Site icon

የክርስቶስ መለኮታዊነት 

የመጀመሪያው ርእሳችን ስለ ክርስቶስ መለኮታዊነት የሚናገር ይሆናል። በዛሬው ትምህርታችን ውስጥ ኢየሱስ እግዚአብሔር ስለመሆኑ በግልጽ የሚያስተምሩን ስድስት ክፍለ ምንባቦችን እንመለከታለን። በተቀሩት ቀናት ደግሞ በአዲስ ኪዳን ውስጥ የክርስቶስን መለኮታዊነት የሚገልጹ ሌሎች መንገዶችን እንመለከታለን። 

አዲስ ኪዳን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህች ምድር ከመምጣቱ አስቀድሞ፤ ወደ ምድርም ከመጣ በኋላና ምድራዊ ሕይወቱ ከተፈጸመም በኋላ እርሱ አምላክ እንደነበረ ያስተምረናል። ይህን ነጥብ በጥናታችን ውስጥ መላልሰን እናነሣዋለን። ሆኖም ኢየሱስ እግዚአብሔር ስለመሆኑ በሚያስተምሩ ክፍለ ምንባቦች ብንጀምር መልካም ነው። የመጀመሪያዎቹ ክፍለ ምንባቦች ስለ ክርስቶስ መለኮታዊነት በግልጽ ሊገባን በሚቻል መንገድ የሚያቀርቡ ናቸው። ብዙ የሃይማኖት ዘርፎችና ክርስቲያን ያልሆኑ ሃይማኖቶች ክርስቶስ አምላክ መሆኑን ይክዳሉ። ስለ ኢየሱስ መለኮትነት የሚያስተምሩ እነዚህ ምንባቦች ኢየሱስ ሙሉ በሙሉ አምላክ አይደለም ብለው ለሚክዱት ወገኖች መልስ ለመስጠት ይረዷችኋል። 

ዮሐንስ 1፡1 

ጥያቄ፡- ዮሐንስ 1፡1 አንብቡ። ዮሐንስ ስለ ቃሉ ምን ይላል? 

ዮሐንስ በወንጌሉ በምዕራፍ 1፡1 ላይ ኢየሱስ «ቃል» መሆኑን ይገልጻል። ወደ ኋላ ወደዚህ ክፍለ ምንባብ መለስ ብለን ዘርዘር ባለ ሁኔታ እናጠናዋለን። ለዛሬው ዮሐንስ ስለ ቃል የተናገረውን እጢኑ። ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ ይህም ቃል እግዚአብሔር ነበረ። ዮሐንስ ኢየሱስ ሙሉ በሙሉ አምላክ የብሉይ ኪዳኑ አምላክ እንደሆነና በአንዳንድ ሁኔታም ከእግዚአብሔር እንደሚለይ ይመሰክራል። ምንም እንኳን ሰው እግዚአብሔር ሊሆን የሚችልበትን ሁኔታ ለመገንዘብ ቢያስቸግረንም። ይህ ጥቅል ግን ኢየሱስ አምላክ መሆኑን በግልጽ ይናገራል። 

አንዳንድ የእምነት ክፍሎች ዮሐንስ 1፡1 ኢየሱስ አንዱና እውነተኛው እግዚአብሔር መሆኑን አያስተምርም፥ ይልቅስ እርሱ የአምላክ ምሳሌ ነው፥ ይላሉ። እንደዚሁም በፅርዕ (በግሪክ) በተጻፈው የመጀመሪያው አዲስ ኪዳን ውስጥ ይህ ጥቅስ የሚያስተምረው፥ ኢየሱስ እግዚአብሔርን የሚመስል መለኮት መሆኑን እንጂ እርሱ አንዱና ብቸኛው እውነተኛው እግዚአብሔር መሆኑን አያስተምርም ይላሉ። እነዚህ መናፍቃን አንድ ሰው በአንድ ጊዜ ከሌላው ጋር ወዲያው ደግሞ ያንኑ ሰው መሆን በሥነ አመክንዮአዊ አይችልም። ስለዚህ ጥቅሱ ኢየሱስ አንዱና እውነተኛው ብቸኛው አምላክ ነው ብሎ አያስተምርም ሲሉ ይደመድማሉ። 

በአንጻሩ ደግሞ ይህ ጥቅስ ኢየሱስ እግዚአብሔር መሆኑን እንጂ እግዚአብሔርን ይመስላል ብሎ እንደማያስተምር የግሪክ ሊቃውንት ያረጋግጣሉ። ምንም እንኳን አንድ ሰው በአንድ ጊዜ ከሌላው ሰው ጋር ሆኖ፥ ያንኑ ሰው ሊሆን መቻሉ የሚታመን መስሎ ባይታይም፥ ጥቅሱ የሚናገረው ግን ይህንኑ ነው። ስለ ክርስቶስ ማንነት የሚኖረን ግንዛቤ ከመደበኛው የሰው ሥነ አመክንዮአዊ መረዳት ውጭ መሆኑን ማወቅ አለብን። ኢየሱስ በአንድ በኩል አንድና ብቸኛ እውነተኛው አምላክ ነው፤ እንዲሁም እርሱ ከእግዚአብሔር ጋር ነው። ደግሞም ከእግዚአብሔር የተለየ ነው። ዮሐንስ 1፡1 ኢየሱስ እግዚአብሔር መሆኑን በግልጽ ያስረዳል። 

ዮሐንስ 20፡28 

ጥያቄ፡- ዮሐንስ 20፡24-29 አንብቡ። ሀ) የተቀሩት ደቀ መዛሙርት ከሞት የተነሣውን ኢየሱስን ማየታቸውን ለቶማስ በነገሩት ጊዜ፣ ቶማስ በመጀመሪያ ምን ተሰማው? ) ቶማስ በመጀመሪያ ኢየሱስን ባየው ጊዜ፥ ኢየሱስ ከሞት መነሣቱን ቶማስ እንዲያምን ለማድረግ ምን አደረገ? ሐህ ቶማስ ለኢየሱስ ምላሽ የሰጠው እንዴት ነበር? 

ይህ በዮሐንስ 20፡24-29 የተጻፈ ታሪክ የተፈጸመው ኢየሱስ በፋሲካው እሑድ ጠዋት ከሞት ከተነሣ ከአንድ ሳምንት በኋላ ነበር። በፋሲካው እሑድ ማታ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ታይቶ ነበር (ዮሐ 20፡19) ይሁን እንጂ፥ ቶማስ ከሌሎቹ ደቀ መዛሙርት ጋር ስላልነበረ በተገናኙ ጊዜ ኢየሱስን እንዳዩ ሲነግሩት ተጠራጠራቸው። ሞቶ የነበረ ሰው አሁን እንዴት ሕያው ይሆናል? በማለት ቶማስ ሊሞት ያየው ኢየሱስ ሕያው መሆኑን በእጆቹ ዳስሶ ካላረጋገጠ በስተቀር እንደማያምን ነገራቸው። ከሳምንት በኋላ ደቀ መዛሙርቱ በሙሉ በዚያው ክፍል ውስጥ ነበሩ፤ ቶማስም አብሮአቸው ነበር። ከዚያም ኢየሱስ ገና እንደ ታያቸው ወዲያውኑ ወደ ቶማስ መለስ አለ። ቶማስ ከሳምንት በፊት የተናገረውን እንዳወቀ በሚገልጽ ሁኔታ ሞቶ የተነሣውና ሕያው የሆነው ያው የበፊቱ ኢየሱስ መሆኑን እንዲያረጋግጥ ቶማስን ጠራው። የቶማስም ምላሽ «ጌታዬና አምላኬ» ማለት ነበር። «ጌታዬ» የሚለውን ቃል ብቻ ቢጠቀም ኖሮ፥ አክብሮትን ብቻ የሚገልጽ ስለሚመስል፥ ቶማስ «ጌታዬ» ብቻ ሳይሆን «አምላኬ» ማለቱንም ማስተዋል ያስፈልጋል። ቶማስ ከፊት ለፊቱ የቆመው ኢየሱስ፥ እግዚአብሔር መሆኑን ተገንዝቦአል።

ጥያቄ፡– ዮሐንስ 20፡30-31 አንብቡ። ዮሐንስ ይህን ስለ ኢየሱስና ስለ ተማስ የሚያወሳ ታሪክ የነገረን ለምንድን ነው? 

ዮሐንስ ይህን ታሪክ የነገረን አንድ ነገር ሊያስተምረን ነው። ይኸውም የኢየሱስን ማንነትና እርሱ አምላክ መሆኑን ሊያስተምረን ነው። ቶማስ ኢየሱስን አምላክ በማለቱ እንደ ተሳሳተ ዮሐንስ አይነግረንም። ይልቁንም ይህን ታሪክ ሲነግረን ዓላማው እኛም ኢየሱስን እንደ አምላክ አድርገን እንድንቀበለው ነው። 

ኢየሱስ እግዚአብሔር መሆኑን የሚክዱ አንዳንድ መናፍቃን ቶማስ፥ «አምላኬ» ማለቱ ኢየሱስ ሕያው ሆኖ ስላየው መገረሙን በአንክሮ መግለጹ ነው እንጂ ሌላ ማለቱ አይደለም ይላሉ። ሆኖም ይህ አባባላቸው እውነት ላለመሆኑ ሦስት ምክንያቶች አሉ። አንደኛ፥ ቶማስ ይህን ቃል ለኢየሱስ መናገሩ በቁጥር 28 ላይ ተጽፎአል። ቶማስ ይህን ሲያደርግ ስሜቱን በአንክሮ መግለጹ ወይም እግዚአብሔር አብን መጥራቱ ብቻ አልነበረም። በልቡ ያመነበትን አውጥቶ ለኢየሱስ መናገሩ ነበረ እንጂ። ሁለተኛ፥ ቶማስ ኢየሱስን፤ «ጌታዬ » ብሎታል። እንደዚሁም «አምላኬ» ሲል ኢየሱስን ለማመልከት ነው። ሦስተኛ፥ ከቁጥር 30=31 ባለው ክፍል እንደተመለከትነው፥ ኢየሱስ ልጅም አምላክም መሆኑን እንድናውቅ ዮሐንስ ይህን ታሪክ መተረኩን ይገልጣል። እርሱም ቶማስ ኢየሱስ አምላክ መሆኑን አስቦ እንደ ተናገረ በመጥቀስ የእርሱን መግለጫ በመጠቀም ለእኛም ሊያሳየን ይፈልጋል። 

ኢየሱስ አምላክ መሆኑን በግልጽ የሚያስተምረን ሁለተኛው ክፍል ዮሐንስ 20፡28 ነው። 

ዕብራውያን 1፡8-9 

ጥያቄ፡- ዕብራውያን 1፡4-9 አንብቡ። ሀ. ልጁ ኢየሱስ ከመላእክት ጋር የሚነጻጸረው እንዴት ነው? ለ) ቁጥር 6 መላእክት ከኢየሱስ ጋር ለላላቸው ግንኙነት ምን ይላል? ሐ) በቁጥር 7 ላይ እግዚአብሔር መላእክትን ምን ብሎ ጠራቸው? መ) ከቁጥር 8-9 ስለ ልጁ ምን ተባለ? 

በዕብራውያን 1፡4-14 ባለው ክፍል ውስጥ ጸሐፊው ኢየሱስ ከማንኛውም መልአክ በላይ መሆኑን ያመለክታል። በቁጥር 4 ላይም ጸሐፊው የእርሱ ነም ከሁሉ በላይ ስለሆነ፥ ኢየሱስ ከመላእክት ሁሉ በላይ ማረግ ያለው መሆኑን ይገልጻል። እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ ነው። እንደዚሁም ልጁ ከአባቱ ጋር ስላለው ልዩ ግንኙነት ሊያስገነዝበን ስለፈለገ በቁጥር 5 ላይ ከብሉይ ኪዳን ሁለት ክፍሎችን ይጠቅሳል። እነርሱም መዝሙር 2፡7 እና 2ኛ ሳሙኤል 7፡14 ናቸው። በቁጥር 6 ላይ መላእክት ለልጁ እንደሚሰግዱለት ለመግለጽ ዘዳግም 32፡43 ይጠቅሳል። እንደዚሁም መላእክት አገልጋዮች መሆናቸውን ለማስረዳት በቁጥር 7 ሥር መዝሙር 104፡4ን ጠቅሷል። እነዚህ ጥቅሶች ሁሉ (ዕብራውያን 1፡4-7)። ኢየሱስ ክርስቶስ ከመላእክት በላይ መሆኑን ያስረዳሉ። በመጨረሻውም ከቁጥር 8-9 ባለው ክፍል መዝሙር 45፡6-7 ያለውን ቃል ይጠቅሳል። በዚህ መዝሙር ውስጥ ልጁ ሁለት ጊዜ አምላክ ተብሎ ተጠርቷል። ልጁ አምላክ እንደ መሆኑ፥ ለዘላለም የጸና ዙፋን አለው። በዚሁ በዕብራውያን 1፡9 ውስጥ፥ ልጁ አምላክ ተብሎ ቢገለጽም የራሱ የተለየ ሕላዌ እንዳለው ማስተዋሉ ይጠቅማል። በዮሐንስ 1፡1 ውስጥ እንዳለው ትምህርት ይህ በሰብአዊ አስተሳሰብ ተቀባይነት ላይኖረው ይችላል። ነገር ግን ስለ ኢየሱስ ማንነት ወይም ባሕርይ ያለን ግንዛቤ እነዚህ ጥቅሶች ከሚሰጡት ትምህርት ጋር ሊስማማ ይገባል። በዕብራውያን 1፡8-9 ያለው ክፍል ልጁ እግዚአብሔርም መሆኑን በግልጽ ሲያመለክት፥ ነገር ግን የተለየ የራሱ ሕላዌ ወይም ማንነት እንዳለውም ይናገራል። 

ቲቶ 2፡12-13 

ጥያቄ፡- ቲቶ 2፡12-13 አንብቡ። ሀ) የክርስቶስን ዳግም ምጽአት ስንጠባበቅ የእግዚአብሔር ጸጋ እንዴት መኖር እንዲገባን ያስተምረናል? ለ) ቁጥር 13 ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተመልሶ ይመጣል ይላል። እርሱ በዚህ ጥቅስ ውስጥ እንዴት ነው የተገለጸው? 

ቲቶ 2፡12-18 ስለ ክርስቶስ መለኮታዊነት በግልጽ ያስተምራል። በዚህ ክፍል ጳውሎስ ለማስተላለፍ የፈለገው ዋና መልእክት፥ የእግዚአብሔር ጸጋ በሕይወታችን ውስጥ ኃጢአትን ተቋቁመን የቅድስና ኑሮ እንዴት መኖር እንደሚያስችለን ነው። የክርስቶስን ዳግም መምጣት በተስፋ ስንጠባበቅ፥ ይህ የጸጋ ተግባር በቅድስና ለመኖር እንድንችል ይረዳናል። ይህ ዳግም ተመልሶ የሚመጣው ኢየሱስ ክርስቶስ ማን ነው? ጳውሎስ «አምላካችንና መድኃኒታችን» ብሎ ይጠራዋል። በአማርኛው ጥቅስ ውስጥ «አምላክ» የሚለው ቃል ኢየሱስን ለመግለጽ ተጽፎአል። በመጀመሪያው፥ ግሪክ «እግዚአብሔር» ተብሎ ሊተረጎም ይችላል። ኢየሱስ መድኃኒታችንና አምላካችን (እግዚአብሔር) ነው። አንዳንድ የእምነት ክፍሎች ጳውሎስ ስለ ሁለት መገለጦች ይናገራል ይላሉ። ይህም ስለ እግዚአብሔር አብ መገለጥ እና ስለ መድኃኒታችን፥ ኢየሱስ ክርስቶስ መገለጥ ነው። ጳውሎስ ኢየሱስ እግዚአብሔር መሆኑን በዚህ ክፍለ ምንባብ አላስተማረም፤ እርሱ ያስተማረው ኢየሱስ ጌታና መድኅን መሆኑን ብቻ ነው ይላሉ። ነገር ግን የግሪኩ ሰዋሰው «አምላክ» እና «መድኅን» የሚሉትን ቃላት እያይዞ ስለ አንድ አካል ይናገራል። ጳውሎስም ያስተማረው ኢየሱስ እግዚአብሔርም መድኅንም እንደሆነ ነው። 

2ኛ ጴጥሮስ 1፡1 

ጥያቄ፡- 2ኛ ጴጥሮስ 1፡1 አንብቡ። ጴጥሮስ ኢየሱስን እንዴት ይገልጸዋል? 

2ኛ ጴጥሮስ 1፡1 ከቲቶ 2፡12-13 ጋር በጣም ተመሳሳይ ነው። ጴጥሮስ በመግቢያው ላይ መልእክቱን የላከው በኢየሱስ ክርስቶስ ጽድቅ አማካይነት እምነትን ላገኙት እንደሆነ ይናገራል። ይህንን ኢየሱስን እንዴት ይገልጸዋል? እርሱ አምላካችንና መድኃኒታችን መሆኑን ይገልጻል። በቲቶ 2፡12-13 በተጠቀሰው መሠረት የግሪኩ ቋንቋ ለአምላክ የሚጠቀምበትን ትርጉም ያቀርባል። ይኸው ቃልም እግዚአብሔር ተብሎ ተተርጉሞአል። ስለሆነም ኢየሱስ እግዚአብሔርም መድኃኒታችንም ነው። 

በሮሜ 9፡5

ጥያቄ፡- ሮሜ 9፡5 አንብቡ፡፡ ጳውሎስ ክርስቶስን እንዴት ይገልጸዋል?

በሮሜ 9፡1-5 ጳውሎስ የእስራኤል ሕዝብ ወደ ክርስቶስ መጥተው እንዲድኑ መፈለጉን ይናገራል። ከቁጥር 4-5 እስራኤላውያን ከእግዚአብሔር ስለተቀበሏቸው በረከቶች ይገልጻል። ለምሳሌም ያህል፥ እግዚአብሔር ተስፋዎቹን፥ ቃል ኪዳኖቹን፥ ሕጎቹንና የብሉይ ኪዳን አባቶችን ሰጥቷቸዋል። ከሁሉም በላይ፥ ክርስቶስ ወይም መሢሕ ራሱ የተገኘው ከእስራኤላውያን ዘር ነው። ኢየሱስ አይሁዳዊ ነው፥ ይህም ለእስራኤላውያን ከፍተኛ በረከት ነበር። ነገር ግን፥ ኢየሱስ አይሁዳዊነቱ በሰብአዊ ደረጃ ብቻ አልነበረም። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚለው ደግሞ እርሱ «በሁሉም ላይ አምላክ ነው» በቲቶ 2፡12-13 እና 2ኛ ጴጥሮስ 1፡1 ውስጥ «አምላክ» የሚለው ቃል እንደ ተጻፈው ሁሉ፥ በመጀመሪያው ግሪክ ውስጥም «እግዚአብሔር» ተብሉአል። ጳውሎስ በሮሜ 9፡5 ውስጥ ኢየሱስ እግዚአብሔር ሲሆን፥ በፍጥረታት ሁሉ ላይም አምላክ የሆነው ይላል። 

በዮሐንስ 1፡1፤ በዮሐንስ 20፡28፤ በዕብራውያን 1፡8-9፤ ቲቶ 2፡12-13፤ እንዲሁም በሮሜ 9፡5 ላይ በሚገኙ ጥቅሶች ሁሉ ክርስቶስ «እግዚአብሔር» መሆኑ በግልጽ ተጽፎአል። ነገር ግን ኢየሱስ እግዚአብሔር ስለመሆኑ የሚያረጋግጡ ጥቅሶች እነዚህ ብቻ አይደሉም። ነገ ኢየሱስ የእግዚአብሔር የሆኑ ተመሳሳይ ባሕርያት እንዳሉት፥ እግዚአብሔር የሚፈጽማቸውን ተመሳሳይ ተግባራትንም እንደሚፈጽም የሚናገሩ ሌሎች ጥቅሶችን እንመለከታለን። 

ጥያቄ፡- ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ መሆኑን ከተጠራጠረ ሰው ጋር የተነጋገራችሁበትን ጊዜ በማስታወሻ ደብተራችሁ ላይ ጻፉ። ዛሬ ካጠናችኋቸው ጥቅሶች ውስጥ የትኛውን ለዚህ ሰው ልታካፍሉ ትችላላችሁ? 

ጥያቄ፡– ዮሐንስ 1፡1 በቃላችሁ አጥኑ። እንደዚሁም ዛሬ ካጠናናቸው ጥቅሶች ውስጥ ሁለቱን በቃላችሁ አጥኑ።

ምንጭ፡- “አስተምህሮ ክርስቶስና ደኅንነት”፤ ጽሑፍ፣ በዶ/ር ስቲቭ ስራውስ፤ ትርጉም በኃይሉ ልመንህ

Exit mobile version