Site icon

በጥንታዊቷ ቤተ ክርስቲያን የተሠገዎ ታሪክ፣ ሞናርካዊነት ወይም ስባልዮሳዊነት 

በጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን ኢቢዮናዊነት ከተወገዘ በኋላ የእግዚአብሔርን እንድነት የሚያስጠብቅ የመሰለ የሐሰት ትምህርት ተነሣ። እነዚህ ቡድኖች «ሞናርካዊነት» በተባለ አስተምህሮ ያምኑ ነበር። እነርሱም እግዚአብሔር አንድ በመሆኑ ላይ አጥብቀው አጽንኦት ይሰጡ ነበር። ነገር ግን እነዚህ ቡድኖች የሚያታግል ጥያቄ ነበራቸው፡ ጥያቄያቸው እግዚአብሔር አንድ ከሆነ ኢየሱስ በምን አኳኋን እግዚኣብሔር ሊሆን ይችላል? የሚል ነበር። ከእነዚህ አንዱ የሞናርካዊነት ቡድን ደግሞ ከኢቢዮናውያን ጋር የሚመሳሰል ትምህርት ያስተምሩ ነበር። እነርሱም ኢየሱስ ሰው ነበር፥ ነገር ግን ጻድቅ የሆነ ሰው ነበር። ስለሆነም እግዚአብሔር ይህን ጻድቅ ሰው (ኢየሱስን) በጥምቀቱ ጊዜ ወስዶ በተለየ መንገድ ተገለገለበት ይላሉ። ቤተ ክርስቲያን ኢቢዮናውያንን በተቃወመችበት መንገድ መልስዋን በመስጠት ትምህርታቸው ሐሰተኛ መሆኑን አጋልጣለች። ነገር ግን ሁለተኛ ዓይነት ሞናርካዊነትም ነበር። ይህ ቡድንም በእግዚአብሔር አንድነት ላይ አጽንኦት ነበረው። እነዚህም አንድ እግዚአብሔር ብቻ አለ፥ ይህም እግዚአብሔር በተለያዩ አካላት አማካይነት ራሱን ገልጧል ይላሉ። እነርሱም አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር ራሱን እንደ አብ፥ በሌላ ጊዜ ደግሞ እንደ ወልድ፥ በሌላ ጊዜ ደግሞ ራሱን እንደ መንፈስ ቅዱስ ገለጠ ብለው ያስተምራሉ። ስለዚህ እነዚህ ቡድኖች ኢየሱስ እግዚአብሔር በመሆኑ ላይ ቢስማሙበትም፥ ነገር ግን ከእግዚአብሔር አብ ጋር አንድ አካል ነው ይሉ ነበር። የዚህ ሐሰት ትምህርት ዋናው መምህር ሳባልዮስ የተባለ ሰው ነበር። ከዚህ የተነሣ አንዳንድ ጊዜ ትምህርቱ ሳባልዮሳዊነት ተብሎ ይጠራል። 

ጥያቄ፡- ሀ) ሞናርካውያን ዋና ትኩረት ይሰጡዋቸው የነበረው ምንን ነበር? ለ) ሰባልዮስ ስለ አብ፥ ወልድና መንፈስ ቅዱስ ያስተማረው ምን ነበር? 46ኛ ጥያቄ፡- ማቴዎስ 3፡13-17 28፡19-20፥ እንዲሁም 2ኛ ቆሮንቶስ 3፡14 አንብቡ። በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ የሳባሊዮስ ትምህርቶች ሐሰት መሆናቸውን የሚያጋልጥ ምን አላቦች ታያላችሁ? 

ሞናርካውያን ሁሉ በእግዚአብሔር ኣንድነት ላይ አጽንኦታቸውን ያደርጋሉ። ማለትም እግዚአብሔር አንድ ብቻ ነው ይላሉ። ብዙዎቹ የሳባሊዮስን አስተምህሮ በመከተል፥ እግዚአብሔር አንድ ሲሆን፥ ራሱን ግን በተለያዩ አካላት ወይም አምሳል ገልጧል በማለት ያምናሉ። ይህን ሲሉ አንዱ እግዚአብሔር አንዳንድ ጊዜ እንደ ኣብ፥ በሌላ ጊዜ እንደ ወልድ፥ እንዲሁም በሌላ ጊዜ ደግሞ እንደ መንፈስ ቅዱስ ራሱን ገልጧል ማለታቸው ነው። ሳባሊዮስ ያስተማረው ራሱን በተለያዩ ሦስት መንገዶች የገለጠ አንድ እግዚአብሔር ብቻ አለ ብሎ ነበር። በአዲስ ኪዳን ውስጥ የሚገኙ አያሌ ጥቅሶች የሳባሊዮላ አስተምህሮ ሐሰት መሆኑን ያረጋግጣሉ። ኢየሱስ – በጥምቀቱ ጊዜ ውኃው ውስጥ ቆሞ ሳለ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወርዶ ሲያርፍበት፥ ከሰማይ ደግሞ የእግዚአብሔር ድምፅ ሲመጣ ተሰምቶአል። ከዚህ ጥቅስ እንደምንረዳው እግዚአብሔር አንዳንድ ጊዜ በአብ፥ ሌላ ጊዜ በወልድ እንዲሁም ደግሞ በመንፈስ ቅዱስ በተለያየ ሁኔታ የሚገለጥ እንዳይደለ ግልጽ ነው። ሁሉም የሥላሴ አካላት በአንድ ጊዜ በተለያዩ ሁኔታዎች ይገለጣሉ። በሁለቱም በማቴዎስ 28፡19-20 እና በ2ኛ ቆሮንቶስ 13፡14፤ አብ፥ ወልድና መንፈስ ቅዱስ ሁሉም አንድ አምላክ የሆኑ ራሳቸውን የቻሉ አካላት መሆናቸው ተገልጾአል። ስለዚህ የሳሳሊዮስ አስተምህሮ መጽሓፍ ቅዱሳዊ ባለመሆኑ በጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን መሪዎች ዘንድ ተወግዟል። 

ጥያቄ፡- ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ የሳባሊዮስን አስተምህሮ የተከተለ ምን የሐሰት ትምህርት ታውቃላችሁ? 

ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ የሳባሊዮስን የሐሰት ትምህርት የሚከተሉ ቡድኖች «የሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን» አማኒያን የሚባሉ አሉ። «የሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን» ሳባሊዮስ እግዚአብሔር አንድ ብቻ ነው፤ እርሱም አንዳንድ ጊዜ እንደ አብ፥ በሌላ ጊዜ እንደ ወልድ፥ እንዲሁም ደግሞ እንደ መንፈስ ቅዱስ ራሱን ይገልጣል ብሎ ያለውን የስሕተት ትምህርት በቀጥታ ይከተላሉ። ከእነዚህ ቡድኖች መካከል አንዳንዶቹ ስሜታዊ የሆኑ ዝማሬዎችን ስለሚያሰሙና እምነታቸውንም በዚሁ ስሜት ስለሚያስፋፉ በጣም ተቀባይነት አግኝተዋል። ስለዚህ ብዙ ሰዎች እነዚህ ቡድኖች ትክክለኛች ናቸው፤ ምክንያቱም የሚታይባቸው ደስታና የመንፈስ ግለት ይህን ይመሰክራል ይላሉ። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ እንደሚያስተምረን እግዚአብሔር አብ፥ እግዚአብሔር ወልድና እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ሦስት አካላት እንጂ የአንድ አምላክ ልዩ ልዩ መገለጫዎች አይደሉም። የሳባሊዮስ አስተምህሮት ሐሰት መሆኑ ቢታወቅም ቤተ ክርስቲያን የሥላሴን አስተምህሮ በተመለከተ በማያሻማ ሁኔታ ጥርት ያለ ግንዛቤና አቋም እንዲኖራት በማድረግ በኩል ረድቷታል። በዚህ መሠረት የሥላሴ ኣስተምህሮ እግዚአብሔር አንድም ሦስትም ነው የሚል ጽኑ አቋም ያዘ።

ምንጭ፡- “አስተምህሮ ክርስቶስና ደኅንነት”፤ ጽሑፍ፣ በዶ/ር ስቲቭ ስራውስ፤ ትርጉም በኃይሉ ልመንህ

Exit mobile version