2ኛ ቆሮ. 13:1-14

ሐዋርያው በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የመጨረሻ ሐሳቡን ይዘረዝራል። ይህ የጥናታችን መደምደሚያ ይሆናል፡፡ እግዚአብሔር በእነዚህ በሁለት መጽሐፎች ማለት በ1ኛና በ2ኛ ቆሮንቶስ ያስተማረን ብዙ ነገሮች አሉ። እነዚህን ራሳችን በሥራ ላይ እያዋልናቸው ለሌሎችም እንድናካፍል እግዚአብሔር ጸጋውን ይስጠን። 

ይህ የጥናታችን የመጨረሻው ነው። በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ያሉት ሃሳቦች በፊት የተጠቀሱ ናቸው። ዋናው የምዕራፉ ነጥብ ሐዋርያው ለሦስተኛ ጊዜ ሊጎበኛቸው ሲሄድ ሁሉም ንስሐ ገብተው በጥሩ የክርስቲያን አቋም እንዲገኙ ማሳሰቢያ ነው። 

ጥያቄ 1 በቁጥር 3 ላይ “ክርስቶስ በእኔ አድሮ እንዲናገር ማስረጃ ከፈለጋችሁ” ሲል ምን ማለቱ እንደሆነ አስረዳ። 

ጥያቄ 2. በቁጥር 5 ላይ “ወይስ ምናልባት የማትበቁ ባትሆኑ” ማለት ምን ማለት ነው? 

ከቁጥር 1-4:- የሐዋርያውን ሥልጣን የናቁትን ያስጠነቅቃቸዋል። የሐዋርያው ኃይል የራሱ ሳይሆን የክርስቶስ ኃይል ነው። ስለዚህ የሐዋርያውን ሥልጣን መናቅ የሾመውን የክርስቶስን ኃይልና ሥልጣን መናቅ ነው፡፡ ይህ ነጥብ አሁንም በቤተ ክርስቲያን ሊታወስ ይገባዋል። ክርስቶስ የሾማቸውን መናቅ ክርስቶስን መናቅ ነው። እርገግ አገልጋዮችም በሕዝቡ ፊት በትሕትና መገኘት አለባቸው። ሕዝቡንም በግል መብታቸው ሳይሆን በክርስቶስ ቃል መሠረት ማዘዝ አለባቸው። ይህ ሲደረግ ይህንን ዓይነት ሥልጣን መናቅ ክርስቶስን መናቅ ነው። 

እንግዲህ ሐዋርያው ሲሄድ ንስሐ ገብተውና ተስተካክለው ካላገኛቸው በእርሱ ውስጥ ያለውን የክርስቶስን ኃይል ያሳያቸዋል። ይህን ማድረግ አይፈልግም፤ ነገር ግን ወደዚያ እርምጃ እንዳያስገድዱት ይለምናቸዋል። 

ከቁጥር 5-10፡- በቁጥር 5 እያንዳንዳቸው እውነት በክርስቶስ ላይ እምነት እንዳላቸው ወይም እንደሌላቸው በግላቸው ማጣራት እንዳለባቸው ይናገራል። ብዙውን ጊዜ በቤተ ክርስቲያን መሪዎችን በመቃወም የጌታን ሥራ የሚከለክሉ በእርግጥ ጌታን አያውቁትም ይሆናልና ልባቸውን እንዲመረምሩ መናገር ተገቢ ይሆናል። 

ጥያቄ 3. በየጊዜው ሕይወታችንን መመርመሩ አስፈላጊ የሆነው ለምንድነው? 

በቁጥር 10 ላይ በመጣ ጊዜ በቁርጥ ሥልጣን በማሳየት ሐዋርያዊ ተግሣጽ ማምጣት እንዳያስፈልገው በሩቅ ሳለ በደብዳቤ ያስጠነቅቃቸዋል። በዚያን ጊዜ የቤተ ክርስቲያን ቅጣት ወዲያውኑ በዓይን የሚታይ መቅሰፍት ያስከትል ነበር። አሁን ብዙውን ጊዜ ይህ ስለማይታይ የቤተ ክርስቲያንን ተግሣጽ ሰዎች አይፈሩም። ነገር ግን በቤተ ክርስቲያን ቅጣት አሁንም ክርስቶስ ተባባሪ መሆኑን መዘንጋት የለብንም! እርግጥ የቤተ ክርስቲያን ቅጣት በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት መደረገ አለበት፤ ካለበለዚያ የቤተ ክርስቲያን ቅጣት ሊባል አይገባውም። ቤተ ክርስቲያን በትክክል የምታቀርበውን ቅጣት የናቁትን እግዚአብሔር  በሚታይ ተግሣጽ እንደሚገሥጽ መዘንጋት የለብንም። ስለዚህ የቤተ ክርስቲያንን ሥልጣን የናቀ የክርስቶስን ሥልጣን የናቀ መሆኑን መዘንጋት የለበትም። 

ጥያቄ 4. ይህንን በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ተግባራዊ ልታዳርገው የምትችለው እንዴት ነው?

2ኛ ቆሮ. 12:11-21

ጥያቄ 15. በቁጥር 11 ላይ «እናንተ እኔን ልታመሰግኑ ይገባ ነበርና» ሲል ምን ማለቱ ነው? 

ጥያቄ 16. በቁጥር 13 «ይህን በደሌን ይቅር በሉኝ» ሲል ምን ማለቱ ነው? በደሉ ምን ነበር? 

ጥያቄ 17. በቁጥር 16 ላይ «ነገር ግን ሸንጋይ ሆኜ በተንኮል ያዝኋችሁ» ሲል ምን ማለቱ እንደሆነ አብራራ። 

ጥያቁ 18. ከቁጥር 19 እስከ ቁጥር 21 ሐዋርያው ወደ ቆሮንቶስ በተመለሰ ጊዜ ይደርስብኛል ብሎ የፈራውን ነገር አብራራ። 

ቁጥር 11-13:- ሐዋርያው ስለራሱ አገልግሎት እራሱን መደገፍ አያስፈልገውም ነበር። የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የሆኑት የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ሊከራከሩለት ይገባ ነበር። ግን የጠላቶቹን ክስ በመስማት ስለራሱ እንዲናገር አደረጉት፤ በዚህም ቅር እንደተሰኘ ይነገራቸዋል፡፡ ስለአገልግሎቱ እነሱ በእርግጥ ያውቃሉ፤ ምክንያቱም በመካከላቸው የጳውሎስ ሐዋርያነት በብዙ ተአምራት ተረጋግጦላቸዋል፡፡ 

በቆሮንቶስና በሌሎቹ አብያተ ክርስቲያናት መካከል የነበረው ልዩነት፥ ጳውሎስ የቆሮንቶስን ሰዎች ገንዘብ በመጠየቅ ሸክም ሊሆንባቸው አለመፈለጉ ብቻ ነው። 

ክቁጥር 14-18- ሐዋርያው ወደ ቆሮንቶስ በሚሄድበት ጊዜ እንዳማይከብድባቸው ያረጋገጥላቸዋል። የሚፈልገው ገንዘባቸውን ሳይሆን እነርሱን ነው። ይህም ገዘቡን ሳይቀር ሕይወቱን እንኳ የሚሠዋላቸው መሆኑን ይመሰክርላቸዋል። እንደ ጥሩ አባት ለልጆቹ ያጠራቅማል እንጂ በልጆቹ ላይ ሸክም አይሆንም። 

በቁጥር 16 ላይ «ሸንጋይ ሆኜ በተንኮል ያዘኋችሁ» ማለቱ ሐሰተኛ አስተማሪዎቹ የሰነዘሩበትን ክስ በአሽሙር ሲያከሽፍ ነው። ምናልባት እንዲህ ብለው ይሆናል፤ «ጳውሎስ በቀጥታ ገንዘብ ከእናንተ ያልተቀበለው ለኢየሩሳሌም ድሆች ብሎ የሰበሰበውን እኪሱ እያስገባ ነው»። 

በሚከተሉት ጥቅሶች (ቁጥር 17ና 18) ራሱ ጳውሎስም ገንዘቡን እንዲሰበስቡ የላካቸውም በታማኝነት እንደነበሩ ያስታውሳቸዋል። ችግር ከተነሣ በኋላ ለችግርና ለሐሜት መፍትሔ ለመፈለገ ከመራወጥ አስቀድሞ ጥንቃቄ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ከዚህ ከሐዋርያው ሕይወት እንማር። 

ከቁጥር 19-21:- በቁጥር 19 ላይ «ለእናንተ ስለራሳችን እንድንመልስ ሁልጊዜ ይመስላችኋልን?» ማለቱ ሐዋርያው ይህንን ስለራሱ ንጽሕና አጥብቆ የቆሮንቶስን ሰዎች ለማሳመን መናገሩ እነርሱ ዳኛ ሆነው እርሱ ተከሳሽ ሆኖ በእነርሱ ፊት አቤቱታ ማቅረቡ አለመሆኑን ማስታወቁ ነው። ይህንም ያደረገው እነርሱ በእርሱ እንዳይሰናከሉ ለእነርሱ ጥቅም እንጂ በእነርሱ ዘንድ ንጹሕ ሆና መታየት ለእርሱ አስፈላጊ ነገር ሆኖ አልነበረም። ራሱን ግን በእግዚአብሔር ፊት ማቅረብና ፍርድን ከእግዚአብሔር  መጠበቅ ያስፈልገው እንደነበር ያስታውቃቸዋል። 

በቁጥር 20 እና 21 በፊት የደረሰበት አሁንም እንዳይደርስበት ይፈራ እንደነበር ይናገራል። በፊት ሊጎበኛቸው በሄደ ጊዜ ብዙዎች በኃጢአት ወድቀው አገኛቸው። በዝሙት በመከፋፈል በመጣላት። አሁን ግን እንደዚያ ሆነው ቢያገኛቸው ጥብቅ ቅጣት እንደሚያደርስባቸውና እርሱም በእነርሱ ውድቀት ከባድ ኃዘን እንደሚደርስበት ይገልጻል። 

2ኛ ቆሮ. 12:1-10

ጥያቄ 11. ከቁጥር 1-7 ባለው ክፍል ውስጥ ሐዋርያው ጳውሎስ የሚናገረው ስለማን ነው? 

ጥያቄ 12. ከቁጥር 7-10 ባለው ክፍል ውስጥ ሐዋርያው በደረሰበት ችግር ምክንያት ምን ተማረ? እኛስ ከሐዋርያው ጳውሎስ ስለዚህ ዓይነት ነገር ምን ልንማር ይገባናል? 

በዚህ ክፍል ውስጥ ሐዋርያው ጳውሎስ የሚናገረው ስለ ራሱ ነው፡፡ ሐሰተኛቹ አስተማሪዎች ስለራሳቸው ራእይ ብዙ በመናገር ራሳቸውን ከፍ ከፍ ሳያደርጉ አይቀሩም። ጳውሎስ ስለራሱ ራእይ ይናገር ስላልነበር ራእይ ያልተሰጠው አድርገው በመገመት ትምህርቱንና ሥልጣኑን ያንቋሸሹ ነበር። ይህን ዓይነት ሐሰታቸውን ለማጋለጥና የቆሮንቶስን ቤተ ክርስቲያን ወደ ሐሰት ትምህርታቸው ለመጠምዘዝ ያደርጉ የነበረውን ሙከራቸውን ለማክሸፍ እርሱ ራሱም ስለተሰጠው ራእይ መናገር ገድ ነበረበት። 

ይህን ራእይ ያየው እርሱ እንዳልሆነ አድርጎ ይናገራል። ግን ዝቅ ብለን በቁጥር 7 ላይ «ስለዚህም በመገለጥ ታላቅነት እንዳልታበይ» በማለት ስለራሱ ራእይ የሚናገር መሆኑን እንረዳለን። ሐሰተኛቹ ስለራሳቸው ራእይ ሳይጠየቁ ያወሩ እንደነበር፥ ሐዋርያው ግን ግድ ደርሶበት ብቻ ይናገራል። ጳውሎስ ያየውን ራእይ ሰፋ ባለ ሁኔታ አያብራራውም። ከአሥራ አራት አመት በፊት ያየው ራእይ ነበር። ራእዩው እንዴት እንደታየው በሥጋ ይሆን ወይም አይሆን ወይም ደግሞ ሥጋው እዚህ ምድር ላይ ቀርቶ በመንፈሱ ወደ ሰማይ ተነጥቆ እንደሆነ የሚያውቀው ነገር የለም። ወደ ገነት በር የተነጠቀው (ሦስተኛ ሰማይ)። ይህ ማለት ወደ መንግሥተ ሰማይ ሲነጠቅ በእግዚአብሔር ፊት ቀርቧል ማለት ነው። (ለምሳሌ ዮሐንስ ያየውን ራእይ በዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ ላይ ተመልከት)። የመጀመሪያው ሰማይ በምድር በላይ ያለው አየር ነው። ሁለተኛው ሰማይ ደግሞ ከበላዩ የሚገኙ የክዋክብትና የፕላኔቶች ጥርቅም ነው። በገነት ያየውን ነገር ለማብራራት አልፈለገም። ለዚያውም እንዳይታበይ የሚጎስመው የሰይጣን መልእክተኛ የተላከበት መሆኑን ይናገራል። 

“የሰይጣን መልእክተኛ” የነበረው ማን እንደሆነ አናውቅም። አንዳንድ ሰዎች የዓይን ሕመም ነው ይላሉ። ሌሎች ደግሞ የተለየ በሽታ ነው ይላሉ። ያም ሆነ ይህ የማያቋርጥ ችግር ነበር። በዚህም ምክንያት በተሰጠው ራእይ ሳይሆን በክርስቶስ ጸጋ ብቻ እንጂመካ እግዚአብሔር እንዳስተማረው ይናገራል። ጳውሎስ፥ የእርሱ አገልግሎት ታላቅነት የተመሠረተው በእርሱ ጥረት ሳይሆን በእግዚአብሔር ላይ እንደነበር ተገንዝቧል። ምንም እንኳ በትምህርቱ፣ በሥራው ወይም ባያቸው ራእዮች በቀላሉ ሊመካ ቢችልም እግዚአብሔር  ጳውሎስ ለኃይልም ሆነ ለድል በእርሱ ላይ መታመን እንደሚገባው አስተምሮታል። ይህም በእግዚአብሔር  ሁሉን አድራጊነት እንዲታመንና በራሱ ላይ እንዳይታመን አድርጎታል። 

ጥያቄ 13. ይህ ሊገነዘቡት የሚገባ በጣም አስፈላጊ መመሪያ የሚሆነው ለምንድነው? 

ከዚህ ሰፊ መንፈሳዊ ትምህርት ልንማር ይገባናል። ችግራችን እንቅፋት ሳይሆን የበረከት መሣሪያ እንደሆነ መዘንጋት የለብንም። ክርስቲያንን ከሚጥለው ታላቁ ችግር ትዕቢት ነው። የትዕቢትም መድኃኒት ሰው ደካማነቱን መረዳቱ ነው። ሰው ደካማነቱን የሚማረው በሚደርስበት መከራ እንደሆነ መዘንጋት የለብንም። 

ሐዋርያው ለጸሎቱ እግዚአብሔር የሰጠው መልስ «ጸጋዬ ይበቃሃል፤ ኃይሌ በድካም ይፈጸማልና» የሚል ነበር። ስለዚህ ሐዋርያውም «እንግዲህ የክርስቶስ ኃይል ያድርብኝ ዘንድ በብዙ ደስታ በድካሜ ልመካ እወዳለሁ» አለ። እኛም የችግራችንን ዓላማ በመረዳት ችግራችን በሚያስተምረን ድካም በመመካት የክርስቶስ ኃይል እንዲያድርብን በእምነት መቆም አለብን። 

ጥያቄ 14. ይህ እውነት እንዴት በአንተና በሌሎች ሕይወት ውስጥ እንደሚታይ ምሳሌ በመስጠት አስረዳ፡፡

2ኛ ቆሮ. 11:22-33

ጥያቄ 5. «ማንም በሚደፍርበት እኔ ደግሞ እደፍርበታለሁ» ሲል ምን ማለቱ ነው? 

ጥያቄ 6. ከቁጥር 22-29 ድረስ በሦስት ዓይነት መንገዶች ሐዋርያው ትምክህቱን ይገልፃል፤ እነዚህ ሦስት መንገዶች ምንድናቸው? 

በዚህ ክፍል ውስጥ ሐዋርያው ስለራሱ ትውልድና ስለአገልግሎቱ በመዘርዘር ትምክህት የሚገባ ቢሆን እርሱ የሚመካበት እንዳለው ይናገራል። የሚመካባቸው ሦስት ነገሮች አሉ፤ እነርሱም፡- እስራኤላዊነቱ፥ በክርስቶስ ወንጌል ምክንያት ብዙ መከራን መቀበሉና ስለራሱ ሳይሆን ስለቤተ ክርስቲያን ደህንነት ያለው ጭንቀቱ ናቸው። 

1ኛ/ በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ላይ ችግርን የፈጠሩት መምህራን አይሁዶች እንደሆኑ ይገምታል። እነዚህ አይሁዶች በአሕዛብ ክርስቲያኖች ላይ ሥልጣናቸውን አሳይተው አሕዛብ የብሉይ ኪዳንን ሥርዓት እንዲከተሉ ያደርጉ በር፡፡ ጳውሎስ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሊመደብ የሚችል አይሁዳዊ መሆኑን ለማሳየት ሦስት ገለፃዎችን ያደርጋል። 

2ኛ/ ጳውሎስ የክርስቶስ አገልጋይ ስለነበር ብዙ ስደትና መከራ አጋጥሞታል። 

ጥያቄ 7. ለወንጌል ሲል ጳውሎስ ያለፈበትን የፈተና ዓይነት በዝርዘር ጻፍ፤ (ከቁጥር 23-27 )። 

አንድ ታማኝ የቤተ ክርስቲያን መሪ የሚታወቀው ወንጌልን ለማስተላለፍ ሲል በሚያልፍባቸው ችግሮች ነው። ሐሰተኛ መምህራን ከማንኛውም ዓይነት ስደት ይሸሹ በር፤ (ለምሳሌ፡- ገላ.6፡12-13)። ጳውሎስ ግን ለእግዚአብሔር ጥሪ ታዛዥ መሆኑን ያስመሰከረው፥ በፈቃደኝነት ይህንን ሁሉ ለመጋፈጥ በመወሰኑ ነው። ብዙዎቹ ያሳለፏአቸው መከራዎች በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ አልተጠቀሱም። ነገር ግን ጳውሎስ ወንጌላዊ ለመሆን ያለፈበትን የመከራ መንገድ በትንሹም ቢሆን ያሳዩናል። 

ጥያቄ 8. ሀ/ ወንጌል የማስተላለፋ ነገር በዚህ ሁሉ መከራ ውስጥ መታጀቡ ለምንድነው? ለ/ ስለክርስቶስ ለመስበክ በሚነሡበት ጊዜ ወንጌላውያንም ሆኑ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ዛሬ የሚያጋጥሟቸውን የተለያዩ ችግሮች በዝርዝር ጻፍ። 

በቁጥር 29 ላይ ሐዋርያው «የቀረውንም ነገር ሳልቆጥር ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ሃሳብ ነው» ይላል። ይህም ማለት አብያተ ክርስቲያናት ደህና ይሆኑ ይሆን ወይ? ወይስ ደህና አይደሉ ይሆን? በማለት ይጨነቅ ነበር፡፡ ይህም መጨነቁ በሥጋው ይቀበል ከነበረው ስደትና መከራ ይልቅ ይከብደው ነበር። እውነተኛ የበጎች እረኛ ስለበጕቹ እንደሚገደው፥ ሞያተኛው ግን እንደማይገደው ጌታ አስቀድሞ ተናግሮአል፡፡ 

«የሚደክም ማን ነው፤ እኔም አልደክምን?» ሲል ስለ ቤተ ክርስቲያን ያለውን ጭንቀቱን መግለጡ ነው። ቤተ ክርስቲያን በድካም በምትወድቅበት ጊዜ እርሱም አብሮ ድካማቸውን በመካፈል በውድቀታቸው ያዝናል። “የሚሰናከል ማን ነው፤ እኔም አልናደድምን?” ይህም ከመጀመሪያው ጥያቄ ጋር የተያያዘ ነው። ክርስቲያኖች ተሰናክለው በሚወድቁበት ጊዜ በነገሩ በጣም እንደሚያዝንና በተለይ የመውደቃቸው ምክንያት በሆነው ነገር ላይ እንደሚቆጣ ነው። 

እነዚህን ሦስት ነጥቦች አንስቶ የተናገረው ምናልባት ሐሰተኞቹ አስተማሪዎች በእነዚህ በጠቀሳቸው ነጥቦች ይመኩ ይሆናል። እንግጺህ እርሱ በእነዚህ ሁሉ ከእነርሱ የበለጠ መሆኑን ያስታውቃል። አሁንም ይህ ዓይነት አነጋገር አስፈላጊ የሆነበት ምክንያት የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ሰዎች በሐሰተኞቹ አስተማሪዎች ይታለሉ ስለነበረ ነው እንጂ በመሠረቱ ትምክህት አስፈላጊ ሆና አይደለም። 

ጥያቄ 9. ሀ/ ለቤተ ክርስቲያን የሚደረገው ጥንቃቄ ብዙ ችግር የሚያስከትለው ለምንድነው? ለ/ ዛሬ ለሚገኙ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ይህ ምን ዓይነት ምሳሌ ይሆናቸዋል? 

ጥያቄ 10. ሀ/ በአደረጉት ነገር የሚመኩ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች አሉ? ለ/ ይህስ ተገቢ ነው?

2ኛ ቆሮ. 11:16-21

ጥያቄ 1. በቁጥር 1 ላይ በሞኝነቴ ታገሡኝ ይላል፤ አሁን ደግሞ በቁጥር 16 ላይ “ለማንም ሞኝ የሆንሁ አይምሰለው” ሲል በሁለቱ መካከል አስታራቂ ሃሳብ ስጥ። 

ጥያቄ 2. ሐዋርያው ደብዳቤዎቹን ይጽፍ የነበረው በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ነው፤ በቁጥር 17 ላይ ያለውን ንግግር ከዚህ ጋር አስታርቅ። 

ጥያቄ 3. በቁጥር 20 የቆሮንቶስ ሰዎች ከሐሰተኛ አስተማሪዎች የተቀበሏቸውን ግፎች ይዘረዝራል፤ ምን ምን ናቸው? 

ምንም እንኳ በቁጥር 1 ላይ «በጥቂቱ ሞኝነቴ ታገሱኝ» ቢልም በእርግጥ ሞኝ ሆና እንዳልነበረ በዚህ በቁጥር 16 ላይ ያረጋግጣል። ግን እነርሱ ይህን በመናገሩ እንደሞኝ ከቆጠሩት «እንደ ሞኝ እንኳ ሆኜ ተቀበሉኝ» እያለ በአሽሙር ይናገራል። 

በቁጥር 17 ላይ እንደዚያ ስለራሱ በመናገር ሞኝ የመሆን ዝንባሌ ሲያሳይ የክርስቶስን ምሳሌ ይዞ ሳይሆን እዚያን በሥጋ ይመኩ የነበሩትን ሐሰተኞች በገዛ መሣሪያቸው ለማጋለጥ የወሰደው እርምጃ ብቻ ነበር። ስለዚህ “በሞኝነቴ እንጂ ጌታ እንዳዘዘኝ አልናገርም» ይላል። የተናገረው በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ አይደለም ማለት ሳይሆን፥ ነገር ግን የዚህ ዓይነቱ ስለራስ መናገር የሥጋ ፀባይ እንጂ የክርስቶስ ፀባይ አይደላም ማለቱ ነው። 

በቁጥር 18 ላይ “ብዙዎች በዓለማዊ ነገር ስለሚመኩ እኔ ደግሞ እመካለሁ” ይላል። በቁጥር 1 ላይ «በጥቂት» እመካለሁ ይላል። ሐሰተኞች በሥጋ ይመካሉ፤ እርሱ ግን ምንም እንኳ እንደእነርሱ ስለራሱ ቢናገር እነርሱን በማጋለጥ የቆሮንቶስን ክርስቲያኖች ከእነርሱ ለማላቀቅ ነበር። ይህ ዓይነት ታክቲክ በምሳሌ 26፡5 “ለራሱ ጠቢብ የሆነ እንዳይመስለው ለሰነፍ አንደ ስንፍናው መልስለት» በሚለው መሠረት ነው። 

ከቁጥር 19-20፡- የጳውሎስ አሽሙር አሁን አይሏል። እነዚያን ሐሰተኞች ሲያጉላሉአቸው ከታገሷቸው እርሱ በጥቂቱ ሐሰተኞችን ለማሳጣት ያሳየውን ሞኝነት መታገሥ ሊከብዳቸው አይገባም! እነዚያ ሐሰተኞቹ፡- 

1ኛ / ባሪያዎች ያድርገዋቸው ነበር፤ ይህም ማለት የሐሰት ትምህርት በማስተማር ክርስቶስ በወንጌል ከሰጣቸው ነፃነት ወደ ባርነት ይጕትቷቸው ነበር። ምናልባት ወደ ተሻረው ወደ ኦሪት ሥርዓት ማለት ሊሆን ይችላል። 

2ኛ / ይበሏቸው ነበር፤ ይህም ማለት ገንዘብ ወዳድ ስለነበሩ ከመጠን በላይ ገንዘብ ይሰበስቡ ነበር። ከዚህ ጋር ማቴ.28፡ 14ን አስተያይ። 

3ኛ / ይቀሟቸው ነበር፤ ይህም ማለት በማታለል ሌሎች ሲጠቀሙባችሁ ማለት ነው። 

4ኛ/ «ማንም ቢኮራባችሁ»፤ 

5ኛ / «ማንም ፊታችሁን በጥፊ ቢመታው» ሲል በባህላችሁ የሕዝብ መሪዎች የነበሩ ዝቅተኞቻቸውን በጥፊ ያስመቱ ወይም ይመቱ እንደነበር ያመለክታል፤ (የሐዋ.23፡2፤ 1ኛ ቆሮ. 4፡11፤ 1ኛ ጢሞ.3፡3፤ ቲቶ 1:7፤ ማቴ.5፡39፤ 1ኛ ጴጥ.2:19)። 

እንግዲህ የቆሮንቶስ ሰዎች ይህንን ሁሉ ከሐሰተኞች አስተማሪዎች እጅ በትዕግሥት ከተቀበሉ ከሐዋርያው ጳውሎስ «ጥቂት ሞኝነት» መታገሥ ሊከብዳቸው አይገባም። 

ጥያቄ 4. ዛሬ ተከታዮቻቸውን የሚያሳዝኑና የሚያናድዱ ሐሰተኛ መምህራን ስንት ናቸው? 

ቁጥር 21:- ጳውሎስ እንደ ሐሰተኞቹ አስተማሪዎች የቆሮንቶስን ቤተ ክርስቲያን ስላልተጫና «ደካማ ሆኜባችኋለሁ» በማለት በአሸሙር ይናገራል!

2ኛ ቆሮ. 11:7-15

ጥያቄ 14. በቁጥር 10 ላይ «ይህ ትምክሕት» ሲል ስለምንድነው የሚናገረው? 

ጥያቄ 15. ቁጥር 12 ላይ «ምክንያትን ከሚፈልጉቱ ምክንያትን እቆርጥ ዘንድ» የሚለውን አብራራ። 

ጥያቄ 16. በቁጥር 13 ላይ ዋናው የሐሰተኛ አስተማሪዎች ፀባይ ምንድነው ይላል? 

ከቁጥር 7-9፡- ሐዋርያው ወንጌልን በመስበክ የወንጌል ተገልጋዮች ሊደግፉት የተገባ እንደሆነና ይህንን መብቱን ግን እንዳልተጠቀመበት አስቀድሞ በ1ኛ ቆሮ. 9:1-18 ዘርዝሮአል። አሁን ደግሞ በተጨማሪ በዚህ ክፍል ይህንኑ ነጥብ ያነሳል። ለቆሮንቶስ ወንጌልን ሲሰብክ ከእነርሱ ሳይሆን ከመቄዶንያ ቤተ ክርስቲያን እርዳታ ይቀበል ነበር። ይህንንም ሃሳብ ሲገልጥ «እናንተን ለማገልገል … ሌሉችን አብያተ ክርስቲያናት ዘረፍሁ» ይላል። ሌሎች ክርስቲያኖች በሚከፍሏቸው ወንጌላውያን እየተገለገሉ ድርሻን አለመወጣት ዝርፊያ ይባላል፡፡ ስለዚህ መንፈሳዊ በረከትን የሚያመጡልንን አገልጋዮች በአቅማችን በደመወዝ ክፍያ መርዳት አለብን!! 

ቁጥር 10፡- በቁጥር 10 “ይህ ትምክህት” የሚለው ወንጌልን ያለ ደመወዝ መስበኩን ነው። አሁን ይህንን የተናገረው ደመወዝ ፍለጋ አለመሆኑን ያረጋገጥላቸዋል። አካይያ የቆሮንቶስ ከተማ የምትገኘበት አውራጃው ነው። 

ከቁጥር 11-12:- እርዳታ ከቆሮንቶስ ሳይሆን ከመቄዶንያ የተቀበለው የቆሮንቶስን ምእመናን ስላልወደደ እንዳልሆነ «እግዚአብሔር ያውቃል» በማለት በእርግጥ የሚወዳቸው መሆኑን ያረጋግጥላቸዋል። ነገር ግን ወዳፊትም ቢሆን የገንዘብ እርዳታ ከቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን የማይቀበለው የሐሰተኛ አስተማሪዎችን አፍ ለማዘጋት እንደሆነ ይናገራል። 

እነዚያ ወደ ቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ሾልከው የገቡት ሐሰተኛ አስተማሪዎች በነፃነት ገንዘብ ይቀበሉ ስለነበር ሐዋርያው ጳውሎስ ግን ገንዘብ ስላልተቀበለ እንደእነርሱ ተቀብሎ ከእነርሱ እኩል እንዲሆን ይፈልጉ ነበር። ሐዋርያው ግን ገንዘብ ከተቀበል ለእነርሱ አመቺ እንደሚሆንላቸው ስላወቀ አልቀበልም አለ። ይህን ያደረገው ስላልወደዳቸው ሳይሆን ሐሰተኞችን  ለማጋለጥ ፈልጎ ነበር! “እንደ እኛ ሆነው ሊገኙ ምክንያትን ከሚፈልጉት ምክንያትን እቆርጥ ዘንድ አሁን የማደርገውን ከዚህ ወዲህ ደግሞ አደርጋለሁ”። ብዙ ጊዜ ሐሰተኛ መምህራን ሌሎችን ወደ ራሳቸው የሚስቡት ያሉትን መሪዎች ድክመት በመጥቀስ ነው። ብዙ ጊዜ ወጥመድ አዘጋጅተው መሪዎች እንዲሰናከሉ ያደርጋሉ። ወይም ጥሩ ለሆኑ ድርጊቶች የተሳሳተ ትርጓሜ ይሰጣሉ። 

ጥያቄ 17. ይህ ሲደረገ አንዴት እንዳየህ የሚገልጽ ምሳሌ ስጥ። 

ከቁጥር 13-15፡- በዚህ ክፍል ተጨማሪ የሆነ የሐሰተኛ አስተማሪዎች ፀባይ ይዘርዘርልናል። 

– የክርስቶስን ሐዋርያት ለመምሰል ራሳቸውን ይለውጣሉ። 

– ውሸተኞች ሐዋርያት ናቸው። 

– ተንኮላኛ ሠራተኞች ናቸው። 

– የሰይጣን ፀባይ አላቸው፤ ሰይጣን የብርሃን መልአክ ለመምሰል ራሱን እንደሚለውጥ እነርሱም የክርስቶስን ሐዋርያት ለመምሰል ራሳቸውን ይለውጣሉ። ነገር ግን እውነተኛው ፈራጅ ፍጻሜአቸውን እንደሥራቸው ያደርጋል! 

የጨለማው አምላክ ሰይጣን ብዙ ጊዜ ሌሎችን የሚያስተው «የብርሃን መልአክ» መስሎ በመቅረብ ነው። በሌላ አነጋገር የሚጠቀምባቸው ዘዴዎችና ሁኔታዎች ሁሉ ክርስቲያኖች ጥሩ ናቸው ብለው የሚገምቷቸውን ነገሮች ነው። በዚህም ምክንያት ብዙዎችን ወደ ኃጢአት ይመራል። የእርሱ አገልጋዮች የሆኑት ሐሰተኛ መምህራንም ብዙ ጊዜ ጥሩ ነው ተብሎ የሚገመተውን ነገርና ሁኔታ በመጠቀም ነው ሌሎችን እነርሱን እንዲያምኑ የሚያደርጉት። ያም ሆነ ይህ ዋናው ዓላማቸው ሌሎችን አታለው ወደ ጥፋት መምራት ነው። ምንም እንኳን በመጃመሪያ አኳኋናቸው በቀላሉ ከጥሩ መሪዎች ለይተን ልናውቃቸው ባንችልም፥ ቀስ በቀስ ግን መከፋፈልን ይፈጥራሉ። በዚህም የራሳቸውን ሐሰተኛ መምህርነት ይፋ ያወጣሉ። 

ጥያቄ 18. በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ሐሰተኛ መምህራን የሰይጣን አገልጋዮች ሆነው ሳለ «የብርሃን መልአክ» መስለው ለመቅረብ የሞከሩበት ጊዜ አለ?

2ኛ ቆሮ. 11፡1-6

ጥያቄ 10. በቁጥር 1 ላይ «በጥቂቱ ሞኝነቴ ብትታገሡኝ መልካም ይሆን ነበር» ሲል ምን ማለቱ ነው? 

ጥያቄ 11. በቁጥር 3 ላይ ሐዋርያው እባብ ሔዋንን እንዳሳታት እናንተም በመታለል እንዳትወሰዱ በማለት ሥጋቱን ይገልጣል፤ ይህ ሥጋቱ የተመሠረተው እምን ላይ በር? 

ጥያቄ 12. በቁጥር 5 ላይ ዋነኞች ሐዋርያት የሚላቸው እነማንን ነው? 

ቁጥር 1፡- «በጥቂት ሞኝነቱ ብትታገሡኝ» ሲል ሞኝነት ያለው ስለ አገልግሉቱ መናገሩን ነው። ሐዋርያው ስለ ራሱ አገልግሎት መናገር ግድ የሆነበት የቆሮንቶስን ምእመናን ከስሕተት ለመመለስ ነበር። ስለዚህ ስለራሱ መናገሩን ሞኝነት በማለት፥ ስለራሱ እንዲናገርና ከስሕተት እንዲመልሳቸው እንዲታገሱት ይጠይቃቸዋል። 

ከቁጥር 2-3፡- ሐዋርያው ለቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን በቅዱስ ቅንዓት እንደቀና ይነግራቸዋል። የቀናላቸው ስላፈቀራቸው ነው። ሰው የሚቀናው ለሚወደው ብቻ ነው። ቅንዓቱም በራሱ ጥቅም ላይ የተመሠረተ ሳይሆን በክርስቶስ ክብር ላይ የተመረኮዘ ነው። የቆሮንቶስን ቤተ ክርስቲያን ለክርስቶስ ሙሽርነት አጭቷል። ስላጫት ሰይጣን በማታለል ከክርስቶስ እንዳይወስዳቸው ቅዱስ ቅንዓቱን ይገልጻል። ሰይጣን ይህን የማታለል ሥራውን በሔዋን ጀምሮ አሁንም በቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ላይ በማካሄድ ላይ ይገኛል። 

ቁጥር 4:- «የሚመጣውም» ያለው ሐሰተኞችን አስተማሪዎች ነው። ሐዋርያው የሰጋላቸው ሐሰተኛ አስተማሪዎችን የመታገሥ ፀባይ ስላሳዩ ነው፡፡ ሐሰተኛ አስተማሪዎችን መታገሥና ማዳምጥ ወደ ጥፋት ማዘንበል ነው። ሔዋን ከጠላቷ ጋር ውይይት ባትይዝ እውድቀት ላይ ባልደረሰችም ነበር። ሐዋርያው ዮሐንስም በ2ኛ ዮሐ.10 ላይ ከሐሰተኛ አስተማሪዎች ጋር ግንኙነት እንዳንፈጥር ይከልክለናል። እንግዲህ ሐዋርያው የሚለው መታገሥ የማይገባችሁን እነዚህን ሐሰተኞች ከታገሣችሁ እኔንም ለእናንተ ጥቅም በማደርገው ስለራሴ የመናገር ሞኝነት ታገሡኝ ነው። 

ቁጥር 5፡- «ዋነኞች ሐዋርያት» የሚለው በአሽሙር አነጋገር ነው። ሐሰተኞቹ አስተማሪዎች ማንም ሳይሾማቸው ዋና ሐዋርያትነትን ለራሳቸው ሰጥተው ይመጻደቁ ስለነበር ነው። ጳውሎስም ከእነርሱ በምንም የማያንስ መሆኑን ይናገራል። 

ቁጥር 6፡- እነዚህ ሐሰተኛ አስተማሪዎች «ጳውሎስ ንግግር አይችልም› የማለት ነቀፋ ሳይሰነዘሩበት አይቀሩም፤ ስለዚህ «በአነጋገሬ ያልተማርሁ ብሆን እንኳ» ይላል። ሆኖም እንደእነርሱ በአፈ ጮሌነትና ቃላትን በማሳመር አይመካም፤ (1ኛ ቆሮ. 2፡4-5)። የሚሰብከው ወንጌል የሰው እውቀት ሳይሆን እግዚአብሔር የገለጠለትን ጥበብ ስለሆነ በእውቀት ከእነዚህ በሰው ጥበብ ከሚመኩ ሐሰተኛ የበለበ መሆኑን ይናገራል። በሁሉም ነገር ግልጥ ሆና አንደቀረበ ያስታውሳቸዋል። 

ጥያቄ 13. ከዚህ ትምህርት ላይ የምታያቸውን የተለያዩ የሐሰተኛ ባሕርያት በዝርዝር ጻፍ፡፡

2ኛ ቆሮ. 10፡13-18

ጥያቄ 5. “እስከ እናንተ እንኳ እንደሚደርስ እንደ ክፍላችን ልክ እንጂ ያለልክ አንመካም” ማለት ምን ማለት ነው? 

ጥያቄ 6. በቁጥር 16 ላይ “በሌላው ክፍል ስለተዘጋጀው አንመካም» ማለት ምን ማለት ነው? 

ቁጥር 13:- ሐዋርያው አገልግሎቱን ለሩጫ እሸቅድድም እንደተሰለፈ ሰው ይመስላል፡፡ በሩጫ ሕጋቸው ለእያንዳንዱ ሯጭ መሥመር ይደለደል ነበር። በመሥመሩ ብቻ መሮጥ ነበረበት እንጂ በሌላ ሰው መሥመር ውስጥ ሾልኮ ቢገባ ከሩጫው ውድድር ይወጣ ነበር። እንዲሁም ጳውሎስ እግዚአብሔር የሥራ መስክ እንደዘረጋለትና በዚያው መሥመር «ሕጉን» ጠብቆ እንዳለ፥ እነዚያ በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ግን ሾልከው የገቡት እግዚአብሔር ባልሰጣቸው የሥራ መሥመር ጣልቃ ገብ መሆናቸውን ይናገራል። ሌሎች ወደ ክርስቶስ የመሩአቸውን አማኞች እየሰረቁ ቤተ ክርስቲያንን ማስፋፋትና አዲስ ቤተ ክርስቲያን እያሉ በሌሎች ድካም ላይ መንጠልጠል የሐሰተኛ አስተማሪዎች ፀባይ መሆኑን በዚህ ቃል እንገንዘብ፡፡ 

ጥያቄ 7. ይህን መሰል ጣልቃ ገብ ሠራተኞች ታውቃለህ? እነማን ናቸው? ጥቀሳቸው! የእነርሱንም ፀባይ ለምእመናን በማስረዳት ከእነርሱ እንዲጠበቁ አስጠንቅቃቸው!! 

ቁጥር 14:- ሐዋርያው በተዘረጋለት የአገልግሎት መሥመር እስከ ቆሮንቶስ ደርሷል። ስለዚህ በሌሎች ሥራ ገብቶ አይደለም የተመካው። ሐሰተኞቹ አስተማሪዎች ግን እርሱ በደከመበት ወይም እርሱ በሠራበት ጣልቃ ገብተው ነበር ይመኩ የነበረው። 

ከቁጥር 15-16፡- ከላይ የጀመረውን ሃሳብ በመቀጠል የወንጌል ሥራውን ከቆሮንቶስ አልፎ ለመቀጠል አንደተዘጋጃ ይናገራል። በራሱ በተሰጠውና ባገለገለበት መሥመር እንጂ ሌሎች በሠሩት ላይ ጣልቃ በመግባት ለመመካት እንደማያስብ ይገልጻል፡፡ ይህን የሚያደርጉት ሐሰተኞች አስተማሪዎች እንደሆኑም በእጅ አዙር ይናገራል። የጳውሎስ ምኞት የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን በእምነት ጎልምሳ አድጋ ቤተ ክርስቲያን ወዳልደረሰበት ቦታ ወንጌልን ይዞ የማሰራጨቱን ሥራ እንድትረዳው ነበር። በትዕቢት ተነፍተው ስለ ራሳቸው ብቃት ከሚያስቡ፥ የጠፉትን ሰዎች በመመለስ መንፈሳዊነታቸውን ማሳየት ነበረባቸው። በዚህ ዓይነት እነርሱ «የሚመኩበት» ነገር ይኖራቸው ነበር። ሐሰተኛ መምህራን ብዙ ጊዜ ክርስቲያኖችን አባል ከሆኑበት ቤተ ክርስቲያን ለማፈናቀል ነው የሚሞክሩት። ወንጌልን ወዳልተዳረሰበት ሥፍራ ይዘው አይሄዱም። አንድ በደንብ ያደገች ቤተ ክርስቲያን የምትለይበት አንዱ ባሕሪዋ ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ አዳኛቸው ለማያውቁት ሰዎች ወንጌልን ለማድረስ ባላት ሸክም ነው። 

ጥያቄ 8. በአካባቢህና በመላው ኢትዮጵያ ያልዳኑትን ሰዎች ለማምጣት የአንተ ቤተ ክርስቲያን የምታደርገውን ጥረት አብራራ። 

ከቁጥር 17-18፡- ሐዋርያው ስለራሱ አገልግሎት እንዲናገር ሁኔታው አስገደደው እንጂ በዚህ ዓይነት ንግግር ከሐሰተኛ አስተማሪዎች ጋር እንካ ስላንቲያ መለዋወጥ አልፈለገም። ይህንንም ያደረገው የቆሮንቶስን ቤተ ክርስቲያን ከሐሰተኞች እጅ ለማውጣት አስፈላጊ ስለሆነበት ብቻ ነው። ሆኖም እንዲህ እውነትን በመመርኮዝ ስለራሱ ሥራ ይናገር እንጂ መመኪያው የእርሱ ሥራ ሳይሆን የእግዚአብሔር ጸጋ እንደሆነ ይናገራል። 

ጥያቄ 9. ሀ/ ስለ ሐሰተኛ መምህራን የተሰጡትን ተጨማሪ ባሕሪያት ዘርዝረህ ጻፍ። ለ/ ቤተ ክርስቲያናችሁን ሊያፈርሱ የሚሞክሩትን ሐሰተኛ መምህራን ቤተ ክርስቲያንህ የምትዋጋቸው በእንዴት ዓይነት ሁኔታ ነው? ሐ/ መወሰድ ይገባቸዋል ብለህ የምትገምታቸው እርምጃዎች ምን ምንድናቸው? 

2ኛ ቆሮ. 10:7-12

ጥያቄ 1. ቁጥር 7ን አብራራ። 

ጥያቄ 2. በቁጥር 12 ላይ ጳውሎስ ራሱን ከአንዳንዶች ጋር ማወዳደር አልደፍርም ሲል ምን ማለቱ ነው? ከእነርሱ አንሳለሁ ማለቱ ነው? አብራራ። 

ቁጥር 7:- “በፊታችሁ ያለውን ተመልከቱ”። በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ሾልከው የገቡት ሐሰተኛ አስተማሪዎች ጳውሎስን ሐሰተኛ ነው በማለት ይናገሩ ነበር። ለእነርሱ መልስ ሲሰጥ «ማንም በእርግጥ የክርስቶስ ከሆነ እኔ ደግሞ በክርስቶስ እንደሆንሁ ያውቅ ነበር፤ ነገር ግን እኔን ሐሰተኛ ነው ካለ እኔ በእርግጥ በክርስቶስ ስለሆንሁ እርሱ ራሱ ሐሰተኛ መሆኑን በራሱ ፍርድ ይመሰክራል» ይላል። ይህ ለእኛም ትምሕርት ይሁነን። ሃሰተኛ አስተማሪዎች ሁልጊዜ ከእነርሱ በስተቀር መንፈሳውያን ወይም ከእነርሱ በስተቀር እውነተኛ ክርስቲያን እንደሌለ አድርገው ሌሎችን በማንገዋለል ራሳቸውን ከፍ ከፍ ያደርጋሉ፡፡ 

ጥያቄ 3. የዚህ ዓይነት ፀባይ ያላቸውን ክርስቲያን ነን ባዮች ታውቃለህ? ጥቀሳቸው። 

ቁጥር 8፡- ሐዋርያው ቤተ ክርስቲያንን ለመገንባት ጌታ ስጦታ እንደሰጠው የመሠረታት የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ማረጋገጫ ናት። ስለዚህ ሐዋርያው ሥልጣን ያለው መሆኑ እንደሐሰተኛ አስተማሪዎች በወሬ ብቻ አልነበረም። 

ከቁጥር 9-11:- ሐዋርያው በዚህ ክፍል ለተሰነዘረበት ሐሜት መልስ ይሰጣል። ክርስቶስ የሰጠው ኃይል በሩቅ በደብዳቤ ብቻ ሳይሆን በቅርብ ፊት ለፊት ያው ነው ይላል። መሆኑንም በእርግጥ በመካከላቸው ተገኝቶ በደብዳቤ የነገራቸውን ፊት ለፊት ሊነግራቸው ዝግጁ መሆኑን ያረጋገጥላቸዋል። 

ቁጥር 12፡- ራሳቸውን ከሚያመሰግኑ ጋር ራሱን ሊያወዳድር የማይደፍር መሆኑን ሲናገር በአሽሙር መናገሩ ነው። በእርግጥ ከእነርሱ ያስሁ ነኝ ማለቱ አይደለም። በዚሁ ቁጥር ላይ ዝቅ ብሉ ራሳቸውን የሚያመሰግኑት ራሳቸውን በራሳቸው በማስተያየት ብቻ ነው ይላል። ሐዋርያው ግን ጥሪውን በክርስቶስ ቃልና በአገልግሎቱ ፍሬ ነበር ይመዝን የነበረው። እንግዲህ በዚህ ቃል መሠረት በግል ቡድን ብቻ ፈጥረን በዚያው በቡድናችን እርስ በርስ እየተመሰጋገንን መኩራራት አደገኛ እንደሆነ አንዘንጋ፡፡ ከግል ቡድናችን ወጣ ብለን ጌታ በሌሎችም ዘንድ በሌሎች ውስጥ የሚሠራውን ማመዛዘን ይኖርብናል። 

ጥያቄ 4. ሀ/ በዚህ ትምህርት ላይ ስለ ሐሰተኛ መምህራን የተሰጡትን ባሕርያት በዝርዝር ጻፍ። ለ/ ይህንን ዓይነት ባሕርይ የያዙ ሐሰተኛ መምህራን በቤተ ክርስቲያንህ ወይም በሌላ ቦታ ያየኸው በእንዴት ዓይነት ሁኔታ ነው? 

2ኛ ቆሮ. 10፡1-6

ጥያቄ 15. በቁጥር 2 ላይ “በዚያ እምነት ግን ከእናንተ ጋር ሆኜ እንዳልደፍር አለምናችኋለሁ” ሲል ምን ማለቱ እንዳሆነ ይህን ክፍል በጥንቃቄ በመመልከት አስረዳ። 

ጥያቄ 16. በቁጥር 3 ላይ ሐዋርያው በሰው ልማድ እመላለሳለሁ ሲል ምን ማለቱ ነው? 

ጥያቁ 17. በቁጥር 2 ላይ ሁለት ወገኖች ተጠቅሰዋል፤ ማንና ማን ናቸው? 

ቁጥር 1:- ሐዋርያው ስለመስጠት ያለውን ትምህርት ጨርሶ ሌላ ርዕስ ይከፍታል። ይህ ርእስ ከምዕራፍ 10 ጀምሮ እስከ ምዕራፍ 13 ይቀጥላል። በዚህ በቁጥር 1 «በእናንተ ዘንድ ሳለሁ ትሑት የሆንሁ» ይላል። ይህንም ያለው በአሽሙር ሲናገር ነው። ዝቅ ብለን በዚሁ ምዕራፍ በቁጥር 10 ላይ በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ሾልከው የገቡት ሐሰተኛ አስተማሪዎች ጳውሎስን “መልእክቶቹስ ከባድና ኃይለኛ ናቸው ሰውነቱ ግን ሲታይ ደካማ ነው” እያሉ ያሙት ነበር። ስለዚህ ያንን ሐሜት በአሽሙር መልክ ይደግመዋል። 

ቁጥር 2፡- ይህ ክፍል አነጋገሩ ጥምዝምዝ ነው ግን ቀጥተኛ ትርጉም ስለሆነ በጥንቃቄ እንረዳው። ሃሳቡ ይህ ነው፡- … በሥጋ የምመላለስ እየመሰላቸው የሚንቁኝ በመካከላችሁ አሉ። በእነርሱ ላይ ልደፍር ሙሉ በሙሉ ተማምኜ እመጣለሁ። ነገር ግን በእነርሱ ላይ ልደፍር በተማመንኩበት ዓይነት ድፍረት በቀራችሁትም ላይ መድፈር አልፈልግምና እባካችሁ ጥፋታችሁን በማረም ከዚያ አድኑኝ፤ … የማለት አነጋገር ነው። 

«በዓለማዊ ልማድ» ቁጥር 2፤ «በሰው ልማድ» ቁጥር 3፤ «ሥጋዊ» ቁጥር 4፤ እነዚህ የተለያዩ ቃላት የሚተረጉሙት በግሪክኛ አንድ ዓይነት ቃል ነው፤ ያም፡- «ሥጋዊ» የሚል ቃል ነው። ስለዚህ ሦስቱንም ጥቅሶች በዚህ ቃል በመተካት ጥቅሱን እናብራራ። 

በሥጋ እንደምንመላለስ በሚቆጥሩን በአንዳንዶች ላይ አምኜ ልደፍር አስባለሁ፤ በዚያ እምነት ግን ከእናንተ ጋር ሆኜ እንዳልደፍር እለምናችኋለሁ። በሥጋ ምንም እንኳ የምንመላለስ ብንሆን በሥጋ አንዋጋም፤ የጦር ዕቃችን ሥጋዊ አይደለምና። 

እንግዲህ በቁጥር 3 ላይ ከላይ እንደተተረጎመው «በሥጋ ምንም እንኳ የምንመላለስ ብንሆን» ሲል በዚህ በሰውነት ነን ማለት ነው። ለምሳሌ በዮሐንስ 1፡14 ላይ «ቃል ሥጋ ሆነ» ያለው ዓይነት ሥጋ ማለት ነው እንጂ ሥጋ የኃጢአት ኑሮ ማለቱ አይደለም። የሐዋርያው ተቃዋሚዎች ግን «ጳውሎስ ሥጋዊ ነው» ሲሉ ኃጢአተኛ ነው ማለታቸው ነበር። እንግዲህ ነገራቸውን ዘወር ያደርግና ምንም እንኳ ሥጋ ለባሽ ብሆንም እንደእነርሱ ውሸትና ሐሜት በተሞላ መንገድ በሥጋ አልዋጋም ይላል። 

ሐዋርያው ሊዋጋ የተነሣው ሾልከው ከገቡት ሐሰተኛ አስተማሪዎች ጋር ነበር። ሐሰተኛ አስተማሪዎች ሾልከው ገብተው በጎችን አንዳይሰርቁ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችና ሽማግሌዎች መዋጋት አለባቸው። አዳም ሰይጣን እገነት አንዳይገባ መዋጋትና ሚስቱን ማስጠንቀቅ ነበረበት! እንዲሁም በትንቢተ ዘካርያስ 3:7 ላይ እግዚአብሔር ሊቀ ካህኑን ኢያሱን «አደባባዮቼንም ትጠብቃለህ» ይለዋል። አደባባይ ማለትም መግቢያ በር ነው። ሰይጣንን እግዚአብሔር እንደገሠጸለት ኢያሱ ደግሞ የሰይጣን ተከታዮች የሆኑትን ሐሰተኛ አስተማሪዎች ሾልከው እንዳይገቡ መከላከል ነበረበት። እንዲሁም ሐዋርያው በቆሮንቶስ የገቡትን ወንበዴዎች ሊያባርር ተዘጋጀ። 

አንደኛው የሐሰተኛ አስተማሪዎች ጸባይ ቤተ ክርስቲያንን መበጥበጥና ሰላም መንሣት ነው። ሁለተኛው ጸባያቸው አስመስሎ መግባት ወይም መሹለክ ነው። በግልጽ እውነትን ተቀብለው ገብተው ሳይሆን በመጀመሪያ በግ መስለው ገብተው ነው በኋላ የተኩላነት ጸባያቸውን የሚያሳዩት። ሦስተኛ ጸባያቸው ለራሳቸው ተከታዮችን መሰብሰብ ነው። ቤተ ክርስቲያንን የመከፋፈል ኑፋቄያዊ ባሕርይ አላቸው። የሐዋርያት ሥራ 20፡29-30 ሐሰተኛ አስተማሪዎች ለራሳቸው ተከታዮችን ይሰበስባሉ ይላል። አራተኛው ጸባያቸው እውነትን በማጣመም ማታላል ነው። 

ጥያቄ 18. ለውይይትህ እንዲረዳህ በዚህ ከአንድ እስከ አራት በተዘረዘሩት መልክ የሚገጥሙ የሐሰተኛ አስተማሪዎችን ስም ዘርዝር! 

ሐዋርያው ዝቅ ብሎ በ11፡3 ላይ እነዚህ ሐሰተኛ አስተማሪዎች የቆሮንቶስን ቤተ ክርስቲያን ሰዎች ሰይጣን ሔዋንን አንዳሳታት እንዳያጣምሟቸው ያስጠነቅቃል። 

ከቁጥር 4-5፡- ሐዋርያው ውጊያውን በሥጋዊ መልክ ሳይሆን እውነትን በመግለጥ በእውነት መሣርያ ብቻ ለመዋጋት ይነሣል። ሐሰተኛ አስተማሪዎች ሥራቸው ሐሰት የተሞላበት ስለሆነ ከመንፈሳዊነታችን ወጥተን እንደእነርሱ በሥጋ እንድንዋጋ ሊያደርጉን ስለሚችሉ በጣም መጠንቀቅ አለብን። እነርሱ ሥጋዊ በሆኑ ከላይ ከአንድ እስከ አሪት በተዘረዘሩት ሲዋጉን በሥጋ በሆነ ስድብና ንዴት እንዳንወድቅ እንጠንቀቅ። በዚህ ዓይነት መንገድ በሥጋ ብንራመድ ጣታቸውን እየጠነቆሉ ምእመናንን ከእኛ ለመጐተት ይመቻቸዋል። 

የፈለጉትን ያህል እርኩሶች ቢሆኑም፥ ሐሰተኛ መምህራንን በመንፈሳዊ ዘይቤዎች በመታገዝ መዋጋት አለብን። ሰይጣን በእነርሱ በመጠቀም ሰዎችን ከእውነት እንዲኮበልሉ ያደርጋል። ጳውሎስ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ለእኛ የተሰጠውን ኃይል ያስታውሰናል። በዚህ ኃይል በመጠቀም ነው የሰይጣንንና የሐሰተኛ መምህራንን ምሽግ? ልናፈራርስ የምንችለው። ለማሸነፍ ፈቃዳችንንና አእምሮአችንን በጥንቃቄ በመጠበቅ መዘጋጃት ይገባናል። ሙሉ በሙሉ በኢየሱስ ክርስቶስ ቁጥጥር ሥር መሆን አለብን፤ በተጨማሪም ለእርሱ ታዛዦች መሆን አለብን። ይህ ካልሆነ ግን እንሸነፋለን። 

ቁጥር 6፡- መታዘዛችሁ በተፈጸመ ጊዜ ማለቱ የእውነተኞች አማኞች ለእውነተኛው መሪ መታዘዝ ማለት ነው። ይህ ከተፈጸመ በኋላ ሐሰተኞችን መቋቋም ይቻላል። ስለዚህ ሐዋርያው ቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ከመድረሱ በፊት ምእመናኑ በመንፈሳቸው ተዘጋጅተው እንዲጠብቁት ይመክራል። ከዚያም በአንድ ልብ ሐሰተኞችን ለመቋቋም ይዘጋጃል። 

ጥያቄ 19. ሀ/ እውነተኞቹን መምህራን ከሐሰተኞቹ መምህራን ልንለይ የምንችልባቸውን መንገዶች በዝርዝር ጻፍ። 

ለ/ የሀሰተኛ መምህራንን ትምህርት ልንከላከል የምንችልበትን መመሪያ በዝርዝር ጻፍ።