Site icon

ጥምቀት የዘላለምን ሕይወት ለማግኘት (ለመዳን) አስፈላጊ ነው ወይ?

የውሃ ጥምቀት ክርስቲያን በምድራዊ ሕይወቱ ሳለ ሊደርጋቸው ወይም ሊታዘዛቸወ ከሚገባቸው መንፈሳዊ ትዕዛዛት መካከል አንዱ እንደሆነ ብናምንም በውሃ ጥምቀት የሃጢአት ስረየት ይገኛል፣ ወይም በዚህ መንገድ የዘላለም ሕይወት ይወረሳል የሚለውን ሃሳብ ግን አጥብቀን እንቃወማለን። የውሃ ጥምቀት አማኝ ከክርስቶስ ሞት፣ መቀበርና መነሳት ጋር በእግዚአብሔር ልዩ አሰራር እንደተባበር የሚገልጥበት ማሳያ ነው። የሮሜ መልክት እንዲህ ይላል፦”ወይስ ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ የተጠመቅን ሁላችን ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ እንደ ተጠመቅን አታውቁምን? እንግዲህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሙታን እንደ ተነሣ እንዲሁ እኛም በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ፥ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን።” (ሮሜ 6:3-4)። አንድ አማኝ በጥምቀት ወቅት በውሃው ውስጥ ሲጠልቅ ከክርስቶስ ጋር አብሮ መሞቱንና መቀበሩን ሲያመለከት ከውሃው ሲወጣ ደግሞ ከክርስቶስ ጋር አብሮ መነሳቱን ያሳያል።

መዳን ወይም የሃጢአት ይቅርታን ማግኘት ወይም የእግዚአብሔር ልጅ ለመሆን ዳግም ልደት ማግኘት በቀጥታ ክክርስቶስ የቤዛነት ስራ ጋር የተገናኘ ነው። ከመዳን ጋር በተያያዘ የሰው ልጅ ዋንኛና ብቸኛ ችግር ሃጢአት ነው። ለዚህ መፍትሄው ደግሞ የሃጢአት ስረየት ማግኘት ነው። ለሃጢአት ስረየት ብቸኛው መፍትሄ ነውር የሌለበት ፍጹም መስዋእት (ደም) መሆኑን ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ከጫፍ እስከ ጫፍ የሚመሰክርልን መንፈሳዊ እውነት ነው (ዕብራውያን 9:22)። እናም የዘላለምን ሕይወት ወይም የሃጢአትን ይቅርታ ከዚህ የክርስቶስ የመስዋዕት ደም ውጪ እንደሚገኝ ማሰበ የዘላለምን ሕይወት በራሳችን ጥረት (በስራችን) ለማግኘት ከመሞከር ውጪ ሌላ ትርጉም ሊኖረው አይችልም። የውሃ ጥምቀትም ሆነ ሌሎች በራሳቸው መልካም የሆኑ ነገሮች፣ ከእግዚአብሔር ጋር እርቅን ፈጽመን የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ከክርስቶስ የመስቀል ስራ ጋር ተደምረው የሚያስፈልጉ እነደሆኑ ማሰብ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን የክርስቶስን ሞት ከንቱ ማድረግም ጭምር ነው (ገላቲያ 2:21)። የክርስቶስ ሞት ብቻውን (ያለምንም ሌላ ተጨማሪ ነገር) ለሃጢአታችን አስፈላጊ የሆነውን ክፍያ ሁሉ ፈጽሟል (ሮሜ 5:8፤ 2ቆሮንቶስ 5:21)። ይህንን በክርስቶስ ስቃይ የተገኘ የእግዚአብሔር ነጻ ስጦታ ያራሳችን የምናደርግበት ብቸኛ መንገድ ደግሞ ማመን እንደሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ማእከላዊ ትምሕርት ነው (ዮሐንስ 3:16፤ የሐዋሪያት ስራ 16:31፤ ኤፌሶን 2:8-9)። እናም የውሃ ጥምቀት አማኝ ይህን የእግዚአብሔርን ስጦታ በእምነት ተቀብሎ የሃጢአት ይቅርታን ካገኘና የዘላለም ሕይወትን ከተቀበለ በኋላ ያሚፈጽመው የመታዘዝ ተግባር እንጂ ለመዳን ብሎ ያሚያደርገው ስርዐት አይደለም (ሐዋሪያት ስራ 8:36-37)።

በእርግጥ በአንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ላይ ጥምቀት ለመዳን የምንፈጽመው ተግባር እንደሆነ የሚመስሉ አገባቦችን እናይ ይሆናል። ሆኖም ግን፣ መጽሐፍ ቅዱስ መዳን የሚገኝበትን መንገድ በአጠቃላዩ አውድ ውስጥ በግልጽ ስለጠቆመን (ዮሐንስ 3:16፤ ኤፌሶን 2:8-9፤ ቲቶ 3:5)፣ እነኚህ ጥቅሶች ከምናስበው ውጪ የተለየ ትርጉም እንዳላቸው ማሰብ ይኖርብናል፤ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ እርስ በእርሱ አይጋጭምና።

የውሃ ጥምቀት ለመዳን አስፈላጊ ቢሆን ኖሮ ቅዱስ ጳውሎስ ለምን “…ከቀርስጶስና ከጋይዮስ በቀር ከእናንተ አንድን እንኳ ስላላጠመቅሁ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ” ይላል? (1ቆሮንቶስ 1:14)። ለምን “ለማጥመቅ ክርስቶስ አልላከኝምና፥ ወንጌልን ልሰብክ እንጂ…” ይላል? (1ቆሮንቶስ 1:17)። የውሃ ጥምቀት ለመዳን አስፈላጊ ነገር ከሆነ እንዴት ቅዱስ ጳውሎስ ባለማጥመቁ እግዚአብሔርን ያመሰግናል? እንዴትስ “ክርስቶስ ለማጥመቅ ስላልላከኝ አመሰግናለሁ” ይላል? እንዴትስ ወንጌል ማለት ምን ማለት እንደሆነ ባብራራበት በዚሁ መልክቱ ላይ ጥምቀትን ሳያካትት ሊያልፍ ይችላል (1ቆሮንቶስ 15:18)? ቅዱስ ጳውሎስ የውሃ ጥምቀት ለመዳናችን አስፈላጊ መሆኑን እያወቀ እነዚህን አረፍተ ነገሮች ተናግሮ ከሆነ፣ እያለ ያለው “ስላልዳናችሁ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ” ነው። ይህ ከአንደበቱ እንደማይወጣ ሁላችንን የሚያስማማ ሃሳብ ከሆነ እንግዲያው ቅዱስ ጳውሎስ እየተናገረ ያለው ከእግዚአብሔር ፍርድ አምልጠን የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ጥምቀት አስፈላጊ ነገር አለመሆኑን ነው።

መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የሕይወትዎ ጌታ በማድረግ ቀሪው ዘመንዎን ለመኖር ወስነው ከሆነ፣ ይህንን ሊንክ በመጫን ስምዎንና የኢ-ሜይል አድናሻዎን ይላኩልንና፣ ለመንፈሳዊ ሕይወት እድገትዎ የሚቻለንን ሁሉ እገዛ እናደርግሎታለን።

Exit mobile version