ኢየሱስ ከእግዚአብሔር ጋር አንድ ዓይነት ባሕርይ እንዳለው ገለጸ 

ጥያቄ፡- ዮሐንስ 8፡54-59 አንብቡ። ሀ) ኢየሱስ በቁጥር 56 ለመግለጽ { የፈለገው ምንድን ነው? ለ) በቁጥር 58 ላይ ምን መግለጽ ፈለገ? ሐ) ኢየሱስ በቁጥር 59 አይሁዶች በነበራቸው ተቃውሞ ላይ ምላሽ በለጠ ጊዜ የተገነዘቡት ምን ነበር? 

ኢየሱስ በዮሐንስ 8፡54-59 ከእግዚአብሔር አብ ጋር የተለየ ግንኙነት እንዳለው አስታውቋል። ምክንያቱም አይሁዶች አብርሃምን በጣም ያከብሩ ስለነበር፥ አብርሃም እራሱ ሕይወቱንና በምድር ላይ ሊያከናውን ያለውን ተባር እንደ ተመኘ በመግለጽ ንግግሩን አጠቃሏል። ቀጥሉም እርሱና አብርሃም እንደሚተዋወቁ ጨምሮ ተናገረ። አይሁዶች ይህን ንግግር በሰሙ ጊዜ፥ እንደ ስድብ ወይም እብደት ቆጠሩት። ገና ወጣት ሆኖ እንዴት አብርሃምን አውቃለሁ ይላል? አሉ። የኢየሱስ መልስ ግን መለኮትነቱን ከሚገልጹት ልጽ ማረጋገጫዎች መካከል አንዱ ነበር። እንዲህም አለ፥ «አብርሃም ከመወለዱ በፊት እኔ አለሁ።» ይህ አባባል በሁለት መንገዶች አምላክነቱን ያመለክታል። መጀመሪያ፥ ኢየሱስ ከአብርሃም መወለድ በፊት እንኳ እንደነበረ የሚገልጽ ነው። ይህን ሲል መኖር የጀመረው ከተወሰነበት ጊዜ አንሥቶ እንዳልሆነና እንደ ሰው ከመወለዱ በፊትም ሕያው እንደ ነበር መግለጹ ነበር። ይህ የቅድመ ሕላዌ (pre-existence) ገለጻ ከተራ ሰብአዊ ፍጡር መብለጥን የሚያመለክት ነው። ነገር ግን ኢየሱስ ስለ መለኮትነቱ ይበልጥ ፍንትው አድርጎ ሲያቀርብ ይታያል። «ክአብርሃም በፊት እኔ ነበርሁ አላለም። ይህ ከሰው መብለጡን ሲያመለክትም፥ ኢየሱስ ጅማሬ እንዳለው የሚጠቁም ይሆናል። ይህም ኢየሱስ ያልነበረበት ጊዜ ነበር ወደሚለው አሳብ ሊወስደን ይችላል። ኢየሱስ ይበልጥ ሲናገር፤ «አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለሁ» የሚለው ዘላለማዊነቱን ሲያላይ ቅድመ አብርሃም ቀናትም ቢሆን ጅማሬ እንደሌለው ያመለክታል። 

በኢየሱስ አገላለጽ እግዚአብሔር ስለመሆን ከዚህም የጠነከረ ቃል አለ። ስለሆነም በዘaአት 3፡14-5 ባለው ክፍል፥ እግዚአብሔር ስሙን ለሙሴ ሲነገረው «እኔ ነኝ» ብሏል። ኢየሱስም «አብርሃም ከመውለዱ በፊት እኔ አለሁ” ሲል፥ በነደደው ቁጥቋጦ ውስጥ በሙሴ ፊት የተገለጠው እርሱ ራሱ መሆኑን ማስረዳቱ ነው። «እኔ» የሚለው የዕብራይስጥ ቃል፥ «ያህዌ» የሚል ፍች አለው። ኢየሱስም ያህዌ መሆኑን ያረጋግጣል። ታላቁ «እኔ ነኝ» ማለቱ ነው። 

ኢየሱስ በንግግሩ ውስጥ የሚሰነዝራቸውን ቃላት ፍች አይሁዳውያን በትክክል መረዳታቸው ልጽ ነው። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ ተሳድቧል በሚል ቁጣቸው ገንፍሎ እርሱን ወግረው ለመግደል ድንጋይ አንሥተዋል። ኢየሱስም የሞቱ ጊዜ አለመድረሱን በመገንዘብ እንዳይገድሉት ተሰወረ። ሆኖም አይሁዳውያን ምን ያህል ተቆጥተው እንደነበረ ማየት እንችላለን። ኢየሱስ በተዘዋዋሪ መንገድ እግዚአብሔር መሆኑን መግለጹ ይገባቸው ነበር። ኢየሱስም በተሳሳተ መንገድ ተረድታችሁኛል ብሎ እንዳልተናገራቸው እንመለከታለን። «የምለው አልገባችሁም። እኔ ያህዌ ነኝ ማለቴ አይደለም።» አላላቸውም፡ በተዘዋዋሪ መንገድ እግዚአብሔር መሆኑን ሲናገር እርሱ ያለው በትክክል ገብቶአቸዋል። በዚህ ክፍለ ምንባብ ውስጥ፥ «እኔ እግዚአብሔር ነኝ። ባይልም እግዚአብሔር መሆኑን በትክክል ገልጾአል። 

ጥያቄ፡- ዮሐንስ 14፡7-10 አንብቡ። በዚህ ክፍለ ምንባብ ውስጥ ኢየሱስ ከአባቱ ጋር ስላለው ግንኙነት እንዴት ይገልጻል? ጥያቄ፡- ዮሐንስ 10፡29-33 አንብቡ። ሀ) ኢየሱስ ከአባቱ ጋር ስላለው ግንኙነት እንዴት አድርጎ ይገልጻል? ለ) የኢየሱስን ንግግር አይሁዳውያን እንዴት ተረጎሙት? 

ኢየሱስ ብዙ ጊዜ እግዚአብሔር አባቱ መሆኑን በተለየ አኳኋን ገልጾአል። ኢየሱስ እግዚአብሔር አባቱ መሆኑን በገለጸባቸው በአንዳንድ ክፍለ ምንባቦች ላይ ከእግዚአብሔር ጋር በማዕረግ እኩል መሆኑን አበክሮ ይናገራል። በዮሐንስ 14፡7-10 ባለው ክፍል ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ለብቻ ሲነጋገር ሳለ እርሱን ካወቁ እብንም ሊያውቁ እንደሚችሉ ነግሮአቸዋል። ፊልጶስ «አብን እንዲያሳያቸው» በጠየቀው ጊዜ፥ ኢየሱስ፥ «እኔን ያየ አብን አይቷል» ብሏል። እዚህ ላይ ኢየሱስ እርሱ ራሱ እግዚአብሔር አብ መሆኑን አልተናገረም። እርሱ ያለው የእርሱ ባሕርይና ማንነት ልክ እንደ እግዚአብሔር አብ መሆኑን ነው። በዚህም አብ በእርሱ ፍጹም ሆኖ ይገለጣል። ከዚህም በበለጠ ኢየሱስ ያለው አባት ልጁን እንደሚወድ እግዚአብሔርም እርሱን እንደሚወድ ከመግለጽ የላቀ ነው። ኢየሱስ እየተናገረ ያለው ከእግዚአብሔር አብ ጋር አንድ የሆነ ባሕርይ አለኝ ነው። ይህም በተዘዋዋሪ አገላለጽ አምላክ ነኝ ማለቱ ነው። 

ኢየሱስ በዮሐንስ 10 ተከታዮቹ በአባቱ ክንድ ውስጥ ስላላቸው ጥበቃ ይገልጻል። ይህንንም ሲያጠቃልልም አብ ለኢየሱስ ተከታዮች ይህን ጥበቃ የሚያድረግላቸው እርሱና አብ አንድ በመሆናቸው ምክንያት መሆኑን ያስገነዝባል። ወዲያውኑ አይሁዶች ኢየሱስን ሊገድሉት ቆረጡ። እርሱን ለመግደል በምን ምክንያት ቆረጡ? ኢየሱስ ከእግዚአብሔር አብ ጋር ስላለው የቅርብ ግንኙነት መግለጡ እርሱ ራሱ እግዚአብሔር መሆኑን እንደሚያመለክት ስለተገነዘቡ ነበር። በዮሐንስ 14 ውስጥ እንዳለው ሁሉ፥ ኢየሱስ እርሱና አብ ተመሳሳይ ባሕርይ ወይም ማንነት እንዳላቸው ይናገራል። በሚከተሉት ቁጥሮች (ዮሐንስ 10፡34-42) ውስጥ ኢየሱስ እግዚአብሔር መሆኑን መግለጹን አልካደም፥ ነገር ግን ለአገልግሎት ለመረጣቸው ሰዎች እግዚአብሔር መለኮታዊ ሥልጣን እንደሚሰጣቸው ጠቅሷል። ስለሆነም ያለጥርጥር ለልጁ መለኮታዊ ሥልጣን ይሰጣል። በውይይታቸው ፍጻሜ እንኳን ቁጥር 39 ላይ ኢየሱስ እግዚአብሔር መሆኑን መግለጺን ሕዝቡ ስለተረዱ ሊይዙትና ሊቀጡት ሞክረው ነበር። 

ኢየሱስ ኃጢአትን ይቅር በማለት፥ ከእግዚአብሔር ቃል ጋር እኩል ሥልጣን በመቀዳጀት፥ እንደዚሁም ከእግዚአብሔር አብ ጋር አንድ ባሕርይና ማንነት እንዳለው በመናገር፥ በተዘዋዋሪ መንገድ አምላክነቱን እንደ ገለጸ ተረድተናል። ነገር ግን ኢየሱስ አምላክ መሆኑን በቀጥታ ወደ መናገሩ የተቃረበበት አንድ ወቅት ነበር።

ምንጭ፡- “አስተምህሮ ክርስቶስና ደኅንነት”፤ ጽሑፍ፣ በዶ/ር ስቲቭ ስራውስ፤ ትርጉም በኃይሉ ልመንህ

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading