Site icon

የመዳኛ መንገድ፡- ንስሐ እምነትና ወደ እግዚአብሔር መመለስ 

ባለፈው ሳምንት ወደ ደኅንነት ስለ መድረሻ መንገዶች ተምረን ነበር። ምንም እንኳን እግዚአብሔር ሰዎች ሁሉ መጥተው ደኅንነቱን እንዲቀበሉ ቢጠራቸውም፥ በራሳቸው ነፃ ምርጫ አምላካዊ ጥሪውን ሳይቀበሉ ቀሩ። ነገር ቀን እርሱ በምሕረቱ ጥቂቶችን መርጦ ወደ እርሱ እንደሚጠራ ተገንዝበናል። ይህ ውጤታማ ጥሪም የተጠሩት ጥሪውን ተቀብለው ወደ እርሱ እንዲመጡ አድርጓል። ይህም ውጤታማ ጥሪ በንስሐና በእምነት ወደ ክርስቶስ እንዲመጡ አድርጓል። በዚህ ሳምንት ደግሞ ሰዎች የእግዚአብሔርን ደኅንነት ለመቀበል ስላለባቸው ኃላፊነት እናጠናለን። ስለሆነም የእኛ ኃላፊነት ንስሐ መግባትና ማመን ነው። 

የመጀመሪያ ቀን 

ንስሐ 

ጥያቄ፡- በአካባቢአችሁ የሚኖሩ ሰዎችን አንድ ሰው ለመዳን ምን ማድረግ አለበት ብላችሁ ብትጠይቋቸው፥ መልሳቸው ምን የሚል ይሆናል? 

ጥያቄ፦ ማርቆስ 1:15 አንብቡ። ኢየሱስ የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለች ብሎ ሕዝቡን ባስተማረ ጊዜ ምን እንዲያደርጉ አሳሰባቸው? 

ጥያቄ፡- ሉቃስ 24፡46-47 አንብቡ። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ለዓለም ሕዝቦች ሁሉ እንዲሰብኩ ባዘዛቸው ጊዜ ምን ነገራቸው? 

ጥያቄ፡- የሐዋ. 3፡19 አንብቡ። ሐዋርያው ጴጥሮለ ለሕዝቡ የመጽናናት ዘመን እንዲመጣላቸው ለማድረጎ የኃጢአታቸውን ይቅርታ ለመቀበል እንዲችሉ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ነበር የነገራቸው? 

ጥያቄ፡- የሐዋ. 1፡18 አንብቡ። እግዚአብሔር ለአሕዛብ ምንን ሰጠ? 

ጥያቄ፡- የሐዋ. 17:30 አንብቡ። ሐዋርያው ጳውሎስ፥ እግዚአብሔር በየክፍሉ ያለውን ሕዝብ ምንን ያዝዘዋል ብሎ ለአቴናውያን ነገራቸው? 

ጥያቄ፡- የሐዋ. 20፡21 አንብቡ። ሐዋርያው ጳውሎስ ለአይሁድና ለአሕዛብ ምን መልእክትን ሰጣቸው? 

ጥያቄ:- 2ኛ ቆሮንቶስ 7፡10 አንብቡ። ሀ) እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነ ኀዘን ወዴት ይመራል? ለ) ዓለማዊ ኀዘን ምንን ያመጣል? 

ጥያቄ፡- 2ኛ ጢሞቴዎስ 2፡25-26 አንብቡ። ሰዎች ከዲያብሎስ ወጥመድ ወደጊያመልጡበት፥ ወደ እውነተኛው እውቀት የሚያደርስ ምንድን ነው? 

ዛሬ አንዳንድ ሰዎች በኢትዮጵያ ውስጥ የእግዚአብሔርን ደኅንነት ለማኘት ሲሉ ብዙ ነገሮችን ማድረቅ እንዳለባቸው ያምናሉ። ለምሳሌም ያህል፡ መቆም፥ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት መፈጸም፥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መጠመቅ፥ እንደዚሁም ያለማቋረጥ ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄድና ለድሆች መመጽወትና ለቤተ ክርስቲያን መባ መስጠት የመሳሰሉትን ያደርጋሉ። ዳሩ ግን መላውን የአዲስ ኪዳን መጽሐፍ ስንመለከት፥ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርት ለወንጌል መልእክት መልስ ሊሰጥበት የሚገባ አንድ ጥሪ ብቻ ያቀርባሉ። አንዳንዴ ይህ ጥሪውን ሰምቶ ምላሽ የመስጠት ነገር ንስሐ ተብሎ ሊገለጽ ይችላል፤ በሌላ ሁኔታ ደግሞ እምነት ወይም በክርስቶስ ማመን ይባላል። እንዲሁም ይኸው ጥሪን መቀበልና ውጤት ማሳየት መለመጥ ወይም ወደ እግዚአብሔር መመለስ ሊሆን ይችላል። ግን በንስሐ፥ በእምነትና በመመለስ ወደ እግዚአብሔር መምጣት ሦስቱም ለደኅንነት ሁኔታ ተለያይተው የሚታዩ ሳይሆኑ፥ አንድ ሰው ለመዳን በየደረጃ ው ሊያሟላቸው የሚገባ ግዴታዎች ናቸው። እንዲህ ማለትም እግዚአብሔር ለደኅንነት ያለው አንድ ሁኔታን የምንመለከትባቸው ሦስት መንገዶች ናቸው። ስለሆነም ንስሐ፥ እምነትና ወደ እግዚአብሔር መመለስ እግዚአብሔር ለደኅንነት ያለውን አንድ ሁኔታ በሦስት መንገዶች የመገንዘብና የማብራራት ነገር ነው። ከዚህ በመነሣት የንስሐን የእምነትና ወደ እግዚአብሔር ስለመመለስ ሁኔታ በማጥናት፥ አንድ ሰው የእግዚአብሔርን የደኅንነት ስጦታ ለመቀበል ምን የጥሪ መልስ መስጠት እንዳለበት መገንዘብ እንችላለን። ስለሆነም ዛሬ ስለ ንስሐ ባለው አስተሳሰብ ላይ ጥናት እናካሂድና ነገ ደግሞ ስለ እምነት ከተማርን በኋላ በሦስተኛው ቀን ወደ እግዚአብሔር መመለስ ሲባል ምን ማለት እንደሆነ እናጠናለን። 

1. እግዚአብሔር ንስሐ ለሚገቡት ደኅንነትን ይሰጣል። 

ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ወንጌልን በሰበኩ ጊዜ ቃሉን በንስሐ መንፈስ እንዲቀበሉ ጥሪ አቀረቡላቸው። በማርቆስ 1፡15 ውስጥ በሚገኘው በኢየሱስ የአገልግሎት መጀመሪያ ላይ እርሱ ያደረገው ሰዎች ንስሐ እንዲገቡና በወንጌል እንዲያምኑ ነበር፥ የዚህንም ምክንያት ሲያስረዳ የእግዚአብሔር መንግሥት መቅረቧን በመግለጽ ነበር። በሉቃስ 24፡46-47 ባለው ክፍል፥ በአገልግሎት ፍጻሜ ላይ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ሄደው የንስሐ ስብከት ለዓለም ሕዝቦች እንዲሰብኩ አዘዛቸው። ሕዝቦች ሁሉ የኃጢአታቸውን ይቅርታ ሊያገኙ የሚችሉት በንስሐ ብቻ ነው። ደቀ መዛሙርቱም ለጌታ ትእዛዝ ተገዙ። በሐዋርያት ሥራ 3፡19 ውስጥ ጰጥሮስ ሽባውን ሰው ከፈወሰ በኋላ በኢየሩሳሌም በነበረው ቤተ መቅደስ ውጭ ለነበሩት ሁሉ ሰበከላቸው። በስብከቱም ላይ ንስሐ እንዲገቡና ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ፥ ይህን ሲያደርጉ ለኃጢአታቸው ይቅርታ እንደሚያገኙና የመጽናናት ዘመንም | እንደሚሆንላቸው ነገራቸው። ይህም እግዚአብሔር ደኅንነትን፥ የሰላም | መንግሥትን፥ ብልጽግናን እንዲሁም ፍትሕንና የተትረፈረፈ በረከትን ለእስራኤል እንደሚሰጥ በብሉይ ኪዳን ውስጥ የሰጠው ተስፋ ፍጻሜ ነው። በዚህ ንስሐ አማካይነት ብቻ ይህን የደኅንነት በረከት ተቀብለው ወደዚያኛው መንግሥት ሊገቡ ይችላሉ። በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 10 ውስጥ ጰጥሮስ ለቆርኔሌዎስ ከሰከለት በኋላ፥ በኢየሩሳሌም ለነበረችው ቤተ ክርስቲያን የአይሁድ መሪዎች ስለ ሁኔታው ዘገባ አቀረበ። እግዚአብሔር የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ ለአሕዛብ ስለ መስጠቱ በሰሙ ጊዜ እግዚአብሔር እንዳዳናቸው ተረዱ። በሐዋርያት ሥራ 11፡18 ውስጥ ስሜታቸውን ሲገልጹ፥ እግዚአብሔር ለአሕዛብ ለአዲስ ሕይወት የሚያበቃቸውን ንስሐ ሰጥቷቸዋል አሉ። እንግዲህ አዲስ ሕይወትን የሚሰጠው በንስሐ አማካይነት ነው። ጳውሎስ ለአቴናውያን ስብከቱን ሊያሰማ በየትም ያሉ ሕዝቦች በፍርዱ ቀን ጻድቃን ሆነው እንዲገኙ ንስሐ መግባት እንዳለባቸው እግዚአብሔር ያዝዛል ብሏቸው ነበር። በሐዋርያት ሥራ 20፡21 ውስጥ ጳውሎስ ለአይሁድም ሆነ ለአሕዛብ በየትም ስፍራ በሰበከ ጊዜ፥ በንስሐ ወደ እግዚአብሔር መመለስ እንዳለባቸውና በኢየሱስ ማመን እንዳለባቸው የመሠከረ መሆኑን ለኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን መሪዎች ነግሮአቸው ነበር። እንዲሁም በ2ኛ ጢሞቴዎስ 2፡25-26 ባለው ውስጥ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ እግዚአብሔር የሚሰጠው ንስሐ ከዲያብሎስ ወጥመድ ሊያወጣ ወደሚችል የእውነት እውቀት ያደርሳል ነበር ያለው። በእነዚህ ክፍለ ምንባቦች ላይ በግልጽ እንደተብራራው እግዚአብሔር ይቅርታን፥ ሕይወትን፥ የእውነት ዕውቀትንና የደኅንነቱንም በረከት የሚሰጠው በንስሐ ወደ እርሱ ለሚመጡት ነው። 

2. ንስሐ ምንድን ነው? 

2.1 ንስሐ ስለ ኃጢአት፥ ስለ ኢየሱስና ስለ ደኅንነት «አሳባችንን መለወጥ» ማለት ነው። 

አንድ ሰው ለመዳን ቢፈልግ ንስሐ መግባት አለበት። ነገር ግን «ንስሐ» ምን ማለት ነው? በግሪኩ ቃል «ንስሐ» ማለት «አስተሳሰብን መለወጥ» ወይም «ስለ አንድ ነገር ለየት ባለ መንገድ ማሰብ» ማለት ነው። ንስሐ መግባት መጸጸት ወይም አሳብን መለወጥ ማለት ነው። ንስሐ ከበፊቱ የተለየ አስተሳሰብ መኖር ነው። ታዲያ ሰዎች ስለ ምን ጉዳይ ነው አሳባቸውን የሚለውጡት፥ ወይም ለየት አድርገው የሚያስቡት? በዚህ ክፍለ ምንባብ እንደ ተመለከትነው አሳባቸው የሚለወጠው ስለ ኃጢአት፥ እንደዚሁም ስለ ክርስቶስና ስለ ይቅርታ የሚያስቡበትን መንገድ ነው። በሉቃስ 24፡46-47 ውስጥ ኢየሱስ ሲናገር ንስሐና ጸጸት የኃጢአትም ይቅርታ «በክርስቶስ ስም» ሊሰበክ ይገባል ይላል። ሰዎች የኃጢአትን ይቅርታ ለመቀበል እንዲችሉ ስለ መሢሑ ያላቸውን አስተሳሰብ መለወጥ አለባቸው። ኢየሱስን እንደ መሢሕ አድርገው ሲቀበሉ ብቻ የኃጢአትን ይቅርታ በእርሱ አማካይነት ሊያገኙ እንደሚችሉ በመግለጽ እርሱን ሊቀበሉ ይገባቸዋል፡ ኢየሱስ ስለ መሢሑ ሞትና ትንሣኤ ብሉይ ኪዳን የተነበየ መሆኑን ደፋ መዛሙርቱን አስታውሶአቸው ነበር። በዚህም ሊያስገነዝባቸው የፈለገው ሰዎች የኃጢአት ይቅርታን ሊቀበሉ እንዲችሉ በሞቱና በትንሣኤው አማካይነት ደኅንነትን ማግኘት እንዳለባቸው ሲያሳስባቸው ነው። ስለዚህ ሰዎች አሳባቸውን በመለወጥ፥ በኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ የሚገኘው የኃጢአት ይቅርታ መቀበል አለባቸው። 

በሐዋርያት ሥራ 3፡19 ውስጥ ተመሳሳይ አሳብ እናገኛለን። ጰጥር በኢየሩሳሌም ከቤተ መቅደስ ውጭ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ኢየሱስ ለሰቀሉት ሰዎች ስብከትን ያሰማ ነበር። እርሱም ኢየሱስን እንደ ሰቀሉ፡ አስታወሳቸውና ቀጥሎም ይህም እግዚአብሔር በነቢያት አማካይነት በብሉ ኪዳን ውስጥ የተናገረው ትንቢት ፍጻሜ እንደሆነ አስገነዘባቸው። ሕዝቡና ይህን በሰሙ ጊዜ ስለ ኢየሱስ የነበረውን አሳባቸውን መለወጥ ነበረባቸው እርሱን ሞት የሚገባው መሢሕ አድርገው በመመልከት ፈንታ እንደ እግዚአብሔር እውነተኛ መሢሕ ሊቀበሉት ይገባ ነበር። ይህን ቢያደርጉ ኖሮ በብሉይ ኪዳን ውስጥ የተሰጠው የደኅንነት በረከት ይህ በሆነባቸው ነበር። እንደዚሁም ኢየሱስን በገደሉት ጊዜ ኃጢአት መሥራታቸውን አምነው መቀበል ይኖርባቸው ነበር። የኃጢአታቸውንም ይቅርታ ለማግኘት እርሱን መቀበል ነበረባቸው። ስለ ኢየሱስ፥ ስለ መስቀል ሞቱና እንዴት ይቅርታን እንደሚያገኙ እንዲሁም የእግዚአብሔርን የደኅንነት በረከት እንዴት እንደሚቀበሉ ጸጸትና ንስሐ አሳባቸውን እያስለወጣቸው ነበር። 

በሐዋርያት ሥራ 10፡34-43 ጴጥሮስ ለቆርኔሌዎስና ለቤተሰቡ ስብከትን ያቀርብ ነበር። ኢየሱስ እንደ ተሰቀለ፥ ከሙታን እንደ ተነሣና ብዙዎችም እንዳዩት ነገራቸው። ኢየሱስ በሰዎች ላይ የሚፈርድ እርሱ ብቻ ነው። በእርሱ የሚያምኑት ብቻ የኃጢአት ይቅርታን ይቀበላሉ። ጴጥሮስ በትምህርቱ ላይ የኃጢአት ይቅርታ የሚያገኙት በኢየሱስ የሚያምኑ ብቻ መሆናቸውን እንደ ነገራቸው መንፈስ ቅዱስ በቆርኔሌዎስና በቤተሰቡ ላይ ወረደ። ይህ አሕዛብ ሰው ከነቤተሰቡ በእርግጥ ለመዳኑ እግዚአብሔር ለጴጥርስ ያረጋገጠበት የራሱ መንገድ ነበር። እንዲሁም በሐዋርያት ሥራ 11፡18፥ በዚህን ጊዜ የአይሁድ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ይህ ወቅት እግዚአብሔር ለእነዚህ አሕዛቦች «ለሕይወት የሚሆን ንስሐ» የሰጠበት ጊዜ ነው አሉ። ቆርኔሌዎስና ቤተሰቡ ስለ ኢየሱስ የነበራቸውን አስተሳሰብ በለወጡ ጊዜ የዘላለምን ሕይወት ተቀብለዋል። እነርሱም እርሱ ሞቶ ከሞት መነሣቱን አምነዋል። ሞቱም ስለ ኃጢአታቸው እንደ ሆነ ተቀብለዋል። እርሱም አንድ ቀን በሁሉም ላይ እንደሚፈርድና የኃጢአታቸውንም ይቅርታ ሊያገኙ የሚችሉት በእርሱ በማመን ብቻ መሆኑን አምነዋል። 

ሰዎች ንስሐ በሚገቡበት ጊዜ ስለ ኃጢአት፥ ስለ ኢየሱስና ስለ ደኅንነትን የነበራቸውን የቀድሞ አስተሳሰብ መለወጥ አለባቸው። በመጀመሪያም፥ ስለ ኃጢአት ያላቸውን አስተሳሰብ መለወጥ አለባቸው። ኃጢአታቸው ይህን ያህል ክፉ እንዳልሆነ ይሰማቸው የነበረውን መተው አለባቸው። እግዚአብሔር ኃጢአታቸውን ችላ ብሎ እንደሚያልፍ አድርገው ማሰብ የለባቸውም። ኃጢአታቸው ከእግዚአብሔር የለያቸውና በእግዚአብሔርም ዘንድ ተቀባይነት እንዳይኖራቸው ማድረጉን አውቀው ከኃጢአታቸው በንስሐ መመለስ ይኖርባቸዋል። ሁለተኛ፥ ሰዎች ንስሐ ገብተው ሊለወጡ ስለ ኢየሱስ የነበራቸውን አስተሳሰብ መቀየር አለባቸው። ስለዚህ ኢየሱስ እንደ ማንኛውም ሰው ተራ ሰው ነው የሚለውን የተዛነፈ አስተሳሰብ መተው ይገባቸዋል። በእርሱ አማካይነት ሰዎች ሁሉ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትና ከእርሱ ጋር እንዲኖሩ የሚያስችላቸው የእግዚአብሔር ምርጥ መሆኑን ማመን አለባቸው። ሦስተኛ፥ ሰዎች ንስሐ ሲገቡ ስለ ደኅንነትና የኃጢአት ይቅርታ የነበራቸውን አስተሳሰብ ሊለውጡ ይገባል። ስለሆነም በመልካም ሥራቸው የእግዚአብሔርን ይቅርታ እንደሚቀበሉ መስሎ ሊታያቸው አይገባም። በዚህ ፈንታ ደኅንነት በኢየሱስ ብቻ እንደሚገኝ ማመን ይኖርባቸዋል። በመሆኑም የኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ ከእግዚአብሔር ጋር እንዲያስታርቀን እግዚአብሔር ለእኛ ያዘጋጀው መንገድ መሆኑን አምነን መቀበል አለብን። 

2.2 ንስሐ ከእምነት ጋር ይመሳሰላል። 

በእነዚህ ጥቅሶች እንደተገለጸው ሁሉ፥ ንስሐ ከእምነት ጋር በጣም ይመሳሰላል። ኢየሱስ በማርቆስ 1፡15 ውስጥ ሕዝቡን የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለችና «ንስሐ ግቡና እመኑ» አላቸው። እንዲሁም ጳውሎስ በሐዋርያት ሥራ 20፡21፥ «ሕዝቡ በንስሐ ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲያምኑ» መስበኩን ይናገራል። ክርስቲያኖች ደኅንነታቸውን ለማግኘት ንስሐና እምነት አንዱን ከሌላው ፍጹም ለይተው የሚያደርጉዋቸው ሁለት የተነጣጠሉ ነገሮች አይደሉም። በምትኩ እነዚህ ሁለቱ ይቅርታን ለማግኘት በሰዎች ልቦና ውስጥ የሚካሄደውን ለውጥ የምንመለከትባቸው መንገዶች ናቸው። አንዱን ለውጥ በሁለት መንገድ መግለጽ ነው። ስለዚህ አንዱን ከሌላው መለየት አይቻልም። አንዳች ልዩነት ካለ ግን፥ ንስሐ የኃጢአት ሕይወት አንገሽግሾን በመመለሳችን ላይ ያተኩራል። እንዲሁም ንስሐ ደኅንነትን በበጎ ሥራ ወይም በራስ ጽድቅ ለማግኘት የምናደርገውን ጥረት ትተን በመመለስ ላይ ትኩረት ያደርጋል። እምነት ደግሞ ደኅንነትን የሚሰጠን ክርስቶስ ብቻ መሆኑንና በእርሱ ብቻ እግዚአብሔርን የሚያስደስት ሕይወትን መኖር እንደምንችል ተረድተን ወደ እርሱ በመመለሳችን ላይ ያተኩራል። 

2.3 ንስሐ በኃጢአታችን ከማዘን የበለጠ ነው። 

ጥያቄ፡- ማቴዎስ 27፡3 እንብቡ። ኢየሱስ እንደ ተፈረደበት ባየ ጊዜ ይሁዳ ምን ተሰማው? 

ጥያቄ፡- ዕብራውያን 12፡16–17 አንብቡ። ኤሳውን ያሳዘነው ምን ነበር? 

አንዳንድ ሰዎች ንስሐ ወይም መመለስ ስለ ኃጢአታቸው ማዘን ወይም መጸጸት ይመስላቸዋል። 2ኛ ቆሮንቶስ 7፡10 እንደሚነግረን ከሆነ፥ ንስሐ ለኃጢአት ከማዘንና ከመጸጸት የበለጠ ነው። በ2ኛ ቆሮንቶስ 7፡10 ውስጥ ጳውሎስ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሚሆን ኀዘን ወደ ደኅንነት የሚያመጣ ንስሐ ለዘላለም ሕይወት ያበቃል ይላል። ኀዘን ከንስሐ ጋር አንድ አይደለም። እርግጥ ስለ ኃጢአት ማዘን ለንስሐ ያበቃል። ግን ንስሐ በኃጢአት ከማዘን ይበልጣል። ንስሐ በኃጢአት በማዘን ይጀመራል። ነገር ግን በዚህ አይገታም። ንስሐ ኃጢአትን በተመለከተ የአስተሳሰብና የልቦና ለውጥ ነው። ይህ የአስተሳሰብና የልቦና ለውጥ ብቻ ደኅንነትን ያመጣል። የዓለም ኀዘን ስለ ኃጢአት መጥፎ ውጤት ማዘንን ያመለክታል። ስለዚህ የዓለም ኅዘን የአስተሳሰብና የልቦና ለውጥን አያመጣም። የዓለም ኅዘን የሚያዝኑ ሰዎች ኃጢአት ስለሠሩ ያዝናሉ። ነገር ግን መሠረታዊ ኀዘናቸው ኃጢአት መጥፎ ውጤትን ስላስከተለባቸው ነው። እንዲህ ያለው ኀዘን ወደ እውነተኛ የልብና የአስተሳሰብ ለውጥ ስለሚያመራ ደኅንነትን ሊያመጣ አይችልም። ይህን የመሰለ ኀዘን ያለባቸው ሰዎች የኃጢአት ውጤት ወደ ሆነው ወደ መንፈሳዊ ሞት እያመሩ ናቸው። 

አንድ ወደ ንስሐ ያልመራ ዓለማዊ ኀዘን ምሳሌ ሆኖ ሊጠቀስ የሚችል ምሳሌ ማቴዎስ 27፡3 ላይ ይገኛል። የአይሁድ መሪዎች በኢየሱስ ላይ መፍረዳቸውን ይሁዳ ባየ ጊዜ ተጸጸተ። እዚህ ላይ የግሪኩ ቃል እኛ ስናጠናው ከነበርነው «ንስሐ» ከሚለው ለየት ይላል። የግሪኩ ቃል ስለ አንድ ነገር መጸጸት ስለ አንድ ነገር ማዘን ወይም ስለ አንድ ነገር ክፉኛ የስሜት መነካት ነው። ነገር ግን አንድ ሰው አስተሳሰቡን ወይም ልቡን ለወጠ ማለት አይደለም። ኢየሱስ ስለ ተፈረደበት ይሁዳ ተጸጸተ። ኢየሱስ ንጹሕ ሰው እንደ ነበረ ትዝ አለው። ስለዚህ ኃጢአት የሌለበትን ሰው እንደ ወንጀለኛ አላልፎ በመስጠቱ ተጸጸተ። ምንም እንኳን በማቴዎስ 27፡24 ላይ ኃጢአቱን ቢናዘዝም፥ የተጻጸተው ንጹሕ ሰው አሳልፎ በመስጠቱ ብቻ ነበር። ግን አስተሳሰቡን ለውጦ ኢየሱስን እንደ መሢሕ ሊቀበል አልፈለገም። ወደ ተቀሩት ደቀ መዛሙርት ዘንድ ሄዶ በፊታቸው ንስሐ በመግባት ፈንታ፥ እንዲሁም ወደ ኢየሱስ መስቀል ቀርቦ በኢየሱስ ፊት ንስሐ መግባት ሲኖርበት፥ ወጥቶ ሄዶ ራሱን ሰቀለ። ኀዘኑ ወደ መንፈስ ጭንቀት ወሰደው። ስለሆነም ለኢየሱስ አዎንታዊ እምነት አላበቃውም። የእርሱ ኀዘን ራሱን እንዲያጠፋ እደረገው እንጂ ለእውነተኛ ንስሐ አላደረሰውም። 

ሌላው ዓለማዊ ኀዘን በዕብራውያን 12፡17 ውስጥ ይገኛል። ዕብራውያን 12፡16 ኤሳውን እግዚአብሔርን የማይፈራና ለአንድ ጊዜ ምግብ ሲል ብኩርናውን የሸጠ ነውረኛ ሰው መሆኑን ይናገራል። ብኩርናውንም እንደ ሸጠ ትዝ ባለው ጊዜም አዘነ። በእውነትም ስላዘነ አለቀሰ፥ ጮኸም። ግን ኀዘኑ ስለ ምን ነበር? ኀዘኑ ውርስ ስላጣ ብቻ ነበር። ስለ ውርሱ መንፈሳዊ እሴት አለማዘኑን ጥቅሱ ያስረዳል። ኃጢአቱ ስላልታየው በኃጢአት የተሞላው ልቡ ሳይለወጥ ቀረ። ከቤተሰቡ መንፈሳዊ ውርስ ይልቅ ምግብንና ዓለማዊ ነገሮች በለጡበት። ስሜቱና አስተሳሰቡ በኃጢአት የተሞላና ዓለማዊ መሆኑ አልታየውም ነበር። እንዲያውም ስላጣው ነገር ዓለማዊ ኀዘን ተሰማው። አዝኗል ምክንያቱም ኃጢአቱ ለእርሱ ጠቃሚ የነበረውን ውድ ነገር አሳጥቶታል። ግን ኀዘኑ እውነተኛ ንስሐን የሚያመለክት ስለ ኃጢአትና ደኅንነት የተደረገ እውነተኛ የአስተሳሰብ ለውጥ አልነበረም። 

ጥያቄ፡- እናንተ የምታውቋቸው ሰዎች ወይም ራላችሁ ስለ ኃጢአታችሁ ተሰምቶአችሁ ያዘናችሁበትን፥ ያለቀሳችሁበትንና የሃችሁበትን፥ ስለ ኃጢአታችሁም ራሳችሁን የጎዳችሁስትን ግን ወደ እውነተኛ ንስሐ ያልገባችሁበትን ምሳሌዎች ታስታውሳላችሁ? እስቲ ምሳሌዎቹን ጻፉ። 

ጥያቄ፡- እናንተም ሆናችሁ ሌላ የምታውቁዋቸው ሰዎች ለእግዚአብሔር መንፈሳዊ ሥራ በመሥራት የኃጢአት ይቅርታ ለማግኘት ሞክራችኋል? ስለዚህ ሁኔታ የምትጠቅሱዋቸው ምሳሌዎች ካሉ ጻፉዋቸው። 

ዛሬ ብዙ ሰዎች ኀዘንንና ጸጸትን ከንስሐ ጋር ያደባልቃሉ። ስለ ኃጢአታቸው ካዘኑ ወይም ከኃጢአታቸው የተነሣ አንድ ነገር እንዳጡ ከተሰማቸው፥ ይህንን ከንስሐ ይቆጥሩታል። ለምሳሌም ያህል፥ አንድ ሰው ያመነዝር ይሆናል። እርሱ ወይም እርሷ ያላገቡ ከሆኑ ድንግልናቸውን አጥተዋልና፥ ያገቡ ከሆኑ ደግሞ ትዳራቸው ተበድሏልና ያዝናሉ። ወይም አንድ ሰው ተናድዶ ወዳጁን ወይም ሚስቱን ወይም ልጆቹን ይመታና ይጎዳቸዋል፣ ኋላም ይህ ሰው ያዝናል። ምክንያቱም የሚወዳቸውን ሰዎች ጎድቷልና ነው። ወይም አንድ ሰው ከመሥሪያ ቤቱ አንድ ነገር ይሠርቅ ወይም አታልሎ ይወስድና ከሥራው ይባረር ይሆናል። ኋላም እንዲህ ያሉ ሰዎች ያዝናሉ። ምክንያቱም ከሥራቸው ስለ ተባረሩ ነው፡፡ እንዲህ ባሉ መንገዶች ኃጢአት የሚሠሩ ሰዎች ስለ ኃጢአታቸው አጥብቀው ያለቅሳሉ። ስለ ኃጢአታቸው ክፉኛ ስለሚያዝኑ አካላቸውን እስከ መጉዳት ይደርሳሉ። ይህ ሁሉ ኀዘን ሲታይ ዓለማዊ ኀዘን ብቻ ነው። ይህንን የመሰለ ኀዘን የንስሐ ኀዘን አይደለም። ንስሐ እንዲያው ብቻ ኃጢአት ስለ ሠራን የምናዝነው ኀዘን አይደለም። ንስሐ አንድ ነገር ስለ ጠፋብን ወይም ስለ አጣን ወይም ስለ ኃጢአት የምናዝነው ኀዘን አይደለም። ንስሐ ስለ ኃጢአት ያለንን አስተሳሰብ መለወጥ ነው። ንስሐ ኃጢአት ከእግዚአብሔር ለይቶ ወደ ሲኦል የሚጥለን መሆኑን መገንዘብ ነው። ንስሐ እኛ በገዛ ኃይላችን ኃጢአት መሥራትን መግታት እንደማንችል ማወቅ ነው። ንስሐ ማለት በኃጢአታችን ጉዳይ ራሳችንን ከእግዚአብሔር ጋር ማስታረቅ እንደማንችል መረዳት ማለት ነው። ንስሐ ስንል ኢየሱስ ብቻ እኛን ከኃጢአት አላቅቆ ሊያድነን እንደሚችል መቀበል ነው። ንስሐ ኢየሱስ ከኃጢአት የሚያድነን መድኅን ስለሆነ ከኃጢአት ተመልሰን ወደ እርሱ መምጣት ነው። 

2.4 ንስሐ ለእግዚአብሔር አንድ መንፈሳዊ ተግባርን መፈጸም ሳይሆን ወደ ኢየሱስ መመለስ ነው። 

ንስሐ አንዳንድ ሰዎች ስለሠሩት ኃጢአት ካሣ ለእግዚአብሔር የሚደረግለት ትልቅ መንፈሳዊ ክፍያ እንደሆነ አድርገው ይቆጥሩታል። ስለዚህ ለድሆች ብዙ ገንዘብ በመመጽወት ወይም ለቤተ ክርስቲያን በመስጠት ለኃጢአታቸው ንስሐና ይቅርታን የሚያገኙ ይመስላቸዋል። እንዴዚሁም ወደ ታወቀ ቤተ ክርስቲያን ወይም ደብር ለብዙ ጊዜ ተጉዘው በመሄድና በመሳለም፥ ይህም ባይሆን በመመንኮስ፥ እንዲሁም ለረጅም ቀናት በመጦም ለኃጢአታቸው ይቅርታ እንደሚያገኙ አድርገው ያምናሉ። ስለዚህ እነዚህ ሰዎች የሚፈጽሟቸውን ተግባራት ስንመለከት፥ ንስሐ ገብቶ የኃጢአት ይቅርታን ማግኘት የሚቻለው አንድ ዓይነት መንፈሳዊ ተግባር ለእግዚአብሔር በመፈጸም ሆኖ ይታያቸዋል። ይህ በመሆኑ እንዲህ ያሉ ሰዎች ይህን መሰል አስተሳሰብ የሚኖራቸውና እንዲህ ያለ ተግባር ለመፈጸም የሚነሣሁት ይህ በጎ ተግባራቸው ለኃጢአት ይቅርታ እንደ ሚዛን ወይም እንደ አቻ ሆኖ ይቅርታውን እንዲያስገኝላቸው በማመን ነው። ስለዚህም ይህ የሚፈጽሙት ጥረት ያለበት ተግባር ቀደም ሲል ለፈጸሙት ትልቅ ኃጢአት ካሣ ለእግዚአብሔር የሚከፈል ተቀባይነት ያለው ሥራ ነው ባይ ናቸው። እዚህ ላይ ማስተዋል ያለብን ሰዎች ለሚፈጽሙት ኃጢአት ማካካሻ ይሆነናል ብለው ወይም ሚዛን ይደፋል በማለት ተነሣሥተው መልካም ሥራ ለመሥራት በሚጥሩበት ጊዜ ይህ እምነታቸው ለንስሐና ለኃጢአት ስርየት አያበቃቸውም። እንደ እውነቱ ከሆነ ለምንፈጽመው ኃጢአት የምናደርገው የበጎ ሥራ ማካካሻ ጥረት ከንስሐና የኃጢአት ይቅርታ መሠረተ አሳብ ጋር ይቃረናል። እውነተኛ ንስሐና የኃጢአት ይቅርታ የመልካም ሥራ ካሣ ክፍያ እንደማይደረግበት አምኖ መቀበል ነው። ስለሆነም ንስሐ ማለት ወደ ኢየሱስ መመለስና እርሱ በመስቀል ላይ ስለ ኃጢአታችን የከፈለውን ካሣ ወይም ተግባር አምኖ መቀበል ነው። 

ጥያቄ፡- ስለ ኃጢአታችሁ በእውነት ንስሐ መግባታችሁን እንዴት ትገልጻላችሁ? 

የእውነተኛ ንስሐ ምልክት መገለጥው ብድግ ብሎ ብቻ መጮኽ ወይም ማልቀስ አይደለም። እንደዚሁም የእውነተኛ ንስሐ ማስመስከሪያው የተለየና ትልቅ መንፈሳዊ ተግባርን ማድረግም አይደለም። በተጨማሪም እውነተኛ ንስሐ ሲባል አካላችንን በመጉዳት የሚፈጸም ሁኔታ አይደለም። ግን የእውነተኛ ንስሐ መገለፃ ኢየሱስ ኃጢአታችንን ይቅር እንደሚለን በመተማመንና እኛ ኃጢአትን መቋቋም እንድንችል እርሱ በሚሰጠን የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ላይ መደገፍ ነው። ይህንንም በእርሱ ላይ የመደገፍ ወይም የመተማመን ሁኔታ በጸሎታችን፥ በጾማችን፥ መጽሐፍ ቅዱሳችንን አዘውትረን በማንበብና ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር ብዙ ጊዜ በቤተ ክርስቲያን በመገኘት እንገልጽ ይሆናል። ይሁንና በኢየሱስ ላይ መደገፍ ማለት ግን አብዛኛውን ጊዜ ልባችንና አስተሳሰባችንን በእርሱ መሙላትና ፈቃዳችንን ሁሉ ለእርሱ አሳልፈን መስጠትን ይመለከታል። 

ጥያቄ፡– በሕይወታችሁ ውስጥ ካሉት ሁኔታዎች በአንዱ ትልቅ የኃጢአት ይቅርታን የምትሹበትንና በኢየሱስም ላይ የምትደገፉበትን ውሳኔ የምትገልጡበትን በመለየት በጽሑፍ አስረዱ። 

ምንጭ፡- “አስተምህሮ ክርስቶስና ደኅንነት”፤ ጽሑፍ፣ በዶ/ር ስቲቭ ስራውስ፤ ትርጉም በኃይሉ ልመንህ

Exit mobile version