Site icon

የውሃ ጥምቀት

ኢየሱስ በእርሱ የሚያምኑትን ሁሉ በውኃ እንዲጠመቁ አዟል፡፡ “ኢየሱስም ቀረበና እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ። እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ …” ማቴዎስ 28:18-20፣ በተጨማሪ ሐዋ. 2፡ 38-41 ተመልከት። 

“መጠመቅ” ማለት “ሙሉ በሙሉ መስመጥ ማለት ነው”። አንድ ሰው ሃጢአተኛ መሆኑን አውቆ ንስሐ ከገባ እና ኢየሱስ የሞተው ስለ እርሱ እንደሆነ ካመነ፣ ውሃ ወዳለበት ስፍራ ተወስዶ የሰው ምስክር ባለበት ስፍራ የውሃ ጥምቀት ሊያደርግ ይገባዋል፡፡ ለምን ይሆን አማኞች ይህን ስርአት እንዲፈጽሙ ኢየሱስ ያዘዘው? 

ሀ) የውሃን ጥምቀትን መረዳት

የውሃ ጥምቀት ምን እንደ ሆነ መረዳት ለአሸናፊ እና ነፃ የወጣ ክርስቲያናዊ ሕይወት ቁልፍ ነው፡፡ አማኙ ውኃው ውስጥ መግባቱ እና መውጣቱ በአማኙ ሕይወት ውስጥ ለተከናወነው መንፈሳዊ ነገር ስዕላዊ (አካላዊ) መግለጫ ነው፡፡ 

ለ) ክርስቶስ ያደረጋቸው አራት ታላቅ ሥራዎች በውሃ ጥምቀት ሲገለጡ

“ከእንግዲህ የኀጢአት ባሮች እንዳንሆን፣ የኀጢአት ሰውነት እንዲሻር አሮጌው ሰዋችን ከእርሱ ጋር እንደ ተሰቀለ እናውቃለን፤ ምክንያቱም የሞተ ከኀጢአት ነጻ ወጥቶአል።”  (አ.መ.ት. ሮሜ 6፡6-7)

“ወይስ ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ የተጠመቅን ሁላችን ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ እንደ ተጠመቅን አታውቁምን? እንግዲህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሙታን እንደ ተነሣ እንዲሁ እኛም በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ፥ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን።” (ሮሜ 6፡3-4)

“እንግዲህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሙታን እንደ ተነሣ እንዲሁ እኛም በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ፥ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን። ሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን፤”

“በሚመጡ ዘመናትም በክርስቶስ ኢየሱስ ለእኛ ባለው ቸርነት ከሁሉ የሚበልጠውን የጸጋውን ባለ ጠግነት ያሳይ ዘንድ፥ ከእርሱ ጋር አስነሣን በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን።” ኤፌ 2፡6-7 በተጨማሪ ቆላስይስ 3፡1 ን ተመልከት

ሐ) የውሃ ጥምቀት፣

የቀበር ስነሥርዐት የሚካሄደው ግለሰቡን ለመግደል አይደለም፡፡ ግለሰቡ አስቀድሞ ስለሞተ ለቀብር እንጂ፡፡

አሮጌው ማንነትህ በክርስቶስ ሆኖ “ስለሞተ” ይህን አሮጌ ሕይወት በ ውሃ ጥምቀት ምሳሌነት ትቀብረዋለህ ማለት ነው፡፡ 

በክርስቶስ አዲስ ፍጥረት እንደሆንክ ከውሃው ውስጥ በመውጣትህ ትመሰክራለህ/ትገልጣለህ፡፡ 

“ነገር ግን ከክርስቶስ ጋር ከሞትን ከእርሱ ጋር ደግሞ በሕይወት እንድንኖር እናምናለን፤ ክርስቶስ ከሙታን ተነሥቶ ወደ ፊት እንዳይሞት ሞትም ወደ ፊት እንዳይገዛው እናውቃለንና። መሞትን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ለኃጢአት ሞቶአልና፤ በሕይወት መኖርን ግን ለእግዚአብሔር ይኖራል። እንዲሁም እናንተ ደግሞ ለኃጢአት እንደ ሞታችሁ፥ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ሆናችሁ ለእግዚአብሔር ሕያዋን እንደ ሆናችሁ ራሳችሁን ቁጠሩ።” ሮሜ 6፡8-11

መ) ሁለቱ መንግሥታት

“እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፥ ቤዛነቱንም እርሱንም የኃጢአትን ስርየት ወዳገኘንበት ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት አፈለሰን።” ቆላስይስ 1፡13-14

በዚህች አለም ውስጥ የሚወለዱ ሰዎች ሁሉ በጨለማው አለም መንግሥት ውስጥ ነው የሚወለዱት፤ በፍጥረታቸው (በውልደታቸው) የአምባገነኑ ሰይጣን ባሪያዎች ናቸው፡፡ በሞት ካልሆነ በቀር በሌላ በምንም አይነት መንገድ ከዚህ የጨለማ መንግሥት ማምለጥ (በውጣት) አይቻልም፡፡ እንዲሁም፣ በዳግም ልደት ካልሆነ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግስት መግባት አይቻልም፡፡ ይህ እንዲሆን ክርስቶስ ሞታችንም ሕይወታችንም (ዳግም ልደታችንም) ሆኖልናል፡፡ ይህንን እውነት በጥምቀት እንመሰክራለን (እናውጃለን)፡፡  

ሠ) ሁለቱ ዘሮች

ሁለት መንግሥታት እንዳሉ ሁሉ በሁለቱ መንግሥታት ውስጥ የሚኖሩ ሁለት የሰው ዘሮች አሉ፡፡ የአዳም ዘር በጨለማው መንግሥተ ውስጥ የሚኖረው የሰው ዘር ሲሆን የአዲሱ ፍጥረት (የሰው የሰው ዘር) ደግሞ በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ የሚኖረው ነው፡፡ 

“ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ…” 1 ቆሮ 15፡22 በተጨማሪ ሮሜ 5:12 ን ተመልከት፡፡ አዳም የሰው ዘር ሁሉ አባት ነው፡፡ የአዳም ሃጢአት እርሱን እና ዘሩን (እኛን ሁላችንን) ከእግዚአብሔር ለይቶናል፡፡ በእርሱ መተላለፍ ምክንያት የእርሱን አመጸኛ እና የተበላሸ ተፈጥሮን ወርሰናል፤ ሞት ወደእኛ የደረሰውም በእርሱ በኩል ነው፡፡ የአዳም ዘሮች “አዳማውያን” ይባላሉ፡፡  

“ገና ደካሞች ሳለን ክርስቶስ ዘመኑ ሲደርስ ስለ ኃጢአተኞች ሞቶአልና” ሮሜ 5:6፡፡ እግዚአብሔር ሃጢአትን ለማስወገድ የወሰደው እርምጃ ይህን በሃጢአት የተበከለውን የአዳም ዘር ማሻሻል ሳይሆን ፈጽሞ በማጥፋት ሌላ አዲስ ዘርን ማምጣት ነበር፡፡ ኢየሱስ ኋለኛው አዳም ነው፡፡ ኢየሱስ ወደዚህች አለም የመጣው እንደ መጨረሻው የአዳም ዘር እና እንደመጀመሪያው አዲስ የሰው ዘር በመሆን ነበር፡፡ በመስቀል ላይ ሲሰቀል እንደመጨረሻው የአዳም ዘር ሆኖ ነበር የተሰቀለው፡፡ በመስቀል ላይ ሲሞት የአዳም ዘርና የዘሩ ሃጢአታዊ ተፈጥሮ አብሮ ሞቷል፡፡ እግዚአብሔር የወደቀውን የሰው ዘር በኢየሱስ ውስጥ ሆኖ እንዲሞት አድርጓል፡፡ የአዳም ዘር በክርስቶስ ሆኖ በመስቀል ላይ እንዲሞት ተደርጓል፡፡ 

“ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ እንዲሁ ሁሉ በክርስቶስ ደግሞ ሕያዋን ይሆናሉና።” 1ኛ ቆሮ 15፡22 በእርሱ አዲስ ፍጥረት ይፈጠር ዘንድ ኢየሱስ ወደምድር የመጣው እንደ እግዚአብሔር ሁለተኛ ሰው ሆኖ ነው፡፡ ኢየሱስ ከሞት የተነሳው እንደ ኋለኛው (መጨረሻ) አዳም ሆኖ አይደለም፤ የአዲስ ፍጥረት ራስ እደሆነ ሁለተኛ ሰው እንጂ፡፡

“እንዲሁ ደግሞ፦ ፊተኛው ሰው አዳም ሕያው ነፍስ ሆነ ተብሎ ተጽፎአል፤ ኋለኛው አዳም ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆነ። ነገር ግን አስቀድሞ ፍጥረታዊው ቀጥሎም መንፈሳዊው ነው እንጂ መንፈሳዊው መጀመሪያ አይደለም። የፊተኛው ሰው ከመሬት መሬታዊ ነው፤ ሁለተኛው ሰው ከሰማይ ነው። መሬታዊው እንደ ሆነ መሬታውያን የሆኑት ደግሞ እንዲሁ ናቸው፥ ሰማያዊው እንደ ሆነ ሰማያውያን የሆኑት ደግሞ እንዲሁ ናቸው። የዚያንም የመሬታዊውን መልክ እንደ ለበስን የሰማያዊውን መልክ ደግሞ እንለብሳለን።” 1 ቆሮ 15፡45-49)

“ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል።” 2ቆሮ 5፡17 በተጨማሪ ኤፌ 2፡10 ን ይመልከቱ

በውሃ ጥምቀት ለወዳጆቻችንና ለእድምተኞቻችን ሁሉ የምናውጀው ነገር ከዚህ ቀን ጀምሮ የአዳም ዘር እና የጨለማው መንግሥት አካል አለመሆናችንን ነው፡፡ በክርስቶስ አዲስ ፍጥረት ነን፤ መኖሪያችንም በእግዚአብሔር መንግስት ውስጥ ነው፡፡ 

ውሳኔዪ

በዚህ ጥናት አማካኝነት፣ አሮጌ ሕይወቴ ከኃጢያቱ እና ከሚያስከትለው ፍርድ ጋር ከክርስቶስ ጋር እንደሞተ አውቂያለው፡፡ አሁን በኢየሱስ ትንሣኤ ምክንያት አዲስ ሕይወት እደተቀበልኩም ተረድቻለሁ። የውሃ ጥምቀት የእነዚህ መንፈሳዊ እውነቶች አካላዊ መገለጫ ስለሆነ በውሃ ለመጠመቅ እና ይህንን እውነት ለሌሎች ለማካፈል ቃል እገባለሁ።

ምንጭ፣ The Shepherd Staff

ትርጉም፣ አዳነው ዲሮ

Exit mobile version