Site icon

የጠፉ ኃጢአተኞችን አስቡ (1ኛ ቆሮ. 6፡1-8)

በቆሮንቶስ የነበረችው ቤተ ክርስቲያን በፍጥነት በከተማው ውስጥ ምስክርነቷን እያጣች ነበር። ያልዳኑት በጉባኤው መካከል ስላለው ዝሙት ማወቃቸው ብቻ ሳይሆን የቤተ ክርስቲያን አባላት መካሰሳቸውንም ደርሰውበት ነበር። የሥጋ ኃጢአቶች ብቻ ሳይሆኑ የመንፈስ ኃጢአቶችም ነበሩ (2ኛ ቆሮ. 7፡1)። 

ግሪኮች በአጠቃላይ፥ ደግሞ አቴናውያን በተለይ የችሎት ሰዎች በመሆን የታወቁ ነበሩ። የግሪክ ቲአትር ደራሲ አሪስቶፋኒስ ከገጸባሕርያቱ አንዱን በካርታ ላይ ግሪክ የት እንዳለች እንዲጠየቅ አደረገ። በዚህ ጊዜ ፈልገው ሲያሳዩት፥ የለም ይኼ ነገር ስሕተት መሆን አለበት- ምክንያቱም ምንም የሙግት ሂደት ሲካሄድ አላይም! ብሎ መለሰ። ይሁንና አሜሪካንም ወደዚህ ዓይነቱ ስመጥርነት በፍጥነት እየተሽጋገረች ነው። በቅርቡ በአሥራ ሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ ከ200,000 በላይ የሚሆኑ ከወንጀል ውጭ የሆኑ ክሶች በፌደራሉ ፍርድ ቤቶች ፋይል ተከፍቶባቸው ነበር። ወደ 610,000 ጠበቃዎች (ቁጥራቸው እየጨመረ ነው) ጉዳዮቹን ይዘዋቸዋል። በ1977፥ ከ12 ሚሊዮን ክሶች በላይ በመንግሥት ፍርድ ቤቶች ፋይል ተከፍቶባቸዋል። 

ጳውሎስ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሦስት አሳዛኝ ነገሮችን ደርሶባቸዋል። በመጀመሪያ፥ አማኞች ላልዳኑ ሰዎች እያሳዩ የነበሩት ደካማ ምስክርነት ነበር። የማያምኑ አይሁድ እንኳ ወንጀል-ነክ ያልሆኑ ጉዳዮቻቸውን የሚፈቱት በምኵራብ ችሎታቸው ላይ ነበር። የክርስቲያኖችን ችግር ወስዶ «ትክክለኛ ባልሆኑ» እና «በማያምኑ» ፊት መወያየት የወንጌልን ምስክርነት የሚያራክስ ነበር። 

ሁለተኛ፥ ምእመናኑ በክርስቶስ የሚጠበቅባቸውን ሙሉ አቋም ይዘው ለመገኘት አልበቁም። ቅዱሳን አንድ ቀን በዓለም እና እንዲያውም በወደቁት መላእክትም ላይ በመፍረዱ ተግባር ስለሚሳተፉ፥ በዚህ በምድር ላይ ሆነው ልዩነቶቻቸውን መፍታት መቻል አለባቸው። ቆሮንቶሳውያን ስለ ታላላቅ ስጦታዎቻቸው በኩራት ይለፍፉ ነበር። ታዲያ ለምን ችግሮቻቸውን ለመፍታት አልተጠቀሙባቸውም? 

የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በቁጥር 4 ላይ ጳውሎስ ሳስቀመጠው አባባል እርስ በርስ ይለያያሉ። አንዳንዶቹ መጠነኛ ምፀት የሚጠቀም ይመስላቸዋል። «ፍርድ ቤት ቢያስፈልጋችሁ በቤተ ክርስቲያን የተናቁትን ሰዎች ፈራጆች እድርጋችሁ ታስቀምጣላችሁን? በሙያው በጣም ወደተካነ ነገር ግን ያልዳነ ዳኛ ዘንድ ከምትሄዱ፥ በቤተክርስቲያን ካሉት በጣም ደካማው ምእመን ጉዳዩን እንዲፈታ ብታደርጉ ይሻላችሁ ነበር!» ሌሎች ደግሞ «በቤተ ክርስቲያን የተናቁትን» የሚለውን ሃይማኖት-የለሽ ዳኞችን የሚያመለክት አድርገው ይወስዱታል። ወይም የጳውሎስ አባባል እግዚአብሔር በጣም የተናቀውን የቤተክርስቲያን ምእምን ፈቃዱን ለማሳየት ሊጠቀምበት ይችላል ማለት ይሆናል። ውጤቱ ዞሮ ዞሮ አንድ ነው። ሙግታቸውን ወደ ፍርድ ቤት ማውጣት ለክርስቲያኖች ስሕተት ነው። 

በእርግጥ አንዳንድ ጊዜ አንዳንድ ጉዳዮችን ለማስፈጸም ሕግ የሚያስገድዳቸው «ጠቃሚ ክሶች» ይኖራሉ። ጳውሎስ የሚናገረው ስለ እነዚህ አይደለም። ጉዳያቸውን በፍርድ ቤት ለማስፈጸም የቤተ ክርስቲያን አባላት «ጉሮሮ ለጉሮሮ የተናነቁ» ይመስላል። ስየቤተ ክርስቲያኖቻችን ዛሬ ክርስቲያን ጠበቃዎች ወንጀል-ነክ ባልሆኑ ጉዳዮች እንደ ሸምጋይ ሆነው ጉዳዮቹን ከፍርድ ቤት ውጭ መፍታታቸውን ማየቴ ያስደስተኛል። 

ሦስተኛ አሳዛኝ ክስተትም ነበር። እርስ በርስ የሚካሰሱት ከወዲሁ የተረቱ ናቸው። ምንም እንኳ አንዳንዶቻቸው የፍርድ ቤት ጉዳዮቻቸውን የረቱ ቢሆኑም፥ ለእግዚአብሔር ቃል ባለመታዘዛቸው የባሰ ኪሣራና ወይም ሽንፈት ገጥሞአቸው ነበር። «ፈጽሞ በእናንተ ጉድለት ነው» (ቁ. 7) የሚለው «ይህ ለእናንተ ፍጹም ሽንፈት ነው» ተብሎ ሊተረጎም ይችላል። ጳውሎስ እዚህ ላይ በማቴዎስ 5፡39-42 ያለውን የጌታ ትምህርት ማመልከቱ መሆኑ ምንም የማያጠራጥር ነበር። ወንድምን አጥቶ ምስክርነትንም ከማጣት ገንዘብን ወይም ንብረትን ማጣት ይሻላል። 

በራሴ የአገልግሎት ዓመታት ውስጥ፥ ቤተ ክርስቲያኖች እና የቤተ ክርስቲያን አባላት የየግል ችግሮቻቸውን በፍርድ ቤት ለመፍታት ሲሞክሩ የተከሰተውን አሳዛኝ ውጤት አይቻለሁ። እንደ እውነቱ ከሆነ ማንም አያሸንፍም- ከሰይጣን በስተቀር! ወደ ፍርድ ቤት ይሄዱ የነበሩ ቆሮንቶሳውያን ልክ ከሥጋ ዘመዱ ጋር ዝሙት እንደፈጸመው ሰው በጌታ እና በቤተ ክርስቲያን ስም ላይ ውርደትን ያስከተሉ ስለሆነ መቀጣት ይገባቸዋል። 

አንድ ለአገልጋይነት የሚማር ተማሪ ትምህርት ቤቱን እንደሚከስ ስልክ ደውሎ የነገረኝ ትዝ ይለኛል። ነገሩ አስተዳደሩ ለትምህርት በጣም አስፈላጊ መስሎ የታየውን ነገር እንደከለከለው ይመስላል። «ረጋ እንዲል»፥ የፋካልቲ አማካሪውን እንዲያናግር እና ይህን አሳብ ከአእምሮው እንዲያወጣ መከርሁት። እርሱም ምክሬን ተቀብሎ መጥፎ ምስክርነትን አራቀ። ከዚህም ሌላ በልምምዱ መንፈሳዊ እድገት አገኘበት። 

ጽሑፍ – በዋረን ዌርዝቢ፣ ትርጉም – በፈቃዱ ገብሬ፣ እርማት–በጌቱ ግዛው 

Exit mobile version