ክርስቲያኖች ሊደሰቱበት ከሚገባቸው እጅግ በጣም ጥልቅና ምሥጢራዊ የሆኑ የደኅንነት በረከቶች አንዱ ከክርስቶስ ጋር የሚኖራቸው ኅብረት ነው። በአንድ አኳኋኑ ሲታይ ከክርስቶስ ጋር ኅብረት ሲባል፥ የደኅንነትን በረከቶች ሁሉ የሚሸፍን አሳብ ነው። በብዙ ክፍለ ምንባቦች ላይ «በክርስቶስ» መሆን ወይም «ከክርስቶስ ጋር መተባበር» ሲባል፥ ሐረጉ ክርስቲያን ወይም በክርስቶስ አማኝ መሆን ማለት ይሆናል። ይህን የተላመደ ማዕከላዊ ሃሳብ በተለየ ርእስ በመውሰድ ስለ ደኅንነት ና በረከቶች ብዙ የምንቀስማቸው ትምህርቶች አሉ።
ጥያቄ፡– ኤፈ 5፡31-32 አንብብ። ሀ) ሐዋርያው ጳውሎስ የክርስቶስንና የቤተ ክርስቲያንን ኅብረት ምን ብሎ ይጠራዋል? ለ) ሐዋርያው የክርስቶስንና የቤተ ክርስቲያንን ኅብረት ለማመልከት እንዴት ካለው ሰብአዊ ግንኙነት ጋር ያመሳስለዋል?
ጥያቄ፡- ቆላ. 1፡26-27 እንብብ። ሐዋርያው ጳውሎስ አሕዛብ እንዲያውቁት ያደረገው ምሥጢር ምን ነበር?
ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቶስ ከአማኞች ጋር ያለውን ኅብረት እንደ ምሥጢር አድርጎ ይገልጸዋል። ምሥጢር ማለት ቀደም ሲል የተደበቀ ጻሩ ግን አሁን እግዚአብሔር ግልጽ ያደረገው እውነት ማለት ነው። እግዚአብሔር አሁን በጳውሎላ አማካይነት ጥንት ተደብቆ የነበረ አስደናቂ እውነትን ገልጧል። ይህ እውነትም በክርስቶስ አምነው ደኅንነቱን የተቀበሉ ከክርስቶስ ጋር የተባበሩ መሆናቸው ነው። በኤፌ. 5:31-32 ውስጥ ጳውሎስ በባልና በሚስት መካከል ስላለው ግንኙነት ያስተምራል። አንድ ወንድና አንዲት ሴት በሚጋቡበት ጊዜ የወላጆቻቸውን ቤት ትተው የራሳቸውን አዲስ ቤት ይመሠርቱና አዲስ ቤተሰብ ይሆናሉ። ይህ ግንኙነታቸውም ከሥጋዊ ንኙነት በላይ ስለሆነ፣ በስሜት፣ በማኅበራዊና በመንፈሳዊ ሁኔታቸውም አንድ ይሆናሉ። ጳውሎስ ይህንን ግንኙነት በክርስቶስና በቤተ ክርስቲያን መካከል ያለው የመተባበር ምሳሌ ነው ይላል። እግዚአብሔር አሁን ክርስቶስና አማኞች ጥልቅና ምሥጢራዊ በሆነ መንገድ የተባበሩ መሆናቸውን ግልጽ እንዲታወቅ አድርጎአል። በቆላ. 1፡26-27 ውስጥ ጳውሎስ ሲናገር ቀድሞ ተደስቶ የነበረውን ምሥጢር እግዚአብሔር እንደ ገለጠለትና ያ ምሥጢር አሁን በይፋ እንዲታወቅ የተደረገ መሆኑን ያብራራል። ይህ ምሥጢር ክርስቶስ ከአማኞች ሁሉ ጋር፥ ከአሕዛብም እንኳን ሳይቀር አብሮ መተባበሩ ነው። ከዚህ ኅብረት የተነሣ አሕዛብ በእግዚአብሔር ዘንድ የዘላለም ሕይወት ተካፋዮች የመሆን ተስፋ አላቸው።
ነገር ግን አማኞች ከክርስቶስ ጋር ተባበሩ ሲባል ምን ማለት ነው? ምንም እንኳን ይህ ጥልቅና ምሥጢራዊ እውነት ቢሆንም፥ እግዚአብሔር አሁን ይህን እውነት ለአማኛች ግልጽ አድርጎታል። እንግዲህ ዛሬ የምናጠናቸው እነዚህና ሌሎች ጥቅሶች ከክርስቶስ ጋር መተባበር ምን ማለት እንደሆነ ያብራሩልናል።
1. ከክርስቶስ ጋር መተባበር ማለት ከክርስቶስ ጋር ሞተን ከእርሱ ጋር ተነሣን ማለት ነው።
ጥያቄ፡- ገላ 2፡20 እንብብ። ጳውሎስ ከክርስቶስ ጋር ምን አደረግሁ አለ?
ጥያቄ፡- ሮሜ 6፡3-5፥8 አንብብ፡፡ እኛስ ከክርስቶስ ጋር ምን አደረግን?
ጥያቄ፡– ኤፌ 2፡5-6 አንብብ። እግዚአብሔር ከክርስቶስ ጋር ምን አደረገልን?
ጥያቄ፡- ቆላ. 2፡13፥ 20 አንብብ። እኛ ከክርስቶስ ጋር ምን አደረገን?
ጥያቄ፡- 2ኛ ቆሮ. 5፡17 አንብብ። በክርስቶስ የሆኑ ሁሉ ምን ሆነላቸው?
በመጀመሪያ ነገር ለአማኞች ከክርስቶስ ጋር መተባበር ማለት፥ ከክርስቶስ ጋር በሞቱና በትንሣኤው አንድ ሆነናል ማለት ነው። ኢየሱስ ሞቶ በተነሣ ጊዜ ከእርሱ ጋር ሞተን ከእርሱ ጋር ተነሥተናል። እኛ በክርስቶስ ከማመናችን በፊት የነበረ አሮጌው ሰው ከሞተ በኋላ፥ በክርስቶስ ባመንን ጊዜ አዲሱ ሰው ሕያው ሆኖ ተነሣ። በአዲስ ኪዳን ውስጥ ብዙ የተለያዩ ክፍለ ምንባቦች የኢየሱስ አማኞች በሞቱም ሆነ በትንሣኤው ከእርሱ ጋር የተባበሩ መሆናቸውን ያስተምራሉ። በገላ. 2፡20 ጳውሎስ ራሱ ከክርስቶስ | ጋር እንደ ተሰቀለ ይናገራል። በሮሜ 6፡3-5፥ 8 ውስጥም ጳውሎስ | እንደሚገልጸው ከኢየሱስ ጋር አንድ ለመሆን የተጠመቅን ሁሉ የሞቱም ተካፋዮች ነን ይላል። በሃያኛው ትምህርታችን ውስጥ እንደምንመለከተው በአዲስ ኪዳን ዘመን ለሰቡ በይፋ እንዳመነ ወዲያውኑ ጥምቀት ይደረግለት ነበር። ስለዚህ የጥምቀቱና ንስሐ ገብቶ የመለወጡ ወቅት አንድ ነበር። ጳውሎስ እንዳለው ሰዎች ወደ ክርስቶስ በሚመጡበት ጊዜ አብረውት ሙተው አብረውት ይነሣሉ፤ ከዚያም አብረውት ይኖራሉ። በኤፌ. 2፡5-6 ውስጥ ጳውሎስ ሲናገር፥ ከክርስቶስ ጋር የሞትን ብንሆንም ከክርስቶስ ጋር ሕይወትን ሰጥተናል ከክርስቶስም ጋር በሰማይ አስቀምጦናል ይላል። በቆላ. 2፡ ውስጥ በኃጢአታችን የሞትን ስንሆን እግዚአብሔር በክርስቶስ ሕያዋን አድርጎናል በማለት ጳውሎስ ያስረዳል። እንደዚሁም በቆላ. 2፡20 ውስጥ ከክርስቶስ ጋር ሞትን ይላል። ሌላው በ2ኛ ቆሮ. 5፡17 ጳውሎስ ሊያስረዳ ማንም በክርስቶስ ቢሆን እርሱ አዲስ ፍጥረት ነው፥ አርጌው ፍጥረት አልፎአል፥ በእርሱ ስፍራ አዲሱ ሰው ተተክቷል በማለት ይናገራል። ከርስቶስን እንደ ግል አዳኛችን ተቀብለን ባመንበት ጊዜ አዲስ ሕይወትን በአዲስ ሁኔታ መኖር የምንችል ሰዎች ሊያደርገን እግዚአብሔር በውስጣችን ሥራን ሠርቷል።
ኢየሱስን የግል አዳኛችሁ በማድረግ የምታምኑበት ከሆናችሁ፥ በእውነት እናንተ አዲስ ሰዎች ናችሁ! በኢየሱስ ከማመናችሁ በፊት የነበረው ሰው ክርስቶስ በመስቀል ላይ በተሰቀለ ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ተሰቅሎ ሞቶአል። «አዲሱ ማንነታችሁ» ኢየሱስ ከሙታን በተነሣ ጊዜ አብሮ ሕያው ሆኖአል። ስለዚህ ከክርስቶስ ጋር መተባበር ማለት አዲስ ሕይወትን አገኛችሁ ማለት ነው። ይህ ከክርስቶስ ጋር የሚደረግ ኅብረት ባለፉት ሁለት ቀናት ትምህርታችን ውስጥ ያጠናነው ርእሰ ጉዳይ ማለትም የዳግም ልደት በረከት መሠረት ነው። ከክርስቶስ ጋር በሞቱና በትንሣኤው የተባበርን በመሆናችን፣ በአዲስ ሕይወት አዲስ ሰዎች ሆነናል።
ጥያቄ፡– ሮሜ 6፡11 አንብብ። ሀ) እኛ ራሳችንን እንደሞትን የምንቆጥረው ለምንድን ነው? ለ) ራሳችንን ሕያዋን እንደሆንን የምንቆጥረው ለምንድን ነው?
ጥያቄ፡– ኤፌ. 2፡10 አንብብ። እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት በምን ምክንያት ፈጠረን?
ከክርስቶስ ጋር ስላለን ኅብረት ምላሻችን ምን ሊሆን ይገባል? ከክርስቶስ ጋር ሞተን ስለ ተነሣን፣ እንደ አዲስ ሰዎች መኖር አለብን። በሮሜ 6፡11 ውስጥ ጳውሎስ አሮጌው የኃጢአት ሕይወታችን ሞቶአል፥ ስለዚህ ራሳችንን ለኃጢአት እንደ ሞትን አድርገን መቁጠር አለብን ይላል። ራሳችንን ለኃጢአት እንደ ሞትን አድርገን መቁጠር ማለት፥ የቀድሞ ሕይወታችን እንደ ሞተ አድርገን መቀበል ማለት ነው። በክርስቶስ አዲሱ ሕይወታችን ተጀምሯል። በክርስቶስ ለእግዚአብሔር ሕያዋን መሆናችንን መገንዘብ አለብን። ለእግዚአብሔር ራሳችንን ሕያዋን አድርጎ መቁጠር ማለት አዲሱ ሕይወታችን መጀመሩን መገንዘብ ማለት ነው። ለምሳሌ ያህል፥ አንድ ሰው ሚስት በሚያገባበት ጊዜ የብቸኝነት አሮጌ ሕይወቱ አበቃ ማለት ነው። እርሱም የብቸኝነት አሮጌ ሕይወቱ ማብቃቱን ይቀበላል። እንደ ብቸኛ ሰው መኖርን ትቶ ትዳርን እንደ መሠረተ አባወራ ሆኖ አዲስ ሕይወትን ይኖራል። ጳውሎስ አሮጌው ሕይወታችን አልፎአል ይላል። አሮጌው ሕይወታችን ማክተሙን ተገንዝበን በአዲስ ሕይወት መኖር መጀመር አለብን። በኤፌ. 2፡10 ውስጥ ጳውሎስ ሲናገር፥ ከክርስቶስ ጋር ሞተን የተነሣን ስለሆንን (ቁ 4-6)፥ እግዚአብሔር ለእርሱ መልካም ሥራዎችን እንድንሠራ አዲስ ሰው አድርጎናል ይላል። እግዚአብሔር ያዳነንና ከክርስቶስ ጋር እንድንተባበር ያደረገን ለዓላማው ነው። ስለዚህ ለአዲስ ፍጥረቱ የሚፈጽመው አስደናቂ ዕቅድ አለው።
ጥያቄ፡- ሀ) ክርስቶስን ከማወቃችሁ በፊት በአርጌ ሕይወታችሁ ውስጥ ከነበረ ተግባርና ስሜት አሁን ምን ያህሉ በውስጣችሁ ቀርቷል? ለ) ምን መልካም ሥራዎችን እንድትፈጽሙ ነው እግዚአብሔር ያጻናትሁ?
ክርስቲያኖች ሁሉ ክርስቶስን ከማወቃቸው በፊት ከነበሩት አሮጌ ኃጢአታዊ ተግባራትና ዝንባሌዎች አንዳንዶቹን ይዘው ይጓዛሉ፡፡ ሁላችንም ብንሆን አሁንም ራሳችንን ወዳዶችና የሌሎችን ሀብትና ንብረት የምንመኝ ነን። አሁንም ትዕቢተኞችና ለዝናና ለክብር የምንቋምጥ ሰዎች ነን። አሁንም ፍትወታዊ ድርጊቶችንና በኃጢአት የተበከሉ ደስታዎችን እንፈልጋለን። አሁንም ሁላችንም እንቆጣለን፥ እንመቀኛለን፥ ምሬት እናሳያለን፥ ደግሞም እንጨነቃለን። ታዲያ እነዚህ ሁሉ የአርጌው ሕይወት ቅሪቶች መሆናቸውን አውቀን እንድንቀበል እግዚአብሔር ይፈልጋል። እነዚህ ተግባራትና ስሜቶች ከክርስቶስ ጋር ከተባበረው ሕይወት ጋር አይስማሙም። እግዚአብሔር በዚህ ፈንታ ያቀደልንን መልካም ሥራ እንድንፈጽም ይፈልጋል። እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን እንድናግዝ ይሻል። ለጠፉትም ወንጌልን እንድናካፍል ይፈልጋል። እንዲሁም ለቤተ ክርስቲያናችን ታማኞች እንድንሆን ይጠብቅብናል። ሌሎች ክርስቲያኖችን እንድናበረታታና እንድናንጽ ይሻል።
2. ከክርስቶስ ጋር ኅብረት ማድረግ ማለት፥ እግዚአብሔር እኛን ከክርስቶስ ጋር አንድ አድርጎ ተመለከተን ማለት ነው፡- እግዚአብሔር ወደ እኛ ሲመለከትም የሚያየው ኢየሱስን ነው።
ከክርስቶስ ጋር መተባበር ማለት ከክርስቶስ ጋር ሞተን ተነሣን ማለት ብቻ አይደለም። እንዲህ ማለት ከክርስቶስና ከእግዚአብሔር ጋር አብረን ሆነን ተገኘን ማለት ነው። እግዚአብሔር አሁን በሚመለከተን ጊዜ ቀድሞ የነበርነውን ዓይነት ሰዎች አድርጎ አይመለከተንም። እግዚአብሔር አሁን ሲመለከተን፣ ኢየሱስን ያያል። እግዚአብሔር ሲመለከተንም ልክ ኢየሱስ ያለውን የጽድቅ ስፍራ እኛም እንደ ያዝን አድርጎ ይመለከታል።
ጥያቄ፡- ገላ. 3፡26-27 አንብብ። በክርስቶስ ኢየሱስ አምነው ለእርሱ የተጠመቁ ምንን ያገኛሉ?
ጥያቄ፡- ቆላ. 3፡3 አንብብ። እኛ የሞትን ስለሆንን አሁን ሕይወታችን የት ነው?
ጥያቄ፡– 2ኛ ቆሮ. 5፡21 አንብብ። እኛ በክርስቶስ ምን ሆነናል?
ጥያቄ፡- ሮሜ 5፡15-19 አንብብ። ሀ) ከእርሱ ጋር አንድ ሆነው በመቀጠራቸው በሰው ልጆች ላይ ሞትን፥ ፍርድን ኩነኔንና ኃጢአትን ያመጣ ማን ነበር? ላ) ከእርሱ ጋር አንድ ሆነው ለተቀጠሩት ሁሉ ጸጋን፥ ተቀባይነትን፥ ጽድቅንና ሕይወትን ለሰው ልጆች ሁሉ ያመጣ ማን ነው?
ከክርስቶስ ጋር ኅብረትን የማድረግ ሁለተኛው ነጥብ እግዚአብሔር ክርስቶስን በሚያይበት እኳኋን እኛንም ይመለከተናል ማለት ነው። በደረጃም ቢሆን ከከርስተስ ለይቶ አይመለከተንም። እኛን በሚመለከተን ጊዘ፣ የሚያየው ክርስቶስን ነው። ገላ 3፡26-27 በጥምቀት ከክርስቶስ ጋር አንድ የሆኑ ሁሉ ክርስቶስን ለብሰዋል ይላል። በትምህርት 20 ውስጥ እንደምንመለከተው በአዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አንድ ሰው የውኃ ጥምቀት የሚወስድበት ጊዜና ክርስቶስን እንደ ብላ መድኃኒቱ አምኖ የሚቀበልበት ጊዜ በጣም የተቀራረበ ነው። ይህም በጣም ጠቃሚ የሆነ፥ አንድ ሰው ክርስቶስን እንደ አዳኙ የመቀበሉ ይፋዊ ምልክት ነው፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ በእምነት አማካኝነት ሁላችሁም የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁ፥ በጥምቀት ከክርስቶስ ጋር አንድ የሆናችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋል ይላል። እግዚአብሔር እነርሱን በሚመለከታቸው ጊዜ የሚያየው ክርስቶስን ነው። ምክንያቱም ልክ ልብስ ሰውን እንደሚሸፍን ክርስቶስ ሸፍኖአቸዋልና ነው። አንድ የፖሊስ መኮንን የደንብ ልብሱን በለበሰ ጊዜ የፖሊስ ሠራዊት አባል መሆኑ ያስታውቃል። በመንገድ ላይ አቁሞአችሁ ሊያነጋግራችሁ ቢፈልግ እንደ ማንኛውም ግለሰብ አትመለከቱትም፥ ግን ልብሱን በመመልከት እንደ ፖሊስ ሠራዊት አባል ትቀበሉታላችሁ። በዚሁ መንገድ፣ እግዚአብሔር በሚመለከተን ጊዜ ክርስቲያኖች ከመሆናችን በፊት የነበረንን ማንነት አያይም። በእኛ ላይ ክርስቶስን ከነመላ ጽድቁ ያያል። 2ኛ ቆሮ. 5፡21 እኛ ከክርስቶስ ጋር በመተባበር የእግዚአብሔር ጽድቅ ሆነን በእምነት የክርስቶስ ስለሆንን እግዚአብሔር በሚመለከተን ጊዜ እርሱ የሚያየው የክርስቶስን መለኮታዊ ጽድቅ ነው ይላል። እንዲሁም በቆላ. 3:3 ሞታችኋልና ሕይወታችሁም በእግዚአብሔር ከክርስቶስ ጋር ተሰውሮአልና ይላል። አሮጌው ሕይወታችን ዳግም አይታይም። ምክንያቱም በክርስቶስ ሕይወት የተተካ በመሆኑ ነው። ስለዚህ የክርስቶስ ሕይወት ብቻ ይታያል። በመሆኑም ከክርስቶስ ጋር ኅብረት ማለት እግዚአብሔር በሚመለከተን ጊዜ ኢየሱስን ያያል ማለት ነው።
ከኢየሱስ ጋር በአንድ ከመታየታችን የተነሣ ከምናገኛቸው ታላላቅ በረከቶች እንዱ ኢየሱስ ያስገኘልን እያንዳንዱ የደኅንነት በረከት ነው። በሮሜ 5፡15-19 ውስጥ ጳውሎስ እንደተናገረው የአዳም ኃጢአት በሰዎች ሁሉ ላይ ሞትን፥ ፍርድን፥ ኩነኔንና ኃጢአትን አምጥቷል። በአዳም የተወለዱ ሁሉ ኃጢአተኞች ስለሆኑ ይሞታሉ፥ ተፈርዶባቸዋል፥ የእግዚአብሔርንም ቅጣት ይቀበላሉ። ሐዋርያው በመቀጠል ኢየሱስ ልጆቹ ለሆኑ ሁሉ ጸጋን፥ ተቀባይነትን፥ ጽድቅንና ሕይወትን ሰጠ ይላል። . ከክርስቶስ ጋር የሚተባበሩ ሁሉ ከእርሱ ጋር በመሆናቸው የእግዚአብሔርን ሞገስ ያገኛሉ፥ የኢየሱስን ጽድቅና ዘላለማዊ ሕይወት ያገኛሉ ፤ ከእግዚአብሔርም ጋር ይታረቃሉ። በአዳም ምክንያት ሰው ሁሉ ከእግዚአብሔር እንደ ተለየ ሁሉ፥ በክርስቶስ ምክንያት ሰው ሁሉ ከእግዚአብሔር ጋር በመታረቅ ሰላምን መልሶ ያገኛል (1ኛ ቆሮ. 15፡22 ተመልከት)።
3. ከክርስቶስ ጋር መተባበር ማለት ክርስቶስ በመንፈስ በውስጣችን ለመኖር መጣ ማለት ነው።
ከክርስቶስ ጋር መተባበር ማለት ከክርስቶስ ጋር ሞተን ከእርሱ ጋር ስለ ተነሣን እግዚአብሔር አሁን ወደ እኛ ሲመለከት በእኛ ላይ ክርስቶስን ያያል ማለት ብቻ አይደለም። ከከርስቶስ ጋር መተባበር ማለት ክርስቶስ በመንፈሱ በውስጣችን ለመኖር መጥቷል ማለትም ነው።
ጥያቄ፦ ገላ. 2፡20 አንብብ። ሐዋርያው ጳውሎስ ከክርስቶስ ጋር በመሰቀሉ ምክንያት ምን በእርሱ ውስጥ ይኖራል አለ?
ጥያቄ፡- ርሜ 8፡9-11 እንብብ። ሀ) እንደ ቁጥር 9 አባባል የኢየሱስ በሆነ ሰው ውስጥ ማን ይኖራል? ለ) እንደ ቁጥር 10 አባባል በውስጣችን የሚኖረው ማን ነው? ሐህ እንደ ቁጥር 1 አባባል በውስጣችን የሚኖረው ማን ነው?
እኛ ክርስቶስን እንደ መድኅናችን አድርገን በምናምንበት ጊዜ ክርስቶስ ራሱ በውስጣችን ለመኖር ወደ እኛ ዘንድ ይመጣል። ቀደም ሲል ቆላ. 1፡26-27 በአጠናንበት ወቅት ክርስቶስ በተቀበሉት፥ በአሕዛብ ሳይቀር በውስጣቸው እንደሚኖር እግዚአብሔር ይህን ምሥጢር እንደ ገለጠ አስተውለናል። አሕዛብም እንኳን እግዚአብሔር ከእነርሱ ዘንድ የመገኘቱንና የክብሩን ተስፋ በማግኘታቸው ሊረኩ ችለዋል፤ ምክንያቱም አሁን ኢየሱስ በውጣቸው ስለሚኖር ነው። ጳውሎስ በገላ. 2፡20 ውስጥ እርሱ ከክርስቶስ ጋር ስለ ተሰቀለ ቀድሞ የነበረው እርሱነቱ ወይም ሕይወቱ አሁን አብሮት እንደሌለ ይናገራል። ይልቁንም፣ አሁን ክርስቶስ በውስጡ ሆኖ የእርሱን ሕይወት ይኖራል። ሮሜ 8፡9-10 በውስጣችን ያለውን የክርስቶስንና የመንፈስ ቅዱስን ቀንኙነትን ያመለክተናል። በሮሜ 8፡9 ውስጥ ጳውሎስ መንፈስ ቅዱስ የክርስቶስ መንፈስም ነው ይልና፥ የክርስቶስ የሆነ ሁሉ የክርስቶስ መንፈስ አለው፥ ይኸውም በውስጡ የሚኖር መንፈስ ቅዱስ ነው ይላል። በሮሜ 8፡11 ውስጥ ጳውሎስ እንደገና መንፈስ ቅዱስ በአማኞች ውስጥ ይኖራል ይላል። በእነዚህ ተከታታይ ሦስት ጥቅሶች ውስጥ አውሎስ የመንፈስ ቅዱስን በአማኞች ውስጥ የመኖርና የክርስቶስን በአማኞች ውስጥ የመኖር አሳብ ማለዋወጡን ወይም አንዱን በአንዱ መተካቱን ልብ በል። እዚህ ላይ ጳውሎስ ክርስቶስ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አንድ አካል ነው አይልም። ይልቅ፣ ሐዋርያው የሚለው ክርስቶስ በአማኞች ውስጥ በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ያድራል ነው። ክርስቶስ በውስጣችን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ያድራል። ሰዎች ክርስቶስን መድኅናቸው አድርገው በሚያምኑበት ጊዜ መንፈስ ቅዱስ በውስጣቸው ለመኖር ይመጣል። በውስጣቸው በሚኖር መንፈስ አማካይነት ክርስቶስ በውስጣቸው ይኖርና ከራሱ ጋር እንዲተባበሩ ያደርጋል። አማኞች ከክርስቶስ ጋር በሚኖራቸው ኅብረት የተነሣ እርሱ በውስጣቸው እንዲኖር ትልቅ ዕድል አላቸው።
4. ከክርስቶስ ጋር መተባበር ማለት የክርስቶስ አካል ለመሆን በመንፈስ ከእርሱ ጋር አንድ ሆነናል ማለት ነው።
ከክርስቶስ ጋር ኅብረት አለን ሲባል ከክርስቶስ ጋር ሞተን ተነሥተናል፥ እግዚአብሔር እኛን ሲመለከት ክርስቶስን ያያል፥ ይህ ክርስቶስ ደግሞ በውስጣችን ይኖራል ማለት ነው። ከዚህም ባሻገር ከክርስቶስ ጋር ኅብረት እለን ማለት እማኞች በምድር ላይ የሚታዩ የክርስቶስ አካል ለመሆን በመንፈስ ይተባበራሉ ማለት ነው።
ጥያቄ፦ ሮሜ 12፡4-5 አንብብ። በክርስተስ ምን ሆነናል?
ጥያቄ፦ 1ኛ ቆሮ. 6፡15-17 አንብብ። ሀ) የምን አባል ወይም ተባባሪ ሆነናል (ቁ 15)? ) ከጌታ ጋር በምንተባበርበት ጊዜ ምን ይሆናል (ቁ 17)?
ክርስቶስን መድኀናቸው አድርገው በመቀበል የሚያምኑበት ሁሉ በክርስቶስ አካል ውስጥ የተሳሰሩ ናቸው። ከክርስቶስ ጋርና እርስ በርስ እንደ እርሱ አካል የተሳሰርን ነን (ሮሜ 12፡4-5)። ብዙ ጊዜ የክርስቶስ አካል ስለ መሆን በምናስብበት ጊዜ የምናስበው ከሌሎች አማኞች ጋር የተሳሰርን ስለ መሆናችን ነው። ነገር ግን በመጀመሪያ ከክርስቶስ አካል ጋር መተሳሰር ማለት በክርስቶስ ያመንን እያንዳንዳችን በመንፈሳዊ መንገድ ከክርስቶስ ጋር ተሳስረናል ማለት ነው። በ1ኛ ቆሮ. 6፡15-17 ውስጥ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች ወሲባዊ ምግባረ ብልሹነት ለምን የከፋ ኃጢአት እንደሆነ ያስረዳቸዋል። እንዲሁም እያንዳንዳቸው የክርስቶስ የአካሉ ክፍል እንደሆኑ ይነግራቸዋል። በቁጥር 15 ላይ ሥጋቸው ከክርስቶስ ጋር የተባበረ መሆኑን፥ በቁጥር 17 ውስጥ ደግሞ ከጌታ ጋር በመንፈስ የተባበሩ መሆናቸውን ይነግራቸዋል። በባልና ሚስት መካከል የሚደረግ አካላዊ የግብረ ሥጋ ግንኙነት በመካክላቸው የመንፈስና የስሜት አንድነትን እንደሚያስከትል ሁሉ፥ በክርስቶስ የሆኑትም የክርስቶስ የአካሉ ክፍል የሚያደርጋቸው የመንፈስ ኅብረት አላቸው። እንዲህ ሲባል ደግሞ የክርስቶስን መለኮታዊ ባሕርይ እንወስዳለን፥ ወይም የእኛ ተፈጥሮአዊ ባሕርይ ከእርሱ ጋር ውኅደትን ያደርጋል ማለት አይደለም። እንዲህ ማለት የክርስቶስ መንፈስና የእኛ መንፈስ በየራሱ እንዳለ ሆኖ እርስ በርስ ይተባበራል፥ ይተሳሰራል ማለት ነው። ልክ ባልና ሚስት የመንፈስና የስሜት ትስስር እንደሚኖራቸው ማለት ነው። ይህ በሚሆንበት ጊዜ ባልም በራኑ ሚስትም በራስዋ ማንነትዋን ይዛ ነው። እንደዚሁም ክርስቶስ ራሱን ከእኛ ጋር በመንፈስ በሚያስተባብርበት ጊዜ እኛነታችን እንዳለ ነው የሚሆነው። ከክርስቶስ ጋር የሚኖረን መንፈሳዊ ኅብረት ማለት በዚህ ምድር ላይ የምንታይ የአካሉ ክፍል ነን ማለት ነው። ባልና ሚስት አንድ ዓይነት መንፈስና ስሜት እንደሚጋሩ ሁሉ፥ እኛም አንድ ዓይነት የሆነ መንፈስ ከእርሱ ጋር እንጋራለን ማለት ነው። ሰዎች ባልና ሚስትን ስሚመለከቱበት ጊዜ ግለሰቦች መሆናቸውን ብቻ ሳይሆን፥ በጋብቻም የተሳሰሩ መሆናቸውን አብረው ያያሉ፡ በዚሁ ረገድ ሰዎች ወደ እኛም በሚመለከቱበት ጊዜ እንደ ግለሰቦች ብቻ የሚመለከቱን ሳይሆኑ፥ ክርስቶስን በእኛ ውስጥ ማየት አለባቸው። እንግዲህ ከክርስቶስ ጋር ተባብረናል ማለት ከእርሱ ጋር ሞተን ተነሥተናል፥ እግዚአብሔር በሚመለከተን ጊዜ በእኛ ዘንድ የኢየሱስን ጽድቅና ማዕረግ ያያል፥ ክርስቶስ በእኛ ውስጥ ይኖራል፥ እንደዚሁም እኛ በመንፈስ ከክርስቶስ አካል ጋር አንድ ሆነናል ማለት ነው።
ምንጭ፡- “አስተምህሮ ክርስቶስና ደኅንነት”፤ ጽሑፍ፣ በዶ/ር ስቲቭ ስራውስ፤ ትርጉም በኃይሉ ልመንህ
