Site icon

ዳንኤል 1-6

የውይይት ጥያቄ፥ ምሳሌ 22፡6ና መክብብ 12፡1 አንብብ። ሀ) እግዚአብሔር ልጆቻቸውን በጌታ መንገድ ለሚያሳድጉ ወላጆች የገባው የተስፋ ቃል ምንድን ነው? ለ) ሰሎሞን እግዚአብሔርን ማክበር አለብን ያለው መቼ ነው?

በወጣትነት ዘመናችን የምንማረው ትምህርት በቀሪው የሕይወት ዘመናችን ምን ዓይነት ሰዎች እንደምንሆን ተጽዕኖ ከሚያሳድሩብን ነገሮች መካከል ከፍተኛው ነው። እንዲሁም በወጣትነት ዘመናችን የምንወስናቸው ውሳኔዎች በቀሪው የሕይወት ዘመናችን በምናደርጋቸው ነገሮች ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ናቸው። ወላጆች ወጣት ልጆቻቸውን እግዚአብሔርን ስለ መከተል በጥንቃቄ ማስተማር የሚያስፈልጋቸው በዚህ ምክንያት ነው። የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ደግሞ ስለ እግዚአብሔር መንገድና በሕይወታቸው ትክክለኛ ውሳኔ እንዴት እንደሚደርሱ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ላሉ ልጆቻቸው ማስተማራቸው አስፈላጊ የሚሆነው በዚህ ምክንያት ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ወላጆች ልጆቻቸውን በትክክል እንዲያስተምሩ የቤተ ክርስቲያንህ መሪዎች ማበረታቻ የሚሰጡባቸው መንገዶች ምንድን ናቸው? ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ይህን በተሻለ ሁኔታ ሊያከናውኑ የሚችሉባቸው መንገዶች ምንድን ናቸው። ሐ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች፥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚገኙትን ልጆች በወጣትነት ዘመናቸው እግዚአብሔርን እንዲያውቁና እንዲከተሉ ለማስተማር ሊከተሏቸው የሚገባ መንገዶች ምንድን ናቸው? መ) ይህንን በተሻለ ሁኔታ ስናወን የሚችሉት እንዴት ነው?

ዳንኤል በምርኮ በተወሰደ ጊዜ ገና ወጣት ነበር። ወደ ምርኮ ሲወሰድ፥ ከወላጆቹና የሃይማኖት መሪዎች ያስተምሩት ከነበረው ትምህርት ተለየ። ይህም ሆኖ ለእግዚአብሔር ለመታዘዝና በባዕድ ምድር የእግዚአብሔር መሣሪያ ለመሆን ችሎአል። ወላጆቹ ዳንኤልን ስለ እግዚአብሔርና ስለ ትእዛቱ ከልጅነቱ ጀምሮ በሚገባ ሳያስተምሩት አልቀሩም። ዳንኤል ከወላጆቹ ከተለየ በኋላ እንኳ ያስተማሩት ትምህርት በሕይወቱ ላይ አዎንታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን ቀጠለ። ምርጫ እንዲያደርግ በተገደደ ጊዜ እግዚአብሔር የፈለገውን ነገር አወቀ ለመታዘዝም ድፍረት አገኘ። ዳንኤል ራሱን ላለማርከስ የወሰነው ውሳኔ እግዚአብሔር ሹመትን በመስጠት እንዲያከብረው አደረገው። ዳንኤል በወጣትነት ዘመኑ እግዚአብሔርን ስላከበረ በሸመገለም ጊዜ እግዚአብሔርን አልተወም።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ዳንኤል 1-6 አንብብ። ለ) ዳንኤል በምዕራፍ 1 እግዚአብሔር ያከበረውን ምን ምርጫ አደረገ? ሐ) ዳንኤል 2 ስለሚገኘው የተቀረጸ ምስል ግለጽ። ይህ ምስል ምን ሆነ? መ) በዳንኤል የምንመለከታቸው ሦስቱ ወጣት አይሁዳውያን ያደረጉት ምርጫ ምን ነበር? ሠ) በዳንኤል አራት እግዚአብሔር ናቡከደነፆርን ምን አስተማረው? ረ) በዳንኤል 5 እግዚአብሔር ብልጣሶርን እንዴት አዋረደው? ሰ) በዳንኤል 6 ዳንኤል በእግዚአብሔር ላይ ያለውን እምነት እንዴት አሳየ?

1. የትንቢተ ዳንኤል መግቢያ (ዳንኤል 1) 

ባቢሎናውያን አንድ መመሪያ ነበራቸው፤ ይኸውም፡- ከምርኮኞች መካከል ምርጦቹን በመውሰድ በባቢሎናውያን መመሪያዎችና ባህል መሠረት ማሰልጠን ነበር። ምርኮኞቹ ከሠለጠኑ በኋላ በተማረኩበት ምድር የንጉሡ አማካሪዎች ይሆኑ ነበር።

ወደ ምርኮ የተወሰዱ አይሁድ ብዙዎች ቢሆኑም፥ ትንቢተ ዳንኤል በተለይ በአራት ሰዎች ላይ ያተኩራል፤ እነርሱም ዳንኤል፥ አናንያ፥ ሚሳኤልና አዛርያ ነበሩ። መሪያቸው ዳንኤል ነበር። ዳንኤል ወጣት ቢሆንም እንኳ በሚበላው መብል እንዳይረክስ በማሰብ የጌታን ትእዛዝ በመጣስ የመሰለውን ነገር ለመቀበል ፈቃደኛ ሳይሆን ቀረ። ዳንኤል ያንን መብል ለመብላት ፈቃደኛ ሳይሆን የቀረው ምናልባት ምግቡ ለሰዎች ከመቅረቡ በፊት ለአሕዛብ ጣዖት የሚሠዋ ስለነበረ ሊሆን ይችላል። ዳንኤል የእግዚአብሔርን ሕግጋት ለመጠበቅ ሲል ሕይወቱን ለአደጋ አጋለጠ። ስለዚህ እግዚአብሔር ከሌሎች ይልቅ ጤነኛና ብልህ አደረገው። ከ70 ዓመታት ለበለጠ ጊዜ ወደ ቈየበት የመሪነት ሥልጣንም ከፍ አደረገው። 

2. ናቡከደነፆር በሕልም ያየው ታላቅ ምስል (ዳንኤል 2)

እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን ከሚገኙ እጅግ ታላላቅ ሕልሞች አንዱን የአሕዛብ ንጉሥ ለሆነ ሰው መግለጡ የሚያስገርም ነው፡፡ የእግዚአብሔር መንግሥት እስከሚገለጥበት ጊዜ ድረስ የሚኖሩትን ዋና ዋና የአሕዛብ መንግሥታት ሁሉ ያየበትን ሕልም እግዚአብሔር ለናቡከደነፆር አሳየው። እንዲሁም እግዚአብሔር ዳንኤልን ከፍተኛ ሥልጣን በመያዝ በመንግሥት ውስጥ እርሱን እንዲያገለግል በማድረግ ይህንን ሕልም ተጠቀመበት።

የሕልሙን ትርጕም ለመረዳት የሚከተለውን ሠንጠረዥ ተመልከት፡- 

ምስሉ፣ የወርቅ ራስ

መንግሥቱ፣ ባቢሎን

ዘመኑ፣ 626-539 ዓ.ዓ.

ምስሉ፣ የብረት ደረትና ክንዶች

መንግሥቱ፣ ሜዶን እና ፋርስ

ዘመኑ፣ 539-330 ዓ.ዓ.

ምስሉ፣ የናስ ሆድና ጭን

መንግሥቱ፣ ግሪክ

ዘመኑ፣ 330-63 ዓ.ዓ.

ምስሉ፣ የብረት እግር

መንግሥቱ፣ ሮም

ዘመኑ፣ 63 ዓ.ዓ.-400 ዓ.ም.

ምስሉ፣ የከፈል ብረትና የከፊል ሸክላ እግሮች

መንግሥቱ፣ እንደገና የሚታደሰው የሮም መንግሥት

ዘመኑ፣ ወደፊት

ምስሉ፣ ድንጋይ ተራራ

መንግሥቱ፣ ዘላለማዊ የእግዚአብሔር መንግሥት

ዘመኑ፣ ወደፊት

የሚከተሉትን ነገሮች አስተውል፡-

ሀ. የምስሉ ሕልም ከናቡከደነፆር ጀምሮ እስከ አዲስ ኪዳን ዘመን ድረስ ያሉትን የዓለም ታላላቅ መንግሥታት በሙሉ የሚያሳይ ነበር።

ለ. ምሁራን ከፊሉ ሸክላ ከፊሉም ብረት ስለሆነው የምስሉ እግሮች ትርጉም በአሳብ ይለያያሉ። አንዳንዶች ይህ የሮም መንግሥትን የሚያመለክት ስለሆነ ስለ አላፊ ጊዜ የሚናገር ነው ይላሉ። ሌሎች ደግሞ እግዚአብሔር ዘላለማዊ መንግሥቱን ከመመሥረቱ ጥቂት ቀደም ብሎ ስለሚነሣ የወደፊት መንግሥት የሚናገር ነው ይላሉ። የዚህ መንግሥት አነሳሥ ከጥንታዊው የሮም መንግሥት ስለሆነ «እንደገና ያንሰራራው የሮም መንግሥት» በመባል ይጠራል።

ሐ. የምድር መንግሥታት በሙሉ ጊዜያዊ ስለሆኑ በእግዚአብሔር ይደመሰሳሉ። ጸንቶ የሚኖረው የእርሱ ዘላለማዊ መንግሥት ብቻ ነው።

3. የወርቁ ምስልና የእቶኑ እሳት (ዳንኤል 3)

ናቡከደነፆር በምዕራፍ 3 የምናገኘውን የወርቅ ምስል ያሠራ ዘንድ ተጽዕኖ ያሳደረበት በምዕራፍ ሁለት የምናገኘው በሕልሙ ያየው ምስል መሆኑን አናውቅም። ነገር ግን ናቡከደነፆር መንግሥቱን በአንድ ሃይማኖት ሥር ለማዋሐድ ፈለገ። ሰው ሁሉ ያንን የወርቅ ምስል እንዲያመልክ ፈለገ። በዚህ ጊዜ ዳንኤል በባቢሉን ያልነበረ ይመስላል። በመንግሥት ሥራ ምክንያት ርቆ ሳይሄድ አልቀረም። ዳሩ ግን ሲድራቅ፥ ሚሳቅና እብደናጎ የተባሉት ሦስት ወጣቶች ለምስሉ እንዲሰግዱ የሚጠይቅ ወጥመድ ተዘረጋባቸው። ለተቀረጸው ምስል የመስገድ ወይም እግዚአብሔርን በማምለክ ረገድ ታማኛች ሆነው ለእምነታቸው የመሞት ምርጫ ነበራቸው። እነዚህ ሦስት ሰዎች እግዚአብሔር ሊያድናቸው እንደሚችል ቢያምኑም እግዚአብሔር እንደሚያድናቸው አላወቁም። ይሁን እንጂ ሐሰተኞች አማልክትን ከማምለክ ይልቅ ለመሞት ፈቃደኞች ነበሩ (ዳንኤል 3፡17-18)።

ሦስቱ ሰዎች ወደ እቶኑ እሳት ቢጣሉም እግዚአብሔር ግን አዳናቸው። በእቶኑ እሳት ውስጥ የታየው «የአማልክትን ልጅ የሚመስለው። አራተኛው ሰው መልአክ ሊሆን ይችላል። አንዳንዶች ደግሞ በብሉይ ኪዳን ውስጥ ለጊዜው ብቻ ይገለጽ የነበረው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ብለው ያምናሉ።

የውይይት ጥያቄ፡ ሀ) ይህ ታሪክ በዚህ ዘመን የሚገኙ ክርስቲያኖችን በከፍተኛ ስደት ጊዜ እንኳ ለእግዚአብሔር ታማኞች ሆነው እንዲቆዩ የሚያበረታታቸው እንዴት ነው? ለ) ተመሳሳይ የሆኑ ምርጫዎች ቀርበውላቸው በውሳኔያቸው እግዚአብሔር ያከበራቸውን ክርስቲያኖች በምሳሌነት ጥቀስ።

4. ናቡከደነፆር ስለ አንድ ታላቅ ዛፍ ያየው ሕልም (ዳንኤል 4)

ዳንኤል ምዕራፍ 4 የአሕዛብ ንጉሥ በነበረ ሰው የተጻፈ ብቸኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ምዕራፍ ነው። ይኸውም የተጻፈው በናቡከደነፆር ነው። የጻፈውም በታበየ ጊዜ እግዚአብሔር እንዴት እንዳዋረደውና ያለፈበትን ልምድ ለመግለጽ ነበር። ይህ ድርጊት የተፈጸመው የናቡከደነፆር ሥልጣን ከከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሰበት ወቅት ነበር። እጅግ በሚያስደንቅ ሁኔታ የባቢሎንን ከተማ ሠራ። የከተማይቱ ግንቦች ሁለት መኪኖች ጐን ለጐን ሊያስኬዱ የሚችሉ እጅግ ሰፋፊ ነበሩ። በከተማይቱ ለልዕልቲቱ መዝናኛ እንዲሆን የሠራው የአትክልት ስፍራ ከዓለም ሁሉ ከጥንት ዘመን ሰባት አስደናቂ ነገሮች አንዱ ነበር። ይሁን እንጂ የቱንም ያህል ኃያልና ገናና ቢሆንም እግዚአብሔር አዋረደው።

ናክቡከደነፆር በሕልሙ አንድ ታላቅ ዛፍ አየ። ዛፉ እጅግ ከዐደገና ከለመለመ በኋላ ጕቶው ብቻ እስኪቀር ድረስ ተቈረጠ። በኋላም ጒተው እንደገና ዛፍ እስኪሆን ድረስ አደገ። ይህ የሆነበት ምክንያት «ልዑሉ በሰዎች መንግሥት ላይ እንዲሠለጥን፥ ለወደደውም እንዲሰጠው፥ ከሰውም የተዋረደውን እንዲሾምበት ሕያዋን ያውቁ ዘንድ» (ዳንኤል 4፡17) ነበር። ናቡከደነፆር እንዳይታበይ ማስጠንቀቂያ ደርሶት ነበር። ስላደረገው ነገር በተኩራራ ጊዜ ግን የአእምሮ ሕመም ተመታና በገዛ የአትክልት ስፍራው ለሰባት ዓመት እንደ እንሰሳ ኖረ፡፡ እግዚአብሔር መንግሥቱን እንደገና የመለሰለት ራሱን ባዋረደ ጊዜ ብቻ ነበር።

ናቡከደነፆር በእውነት በእግዚአብሔር አምኖ እንደሆነ አናውቅም። የታሪክ መጻሕፍት የሚያሳዩት ጣዖትን ያመልክ እንደነበረ ነው። ዳሩ ግን እግዚአብሔርን በማወቅ እንዳደገና እግዚአብሔር እውነተኛና ከሁሉም አማልክት የላቀ አምላክ እንደሆነ መገንዘቡን እናውቃለን።

መጽሐፍ ቅዱስ መሪዎችን ከፍ ከፍ የሚያደርግና የሚያዋርድ እግዚአብሔር እንደሆነ ያስተምረናል። መሪዎች የሚሆኑት በራሳቸው ፈቃድ አይደለም። ደግሞም መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር የትዕቢትን ኃጢአት እንደሚጠላ ያስተምራል። የሕዝብ፥ የአገር ወይም የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በሚታበዩበት ጊዜ እግዚአብሔር ያዋርዳቸዋል። ብዙ ምድራዊ መሪዎች በሕይወታቸው እግዚአብሔርን የሚያከብሩ ቢሆኑም እንኳ አንድ ቀን ሁሉም ለኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚሰግዱና ጌትነቱን እንደሚመሰክሩ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል (ፊልጵስዩስ 2፡10-11)።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) መሪዎች ሊታበዩና እግዚአብሔር በሰጣቸው ችሎታ ስላደረጉት ነገር ክብሩን ለራሳቸው ሊወስዱ የሚቀልላቸው ለምንድን ነው? ለ) እግዚአብሔር እንደዚህ ዓይነት መሪዎችን ሲያዋርድ ያየኸው እንዴት ነው?

5. ብልጣሶር በግድግዳ ላይ የተጻፈውን ጽሑፍ አየ (ዳንኤል 5) 

የዳንኤል ታሪክ ብዙ ዓመታትን አልፎ ወደ ባቢሎን መንግሥት የመጨረሻ ቀናት ይዘልቃል። በታሪኩ ውስጥ የናቡከደነፆርን ሞትና ከእርሱ በኋላ የነገሡትን ነገሥታት ታሪክ አናገኝም። ምክንያቱም የዳንኤል ፍላጎት ታሪክን መተረክ ሳይሆን የእግዚአብሔርን ታላቅነትና በዓለም ሕቦች ሁሉ ላይ ያለውን ሉዓላዊ ቍጥጥር መግለጽ ነው።

በዚህ ምዕራፍ የሚገኘው ታሪክ በተፈጸመ ጊዜ የባቢሎን ጦር በአብዛኛው የባቢሎን ግዛት ውስጥ ተሸንፎ ነበር። ንጉሥ ናቦኒዱስ የተማረከ ሲሆን፥ ከእርሱ ጋር ነግሦ የነበረው ልጁ ንጉሥ ብልጣሶር ከባቢሎን የመጨረሻ ጦር ጋር በባቢሎን ከተማ ቀርቶ ነበር። የከተማይቱ የመከላከያ ኃይል ጠንካራ ስለነበር ብልጣሶር የዋስትና ስሜት ተሰምቶት ነበር። አማልክቱንም ለማክበር ግብዣ አዘጋጅቶ ነበር። ታላቅነቱን ለማሳየት ከኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ተወስደው የነበሩትን የአምልኮ ዕቃዎች ለጣዖት አምልኮ ተጠቀመባቸው። እግዚአብሔር በግድግዳ ላይ በተጻፈ ጽሑፍ የባቢሎን መንግሥት አገዛዝ በዚያ ምሽት እንደሚፈጸምና የሜዶንና የፋርስ መንግሥት ጅማሬ እንደሚሆን ለብልጣሶር ነገረው። በዚያ ምሽት የቂሮስ ሠራዊት የባቢሎንን ግንቦች ጥሶ በመግባት ከተማይቱን ተቆጣጠረ። ብልጣሶር ተገደለና ናቡከደነፆር በሕልሙ ባየው ምስል ውስጥ ሁለተኛ መንግሥት የሆነው የሜዶንና ፋርስ ዘመነ መንግሥት ጀመረ። 

6. ዳንኤል በአንበሳ ጕድጓድ (ዳንኤል 6)

ይህ የሆነው በሜዶንና ፋርስ ዘመነ መንግሥት ነበር። በናቡከደነፆር ዘመነ መንግሥት እንደነበረው፥ ዳንኤል በአዲሱ መንግሥትም ውስጥ ከፍተኛ ሥልጣን አገኘ። ዳንኤል የባዕድ አገር ሰው ሆኖ ይህንን ሥልጣን በማግኘቱ ሌሎቹ አስተዳዳሪዎች ቀኑበት። ስለዚህ በዳንኤል ላይ ስሕተት በመፈለግ ሊከሱትና ሊያጠፉት ወሰኑ። ከዳንኤል ሊያገኙት የቻሉት «ስሕተት» ግን እግዚአብሔርን ማምለኩ ብቻ ነበር። ስለዚህ ሕዝቡ ሁሉ ለ30 ቀናት ንጉሥ ዳርዮስን ብቻ እንዲያመልክ በሚያስገድድ መልክ ሕጉን ለወጡት። ዳንኤልም ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ ሳይሆን ቀረ። በእግዚአብሔር እንዳፈረ ሆኖ ሃይማኖቱን ለመደበቅም ፈቃደኛ ሳይሆን ቀረ። በዚህ ምክንያት ዳንኤል አናብስት ባሉበት ጕድጓድ ውስጥ ተጣለ። ጻሩ ግን እግዚአብሔር ሦስቱን ወጣቶች በእቶን እሳት ውስጥ እንደጠበቃቸው፥ ዳንኤልንም የአናብስቱን አፍ በመዝጋት ጠበቀው። ንጉሥ ዳርዮስ «የዳንኤልን አምላክ» ለማክበር ተገደደ፡፡ ሌሎችም ለ «ዳንኤል አምላክ» ክብር እንዲሰጡ አዘዛቸው።

የሜዶኑ ዳርዮስ የሚያመለክተው ማንን እንደሆነ አናውቅም። አንዳንዶች ይህ የቂሮስ ሌላው ስሙ ነው ሲሉ፥ ሌሎች ደግሞ ጉባሩ የተባለውን የባቢሎን ገዥ የሚያመለክት ነው ይላሉ።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እግዚአብሔር ዳንኤልን የጠበቀውና ኢሳያይስን ግን በመጋዝ ለሁለት እንዲሰነጠቅ የፈቀደው ለምን ይመስልሃል? ለ) እግዚአብሔር ከአሳዳጆች ነፃ ሊያወጣ ወይም ሊታደግ ወይም ደግሞ በስደት ምክንያት እንድንሞት የመፍቀድ መብት ያለው ስለ መሆኑ ይህ ምን ያስተምረናል? ሐ) አንድ ክርስቲያን የዳንኤልን የመሰለ ምርጫ በሚያጋጥመው ጊዜ ምላሹ ምን መሆን አለበት? መ) በኢትዮጵያ ያሉ ክርስቲያኖች ተመሳሳይ ምርጫ ገጥሟቸው ባደረጉት ውሳኔ እግዚአብሔር ነፃ እንዳወጣቸው የሚያሳዩ ምሳሌዎችን አቅርብ። 

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

https://forms.gle/VbAFb434Q4xBU1g88
Exit mobile version