Site icon

የ1ኛ ዮሐንስ መልእክት ዓላማ

የውይይት ጥያቄ፡- የሚከተሉትን ጥቅሶች አንብብ። 1ኛ ዮሐ 1፡4፤ 2፡1፤ 2፡7-8፣ 2፡12-14፤ 2፡21፤ 2፡26፤ 5፡13። ዮሐንስ መልእክቱን የጻፈባቸውን ምክንያቶች ዘርዝር።

የ1ኛ ዮሐንስ መልእክት ጸሐፊው መልእክቱን ለመጻፍ የተነሣሣባቸውን አያሌ ዓላማዎች ያመለክታል። እነዚህን ዓላማዎች ከሚያመላክቱት ርእሰ ጉዳዮች መካከል የክርስቶስን አምላክነትና ሰብአዊ አዳኝነት መግለጽ፥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉትን ሐሰተኛ ትምህርቶች መከላከል እና ክርስቲያኖች ክርስቶስን በሚያስከብር መንገድ መመላለስ ስለሚገባቸው ሁኔታ ማስተማር ይገኙባቸዋል። በ1ኛ ዮሐንስ መልእክት ውስጥ የተጠቀሱ አንዳንድ ዐበይት ዓላማዎች የሚከተሉት ናቸው፡

የመጀመሪያ ዓላማ፡- ክርስቲያኖች ከዘላለማዊ አምላክ ጋር አስደሳች ኅብረት ሊያደርጉ እንደሚችሉ ማስገንዘብ (1ኛ ዮሐ 1፡4)። ነገር ግን ይህ ኅብረትን የማድረግ መብት የሚመጣው አንድ ሰው የክርስቶስን ማንነት በትክክል ከተገነዘበ በኋላ ብቻ ነው። እምነታችን ክርስቶስ ፍጹም አምላክና ፍጹም ሰው በመሆኑ እውነታ ላይ መመሥረት ይኖርበታል (1ኛ ዮሐ. 4፡14-15)። ክርስትና ሰው እግዚአብሔርን ለማስደሰትና ድነትን (ደኅንነትን) ለመቀበል የተለያዩ ተግባራትን የሚያከናውኑበትን ሥርዓት ያካተተ ሃይማኖት አይደለም። የክርስትና እምነት እምብርት በሕያው አምላክና ኃጢአተኛ በሆነ የሰው ልጅ መካከል የሚደረግ ግንኙነት ነው። እግዚአብሔር ክርስቶስን የላከው ከኃጢአት ነፃ አውጥቶ እንዲተወን አይደለም። ነገር ግን በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የነበረው መጋረጃ እንዲወገድና በአንድ ወቅት በኤድን ገነት ውስጥ አዳምና ሔዋን ያደርጉት እንደነበረው ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት እንድናደርግ ነው (ዘፍጥ. 3፡8-9)።

ሁለተኛ ዓላማ፡ ክርስቲያኖች የተቀደሰ ሕይወት መኖር እንዳለባቸው ለማብራራት። ይህም ሕይወት ከማያቋርጥ ኃጢአት የጸዳ መሆን ይኖርበታል (1ኛ ዮሐ 2፡1)። ዮሐንስ አማኞችን ከሁለት አክራሪ ጫፎች ለመጠበቅ ይፈልጋል። በመጀመሪያ፥ ፍጹምና ኃጢአት የሌለብን ነን ብለን እንዳናስብ ይፈልጋል (1ኛ ዮሐ 1፡8-10)። አማኞች አሁንም የኃጢአት ባሕሪ ስላለባቸው፥ እግዚአብሔር በሰጠን በአዲሱ ባሕሪ እና ከአዳም በወረስነው የኃጢአት ባሕሪ መካከል አሁንም ጦርነት ይካሄዳል። ሁላችንም በኃጢአት የምንወድቅባቸው ጊዜያት ይኖራሉ። ክርስቶስ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ በሚያጋጥመን ጊዜ ከእግዚአብሔር ጋር የነበረንን ግንኙነት መልሰን እንድናገኝ የሚያስችለን ቀላል መፍትሔ እንዳለ ይናገራል። ኃጢአታችንን ብንናዘዝ የክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል (1ኛ ዮሐ 1፡9)። ሁለተኛ፥ ዮሐንስ አማኞች ኃጢአትን ቀለል አድርገን እንዳንመለከት ባለማቋረጥና በፈቃደኝነት ኃጢአት የምንፈጽምበትን የአኗኗር ስልት ማስወገድ እንዳለብን ያስጠነቅቀናል። በፈቃደኝነትና ባለማቋረጥ የሚፈጸም ኃጢአት የእግዚአብሔር ልጆች አለመሆናችንን ያሳያል። የዚህ ዓይነቱ አኗኗር ከእግዚአብሔር እንደ ተወለድንና ባሕርያቱን እንደ ተላበስን የሚያስረዳውን እውነት ይቃረናል። ስለሆነም ዮሐንስ ክርስቲያኖች የዓለምን ሥርዓት በመውደድ በኃጢአት ውስጥ እንዳይዘፈቁ ያስጠነቅቃቸዋል። ለእግዚአብሔር እየታዘዝን የቅድስናን ሕይወት እንድንኖር ያደፋፍረናል።

ሦስተኛ ዓላማ፡ አማኞች በፍቅራቸው ተለይተው እንዲታወቁ ለማበረታታት (1ኛ ዮሐ 2፡7-8)። የሚወደንን እግዚአብሔር ልንወደው ይገባል። ሰዎችንም እንዲሁ መውደድ ይኖርብናል። ዮሐንስ በምድር ላይ ከክርስቶስ ጋር ሲመላለስ በነበረበት ወቅት ተለይቶ የሚታወቀው በነጎድጓድነት ወይም በቁጣው ነበር። ዮሐንስ በሞተበት ጊዜ ግን ተለይቶ የሚታወቀው የፍቅር ሐዋርያ በመሆኑ ነበር። አንድ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደሚናገረው በጣም አርጅቶ መራመድ በተሣነው ጊዜ፥ ክርስቲያኖች በቃሬዛ ላይ አድርገው በመሸከም ወደ ቤተ ክርስቲያን ይወስዱት ነበር። እዚያም ሲደርስ፥ «ልጆቼ፥ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ» ይል ነበር። ክርስቲያኖች ሊኖራቸው የሚገባውና የእግዚአብሔር ልጆች መሆናቸውን የሚያንጸባርቀው ወሳኝ ባህሪ ፍቅር ነው። ነገር ግን ዛሬ አብያተ ክርስቲያናቶቻችንን ስንመለከት ይህን ባህሪ ብዙም አናየውም።

አራተኛ ዓላማ፡- አማኞች በክርስቶስ ባመኑበት ወቅት እግዚአብሔር የዘላለምን ሕይወት ስጦታ እንደሰጣቸው ለማረጋገጥ (1ኛ ዮሐ. 5፡13)። በክርስቶስ ላይ ባለን እምነት አማካኝነት መንፈሳዊ ሕይወታችንን ለማጥፋት የሚጣጣረውን ሰይጣንን አሸንፈነዋል። የእግዚአብሔር ልጆች እንደ መሆናችንና እግዚአብሔርም በውስጣችን ስለሚኖር፥ ከሰይጣን እንበልጣለን (1ኛ ዮሐ 4፡4)። ከእግዚአብሔር ጋር ባለን ግንኙነት፥ ዓለምን አሸንፈናል (1ኛ ዮሐ 5፡4)። እነዚህ ሁሉ መንፈሳዊ ጉዞአችንን ተወጥተን ለዘላለም ክርስቶስ በሚሰጠን የዘላለም ሕይወት ደስ እንደምንሰኝ ያረጋግጡልናል።

አምስተኛ ዓላማ፡- አማኞችን በማወክ ላይ ያለውን የሐሰተኛ አስተማሪዎች ትምህርት ለማፍረስ። ይህ ሐሰተኛ ትምህርት አማኞችን ከፋፍሎአቸው ነበር። አንዳንዶቹ (አስተማሪዎቹን ጨምሮ) ቤተ ክርስቲያንን ለቅቆ በመውጣት የራሳቸውን ማኅበረ ምእመናን አቋቁመው ነበር (1ኛ ዮሐ 2፡19)። ከቤተ ክርስቲያን የተለዩት ሰዎች ክርስቲያኖች ከእነርሱ ጋር እንዲቀላቀሉ ባለማቋረጥ ይቆሰቁሷቸው ነበር።

ጳውሎስ ቀደም ሲል ከእነርሱ መካከል አንዳንዶቹ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሁከትን ለመፍጠር የሚያስችል ሐሰተኛ ትምህርት የሚያስተምሩ «ተኩላዎች» እንደሚሆኑ ለኤፌሶን ሽማግሌዎች አስጠንቅቆ ነበር (የሐዋ. 20፡29-30)። የኤፌሶንን ሽማግሌዎች ካስጠነቀቀ አያሌ ዓመታት በኋላ፥ ጳውሎስ በጢሞቴዎስ በኩል እነዚሁ የኤፈሶን አማኞች ከሐሰተኛ ትምህርት እንዲጠነቀቁ በድጋሚ ገልጾላቸው ነበር (2ኛ ጢሞ. 3፡1-7፤ 4፡3-4)። አሁን ጳውሎስ ያስጠነቀቃቸው ነገር ነፍስ ዘርቶ በመገኘቱ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ሐሰተኛ አስተማሪዎች ክፍፍል በመፍጠራቸው፥ ብዙዎች ሐሰተኛ ትምህርት መከተል ጀምረው ነበር።

ዮሐንስ ሐሰተኛ ትምህርት ምን እንደነበረ በግልጽ ስለማይናገር፥ ምሁራን ይህ ሐሰተኛ ትምህርት ምን ነበር? በሚለው ጉዳይ ላይ ይከራከራሉ። በ1ኛ ዮሐንስ ውስጥ እነዚህ አስተማሪዎች የካዱአቸውን ነገሮች በመመልከት ለክርስቲያኖቹ ምን እንዳስተማሩ ማወቅ ይቻላል። እነዚህ ሐሰተኛ አስተማሪዎች፥ ሀ) ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅና መሢሕ መሆኑን (1ኛ ዮሐ 2፡22፤ 5፡1፥ 5)። ለ) ክርስቶስ በሥጋ መምጣቱን (1ኛ ዮሐ 4፡2)። ሐ) የክርስቶስን ትእዛዛት ሥልጣን (1ኛ ዮሐ 2፡4)፥ መ) የራሳቸውን ኃጢአተኝነት (1ኛ ዮሐ 1፡8፥ 10)፥ ሠ) የክርስቶስ ሥራ ድነትን (ደኅንነትን) እንደሚያስገኝ (1ኛ ዮሐ 2፡2) እና ረ) ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረትን ለማድረግ ጽድቅን የተሞላ ባህሪ እንደሚያስፈልግ የሚያመለክቱትን ክርስቲያናዊ ትምህርቶች ይክዱ ነበር (1ኛ ዮሐ 1፡6፤ 2፡29፤ 36፤10)። እነዚህ ሐሰተኛ ትምህርቶች ኖስቲሲዝም ተብሎ የሚታወቀው ፍልስፍና ትምህርቶች ሳይሆኑ አይቀርም። ዮሐንስ እውነትን ይዘው የቆሙትን ክርስቲያኖች በመደገፍ፥ አማኞችን ወደ ተሳሳተ ትምህርት የሚመሩትን ሰዎች ያስጠነቅቃል።

የቀድሞው የኖስቲሲዝም ገጽታ ከተጠነሰሰበት ከዮሐንስ ጊዜ ጀምሮ ለቀጣይ 200 ዓመታት ይህ ሐሰተኛ ትምህርት ለቀድሞይቱ ቤተ ክርስቲያን እጅግ አደገኛ ነበር። በዚህ የ1ኛ ዮሐንስ መልእክት ውስጥ ይህ ሐሰተኛ ትምህርት ወደ ቤተ ክርስቲያን ያመጣቸውንና ዮሐንስ የተቃወማቸውን ሁለት ዐበይት ስሕተቶች እንመለከታለን።

ሀ) ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰጠ የስሕተት ትምህርት፡ አንዳንድ ኖስቲኮች ክርስቶስ መለኮታዊ መንፈስና ከአነስተኛ አማልእክት አንዱ እንደሆነ ያስተምሩ ነበር። ክርስቶስ ሰው መስሎ ቢታይም፥ ሙሉ ለሙሉ ሰው አልነበረም ሲሉ ያስተምራሉ። ዮሐንስ ለዚህ ምላሽ ሲሰጥ፥ ክርስቶስ ሲያስተምር መስማቱን፥ ማየቱንና የክርስቶስን አካል መዳሰሱን ይናገራል። ዮሐንስ ክርስቶስ አካል እንዳለውና መንፈስ ብቻ እንዳልሆነ ይናገራል። ሌሎች ኖስቲኮች ደግሞ ክርስቶስ የተባለ መለኮታዊ መንፈስ ኢየሱስ ወደተባለው ሰው በጥምቀት እንደመጣ ይናገራሉ። ይህ መለኮታዊ መንፈስ ሰብአዊው ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት እንደተለየው ይናገራሉ። ዮሐንስ ለዚህም ምላሽ ሲሰጥ፥ ፍጹም ሰውና ፍጹም አምላክ የነበረው አንዱ ክርስቶስ በመስቀል ላይ እንደ ሞተ ያስረዳል (1ኛ ዮሐ 5፡6)። ዮሐንስ እውነተኛ እማኝ ሰብአዊው ኢየሱስ እና መለኮታዊው ክርስቶስ አንድ መሆኑን ማመን እንዳለበት ያስረዳል (1ኛ ዮሐ 2፡22-23፥ 4፡2-3)። አሁንም ሌሎች ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅና ከእግዚአብሔር ጋር እኩል የሆነ አምላክ መሆኑን ለማመን ተቸግረው ነበር። እርሱ አነስ ያለ መንፈሳዊ ፍጥረት እንደሆነ አስተምረዋል (1ኛ ዮሐ 2፡22-23፤ 4፡15)። ዮሐንስ ኢየሱስ ፍጹም አምላክና ከዚህም የተነሣ በአካል ከእግዚአብሔር አብ ጋር እኩል እንደሆነ ያስረዳል።

ለ) ስለ ኃጢአት የተሰጠ የተሳሳተ ትምህርት፡- ከኖስቲኮች አንደኛው ቡድን አስፈላጊው ነገር የሰው መንፈስ ብቻ እንደሆነ ያስተምር ነበር። ለእነዚህ ቡድኖች የሰው ሥጋ ክፉ ነበር። ሥጋ ሟች ስለሆነ በሥጋ ላይ የተፈጸመ ነገር የሰውን መንፈስ አይነካም ሊሉ ያስተምራሉ። በመሆኑም፥ ክርስቲያኖች የፈለጉትን ኃጢአት ሊሠሩና በራሳቸው ላይ ጉዳት እንደ ፈጸሙ ሳይቆጥሩ ሊኖሩ ይችሉ ነበር። ዮሐንስ ለዚህ አመለካከት በሰጠው ምላሽ፥ በእምነት ከእግዚአብሔር የተወለዱ አማኞች ከተለመደ የኃጢአት አኗኗር ወጥተው የቅድስናን ሕይወት እንደሚመሩ ያስገነዝባል (1ኛ ዮሐ 1፡5-7፥ 3፡8-10)። ሌሎች ደግሞ ክርስቲያኖች ከስደት በኋላ ሙሉ በሙሉ ከኃጢአት ሊነጹ እንደሚችሉ ያስተምሩ ነበር። ዮሐንስ ለዚህ በሰጠው ምላሽ፥ የእግዚአብሔር ልጆች ብንሆንም እንኳን የኃጢአት ባህሪ ስላለብን በኃጢአት ልንወድቅ እንደምንችል ይናገራል (1ኛ ዮሐ 1፡8-10)። ክርስቶስ ቀድሞውኑ የኃጢአትን ዋጋ በመስቀል ላይ ስለከፈለ፥ ልናደርግ የሚገባን ነገር ቢኖር ኃጢአታችንን ተናዘን ወደ እግዚአብሔር ኅብረት መመለስ ነው።

ለዚህ የመናፍቅነት አስተሳሰብ ዮሐንስ በሰጠው ምላሽ፥ የእውነተኛ አማኛች ሦስት ባሕርያት እንዳሉና እነዚህም እነርሱን ከሐሰተኛ አማኞች ለይተን እንድናውቃቸው እንደሚያስችሉ ይናገራሉ። እነዚህም፥ ሀ) የተቀደሰ አኗኗር፥ ለ) ለሰዎችና ለእግዚአብሔር ያለ ፍቅርና ሐ) ትክክለኛ እምነታቸው፥ ይህ እምነት በተለይ ኢየሱስ ክርስቶስን የሚመለከት ነው።

ዮሐንስ ከእግዚአብሔር እና ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር የሚደረግ ኅብረት በእውነት ላይ የተመሠረተ መሆኑን ያስረዳል። ክርስትና በባህሪው ሁሉን አቀፍ ባለመሆኑ፥ በዓለም ላይ ያሉት ሰዎች በሁለት ዐበይት ክፍሎች ይከፈላሉ። ስለ እግዚአብሔርና ኢየሱስ ክርስቶስ እውነቱን የሚያውቁ፥ ከእግዚአብሔር የተወለዱና እግዚአብሔርን በመታዘዝ የሚመላለሱና የቅድስና፥ የጽድቅና የፍቅር ባህሪውን የሚያንጸባርቁ ሰዎች ብቻ ድነትን (ደኅንነትን) ያገኛሉ። የእግዚአብሔር ልጆች ያልሆኑት ግን ድነትን አያገኙም። ይህ በዛሬው ዓለም ውስጥ ወሳኝ እውነት ነው። ሰዎች ሀ) ከሌላ ሃይማኖት ተከታዮች፥ ለ) በክርስትና ሃይማኖት ውስጥ ከሚገኙ ኑፋቄዎችና ሐ) መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን በአእምሮአቸው እያመኑ ተግባራዊ ከሚያደርጉት ሰዎች ጋር በመቻቻል አብረው ለመኖር ይፈልጋሉ። እንዲህ ዓይነቶቹ ሰዎች፥ «እንዴት አልዳኑም፥ ማለት ይቻላል? ይሄ ሃይማኖታዊ አምባገነናዊነት አይመስልምን? ይህ ሃይማኖታዊ ትዕቢት አይደለምን?» ሲሉ ይጠይቃሉ። ዮሐንስና ሌሎችም የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች ክርስትና የተለየ ሃይማኖት መሆኑን ይናገራሉ። እኛ የእግዚአብሔር እውነት አለን ሌሎች ሃይማኖቶች ግን ሰውን የሚያድን እውነት የላቸውም። ሰውን የሚያድነው ሃይማኖታዊ ቅንአት ሳይሆን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን ነው። በሌላ ሃይማኖት ተከታዮች ላይ የትዕቢት ስሜት ሊሰማን አይገባም። ሰዎች ወደ ክርስቶስ እንዲመጡ ልናስገድዳቸውም አይገባም። ነገር ግን ክርስቶስ መንገድ፥ እውነትና ሕይወት መሆኑን በእርጋታ ልናብራራላቸው ይገባል ( ዮሐ. 14፡6)። ጴጥሮስ እንዳለው «እንድንበት ዘንድ የሚገባ፥ ለሰዎች፥ ከሰማይ በታች የተሰጠ ሌላ ስም የለም።» (የሐዋ. 4፡12)። እኛ ትክክል የሆነውና እነርሱ የተሳሳቱት ታላላቆች ወይም ከእነርሱ የተሻለ እውቀት ያለን ሰዎች በመሆናችን አይደለም። እግዚአብሔር ብቸኛውን የድነት (ደኅንነት) መንገድ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጠቅሶታል። እኛም በክርስቶስ ኢየሱስ በማመናችን ይህንኑ እውነት እናውጃለን።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የሌሎችን ሃይማኖቶች ተከታዮች ወይም ክርስቲያናዊ ኑፋቂዎች ምንም እንዳይደሉ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት እንደሚያገኙ አድርገህ እንድታስብ የሚገፋፉህ ጫናዎች የደረሱት እንዴት ነው? ለ) ይህ ትምህርት አደገኛ የሚሆነው ለምንድን ነው? ሐ) ለክርቲያኖች እውነተኛውንና እውነት ያልሆነውን ትምህርት ለይቶ ማወቅ፥ እንዲሁም ከሌሎች ሃይማኖቶችና የኑፋቄ ተከታዮች ጋር ግንኙነት የሚያደርጉበትን ሁኔታ ማወቅ ጠቃሚ የሚሆነው ለምንድ ነው?

ስድስተኛ ዓላማ፡ ዮሐንስ ከሐሰተኛ ትምህርቶች በተጨማሪ የውሸት እውነትንም ይቃወማል። ዮሐንስ የአንድ ሰው እምነት እውነተኛነት በቀዳሚነት የሚታወቀው ግለሰቡ በሚያውቀው እውነት ሳይሆን፥ ሕይወቱን በሚመራበት መንገድ መሆኑን ያሳያል። እግዚአብሔር ቅዱስ (ብርሃን) እንደሆነ እናውቃለን። ይህ እውነት ግን በቅድስና (በብርሃን) በመመላለሳችንና የእግዚአብሔርን ትእዛዛት በመቀበላችን በይፋ ሊታወቅ ይገባል። እግዚአብሔር ጻድቅ እንደሆነ እናውቃለን። ነገር ግን ይህ እውቀታችን ጠቃሚ የሚሆነው በጽድቅ ወደምንኖርበት ደረጃ ካደረሰን ብቻ ነው። እግዚአብሔር ፍቅር እንደሆነ እናውቃለን። ነገር ግን ለእግዚአብሔር ያለን ፍቅር የሚፈተነው እርስ በርሳችን በመዋደዳችን ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ለአማኞች በ1ኛ ዮሐንስ ውስጥ የቀረቡትን እውነቶች ማወቅ አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Exit mobile version