Site icon

የማቴዎስ ወንጌል መዋቅር እና አስተዋጽኦ

መጽሐፍ ቅዱስን የመጻፉ ተግባር እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስና ሰዎች በጋራ ያከናወኑት መሆኑን ቀደም ብለን ተመልክተናል። መንፈስ ቅዱስ ቃል በቃል እየተናገረ አላጻፋቸውም። ነገር ግን ደራሲያኑ ቃላት እየመረጡ መንፈስ ቅዱስ በልባቸው ውስጥ ያስቀመጠውን ዐላማ ለማሳካት እንዲጽፉ መርቷቸዋል። እንዲሁም መንፈስ ቅዱስ ደራስያኑ መጽሐፎቻቸውን በልዩ መንገድ እንዲያደረጁ ፈቅዷል። ይህም ሆኖ መንፈስ ቅዱስ የተለያዩ ስልቶችን እየተጠቀሙ፥ በሁሉም ዘመን የሚኖሩ ሰዎች እንደ እግዚአብሔር ቃል የሚጠቀሙባቸውን እውነቶች እንዲያስተላልፉ ተቆጣጥሯቸዋል።

ማቴዎስ ቁጭ ብሎ ስለ ክርስቶስ የቻለውን ያህል ታሪክ ለመጻፍ አልሞከረም። ነገር ግን ክርስቲያኖችና ክርስቲያን ያልሆኑ ወገኖች ሊያውቋቸው የሚገቧቸውን ታሪኮች በጥንቃቄ መርጧል። እነዚህን ታሪኮች ያዋቀረው ደግሞ በጊዜ ቅደም ተከተላቸው ሳይሆን፥ በተለየ መንገድ ነበር። ብዙ ምሑራን ማቴዎስ አይሁዶች እጅግ የተቀደሱ የብሉይ ኪዳን ክፍሎች አድርገው የሚመለከቷቸውን የሙሴን መጻሕፍት ተከትሎ፥ መጽሐፉን በአምስት ክፍሎች እንዳደራጀ ያምናሉ። ማቴዎስ በአምስት የተለያዩ የማስተማሪያ ክፍሎች፥ ላይ አተኩሯል (ማቴ. 5-7፥ 10፥13፥ 18፥ 24-25)። እነዚህ አምስት የትምህርት ክፍሎች «ክርስቶስ ይህን በፈጸመ ጊዜ» በሚሉ ቃላት ይጠቃለላሉ (ማቴ. 7፡28፤ 11፡1፤ 13፡53፣ 19፡1፤ 26፡)። የክርስቶስ ታሪኮች የተደራጁት የክርስቶስን ትምህርት ለማስተዋወቅ ነው።

የማቴዎስን ወንጌል አስተዋጽኦ ማዘጋጀት የሚቻልባቸው የተለያዩ መንገዶች ሲኖሩ፥ ከእነዚህ መካከል አንዱ ክርስቶስ ያገለገለባቸውን አገሮች መከተል ነው።

  1. የክርስቶስ መወለድና ለአገልግሎት መዘጋጀት (ማቴ. 1፡1-4፡16)
  2. የክርስቶስ አገልግሎት በገሊላ (ማቴ. 4፡17-14፡12)
  3. የክርስቶስ አገልግሎት ከገሊላ ውጭ (ማቴ. 14፡13-17፡20)
  4. የክርስቶስ የመጨረሻ አገልግሎት በገሊላ (ማቴ. 17፡21-18፡35)
  5. የክርስቶስ አገልግሎት በይሁዳና ጴሪያ (ማቴ. 19-20)
  6. ክርስቶስ ከመሰቀሉ በፊት የፈጸመው የመጨረሻው ሳምንት አገልግሎት (ማቴ. 21-27)
  7. የክርስቶስ ትንሣኤ (ማቴ. 28)

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ አይ ኤም ከታተመውና የዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው)

Exit mobile version