዚህ መልእክት ውስጥ ወደዚሁ ማዕከላዊ ትምህርት ብዙ ጊዜ ደጋግሞ ይመለሳል።

እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ የሚለው ትእዛዝ በአንድ በኩል በጣም ያረጀ ነው። ይህ ትእዛዝ ብሉይ ኪዳን ውስጥ ይገኛል (ዘሌዋ. 19፡18 አንብብ)። በተጨማሪም ይህ ትእዛዝ አዲስ የሆነው በብዙ መንገዶች ነው። በመጀመሪያ፥ የብሉይ ኪዳን የፍቅር ትእዛዝ የተመሠረተው በጎሰኝነት ላይ መሆኑ፥ ይህ እርስ በርስ ተዋደዱ የሚለው ትእዛዝ አዲስ ነው። አይሁዳውያን ወገኖቻቸውን እንዲወዱ ነበር የተጠየቁት። ነገር ግን አይሁዳውያን ያልሆኑትን እንዲወዱ የታዘዙበት ስፍራ አልተጠቀሰም። አሁን ግን እግዚአብሔር ሰዎችን ሁሉ እንድንወድ አዞናል (ማቴ. 22፡39-40)፡፡ ሁለተኛ፥ በስፋቱም አዲስ ነው። ብሉይ ኪዳን አይሁዶች ድሆችን እንዲረዱ ሲያዛቸው፥ ወዘተ… ፥ ከሰዎች የሚጠበቀውን ነገር ይወስነዋል። በመጀመሪያ: የብሉይ ኪዳን ፍቅር በተለይም ለአይሁዶች መልካም ከሆኑት ሰዎች ጋር ግንኙነት ማድረግን ያበረታታል። አዲስ ኪዳን ግን በመሥዋዕትነት ፍቅር ላይ ያተኩራል። ይህም ለእኛ ጥሩዎች ያልሆኑትን (ጠላቶቻችንን ጨምሮ) መውደድን ያካትታል (ማቴ. 5፡43-47)። የአዲስ ኪዳን ፍቅር ሕይወታችንን ሳይቀር ለሌላ ሰው ፍቅር በመሥዋዕትነት እንድናቀርብ ይጠይቀናል (1ኛ ዮሐ. 3፡16)።

ዮሐንስ አንድ ሰው የክርስቶስ ተከታይ ነኝ እያለና ከእግዚአብሔር አብ ጋር መልካም ኅብረት እንዳለው እየተናገረ ዳሩ ግን ፍቅርን ሳይሆን ጥላቻን የሚያሳይ ከሆነ፥ ድነትን (ደኅንነትን) ያላገኘ የጨለማ ውስጥ ተጓዥ መሆኑን ይናገራል። አሁንም ዮሐንስ «ጥላቻ» የሚለውን ቃል የሚጠቀመው እንደ ስሜታዊ አለመውደድ ሳይሆን፥ ሌሎችን ለመርዳት አለመፈለግን ለማሳየት ነው። አንድ አማኝ በችግር ውስጥ እያለ ልንረዳው ካልፈለግን ጠልተነዋል ማለት ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ያሉት አብዛኞቹ ግንኙነቶች ተለይተው የሚታወቁት በፍቅር ነው ወይስ በጥላቻ? ለ) የኮሚኒስት መንግሥት ከወደቀ በኋላ በአማኞች መካከል መከፋፈል የበረከተው ለምን ይመስልሃል ? ሐ) ይህ በክርስቶስ ላይ ስላለን እምነት ምን ያሳያል?

በ1ኛ ዮሐንስ 2፡12-14፤ ጸሐፊው በአማኞች ሕይወት ውስጥ የተመለከተውን ነገር ያስታውሳል። ይህም የእግዚአብሔር ልጆች መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ነበር። ምሁራን ልጆች፥ ጎበዞችና አባቶች የሚለው ማንን እንደሚያመለክት ይጠራጠራሉ? ይህ ቅደም ተከተላዊ የዕድሜ መግለጫ ነው? ወይስ የመንፈሳዊ ብስለት መግለጫ ? በአመዛኙ ዮሐንስ መንፈሳዊ ብስለትን የሚያመለክት ይመስላል። ዮሐንስ እነዚህን የተለያዩ ነገሮች ከተለያዩ የዕድሜ ቡድኖች ጋር የሚያዛምደው ለምንድን ነው? አናውቅም። ዮሐንስ አማኞች ሁሉ ሊያስታውሷቸውና ሊያድጉባቸው የሚገባቸውን ሦስት ባሕርያት ለማሳየት የሚፈልግ ይመስላል።

ሀ) ኃጢአታችን እንደ ተሰረየ እናውቃለን። አዳዲስ እማኞች፣ ሊያውቋቸው ከሚገቡ ነገሮች አንዱ ከክርስቶስ ደም የተነሣ ለቀድሞዎቹ፣ ለአሁኖቹና ወደፊት ለሚያደርጓቸው ኃጢአቶች ሁሉ ዋጋ እንደ ተከፈለ ነው። እግዚአብሔር ሙሉ በሙሉ ይቅር ብሏቸዋል። ሰይጣን በቀድሞው ኃጢአታቸው ሳቢያ ልባቸውን እንዳያዝልባቸው፥ ይህን ማወቁ ጠቃሚ ነው። በክርስቶስ ከማመናችን በፊትና ካመንን በኋላ ለበደለኛነት ስሜት የሚያጋልጡንን ኃጢአቶች ልንፈጽም እንችላለን። ዮሐንስ ግን እነዚህን ኃጢአቶች ለእግዚአብሔር ከተናዘዝን ይቅርታ እንደሚደረግልን ይናገራል፡፡ ለፈጸምናቸው ኃጢአቶች ዋጋ መክፈላችንን ልንቀጥል እንችላለን (ለምሳሌ: አንዲት ሴት ከጋብቻ ውጭ ዝሙት ፈጽማ ብታረግዝ፣ እግዚአብሔር እርግዝናውን አያስወግድላትም)። ነገር ግን እግዚአብሔር ይቅር ስላለን ለዚያ ኃጢአት አይቀጣንም። ኃጢአት እንዳልፈጸምን ያህል ከእርሱ ጋር ግንኙነት ልናደርግ እንችላለን።

ለ) አማኞች «ከመጀመሪያው ከነበረው» ወይም ከእግዚአብሔር አብ ጋር ሕያው ግንኙነት አላቸው። ዮሐንስ «ማወቅ» የሚለውን ቃል የተጠቀመው ምሁራዊ እውቀትን ሳይሆን ዝምድናዊ እውቀትን ለማሳየት ነው። በብስለት የሚያድጉ ሰዎች የእግዚአብሔርን ማንነት በማወቅ ይበልጥ ወደ እርሱ እየቀረቡ ይሄዳሉ። ግንኙነቶች ሁሉ በእውቀት ላይ የተመሠረቱ ናቸው። አንድን ሰው የበለጠ ስናውቅና ብዙ ጊዜ አብረነው ስናሳልፍ፥ ግንኙነታችን እየጠለቀ ይመጣል። እንደ አባት ከሚወደንና ዳሩ ግን ዘላለማዊ ከሆነ አምላክ ጋር ግንኙነት ማድረጉ ምንኛ ታላቅ ዕድል ነው።

ሐ) በሕይወታችን ውስጥ ባለ ኃጢአት ላይ ድልን እንቀዳጃለን። ዮሐንስ ሙሉ በሙሉ ከኃጢአት ነፃ ልንሆን እንደማንችል ይናገረናል። ይህ ማለት ግን በቅድስና ልናድግ፥ ኃጢአትን ልናሸንፍና ለእግዚአብሔር ክብር ልንኖር አንችልም ማለት አይደለም። ነገር ግን ዮሐንስ የሚናገረው በሕይወታችን ውስጥ ስላለ ኃጢአት ብቻ ሳይሆን ከክፉ ስለሚመጣው የፈተና ምንጭ ጭምር ነው። (በግሪክ ቋንቋ፥ ትኩረት የተሰጠው ኃጢአትን በማሸነፍ ላይ ሳይሆን፥ «ክፉ» የተባለውን ሰይጣንን በማሸነፍ ላይ ነው፥ የሚፈትነን እርሱ ነውና።) ዮሐንስ የሚናገረው ሰይጣን መቼ በኃጢአት እንደሚፈትነን ነው? በብስለት እያደግን ስንሄድ በመንፈሳዊ ጥንካሬም እናድጋለን። በመንፈሳዊ ብስለት ማደግ ከሚያስገኛቸው ውጤቶች አንዱ ሰይጣን እንዳያሸንፈንና ወደ ኃጢአት እንዳይመራን መከላከል መቻል ነው። እግዚአብሔር በእምነታችን ጠንካሮች እንድንሆን ለማገዝ የሰጠን ዋናው መሣሪያ ምንድን ነው? ይህ በውስጣችን ሊኖር የሚገባው የእግዚአብሔር ቃል ነው።

የውይይት ጥያቄ፡– ሀ) እነዚህ ሦስት እውነቶች ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት የሚያሳይ ጠቃሚ አመልካቾች የሚሆኑት ለምንድን ነው? ለ) መዝ 119፡9 አንብብ። ይህ ምንባብ ሰይጣንንና ኃጢአትን ስለምናሸንፍበት መንገድ ምን ይላል? ይህ ሰይጣንን ከሕይወታችን ለማራቅ መጸለይና መገሠጽ ብቻ በቂ እንዳልሆነ የሚያሳየን እንዴት ነው?

፪. ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት ማድረግ ማለት የዓለምን የአኗኗር ዘይቤ አለመውደድ ነው (1ኛ ዮሐ 2፡15-17)

አንድን ሰው ስትወድ ሰውየው የሚወደውን እንጂ የሚጠላውን አታደርግም። እንወደዋለን የምንለው ሰው የማይፈልገውን ነገር የምናደርግ ከሆነ፥ ይህ ግንኙነታችንን፥ ከማደፍረሱም በላይ ለግለሰቡ ፍቅር እንደሌለን ያሳያል። እግዚአብሔርን ከወደድን እንዲሁም ከእርሱ ጋር ኅብረት ካለን፥ እርሱ የሚወደውን ልንወድና ደስ የማያሰኘውን ከማድረግ ልንቆጠብ ይገባል። ዮሐንስ እግዚአብሔር ከማይወዳቸው ነገሮች አንዱን ይጠቅሳል። ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ ሲል ይመክረናል። ይህ ምን ማለት እንደሆነ መረዳቱ ጠቃሚ ነው። ዮሐንስ የሚናገረው ስለተፈጠረው ዓለም አይደለም። ምክንያቱም እግዚአብሔር ዓለምን ከመፍጠሩም በላይ መልካም መሆኑን ተናግሯልና (ዘፍጥ. 1፡31)። ዮሐንስ ሰዎችን ማለቱም አይደለም፥ ምክንያቱም እግዚአብሔር ሰዎችን ከመውደዱ የተነሣ ልጁ እንዲሞትላቸው ልኮታልና (ዮሐ 3፡16)። ዮሐንስ «ዓለም» ሲል ከእግዚአብሔር ፈቃድ ውጭ የሆነ ፍልስፍና ወይም ትምህርት ማለቱ ነው። ይህ የዓለም ዘይቤ በኩራትና በራስ ወዳድነት የተሞላ ነው። እነዚህ ባሕርያት በዐመፅ ወደ ተሞሉ ተግባራትና የግንኙነቶች መፈራረስ ይመራሉ። የገንዘብ፥ የሥልጣን፥ በወሲባዊ ግንኙነቶች ሌሎችን የማሸነፍና ለተሳሳቱ ዓላማዎች የመማር ፍቅር የሚመጣው የማያምኑ ሰዎች ከሚያስተምሩት የአኗኗር ዘይቤ ነው። እግዚአብሔር ልጆቹ እነዚህን ነገሮች ባለመውደድ ለእርሱ ያላቸውን ፍቅር እንዲገልጹለት ይፈልጋል።

የውይይት ጥያቄ፡– ከዓለም ዘይቤ ክርስቲያኖች እንዳንድ ጊዜ የሚወዷቸውንና በሕይወታቸው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድሩትን ነገሮች ዘርዝር።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

በብርሃን መመላለስ (1ኛ ዮሐንስ 1፡1-2፡6)

አንድ ቀን ግርማዊ ወደ ዩኒቨርሲቲ ካፊቴሪያ ሲሄድ ሦስት ተማሪዎች በሃይማኖት ጉዳይ ላይ ይከራከሩ ነበር። ከሦስቱ ልጆች አንዱ ሙስሊም፥ ሌላኛው የአዲሱ ትውልድ (New Age) እምነት ተከታይ፥ ሦስተኛው ደግሞ የጂሆቫ እምነት ተከታይ ነበር። ግርማዊ ደግሞ የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያን አባል ነበር። እያንዳንዳቸው ስለ እምነታቸው ገለጻ አደረጉ። ከዚያም በአራቱም ሃይማኖቶች ውስጥ ስላሉት ጥሩ ጥሩ ነገሮች ተወያዩ። በውይይታቸው መጨረሻ ላይ በአራቱ ሃይማኖቶች ውስጥ አንድ አንድ ጥሩ ነገሮች እንዳሉ ተስማሙ። በውይይቱ፥ መጨረሻ ላይ ግርማዊ ከካፊቴሪያው ወጥቶ ሲሄድ ብዙ ጥያቄዎች አእምሮውን አጨናነቁት። «በሁሉም ሃይማኖቶች ውስጥ መልካም ነገሮች ካሉ፥ ሁሉም ሃይማኖት ወደ እግዚአብሔር የሚያደርሰን ትክክለኛ ሃይማኖት ነው ማለት ይቻላል? ወደ እግዚአብሔር የሚያደርሱ ብዙ መንገዶች አሉ? ወይስ ሰው የሚድነው በክርስቶስ ኢየሱስ ብቻ ነው? እግዚአብሔር የሚያሳስበው አንድ ሰው እርሱን ለማወቅ እና መልካም ሕይወት ለመኖር መቅናቱ ብቻ ነው? ወይስ ለእግዚአብሔር እውነት ወሳኝ ጉዳይ ነው?» ሲል አሰላሰለ።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የግርማዊን ጥያቄዎች እንዴት ትመልሳለህ? ለ) እግዚአብሔር ከእውነት በላይ ሃይማኖታዊ ቅናትን ይፈልጋል? ወይስ ትክክለኛ እምነትን? ሐ) አንድ ሰው ድነት (ደኅንነት) የሚያገኘው ክርስቶስን በማመን ብቻ እንደሆነ ከተናገረ፥ ይህ ትዕቢትን አያሳይምን? መልስህን አብራራ። መ) እውነትን ማወቅና ማመን አስፈላጊ ነው የምንል ከሆነ፥ ብዙ ክርስቲያኖች ስለ አንድ ነገር እውነተኛነት ብዙም የማይጨነቁት ለምንድን ነው? ሠ) ከሰዎች አስተሳሰብ ይልቅ ፍጹማዊ እውነትን የምናውቅበት ብቸኛው ምንጭ ምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ እውነት ለእግዚአብሔር አስፈላጊ መሆኑን በግልጽ ይናገራል። ለዚህም ነው እግዚአብሔር እውነትን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የገለጠው። ይህም የእርሱ የሆነው እውነት ነው። የእግዚአብሔርን ማንነት፥ ባህሪውን እና ከእርሱ ጋር ኅብረት ለመፍጠር ከሚፈልጉት ሰዎች ምን እንደሚፈልግ በትክክል የምናውቀው ከመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው። ስለ ክርስቶስ እና በእርሱ መንገድ ስለሚገኘው የድነት (ደኅንነት) መንገድ ማወቃችን ወሳኝ ነው። ምክንያቱም ክርስቶስ እንዳለው ወደ እግዚአብሔር የሚያደርስ አንድ ጠባብ መንገድ እርሱ ብቻ ነው። ሌሎች ሰፋፊ መንገዶች ሁሉ ወደ ዘላለማዊ ሞት የሚወስዱ ናቸው (ማቴ. 7፡13-14)። ስለሆነም፥ አንድም መጽሐፍ ቅዱስ ውሸት ነው ብለን ማመን አለብን፥ አለዚያም የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት ተቀብለን ወደ እግዚአብሔር የሚያደርሰን አንድ የድነት (ደኅንነት) መንገድ ብቻ እንዳለ መቀበል አለብን። ስለሆነም ዋናው ነገር የእኛ አሳብ አይደለም። በመሆኑም ድነት (ደኅንነት) የሚገኘው በክርስቶስ ነው የሚለው አሳብ ከእኛ የፈለቀ አይደለም። ይህም በመሆኑ ትዕቢትን እያመለክትም። እግዚአብሔር አንድ ብቸኛ የድነት (ደኅንነት) መንገድ እንዳለ ገልጾአል። እኛም ይህንኑ የእግዚአብሔርን ቃል እንደ ገደል ማሚቶ እንደግማለን።

የ1ኛ ዮሐንስ መልእክት እውነት ወሳኝ መሆኑን አበክሮ ይገልጻል። ዮሐንስ የሃይማኖት ቅናት ወይንም ስለ ክርስቶስ ደብዛዛ ግንዛቤ መያዙ በቂ አይደለም ይላል። ክርስቲያኖች ስለ እውነት ጥርት ያለ መረዳት ሊኖረን ይገባል። እውነትን ከሚያውቁት ሰዎች ጋር በፍቅር እና በትሕትና አብረን ልንኖር ሲገባንም፥ በመጽሐፍ ቅዱስ የተገለጸ አንድ እውነት ብቻ እንዳለ መግለጽ ይኖርብናል። ይህ አመለካከት ዛሬ በዓለም ውስጥ ሰፊ ተቀባይነት ያለው አይደለም። ክርስቲያኖችን ጨምሮ ድነት (ደኅንነት) የሚገኘው በክርስቶስ ብቻ መሆኑን የማይቀበሉ ብዙ ሰዎች አሉ። ሰዎች እንደ «ኢየሱስ ብቻ» ተከታዮች በሥላሴ ባያምኑም ችግር አለው? ክርስቶስ ነቢይ እንጂ እምላክ አልነበረም ቢሉስ? ድነት (ደኅንነት) የሚገኘው በመልካም ተግባርና እግዚአብሔርን የሚያስደስት ሥራ በመሥራት ነው የሚሉትስ ወገኖች? አንዳንዶች ድነትን የሚያገኙት በልሳኖች የሚናገሩት አማኞች ብቻ ናቸው ብለው ቢያስተምሩ ችግር አለው? ምንም እንኳን ብዙ ክርስቲያኖች ስለ እነዚህ ጉዳዮች ደንታ ባይኖራቸውም፥ ይህ ለእግዚአብሔር አስፈላጊ መሆኑን በ1ኛ ዮሐንስ መልእክት ውስጥ እንመለከታለን። እውነት አስፈላጊ ነው ፍቅርና መቀባበል ከእውነት ጋር መዋሃድ አለባቸው። እግዚአብሔርን ማስደሰት የሚቻለው ይህ ሲሆን ብቻ ነው (ኤፌ. 4፡15)።

እግዚአብሔር መጀመሪያ ሰውን ሲፈጥር ቀዳሚ ዓላማው ከሰው ጋር ኅብረት ማድረግ ነበር። እግዚአብሔር ከእንስሳት በተለየ ሁኔታ ሰውን በምሳሌው ፈጥሮታል። ከመጀመሪያ ጀምሮ እግዚአብሔር ከአዳም እና ሔዋን ጋር በመደበኛነት ኅብረት ያደርግ ነበር። (ዘፍጥ. 3፡8-9)። የሰው ልጆች ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት በሚያደርጉበት ጊዜ እጅግ የላቀ እርካታ ያገኙ ነበር። አዳምና ሔዋን ኃጢአት በሠሩ ጊዜ ይሄ ሁሉ ተለወጠ። በእግዚአብሔር እና በሰው መካከል ክፍተት ተፈጠረ። መጀመሪያ በእንስሳት መሥዋዕቶች፥ የኋላ ኋላም ክርስቶስ የኃጢአትን ዋጋ ለመክፈል በመስቀል ላይ በመሞቱ ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት የምናደርግበት መንገድ እንደገና ተከፈተ። ሐዋርያው ዮሐንስ ከእግዚአብሔር ጋር እንዴት ኅብረታችንን ጠብቀን ልንኖር እንደምንችል በመግለጽ መልእክቱን ይጀምራል። በሕይወት ውስጥ እውነተኛ ደስታ ሊገኝ የሚችለው ከእግዚአብሔር ጋር እያደገ የሚሄድ ኅብረት ሲኖረን ነው።

፩. መግቢያ፡- ከእግዚአብሔር ጋር የሚደረገው ኅብረት በእውነት ላይ የተመሠረተ ነው፤ ይህም እውነት ክርስቶስ በሥጋ የተገለጠ አምላክ መሆኑን የተመለከቱት የዓይን ምስክሮቹ ሐዋርያት ያስተማሩት ነው (1ኛ ዮሐ. 1፡1-4)።

ከክርስትና እምነት መሠረታዊ እውነቶች አንዱ እግዚአብሔር ሰው መሆኑ ነው። ዘላለማዊ የእግዚአብሔር ልጅ የሆነው ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም መጥቶ ተወልዶአል፥ ኖሮአል፥ ሞቶአል፥ ከሙታንም ተነሥቶ ወደ ሰማይ አርጓል። በዚህ ዓለም ላይ ሲመላለስ ከመኖሩም በላይ ለኃጢአታችን ሞቷል፥ ከሞትም ተነሥቶ ወደ መንግሥተ ሰማያት አርጓል። እግዚአብሔር ለኃጢአታችን መፍትሔ የሰጠው በዚህ መንገድ ነበር። ፍጹማዊ መሥዋዕት ሊቀርብ የሚችለው በዚህ መንገድ ብቻ ነበር። በዚህ ዓይነት የእግዚአብሔርን ኃይል የተላበሰ እና ዳሩ ግን ችግሮቻችንን የሚረዳ፥ ብሎም ከሰማይ ለእኛ የሚማልድ ዘላለማዊ ሊቀ ካህናት ሊኖረን ችሏል። የዮሐንስ ልብ ለዚህ ታላቅ ምሥጢር ሲከፈት እንመለከታለን። እግዚአብሔር ለሰው ልጆች የገለጸው ፍቅር ምንኛ ታላቅ ነው። ነገር ግን ይህ መሠረታዊ እውነት በሐሰተኛ አስተማሪዎች ሲጠቃ ተመለከተ። አንዳንዶች ክርስቶስ አምላክ መሆኑን ሲጠራጠሩ፥ ሌሎች ደግሞ ሰው መሆኑን ይጠራጠሩ ነበር። ስለሆነም ዮሐንስ በመግቢያው ላይ ሰላምታ ከማቅረብ ይልቅ ሥነ መለኮታዊ እውነትን ይነግረናል። በዚህም ክርስቶስ በሥጋ የተገለጠ አምላክ መሆኑንና ይህንን መረዳት ለአማኞች ለምን እንደሚያስፈልግ ተናግሯል። ለእግዚአብሔር እውነት ወሳኝ ነው። ምክንያቱም ይህ ዘላለማዊ ሕይወትና ዕጣ ፈንታቸው የዛሬ አኗኗራቸውን ይወስነዋል። ዮሐንስ ትኩረት ከሰጠባቸው ነገሮች መካከል የሚከተሉት ይገኙባቸዋል፡

ሀ) ክርስቶስ ከመጀመሪያው የነበረ አምላክ ነው። ይህም ዘላለማዊነቱን ያመለክታል። እርሱ የሕይወት ቃል ነው። እግዚአብሔር እውነትን ለሰዎች ያስተላለፈበት ምንጭ ነው። እርሱ ዘላለማዊ ሕይወት ነው። እንዲሁም ክርስቶስ ከአብ ጋር እኩል እና ነገር ግን የተለየ ነው።

ለ) ክርስቶስ ፍጹም ሰው ነው። ዮሐንስ የክርስቶስን ንግግር እርሱ ራሱ እንደ ሰማ፥ በዓይኑ እንዳየው እና በእጁ እንደ ዳሰሰው ይናገራል። ክርስቶስ መንፈስ አልነበረም። ወይም ደግሞ ክርስቶስ የምናብ ውጤት አልነበረም። ክርስቶስ በታሪክ ውስጥ የነበረ የታሪክ ሰው መሆኑን ያስመሰክራል። ዮሐንስ ክርስቶስን ያየው ሲሆን፥ ምናልባትም ከሞት የተነሣውን ጌታ ከተመለከቱት እና በሕይወት ካሉት የመጨረሻዎች ሰዎች ዮሐንስ አንዱ ሳይሆን አይቀርም። በዚህ ጊዜ ሌሎች ደቀ መዛሙርት ሁሉ ሞተው ነበር።

ሐ) ይህ አምላክ ሰው የመሆኑ ሁኔታ የሁለት ዓይነት እውነት መሠረት ነው። በመጀመሪያ፥ እንደ ክርስቶስ አካል ለሚኖረን ኅብረት መሠረት ነው። ዮሐንስ ክርስቶስ አምላክና ሰው መሆኑን የሚያምኑ አማኞች ከእርሱና ከሌሎች አማኞች ጋር ኅብረት ሊያደርጉ እንደሚችሉ ይናገራል። ዮሐንስ ይህን ሊል ክርስቶስ ፍጹም አምላክና ፍጹም ሰው እንደሆነ የማያምኑ ሰዎች የእግዚአብሔር ቤተሰብ አባል አለመሆናቸውን እና ከዚህም የተነሣ የአማኞችን አምላክ ኅብረት እያደረጉ ደስ ሊሰኙ እንደማይችሉ ማሳየቱ ነው። ሁለተኛ፥ ይህ ከእግዚአብሔር አብና ወልድ ጋር ኅብረት ለመፍጠር መሠረት ይሆናል። አሁንም ክርስትና ልዩ ሃይማኖት ያለመሆኑን እንመለከታለን። አንድ ሰው ከእግዚአብሔር አብና ወልድ ጋር ኅብረት ሊያደርግ የሚችለው ስለ ክርስቶስ ትክክለኛ እውቀት ካለውና የኃጢአትን ዋጋ ለመክፈል ክርስቶስ በመስቀል ላይ እንደ ሞተ በግሉ ሲያምን ብቻ ነው። ዮሐንስ እውነትን ስናውቅ እና ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ግንኙነት ግልጽ፥ እንዲሁም በእውነት ላይ የተመሠረተ ሲሆን፥ በፍጹም ደስታ እንደምናገኝ ያስረዳል።

የውይይት ጥያቄ፡– ሀ) ይህ ክፍል አማኞች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች በትክክል መረዳታቸው ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ያሳያል። ይህንን አሳብ አብራራ። ለ) ይህ ክፍል ዋናው አምልኳችን ወይም ቅናታችን እንጂ እውነት አይደለም ለሚሉ ወገኖች ምን ዓይነት ማስጠንቀቂያ ይሰጣል? ሐ) ይህ ክፍል ሁሉም ሃይማኖቶች ወደ እግዚአብሔር ያመጣሉ የሚለውን አሳብ እንዴት ፉርሽ እንደሚያደርግ ግለጽ።

፪. ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት ማድረግ ማለት የኃጢአትን ይቅርታ አግኝተን በቅድስና እና በታዛዥነት መመላለስ ማለት ነው (1ኛ ዮሐ. 1፡5-2፡6)

የተሳሳተ ግንዛቤ በአማኞች ላይ ተጽዕኖ ከሚያሳድርባቸው መንገዶች አንዱ ወደ ተሳሳቱ ተግባራት መምራት ነው። ከቀድሞዎቹ አማኞች አንዳንዶቹ የሰው ሥጋ ክፉ እንደሆነና መንፈስ ብቻ የተቀደሰ መሆኑን የሚያመለክት ሐሰተኛ ትምህርት ይሰሙ ነበር። ይህም በትክክለኛ መንገድ እግዚአብሔርን እስካመለክነውና ለመንፈሳችን ጥንቃቄ እስካደረግን ድረስ፥ በሥጋችን የምንሠራው አሳሳቢ አይደለም ወደሚለው አመለካከት መራቸው። ዮሐንስ ግን በመንፈሳችን ከእግዚአብሔር ጋር የምናደርገው ኅብረት በትክክለኛ እውቀትና ተግባራት ላይ የተመሠረተ መሆኑን ይገልጻል። ስለሆነም ዮሐንስ ለአማኞቹ የምንኖርበት ሁኔታ በልባችን ውስጥ ያለውን እውነት ምንነት ያረጋግጣል ይላቸዋል።

ሀ) ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት የሚያደርጉ ሰዎች በብርሃን ወይም በቅድስና መመላለስ ይኖርባቸዋል። ቅድስና ከእግዚአብሔር ቀዳማይ ባሕርያት አንዱ ነው። እግዚአብሔርን የሚከተሉትና ከእርሱ ጋር ግንኙነት ለማድረግ የሚፈልጉ ሰዎች ለቅድስና ራሳቸውን ማዘጋጀት ይኖርባቸዋል። በእውነትና በቅድስና ብርሃን ለመኖር በምንፈልግበት ጊዜ በኃጢአት ብንወድቅ የክርስቶስ ኢየሱስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል።

ለ) እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ኅብረት ለማድረግ ፍጹማን እንድንሆን አይጠብቅብንም። እንዲያውም፥ ፍጹምና ኃጢአት የለሽ መሆኑን የሚናገር ሰው ውሸተኛ መሆኑን እንገነዘባለን። የእግዚአብሔርም ቃል በእንዲህ ዓይነቱ ሰው ሕይወት ውስጥ አይሠራም። ኃጢአት አድርገን በእግዚአብሔርና በእኛ መካከል ያለው ኅብረት በሚበላሽበት ወቅት ምን ማድረግ ይኖርብናል? በኃጢአታችን ምክንያት የተበላሸውን ግንኙነት እንዴት መጠገን ይቻላል? መጀመሪያ ለእግዚአብሔር፥ ቀጥሎም ለበደልነው ሰው ኃጢአታችንን በመናዘዝ ከእግዚአብሔር ጋር ወደ ነበረን ኅብረት ልንመለስ እንችላለን። የበደልነውን ሰው ይቅርታ የምንጠይቀው ኃጢአታችን ሌላውን ሰው የሚያካትት ከሆነ ነው። እግዚአብሔር ኃጢአታችንን በክርስቶስ ደም ተሸፍኖ ስለሚመለከትና ይቅር ስለሚለን፥ ንስሐ መግባታችን ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ኅብረት ያድሰዋል። ዮሐንስ ይቅርታ እንደሚደረግልን ብቻ ሳይሆን፥ ኃጢአት በምንፈጽምበት ጊዜ ስለ እኛ በእግዚአብሔር ፊት የሚቆምና የሚማልድ ጠበቃ በሰማይ እንዳለን ይናገራል። ዮሐንስ «ጠበቃ» የሚለውን ቃል የወሰደው ከሕግ ሙያ ነው። አንድ ሰው ተከስሶ ችሎት ፊት በሚቀርብበት ጊዜ ከወንጀሉ ነፃ መሆኑን የሚያረጋግጥለት ጠበቃ ይቀጥራል። በተመሳሳይ ሁኔታ፥ በእግዚአብሔር አብ ፊት በምንቆምበት ጊዜ (ሰይጣን በኃጢአታችን ሲከስሰን) ክርስቶስ በችሎቱ ፊት ቆሞ ንጹሕ ለመሆናችን ይከራከርልናል። ኃጢአት ሠርተን ሳለን እንዴት ንጹሐን ልንሆን እንችላለን? ንጹሐን የምንሆንበት ምክንያት ቀደም ሲል ክርስቶስ በመስቀል ላይ በመሞት ለወንጀላችን (ለኃጢአታችን) ክፍያ የፈጸመ በመሆኑ ነው። ስለሆነም ክርስቶስ አማኙ ኃጢአት አልፈጸመም አይልም። ነገር ግን፥ «የኃጢአቱ ዋጋ ስለተከፈለ ሊቀጣ አይችልም። ስለሆነም ነፃ ነህ ተብሎ መሰናበት አለበት» ሲል ይከራከራል። (ማስታወሻ፡ ኃጢአትን በምንሠራበት ጊዜ ደኅንነታችንን አናጣም። ነገር ግን ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ኅብረት ይቋረጣል። ይህ አንድ ልጅ ወላጆቹን በማይታዘዝበት ጊዜ ከሚሆነው ሁኔታ ጋር ተመሳሳይ ነው። በመሆኑም ልጁ ባለመታዘዙ ምክንያት ልጅነቱን አያጣም። ነገር ግን ቀደም ሲል እንደ ነበረው ከወላጆቹ ጋር መልካም ግንኙነት ላይኖረው ይችላል።)

ሐ) ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት ለማድረግና እውነተኛ የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ለማረጋገጥ ኃጢአታችንን መናዘዝ ብቻ ሳይሆን፥ እውነትን መታዘዝ አለብን። ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ግንኙነት የሚገለጸው ኃጢአት ባለመሥራታችን ብቻ አይደለም። ነገር ግን ለእግዚአብሔር ቃል በመታዘዝ የጽድቅን ኑሮ በመኖራችን ይገለጻል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ለአማኞች በተደጋጋሚ ኃጢአታቸውን በመናዘዝ ንጹሕ ሕይወት መምራት አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድ ነው? ለ) በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ አብዛኞቹ ክርስቲያኖች ለኃጢአት ትኩረት በመስጠት በእግዚአብሔር ፊት ንጹሕ ሕይወት ለመኖር የሚሞክሩ ይመስልሃል? የራስህን ሕይወት መርምርና ያልተናዘዝክበት ኃጢአት ካለ ተመልከት። ከእግዚአብሔር ጋር ያለህ ኅብረት እንዲታደስ ኃጢአትህን ተናዘዝ። ሐ) ብዙውን ጊዜ ከእግዚአብሔር ጋር ስላለን ግንኙነት ስናስብ፥ ስለ ጽድቅ ሳይሆን ኃጢአትን ስላለመሥራት እናስባለን። እግዚአብሔር ለእርሱ በመታዘዝና በጽድቅ እንድንኖር የሚጠይቃቸውን የተለያዩ ነገሮች ዘርዝር። እነዚህ ነገሮች ለምን እንደሚያስፈልጉ ግለጽ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የ1ኛ ዮሐንስ ልዩ ባሕርያት፣ ማዋቅር እና አስተዋጽኦ

የ1ኛ ዮሐንስ ልዩ ባሕርያት

 1. ዮሐንስ ክርስቲያኖችን «ልጆቼ ሆይ» እያለ ይጠራል። በእድሜ መግፋቱንና አብዛኞቹ አማኞች ከእርሱ ታናናሾች የነበሩ መሆናቸውን ያሳያል። ይህ በተጨማሪም፥ ዮሐንስ አማኞቹን በቅርብ እንደሚያውቃቸው ያሳያል።
 2. እንደ ዮሐንስ ወንጌል ሁሉ፥ የ1ኛ ዮሐንስ ጸሐፊ እውነትን በተቃራኒ አሳቦች ይገልጻል። በመሆኑም እንደ ጨለማና ብርሃን (1ኛ ዮሐ. 1፡5-7)፥ ሕይወትና ሞት (1ኛ ዮሐ. 3፡14-15)፥ እውነትና ውሸት (1ኛ ዮሐ. 2፡21)። ፍቅርና ጥላቻ (1ኛ ዮሐ 4፡19-21) የመሳሰሉትን ቃላት ይጠቀማል።
 3. ዮሐንስ የፍቅር ሐዋርያ በመባል ይጠራል። በዚህች አጭር መልእክት ውስጥ «ፍቅር» የሚለው ቃል 25 ጊዜ ተጠቅሷል።
 4. ዮሐንስ በመጨረሻው ዘመን ለሚገለጠው ገዢ የወል ስም ይሰጠዋል። ዮሐንስ ይሄንን ገዢ «የክርስቶስ ተቃዋሚው» ሲል ይጠራል። ይህም ሐሰተኛው መሢሕ በሁሉም ነገር የክርስቶስ ተቃዋሚ (ተቃራኒ) እንደሚሆን ያመለክታል (1ኛ ዮሐ 2፡18)። እንዲሁም ዮሐንስ ውሸትን የሚያስተምሩ ሰዎች ሁሉ በዚሁ የመጨረሻው ዘመን ገዢ መንፈስ የሚሠሩ መሆናቸው፥ የክርስቶስ ተቃዋሚዎች መሆናቸውን ይገልጻል።
 5. ዮሐንስ «ማወቅ» የሚለውን ቃል ከ40 ጊዜያት በላይ ደጋግሞ ጠቅሷል። ይህም ዮሐንስ መልእክቱን ከጻፈባቸው ዐበይት ምክንያቶች አንዱ ክርስቲያኖች እውነትን እንዲያውቁና በእግዚአብሔር የተስፋ ቃሎች ላይ ተመሥርተው በልበ ሙሉነት እንዲመላለሱ ለማገዝ መሆኑን ያሳያል።

የ1ኛ ዮሐንስ መዋቅር

በአንዳንድ በኩል የ1ኛ ዮሐንስ መልእክት ግልጽ ምክንያታዊ መዋቅርን የተከተለ አይደለም። ዮሐንስ ከአንድ ጉዳይ ወደ ሌላው፥ ከዚያም ወደ አንዳንድ ጉዳዮች እንደገና እየተመለሰ አጽንኦት የሚሰጥ ይመስላል። አንዳንድ ምሁራን ይህ መልእክት በሦስት ክፍሎች እንደ ተከፈለ ይናገራሉ።

 1. ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረትን ለማድረግ እንዴት በብርሃን መመላለስ እንደሚቻል (1ኛ ዮሐ. 1፡1-2፡17)። ጸሐፊው ከመግቢያው ቀጥሎ ከእግዚአብሔር አብና ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ኅብረት እንዲኖረን ኃጢአታችንን መናዘዝ እንዳለብን ያስረዳል። ይሄም ኃጢአታችን ክርስቶስ በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደም እንደ ተሸፈነ ያስረዳል። ከዚያም የእግዚአብሔርን ትእዛዛት በመከተል መመላለስ ይኖርብናል። በተለይም እርስ በርሳችን ከመጠላላት ይልቅ መዋደድ ይኖርብናል። በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ያለውን እውነት ማመን አለብን። እንዲሁም፥ የዓለም ክፉ የአኗኗር ዘይቤ ሕይወታችንን እንዳይበክል መጠንቀቅ ይኖርብናል
 2. በሐሰተኛ ትምህርቶች መካከል እንዴት መኖር እንደሚቻል (1ኛ ዮሐ. 2፡18-3፡24)። ዮሐንስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ክፍፍል የሚመጣው ከሐሰት ትምህርት መስፋፋት ሳቢያ እንደሆነ በመግለጽ፥ ክርስቲያኖች ለዚህ ሁኔታ ምን ዓይነት ምላሽ ሊሰጡ እንደሚገባ ያስጠነቅቃል። የክርስቶስ ተቃዋሚዎች እኛን ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ ለመምራት በትጋት እየሠሩ መሆናቸውን ይነግረናል። ስለሆነም፥ ከመጀመሪያው የሰማናቸውን እውነቶች በጥንቃቄ መያዝ ይኖርብናል። እንዲሁም የተቀደሰ ሕይወት በመምራት ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት መጠበቅ አለብን። እርስ በርሳችን በመዋደድ ክርስቲያናዊ ሕይወትን ማጠናከር አለብን።
 3. ሐሰተኛና እውነተኛ አስተማሪዎችን እንዴት መለየት እንደሚቻል (1ኛ ዮሐ. 4፡1-5፡1-21)። ዮሐንስ ክርስቲያኖች የመጣውን ትምህርት ሁሉ ከእግዚአብሔር እንደሆነ በማሰብ እንዳይቀበሉና ነገር ግን መናፍስትን እንዲመረምሩ በማዘዝ፥ አማኞች አንድ ትምህርት ከእግዚአብሔር መሆን አለመሆኑን ለመፈተን የሚጠቀሙባቸውን ሦስት መፈተኛዎች ይሰጣል። እነዚህም ሦስት ዐበይት መፈተኛዎች፥ ሀ) ትክክለኛ እምነት። የዮሐንስ መልእክት ክርስቶስ በሥጋ የተገለጠ አምላክ በመሆኑ ላይ ያተኩራል። ለ) የእግዚአብሔር ቃል በሚያዘው መሠረት በጽድቅ መኖር ነው፤ ሐ) ከጥላቻና ክፍፍል ይልቅ የእግዚአብሔርን ሕዝብ መውደድ።

የ1ኛ ዮሐንስ አስተዋጽኦ

 1. ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት ለማድረግ በብርሃን መመላለስ (1ኛ ዮሐ. 1፡1-2፡17)።

ሀ) መግቢያ፡ ከእግዚአብሔር ጋር የሚደረግ ኅብረት ሐዋርያት ባስተማሩት እውነት ላይ የተመሠረተ ነው። እነዚህም ሐዋርያት ኢየሱስ ሰው ሆኖ በሥጋ የተገለጠ አምላክ መሆኑን በዓይናቸው አይተዋል (1ኛ ዮሐ 1፡1-4)።

ለ) ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት ማድረግ ማለት የኃጢአትን ይቅርታ አግኝተን በቅድስናና በታዛዥነት መመላለስ ማለት ነው (1ኛ ዮሐ. 1፡5-2፡6)።

ሐ) ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት ለማድረግ ሌሎች አማኞችን መውደድ ይኖርብናል (1ኛ ዮሐ 2፡7-14)።

መ) ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት ማድረግ ማለት የዓለምን የአኗኗር ዘይቤ አለመውደድ ማለት ነው (1ኛ ዮሐ 2፡15-17)

 1. በሐሰተኛ ትምህርቶች መካከል እንዴት መኖር እንደሚገባ (1ኛ ዮሐ 2፡18-3፡24)።

ሀ) የእግዚአብሔር ልጆች የሰይጣንን ውሸቶች ከማመን ይልቅ እውነትን አጥብቀው መያዝ አለባቸው (1ኛ ዮሐ 2፡18-27)።

ለ) የእግዚአብሔር ልጆች ተስፋችንን በክርስቶስ ዳግም ምጽአት ላይ ማኖር አለብን። ይህም የጽድቅን ኑሮ እንድንኖር ይረዳናል (1ኛ ዮሐ 2፡28–3፡10)። ሐ) የእግዚአብሔር ልጆች እርስ በርሳቸው በመዋደድ አንድነትን መጠበቅ አለባቸው (1ኛ ዮሐ. 3፡11-24)።

 1. ሐሰተኛና እውነተኛ ትምህርትን፥ እንዲሁም አማኞችን እንዴት መለየት እንደሚቻል (1ኛ ዮሐ 4፡1-5፡21)

ሀ) እውነተኛ አስተማሪዎችና አማኞች በተለይም ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚይዙት አስተምህሮ ትክክለኛ ነው (1ኛ ዮሐ. 4፡1-8)።

ለ) እውነተኛ አስተማሪዎችና አማኞች ሌሎች አማኞችን በመውደድ ለእግዚአብሔር ያላቸውን ፍቅር ይገልጻሉ (1ኛ ዮሐ 4፡7-21)።

ሐ) እውነተኛ አስተማሪዎችና አማኞች በክርስቶስ ኢየሱስ ላይ ትክክለኛ እምነት ሲኖራቸው፥ ከእርሱ ጋር ያላቸው ግንኙነትም የተስተካከለ ነው (1ኛ ዮሐ 5፡1-12)።

መ) እውነተኛ አስተማሪዎችና አማኞች የእግዚአብሔር ልጆች መሆናቸውን ያውቃሉ። ይህንንም በተቀደሰ አኗኗር ያሳያሉ (1ኛ ዮሐ 5፡13-21)።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)