Site icon

አይሁዶች ለሁለተኛ ጊዜ ክርስቲያኖችን አሳደዱ (የሐዋ. 12፡1-25)

ክርስቶስ ከተሰቀለ፥ ከሞት ከተነሣ፥ ወደ ሰማይ ካረገና ቤተ ክርስቲያንም ከተመሠረተች አሥራ አራት ዓመት ሆኖታል። ቤተ ክርስቲያን በአንድ ወቅት የተነሣባትን ስደት ተቋቁማለች። አሁን ደግሞ ስደት ለሁለተኛ ጊዜ ተነሳባት፡፡ ስደት በጥንታዊቷ ቤተ ክርስቲያን ላይ በተደጋጋሚ የሚደርስና በየጊዜው እየጨመረ የሚሄድ ነገር በመሆኑ፥ ሉቃስ ስለ ስደት እንዲያውቁ ፈለገ፡፡

የሁለተኛው ስደት ዋናው ቀስቃሽ ሄሮድስ አግሪጳ ነበር። ሄሮድስ አግሪጳ ይሁዳን፥ ሰማርያንና ገሊላን እንዲያስተዳድር በሮማውያን ተሹሞ ስለነበር፥ በይሁዳ ከነበሩ አይሁዶች ጋር ለመወዳጀት ፈለገ፡፡ በዚያን ጊዜ ብዙ አይሁዶች ክርስቲያኖችን ይጠሉ ስለነበር ሊያሳድዳቸው ወሰነ። ስደቱ ከመሪዎች እንዲጀምር ፈልጎ ሐዋርያው ያዕቆብን አስገደለው። ይህ ድርጊቱ አይሁድን ምን ያህል እንዳስደሰተ ሲመለከት ጴጥሮስንም ለማስገደል ሊል አሳሰረው። እግዚአብሔር ግን ለጴጥሮስ የተለየ ዕቅድ ስለነበረው፥ መልአኩን ልኮ አስፈታው። ደቀ መዛሙርቱ ጴጥሮስ እንዲለቀቅ እየጸለዩ ስለ ነበር፥ እግዚአብሒር ጸሎታቸውን በመመለሱ ተደነቁ።

ታሪኩ በክርስቲያኖች ላይ ስደት እንደሚመጣ ያስተምራል። የስደቱ ውጤት ግን በእግዚአብሔር ፈቃድ ውስጥ የተሰወረ ነው። ክርስቲያኖች እግዚአብሔር እንዲጠብቃቸው መጸለይ አለባቸው። እግዚአብሔር ሕዝቡን ለማዳን እንደሚሠራና እንዲያውም ተአምር እንደሚያደርግ መጠበቅ አለብን። እግዚአብሔር አንዳንድ ጊዜ ጸሎታችንን በመመለስ ከስደትና ከሞት ይጠብቀናል። ሌላ ጊዜ ደግሞ ከጸሎታችን ባሻገር ልጆቹ እንዲሞቱ ወይም ስደት እንዲደርስባቸው ያደርጋል። ክርስቲያኖች እግዚአብሔር ስደትን ለማስቆምም ሆነ ስደቱ በርትቶ በሞት ውስጥ እንዲያልፉ ሊፈቅድ እንደሚችል ማወቅ አለባቸው። ቁም ነገሩ ለጸሎት ያለን አመለካከት መለወጡ ላይ ነው። ጴጥሮስ እግዚአብሔር እንደሚያድነው ባያውቅም እንኳ፣ በእግዚአብሔር ፈቃድ ውስጥ መኖሩን በማሰብ በፍጹም ሰላምና ዋስትና ውስጥ እንደነበረ ሁሉ፥ እኛም የስደቱን ውጤት በእግዚአብሔር እጅ ውስጥ ትተን በእግዚአብሔር ፍጹም ፈቃድ ውስጥ ልናርፍ እንችላለን። ነገር ግን ሞት እያንዣበበብን ሳለ እንዴት በሰላም መኖር እንችላለን? ምክንያቱም ለእግዚአብሔር ልጆች እርሱ ወደሚገኝበት ስፍራ መሸጋገሪያ መንገድ ነው። ሞት የሕይወት ፍጻሜ ሳይሆን፥ የታላቁ ሕይወት መጀመሪያ ነው። ይህንን አምነን የምንቀበለው በእምነት ነው።

የውይይት ጥያቄ:- – ሀ) ከዚህ ታሪክ ስለ ጸሎት መልስ ምን እንማራለን? ለ) ምንም ቢሆን ምን ለእግዚአብሔር ፈቃድ ራስን ስለ ማስገዛት ምን እንማራለን?

እግዚአብሔር ያዕቆብን ለማዳን ይችል ነበር፥ ነገር ግን እንዲሞት ፈቀደ። ጴጥሮስም ሊሞት ይችል ነበር፥ እግዚአብሔር ግን ተአምር ሠርቶ አዳነው። ይህ እኛ ልንረዳው የማንችለው የእግዚአብሔር ሉዓላዊ ፈቃድ አካል ነው። ነገር ገን እግዚአብሔር በሁሉ ላይ ጌታ ስለሆነ የያዕቆብን ገዳዮች ሳይቀጣ እያልፍም። ሄርድስ አግሪጳ የእግዚአብሔርን ልጅ ስለ ገደለና በትዕቢት ለአምላክ ብቻ የሚገባውን ስግደት ስለ ተቀበለ፥ እግዚአብሔር በሕመም ቀስፎታል። ሰውነቱም በትል ተበልቶ እንዲሞት አድርጓል።

የክርስቲያኖች ጠላት የሆነ ሰው የእግዚአብሔርን ልጆች ለመግደል ይችል ይሆናል። ግን እግዚአብሔር ሁልጊዜ ጌታ ነው። እግዚአብሔር በራሱ ጊዜ ሄሮድስን ቀጥቶታል። በአንጻሩም የቤተ ክርስቲያን እድገትና የእግዚአብሔርን ቃል መስፋት ሊገታ የሚችል ነገር አልነበረም። ንጉሥ ሄሮድስም ሆነ የሲኦል ልጆች ይህንን ማሸነፍ አይችሉም።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Exit mobile version