የሉቃስ ወንጌል የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፡፡
ምልከታ እና ትርጓሜ
የሉቃስ ወንጌል ማጠቃለያ ላይ የምናገኘው ይህ ታላቅ ታሪክ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከትንሣኤው በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ ተገልጦ ሰላምንና ተስፋን የሰጠበት እንዲሁም ወደ ሰማይ ያረገበት እጅግ ድንቅ ክፍል ነው። ደቀ መዛሙርቱ ከኤማሁስ የተመለሱት ሰዎች የሚናገሩትን እየሰሙ ሳለ፣ ጌታችን ራሱ በመካከላቸው ቆሞ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው። ምንም እንኳ ስለ ትንሣኤው ቢሰሙም፣ ጌታን በድንገት በመካከላቸው ሲያዩት ግን መንፈስ ያዩ መስሏቸው ደነገጡና ፈሩ። ጌታችን ግን የልባቸውን ጥርጣሬና ፍርሃት ለማስወገድ እጆቹንና እግሮቹን እንዲመለከቱ፣ እንዲዳስሱትም ነገራቸው። “መንፈስ እንደ እኔ የምታዩት ሥጋና አጥንት የለውምና” በማለት ትንሣኤው ሥጋዊና እውነተኛ መሆኑን በተግባር አረጋገጠላቸው።
ደቀ መዛሙርቱ ከደስታ የተነሳ ገና ሳያምኑና እየተደነቁ ሳሉ፣ ጌታችን ይበልጥ እንዲረዱት የሚበላ ነገር እንዲሰጡት ጠየቀ። የተጠበሰ ዓሣና የማር ወለላም ሰጡት፤ እርሱም በፊታቸው በላ። ይህ ድርጊት ጌታችን ከሞት የተነሣው በምኞት ወይም በራእይ ሳይሆን፣ በእውነት ሞትን ድል አድርጎ ሕያው ሆኖ መነሣቱን የሚያሳይ ታላቅ ምስክርነት ነው። ዛሬም እኛ የምናመልከው ጌታ በመቃብር የቀረ ሳይሆን፣ ሞትን ድል አድርጎ የተነሣና አሁንም ሕያው ሆኖ በመካከላችን የሚገኝ አምላክ ነው።
ጌታችን በመቀጠል ትኩረታቸውን ወደ እግዚአብሔር ቃል መለሰ። ገና ከእነርሱ ጋር ሳለ በሙሴ ሕግና በነቢያት በመዝሙርም ስለ እርሱ የተጻፈው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ እንደሚገባ የተናገረውን ቃል አስታወሳቸው። መጻሕፍትንም ያስተውሉ ዘንድ አእምሮአቸውን ከፈተላቸው። ይህ እጅግ አስፈላጊ ነጥብ ነው፤ ጌታን በትክክል ለማወቅና ለማገልገል የእግዚአብሔርን ቃል በጥልቀት መረዳት ያስፈልጋል። ክርስቶስ መከራ መቀበልና በሦስተኛው ቀን ከሙታን መነሣት እንዳለበት፣ በስሙም ንስሐና የኃጢአት ስርየት ከኢየሩሳሌም ጀምሮ በአሕዛብ ሁሉ ዘንድ እንደሚሰበክ ገለጸላቸው። እነርሱም ለዚህ ታላቅ ወንጌል ምስክሮች እንዲሆኑ አዘዛቸው።
ለዚህ ታላቅ ተልእኮ ግን በገዛ ራሳቸው ጉልበት እንዲወጡ አልፈለገም። “አባቴ የሰጠውን ተስፋ እኔ እልክላችኋለሁ፤ እናንተ ግን ከላይ ኃይል እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ” አላቸው። ይህ የተስፋ ቃል ስለ መንፈስ ቅዱስ መውረድ የተነገረ ነው። ወንጌልን ለመመስከርና በእግዚአብሔር መንግሥት ሥራ ለመሰማራት ሰማያዊው ኃይል (መንፈስ ቅዱስ) የግድ ያስፈልጋል። ያለ እግዚአብሔር እርዳታና ኃይል መንፈሳዊ ጉዞን መጨረስ እንደማይቻል ጌታችን በሚገባ አስተማራቸው።
በመጨረሻም ጌታችን እስከ ቢታንያ ድረስ አወጣቸውና እጆቹን አንሥቶ ባረካቸው። ሲባርካቸውም ከእነርሱ ተለየና ወደ ሰማይ ወጣ። ጌታችን ወደ ክብር ያረገው እየባረካቸው መሆኑ፣ የእርሱ መሄድ ለደቀ መዛሙርቱ ሐዘን ሳይሆን በረከት መሆኑን ያሳያል። እነርሱም ሰገዱለትና በታላቅ ደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። ዘወትርም እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እየባረኩ በመቅደስ ነበሩ። ሉቃስ ወንጌሉን የደመደመው በሐዘን ሳይሆን በታላቅ ደስታና በአምልኮ ነው። ጌታችን ዛሬም በሰማይ በአባቱ ቀኝ ሆኖ ስለ እኛ ይማልዳል፤ ዳግመኛም በክብር ይመጣል።
ተግባራዊ የውይይት ጥያቄዎች
👉ኢየሱስ የትንሳኤ ሰውነቱን (ዓሣ በመብላት) ማሳየቱ ስለ ትንሳኤ አካል እውነታ
ምን ያስተምረናል?
👉“የላይኛው ኃይል” (ቁ. 49) ለሐዋርያቱ አገልግሎት ለምን የግድ አስፈላጊ ሆነ?
👉ምስክርነት ከኢየሩሳሌም ጀምሮ እስከ አሕዛብ ሁሉ መሆኑን መናገሩ የሉቃስን ዓለም
አቀፋዊ ራዕይ እንዴት ያጠናክራል?
👉ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እየባረካቸው ማረጉ (ቁ. 51) ለእኛ ለቤተ ክርስቲያን ምን
ትርጉም አለው?
👉ደቀ መዛሙርቱ ከእርገቱ በኋላ ለምን በደስታ ተሞሉ? (ቁ. 52)
👉በቤተ መቅደስ ዘወትር እግዚአብሔርን እያመሰገኑ መኖራቸው የሉቃስን ወንጌል
መደምደሚያ ከጅምሩ (ምዕራፍ 1) ጋር እንዴት ያገናኘዋል?
👉የኢየሱስ እርገት ለሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ (ሁለተኛው ቅጽ) ምን አይነት መነሻ ሆነ?
👉“መጻሕፍትን ያስተውሉ ዘንድ አእምሮአቸውን ከፈተላቸው” (ቁ. 45) መባሉ
ለመንፈሳዊ መረዳት ያለውን አስፈላጊነት እንዴት ያሳያል?
