Site icon

የትንቢተ ዳንኤል ሙግቢያ

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ለክርስቲያኖች እግዚአብሔር በሕይወታቸው ውስጥ ማንኛውንም ነገር እንደሚቆጣጠር ማወቃቸው አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው? ለ) በሕይወትህ ውስጥ በተፈጸመ ድርጊት እግዚአብሔር ተቆጣጣሪ መሆኑን የረሳህበትን ሁኔታ ግለጥ። ውጤቱ ምን ነበር? መ) በችግር ውስጥ ሆነህ በእግዚአብሔር ሉዓላዊነት የተጽናናህበትን ሁኔታ ግለጽ።

ለክርስቲያን እግዚአብሔር በነገሮች ሁሉ ላይ ሉዓላዊ መሆኑን ከማወቅ ጋር የሚስተካከሉ እውነቶች ቢኖሩ ከቊጥር የማይገቡ ናቸው። እግዚአብሔር የበላይ ተቁጣጣሪ ነው። የዓለምን ሕዝቦች በሙሉና በዓለም ላይ የሚፈጽሙትን ነገሮች ሁሉ ይቆጣጠራል። በልጆቹ ሕይወት ውስጥ የሚፈጸሙትን ነገሮች ሁሉ ይቆጣጠራል። ይህንን እውነት በሚገባ መረዳትና ማመን እንደ አንድ ትልቅ ዛፍ ሥር ጠንካራ መሠረት ይሆናል። የስደት ወይም የችግርና የመከራ ማዕበል ወደ ሕይወታችን በሚመጣበት ጊዜ ፍቅር በሆነው አምላካችን ቁጥጥር ሥር መሆኑን በጥብቅ ካመንን፥ እምነታችንን እንዳይጠፋ ማድረግ እንችላለን። ነገሮች በመጥፎ ሁኔታ ሲከናወኑ ብዙ ጊዜ ማጕረምረምና ማጕተምተም የምንጀምረው ይህንን እውነት ስንዘነጋ ነው። ይህ በተለይ እውነት የሚሆነው ክርስቲያኖች በስደት ጊዜ እምነታቸውን ሲክዱ ነው። እግዚአብሔር ነገሮችን ሁሉ እንደሚቆጣጠርና ቢጸኑ ከእግዚአብሔር ዘንድ ክብርን እንደሚያገኙ ረስተዋል ማለት ነው።

ትንቢተ ዳንኤል ስለ እግዚአብሔር ሉዓላዊ ቁጥጥር ያስተምራል። በትንቢተ ዳንኤል እግዚአብሔር ወደ ልጆቹ ሕይወት የመጣውን እያንዳንዱን ሁኔታ እንዴት እንደተቈጣጠረ እናያለን። እንዲሁም እግዚአብሔር ኃያላን የሆኑትን የጥንት መንግሥታትና ነገሥታት እርሱ የሚፈቅደውን ነገር ብቻ እንዲያደርጉ እንዴት እንደተቈጣጠራቸው እናያለን።

ብዙ ክርስቲያኖች በትንቢተ ዳንኤል ውስጥ የሚገኙትን ታሪኮች የሚያውቁና ከእርሱ ውስጥ አጽናኝና አበረታች የሆኑ በርካታ ትምህርቶችን የሚያወጡ ቢሆኑም፥ በመጽሐፉ ያሉትን ትንቢቶች ለመረዳት ግን ይቸገራሉ። ይሁን እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን ስለ መረዳት ጉዳይ ስንመለከት እግዚአብሔር ለዘመናት ሁሉ ያለውን ዕቅድና በመጨረሻው ዘመን ምን እንደሚሆን ለመረዳት የትንቢተ ዳንኤልን ያህል እጅግ ጠቃሚና አስፈላጊ የሆነ መጽሐፍ የለም። አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ተገቢ የሆነ ግንዛቤ ለማግኘት፥ መሠረቱ ትንቢተ ዳንኤል እንደሆነ ይናገራሉ። ስለዚህ ትንቢተ ዳንኤልን «የትንቢት ቍልፍ» ብለው ይጠሩታል። 

በሌላ በኩል ደግሞ በማያምኑ ምሁራን ዘንድ ከማንኛውም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ይልቅ ተቃውሞ የገጠመው መጽሐፍ ትንቢተ ዳንኤል ነው። ይህንን መጽሐፍ የጻፈው ዳንኤል መሆኑን አይቀበሉም። እንዲሁም ትንቢተ ዳንኤል በርካታ ስሕተቶች አሉበት በማለት ይቃወሙታል። ሰይጣን ክርስቲያኖችን የእግዚአብሔርን ቃል ትክክለኛነት እንዲጠራጠሩ ሊያደርግ ከቻለ እምነታቸውንም ፈጽሞ ሊያጠፋ ተቃርቧል ማለት ነው። 

የትንቢተ ዳንኤል ጸሐፊ

ትንቢተ ዳንኤል የተሠየመው ነቢይና የፖለቲካ ሰው በነበረው የመጽሐፉ ዋና ገጸ-ባሕርይ ስም ነው። መጽሐፉ የተጻፈው በ6ኛው ምዕተ ዓመት ከክርስቶስ ልደት በፊት ይኖር የነበረው በዳንኤል ስለመሆኑ ከመጽሐፉ በግልጽ ይታያል። በትንቢተ ዳንኤል ውስጥ ከምንመለከተው የታሪክ መረጃ፥ ዳንኤል ወደ ምርኮ የተወሰደው በ605 ዓ.ዓ. እንደሆነና በባቢሎን ምድር ከናቡከደነፆር ጀምሮ እስከ ቂሮስ ዘመን (536 ዓ.ዓ. ገደማ) ድረስ እንደኖረ እንገነዘባለን።

ይሁን እንጂ ክርስቲያን ያልሆኑ ብዙ ምሁራን መጽሐፉን የጻፈው ዳንኤል አይደለም ይላሉ። ይልቁንም ከ164 ዓ.ዓ. በኋላ ዳንኤል ነኝ ያለ አንድ ያልታወቀ አይሁዳዊ የትንቢተ ዳንኤል 11 ድርጊቶች ከተፈጸሙ በኋላ ጽፎታል ብለው ያምናሉ። ክርስቲያን ያልሆኑ ሰዎች ይህን የሚሉት ለምንድን ነው?

1. በዳንኤል 11 የተነገሩ ትንቢቶች ከመፈጸማቸው ከ400 ዓመታት በፊት የተነገሩ ናቸው ብሎ ለማመን በማያስችል ሁኔታ በትክክል የተዘገቡ ናቸው። የነገሥታቱ ስም ባይጠቀስም እንኳ ታሪካዊ ድርጊቶች ከ164 ዓ.ዓ. በፊት ከተፈጸሙት ድርጊቶች ጋር ፍጹም አንድ ዓይነት የነበሩ ናቸው። ስለዚህ ሐያስያን መጽሐፉ የተጻፈው ድርጊቶች ከተፈጸሙ በኋላ ነው ይላሉ። 

2. ትንቢተ ዳንኤል «አፓካሊፕቲክ» ተብሎ ከሚጠራው የሥነ ጽሑፍ ዓይነት የሚመደብ ነው። አፓካሊፕቲክ ሥነ-ጽሑፎች የተጻፉት ከ200 ዓ.ዓ. እስከ 200 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ነበር። ትንቢተ ዳንኤል ከእነዚህ መጻሕፍት ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ በመግለጽ፥ ጸሐፊው በአይሁድ ታሪክ ውስጥ በጣም የታወቀውን ሰው ስም በመጠቀም ለመጽሐፉ የበለጠ ዋጋ ሊያሰጠው ችሎአል ይላሉ። ጸሐፊው የጻፈው ድርጊቱ ከተፈጸመ በኋላ ቢሆንም እንኳ መጽሐፉ ድርጊቱ ከመፈጸሙ መቶ ዓመታት አስቀድሞ እንደተጻፈ ተደርጎ በመቅረቡ ከአፓሊፕቲክ መጻሕፍት ጋር እንደሚመሳሰል ይናገራሉ። 

3. ትንቢተ ዳንኤል ሊከሠቱ በማይችሉ ስሜታዊ ታሪኮች የተሞላ ነው በማለት፥ ቅዱሳት መጻሕፍትን የሚያቃልሉ ሐያስያን፡- በእቶን እሳት ውስጥ የተጣሉት ሦስት ሰዎች፥ የዳንኤል በአንበሳ ጉድጓድ ውስጥ መጣልና በግድግዳ ላይ የታየው ጽሑፍ የመሳሰሉ ታሪኮች ልብ ወለድ ናቸው ይላሉ። 

4. ትንቢተ ዳንኤል በታሪካዊ ስሕተቶች ወይም ሊታመኑ በማይችሉና ማረጋገጫ በሌላቸው እውነቶች የተሞላ መጽሐፍ ነው ይላሉ። ለምሳሌ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ ባሉ የታሪክ መጻሕፍት ውስጥ የሜዶኑ ዳርዮስ (ምዕራፍ 6፤ 9፤ 11) ወይም የናቡከደነፆር ዕብደት ታሪክ አይገኝም ይላሉ። 

እንዲህ ያሉ ምሁራን ትንቢተ ዳንኤልን የጻፈው ዳንኤል ስለ መሆኑ ጥያቄ የሚያነሡት ለምንድን ነው? መሠረታዊው ምክንያት እግዚአብሔር በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ በመግባት ተአምራትን ሊያደርግ እንደሚችል አለማመናቸው ነው። እግዚአብሔር ሕዝቡን ከእቶን እሳት ሊያድን፥ በግድግዳ ላይ ጽሑፍ ሊጽፍ መቻሉን ወይም የአናብስትን አፍ መዝጋት መቻሉን ለማመን ፈቃደኞች አይደሉም። እንዲሁም እግዚአብሔር አንድን ድርጊት ከመፈጸሙ ከብዙ መቶ ዓመታት አስቀድሞ እንኳ ለሰው ሊገልጥ እንደሚችል አያምኑም። ስለዚህ በእግዚአብሔር ላለማመንና ሕይወታቸው እንዲለወጥ ላለማድረግ እነዚህን መከላከያዎች ለማቅረብ ተገደዋል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የእግዚአብሔርን ቃል ትክክለኛነት መጠራጠር ለክርስቲያን አደገኛ የሚሆነው ለምንድን ነው? ለ) የእግዚአብሔር ቃል የማይታመን ከሆነ፥ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የምናምናቸውና አጠራጣሪ ሆነው ሊቀርቡ የሚችሉ አንዳንድ ጠቃሚ ነገሮችን ዘርዝር፡፡ 

መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑንና አንዳችም ስሕተት እንደሌለበት የሚያምኑ ክርስቲያኖች ግን ትንቢተ ዳንኤልን የጻፈው ዳንኤል እንደሆነ ያምናሉ። እግዚአብሔር ተአምራትን እንደሚያደርግና የወደፊቱን ሁኔታ ከመፈጸሙ በፊት ለመግለጥ እንደሚችል ለማመን ምንም ችግር የለባቸውም። ክርስቲያን ምሁራን ከላይ የዘረዘርናቸውን መከላከያዎች ለሚያቀርቡ ክርስቲያን ላልሆኑ ምሁራን የሚከተሉትን መልሶች ይሰጣሉ፡

1. ትንቢተ ዳንኤል ከአፓካሊፕቲክ የሥነ ጽሑፍ ዓይነት ጋር ተመሳሳይነት ቢኖረውም፥ የተለየ መሆኑ ግልጽ ነው። 

2. ትንቢተ ዳንኤል በ164 ዓ.ዓ. ተጽፎ፥ ከጥቂት ዓመታት በኋላ በስፋት ሊሠራጭና በአይሁድ ዘንድ የእግዚአብሔር ቃል ተደርጎ ሊታመን አይችልም። በ200 ዓ.ዓ. ገደማ በተተረጐመው ሴፕቱዋጀንት ተብሎ በሚጠራው የግሪክ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጒምና (ከ200-100 ዓ.ዓ. ባሉት ጊዜያት የተጻፉትና የሙት ባሕር የቅዱሳት መጻሕፍት ጥቅልል የሚባሉት) የጥንት ቅጂዎች ውስጥ መገኘቱ በእነዚህ ጊዜያት አይሁድ ትንቢተ ዳንኤልን የእግዚአብሔር ቃል ክፍል አድርገው መቀበላቸውን የሚያሳይ ነው። አይሁድ አንድን መጽሐፍ የእግዚአብሔር ቃል ክፍል አድርገው ከመቀበላቸው በፊት፥ በመጽሐፉ ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንድ ትንቢቶች እስኪፈጸሙ ይጠብቁ ስለነበር፥ ሁኔታው ረጅም ጊዜ የሚወስድ ሂደት ነበር። ስለዚህ ትንቢተ ዳንኤል የተጻፈው ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት መሆን አለበት። አይሁድ ይኖሩ ከነበሩበት ዘመን ጋር እጅግ ተቀራራቢ በሆነ ጊዜ የተጻፈን ነገር የቅዱስ መጽሐፋቸው ክፍል አድርገው አይቀበሉም ነበር። 

3. በጥንት ታሪክ ውስጥ የማይታወቅ ብዙ ነገር አለ። ስለ ጥንት ታሪክ በቂ መረጃ ስለሌለን ብቻ በትንቢተ ዳንኤል ውስጥ ትክክል እንዳልሆኑ የተገመቱትን ነገሮች የምንጠራጠርበት ምክንያት የለም። 

4. በትንቢተ ዳንኤል ውስጥ የምንመለከተው ዕብራይስጥ በ200 ዓ.ዓ. ከነበረው የዕብራይስጥ ቋንቋ ይዘት በብዙ የሚቀድም ነው። ከክርስቶስ ልደት በፊት በ6ኛው ምእተ ዓመት ይጠቀሙበት ከነበረው የዕብራይስጥ ቋንቋ ጋር የበለጠ የሚመሳሰል ነው። 

5. ኢየሱስ ይህን መጽሐፍ የጻፈው ዳንኤል እንደሆነ ተናግሯል (ማቴዎስ 24፡15)። በእግዚአብሔር ቃል ትክክለኛነት ላይ ዋስትና እንዲኖረን ከፈለግን፥ የተጻፈውን ማመን ያስፈልገናል። መጽሐፍ ቅዱስ የዚህ መጽሐፍ ጸሐፊ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ6ኛው ምዕተ ዓመት ይኖር የነበረ ዳንኤል የተባለ አይሁዳዊ እንደሆነ ይናገራል። መጽሐፉ የተጻፈው ነቢዩ ዳንኤል ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ በ530 ዓ.ዓ. ነበር።

ዳንኤል ከይሁዳ ነገድ ነበር፤ ምናልባትም ከዳዊት ንጉሣዊ ቤተሰብ ሐረግ የተወለደ አይሁዳዊ ሳይሆን አይቀርም። የተወለደው እግዚአብሔርን ይፈራ በነበረው በንጉሥ ኢዮስያስ ዘመነ መንግሥት ነበር፡፡ ወላጆቹ እግዚአብሔርን እንዲወድ፥ እንዲፈራና የእግዚአብሔርን ትእዛዛት እንዲከተል ማስተማራቸው ኢዮስያስ አነሣስቶት በነበረው መንፈሳዊ እንቅስቃሴና በኤርምያስ አገልግሎት የመጀመሪያ ዓመታት በሆነው ነገር ሕይወታቸው የተነካ ስለነበረ ነው። ዳንኤል አመጣጡ ከዳዊት ወገን የሆነ ንጉሣዊ ዝርያ ያለው ስለነበር በይሁዳ ውስጥ ከሁሉ የተሻለ ትምህርት እንደተማረ መገመት ይቻላል። ዳንኤል በታናሽነቱ የንጉሥ ኢዮስያስን ሞት፥ የኢዮአኪንን በምርኮ መወሰድና ክፉ የነበሩትን የንጉሥ ኢዮአቄምን ዘመናት ሁኔታዎች በሚመለከት ምስክር ነበር። ንጉሥ ኢዮአኪን ለባቢሎን መገዛት እምቢ ከማለቱ የተነሣ በ605 ዓ.ዓ. ዳንኤል በይሁዳ ከነበሩ ሌሎች ጥቂት የተማሩ ሰዎች ጋር በአንድነት ወደ ባቢሎን በምርኮ ተወሰደ። በፈሪሀ-እግዚአብሔር እንዲያድግ ከረዱት ቤተሰቦቹ ተነጥሎ ጣዖት አምላኪ በሆነው በባቢሎን ሕዝብ መካከል ተገኘ። ማምለክ የሚችልበት ቤተ መቅደስ ስላልነበረ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ለማቅረብ አይችልም ነበር። በዚያ ዳንኤል በሕይወቱ እጅግ አስቸጋሪ የሆነ ምርጫ ለማድረግ ተገደደ። የወላጆቹን አምላክ ማምለኩን ለመቀጠል ወይም የአሕዛብን አማልክት ለማምለክ ምርጫ ማድረግ ነበረበት። እግዚአብሔርን ማምለክና መታዘዝ ሞትን የሚያስከትል ቢሆንም እንኳ ዳንኤል ይህንን መረጠ። ስለዚህ እግዚአብሔር አከበረው። ዳንኤል ከብሉይ ኪዳን ታላላቅ ነቢያት አንዱ ሆነ። እንዲሁም በመጀመሪያ በባቢሎን፥ በኋላ ደግሞ በሜዶንና በፋርስ መንግሥት ውስጥ የፖለቲካ ሰዎች ከነበሩት ከፍተኛ ባለሥልጣናት አንዱ ሆነ። ዳንኤል በናቡከደነፆር መንግሥት ውስጥ ሁለተኛ ሰው ነበር (ዳንኤል 2፡48)። በብልጣሶር መንግሥት ውስጥ ሦስተኛ፥ በዳርዮስ መንግሥት ውስጥ ደግሞ ሁለተኛ ሰው ነበር (ዳንኤል 6፡1-2)።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የዳንኤልን ምርጫ እጅግ ከባድና አስቸጋሪ ያደረገው ነገር ምን ነበር? ለ) ዛሬም ከዳንኤል ጋር ተመሳሳይ የሆነ ምርጫ እንድናደርግ የምንገደደው እንዴት ነው? ሐ) የዚህ ዓይነት ምርጥ እንዴት እንዳደረግህ ግለጽ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

https://forms.gle/bhAi3CdAf7q2PC2eA
Exit mobile version