ሁሉን ፈትኑ መልካሙንም ያዙ፡፡
ኮትኩቶ ያሳደገን ባህል ጥያቄ መጠየቅ ነውር እና ትዕቢት እንደሆነ ነግሮናል። ስለ እግዚአብሔር፣ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ፣ በጥቅሉ ሰለ መንፈሳዊ ነገሮች መጠየቅ መቅሰፍትን ወደ ቤታችን እንደ መጋበዝ፣ በእግዚአብሔር ላይ ያለንን እምነት ጥያቄ ውስጥ እንደመክተት አድርጎ በሚቆጥር ቤተሰብ እና ማህበረሰብ መካከል ያደገ፣ የነፍሱን ጥያቄዎች በአግባቡ ለመመለስ ብዙ እንቅፋቶች ይገጥመዋል። እግዚአብሔርን ማመን፣ ከእውቀት ይነሳል። ይህ እውቀት ደግሞ ከእግዚአብሔር ቃል ይመነጫል፣ ‘‘እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው’’ (ሮሜ 10፡17)። ‘‘የአባትህን አምላክ እወቅ በፍጹም ልብና በነፍስህ ፈቃድም አምልከው ብትፈልገው ታገኘዋለህ ብትተወው ግን ለዘላለም ይጥልሃል’’ (1ዜና 28፡9) ‘‘በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፥ እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል’’ (መጽሐፈ ምሳሌ 3፥6) የሚለው የእግዚአብሔር ቃል፣ አምላከችንን እንድናውቅና እንድንፈልግ አይመክረንም ወይ?
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እውቀት ምን ይላል?
በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ስለ እውቀት ተናግረዋል። እስቲ ለአብነት የተወሰኑትን እንመልከት፡-
መዝሙር 119፥66 “በትእዛዛትህ ታምኛለሁና መልካም ምክርና እውቀትን አስተምረኝ።”
ምሳሌ 1፡29-31 “እውቀትን ጠልተዋልና፥ እግዚአብሔርንም መፍራት አልመረጡምና፣ ምክሬን አልፈቀዱምና፥ ዘለፋዬንም ሁሉ ንቀዋልና ስለዚህ የመንገዳቸውን ፍሬ ይበላሉ፥ ከራሳቸው ምክር ይጠግባሉ።”
ምሳሌ 2፡1-5 “ልጄ ሆይ፥ ቃሌን ብትቀበል፥ ትእዛዜንም በአንተ ዘንድ ሸሽገህ ብትይዛት፥ ጆሮህ ጥበብን እንዲያደምጥ ታደርጋለህ፥ ልብህንም ወደ ማስተዋል ታዘነብላለህ። ረቂቅ እውቀትን ብትጠራት፥ ለማስተዋልም ድምፅህን ብታነሣ፥ እርስዋንም እንደ ብር ብትፈላልጋት፥ እርስዋንም እንደ ተቀበረ ገንዘብ ብትሻት የዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን መፍራት ታውቃለህ፥ የአምላክንም እውቀት ታገኛለህ።”
ምሳሌ 2፡6 “እግዚአብሔር ጥበብን ይሰጣልና ከአፉም እውቀትና ማስተዋል ይወጣሉ፡፡”
ምሳሌ 8፡10 “…ከምዝምዝ ወርቅም ይልቅ እውቀትን ተቀበሉ።”
ምሳሌ 19፥2 “ነፍስ እውቀት የሌለባት ትሆን ዘንድ መልካም አይደለም …”
ያለ እውቀት ትክክለኛ አምልኮ ሊኖር አይችልም፡፡
እውቀትን ወደ ጎን ያደረገ ክርስትና ሊኖር አይችልም። ሊነሳ የሚገባው ጥያቄ፣ ‘‘እውቀት ያስፈልጋል ወይስ አያስፈልግም?’’ የሚል ሳይሆን ‘‘የያዝነው እውቀት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው ወይስ ባህላዊ ወግ እና ስርአት ብቻ?’’ የሚለው ነው። አምልኮ በእግዚአብሔር ቃል ላይ ካልተመሰረት ከንቱ ነው ነው፡፡ እኛ በመረጥነው መንገድ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ አምልኮ ልንፈጽም አንችልም፡፡ ‘‘የሰውም ሥርዓት የሆነ ትምህርት እያስተማሩ በከንቱ ያመልኩኛል …’’ (ማቴዎስ 15፥9)፡፡ ከንቱ አምልኮ፣ ትክክለኛ እውቀት ጠልቶ እና ፈርቶ በሰው ስርአት እግዚአብሔርን ለማምለክ መጣር ነው።
እውቀት የጎደላቸው እግዚአብሔርን በተሳሳተ መንገድ “ያመልኩታል”። የክርስቲያን ደሴት እየተባለች በምትጠራው አገራችን ኢትዮጵያ ያለውን የባእድ አምልኮ ላስተዋለ በእርግጥ የክርስቲያን ደሴት ናት ወይ ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው። ይህ ሁሉ ውጥንቅጥ የእግዚአብሔርን ቃል ያማቅለል ውጤት ነው፡፡ ‘‘እናንተ ከአሕዛብ ወገን ሆናችሁ ያመለጣችሁ፥ ተሰብስባችሁ ኑ በአንድነትም ቅረቡ የተቀረጸውን የምስላቸውን እንጨት የሚሸከሙና ያድን ዘንድ ወደማይችል አምላክ የሚጸልዩ እውቀት የላቸውም’’ (ኢሳይያስ 45፥20)። ይህን ምስኪን ሕዝብ እናውቃለን እያሉ ያለእውቀት የመሩትን፣ እረኛ ነን እያሉ ወደጠላት ወጥመድ የከተቱትን አላዋቂ እውር መሪዎችን፣ እግዚአብሔር እነዲህ ይላል፣ ‘‘ሕዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሣ ጠፍቶአል አንተም እውቀትን ጠልተሃልና እኔ ካህን እንዳትሆነኝ እጠላሃለሁ የአምላክህንም ሕግ ረስተሃልና እኔ ደግሞ ልጆችህን እረሳለሁ’’ (ትንቢተ ሆሴዕ 4፥6)።
ዘመን የጠገበ እውቀት፣ የሸመገለ ውሸት ሊሆን ይችላል፡፡
እውቀት ሁሉ እውነት አይደለም። ከ1000 አመት በላይ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣም ሆነ ትላንት የገበየነው እውቀት፣ የሁለቱም ትክክለኛነት ከእግዚአብሔር ቃል አንፃር ሊጣራ ይገባል። እውቀት ዘመን ስለጠገበ እውነት ሊሆን አይችልም፤ ስለዘገየም ውሸት ሊሆን አይችልም። እውቀትን እውነት የሚያደርገው መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሆኑ ብቻ ነው። ፓትሪያርክ ይናገረው ተራ ምዕመን፣ ሴትም ትናገረው ወንድ፣ ልጅም ይናገረው አዋቂ፣ የተማረም ይናገረው ፊደል ያልቆጠረ፣ የቺን እውቀት እውነት የሚያደርጋት በእግዚአብሔር ቃል ተመዝና ማለፏ ብቻ ነው።
“አትመራመር”፤ የሚለው የአገራችን የተለመደ አባባል ራሱ ሊመረመር ይገባዋል፡፡
የእግዚአብሔርን ቃል እንዳንመረምር የሚሞጉቱን ሰዎች የቤሪያ ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተመዘገቡ ክርስቲያኖች መሆናቸውን ዘንግተውት ይሆን? ‘‘እነዚህም በተሰሎንቄ ከሚኖሩት ይልቅ ልበ ሰፊዎች ነበሩና። ነገሩ እንደዚሁ ይሆንን? ብለው ዕለት ዕለት መጻሕፍትን እየመረመሩ ቃሉን በሙሉ ፈቃድ ተቀበሉ (የሐዋርያት ሥራ 17፡11)። እነዚህ ክርስቲያኖች፣ ቃሉን መሙሉ ፈቃድ ከመቀበላቸው በፊት ይመረምሩ ነበር። ‘‘ቃሉን አትመርመር’’ የሚል የእግዚአብሔር ቃል የለም። ይህ የሰው ወግ እና ስርአት ብቻ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የሚለው፣ “ቃሉ በሙላት ይኑርባችሁ” (ቆላሲያስ 3፡16)፣ “ለሚጠይቋችሁ ጥያቄ ሁሉ መልስ ለመስጠት የተዘጋጃቹ ሁኑ” (1ጴጥሮስ 3፡15) ነው።
ይህ መድረክ፣ ሰከን ባለ መንፈስ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረንን እውነት የምንመረምርበት እና አንዳችን ከሌላችን እውቀት የምንገበይበት ነው።
አሰተያየትዎን ከእያንዳንዱ ትምሕርት ግርጌ በሚገኙ የሃሳብ መስጫ ሳጥኖች ውስጥ በማስፈር እንዲልኩ በትህትና ተጋብዘዋል። መልካም ጥናት!!!
የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፣ የእግዚአብሔር አብ ፍቅር የመንፈስ ቅዱስም ኅብረት ከሁላችሁ ጋር ይሁን። አሜን።
አዳነው ዲሮ ዳባ
የድረ-ገጹ አዘጋጅ