Site icon

ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ጸሎት አስተማራቸው (ሉቃስ 11፡1-13)

ከወንጌላት እንድምንረዳው፣ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው አንድ ነገር እንዲያስተምራቸው የጠየቁት ጥቂት ጊዜ ብቻ ነው። ይህንንም ያደረጉት፥ ኢየሱስ ሲጸልይ ተመልክተው ከእርሱ የጸሎት ሕይወት አንድ ነገር ለማግኘት ስለ ፈለጉ ነበር። ምናልባት እነዚህ ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ በጸሎቱ ቅድሚያ የሚሰጥባቸውን ጉዳዮች ብቻ ሳይሆን፥ በእነርሱና በዮሐንስ ደቀ መዛሙርት መካከል ያሉትንም ልዩነቶች ሳያጠኑ አልቀሩም። የኢየሱስ ተከታዮች ሊማሩ ከሚገባቸው እጅግ አስፈላጊ ነገሮች አንዱ ጸሎት ነው። ጸሎት ትክክለኛ ቃላትን መናገር ብቻ ሳይሆን፥ ትክክለኛ አመለካከትንም መያዝ ነው። ስለሆነም ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የጸሎት መመሪያን በመስጠት እግዚአብሔር ጸሎታቸውን እንዲሰማ ከፈለጉ ምን ዐይነት አመለካከት ሊኖራቸው እንደሚገባ አስተምሯቸዋል። ኢየሱስ ለተከታዮቹ ካስተማራቸው ነገሮች መካከል አንዳንድ እውነቶችን ቀጥለን እንመለከታለን፡፡

ሀ. ጸሎት፥ ሰዎች ከመለኮታዊ አባታቸው ጋር ግንኙነት የሚያደርጉበት መሆኑን ነገራቸው። እግዚአብሔርን የሚያስፈልገንን ነገር እንደማይሰጥ ጓደኛ በጥርጣሬ መመልከት የለብንም። ስለዚህ ጸሎት በምናደርግበት ጊዜ አንድ ጓደኛችንን የምንፈልገውን ጠይቀን እንደምናገኝበት ዘዴ አድርገን መጠቀም የለብንም። እግዚአብሔር ሩቅ ስላይደለ፥ በቅርብ ሆኖ የልጆቹን ጸሎት ይሰማል።

ለ. ጸሎት የእግዚአብሔርን ክብር መፈለግ ነው። ጸሎት ከእግዚአብሔር ነገሮችን ለማግኘት ሳይሆን፣ ከእግዚአብሔር ጋር በመነጋገር እርሱን የሚያስከብሩትን ነገሮች የምንጠይቅበት መሣሪያ ነው። ብዙ ክርስቲያኖች ስለ ጸሎት የተጻፉ ጥቅሶች የፈለግነውን ነገር ሁሉ ለመጠየቅ ዋስትና እንደሚሰጡን አድርገው ያስባሉ። ኢየሱስ እንዳስተማረው፣ ከጸሎት ጥያቄያችን በስተ ጀርባ ሁልጊዜ የእግዚአብሔርን ክብር ማስቀደም አለብን።

ሐ. ጸሎት የእግዚአብሔርን መንግሥት በሚያስፋፉ ጉዳዮች ላይ እንጂ፥ በግል ጉዳዮች ላይ ማተኮር የለበትም። ጸሎታችን የእግዚአብሔር መንግሥት በሰዎች ልብና አእምሮ ውስጥ እንዲገዛ ከማሰብ ሊመነጭ ይገባል።

መ. ጸሎት ለዕለታዊ ፍሎጎታችን ማሟያ በሚያገለግሉ ነገሮች እንጂ፥ በስግብግብነት አሳብ ላይ ሊመሠረት አይገባውም። ብዙውን ጊዜ የሚያስፈልጉንን ሳይሆን የምንፈልጋቸውን ነገሮች ለማግኘት እንጸልያለን።

ሠ. ጸሎት ሊቀርብ የሚችለው ከሰዎች ጋር የተስተካከለ ግንኙነት ሲኖረን ብቻ ነው። የበደለንን ሰው ይቅር ለማለት ካልፈለግን፥ መጸለይና ከእግዚአብሔር ዘንድ መልስ ለማግኘት መሞከር የለብንም።

ረ.ጸሎት በእግዚአብሔር ፊት በቅድስና መመላለስን ይፈልጋል።

ሰ. እግዚአብሔርን ለሚያስከብሩ ነገሮች ስንጸልይ፣ እግዚአብሔር መልስ እንደሚሰጠን እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን (ሉቃስ 11፡13)። እግዚአብሔርን ከሚያስከብሩ ጸሎቶች አንዱ መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል መጸለይ ነው። የሚከተለውን ጥቅስ ከሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ጋር በጥንቃቄ ማገናዘብ አለብን (ሉቃስ 11፡13)። ለምሳሌ ከዚህ ጋር ተጓዳኝ በሆነው በማቴዎስ ምንባብ እግዚአብሔር መልካም ስጦታዎችን እንደሚሰጥ ይናገራል (ማቴ. 7፡1)። ይህም መንፈሳዊ ስጦታዎችን የሚያመላክት ነው። መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር ከሚሰጠን ስጦታዎች አንዱ ነው። ኢየሱስ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 2 ላይ መንፈስ ቅዱስ በተከታዮቹ ሁሉ ላይ እንዲወርድ ከማድረጉ በፊት ይህንን ማብራሪያ ሰጥቷል። የእግዚአብሔር ልጆች የሆንን ሁሉ መንፈስ ቅዱስ በውስጣችን እንዳለ ሮማ 8፡9 በግልጽ ያስረዳል። ስለሆነም የምንጸልየው መንፈስ ቅዱስ ወደ እኛ እንዲመጣ አይደለም። ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በይበልጥ እንዲቆጣጠረንና ለእግዚአብሔር ክብር እንዲጠቀምብን ነው።

የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሊያደርጉ ከሚገባቸው ነገሮች አንዱ ለአዳዲስ ክርስቲያኖች ጸሎትን ማስተማር ነው። ብዙዎቻችን ለእግዚአብሔር ክብር ሳይሆን ለተሳሳቱ ዓላማዎች፣ ለራስ ወዳድነት ፍላጎቶች ወይም ለግል ጥቅሞች እንጸልያለን። አንዳንዶቻችን ደግሞ እግዚአብሔርን ከእንቅልፉ የምንቀሰቅሰው እስኪመስል ድረስ በኃይል እየጮኽን እንጸልያለን። ወይም ደግሞ የእግዚአብሔርን ስም ከሚገባው በላይ ደጋግመን እንጠራለን። በረዥም ጸሎታችን እግዚአብሔርን ለማስደነቅ የምንሞክርም አለን። (የኢየሱስ ጸሎት እንዴት ቀላል እንደሆነ ተመልከት!!!) የአንድ ሰው ልብ ከእግዚአብሔርና ከሰዎች ጋር ትክክል ከሆነና የጸሎት ዓላማውም ንጹሕ ከሆነ፣ ጸሎቱ ታላቅ ኃይል እንዳለው ግልጽ ነው። እግዚአብሔር ምሥጢራዊ አሠራር ውስጥ አብዛኛውን ጊዜ ጸሎታችን፥ ስአንድ ሁኔታ ውስጥ እርሱ ለመሥራት የሚፈልገውን ሥራ እንዲወስን ይደረጋል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ለአዳዲስ አማኞች እንዴት መጸለይ እንዳለባቸው ማስተማር የሚያስፈልገው ለምን ይመስልሃል? ለ) ለመጨረሻ ጊዜ የጸለይኸውን ጸሎት አስብ። ከእነዚህ መርሆዎች ጸሎትህ የተከተለው የትኛውን ነው? ሐ) ብዙ ክርስቲያኖች በጸሎታቸው ላይ የማይጠቀሙባቸው መርሆዎች የትኞቹ ናቸው? ለምን?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Exit mobile version