Site icon

2ኛ ዮሐ 1:1-13

፩. ሰላምታ (2ኛ ዮሐ 1-3)

ሐዋርያው ዮሐንስ ለረጅም ዘመን የኖረ አገልጋይ ነው። ከክርስቶስ ጋር በመኖር እውነትን ሲያስተምር ሰምቷል (ዮሐ. 8፡31-32፤ 45)። ቤተ ክርስቲያን እያደገች ከመጀመሪያው ትውልድ አማኞች ወደ ሁለተኛ ትውልድ አማኞች (የአማኞች ልጆች) ስትሄድ ተመልክቷል። የክርስትናን ዕድገት ሲመለከት ንጹሕ እውነተኛ ወንጌል በሁለት መንገዶች መበከሉ አሳሰበው። ወንጌሉ የተሳሳቱ ትምህርቶች በቤተ ክርስቲያን ላይ በሚያሳድሩት ተጽዕኖ ምክንያት እየተበከለ ነበር። ወንጌሉ ከአማኞች ጋር በማይዛመድበት ጊዜም እንዲሁ ሲበከል ተመልክቷል። ክርስቲያኖች በተለይም እርስ በርሳቸው ተዋደዱ የሚለውን የክርስቶስን ትእዛዝ ይተላለፉ ነበር።

ዮሐንስ በመግቢያው ላይ ሁሉም ክርስቲያናዊ ኅብረት የተመሠረተበትን የወንጌል እውነት መሠረት ይጠቅሳል። ዮሐንስ እመቤቲቱን እና ልጆቿን የወደደው ሁሉም በወንጌሉ እውነት በማመናቸው ነው። የወንጌል እውነት በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዓለማቀፋዊቷ ቤተ ክርስቲያን ጭምር ክርስቲያኖችን የሚያስተሳስር ጥላ ሆኖ ያገለግል የነበረ ነው። ዮሐንስ ትኩረት የሰጠው ሁላችንም በስም ወይም የአንድ ታላቅ ቤተ እምነት ክፍሎች በመሆናችን ላይ አይደለም። ነገር ግን የሁሉም አማኞች አንድነት በማይለወጥ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ላይ በሚጣል ንጹሕ እምነት ላይ የተመሠረተ መሆኑን ተመለከተ።

፪. እውነትን የሚያውቁ ሰዎች በፍቅርና በታዛዥነት ይመላለሳሉ (2ኛ ዮሐ. 4-7)

ዮሐንስ ይህንን መልእክት የጻፈው ከእውነት ተቅበዝብዘው የጠፉትን ሰዎች ለማስጠንቀቅ አልነበረም። ነገር ግን ካልተጠነቀቁ ሊያጋጥማቸው ስለሚችል አደጋ ያስጠነቅቃቸዋል። ስለሆነም ዮሐንስ ዋና ትምህርቱን የጀመረው አማኞቹ በእምነታቸውና በተግባራቸው በእውነት የሚመላለሱ በመሆናቸው በማመስገን ነው። ነገር ግን ወሳኝ የሆኑትን ነገሮች እንዳይዘነጉ ለማገዝ በክርስቶስ ማመኑ ብቻ በቂ እንዳልሆነ ያስገነዝባቸዋል። በእውነት መኖር ማለት በተለይ እርስ በርሳቸው በመዋደድ ክርስቶስን መታዘዝ ማለት ነው። ዮሐንስ ለሐሰተኛ ትምህርት ትልቁ መከላከያ እርስ በርሳቸው የሚዋደዱ አማኞች የሚገኙበት ኅብረት መሆኑን ያውቃል። ሰይጣን ሰዎች በቀላሉ ወደ ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት እንዲመለከቱና ሐሰተኛ አስተምህሮ እንዲከተሉ የሚያደርገው ጸብ ወይም የፍቅር ጉድለት በሚኖርበት ጊዜ ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የቤተ ክርስቲያንህ መለያ ፍቅር ነውን? አማኞች ለጎብኚዎች ፍቅርን የሚያሳዩት እንዴት ነው? አማኞች ለተለያዩ የጎሳ ቡድኖች ወይም ማኅበራዊ ቡድኖች ፍቅርን የሚያሳዩት እንዴት ነው? ለጎረቤቶቻቸው ፍቅርን የሚያሳዩት እንዴት ነው? ለ) ቤተ ክርስቲያንህ በፍቅሯ ተለይታ ትታወቅ ዘንድ እግዚአብሔር ምን እንድታደርግ የሚፈልግ ይመስልሃል?

፫. ክርስቲያናዊ ኅብረት የሚያቅፈው እውነትን የሚያምኑትን ብቻ ነው (2ኛ ዮሐ 8-13)

ምርመራ ያልታከለበትን ፍቅር ሰይጣን ለክፉ ዓላማ ሊጠቀምበት ይችላል። በ2ኛ ዮሐንስ መልእክት ውስጥ የተጠቀሰችው ቤተ ክርስቲያን የምትጋፈጠው አደጋ ይህንኑ ይመስላል። ክርስቲያኖች በፍቅር ላይ በማተኮራቸው ከሐሰት ራሳቸውን መጠበቅ እንደነበረባቸው ዘነጉ። ስለሆነም ዮሐንስ ከቤተ ክርስቲያን ቤተ ክርስቲያን በሚቅበዘበዙ በርካታ አሳቶች እንዳይታለሉ ያስጠነቅቃቸዋል። በዮሐንስ ዘመን፥ እነዚህ ሐሰተኛ አስተማሪዎች ክርስቶስ በሥጋ እንዳልመጣ በመግለጽ የተሳሳተ መረጃ ያሰራጩ ነበር። የውሸት አባት የሆነው ሰይጣን ሰዎች ውሸትን እንዲያምኑ ስለሚፈልግ፥ እነዚህ ሐሰተኛ አስተማሪዎች፥ «የክርስቶስ ተቃዋሚዎች» ተብለዋል። ክርስቶስ ሰው የሆነ እና ለኃጢአታቸው የሞተ መለኮታዊ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ካመኑ በኋላ ይህን እምነት እውነተኛ ባልሆነ ነገር በመለወጡ ያገኙትን በረከት ሁሉ ያሳጣቸው ነበር። ከእንግዲህ ከክርስቶስ ወይም ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት አይኖራቸውም ነበር። ምክንያቱም እምነታቸው በእውነት ላይ አልተመሠረተምና። የሚያድነን እምነት ሳይሆን በትክክለኛ እውነት ማመናችን ነው። ይህም ማለት ክርስቶስ ብቸኛው የድነት (ደኅንነት) መንገድና መለኮታዊ እንዲሁም ሰብአዊ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ማመን ይኖርባቸዋል ማለት ነው።

አማኞች፥ ክርስቲያኖች ነን እያሉ እውነትን የማያስተምሩ ሰዎችን ምን ማድረግ ይገባቸው ነበር? ዮሐንስ ከእነዚህ ሰዎች ጋር ምንም ዓይነት ኅብረት እንዳያደርጉ ያስጠነቅቃቸዋል። አማኞች እነዚህን ሰዎች ወደ ቤታቸው መጋበዝ፥ አብሮ መመገብ ወይም ኅብረት ማድረግ አያስፈልጋቸውም ነበር። ከእነርሱ ጋር ኅብረት ማድረጉ በተዘዋዋሪ መንገድ አገልግሎታቸውን ስለሚደግፍ፥ አማኞች የጠላትን ውሸት በማሰራጨቱ በኩል እገዛ ያደርጋሉ።

የውይይት ጥያቄ፡– ይህ ትምህርት ከዛሬው ዘመን አብያተ ክርስቲያኖቻችን ጋር የሚዛመደው እንዴት ነው? ይህ ትእዛዝ ከ«ኢየሱስ ብቻ» ቤተ ክርስቲያን አባላት ጋር የሚዛመደው እንዴት ነው? ከጆሆቫ ምስክሮች ጋርስ? ይህ በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ሊሰጥ የሚገባው ጠቃሚ ትምህርት ይመስልሃል? ለምን?

ከእኛ ጋር የሚመሳሰል እምነት ያላቸውን ሰዎች አለመታገሱ አስቸጋሪ ነው። የ«ኢየሱስ ብቻ» እማኞች ክርስቶስን ይወዳሉ፥ ነገር ግን የሥላሴን መሠረታዊ ትምህርቶች ይክዳሉ። የጆሆቫ ምስክሮች ክርስቶስ ፍጹም አምላክ መሆኑን ይክዳሉ። ሌሎች ብዙ ቡድኖች ስለ ክርስትና መሠረታዊ እምነቶች የተሳሳቱ መረዳቶች አሏቸው። ከእነዚህ ሰዎች ጋር ኅብረት ልናደርግ ይገባል? ወደ «ኢየሱስ ብቻ» አብያተ ክርስቲያናት መሄድ አለብን? የእነርሱ መጋቢዎች ከእኛ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ እንዲያገለግሉ ልንጋብዛቸው ይገባል? ዮሐንስ በዚህ አጭር መልእክት ውስጥ ጠንካራ ማስጠንቀቂያዎችን ይሰጠናል። ተኩላዎች በበጎች መካከል እንዲሰማሩ መፍቀዱ አደገኛ ነው። ሐሰተኛ ትምህርትን ከሚያስፋፉ ሰዎች ጋር መተባበር አደገኛ ነው። ክርስቲያናዊ ፍቅርና ትዕግሥት እውነትን እንድንጥል ወይም እምነቶችን ሚዛናዊ ባልሆነ መንገድ እንድንጠቀም እንዳያደርገን መጠንቀቅ ይኖርብናል። ሚዛናዊ ካልሆኑት የእምነት ገጽታዎች መካከል በልሳን መናገር፥ ፈውስ፥ በመንፈስ መገንደስ፥ እንደ እንስሳት መጮህ የመሳሰሉት ሊጠቀሱ ይችላሉ።

ዮሐንስ መልእክቱን የሚጽፈው በትንሽ የፓፒረስ ወረቀት ላይ መሆኑ፥ በቅርቡ እንደሚጎበኛቸውና ነገሮችን የበለጠ በዝርዝር እንደሚገልጽላቸው በመናገር ደብዳቤውን ይደመድማል። የተመረጠችው የእኅትሽ ልጆች ሰላምታ ያቀርቡልሻል በማለት መልእክቱን ይፈጽማል። ምንም እንኳን ይህ በቁጥር 1 ላይ የተጠቀሰችውን ሴት የሥጋ እኅት የሚያመላከት ሊሆን ቢችልም፣  በአመዛኙ ግን ዮሐንስ መልእክቱን በሚጽፍበት ጊዜ የሚያገለግለውን ማኅበረ ምእመናን የሚያሳይ ይመስላል።

የውይይት ጥያቄ፡- ከ2ኛ ዮሐንስ የተረዳሃቸውን ዋና ዋና ትምህርቶች ዘርዝር።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Exit mobile version