Site icon

ሉቃስ 9፡1-62

ዘሪሁን ሰዎች ከበሽታቸው እንደሚፈወሱ ስለ ሰማ፥ ወደ አንድ የወንጌል አማኝ ቤተ ክርስቲያን ሄደ። በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ገብቶ ሲቀመጥ፥ ሰባኪው በኢየሱስ ለማመን የሚፈልግ ሰው ከኃጢአቱ መዳን ብቻ ሳይሆን ከየትኛውም በሽታ እንደሚፈወስና ቁሳዊ በረከቶችን እንደሚያገኝ ሲናገር ሰማ። ዘሪሁን፣ “ይሄ ጥሩ ዜና ነው። አምናለሁ ብዬ እነግራቸውና ለቀሪ ዘመኔ ጥሩ ሕይወት የምኖርበትን ዕድል አገኛለሁ። ሀብታምም እሆናለሁ” ሲል አሰበ። ብዙም ሳይቆይ ዘሪሁን ታመመ። በዚህ ጊዜ፣ «አንተ በሽታ፣ በኢየሱስ ስም ከእኔ ራቅ» እያለ ያዝዝ ጀመር። ነገር ግን በሽታው ሊለቅቀው አልቻለም። በመጨረሻም ወደ ሐኪም ቤት ሲሄድ ሐኪሞቹ ሊረዱት እንደማይችሉ ገለጹለት። ያለችውን አነስተኛ ገንዘብ ለቃቅሞ መድኃኒት ለመግዛት ሞከረ። የኋላ ኋላ ልቡ በብስጭት በመሞላቱ፣ «ኢየሱስ ከበሽታዬ ሊፈውሰኝና ሀብታም ሊያደርገኝ ካልቻለ፣ ለምን አምነዋለሁ?» ሲል ጠየቀ። በዚህ ጊዜ እምነቱን ትቶ፥ ወደ ጠንቋዮች ሄደ።

የውይይት ጥያቄ፡- ሉቃስ 9፡23-26 አንብብ። ሀ) ኢየሱስ ስለ ደቀ መዝሙርነት መንገድ ያስተማረው ምንድን ነው? ለ) ይህ ከዘሪሁን አሳብ ጋር እንዴት ይነጻጸራል? ሐ) ኢየሱስና ሐዋርያቱ ክርስቲያኖች ስደትና መከራ እንደሚቀበሉ በተደጋጋሚ የሚያስጠነቅቁት ለምንድን ነው? የሐዋርያት ሥራ 14፡22፤ ሮሜ 5፡3፤ 8፡17-18፤ ፊልጵ. 3፡10 አንብብ። መ) አዳዲስ ክርስቲያኖችን ለመስቀሉ መንገድ ለማዘጋጀት የማስተማር ስልታችንን መቀየር ያለብን እንዴት ነው?

ስለ ክርስትና ሰዎች ከሚናገሩት ነገር ውስጥ አንዱ፥ ክርስትና የበረከት መንገድ ነው የሚለው የተሳሳተ አመለካከት ነው። ለእነዚህ ሰዎች ክርስትና እንደ ቁሳዊ ሀብት፣ ጤና፣ ከስደት ነፃ መሆን፣ የመሳሰሉት ማለት ነው። ለመሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው ይህንን ነው? በአንድ ጊዜ ቤተሰቡን፣ ሀብቱንና ጤንነቱን ምንም ባላወቀበት ምክንያት ላጣው ኢዮብ የበረከት መንገድ ነበር? እግዚአብሔር የተስፋ ቃሉን ይፈጽምለት ዘንድ ከ20 ዓመት በላይ ለጠበቀው አብርሃም፣ ብዙ ዓመት በስደት ለኖረው ዳዊት፣ ከመደህየታቸው የተነሣ በሌሎች እርዳታ ለመኖር ለተገደዱት ኤልያስና ኤልሳዕ፣ እንደ እስረኛ ለወራት በጉድጓድ ውስጥ ለኖረው ኤርምያስ፣ ለሁለት በመጋዝ ተሰንጥቆ ለተገደለው ኢሳይያስ፣ ለወንጌሉ ሲሉ ሕይወታቸውን ላጡት አሥሩ ደቀ መዛሙርት ክርስትና የበረከት መንገድ ነበርን? የጳውሎስን ሕይወት በረከት በ2ኛ ቆሮንቶስ 11፡23-29 ላይ አንብብ! ከድህነቱ የተነሣ የሚተኛበት አልጋ ላልነበረውና በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ሥቃይ ለተቀበለው ክርስቶስ የበረከት መንገድ ነበርን? እግዚአብሔር ሙሉ ጤና፥ በቀላሉ አልጋ ባልጋ የሆነ ሕይወት፣ ወይም ስደት የሌለበት ኑር እንደምንኖር ቃል አልገባልንም። ጤነኞችም ሆንን በሽተኞች፣ ድሆችም ሆንን ሀብታሞች ሊያበረታታን የሚገባው በመከራ መንገድ እርሱን መከተላችን ነው። በዘላለማዊ ቤት እነዚህ ምድራዊ ችግሮች ይወገዳሉ።

  1. ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ለአገልግሎት ላከ (ሉቃስ 9፡1-9)

ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ የወደፊት የቤተ ክርስቲያኑ መሪዎች ይሆኑ ዘንድ በማሠልጠን ለተወሰነ ጊዜ አብሯቸው ቆየ። ሥልጠና ለሰዎች መረጃ ከመስጠት ያለፈ ነው። አንድ ሰው የተማረውን ነገር ተግባራዊ ማድረግ መቻል አለበት። ኢየሱስ የጊዜውን አጭርነትና ብቻውን ወደ ሰዎች ሁሉ ለመድረስ አለመቻሉን ያውቅ ስለ ነበር፣ ደቀ መዛሙርቱ በእርሱ ምትክ እንዲሠሩ በማሠልጠንና በመላክ ተልዕኮውን አሰፋ። ለመሆኑ በየዘመኑ የሚነሱ ደቀ መዛሙርት ሁሉ ምን ዐይነት ሕይወት መኖር እንደሚገባቸው በምሳሌነት ከሚያሳዩት ከእነዚህ ደቀ መዛሙርት ሕይወት የምንቀስማቸው እውነቶች ምንድን ናቸው?

ሀ. የአገልግሎት ሥልጣን ምንጭ ኢየሱስ ነው። ደቀ መዛሙርቱን የሚያሰማራቸው እርሱ ነው። ወንጌላውያን አንዳንድ ጊዜ ይህንን እውነት ሊዘነጉ ይችላሉ። “የላከችኝ ቤተ ክርስቲያኔ ነች። ደመወዝ የሚከፍሉኝ እነርሱ ናቸው። ደመወዜ እስከተላከልኝ ጊዜ ድረስ እሠራለሁ” ሲሉ ይደመጣሉ። እንዲህ ዐይነቱ አመለካከት መቼም ቢሆን የእግዚአብሔርን በረከት አያስገኝም። በቤተ ክርስቲያንም ሆነ በሥራ ወደምናገለግልበት ስፍራ ያመጣን ኢየሱስ እንደሆነ ልብ ልንል ይገባል።

ለ. የአገልግሎት ኃይል የሚመጣው ከኢየሱስ ነው። ብዙውን ጊዜ የአገልግሎት ኃይል የሚመጣው ከራሳችን ተፈጥሯዊ ችሎታ ወይም ከትምህርት እንደሆነ ልናስብ እንችላለን። ነገር ግን ኃይል ከኢየሱስ በሚመጣበት ጊዜ መልካም ፍሬ እንደሚያፈራ ከሉቃስ ወንጌል እንገነዘባለን።

ሐ. ይህ ኃይል በሦስት የአገልግሎት መስኮች ይታያል። አንደኛው፥ በሰዎች ሕይወትና ባህል ውስጥ ያለውን የሰይጣንን ኃይል ያፈራርሳል። የኢየሱስ መንግሥት አካል እንደ መሆናችን፣ ኃይለኛ የተባለውን ሰይጣንን አስረን መንግሥቱን ልንበዘብዝ እንችላለን (ሉቃስ 11፡19-22)። ሁለተኛው፣ አገልግሎቱ ፈውስን ያካትታል። የእግዚአብሔርን ህልውና ከሚያረጋግጡልን ነገሮች አንዱ ከርኅርኄው የተነስ ሰዎችን መፈወሱ ነው። ሦስተኛው፣ የእግዚአብሔር መንግሥት ይሰበካል። ሰዎችን መፈወስና አጋንንትን ማውጣት ብቻውን በቂ አይደለም። ሰዎች ሕይወታቸው እንዲለወጥ ከፈለጉ የኢየሱስን መንግሥት መምረጥ አለባቸው።

ደቀ መዛሙርቱ በታላቅ ኃይል እያገለገሉ ቢሆኑም፣ ማንም ሰው ለእነርሱ ቦታ አለመስጠቱ አስገራሚ ነው። መሪው ኢየሱስ እንደሆነ ስለሚያውቁ፣ እርሱኑ ነበር ያከበሩት። መጥምቁ ዮሐንስን ያስገደለው አንቲጳስ ሄሮድስ እንኳ ዮሐንስ ከሞት የተነሣ መስሎት ኢየሱስን ለማየት ጓጉቷል። ኢየሱስ በተሰቀለባት ሌሊት ሄሮድስ የሚፈልገውን ሊሰጠው ፈልጎ ነበር። ኢየሱስ ግን ሊያነጋግረው አልፈለገም (ሉቃስ 23፡6-11)።

  1. ኢየሱስ አምስት ሺህ ሰዎችን መገበ ሉቃስ (9፡10-17)

ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ የተማሩትን ነገር በሌሎች የሕይወት ዘርፎችም ተግባራዊ ለማድረግ ይችሉ እንደሆነ ለመመልከት ፈለገ። ታላላቅ ተአምራትን እንዲያደርጉ ኃይልን ከሰጣቸው በኋላ አምስት ሺህ ሰዎችን እንዲመግቡ ጠየቃቸው። ኢየሱስ የማይቻለውን ነገር እንዲያደርጉ በሚያዛቸው ወቅት ተግባራዊ የሚያደርጉበትን ኃይል እንደሚሰጣቸው አሳያቸው።

  1. ጴጥሮስ ኢየሱስ መሢሕ መሆኑን መሰከረ (ሉቃስ 9፡18-27)

መልካም አስተማሪዎችና ሰባኪዎች ሰዎች የግል ውሳኔ ለማድረግና በተማሩት ላይ ተመሥርተው ሕይወታቸውን እንዲለውጡ የሚጠየቁበት ጊዜ እንዳለ ያውቃሉ። ለሦስት ዓመት ያህል ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ሲያስተምርና ተአምራትን ሲሠራ ነበር የቆየው። ነገር ግን ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ በሕይወታቸው ላይ ያሳደረውን ተጽዕኖ ልብ ሳይሉ በሚሆነው ሁሉ እየተደሰቱ ይኖሩ ነበር። ስለሆነም ኢየሱስ ወደ አባቱ ከጸለየ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ስለ እርሱ ውሳኔ የሚያደርጉበት ጊዜ እንደ ደረሰ ተነዘበ።

የቡድኑ አፈ ጉባዔ የሆነው ጰጥሮስ፥ ኢየሱስ ከእግዚአብሔር የተላከ መሢሕ እንደሆነ የሚያምኑ መሆናቸውን ተናገረ። ወዲያውም ኢየሱስ ይህንን ለማንም እንዳይናገሩ አዘዛቸው። ለምን? ምናልባትም ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ ምን ዐይነት መሢሕ እንደሆነ አያውቁም ነበር፡ አሁንም ድል-ነሺው ንጉሥ መሢሑ እንደሆነ ያስቡ ነበር። ኢየሱስ ግን እርሱ መከራ ለመቀበል የመጣ መሢሕ እንደሆነ አስተማራቸው፡፡ ይህ ለመገንዘብ የሚከብዳቸው አሳብ ነበር።

ሉቃስ ኢየሱስ ጴጥሮስን እንደ ገሠጸው አለመግለጹ ግር ይላል። ሉቃስ ያተኮረው በደቀ መዝሙርነት መንገድ ላይ ነው። የሰው ልጅ የሆነው ኢየሱስ የሚሸከመው መስቀል፣ ማለትም የመከራ፣ ተቀባይነት የማጣት፣ የሞትና የትንሣኤ መንገድ እንደነበረው ሁሉ፣ ኢየሱስን የሚከተሉ ሰዎችም ተመሳሳይ ዕጣ ፈንታ ይጠብቃቸዋል። እኛም የምንሸከመው መስቀል አለን። ይህ መስቀል ቁሳዊ ባይሆንም፣ የመከራ መንገድ ግን ሊሆን ይችላል። ይህም ሕይወታችንን ሊቆጣጠር የሚፈልገውን ምኞት፥ ምድራዊ ተድላን፥ ከሰዎች ዘንድ ክብርን መግደልን ይጨምራል። ሞትን የሚያስከትል ቢሆንም እንኳ፥ ኢየሱስን ለመከተል መወሰን መስቀል ነው። የዓለም ሰዎች እንደ ሞኝነት ቢቆጥሩትም፣ የዘላለምን ሕይወት ለመቀበል የምንፈልገውን በመተውና (ለራስ በመሞት) እግዚአብሔር የሚፈልገውን በመምረጥ ነው። በሐፍረት ወይም ስደትን በመፍራት እምነትን መደበቅ ምን ያህል ቀላል እንደሆነ ኢየሱስ ያውቃል። ስለሆነም ደቀ መዛሙርቱ ሰዎች የኢየሱስ ተከታዮች መሆናቸውን እንዳያውቁ በማሰብ በእርሱ ካፈሩ፣ ይህ በትክክል የእርሱ ተከታዮች አለመሆናቸውን እንደሚያሳይ ገልጾአል። ስለሆነም ኢየሱስ እነዚህን ሰዎች በፍርድ ቀን እንደ ራሱ ተከታዮች አይቀበላቸውም።

ሉቃስ ይህ የዕለት ተዕለት ውሳኔ እንደሆነ መግለጹ የሚደንቅ ነው። አንድ ጊዜ ብቻ ኢየሱስን ለመከተል መወሰኑ በቂ አይደለም። በየቀኑ ከመኝታችን ስንነሣ ሥጋዊ ምኞታችንን ለመግደልና ለእግዚአብሔር ለመግዛት መወሰን አለብን። ይህም የመስቀሉ መንገድ ነው። ኃጢአት በመሠረቱ የራስ ወዳድነት ፈቃዳችን ሕይወታችንን እንዲቆጣጠር የማድረግ ፍላጎት ነው። የመስቀሉ መንገድ የራስ ወዳድነት ፈቃድ በመካድ ኢየሱስ የሕይወታችን ጌታ እንዲሆን መፍቀድ ነው። ሕይወታችን በኢየሱስ አመራር ሥር እየዋለ ሲሄድ በመንፈሳዊ ብስለት እናድጋለን።

የውይይት ጥያቄ:- ሀ) ክርስቲያኖች ብዙ ጊዜ የሚፈጽሟቸውን አሥር ኃጢአቶች ዝርዝር። ለ) እነዚህ ከራስ ወዳድነት የሚመነጩት ኀጢአቶች፥ ሕይወታችንን የሚቆጣጠሩት እንዴት ነው? ሐ) ኢየሱስ የሕይወታችን ጌታ በሚሆንበት ጊዜ እንዲህ ዐይነቱ ሁኔታ የሚለወጠው እንዴት ነው?

  1. ኢየሱስ ክብሩን ለሦስት ደቀ መዛሙርቱ ገለጸ ሉቃለ 9:28–36)

ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ መሢሕ እንደሆነ ከመሰከሩ ከስምንት ቀን በኋላ፣ ኢየሱስ ክብሩን ለጴጥርስ፣ ለያዕቆብና ለዮሐንስ ገልጧል። ይህ ክስተት የተፈጸመው ኢየሱስ በሚጸልይበት ጊዜ መሆኑን ሉቃስ በግልጽ ጠቅሷል። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ስለ ማንነቱ ጥልቅ ግንዛቤ እንዲኖራቸው የጠየቀውም በሚጸልይበት ጊዜ ነበር (ሉቃስ 9፡18)። አሁንም ኢየሱስ በሚጸልይበት ጊዜ እግዚአብሔር በሰባዊነቱ ፈንታ አምላካዊ ክብሩ እንዲያበራ አደረገ። የኢየሱስ መለኮታዊ ባሕርይ በሚያበራበት ጊዜ ሙሴ፣ ኤልያስና ራሱ ኢየሱስ ስለ ሞቱ መነጋገራቸው የእግዚአብሔርን አስደናቂ የምሥጢር መንገዶች የሚያሳይ ነው። በእግዚአብሔር ዕቅድ መሠረት ብሉይ ኪዳን ኢየሱስ የዓለምን ኃጢአት ለማስወገድ ስለሚሞትበት ቀን ይናገር ነበር። ለኢየሱስ ታላቅ መሸነፍ የሚመስለው ነገር ክብሩ የተገለጸበት ድል ነበር። ጳውሎስ እንደ ተናገረው፣ ከመስቀሉ የተነሣ አንድ ቀን ጉልበት ሁሉ ኢየሱስን ለማክበር ይንበረከካል (ፊልጵ. 2፡5-11 አንብብ።) በተመሳሳይ መንገድ ታላቅ ክብር የምናገኘው ተወዳጅነትን ስናተርፍና ስብከት ስንሰብክ አይደለም። የምንከብረው ለኢየሱስ መከራን ስንቀበልና ይህንንም እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ ስንፈጽመው ነው። መከራ እግዚአብሔር ክብሩን ለእኛ የሚገልጥበት መንገድ ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ሰዎች በከፍተኛ መከራ ውስጥ እያለፉ የእግዚአብሔር ክብር በሕይወታቸው ሲገለጥ ያየኸው እንዴት ነው? ለ) እግዚአብሔር ሥጋዊ በረከት በበዛበት ወቅት ሳይሆን፥ በመከራ ጊዜ ታላቅ ክብሩን የሚገልጸው ለምን ይመስልሃል?

  1. ደቀ መዛሙርቱ አጋንንትን ማስወጣት ተሳናቸው (ሉቃ. 9፡37-45)

ሦስቱ ደቀ መዛሙርት የኢየሱስን ክብር አይተው ሲመለሱ፥ የተቀሩት ደቀ መዛሙርቱ በችግር ውስጥ ነበሩ። ምንም እንኳ ቀደም ሲል በተሳካ ሁኔታ ከሰዎች አጋንንት ያስወጡ ቢሆንም፣ አሁን ግን በአንድ ልጅ ውስጥ የሰፈረውን ጋኔን ለማስወጣት አልቻሉም። ችግሩ ምንድን ነው? አጋንንቱ ሊወጣላቸው ያልቻለው ለምንድን ነው? ሉቃስ ለዚህ የሰጠው መልስ ባይኖርም፥ የእምነት ማነስ እንዳለባቸው ጠቁሟል። ማቴዎስ ደቀ መዛሙርቱ እምነት እንደ ጎደላቸው ሲያመለክት (ማቴ. 17፡19-20)፣ ማርቆስ ደግሞ ተግተው እንዳልጸለዩ ገልጾአል (ማር. 9፡28-29)። ምናልባትም ሉቃስ ለማሳየት የፈለገው ብዙ ክርስቲያኖች ከኢየሱስ ጋር በተራራ ላይ ለመቆየት እንደሚፈልጉ፥ ነገር ግን ብርቱ ትግል ባለበት ሜዳ ላይ እምነት ያላቸውና የሌላቸው ተለይተው እንደሚታወቁ ነው። ሉቃስ ኢየሱስ አክብሮትና አድናቆት ባገኘበት ወቅት ለደቀ መዛሙርቱ ስለ መጭው ሞቱ ለማስተማር እንደ ፈለገ አመልክቷል።

  1. ኢየሱስ መሪዎች ሊኖራቸው ስለሚገባ አመለካከት አስተማረ (ሉቃስ 9:46-56)

የውይይት ጥያቄ:- የመሪዎች ትዕቢት የቤተ ክርስቲያንንና የእግዚአብሔርን መንግሥት መስፋፋት በአሉታዊ መልኩ ሲጎዳ የተመለከትነው እንዴት ነው? ለ) የኢየሱስ ተከታዮች መሪነትን ከዓለማውያን በተለየ መንገድ ለመረዳት የሚቸገሩት ለምንድን ነው?

የምንኖረው የቤተ ክርስቲያን መከፋፈል በተስፋፋበት ዘመን ነው። በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት፣ በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያንና በቤተ እምነቶች፣ እንዲሁም በተለያዩ ክርስቲያናዊ ቡድኖች መካከል መከፋፈል ይከሰታል። ይህ መከፋፈል የሚመጣው ከየት ነው? አብዛኛውን ጊዜ እነዚህ ክፍፍሎች የመሪዎች አለመግባባት ውጤቶች ናቸው። ብዙውን ጊዜ የጠብ ምንጭ ሆኖ የሚገኘው ትዕቢት ነው። ይህ በኢየሱስ ደቀ መዛሙርትም ሕይወት ተከስቷል። በዚህ ክፍል የኢየሱስ ተከታዮች ተግባራዊ ሊይደርጓቸው የሚገቧቸውን ሦስት የአመራር መንገዶች ሉቃስ ዘርዝሯል።

ሀ. አመራር እንደ ሕጻናት ያሉትን ያከብራል (ሉቃስ 9፡46-48)። ይህ እውነት ሁለት ነገሮችን ሊያስተምር ይችላል። አንደኛው፥ ዓለም ታላላቅ ለሚባሉ ሰዎች ከምትሰጠው ስፍራ በተቃራኒ፣ በቤተ ክርስቲያን እንደ ሕጻናት ብዙም ስፍራ የማይሰጣቸውን ሰዎች እናከብራለን። ሁለተኛው፣ የግል ክብርን ከመፈለግና ከዝና ጥማት ነፃ ሆነን ማገልገል አለብን። ራሳችንን በትሕትና ዝቅ አድርገን መመልከት አለብን። በዚህ ጊዜ በእግዚአብሔር ዐይን ፊት እንከብራለን። እግዚአብሔር ለትሕትና እንጂ ለትዕቢት ስፍራ የለውም። ታላቅነት የሚለካው በትሑት አገልግሎት እንጂ በትልቅ ሥልጣን አይደለም።

ለ. መሪዎች የኢየሱስን ክብር መሻት እንጂ በራስ ወዳድነት የቡድናቸውን ክብር መጠበቅ የለባቸውም (ሉቃስ 9፡49-50)። ደቀ መዛሙርቱ ከ12ቱ ውስጥ ያልሆነ ሌላ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር በኢየሱስ ሥልጣን አጋንንት በማውጣቱ ተቆጥተው ነበር። ያ ሰው ከ12ቱ መካከል ባለመሆኑ፣ ኢየሱስ አገልግሎቱን እንዲያስቆም ጠየቁት። ኢየሱስ ግን ለእርሱ ክብር ማምጣቱ እንጂ የሰውዬው ማንነት አሳሳቢ እንዳልሆነ ገለጸላቸው። አንድ ሰው ክብሩን ማን እንደሚቀበል በማይታወቅበት ጊዜ በጣም ብዙ ሥራ እንደሚሠራ ገልጾአል። የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የእኛ ሊሆን ይገባል የሚሉትን ክብር ወጣቶች፣ ሴቶች ወይም ሌላ ቤተ ክርስቲያን በሥራቸው ሲቀዳጁ ተመልክተው በቀላሉ ሊቀኑ ይችላሉ። ብዙውን ጊዜ ሰዎች እግዚአብሔር በሚጠቀምበት ሰው ይቀናሉ። ደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ዐይነት ተግባር በመፈጸማቸው እግዚአብሔር የፈለገውን ሰው ሊጠቀም እንደሚችል፣ እርሱን የሚያሳስበው ሽማግሌዎች ወይም ቤተ ክርስቲያናችን ክብር ማግኘታቸው ሳይሆን የኢየሱስ ከፍ ከፍ ማለት እንደሆነ ሳይገነዘቡ ቀርተዋል።

ሐ. መሪዎች የማያከብሯቸውን ሰዎች አይበቀሉም (ሉቃስ 9፡51-56)። በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ፤ የሚያምኑትም ሆኑ የማያምኑ ሰዎች እኛንና የምንሰጣቸውን ቃል እንዲቀበሉ ማስገደድ የለብንም። ከማይቀበሉን ሰዎች ጋር መጣላትም የለብንም። ነገር ግን ተቃውሞ በሚያጋጥመን ጊዜ ነገሩን ለእግዚአብሔር አሳልፈን ልንሰጥና ልንተወው ይገባል። ኢየሱስ እግዚአብሔር በሳምራውያን ላይ ፍርዱን እንዲያወርድ በመጠየቅ ፈንታ፥ ወደ ሌላ ስፍራ የሄደው በዚህ ግንዛቤ ነበር።

የውይይት ጥያቄ:- መሪዎች ለሚሳሳቱባቸው ለእያንዳንዳቸው ሦስት መንገዶች ሁለት ሁለት ማብራሪያዎችን ስጥ። ለ) ኢየሱስ ተከታዮቹን ለመውሰድ የሚፈልግበት ተቃራኒ መንገድ የትኛው ነው?

በሉቃስ በ9፡51 ላይ የሉቃስ ወንጌል የትኩረት አቅጣጫውን ይቀይራል። እስካሁን ድረስ የኢየሱስ አገልግሎት ያተኮረው በገሊላና በአካባቢዋ ነበር። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ በሞቱ ላይ አሳቡን መጣል ጀመረ። መስቀሉ ሁልጊዜ ከፊቱ ስለ ነበር ለደቀ መዛሙርቱም ይህንኑ ነገራቸው። አገልግሎቱም እንዲሁ መለወጥ ጀመረ። ተአምራት የሚሠራበትንና ሕዝብ የሚያስተምርበትን ጊዜ እየቀነሰ ደቀ መዛሙርቱን በማስተማሩ ላይ አተኮረ። የአገልግሎት ስፍራውም ተቀየረ። ሉቃስ፣ ኢየሱስ ወደ ሰማይ የሚወሰድበት ጊዜ እንደ ተቃረበ ገልጾአል (ይህም ሞቱን፥ ትንሣኤውንና ዕርገቱን ያመለክታል)። ስለሆነም ኢየሱስ ፊቱን ወደ ኢየሩሳሌም አቀና። ከገሊላ ተነሥቶ ወደ ደቡብ መጓዝ ጀመረ። በመጀመሪያ፣ በይሁዳና ከይሁዳ በስተ ምሥራቅ በምትገኘው በጲሪያ ካገለገለ በኋላ፣ ለመሞት ወደ ይሁዳና ወደ ኢየሩሳሌም ይመለሳል። ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም መጓዝ የጀመረው በሉቃስ 9፡51 ቢሆንም፣ እስከ ሉቃስ 19፡28 ድረስ ኢየሩሳሌም አይደርስም። ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም በመሄድ ላይ መሆኑ በሌሎችም አራት ስፍራዎች ተመልክቷል (ሉቃስ 13፡22፣ 17፡11፣ 18፡31፡ 19፡11)። ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣበትን ምክንያት ያውቅ ስለ ነበር፣ አገልግሎቱ ምንም ያህል ሥቃይ የበዛበት ቢሆንም፥ እግዚአብሔርን ለመታዘዝ ቆርጦ ነበር።

  1. ኢየሱስ ከምንም በላይ ቅድሚያ እንዲሰጠው ጠየቀ (ሉቃስ 9፡57-62)

ኢየሱስን መከተል ቀላል ነውን? ኢየሱስን መከተል ማለት አንድ ሰው እሑድ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሄዶ እጁን በማንሣት በኢየሱስ ለማመን እንደሚፈልግ መናገር ማለት ነው? ወይስ ኢየሱስን መከተል ማለት ከሌሎች ፍቅራችንን ከሚጋሩት ነገሮች ሁሉ እርሱን ማስቀደም ማለት ነው? ሉቃስ ኢየሱስን መከተል ከበድ ያለ ውሳኔ መሆኑን በአጽንኦት ገልጾአል። ኢየሱስን መከተል ማለት እርሱን ከግል ምቾትና ደስታ በላይ መምረጥ ነው። ኢየሱስን ከቤተሰብ ግዴታዎች ወይም ፍላጎቶች ማስቀደም አለብን። ይህ የዓለም ትብታቦች እንዳይይዙን በመከላከል ከኢየሱስ ጋር ለመጓዝ የሚደረግ ዘለቄታዊ ውሳኔ ነው።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Exit mobile version