Site icon

ምስጋናና ጸሎት (ፊል. 1፡1-10)

ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ፥ ሁለት ዐበይት እውነቶችን ለማስተላለፍ ይፈልጋል። በመጀመሪያ፥ የፊልጵስዩስ አማኞች በማንኛውም ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ቢሆኑ በክርስቶስ ደስ መሰኘትን እንዲማሩ ይፈልጋል። እሥራት፥ ስደት፥ ድህነት፥ ሞትም እንኳን ቢያጋጥማቸው ደስታቸውን ማጣት አይኖርባቸውም። በሚጎዱን ነገሮች አንደሰትም። አፍቃሪው አምላካችን ሁኔታዎችን በመቆጣጠር ላይ በመሆኑ ደስ ልንሰኝ እንችላለን።

ሁለተኛ፥ ጳውሎስ የፊልጵስዩስ አማኞች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አንድነትን ለመፍጠር እንዲጥሩ ይፈልጋል። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ክፍፍል የተስፋፋ ይመስላል። ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸው ሁለት ሴቶች ግብግብ የገጠሙ ሲሆን፥ የቤተ ክርስቲያኒቱ አባላትም በቲፎዞነት የተከተሏቸው ይመስላል። ጳውሎስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሰላም፥ አንድነትና ፍቅር እንዲኖር ይለምናቸዋል። ሰዎች የተለያዩ አቋሞችን ይዘው ሳለ እንዴት ሰላምና አንድነት ሊኖር ይችላል? ይህ ሊሆን የሚችለው የክርስቶስን ምሳሌነት በመከተል የግል አመለካከታችንን ስንተውና ሌሎችን ስናከብርን ነው። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ክፍፍል በሚኖርበት ጊዜ ሁሉ የችግሩ ሥር ትዕቢትና ራስ ወዳድነት ሆኖ ይገኛል። ይህ የራሳችንን መሳሳት ወይም የሌሎችን አስተሳሰብ ተገቢነት ለመቀበል ካለመፈለግ የሚመነጭ ነው። ይህ ይቅር ለማለት አለመፈለግ፥ ሰዎች እኛን የሚጎዱበትን መንገድ መመርመርና ሳይቃወሙን ተቃውመውናል ብሎ ማሰብ ነው። የሐሰት ትምህርትን ከመቃወም ውጭ የሚመጣ ማንኛውም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚከሠት ክፍፍል ክርስቶስ አንድ እንሆን ዘንድ ባቀረበው ጸሎት ላይ የሚሰነዘር ስድብ ነው። በተጨማሪም፥ ይህ ጳውሎስ ለእኛ ለመሞት ሲል ሰማይን ትቶ ወደ ምድር የመጣውን የክርስቶስን ምሳሌነት እንድንከተል ያቀረበውን ልመና አለመቀበል ነው።

አንድ የቤተ ክርስቲያን መሪ ከሚያገለግልበት ቤተ ክርስቲያን ጸሎትና እገዛ በሚያገኝበት ጊዜ፥ ሥራው አስደሳች ይሆንለታል። ይህም በቤተ ክርስቲያኒቱና በመሪው መካከል ጠንካራ ትሥሥርን በመፍጠር እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋል። በጳውሎስና በፊልጵስዩስ ቤተ ክርስቲያን መካከል የተከሠተው ይኸው ነበር። እንደ ቆሮንቶስና ገላትያ ያሉት አብያተ ክርስቲያናት የጳውሎስን ሥልጣን ሲጠራጠሩ፥ የፊልጵስዩስ ቤተ ክርስቲያን ግን አጥብቃ ደግፋዋለች። ጳውሎስን ከማክበራቸውና ለአገልግሎቱ ከመጸለያቸው በተጨማሪ፥ ጳውሎስ በሌሎች አካባቢዎች የሚያካሂደውን አገልግሎት ለመደገፍ ገንዘባቸውን ሰጥተውታል።

ይህ የፊልጵስዩስ መልእክት መግቢያ ይህንኑ በጳውሎስና በፊልጵስዩስ ቤተ ክርስቲያን መካከል የነበረውን በፍቅር ያንቆጠቆጠ ግንኙነት ያሳያል። ጳውሎስ ራሱንና ጢሞቴዎስን ካስተዋወቀና ሰላምታ ካቀረበ በኋላ፥ ቤተ ክርስቲያኒቱንና የወንጌል ተካፋይነቷን በሚያስታውስበት ጊዜ ምን ዓይነት ደስታ እንደሚሰማው ይገልጻል። የወንጌል ሸሪኮች ለመሆን መፍቀዳቸው እያደገ የመጣው የመንፈሳዊ ብስለታቸው ምልክት ነበር። ጳውሎስ ወደ ክርስቶስ አምሳል ሊለውጣቸው የጀመረው እግዚአብሔር እስከ ክርስቶስ ምጽአት ድረስ ይህንኑ ተግባር እንደሚያጠናቅቅ ይናገራል። ከእነርሱ ርቆ በወኅኒ ቤት ውስጥ መቀመጡ ጳውሎስ ከእነርሱ ጋር ካለው ግንኙነት የተነሣ የተሰማውን ደስታና ፍቅር ሊቀንስበት አልቻለም።

እግዚአብሔር ለአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን የወጠነው እማኞች በብስለት እንዲያድጉ ነው። ብስለት ከሚገለጽባቸው መንገዶች አንዱ የቤተ ክርስቲያን ከጥገኝነት ራስን ወደ መቻል መለወጥ ነው። ይህም ቤተ ክርስቲያን መርሐ ግብሮቿን ለማካሄድና ለገንዘብ ፍጆታዋ በውጭ ወንጌላውያን፥ ሚሲዮናውያን ወይም ለጋሾች ላይ ከመደገፍ ወጥታ በራሷ ገንዘብ የወንጌል ስርጭትና ድሆችን የመርዳት ተግባር የምታከናውንበት ነው። ከዚህ በኋላ ቤተ ክርስቲያን ከሌሎች ጋር በመተባበር ወንጌልን ወደ ሌሎች አካባቢዎች ልታደርስ ትችላለች። የሚያሳዝነው ብዙ አብያተ ክርስቲያናት በውጭ እገዛ ላይ ይደገፋሉ። እንዲሁም ብዙ አብያተ ክርስቲያናት በራስ ወዳድነት የራሳቸውን ፍላጎት ብቻ በማሟላት ላይ ይገኛሉ። እግዚአብሔር የሚፈልገው ግን ቤተ ክርስቲያን በፍጥነት ተጠናክራ ወንጌልን በማስፋፋቱ ሥራ ላይ እንድትሳተፍ ነው። የሚያስገርመው የፊልጵስዩስ ቤተ ክርስቲያን ሰዎች ወንጌሉን ከሰሙ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ወንጌሉን ለሌሎች ለማካፈል ተግተው ይሳተፉ ጀመር።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የቤተ ክርስቲያንህን ዕድገት ገምግም። ቤተ ክርስቲያንህ ከሦስቱ የዕድገት ደረጃዎች በየትኛው ላይ ነች? (ጥገኛ፥ ራሷን የቻለች፥ ወይስ ከሌሎች ጋር ተባብራ ወንጌልን የምታሰራጭ?) ለ) ቤተ ክርስቲያንህ ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ጋር ተባብራ ወንጌሉን ለማስፋፋት ትችል ዘንድ ምን ማድረግ ያስፈልጋታል? ሐ) ለቤተ ክርስቲያን በጥገኝነት ወይም ራሷን ችላ የራሷን ፍላጎቶች በማሟላቱ ተግባር ላይ ብቻ ማተኮር ቀላል የሚሆነው እንዴት ነው?

ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ቤተ ክርስቲያን እንደሚጸልይ ገልጾአል። ይህ ጸሎት በመንፈሳዊ ብስለት ማደጋቸው ላይ እንደሚያተኩር አስተውል።

ሀ. ጳውሎስ ፍቅራቸው፥ እውቀታቸውና የማስተዋላቸው ጥልቀት ይበልጥ እንዲጎለብት ጸልዮአል። አሁንም ጳውሎስ በመንፈሳዊ ዕድገትና ጤንነት ትክክለኛነት ላይ እንዳተኮረ እንመለከታለን። በስሜት የተጋጋለ አምልኮ ማካሄዱ ብቻ በቂ አይደለም። የመንፈሳዊ ብስለት መሠረቱ ስለ እግዚአብሔር፥ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ፥ በክርስቶስ ስላለን በረከት፥ ወዘተ… እያደገ የሚሄድ ግንዛቤ መጨበጥ ነው። ማንም ክርስቲያን እግዚአብሔርን ካላወቀና ቃሉን ካልተከተለ በቀር ስሜታዊ አምልኮ በማካሄዱ ብቻ እግዚአብሔርን ደስ ሊያሰኝ አይችልም። የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የምእመኖቻቸውን እውቀት ለማሳደግ መትጋት ያለባቸው ለዚህ ነው።

ለ ጳውሎስ የፊልጵስዩስ አማኞች ለክርስቶስ ቀን ተዘጋጅተው ቅኖችና አለነውር እንዲሆኑ ይጸልያል። ክርስቲያኖች ወይም ቤተ ክርስቲያን ልታደርጋቸው የሚገቡ መልካም ነገሮች አሉ። ጳውሎስ ግን እነዚህ ክርስቲያኖች ከመልካም ነገሮች ሁሉ ምርጥ የሆኑትን እንዲመረምሩና እነዚሁኑ ከሁሉም የበለጠ መንፈሳዊ ለውጥ የሚያስከትሉትን ተግባራት እንዲያከናውኑ ይጸልያል። ቤተ ክርስቲያን ሕንጻ ትገንባ ወይስ ለወንጌላውያን ገንዘብ ትስጥ? የቤተ ክርስቲያን ገንዘብ ለኳዬር ልብስ መግዣ ይዋል ወይስ ሰዎች በመንፈሳዊ ሕይወታቸው እንዲያድጉ የሚያግዙትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መሣሪያዎችን ለመግዛት? በእንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች ውስጥ ከሁሉም የሚበልጠውን ለማወቅ መንፈሳዊ ጥበብን መጠቀም አስፈላጊ ነው። ጳውሎስ የፊልጵስዩስ አማኞች ከሁሉም የሚሻለውን እንዲያውቁና እንዲመርጡ የፈለገበት ምክንያት እግዚአብሔር ምን እንዲያደርጉ እንደሚፈልግ እንዲያውቁና ክርስቶስ ሲመጣም፥ ንጹሐንና እንከን የሌላቸው ሆነው እንዲገኙ ነው።

ሐ. ጳውሎስ በጽድቅ ፍሬ እንዲሞሉ ይጸልያል። ጳውሎስ የሚሻው ሰዎች እግዚአብሔር እንደሚፈልገው በመኖር የእምነታቸውን እውነትነት እንዲያሳዩ ነው። ጽድቅ ኃጢአትን አለመፈጸም ብቻ አይደለም። ይህ በእግዚአብሔር ዓይኖች ፊት ትክክል የሆነውን መፈጸም ጭምር ነው። ይህም ድሆችን መርዳት፥ ሌሎችን መታዘዝ፥ በፍቅርና በአንድነት መኖር፥ በአጠቃላይም ማንኛውም እግዚአብሔርን ለማስደሰት ሲባል በጥሩ የመነሻ እሳብ የሚወሰድ እርምጃ ነው።

የውይይት ጥያቄ፡– እነዚህ ሦስት ጥያቄዎች የመንፈሳዊ ብስለት አመልካቾች ናቸው። እስኪ የራስህን ሕይወት ገምግም። ሀ) ፍቅርህ በይበልጥ በእግዚአብሔር ቃል እውቀት ላይ ተመሥርቶ እያደገ የሄደበትን ሁኔታ ግለጽ። ለ) እግዚአብሔር ሁልጊዜም እንድታከናውን ከሚፈልጋቸው ነገሮች ሁለቱን በምሳሌነት ጥቀስ። ከሁለቱ የሚሻለው የትኛው ነው? መሻሉን እንዴት አወቅህ? ሐ) ባለፈው ሳምንት በሕይወትህ ውስጥ የተገለጡትን አንዳንድ የጽድቅ ፍሬዎች ዘርዝር። እነዚህ ፍሬዎች እያደጉና እየተደጋገሙ የመጡት እንዴት ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Exit mobile version