የወንጌል በድረ-ገጽ አገልግሎት የእምነት አቋም

  1. በሶስትነትና በአንድነት በሚኖር በአብ፣ በወልድ እና በመንፈስ ቅዱስ አንድ አምላክ እናምናለን።
  2. ሰው በእግዚአብሔር አምሳል መፈጠሩን በኃጢአት መውደቁን እና በኢየሱስ ክርስቶስ እስከሚያምን ድረስ የእግዚአብሔር ቁጣና ፍርድ ያለበት በደለኛ መሆኑን እናምናለን፡፡
  3. ከኃጢአት ዕዳ ኃይልና ቅጣት ሰው ሊድን የሚችለው በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ብቻ እንደሆነ እናምናለን፡፡
  4. መጽሐፍ ቅዱስ ዘላለማዊና የማይሻር የእግዚአብሔር ቃል እንደሆነ እናምናለን፡፡ 
  5. ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ፤ ፍፁም አምላክ ፍፁም ሰው መሆኑን፤ እኛን ለማዳን ከድንግል ማሪያም መወለዱን፤ ለአዳም ዘር ሁሉ ስለ ኃጢአታቸው ሲል ሞቶ መቀበሩን፤ በአካል ከሙታን ተነስቶ በክብር ማረጉን፤ በአብ ቀኝ መቀመጡን፤ ዳግመኛም በታላቅ ክብርና ኃይል ለፍርድ እንደሚመለስ እናምናለን፡፡
  6. መንፈስ ቅዱስ በዚህ ዘመን በአማኞች ሕይወት እንደሚሰራ ለአገልግሎታቸውም ኃይልን እንደሚያለብስ እናምናለን፡፡
  7. ቅዱሳን መላዕክት ሕያዋን መሆናቸውን፤ በእግዚአብሔር ፊት እንዳሉ፤ ቅዱሳንን እንደሚያገለግሉ፡፡ ሰይጣን በእግዚአብሔር ያመጸ የውሸት አባት መሆኑን እና በመጨረሻም ወደ ተዘጋጀለት ወደ ገሃነም እሳት እንደሚጣል እናምናለን።
  8. በክርስቶስ ኢየሱስ የሚያምኑ በቅድስና መመላለስ እንዳለባቸው እናምናለን፡፡
  9. በክርስቶስ ኢየሱስ ያመነ ሰው፣ በክርስቶስ ሞት እና ትንሳኤ መተባበሩን ለመግለጽ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም በውሃ ውስጥ በመጥለቅ መጠመቅ እንዳለበት እናምናለን፡፡
  10. የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ስጋ እና ደም ዳግመኛ ልደት የተቀበሉ የውኃ ጥምቀት ሥርዓት የፈፀሙና ራሳቸውን መርምረውና ፈትነው ያዘጋጁ ምዕመናን መውሰድ እንደሚችሉ እናምናለን፡፡
  11. የክርስቶስ አካል በሆነች ከእግዚአብሔር መንፈስ ዳግም የተወለዱ ሁሉ በሚገኙባት በአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን፡፡
  12. ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በክብር እንደገና ሲመጣ፣ በእርሱ አምነው የሞቱት ቀድመው እንደሚነሱ ሕያዋን የሆኑት ደግሞ እርሱን ለመቀበል እንደሚነጠቁ ኃጥአን ግን ወደ ዘላለማዊ ስቃይ እንደሚሄዱ እናምናለን::