የተወሰኑ ሰዎች ልጆች ኃጢአትን ለመሥራት እስካልደረሱ ድረስ የኃጢአት በደል አለባቸው አይባልም ይላሉ። ግን መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ልጆች የኃጢአት በደል ምን ይላል?
ጥያቄ፡- መዝ (51)፡5 አንብቡ። ሀ) ዳዊት ከመቼ ጀምሮ ኃጢአተኛ ተባለ? ላ) መዝ. (58)፡3 አንብብ። ለ) ክፉዎች ከመቼ ጀምረው ይሳሳታሉ?
ጥያቄ፡- ሮሜ 5፡14 አንብብ። ከአዳም እስከ ሙሴ ድረስ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ባላፈረሱት ላይ ሳይቀር ምን ነግሦ ነበር?
\ጥያቄ፡- 1ኛ ሳሙ 12፡23 አንብብ። ጳዊት ከቤርሳቤሕ የወለደው ልጅ መች ሞተ? በዚያን ጊዜ ዳዊት የት እንደሚያገኘው ተናገረ?
ባለፉት ሁለት ሳምንታት በተማርናቸው ትምህርቶች ውስጥ እንደተከታተልነው ሰዎች ሁሉ በኃጢአት ስለ ተወለዱ፥ በእግዚአብሔር ፊት በደለኞች ናቸው። ዳዊትም ገና በእናቱ ማኅፀን ውስጥ እያለ ኃጢአተኛ እንደ ነበረ ይናገራል። እንዲሁም ክፉዎች ተለዩ፣ ደግሞም ከማኅፀን ጀምር ሳቱ ይላል። እንዲህም ማለት እግዚአብሔር ከተወለዱበት ጊዜ ጀምሮ ኃጢአተኞች አድርጎ ይመለከታቸዋል ማለት ነው። በሮሜ ምዕራፍ 5 ውስጥ ከአዳም የተነሣ፥ ሰዎች ሁሉ ኃጢአተኞች እንደሆኑና የኃጢአት ቅጣት የሆነው ሞት እንደ ተበየነባቸው ያስረዳል። ሮሜ 5፡14 እንደ አዳም ሕግን በመተላለፍ ኃጢአት ያልሠሩት እንኳ ሳይቀሩ ክአዳም እስከ ሙሴ ባሉት ዘመናት የነበሩ ብዙ ሰዎች ሞተዋል ይላል። በአዳም ኃጢአት ምክንያት እነርሱም በደለኞች ስለሆኑ ሞቱ። አንዳንድ ሕፃናትም ስለሚሞቱ እነርሱም ቢሆኑ የአዳም ውርስ ኃጢአት ቅጣት እየተቀበሉ እንደሆነ መደምደም እንችላለን። ምንም እንኳን በእርግጥ ኃጢአት የፈጸሙ ሳይሆኑም፥ ከኃጢአት ጋር ስለ ተወለዱና ይህም በደል ስለሆነ ይሞታሉ። ምንም እንኳን ሕፃናት ኃጢአትን ለመሥራት ከመድረሳቸው በፊት በአዳም ምክንያት ኃጢአት አለባቸው ቢባልም፣ የሚሞቱ ሕፃናት ወደ ሲኦል ወይም ገሃነም ይወርዳሉ ማለትም አይደለም። ከቤርሳቤሕ የወለደው ልጁ በሞተ ጊዜ ዳዊት ተመልሶ ወደ ሕይወት እንደማይመጣና ከሞት በኋላ እንደሚያገኘው ገልቆአል (2ኛ ሳሙ. 12፡23)። ዳዊት ይህን ማለቱ አንድ ቀን እንደሚሞትና ወደ ሙታን ስፍራ እንደሚሄድ አይደለም። ነገር ን፥ “እኔም ወደ እርሱ ዘንድ እሄዳለሁ» አለ። ዳዊት ልጁን በእግዚአብሔር ዘንድ እንደሚገናኘው ተስፋ ነበረው። ከዚህ በሕፃንነታቸው የሚሞቱ የአማኞች ልጆች ወደ መንግሥተ ሰማይ እንደሚሄዱ አሳብ ልናገኝ እንችላለን። ምንም እንኳን መጽሐፍ ቅዱስ ሕፃናት ሁሉ ወደ መንግሥተ ሰማይ ይሄዳሉ ብሎ በግልጽ ባይነግረንም፥ ሕፃናት ወደ መንግሥተ ሰማይ የሚገቡ ይመስላል። ሆኖም ግን፣ ከአዳም በደል የተነሣ ሕፃናት ከኃጢአት ጋር ይወለዳሉ። ሕፃናት ሲሞቱ እግዚአብሔር የክርስቶስን ደም የማዳን ኃይል በመጠቀም ከበደላቸው አንጽቶ ከኃጢአት ዕዳ ይቤዣቸዋል። ሕፃናቱ ስለ ተጠመቁ ወይም ስለ ተገረዙ እግዚአብሔር አያድናቸውም። እንዲሁም ወላጆቻቸው መልካም ሥራ ስላደረጉ እግዚአብሔር አያድናቸውም። እግዚአብሔር የሚያድናቸው ክርስቶስ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ለኃጢአታቸው ቤዛ ስለሆናቸውና በምሕረቱና በጸጋውም ነው።
ምንጭ፡- “አስተምህሮ ክርስቶስና ደኅንነት”፤ ጽሑፍ፣ በዶ/ር ስቲቭ ስራውስ፤ ትርጉም በኃይሉ ልመንህ