ስለ «ደኅንነት» በምንናገርበት ጊዜ ምን ማለታችን ነው? «ደኅንነት» የሚለው ቃል አንድ ሰው ከአንድ ነገር መዳኑን የሚያመለክት ከሆነ፥ እኛ የዳንነው ከምንድን ነው?
ጥያቄ፡- ሀ) በለፈራችሁ የሚገኙ ሰዎችን ስለ ደኅንነት ትርጉም ወይም ምንነት፥ ወይም መዳን ምን ማለት እንደሆነ ብትጠይቋቸው መልሳቸው ምን የሚሆን ይመስላችኋል? ለ) ዛሬውኑ ጥቂት ቆየት ብላችሁ ቢያንስ ለሦስት ሰዎች ይህንኑ ጥያቄ አቅርቡላቸው። ሰዎቹም፡- ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን፥ ከሙስሊሙ አማኝና ከወንጌል አማኞች መካከል ሊሆኑ ይችላሉ። ሰዎቹን እግኝታችሁ ከጠየቃችኋቸው በኋላ ተመልሳችሁ፥ እነርሱ የሚሰጧችሁን መልሶች እናንተ ቀደም ብላችሁ ከጻፋችኋቸው አሳቦች ቀን አስፍሩ።
እኔ አንድ ጊዜ ራሱን ክርስቲያን አድርጎ ከሚቆጥር ሰው ጋር እነጋገር ነበር። እናም ሰውዬውን፡- «እስቲ እግዚአብሔር አንተን ስላዳነበት ጊዜ ንገረኝ» አልኩት። እርሱም አንድ ጊዜ የመኪና አደጋ አጋጥሞት ከሞትና ከመቁሰል እግዚአብሔር እንደ ጠበቀው አጫወተኝ። በሌላ ጊዜ ደግሞ ራስዋን ክርስቲያን አድርጋ ከምትቆጥር ወይዘሮ ጋር እነጋገር ነበር። እርሷ ከእግዚአብሔር መዳንን ስላገኘችበት ጊዜ እንድትነግረኝ ጠየቅኋት። እርሷም ወንዝ ልትሻገር ስትል ጅብ ስለ መጣባት፥ ቅዱስ ገብርኤል እንዲያድናት ተማጽናው ጅቡ ሳይበላት ትቷት እንደ ሄደና ቅዱስ ገብርኤል እንዳዳናት ነገረችኝ። በእነዚህ ሁለት ሰዎች አስተሳሰብ «ደኅንነት» ወይም መዳን ማለት፥ በአካል ላይ ጉዳት ወይም ሞት ሳይደርስ መትረፍ ማለት ነው።
ጥያቄ፡- ሀ) ኢያሱ 2፡12-13 አንብቡ። ረዓብ ክን ለመዳን ፈለገች? ለ) መዝሙር 33፡18-19 አንብቡ። እግዚአብሔር የሚፈሩትን ሰዎች ከምን ያድናቸዋል?
መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ጊዜ ከጉዳትና ከሞት ስለ መዳን፥ ማለትም ስለ አካላዊ ደኅንነት ይናገራል። ለምሳሌ ያህል፥ በኢያሱ 2፡12-13 ውስጥ እንደምንመለከተው ረዓብ ኢያሱ ወደ ኢያሪኮ ለላካቸው ሁለቱ ሰላዮች እስራኤላውያን ከተማይቱን በሚይዙበት ጊዜ እርሷንና ቤተሰብዋን ከሞት እንዲያድኑዋቸው ተማጸነቻቸው። ዳዊት በመዝሙር 33፥18-19 ውስጥ እግዚአብሔር የሚፈሩትን ከሞትና ከረሃብ የሚያድን በመሆኑ ውዳሴ አቅርቦለታል። ሆኖም ሰው ከሥጋዊ ወይም ከአካላዊ ሞት በሚድንበት ጊዜ፥ ደኅንነቱ ጊዜያዊ ብቻ ነው። በመጨረሻው ላይ ሰዎች ሁሉ ሟቾች ናቸው (ዕብ. 9፡27)። ምንም እንኳን እግዚአብሔር ሰውን በረሃብ ወይም በመኪና አደጋ ከሚከሰት ሞት ወይም በጅብ ከመበላት ቢያድነውም፣ ከእነዚህ ሁሉ ድኖ የሚቆየው ለተወሰነ ጊዜ ሲሆን፥ በሌሎች ምክንያቶች መሞቱ የማይቀር ነው። ከሥጋ ሞት ከመዳን እጅግ የሚበልጠውና ጠቃሚው ከመንፈስ ሞት መዳን ነው። አንድ ሰው ከእግዚአብሔር ተለይቶ ሳለ የሥጋ ሞት ቢሞት፥ ሰውዬው ለዘላለም ይሞታል፥ ከእግዚአብሔርም ለዘላለሙ ተለይቶ ይቀራል። ስለዚህ እጅግ ጠቃሚው የደኅንነት ዓይነት ከሥጋዊ ሞት መዳን ሳይሆን፥ ከእግዚአብሔር በመንፈስ ከመለየት መዳን ነው።
በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች እጅግ በጣም አስፈላጊ የሆነው የደኅንነት ዐይነት፥ ከጭቆናና ከድህነት የሚገላግል ደኅንነት እንደሆነ አድርገው ያምናሉ። ለዚህም የሚሰጡት ምክንያት በዓለም ላይ ብዙ ሕዝቦች ድሆችና የሚሠቃዩ መሆናቸውን ነው። ሀብታሞችና ኃይለኞች የሆኑ ሰዎች ብዙ ጊዜ ይጨቁኗቸዋል። ስለዚህ እንዲህ ያሉ ሰዎች ከሚደርስባቸው ጭቆናና ድህነት ሊድኑ ይገባል። አንዳንድ ጊዜ እስራኤላውያን በግብፅ በባርነት ቤት በነበሩበት ጊዜ፥ እግዚአብሔር ይደርስባቸው የነበረውን ጭቆናና ድህነት ተመልክቶ እንዳዳናቸው በመጥቀስ ይናገራሉ። ከግብፅ ባርነት ነፃ መውጣት (ዘጸአት) የተጨቆኑ ሕዝቦች ሊያገኙት የሚገባቸው መዳን ምሳሌ ነው ይላሉ።
ጥያቄ፡- ሀ) መዝሙር 35፡10 አንብቡ። እግዚአብሔር ለድሆችና ለተቸገሩ ምን| ያደርግላቸዋል? መዝሙር 72፡12-14 አንብቡ። እግዚአብሔር የተቸገሩትን ከምን ያድናቸዋል? ለ) መዝሙር 82፡2-4 አንብቡ። እግዚእብሔር ለደካሞች፥ ለተቸገሩና ለድሆች ምን እንዲደረግላቸው ያዝዛል?
የእኛ አምላክ በድሆችና በተጨቆኑት ጎን የሚቆም እምላክ ነው። መዝሙር 35፡10 ውስጥ እንዲህ ይላል፡- «ችግረኛን ከሚቀማው እጅ፥ ችግረኛንና ድሀውንም ከሚነጥቀው እጅ ታድነዋለህ።» እንዲሁም በመዝሙር 72፡12-14 ባለው ክፍል፡- «ምስኪኖችን ከሞት ያድናል፥ ሕይወታቸውንም ከግፍና ከአስጨናቂዎች ያድናል» ይላል። በመዝሙር 82፡2-4 ውስጥ፡ ደካሞችን፥ ምስኪኖችንና ድሆችን ኃጢአተኞች ከሚያደርሱባቸው ጭቆና እንድንታደጋቸውና መብታቸውን እንድናስከብር እግዚአብሔር ያዝዛል።
መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ሕዝብ ድሆችንና የተጨቆኑትን እንዲረዱ ያዝዛል። ለተበደሉት ፍትሕን ለማምጣት መጣር አለብን። የድሆችንና የሚሠቃዩ ሰዎችን ችግር ለማቃለል መሞከር ይገባናል። ሆኖም በዚህ ምድር ላይ የፍትሕ መጓደልና ድኅነት ሊኖር የቻለው በኃጢአት ምክንያት ነው። የግለሰቦች ኃጢአት የፍትሕ መጓደልንና ድኅነትን ያስከትላል። የፍትሕ መጉደልና የድኅነት ችግር መፍትሔ ሊያገኝ የሚችለው የጨቋኞች ልብና ሕይወት ሲለወጥ ብቻ ነው። ከእግዚአብሔር መራቃቸው ሲቀርና ሌሎችን መጨቆናቸው ሊገታ ከዚያም ለፍትሕ መቃናት መሥራት ሲጀምሩ ያን ጊዜ መፍትሔ ያገኛል። ከእግዚአብሔር ጋር ሊታረቁና ነገሮች ትክክል ሲሆኑ ብቻ ነው በዚህ ምድር ላይ ትክክለኛ ድርጊት የሚፈጽሙት።
ነገር ግን ክርስቶስ ወደዚህ ምድር ዳግም ተመልሶ እስከሚመጣ ድረስ፥ ሌሎችን በመጨቆን የፍትሕ መጓደልንና ድህነትን የሚያመጡ ኃጢአተኞች የሆኑ ሰዎች ምን ጊዜም ይኖራሉ። ክርስቶስ ፍጹም የሆነ የጽድቅ መንግሥቱን ለማቋቋም ወደ ምድር በሚመለስበት ጊዜ ብቻ እግዚአብሔር የፍትሕ መጓደልንና ድህነትን ያስወግዳል። ድሆችና የተጨቆኑ ሁሉ ካሉበት አሰቃቂ ኑሮ ተላቅቀው ደኅንነትን የሚያገኙት ወደ እግዚአብሔር የጽድቅ መንግሥት ለመግባት እርግጠኞች ሲሆኑ ብቻ ነው። ስለዚህ ወደፊት የሚመጣው ፍጹም የሆነው የእግዚአብሔር መንግሥት ተሳታፊዎች ለመሆን፥ ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅ ይኖርባቸዋል። ከድህነትና ከፍትሕ እጦት ለመዳን ያለው ፍላጎት የላቀ ነው። ነገር ግን ከዚህ የሚበልጠው ከእግዚአብሔር ፊት ሰዎችን ከሚለየው ከኃጢአት መዳን ነው። በመሆኑም፥ ሰዎች ከኃጢአታቸው ከዳኑ በኋላ ብቻ፥ የፍትሕ መጓደልንና ድህነትን ለማስወገድ ሊሠሩ ይችላሉ። እንዲሁም ሰዎች በምድር ላይ ሆነው የእግዚአብሔር ፍጹማዊ መንግሥት ተካፋዮች ሊሆኑ የሚችሉት ከኃጢአታቸው ከዳኑ በኋላ ብቻ ነው።
ጥያቄ፦ ሀ) ዮሐንስ 3፡16-17 አንብቡ። እግዚአብሔር ልጁን ወደዚህ ዓለም የላከው ለምንድን ነው (ቁጥር 17? ለ) በልጁ ለሚያምን ምን ይሆንለታል (ቁጥር 16)?
ጥያቄ፡- ሀ) ዮሐንስ 11፡25-26 አንብቡ። በኢየሱስ ለሚያምኑት ምን ይሆንላቸዋል?
ጥያቄ፡- ሀ) ሮሜ 1፡16-17 አንብቡ። ሰዎች የሚድኑበት የእግዚአብሔር ኃይል ምንድን ነው (ቁጥር 16)? ለ) በወንጌል ውስጥ ምን ተገለጠ (ቁጥር 17)?
መጽሐፍ ቅዱስ አበክሮ እንደሚገልጸው፥ የሰው ልጆች ትልቁ ችግር ኃጢአት ነው። ኃጢአት ሰዎችን ከእግዚአብሔርና ሰዎችን ከሰዎች ለይቶአቸዋል። ኃጢአት ሕይወትን አሰቃቂ የሚያደርጉትን ሞትን፥ ጥፋትንና ጭቆናን አምጥቷል። በሞት የሚመጣው ችግር ሰዎች የኃጢአትን ተግባር መፈጸማቸው ብቻ አይደለም። ባለፈው ሳምንት እንደተመለከትነው፥ ሰዎች ሁሉ በኃጢአት ተወልደዋል። እንደዚሁም ሰዎች ሁሉ በተበላሸና በኃጢአት በተበከለ ባሕርይ ተወልደዋል። አእምሮአችን በኃጢአት ጨልሟል።
ምኞታችንም በኃጢአት ረክሷል። ፈቃዳችንም የኃጢአት ባሪያ ሆኖአል። በኃጢአት ስለተወለድን ከእግዚአብሔር ጋር የነበረንን ግንኙነት ለማደስና እንደ ቀድሞው ለማድረግ ምንም መልካም ተግባር ለማድረግ አቅም የለንም። ይህ በመሆኑ ሰዎች የሚያስፈልጋቸው፥ ከኃጢአትና እርሱ ከሚያስከትላቸው የከፉ ችግሮች ሊታደጋቸው የሚችል መድኅን ማግኘት ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ ትልቅ ትኩረት ወይም ክብደት የሚሰጠው ይህን ለመሰለው ደኅንነት ነው። በዮሐንስ 3፡17 ውስጥ ኢየሱስ ለኒቆዲሞስ እግዚአብሔር ዓለሙን ከኃጢአት ለማዳን ልጁን ወደ ምድር እንደ ላከው ነግሮታል። ይህ ታዲያ ምን ዓይነት ደኅንነት ነው? ከዚህ ቀደም ብሎ በተጠቀሰው በዮሐንስ 3፡16 ውስጥ ኢየሱስ ይህ ደኅንነት የዘላለም ሕይወት እንደሆነ ገልጾአል። የሥጋ፥ የመንፈስና ዘላለማዊ ሞት ሁሉም የኃጢአት ውጤቶች ናቸው። ሥጋዊ፥ መንፈሳዊና የዘላለም ሕይወት ደግሞ ልጁ የሚያመጣቸው የደኅንነት ውጤቶች ናቸው። በልጁ የሚያምኑ ሁሉ መንፈሳዊ ሕይወት ይኖራቸዋል። በዚህም ከእግዚአብሔር ጋር ባላቸው ግንኙነትና አንድነት ደግሞ ይተሳሰራሉ። በምንም አኳኋን ዳግም በመንፈሳቸው አይሞቱም (ዮሐ 11፡26)። በልጁ የሚያምኑ ሁሉ ሥጋዊና ዘላለማዊ ሕይወት ይኖራቸዋል። ቢሞቱም እንኳ ከእግዚአብሔር ጋር በአንድነት ለመኖር በዳግም ትንሣኤ ይነሣሉ (ዮሐ 11፡25)። ኢየሱስ የሚያመጣው ደኅንነት፥ በእርሱ ለሚያምኑት ሁሉ የዘላለም ሕይወትን በመዋጀት፥ በኃጢአት ምክንያት ለተከሰተው ችግር መፍትሔውን ይሰጣል።
ሐዋርያው ጳውሎስም የኢየሱስ ደኅንነት፥ ከኃጢአት መዳን እንደሆነ ያስተምራል። በሮሜ 1፡16 ውስጥ ሐዋርያው ጳውሎስ ሲናገር፥ ወንጌል የሚያምኑትን ሁሉ ለማዳን የእግዚአብሔር ኃይል ነው። ታዲያ ወንጌል ምንን ያመጣል? የሚቀጥለው ቁጥር (ሮሜ 1፡17) ጽድቅን ያመጣል ይላል። ደኅንነት ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቀናል። እንደዚሁም ደኅንነት፥ ሰዎች ከእግዚአብሔር ለተለዩበት ችግር መፍትሔውን ይሰጣል።
ምንም እንኳን መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ደኅንነት በብዙ አኳኋን የሚናገር ቢሆንም፥ ትልቅ አጽንኦት የሰጠው ኢየሱስ በሕይወቱ ወደዚህ ዓለም ስላመጣው ከኃጢአት መዳን፥ ደግሞም ስለ ሞትና ትንሣኤው ነው። ኃጢአት የሰው ልጅ መሠረታዊ ችግር ስለሆነ፥ በኢየሱስ የተገኘው የኃጢአት ደኅንነት፥ ማንም ሰው ከሚያገኘው በላይ የከበረ የደኅንነት ዓይነት ነው።
ጥያቄ፡- በምትኖሩበት አካባቢ ባሉ በአብዛኛዎቹ ሰዎች ዘንድ መጽሐፍ ቅዱስ በደኅንነት ላይ አጽንዖት የሰጠበት ትምህርት ከእነርሱ እምነት በምን ይመሳሰላል? ደግሞስ እንዴት ይለያል? ልዩነቶችስ እንደሚኖሩ ለምን አሰባችሁ?
በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች በዚህ ምድር ላይ የተደላደለ ሕይወት እንዲኖራቸው ይፈልጋሉ። ስለዚህ ማለፊያ ጤናና ሀብትም እንዲያገኙ ይሻሉ። እንደዚሁም ነጻነትንና በሌሎች ሰዎች ዘንድም መከበርን ይፈልጋሉ። እንግዲህ እንዲህ ያሉ ሰዎች የሚፈልጉት የደኅንነት ዓይነት በዚህ ምድር ላይ የተሟላ ኑሮን የሚሰጣቸውን ነው። ከዚህ የተነሣ ከኃጢአት የመዳኑ ጉዳይ ይህን ያህል አይማርካቸውም። እነርሱ ራሳቸው ከእግዚአብሔር የተለዩ መሆናቸው አይታወቃቸውም። በተጨማሪም ይህን ዓለም የሚያጋጥመውና በዓለምም ውስጥ የሚታዩ ችግሮችና ሥቃዮች ሁሉ የሰው ልጆች ከእግዚአብሔር ከመለየታቸው የተነሣ የሚከሰቱ መሆናቸውን አይገነዘቡም።
አንዳንድ ክርስቲያኖች እንዲህ ያሉ ሰዎች የእግዚአብሔርን ደኅንነት አምነው ቢቀበሉ እግዚአብሔር የተቀሩትን ችግሮቻቸውን ሁሉ እንደሚያስወግድላቸው በማሳሰብ ወደ ክርስቶስ ሊያመጡዋቸው ይሞክራሉ። ከዚህም በስተቀር የክርስቶስን ደኅንነት ቢቀበሉ፥ እግዚአብሔር መልካም ጤናና ቁሳዊ ሀብትን በሙሉ እንደሚቸራቸው ይነግሯቸዋል። የክርስቶስን ደኅንነት በሚቀበሉበት ጊዜ እግዚአብሔር ድህነታቸውንና ጭቆናቸውን እንደሚያስወግድላቸው ያወሷቸዋል።
ሆኖም፥ እግዚአብሔር ወደ ክርስቶስ የሚመጡትን ሰዎች ድህነትና ጭቆና በዚህ ሕይወት እያሉ የሚያስወግድላቸው ስለ መሆኑ በፍጹም ተስፋ አልሰጠም። በዚህ ፈንታ እግዚአብሔር የሰጠው ተስፋ እኛንና እርሱን የለየንን ኃጢአት የማስወገድ ተስፋ ነው። ከእርሱ ጋር ታርቀው አንድነታቸውን ለሚያድሱት፥ እግዚአብሔር የዘላለምን ሕይወት ሊሰጣቸው ቃል ይገባል። እንዲሁም ከእርሱ ጋር ያላቸውን ኅብረት ለሚያድሱ ሁሉ የዘላለምን ሕይወት ተስፋ ይሰጣል። ደኅንነታችንም ከፍጻሜ የሚደርሰው ወደዚህ ዘላለማዊ ሕይወት በምንገባበት ጊዜ ብቻ ነው።
ስለዚህ ከማያምኑ ሰዎች ጋር ስለ ወንጌል በምንወያይበት ጊዜ፥ ክብደትና ትኩረት ሰጥተን ማስረዳት የሚያስፈልገን የክርስቶስ ደኅንነት ከኃጢአት የሚያድንና ከእግዚአብሔር ጋር የሚያስታርቅ መሆኑን ነው። ይህ በመሆኑ ይህ ደኅንነት ችግራችንን ሁሉ አስወግዶ፥ ጤናንና ሀብትን በዚህ ዓለም ላይ የሚያድለን አይደለም። ይህኛው ደኅንነት፥ ለዘላለሙ ከእግዚአብሔር ጋር ፍጹም ደስታ እንደሚኖረን ተስፋን የሚሰጥ ደኅንነት ነው።
የደኅንነት መሠረት፡- የክርስቶስ ሞት
ከኃጢአትና ከክፉ ውጤቶች ለመዳን የሚያስችለው የዚህ ደኅንነት መሠረት ምንድን ነው? የደኅንነት መሠረቱ የኢየሱስ ክርስቶስ ሞት ነው።
ጥያቄ፡- 1ኛ ቆሮንቶስ 15፡3 እንብቡ። «ከሁሉም በፊት» በማለት ሐዋርያዉ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች ያስተማራቸው ምንን ነበር?
ጥያቄ፡- ሀ) ሮሜ 5፡6-8 አንብቡ። ክርስቶለ እግዚአብሔርን ለማያውቁት ምን አደረገ (ቁጥር 6)? ለ) ክርስቶስ በሞተልን ጊዜ እኛ ምን ዓይነት ሰዎች ነበር (ቁጥር 8)? 10ኛ ጥያቄ፦ 1ኛ ጴጥሮስ 3፡18 አንብቡ። የክርስቶስ ሞት ለእኛ ምን አደረገልን?
ጥያቄ፡– ኤፌሶን 1፡7 እና ማቴዎስ 26፡28 አንብቡ። የኃጢአት ይቅርታ በማን አማካይነት መጣ?
ጥያቄ፡- ዕብራውያን 9፡14-15 አንብቡ። ሀ) የክርስቶስ ደም ለእኛ ምን አደረገልን (ቁጥር 14)? ለ) የክርስቶስ ሞት ለእኛ ምን አደረገልን (ቁጥር 15)?
ከኃጢአት የመዳኛው መሠረት የክርስቶስ ሞት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ የቆሮንቶስ ሰዎችን ባስተማረ ጊዜ «ከሁሉ በፊት» ሲል የገለጸው ክርስቶስ ስለ እኛ ኃጢአት መሞቱን ለመናገር ነበር። ክርስቶስ ኃጢአታችንን ሊያስወግድልን ሞተ። እንዲሁም በኃጢአታችን ምክንያት የሚመጡትን ክፉ ውጤቶች ለማጥፋት ሕይወቱን ሰጠ። ሮሜ 5፡6፥ 8 ውስጥ ክርስቶስ ስለ ኃጢአተኞች ሞተ ይላል። ስለዚህ ክርስቶስ የሞተላቸው ሰዎች ኃጢአተኞች ነበሩ። የክርስቶስ ሞት በኃጢአታቸው ምክንያት ከእግዚአብሔር ለተለዩት ሰዎች ነው። 1ኛ ጴጥሮስ 3፡18 ሲናገር፥ ክርስቶስ ወደ እግዚአብሔር እንዲያቀርበን በኃጢአታችን ምክንያት ሞቷል ይላል። ኃጢአታችን ከእግዚአብሔር ለይቶናል። የክርስቶስ ሞት ግን ኃጢአታችንን አስወግዶ ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ግንኙነት እንዲታደስ አድርጓል። ኤፌሶን 1፡7ና ማቴዎስ 26፡28 የኃጢአት ይቅርታ የሚገኘው በክርስቶስ ደም አማካይነት ለመሆኑ አጽንዖት የሚሰጡ ክፍሎች ናቸው። ሰዎች ሁሉ ኃጢአትን የሠሩና ሕጉን ያፈረሱ በመሆናቸው የክርስቶስ ሞት ሰዎች ሁሉ የሚያስፈልጋቸውን ይቅርታ አስገኝቶላቸዋል። እንዲሁም በዕብራውያን 9፡14 እንደሚለው፡ የክርስቶስ ደም ከሞተ ሥራ ሕሊናችሁን ያነጻል ይላል። ስለሆነም ሥጋዊ፥ መንፈሳዊና ዘላለማዊ ሞትን ያመጣውን ኃጢአትን ያስወገደው የክርስቶስ ሞት ነው። የክርስቶስ ሞት፥ ለሞት ይዳርገን ከነበረው ኃጢአት ሁሉ ያነጻናል። በተጨማሪ ዕብራውያን 9፡5 የክርስቶስ ሞት ከኃጢአት ሁሉ ነፃ ያወጣናል ይላል።
የደኅንነታችን መሠረት የክርስቶስ ሞት ነው። ነገር ግን የክርስቶስ ሞት እንዴት አድርጎ ደኅንነትን ይሰጣል? በነገው ዕለት የክርስቶስ ሞት መሥዋዕታዊ ምትክ ስለ መሆኑ መማር እንጀምራለን።
ምንጭ፡- “አስተምህሮ ክርስቶስና ደኅንነት”፤ ጽሑፍ፣ በዶ/ር ስቲቭ ስራውስ፤ ትርጉም በኃይሉ ልመንህ