Site icon

ሰዎች የክርስቶስን መልእክት ሳይሰሙ ሊድኑ ይችላሉ? 

እንግዲህ ዛሬ ስለ ደኅንነት ከሚነሡ ከባድ ከሆኑ ጥያቄዎች አንዱን ለመመለስ እንሞክራለን። ስለ ክርስቶስ ስፍጹም ሰምተው የማያውቁ አንዳንድ ሰዎች በእግዚአብሔር በማመናቸው ይድናሉ? 

ከአንድ መቶ ዓመት በፊት አካባቢ፥ በደቡብ ኢትዮጵያ ኢሳ የተባለ ነቢይ ተነሥቶ ነበር። ይህ ነቢይ በሕይወቱ ዘመን በአብዛኛው በኢትዮጵያ ደቡባዊው ክፍል እየተዘዋወረ፥ ሰዎች ለርኩስ መናፍስት መስገዳቸውን ትተው አንዱን በሰማይ የሚኖር እውነተኛ አምላክ እንዲያመልኩ ያስተምራቸውና ያሳስባቸው ነበር። እስከምናውቀው ድረስ፣ ኢሳ የክርስቲያኖችን ወንጌል ጨርሶ አልሰማም ነበር። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰውም አምላክም ሆኖ ወደዚህ ዓለም በመምጣት የንጽሕና ሕይወትን በመኖር የመሥዋዕትነትን ሞት እንደ ሞተ በፍጹም አልሰማም። እንዲሁም ከኃጢአቱ ለመዳን ሲል በክርስቶስ የማመን ዕድልም አላገኘም። ሆኖም ግን ኢሳ የሰማይ አምላክ የሆነውን አንዱን እግዚአብሔርን የማምለክ ዝንባሌ ይታይበት ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ኢሳን ስለ መሰሉ ሰዎች የሚናገረው ነገር አለው? እግዚአብሔር እንደ ኢሳ ያለ፥ በእርሱ የሚያምን፥ ግን የክርስቶስን መልእክት ለመስማት ዕድል ያላገኘን ሰው ያድን ይሆን? እግዚአብሔር በክርስቶስ ሞት የተገኘው ትሩፋት፥ እንደ ኢሳ ያሉ ስለ ክርስቶስ ጨርሰው ያልሰሙ ወይም በእርሱ ያላመኑ ሰዎች እንዲድኑበት ያደርግ ይሆን? 

1. የአዲስ ኪዳን አጠቃላይ ዓላማ ሰዎች የክርስቶስን መልእክት ሰምተው፥ ደኅንነቱን ስለ መቀበላቸው በእምነታቸው አማካይነት እንዲያስታውቁ ነው። 

ጥያቄ፡- ዮሐ 14፡6 አንብብ። ወደ አብ የሚያደርሰው ብቸኛው መንገድ ማን ነው? 

ጥያቄ፡- የሐዋ. ሥራ 4፡12 አንብብ። ሰዎች በማን ስም ብቻ ይድናሉ? 

ጥያቄ፡- ሮሜ 1፡18-23 አንብብ። ሀ) ሰዎች ሁሉ ለለ እግዚአብሔር ምን ያውቃሉ? (ቁጥር 20) ለ) ሰዎች ስለ እግዚአብሔር ባላቸው በዚህ እውቀት ምን ያደርጋሉ? (ቁጥር 18፣ 21-23) 

ጥያቄ፡- ሮሜ 10፡13-14 እንብብ። ሀ) የሚድነው ማን ነው? (ቁጥር 13) ለ) ሰዎች የጌታን ስም መጥራት እንዲችሉ ምን ያስፈልጋቸዋል? (ቁጥር 14) 

አዲስ ኪዳን በግልጽ እንደሚናገረው፥ የደኅንነት አጠቃላይ ዓላማ፥ የክርስቶስን መልእክት ማድመጥና የሰሙትንም በእምነት መግለጥ ነው። በዮሐንስ 14፡6 ውስጥ ኢየሱስ ራሱ፥ ማንም ቢሆን በእርሱ በኩል ካልሆነ ወደ አብ ሊመጣ እንደማይችል ተናግሮአል። ብዙ ምንባቦችን ከጻፈ በኋላ ሰዎች መዳን ከፈለጉ እምነታቸውን በኢየሱስ ላይ ማድረግ እንዳለባቸው ዮሐንስ ጽፎአል (ምሳሌዎቹ፡- ዮሐንስ 1፡12፤ 3፡15፤ 16፣ 36)። በግልጽ እንደሚታየው፥ ኢየሱስ የተናገረው፥ ወደ አብ ለመድረስ የሚቻለው በእርሱ በማመን ብቻ መሆኑን ነው። ቀደም ባሉት የሐዋርያት ሥራ ምዕራፎች እንደተጻፈው፥ ሐዋርያት በኢየሱስ አማካይነት ስለሚገኘው ደኅንነት ስለ ሰበኩ፥ የአይሁድ መሪዎች ተቆጥተው ነበር። ልክ እንደ ሐዋርያት፥ እነዚህ የአይሁድ መሪዎችም በእስራኤል አንድ አምላከ ያምኑ ነበር። እንዲሁም መዳን የሚገኘው በእርሱ መሆኑን ያወቁ ነበር። ነገር ግን በሐዋርያት ሥራ 4፡10-12 ውስጥ፥ ጴጥሮስ አንዱንና የደኅንነት መንገድ እርሱ ብቻ የሆነውን ክርስቶስን አለመቀበላቸውን ነገራቸው። ስለሆነም እነዚህ የሃይማኖት መሪዎች ደኅንነትን ለማግኘት በሰማይ የሚኖር አንዱን እውነተኛ አምላክ ማመናቸው ብቻ አይበቃም ነበር። ደኅንነትን ለማግኘት እንዲችሉ በኢየሱስ ማመን ነበረባቸው። 

ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱም እንደሚያስተምረው፥ በሰማይ ስለሚኖረው አምላክ ማወቅ ብቻ አይበቃም ይላል። ቀጥተኛው የደኅንነት መንገድ ስለ ክርስቶስ የሚታወጀውን ቃል መስማትና የሰሙትን በእምነት መግለጥ ነው። በሮሜ ምዕራፍ 1 ውስጥ ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚለው፥ ሰዎች ሁሉ ስለ ሰማዩ አምላክ የተወሰነ እውቀት አላቸው። ነገር ግን ይህ እውቀት ሊያድናቸው የሚበቃ አይደለም። በሰማይ ስለሚኖረው አምላክ የሚያውቁት «ዘላለማዊ ኃይሉንና አምላክነቱን» ነው (ሮሜ 1፡20) ይላል። ታዲያ ሰዎች በዚህ እውቀት እንዴት ይጠቀሙበታል? «እውነቱን ሸፈኑበት» እግዚአብሔርን በማክበር ፈንታ፥ ፍጥረታትን አመለኩ (ሮሜ 1፡18፥21-23)። በፍጥረታት አማካይነት ስለ እግዚአብሔር ማወቅ ደኅንነትን ለማስገኘት በቂ አይደለም። ብዙ ጊዜ ሰዎች ይህን እግዚአብሔርን የማወቅ ሁኔታ ትተው ፊታቸውን ያዞሩና እግዚአብሔር የፈጠራቸውን ነገሮች ያመልካሉ (ሮሜ 1፡25)፡፡ ጳውሎስ በሮሜ 10፡13-14 እንደሚናገረው፥ ሰዎች መዳን ከፈለጉ የጌታን ስም መጥራት አለባቸው፡፡ ጳውሎስ፥ «የጌታ ስም» በሚልበት ጊዜ፥ በትክክል ስለ ጌታ ኢየሱስ ማሰቡ ነው። (በሮሜ 10፡9 ውስጥ የተጻፈውን ዐውደ ንባብ ተመልከት።) ሰዎች፥ የጌታን ስም ለመጥራት ስለ ክርስቶስ የተነገረውን መልእክት ሰምተው በእምነት ሊገልጡት ይገባል (ሮሜ 10፡14)። የደኅንነት ዓላማ ሰዎች ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወትና ሞት የተነገረውን ሰምተው ለደኅንነታቸው በእርሱ ማመን ነው። 

2. ሰዎች ሁሉ ስለ ክርስቶስ ሳይሰሙ እንዲድኑ እግዚአብሔር በቂ ፍንጭ ሰጥቶአል? 

ቢያንስ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ሁለት ጥቅሶች ስለ ክርስቶስ ጨርሶ ያልሰሙና በእርሱ አምነው ደኅንነትን ስላላገኙ ሰዎች እግዚአብሔር የሚለው ፍንጭ እንዳለ ይጠቁማሉ። እነዚህ ጥቅሶች ለእኛ ምን ይሉናል? 

ጥያቄ፡- ዮሐ 1፡9 አንብብ። ሀ) ጌታ ኢየሱስ ወደ ዓለም በመጣ ጊዜ ለእነማን ብርሃንን ሰጠ? ለ) ዮሐንስ 1:5፥10 አንብብ። ኢየሱስ ግን እንደ ነበረ ሁሉም አውቀው ነበር? ሐ) ዮሐ 1:12 አንብብ። እነማን በእውነት የእግዚአብሔር ልጆች ሆኑ? 

ጥያቄ፡- የሐዋ. ሥራ 14፡16-17 አንብብ። ባለፉት ዘመናት እግዚአብሔር ለሕዝቦች ሁሉ ምን አደረገላቸው? 

ዮሐንስ 1፡9 እንደሚናገረው ኢየሱስ ወደ ዓለም በመጣ ጊዜ ለእያንዳንዱ ሰው የሚያበራ ብርሃን ነበር ይላል። ነገር ግን ይህን ክፍል ሲመለከቱት መሠረተ አሳቡ ግልጽ እንደሚያደርገው የኢየሱስ መምጣት ሰዎች ሁሉ ለመዳን እግዚአብሔርን በበቂ ሁኔታ እንዲያውቁ አላደረጋቸውም የሚል ነው። ኢየሱስ የሚያበራው ብርሃን፥ በሰዎች ልቦና ላይ የሚበራ ብርሃን ነው። በልባቸው ውስጥ ያለውን ጨለማ ወደ ብርሃን አውጥቶ ያሳያል ( ዮሐንስ 1፡5)። እርሱ ራሱ እግዚአብሔር ለሰዎች የገለጠው ዋናው መገለጫ ነው። ይህን ብርሃን ያዩ ብዙዎች ግን እንደ ፈጣሪያቸው አድርገው አላወቁትም፥ ደግሞም እግዚአብሔርን የሚገልጥ ብርሃን አድርገው አልተቀበሉትም (ዮሐንስ 15፥10)። ነገር ግን ስለ እርሱ የሰሙት፥ ሰምተውም በእምነት የተቀበሉት የእግዚአብሔር ልጆች ስመሆን ደኅንነትን አገኙ ዮሐንስ 1፡12)። ዮሐንስ 1፡9 እግዚአብሔር፥ ሰዎች ሁሉ ስለ ክርስቶስ ዉርሶ ባይሰሙም፥ ይድኑ ዘንድ በቂ ብርሃን ይሰጣል ብሎ አያስተምርም። ምክንያቱም የጥቅሉ መሠረተ አሳብ፥ ሰዎች የእግዚአብሔር ልጆች ለመሆን ሲፈልጉ፥ አስቀድመው ሊቀበሉት እንደሚገባ በግልጽ ያስተምራል (ዮሐ 1፡12)። 

በሐዋርያት ሥራ 14፡16-17 ውስጥ እንደተጻፈው፥ እግዚአብሔር ሕዝቦች ሁሉ በገዛ ራሳቸው መንገድ እንዲሄዱ ትቶአቸው ነበር። ይሁን እንጂ እርሱ እንዴት ያለ ቸር አምላክ መሆኑን የሚመሰክር መልካም ሥራ ማድረጉን አልተወም ነበር። ልብ በሉ እነዚህ ጥቅሶች እግዚአብሔር ለሕዝቡ ደኅንነትን ሰጠ አይሉም። በዚህ ፈንታ እነዚህ ጥቅሶች በርሜ ምዕራፍ 1 ውስጥ ካለው ጋር አንድ ዓይነት አሳብ ይናገራሉ። እርሱም እግዚአብሔር ሰዎች ስለ እርሱ የሚያውቁትን እንዳላወቁ ሆነው የራሳቸውን መንገድ ተከትለው ወደ ኃጢአት እንዲሄዱ አድርጎ ነበር። አሁን ግን በክርስቶስ ወደ ደኅንነት ይጠራቸዋል። ምንም እንኳን በመረጡት መንገድ እንዲሄዱ እርሱ ቢተዋቸውም፥ በተፈጥሮ አማካይነት ስለ ቸርነቱ በአጠቃላይ ሁኔታ መግለጡን ቀጠለ። የሐዋርያት ሥራ 14፡16-7 ያለው ክፍል፥ እግዚአብሔር ስለ ክርስቶስ ጨርሰው ያልሰሙ ሰዎችን ያድናል ብሎ አያስተምርም። 

አንዳንድ ጊዜ ቆርኔሌዎስ ስለ ክርስቶስ ከመስማቱ በፊት በእግዚአብሔር አምኖ የዳነ ሰው ምሳሌ ሆኖ የሚቀርብበት ጊዜ አለ። እግዚአብሔር ቆርኔሌዎስን ስለ ክርስቶስ ከመስማቱ በፊት ነበር ያዳነው? የሐዋርያት ሥራ 10፡2 ቆርኔሌዎስና ቤተሰቡ ሃይማኖተኛችና እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች ነበሩ ይላል። ከኢየሱስ የተነገራቸውን መልእክት ከመስማታቸውም በፊት ቢሆን፥ አንዱን እውነተኛ የእስራኤል አምላክን ያመልኩና እርሱንም ለመታዘዝ ይጥሩ ነበር። ቢሆንም፣ ቆርኔሌዎስና ቤተሰቡ የእስራኤል አምላክ አንዱና እውነተኛው አምላክ መሆኑን ተረድተው ሊያመልኩት ይጥሩ የነበሩ አሕዛብ ነበሩ። ነገር ግን የሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 10 ቆርኔሌዎስ ለለ ኢየሱስ ከመስማቱ በፊት ጻነ አይልም። ታዲያ እግዚአብሔር እንዲህ ለሚያከብረውና እንዲያድነውም ለሚፈልገው ለቆርኔሌዎስ ምን እደረገለት? ሐዋርያው ጴጥሮስ ሄዶ ስለ ክርስቶስ እንዲሰብክለት ላከው። ቆርኔሌዎስ፥ «በኢየሱስ የሚያምን ሁሉ በስሙ የኃጢአት ይቅርታ ያገኛል» (የሐዋ. ሥራ 10፡43) የሚለውን የጴጥሮስ መልእክት እንደ ሰማ፥ እርሱና ቤተሰቡ በኢየሱስ አመኑ፥ መንፈስ ቅዱስንም ተቀበሉ። ስለ ኢየሱስ የተናገራቸውን መልእክት ከሰሙ በኋላ ነበር ሙሉ የአዲስ ኪዳን አማኞች በመሆን ሙሉውን የአዲስ ኪዳን ደኅንነትን ያገኙት። ስለዚህ የቆርኔሌዎስ ታሪክ እንደሚያመለክተው፥ በአንድ እውነተኛ አምላክ ለማምለክ የሚፈልጉ ሰዎች ካሉ፥ እግዚአብሔር ስለ ክርስቶስ የሚናገር መልእክት የሚያቀርብላቸው ሰው እንደሚልክላቸው ነው። እግዚአብሔር የእርሱን ደኅንነት ለማግኘት በእርሱ ለማመን የሚፈልጉትን አይኮንናቸውም። 

3. ክርስቶስ ለኃጢአት ሲል ለመሞት ከመምጣቱ በፊት ሰዎች ቀድሞ በብሉይ ኪዳን ጊዜ ይድኑ እንደ ነበሩት፥ ዛሬም ሊድኑ ይችላሉ? 

አንዳንድ ጊዜ በብሉይ ኪዳን ዘመን ሰዎች ይድኑ በነበረበት መንገድ ዛሬም ሊድኑ ይችላሉ ይባላል። በብሉይ ኪዳን ዘመን የነበሩ ሰዎች ክርስቶስ መጥቶ ለኃጢአት ሲል ከመሞቱ በፊት ነበር የዳኑት። ደኅንነታቸው የክርስቶስን መልእክት በመስማትና በእርሱ በማመን አልነበረም። ዛሬ ሰዎች ይህንኑ በመሰለ መንገድ ሊድኑ ይችላሉ? 

ልንመልሰው የሚገባን የመጀመሪያው ጥያቄ፡- በብሉይ ኪዳን ጊዜ የነበሩ ሰዎች እንዴት ሊድኑ ቻሉ? የሚል ነው። 

ጥያቄ፡- ዕብ 9፡13-15 አንብብ። ሀ) የብሉይ ኪዳን መሥዋዕት በሚያቀርቡት ሰዎች ላይ ምን ውጤት ነበረው? (ዕብ 9፡13)። ለ) የክርስቶስ የመሥዋዕትነት ሞት በብሉይ ኪዳን አማኞች ላይ ምን ውጤት ነበረው? (ዕብ. 9፡15)። 

ጥያቄ፡- ዕብ. 10፡1፥4፥11 አንብብ። በብሉይ ኪዳን ጊዜ ይቀርቡ የነበሩ መሥዋዕቶች ያቀርቡ የነበሩ ሰዎችን ኃጢአት ያስወግዱላቸው ነበር? 

ጥያቄ፡– ሮሜ 3፡25-26 አንብብ። የብሉይ ኪዳን አማኞች ኃጢአት ምን ጊዜ ቅጣቱን ይቀበል ነበር? 

ጥያቄ፡– ሮሜ 3፡9-12፥20 አንብብ። ሀ) የብሉይ ኪዳንን ሕግ አሟልቶ ይፈጽም የነበረ ሰው ነበር? (ሮሜ 3፡9-12) ለ) ለብሉይ ኪዳን ሕግ በመታዘዙ አንድ ሰው ይጸድቅ ነበር? (ሮሜ 3፡20) 

ጥያቄ፡- ሮሜ 4፡3 አንብብ። የአብርሃም ጻድቅነት እንዴት ተረጋገጠለት? 

ጥያቄ፡- ኦሪት ዘዳግም 10፡16ና ኤርምያስ 4፡4 አንብብ። ሀ) እግዚአብሔር ሕዝቦቹ እንዴት እንዲገረዙ ይነግራቸው ነበር? ለ) እንዲህ ማለት ምን ማለት ይመስላችኋል? 

ጥያቄ፡- ሮሜ 2፡28-29 አንብብ። በእግዚአብሔር ዓይን እውነተኞቹ አይሁዶች እነማን ናቸው? 

በብሉይ ኪዳን ጊዜ ሰዎች እንዴት ይድኑ ነበር? አንዱና አደናጋሪ የሆነው ነገር፥ እነዚያ ሰዎች መሥዋዕትን በማቅረብ ወይም በመልካም ሥራቸው ዳኑ የሚለው ሁኔታ ነው። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ ግልጽ እንደሚያደርገው፥ በብሉይ ኪዳን ዘመን የነበሩ ሰዎች በሕጉ ወይም በመሥዋዕቱ አልዳኑም። በብሉይ ኪዳን ጊዜ ማንም ሰው ሕጉን አሟልቶ አልጠበቀም። ሕጉንም በመጠበቅ በእግዚአብሔር ዘንድ የጸደቀ አልነበረም (3፡9-12፥20)፥ የብሉይ ኪዳን ጊዜ መሥዋዕት ውጪአዊና ሥነ ሥርዓታዊ ማንጻት መሥዋዕቱን ለሚያቀርቡት ሰዎች ይሰጣቸው ነበር (ዕብ. 9፡12)፥ እንጂ እውነተኛ የኃጢአት ስርየት አይሰጣቸውም ነበር። ምንም ዓይነት የእንስሳ መሥዋዕት እውነተኛውን የኃጢአት ስርየት ሰጥቶ ስእግዚአብሔር ፊት ለጽድቅ አያበቃም (ዕብራውያን 10፡1፥4፥11)። ከዚህ ይልቅ ለብሉይ ኪዳን አማኞች የኃጢአትን ይቅርታ የሰጣቸው የክርስቶስ ሞት ነበር። የብሉይ ኪዳን ሰዎች ወደ እግዚአብሔር ፊት በእምነት ቀርበው መሥዋዕትን ሲያደርጉ፥ እግዚአብሔር ተስፋውን በመጠበቅ የኃጢአት ይቅርታን እንደሚሰጣቸው በማመን ሲሆን፥ እግዚአብሔርም ውጫዊ ሥነ ሥርዓታዊ ማንጻትን ያደርግላቸው ነበር (ዕብ. 9፡13)። ቢሆንም ኃጢአታቸው የቅጣቱን ዋጋ ስላላገኘ በሙሉና ዘላለማዊ ይቅርታን አላገኙም ነበር። በዚህ ፈንታ እግዚአብሔር ያደረገው ነገር ቢኖር ኢየሱስ እስከመጣበት ጊዜ ድረስ የኃጢአታቸውን ሙሉና የመጨረሻ ቅጣት አቆየው። ግን ኢየሱስ በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ፥ እግዚአብሔር የክርስቶስን የሞት መሥዋዕትነት፥ በብሉይ ኪዳን ጊዜ በእውነተኛ እምነት ወደ እርሱ ዘንድ ለመጡት ኃጢአት ቤዛ አደረገው (ሮሜ 3፡25-26፥ ዕብራውያን 9፡15)። 

ብዙ ጊዜ እግዚአብሔር የብሉይ ኪዳን ሕዝቡን «የልባችሁን ሸለፈት ግረዙ» ሲል ያዛቸው ነበር (ዘዳግም 10፡16፤ ኤርምያስ 4፡4)። እንግዲህ ሕዝቡ ውጪአዊውን የግርዘት ሥነ ሥርዓት በመፈጸም ብቻ የኃጢአት ይቅርታን ሊያገኙና ደኅንነትን ሊቀበሉ እንደማይችሉ በዚህ ሁኔታ ይገልጽላቸው ነበር። ለማንም ሰው ቢሆን ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት በምንም አኳኋን የኃጢአት ይቅርታን ወይም ደኅንነትን ሊሰጥ አይችልም። ስለዚህ ሰዎች እነዚህን ለማግኘት ከፈለጉ ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ከልባቸው ለእግዚአብሔር መታዘዝ አለባቸው። በብሉይ ኪዳን ጊዜ በእግዚአብሔር ፊት ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ወደ እርሱ የቀረቡና በልባቸው በእርሱ ላይ የተሞረኮዙ፥ የእግዚአብሔር እውነተኞች ሰዎች ብቻ ደኅንነቱን ሊቀበሉ ቻሉ (ሮሜ 2፡28-29)። 

ክርስቶስ በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ፥ እግዚአብሔር ይህን በሞቱ የተገኘውን ትሩፋት ብሉይ ኪዳን አማኞች ወደ ኋላ ተመልሶ እንዲጠቅማቸው አድርጎአል። እግዚአብሔር ተስፋ የገባበትን ደኅንነት ይሰጥ ዘንድ፥ ሰዎች በእምነት መሥዋዕታቸውን ለእግዚአብሔር ያቀርቡ ነበር። በእግዚአብሔር ያመኑ ቢሆኑም፥ የተስፋውን መፈጻም ሊያዩ አልቻሉም። በብሉይ ኪዳን ጊዜ ለነበሩ አማኞች የወደፊቱ የክርስቶስ መስቀል ተሸፍኖባቸው ነበር።

የብሉይ ኪዳን አማኞች በአንድ በሰማይ በሚኖር በእግዚአብሔር በማመናቸው ብቻ አልዳኑም። እርሱ በሰጠው ተስፋ መሠረት ደኅንነትን እንደሚቸራቸው ስላመኑ ሊድኑ ችለዋል። እንዲሁም በእግዚአብሔር ቃል ስለ አመኑ ጻኑ። ይህም እኛ በእግዚአብሔር ቃል በእምነት እንደዳንነው ዓይነት ማለት ነው። በብሉይ ኪዳን ውስጥ ፈውስን ያገኙ እንደ ንዕማን ያሉ አሕዛብ ስለ እስራኤል እውነተኛ የሆነ አንድ አምላክ ሊያውቁና በእርሱና በተስፋዎቹ ሊያምኑ ችለዋል። ዛሬ እግዚአብሔር በእርሱ የሚያምን ግን ስለ ኢየሱስ በፍጹም ያልሰማውን ሰው ያድነዋል? በክርስቶስ ሥራ የተገኙትን ትሩፋቶች ማለትም የሞቱንና ትንሣኤውን ትሩፋቶች ስለ ኢየሱስ ሰምቶ ለማያውቅ ሰው ግን በአንዱ በእውነተኛው አምላክ ለሚያምን ሰው ይሰጠዋልን? አዲስ ኪዳን እንደሚያስተምረው ኢየሱስ ወደዚህ ምድር መጥቶአል፥ የእግዚአብሔር ፍላጎት ስለ ኢየሱስ ሕይወትና ሞት ሰምተው በእምነት የሚያረጋግጡትን ማዳን ነው። ስለ ኢየሱስ በፍጹም ያልሰሙ ሰዎች ካሉ፥ ነገር ግን ቆርኔሌዎስ እንዳደረገው በአንዱ በሰማይ የሚኖር አምላክ ፊት ራሳቸውን ዝቅ ለሚያደርጉት፥ ስለ ኢየሱስ የሚናገረው መልእክት እንዲሰብኩላቸው እግዚአብሔር መልእክተኛውን ይልክላቸዋል። የኢሳን ታሪክ የመሰለ በምንሰማበት ጊዜ፥ በአስተሳሰባችንም ሆነ በአስተያየታችን ረገድ መጠንቀቅ አለብን። ምክንያቱም ስለ ኢሳ ፍጻሜ የማናውቃቸው ብዙ ነገሮች አሉ። ምናልባት ከመሞቱ በፊት ስለ ኢየሱስ ሰምቶ፥ እንደ አዳኙ አምኖበት ይሆናል። ምንም ያክል ኢሳ ስለ ኢየሱስ የምሥራቹን ለመስማት ባይታደልም፥ እግዚአብሔር እግዚአብሔር ስለሆነ፥ እርሱ በመረጠው መንገድ ማንንም ሊያድን ይችላል። ስለሆነም እግዚአብሔር በጥበቡና በምሕረቱ እንደ ኢላ ያሉትን ሰዎች ማዳን አያዳግተውም። ሆኖም አዲስ ኪዳን ይህን የመሰለ ትምህርት አያስተምርም። የተደጋገመው የአዲስ ኪዳን ትምህርት እግዚአብሔር ስለ ጌታ ኢየሱስ የሚናገረውን ሰምተው በእምነት የሚቀበሉትን እንደሚያድን ነው። 

ጥያቄ፡- ሰዎች ሊድኑ የሚችሉት ስለ ኢየሱስ በሚነገራቸው መልእክት ባላቸው እምነት ነው ስለሚለው አሳብ ምን አስተያየት አለን? 

ሰዎች ስለ ኢየሱስ የሚናገረውን መልእክት ሰምተው ስለማመናቸው ጠቃሚነት በምናስብበት ጊዜ፥ አንድ ግልጽ የሆነ አስተሳሰብ ሊኖረን ይገባል፥ ይህም በሕይወታችን ውስጥ ሊኖር የሚገባው ነገር ይህን መልእክት ከሌሎች ሰዎች ጋር መካፈል ነው። በአኗኗራችን ስለ ኢየሱስ ልንመሰክር ይገባናል። ስለዚህ በአኗኗራችን በስሙ ላይ ሐፍረትንም ወይም ነቀፌታን እንዳናደርስ መጠንቀቅ አለብን። ከመልካም ሕይወታችን ወይም አኗኗራችን በመነሣት፥ ስለ ኢየሱስ የምናቀርበውን የምሥራች ቃል የሚስብና ሌሎች ሊቀበሉት የሚችሉት እንዲሆን መጣር ይገባናል (ቲቶ 2፡10)። ከዚህም በስተቀር ሁልጊዜ፥ ስለ ክርስቶስ የሚያወሳ መልእክት የምናቀርብበትን አጋጣሚ ሁሉ መፈለግ ይገባናል። ከሰዎች ሁሉ ጋር ስለ ክርስቶስ የደኅንነት ደስታና በረከቶች ማካፈል እጅግ ከፍ ያለ ዋጋ ያለው ድርጊት ነው። ሰዎች ሊድኑና ከእግዚአብሔር ጋር ሊታረቁ የሚችሉበት መንገድ ክርስቶስ ብቻ ነው። ሁል ጊዜ ልታካፍሉት የሚገባችሁ ዜናም ይህ ነው፡፡

ምንጭ፡- “አስተምህሮ ክርስቶስና ደኅንነት”፤ ጽሑፍ፣ በዶ/ር ስቲቭ ስራውስ፤ ትርጉም በኃይሉ ልመንህ

Exit mobile version