የደኅንነት በረከቶች – ክፍል አንድ
በዛሬው ትምህርታችን እግዚአብሔር ስለሚሰጠን የደኅንነት በረከተች እናጠናለን። እንደሚታወቀው እኛ በኃጢአት የተወለድን ከመሆናችንም በላይ እያንዳንዳችን ብዙ የኃጢአት ተግባራትን ስለምንፈጽም በኃጢአታችን ሙታን ነን። ስለዚህ እግዚአብሔር በሕይወታችን ውስጥ ጣልቃ ገብቶ ከኃጢአታችንና ከሚያስከትልብን ክፉ መዘዝ ሁሉ ሊያድነን ይገባል። ትዝ እንደሚላችሁ ደኅንነት እንደሚያስፈልገን በትምህርት 11ና 12 ላይ አጥንተናል። እግዚአብሔር እኛን መርጦ ወደ ራሱ ሊያቀርበን በማለት በክርስቶስ ሞት አማካይነት ለደኅንነታችን አስፈላጊ የሆነውን ነገር ሁሉ ፈጽሞልናል። በትምህርት 13ና 14 ላይ እግዚአብሔር ደኅንነትን ሊሰጠን ስለፈጸመው ተግባር አጥንተናል። ለደኅንነት የበቃነው እግዚአብሔር በራሱ ተነሣሽነት ባዘጋጀው ዕቅድ ማለትም ባደረገልን ምርጫና ጥሪ ሲሆን፣ ከዚሁ ጋር አብሮ የሚሄደው ደግሞ የእኛ ንስሐ መግባትና ወደ እግዚአብሔር መመለስ፥ እግዚአብሔር እኛን ለማዳን ሲል በኢየሱስ ሕይወት፥ በሞቱና በትንሣኤው የፈጸማቸውን ተግባራት በማመን ምላሽ መስጠታችን ነው። ስለዚህ የደኅንነት መንገድ በትምህርት 15 እና 16 ላይ መማራችን ትዝ ይለናል። በንስሐ ወደ እርሱ ተመልሰን በክርስቶስ በምናምንበት ጊዜ እግዚአብሔር የደኅንነቱን በረከቶች በላያችን ላይ ያፈስሳቸዋል። ታዲያ እነዚህ በረከቶች ምንድን ናቸው? በዚህ ሳምንት ውስጥ እነዚህን በረከቶች ማጥናት እንጀምራለን።
ዳግም መወለድ፥ ክፍል 1
በትምህርት 11ና 12 ትምህርቶቻችን ውስጥ በዓለም ላይ ያሉ ሰዎች ሁሉ ኃጢአተኞች ሆነው እንደ ተወለዱና ሁላቸውም ኃጢአትን እንደሚሠሩ አስተውለናል። ከኃጢአታችን የተነሣ፥ ሁላችንም ከእግዚአብሔር የተለየን በመንፈሳችንም የሞትንና የታወርን ነበርን። ይህ ኃጢአታችንም በእኛና በእኛ አካባቢ ባሉ ሰዎች ሁሉ ሕይወት ላይ ሞትንና ጥፋትን አስከትሏል። ስለዚህ ከዚህ አሰቃቂ ከሆነ የኃጢአት መዘዝ ለመዳን እያንዳንዳችን አዲስ ሕይወትን እንሻለን። እንደዚሁም አርጌውና ኃጢአታዊው ተፈጥሮአችን ሙሉ በሙሉ ወደ አዲስ ተፈጥሮ ሊለወጥ ይገባል። በመንፈሳችን ሙታን ስለሆንን፣ መንፈሳዊ ሕይወትን መቀበል አለብን። እግዚአብሔር የሚሰጠን የመጀመሪያው የደኅንነት በረከት ይህ አዲስ ሕይወት ነው። እግዚአብሔር ደኅንነትን በሚሰጠን ጊዜ ሕይወታችንን ይለውጠውና የተሟላ አዲስ ተፈጥርን ይሰጠናል። መንፈሳዊ ሕይወትን የተላበስን አዲስ ሰዎች ያደርገናል። እግዚአብሔር በዚህ አኳኋን የሚሰጠን አዲስ ሕይወት «ዳግም መወለድ» ይባላል።
ጥያቄ፦ ዮሐ 3፡1-8 አንብብ። ኒቆዲሞስ ስለ ኢየሱስ ያስተዋለው ምን ነበር? (ቁ 2)
ጥያቄ፡- ኢየሱስ ኒቆዲሞስ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመግባት እንዲችል ምን ማድረግ እንዳለበት ነገረው? (ቁ. 3)
ጥያቄ፡- ኒቆዲሞስ ኢየሱስ የተናገረውን ያላስተዋለው እንዴት ነበር? (ቁ. 4)
ጥያቄ፡- ኢየሱስ «ዳግም መወለድ» ብሎ ለተናገረው ቃል ምን ማብራሪያ ሰጠ? (ቁ 5)
ጥያቄ፡- ሀ) የሥጋዊ ልደት ውጤት ምንድን ነው? ለ) የመንፈሳዊ ልደትስ ውጤት ምንድን ነው? (ቁ. 6)
ጥያቄ፡- መንፈስ የሰውን ሕይወት በመለወጥ ረገድ እንዴት ባለ ሁኔት በነፋስ ይመሰላል?
ጥያቄ፡- ዘሌዋ. 17፡17-19 አንብብ። ሀ) እንደዚህ ክፍል አነጋገር እስራኤላውያን ከኃጢአታቸው የሚነጹት እንዴት ነው? ለ) መዝ. 50፡7 አንብብ። ዳዊት እግዚአብሔር እንዴት እንደሚያነጻው ተናገረ?
ጥያቄ፡- ኢሳ 55፡1 አንብብ። እስራኤላውያን በልተውና ጠጥተው እንዲደሰቱ የተጠሩት ወዴት ነው? ለ) ዘካ. 14፡8-9 አንብብ። እግዚአብሔር በመላው ምድር ላይ በሚነግሥበት ጊዜ ከኢየሩሳሌም ምን ይመነጫል? ሐ) ኤር. 2፡13 አንብብ። የእስራኤል የሕይወት ውኃ ምንጭ ማን ነው?
ጥያቄ፡- ኢሳ. 44፡1-3 አንብብ። እስራኤላውያን በእግዚአብሔር የተመረጡ የተለዩ ሕዝብ እንደ መሆናቸው ምን ሁለት ነገሮች ይፈስሱባቸዋል?
ጥያቄ፡ ሕዝ 36፡24-27 አንብብ። እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ወደ ምድራቸው መልሶ በሚያመጣቸው ጊዜ ምን ያደርግላቸዋል?
ጥያቄ ኢሳ. 32፡15 አንብብ። የጽድቅ ንጉሥ በሚነግሥበት ጊዜ እግዚአብሔር ለእስራኤል ሕዝብ ምን ያደርግለታል?
እግዚአብሔር ስለሚሰጠን ስለ አዲሱ ሕይወት ዘርዝሮ የሚያስረዳን ክፍል በዮሐ 3፡1-21 የተጻፈው ነው። ዛሬ መላው ትምህርታችን በዚህ ርእስ ላይ ያተኮረ ይሆናል። የዮሐንስ ምዕራፍ 3 በኢየሱስና በፈሪሳዊው በኒቆዲሞስ መካከል የተካሄደ ውይይት ዘገባ ነው። ኒቆዲሞስ ወደ ኢየሱስ የመጣው ኢየሱስ የፈጸማቸውን ታምራት ስላየና የበለጠ ስለ እርሱ ማወቅ ስለፈለገ ነበር። በዮሐ 3፡2 ውስጥ፣ ኒቆዲሞስ ስለ ኢየሱስ ታምራት የጠቀሰ ቢመስልም፥ እውነታው ግን በተዘዋዋሪ መንገድ አንተ ማን ነህ? በምትፈጽማቸው ተአምራት ላይ በመመሥረት ስለ ራስህ ምን ትላለህ? የሚሉ ጥያቄዎችን ማንሣቱ ነበር። ኢየሱስ ግን እርሱ ለጠየቃቸው ጥያቄዎች መልስ ከመስጠት በላይ አድርጓል። እንዲያውም ኒቆዲሞስ አዲስ ልደት እንደሚያስፈልገው ወዲያው በመንገር አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ጥሎታል። ምንም እንኳን እርሱ መንፈሳዊ ግምት መውሰድ ለምሳሌ፥ ኢየሱስ ከእግዚአብሔር መሆኑን መረዳት) የሚችል ፈሪሳዊ አድርጎ ራሱን ቢቆጥርም፥ ለእግዚአብሔር መንግሥት ገና ያልበቃ ሰው ነበር። ማንም ቢሆን ዳግም ካልተወለደ በስተቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይም ሆነ ሊነዘብ አይችልም።
1. «ዳግም መወለድ» ማለት ምን ማለት ነው?
ኢየሱስ ኒቆዲሞስን ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ለመገንዘብም ሆነ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመግባት ዳግም መወለድ አለብህ ሲለው ምን ማለቱ ነበር? ወደ አማርኛ (ዳግም፥ ዳግመኛ) በአዲሱ ትርጉም (እንደገና) ተብሎ የተተረጎመው የግሪኩ ቃል ሁለት ትርጉሞች አሉት። እንደገና ወይም ከላይ የሚል ፍቺ ሊኖረው ይችላል። ዮሐንስ በወንጌሉ በሌሎች ክፍሎች ውስጥ ይህንኑ አሳብ ለመግለጽ «ከላይ» በሚለው ቃል ይጠቀማል ( ዮሐ. 3፡31፤ 19፡11፥23)፣ ይህንንም ሊል ምናልባት «ከላይ መወለድ» እንዳለብን ለመግለጽ ሊሆን ይችላል። አንድ ሰው በሥጋ ከተወለደ በኋላ «ከላይ መወለድ» ካለበት፥ ጻግሞ መወለድ ይኖርበታል ማለት ነው። ስለዚህ ኢየሱስ ኒቆዲሞስን ዳግም ልትወለድ» ይገባሃል በሚልበት ጊዜ፣ እነዚህ ሁለት ልደቶች በአሳቡ የነበሩ ሳይሆን አይቀርም። ስለዚህ ኢየሱስ ለኒቆዲሞስ የነገረው፣ ሥጋዊ ልደትህ በቂ ስላልሆነ፥ ሁለተኛ ጊዜ መወለድ አለብህ፥ ይህም ከላይ መወለድ ነው» የሚል ነበር። ዮሐንስ ቀደም ሲል በወንጌሉ ደም ውስጥ ለአንባቢያኑ፥ ኢየሱስን የተቀበሉትና በስሙም ያመኑ ሁሉ ከእግዚአብሔር ዘንድ በመወለድ የእግዚአብሔር ልጆች ሆነዋል ሲል ነግሮአቸዋል (ዮሐ 1፡12-13)። አንባቢዎቹም ዮሐ 3፡3። በሚያነቡበት ጊዜ እነዚህን ቃላት እንዲያስታውሱ ይፈልጋል። ከእግዚአብሔር መወለድና የእግዚአብሔር ልጅ መሆን ከላይ መወለድ ከሚለው ጋር አንድ ነው።
ሆኖም፣ ኒቆዲሞስ የሰማው ትምህርት አልገባውም ነበር። ለእርሱ የገባው ኢየሱስ ስለ አንዳች ዳግመኛ ሥጋዊ ልደት የሚናገር መስሎት ነው። ከዚህም የተነሣ ሰው ዳግመኛ ወደ እናቱ ማኅፀን ገብቶ መወለድ ይችላልን ብሎ ኢየሱስን ጠየቀ።
ኢየሱስም የሚናገረው ስለ ዳግመኛ ሥጋዊ ልደት አለመሆኑን በመግለጽ ለኒቆዲሞስ መለሰለት። «ሰው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ የሚችለው ከውኃና ከመንፈስ በሚወለድበት ጊዜ ብቻ ነው። ስለዚህ ኢየሱስ ለኒቆዲሞስ የነገረው የዘላለም ሕይወትን ለማግኘት በመንፈስ ቅዱስ መንጻት እንዳለበት ነው።
2. «ከውኃና ከመንፈስ መወለድ» ማለት ምን ማለት ነው?
ኢየሱስ ኒቆዲሞስ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንድትገባ «ከውኃና ከመንፈስ መወለድ አለብህ» ባለው ጊዜ ምን ማለቱ ነበር? ምላሽ ይሆናሉ ተብለው የሚታሰቡ ቢያንስ አራት አሳቦች ይቀርባሉ፦
1) አንዳንዶቹ እንደሚያስቡት ኢየሱስ ስለ ውኃ መጥቀሱ ስለ ክርስቲያኖች ጥምቀት ሲናገር ነው ይላሉ። ይህን የሚሉት ሰዎች አንድ ሰው ለመዳን በእምነት ከመንፈስ ቅዱስ መወለድና መጠበቅ አለበት ይላሉ። ምንም እንኳ ብዙዎች ይህን ጥቅስ በዚህ ዓይነት ግንዛቤ ቢቀበሉትም፥ የክፍሉን ዓውደ አሳብ በተመለከተ ይህ ጥሩ ንዛቤ አይደለም። ኢየሱስ ሞቶ እስከሚነሣ ድረስ ክርስቲያናዊ የጥምቀት ሥርዓትን አልመሠረተም ነበር (ማቴ. 28፡19-20)። በኢየሱስና በኒቆዲሞስ መካከል የተካሄደው ይህ ውይይት ከኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ በፊት ቀደም ብሎ ስለነበር፣ ኢየሱስ ስለ ክርስቲያናዊ ጥምቀት ነግሮት ቢሆን ኖር ኒቆዲሞስ አሳቡ ሊገባው የሚችል አይሆንም ነበር። በቁጥር 10 ውስጥ ኢየሱስ ኒቆዲሞስ የእስራኤል መምህር እንደ መሆኑ መጠን የነገረውን ሊገነዘብ ይገባው እንደ ነበር ያሳስበዋል። ኢየሱስ መጠመቅ እንደሚያስፈልግ እስከ ሞቱና ትንሣኤው ድረስ ትእዛዝ ስላልሰጠ፣ እርሱ የሚናገረው ለኒቆዲሞስ ይገባዋል ብሎ ሊጠብቅ አይችልም ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ ስለ ክርስቲያናዊ ጥምቀት እየተናገረ አልነበረም። ከዚህም በስተቀር፣ የክፍሉ ሙሉ መልእክት ስለ ሥጋዊና መንፈሳዊ ሁኔታ ማነጻጸር ነበር። ኢየሱስ ለኒቆዲሞስ የነገረው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንዲገባ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት የሚፈጸም መንፈሳዊ ልደት እንዲኖረው ነው። ስለዚህ፣ በዚህ ክፍል የተጠቀሰው ስለ ውኃ የሚናገረው ሐረግ በእርግጥ ስለ ክርስቲያናዊ ጥምቀት ነው ለማለት ያስቸግራል።
2) አንዳንድ ሰዎች ደግሞ ኢየሱስ የተናገረው ስለ ዮሐንስ መጥምቁ ጥምቀት ነው ይላሉ። የዮሐንስ ጥምቀት ግን የንስሐ ጥምቀት ነበር (ሉቃስ 3፡3፤ የሐዋ. 19፡6)። ኢየሱስ ስለ ዮሐንስ ጥምቀት ተናግሮ ቢሆን ኖሮ፣ ኒቆዲሞስ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንዲገባ ራሱን አዋርዶ በትሕትና ከኃጢአቱ ንስሐ መግባትና ከመንፈስ መወለድ እንዳለበት በነገረው ነበር። በዚህ አካሄድ ኒቆዲሞስ መንፈሳዊ ልደትን እንዲቀበል የነበረበት ኃላፊነት ንስሐ መግባት ነው። ኢየሱስ የተናገረውን ቃል የምንገነዘብበት አንዱ መንገድ ይህ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ይህ ወሳኝ እሳብም አይደለም። ኢየሱስ «ከውኃ ስለ መወለድ» በጠቀሰ ጊዜ ኒቆዲሞስ ስለ ዮሐንስ ጥምቀት ወዲያው ትዝ አለው ማለትም አይቻልም።
3) አንዳንዶቹ ደግሞ ኢየሱስ ሥጋዊውንና መንፈሳዊውን ልደት ያነጻጸረ ይመስላቸዋል። «ከውኃ የተወለደ» የሚለው ሐረግ የሕፃንን ሥጋዊ ውልደት ሊያመለክት ይችላል። ሕፃን ከመወለዱ በፊት ሕፃኑን በእናቱ ማኅፀን ውስጥ ሸብልሎ ያቆየው ከረጢት ይከፈታል። ከዚያም የእንሽርት ውኃው ከእናቱ ማኅፀን በብልቷ በኩል ወደ ውጭ ይፈሳል። ይህ አተረጓጎም ትክክል ከሆነ፥ ኢየሱስ ለኒቆዲሞስ የተናገረው፣ «ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመግባት በሥጋ መወለድ ብቻ አይበቃህም፤ ከመንፈስ ዳግም መወለድ ያስፈልግሃል፤ እንዲሁም የዘላለም ሕይወትን ለማግኘት በሥጋም ሆነ በመንፈስ ከላይ መወለድ አለብህ» የሚል ነው ማለት ነው። ይህ አሳብ በሚከተለው በቁጥር 6 ላይ ባለው ጥቅስ የተደገፈ ነው። ጥቅሱም፥ «ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፥ ከመንፈስ የተወለደ መንፈስ ነው» የሚል ነው። ኢየሱስ ለኒቆዲሞስ ሥጋዊ ልደት ሥጋዊ ሕይወትን ብቻ እንደሚሰጥ ካስረዳው በኋላ፥ ቀጥሎ መንፈሳዊ ሕይወትን አግኝቶ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመግባት እንዲችል በመንፈሳዊ ልደት ዳግም መወለድ እንዳለበት አበክሮ ነግሮታል። እንግዲህ ይህ አገላለጽ ከክፍሉ ጋር በጣም ይስማማል። ግን ደግሞ ሌላ ችግሩ ኢየሱስ በነበረበት ታሪክም ሆነ ሳሕል ውስጥ «ከውኃ መወለድ» የሚለው ሐረግ ሥጋዊ ልደትን እንዲገልጽ ሆኖ በጥቅም ላይ ስለ መዋሉ ማስረጃ የለንም። ምናልባትም ኢየሱስ በዚህ ክፍል ሥጋዊ ልደትን ለማሳየት ይህን አገላለጽ ተጠቅሞ ይሆናል። ነገር ግን ኢየሱስ በተጠቀመበት በዚህ አገላለጽ ሌሎችም በጊዜው የነበሩ ሰዎች ተጠቅመውበት ነበር ለማለት እስከ ዛሬ ድረስ የተመዘገበ ማስረጃ የለንም። ስለዚህ ይህ አተረጓጎም ከይሆናል ግምት ሌላ ሊዘል አይችልም።
4) አንዳንዶች ደግሞ «ውኃና መንፈስ» የተባሉት ቃላት በአንድ አሳብ ተቀናጅተው «የመንፈስ ቅዱስ ማንጻት» ሊባሉ ይችላሉ ይላሉ። በግሪኩ ጥቅስ ውስጥ «ውኃ» እና «መንፈስ» የሚሉት ቃላት «ከ» በሚል አንድ መስተዋድዳዊ ቃል ተያይዘው አንድ ቃል ይሆናሉ። ይህም ኢየሱስ «ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመግባት ከውኃ-ከመንፈስ መወለድ አለባችሁ እንዳለ ያክል ነው። ለመሆኑ ኢየሱስ «ከውኃ-ከመንፈስ» ሲል ምን ማለቱ ነበር? ኒቆዲሞስ ብሉይ ኪዳንን ደህና አድርጎ የሚያውቅ ሰው ነበር። ኢየሱስ በኋላ ለኒቆዲሞስ ሲናገር ስለዚህ ስለ ሁለተኛው ከላይ ስለ መወለድ ማወቅ ነበረብህ ስላለው (ቁ 10)፥ የዚህን ሐረግ ትርጉም ከብሉይ ኪዳን መፈለግ አለብን። ውኃ በብሉይ ኪዳን ውስጥ በዘይቤአዊ ምሳሌ በሚቀርብበት ጊዜ ከኃጢአት መንጻትንና ከዚያም የሚመጣውን የእግዚአብሔርን መንግሥት በረከቶች ያመለክታል። ለምሳሌ ያህል፥ በዘኁ. 17፡17-19 ባለው ክፍል ከኃጢአት የማንፃት ተግባር በሂጾጵ በሚረጭ ውኃ አማካይነት ይሰጥ ነበር። በመዝ. (51)፡7 ላይ ጻዊት በሂኦጵ በሚረጭ ውኃ ከኃጢአቱ እንዲነጻ ይጸልያል። በኢሳ. 55፡1-5 ውስጥ በዳዊት በኩል የተሰጠው ተስፋ ወደ ውኃው መጥተው በደስታ እንዲበሉና እንዲጠጡ የተላለፈው ጥሪ እንደ ተፈጸመ ይናገራል። በዘካ 14፡8 ላይ እንደተነገረው፥ «የጌታ ቀን ሲመጣ» ጌታም ንጉሥ ሆኖ ሲመለስ፣ «የሕይወት ውኃ» ከኢየሩሳሌም ምሥራቅና ምዕራብ ይፈልቃል ይላል። በኤር. 2፡13 እና 17፡13 ውስጥ እግዚአብሔር ራሱ የእስራኤል «የሕይወት ውኃ ምንጭ» ተብሎ ተጠርቷል። ከዚህም በተጨማሪ፣ ብዙ የብሉይ ኪዳን ክፍሎች መንፈስ ቅዱስን ከውኃ ጋር በተለየ ሁኔታ በማገናኘት ከኃጢአት ማንጻት የሚችል ልብን የሚለውጥ፥ እንደዚሁም የሚመጣውን የእግዚአብሔርን መንግሥት በረከቶች የሚገልጥ እርሱ መሆኑን ያመለክታሉ። በኢሳ. 44፡1-5 ውስጥ የውኃ መፍሰስ ሁኔታ ከመንፈስ ቅዱስ መፍሰስ ሁኔታ ጋር አቻ በመሆን ተጽፎአል። ይህ ውኃና ይህ መንፈስ የመጣው የእግዚአብሔር ባሪያ ወደሆነውና ወደተመረጠው ወደ እስራኤል ነው። ይህም እስራኤል የእግዚአብሔር ስም ያለውና የእርሱ የግሉ መሆኑንም ይገልጻል። በሕዝ. 36፡24-29 ውስጥ እግዚአብሔር ለእስራኤል መንግሥትን መልሶ ሊያቆም ከርኩሰታቸው እንዲነጹ በውኃ እንደሚረዳቸው ልባቸውን የሚለውጥ አዲስ መንፈስ እንደሚሰጣቸውና ሕጉን እንዲጠብቁ መንፈሱን በላያቸው ላይ እንደሚያኖር ተስፋ ይሰጣል። እርሱም ከርኩሰታቸው ያድናቸዋል። በኢሳ. 32፡15 ውስጥ የእግዚአብሔር የጽድቁ ንጉሥ በሚነግሥበት ጊዜ እግዚአብሔር መንፈሱን እንደ «ውኃ» እንደሚያፈስና ምድረ በዳው እንደሚለመልም ተስፋ ይሰጣል። እንደዚሁም በኢዩ 2፡28-32 እንደተጻፈው መንፈስ የእግዚአብሔር መንግሥት መምጣት ምልክት ሆኖ እንደ ውኃ ይፈስሳል። ኢየሱስ ለኒቆዲሞስ ስለ ውኃና ስለ መንፈስ በነገረው ጊዜ ስለ እነዚህ የብሉይ ኪዳን ክፍሎች እንዲያስብ በማለት ነበር። አንድ ሰው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንዲገባ በሞንፈስ ቅዱስ ነጽቶ መለወጥ ይገባዋል።
«ከውኃና ከመንፈስ» የመወለድን ትርጉም በተመለከተ ይህ የመጨረሻው አሳብ ስለ ክፍሉ ከሁሉም የላቀ ግንዛቤን ያንጸባርቃል። ኢየሱስ «ዳግም ስለ መወለድ» ለኒቆዲሞስ ነገረው። እግዚአብሔር በመንፈስ ቅዱስ የማንጻት ተግባር አማካይነት ሕይወቱ በፍጹም መለወጥ እንዳለበት ነበር። በዚህ በመንፈስ ቅዱስ የማንጻት ተግባር መንጻትን አግኝተው ሕይወታቸው የተለወጠላቸው ብቻ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ይገባሉ።
የሰዎች ሕይወት ከመንፈስ ቅዱስ ዳግም በመወለድ እንዲለወጥ ለምን አስፈለገ? ለዚህ ምክንያቱ የሥጋዊና የአካላዊ ልደት ውጤት አካላዊ ሰውን ብቻ የሚያስገኝ በመሆኑ ነው። መንፈስ ቅዱስ ብቻ አዲሱንና መንፈሳዊ ተፈጥር ያለውን ሰው ሊፈጥር ይችላል። ሰዎች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዲችሉ አዲስ ሕይወትን ሊሰጣቸው የሚችል መንፈስ ቅዱስ ብቻ ነው። ኢየሱስ ለኒቆዲሞስ ያስተምር የነበረው ከሕዝ 36፡24-27 ካለው ክፍል መገንዘብ የነበረበትን እውነት ነበር። ምክንያቱም ሰዎች ሁሉ፣ እንደ ኒቆዲሞስ ያሉ ሃይማኖተኞች ሰዎች እንኳ፣ ኃጢአተኛ የሆነ ልብ ስላላቸው፣ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመግባት የልብ ለውጥ ሊኖራቸው ይገባል። የእግዚአብሔርን መንግሥት ከማወቃቸውም ሆነ ወደ እርሱ ከመግባታቸው በፊት የእግዚአብሔር መንፈስ አንጽቶ ወደ አዲስ ሰውነት ሊለውጣቸው ይገባል።
3. አዲስ ልደትን ለማምጣት መንፈስ የሚሠራው እንደ ነፋስ ነው ሲባል ምን ማለት ነው?
ኢየሱስ የሰዎችን ልቦና ለመለወጥ መንፈስ የሚፈጽመው ሥራ እንደ ነፋስ ነው በማለት ገለጻውን ይቀጥላል። ማንም ሰው ነፋስን ለመቆጣጠርና ሙሉ በሙሉ ለመገንዘብ እንደማይችል ሁሉ (በተለይም በአዲስ ኪዳን ዘመን)፥ እንደዚሁም ማንም ሰው የመንፈስን ሥራ ሊገነዘበውም ሆነ ሊቆጣጠረው አይችልም። መንፈስ ቅዱስ በሥልጣኑ ብቻ በሰዎች ሕይወት ውስጥ ሥራውን ይሠራል። ለሰዎች እንዴት አድርጎ አዲስ ሕይወትን በመስጠት እንደሚለውጣቸው መገንዘብ አንችልም። ምንም እንኳን ክርስቶስን እንደ ግል መድኃኒታቸው አድርገው ላልተቀበሉ ሰዎች ብንጸልይም፡ መንፈስ ቅዱስ አዲስ ሕይወትን እንዴት አድርጎ እንደሚሰጣቸው ወይም እንዴት አድርጎ ተግባሩን እንደሚፈጽም መቆጣጠር የእኛ ችሎታ አይደለም። ነገር ግን ነፋስ ሲነፍስ ምን እንደሚያደርግ እንደምንመለከት ሁሉ፥ የመንፈስ ቅዱስንም የሥራ ውጠት እንዲሁ እናያለን። ሰዎች ዳግም በሚወለዱበት ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ለሰዎች የሕይወት ለውጥ ሊያመጣ እናያለን።
ጥያቄ፡- ሀ) መንፈስ ቅዱስ ቀደም ሲል ሊቃወሙት የነበሩትን ሰዎች ወደ ክርስቶስ መልሶ ለማምጣት በሉዓላዊነት መሥራቱን እንዴት ተመለከታችሁት? ለ) መንፈስ ቅዱስ የራሳችሁን ሕይወትና እንደዚሁም ዳግም መወለዳቸውን የምታውቁዋቸውን ሰዎች ሕይወት የመለወጡን ሁኔታ እንዴት ተመለከታችሁት?
ለረጅም ጊዜ ሳይቀበሉት የቆዩትን ሰዎች መንፈስ መልሶ ወደ ክርስቶስ የምጣት ሉዓላዊ ሥራውን ሲሠራ ማየት እንችላለን። ብዙ ክርስቶስን አስቀድመው ይቃወሙ የነበሩና ጠላቶቹ የነበሩ ሰዎችን መንፈስ ቅዱስ በሉዓላዊ ተግባሩ ለውጦ ወደ ክርስቶስ መልሶ እንዳመጣቸው የሚገልጹ ብዙ የታወቁ ገናና ታሪኮች አሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ ለዚህ እውቅ ምሳሌ ነው። ሌሎችም ምሳሌዎች በታሪክ ውስጥ ነበሩ። ፍራንክ , ሞሪሰን የኢየሱስ ትንሣኤ ሐሰት መሆኑን ለማረጋገጥ የሞከረ የእንግሊዝ ጋዜጠኛ ነበር። ከዚህም የተነሣ ጥናቱና ክትትሉ ኢየሱስ በእውነት ከሞት መነሣቱን ስላረጋገጠለት፣ ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ ግል መድኃኒቱ በመቀበል አምኖበታል። መንፈስ ቅዱስ የፍራንክ ሞሪሳንን ሕይወት ለውጦ አዲስ ሰው ለማድረየ በሉዓላዊነት ሠርቷል። እንደዚሁ ጂኦቫኒ ፓፒኒ የተባለ ጣሊያናዊ ምሑር ከሐዲ ስለነበረ በመጻሕፍቱ ውስጥ ክርስትናን አጣጥሎና ዝቅ አድርጎ ይጽፍ ነበር። ነገር ቀን አንድ ጊዜ ከቤተሰቡ ጋር በዕረፍት ስፍራ በነበረ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ጀመረ። በዚህን ጊዜ መንፈስ ቅዱስ የወቀሳ ሥራውን ሠርቶ እንዲመለስ ስላደረገው በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሊያምን ቻለ። ከዚያም በክርስቶስ ስላገኘው ስለ አዲስ እምነቱ ለዓለም ሊያሳውቅ ብሎ መጽሐፍ ጻፈ። የጂኦቫኒ ፓፒኒ ሕይወት አዲስ የሆነው በመንፈስ ቅዱስ ሉዓላዊ ሥራ ነው። ቻርልስ ኮልሰን የተባለ ለፖለቲካ ሥልጣን የቋመጠ አሜሪካዊ ፖለቲከኛ ነበር። አንድ ጊዜ አንድ ክርስቲያን ወጻኢ የሆነ ሰው መሰከረለት። ከዚያም ቻርልስ ክርስቶስን አምኖ በመቀበል የእስረኞች ወንጌላዊ ሆነ፡ ቻርልስ ኮልሰን በመንፈስ ቅዱስ ታላቅ ሥራ የተሟላ አዲስ ሕይወትን ሊያገኝ ቻለ። በኢትዮጵያም ውስጥ በፊት ማርክሲስት ፖለቲከኞች የነበሩና ኋላም ወደ ክርስቶስ ስለተመለሱ ሰዎች ብዙ የሚነገር ታሪክ አለ። እንግዲህ እነዚህ ሁሉ ምሳሌዎች መንፈስ ቅዱስ በሉዓላዊ ሥራው ለማንም ቢሆን በክርስቶስ አዲስ ሕይወትን ሊሰጥ የሚችል መሆኑን የሚያረጋግጡ ናቸው።
ጥያቄ፡- አንድ ስለምታውቁት ወንጌልን ክፉኛ ስለሚቃወም ሰው አስቡ። መንፈስ ቅዱስ በውስጡ ሠርቶ ዳግም እንዲወለድ በማድረአዲስ ሕይወትን እንዲሰጠው ጸልዩለት፡፡
ምንጭ፡- “አስተምህሮ ክርስቶስና ደኅንነት”፤ ጽሑፍ፣ በዶ/ር ስቲቭ ስራውስ፤ ትርጉም በኃይሉ ልመንህ
