ስለ እግዚአብሔር ምርጫና ለደኅንነት ስለሚያደርገው ጥሪ ጥያቄዎች 

በዚህ ሳምንት ውስጥ ሰዎችን ለደኅንነት ስለሚያበቃው አስቸጋሪ ስለሆነ የምርግ ርእሰ ጉዳይና ስለ ውጤታማ ጥሪ ስናጠና ቆይተናል። በዚህ ትምህርታችን ውስጥም ሰዎች እንዴት ወንጌልን ሰምተው የእርሱን ደኅንነት እንደሚቀበሉ ለመገንዘብ ችለናል። ነገር ግን ሰዎች በኃጢአታቸው ምክንያት ምርጫው ለእነርሱ ቢተው፥ ለእግዚአብሔር ጥሪ ስፍራ ስለማይሰጡት ላይቀበሉት ይቀራሉ። እግዚአብሔር አንዳንድ ሰዎችን መርጦ ወደ ራሱ እንደሚጠራቸው መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ የሚያስተምር መሆኑን አስተውለናል። ስለዚህ የእግዚአብሔር ምርግና ጥሪ ሰዎች ጥሪውን ተቀብለው መቀበላቸውን እንዲገልጹ ይረዳቸዋል። 

ብዙ ክርስቲያኖች በእነዚህ አስቸጋሪ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ላይ ጥያቄዎች አሉዋቸው። እንዲህ ይላሉ፡- እግዚአብሔር አንዳንድ ሰዎችን መርጦ ሊጠራ፥ ሌሎችን በመተው እነርሱም እርሱን ችላ ማለታቸውን ቢቀጥሉበት ታዲያ ይህ ፍትሐዊ ነውን? እንግዲህ ቀደም ሲል እንዲህ ላሉት አንዳንድ ጥያቄዎች ሮሜ ምዕራፍ 9 መልስ ሊሰጥ ተመልክተናል። ሮሜ ምዕራፍ 9 እግዚአብሔር አንዳንድ ሰዎችን መርጦ ለምን ወደ ደኅንነት እንደሚጠራቸው ሦስት እውነታዎችን ያስታውሳል፡ 

1. ሰዎች ሁሉ እግዚአብሔርን ስላልተቀበሉት ለእግዚአብሔር ቁጣ በቅተዋል። ስለዚህ ማንም ሰው የእርሱን ምሕረት በራሱ ለማግኘት ብቁ አይደለም። ስለዚህ ሰዎች ሁሉ ለቁጣው የተገቡ ሆነው ሳለ ምሕረቱን ለአንዳንዶቹ በመስጠቱ ፍትሐዊ አይደለም ሊባል አይችልም። ምሕረት ምሕረት እንዲሆን ምሕረቱን ለመቀበል ብቁ ላልሆነው ሰው ሉዓላዊ ክፍል በሥልጣኑ መርጦ ሊሰጠው ይገባል። 

2. እግዚአብሔር ፍጹም ጠቢብና ሁሉን ቻይ ነው። የሚሰጠውም ምሕረት የተመሠረተው በጥበቡ፥ በጻድቅነቱና በቁጥጥሩ ላይ ነው። ለውሳኔምቹ ሁሉ መልካም ዓላማ አለው። 

3. እግዚአብሔር ምሕረቱን ለሌሎች ለመስጠት የተቀሩት በነፃ ፈቃዳቸው እርሱን መተዋቸውን ይመለከታል። 

ዛሬ ሰዎች ስለ እግዚአብሔር ምርጫና ጥቂቶቹን ወደ ደኅንነት ስለ መጥራቱ የሚያቀርቡዋቸውን ሌሎች ጥያቄዎች ለመመለስ እንሞክራለን። እግዚአብሔር አስቀድሞ በማወቁ ጥሪው እንዴት ይመጣል? 

ጥያቄ፡- ሮሜ 8፡29 አንብቡ። እግዚአብሔር፥ የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ እነማንን መረጠ? 

ጥያቄ፡- 1ኛ ጴጥሮስ 1፡2 አንብቡ። እግዚአብሔር ሕዝቡን በምን መሠረት መረጠ? 

ጥያቄ፡- ዘፍጥረት 4፡1 አንብቡ። አዳም ሚስቱን አወቀ ሲል ምን ማለት ነው? 

ጥያቄ፡– ኤርምያስ 1፡5 አንብቡ። እግዚአብሔር ኤርምያስን አስቀድሞ መች አውቀው? 

ጥያቄ፡- 1ኛ ቆሮንቶስ 8፡3 አንብቡ። እግዚአብሔርን ስለሚወድ ሰው የተረጋገጠለት ምንድን ነው? 

ጥያቄ፡- ሮሜ 11፡2 አንብቡ። እግዚአብሔር እነማንን አልጣላቸውም? 

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተለያዩ ስፍራዎች የእግዚአብሔር ጥሪ የመጣው አስቀድሞ ከሚያውቀው አኳያ መሆኑን እንማራለን። በሮሜ 8፡29 ውስጥ አስቀድሞ የመረጣቸውን የልጁን መልክ እንዲመስሉ ወሰነ ይላል። 1ኛ ጴጥሮስ 1፡2፣ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያወቃቸውን መረጠ ይላል። ታዲያ እንዲህ ማለት ለዘላለም ባለፉት ጊዜያት ውስጥ እግዚአብሔር በጊዜ አማካይነት አሻግሮ ሲመለከት ሰዎች በነፃ ምርጫ የሚያደርጉትን ውሳኔ ካስተዋለ በኋላ ባየው ላይ በመመሥረት መረጣቸው ማለት ነው? ይህ አጠያየቅ ስእነዚህ ጥቅሶች ጽንሰ-አሳብ ላይ ያተኮረ ቢመስልም፣ እንደ እውነቱ ከሆነ ጥቅሶቹ የሚገልጹት አሳብ ይህ አይደለም። «አስቀድሞ ማወቅ» የሚለው አሳብ እግዚአብሔር የሚሆነውን ያውቃል ማለት አይደለም። «አስቀድሞ ማወቅ» ማለት እግዚአብሔር አስቀድሞ እነዚህን ሰዎች ስለሚያውቃቸው በዘመናት አስቀድሞ እንደ ራሱ ሕዝብ አብሮአቸው ግንኙነት ነበረው ማለት ነው። በዘፍጥረት 4፡1 ውስጥም ስለ አዳም ሚስቱን ስለማወቅ የተጠቀሰው ተመሳሳይ ቃል ነው። አዳም ስለ ሚስቱ አንዳንድ ነገሮችን ብቻ የሚያውቅ አልነበረም። እንደ ሰው በግል በሚታወቅ ሁኔታ ሁሉ ያውቃት ነበር። በኤርምያስ 1፡5 ውስጥ ተመሳሳይ ቃል የተጠቀሰ ሲሆን፥ ቃሉ እግዚአብሔር ኤርምያስ ከመወለዱ አስቀድሞ ስለ እርሱ አንዳንድ ነገሮችን ያውቅ ነበር አይልም። በዚህ ፈንታ ቃሉ፥ እግዚአብሔር ኤርምያስ ከመወለዱ በፊት በግል ያውቀው ነበር ነው የሚለው። 1ኛ ቆሮንቶስ 8፡3። ውስጥ ያለውም ቃል ይህንኑ የመሰለ ስለሆነ እግዚአብሔርን የሚወድ ሰው በእግዚአብሔር ይታወቃል ይላል። ስለዚህ እግዚአብሔር ስለሚወደው ሰው አንዳንድ ነገሮችን ብቻ የሚያውቅ አይደለም። እግዚአብሔር ስለሚወደው ሰው ከቅርብና ከተወዳጀ ሁኔታ በመነሣት ያውቀዋል። ስለዚህ እግዚአብሔር ከሚወደው ሰው ጋር ግንኙነት አለው። ሮሜ 112 ተመሳሳይ በሆነ ቃል በመጠቀም እግዚአብሔር አስቀድሞ የሚያውቀውን ሕዝቡን እስራኤልን አልጣለም ይላል። እግዚአብሔር ስለ እስራኤል አንዳንድ ነገሮችን ብቻ አልነበረም የሚያውቀው። ነገር ግን እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር ቀንኙነትም ነበረው። እነርሱ ሕዝቡ ሲሆኑ፣ እርሱ ደሞ አምላካቸው ነበር። ስለዚህ እንግዲህ «አስቀድሞ ማወቅ» ሲባል፣ «አስቀድሞ ስለ አንድ ሰው አንዳንድ ነገሮችን ማወቅ» ማለት አይደለም። በመሆኑም «አስቀድሞ ማወቅ ሲባል፣ «አስቀድሞ ከአንድ ሰው ጋር እንኙነትን መመሥረት» ማለት ነው። ስለዚህ ሮሜ 8፡29 እና 1ኛ ጴጥሮስ 1፡2 የሚያስተምሩት እግዚአብሔር ስለ ሰዎች በሚያውቀው ላይ በመመሥረት እንደሚመርጣቸው አይደለም። ይልቅስ፣ እነዚህ ጥቅሶች የሚሉት ከዘመናት በፊት በእነርሱ ላይ ባለው ፍቅርና ከእነርሱ ጋር ባለው ግንኙነት መሠረት መረጣቸው ነው የሚሉት። 

እግዚአብሔር ሰዎች ሁሉ ለጥሪው መልስ እንዲሰጡት ሁኔታዎችን አመቻችቷል? 

ጥያቄ፡- ዮሐንስ 1፡9 አንብቡ። ሀ) እውነተኛው ብርሃን፥ ለእነማን ብርሃን ይሰጣል? ለ) ዮሐንስ 1፡10-11 አንብቡ። ኢየሱስን አውቀው ያልተቀበሉት እነማን ናቸው? ሐ) ዮሐንስ 1፡12-13 እንብቡ። ኢየሱስን እነማን ተቀበሉ? መ) ዮሐንስ 

3፡19-21 እንብቡ፡ ይህ ብርሃን ምን ያደርጋል? 

በዚህ ሳምንት ትምህርት ውስጥ እንደተመለከትነው እግዚአብሔር ወደ ራሱ ከሳባቸው በስተቀር ሌሎች ለእግዚአብሔር ጥሪ መልስ እንዳይሰጡ ኃጢአታቸው ከልክሎአቸው ነበር (ዮሐንስ 6፡37፥44፤ 8፡34 ኤፌሶን 2፡1-10፤ 4፡18፤ ሮሜ 3፡11፤ 1ኛ ቆሮንቶስ 2፡6-16፤ 2ኛ ቆሮንቶስ 4፡3-4)። ሰዎች ሁሉ ወደ ክርስቶስ ሊመጡ እንዲችሉ እግዚአብሔር በልባቸው ውስጥ ሥራ ሠርቷልን? ዮሐንስ 1፡9 እውነተኛው ብርሃን የሆነው ኢየሱስ ብርሃኑን በሰዎች ሁሉ ላይ አበራ ይላል። እንዲህ ማለት ሰዎች ሁሉ ወደ እርሱ ዘንድ ለመምጣት ይችሉ ዘንድ ኢየሱስ ራሱን ገልጦላቸው ነበር ማለት ነውን? አይደለም። ዮሐንስ 1፡9 ሰዎች ሁሉ ወደ እርሱ ይመጡ ዘንድ ኢየሱስ አመቻችቶላቸዋል አይልም። ዮሐንስ 1፡9 የሚለው ኢየሱስ ወደዚህ ዓለም በመጣ ጊዜ በሰዎች ልጅ ውስጥ የነበረውን ይፋ አውጥቶ ለማሳየት ብርሃኑን በእያንዳንዱ ሰው ላይ አበራ ነው። በዚህ ክፍል “ብርሃን” ተብሎ የተጠቀሰው ቃል ወደ መንፈሳዊ ንዛቤ ስለሚመጣ ሰው እንዲገለጽ ተደርጎ በጥቅም ላይ አልዋለም። ዮሐንስ 1፡10–13 ያለው ክፍል የዮሐንስ 1፡9ን ቃል ትርጉም ግልጽ ያደርገዋል። ዮሐንስ 1፡10-11 የተጻፈው ቃል እውነተኛ ብርሃን የነበረውን ኢየሱስን ያልተቀበሉትን ክፉዎች አድርጎ አቅርቦአቸዋል። ዮሐንስ 1፡12-13 በአንጻሩ ኢየሱስን የተቀበሉትን ወገኖች ጻድቃን አድርጎ አቅርቦአቸዋል። ዮሐንስ ይህንኑ አሳብ በወንጌሉ በምዕራፍ 3፡19-21 ባለው ላይ በድጋሚ ሊናገር ኢየሱስ ወደ ዓለም ያመጣው ብርሃን በእያንዳንዱ ሰው ሥራ ላይ በማብራት በእያንዳንዱ ሰው ልብ ውስጥ የነበረውን አሳየ ብሎ ነው። ዮሐንስ 1፡9 የኢየሱስ ብርሃን እያንዳንዱ ሰው ልብ ውስጥ ያለውን ገልጦ ማሳየት እንጂ የእርሱ ብርሃን ሰዎች ሁሉ ማንነቱን አውቀው ወደ እርሱ ይመጡ ዘንድ ማድረግ እንዳልነበረ ያስተምራል። 

ሰዎች ሁሉ ወደ እርሱ ይመጡ ዘንድ የእግዚአብሔር ፈቃድ አይደለምን? 

ጥያቄ፡- 2ኛ ጴጥሮስ 3፡9 አንብቡ። እግዚአብሔር እነማን ወደ ንስሐ ይመጡ ዘንድ ይላል? 

ጥያቄ፡- 1ኛ ጢሞቴዎስ 2፡3-4 አንብቡ። እግዚአብሔር እነማን ይድኑ ዘንድ ይፈልጋል?

ጥያቄ፡- ሕዝቅኤል 18፡23 አንብቡ። እግዚአብሔርን የሚያስደስተው ምንድን ነው? 

ጥያቄ፡- 1ኛ ጴጥሮስ 2፡15፤ 4፡2 አንብቡ። ሀ) በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ «የእግዚአብሔር ፈቃድ የተባለው አገላለጽ ትርጉም ምንድን ነው? ለ) 1ኛ ጴጥሮስ 3፡17፤ 4፡19 አንብቡ። በእነዚህ ጥቅሶች መሠረት «የእግዚአብሔር ፈቃድ” ተብሎ የቀረበው አገላለጽ ትርጉም ምንድን ነው? 

ጥያቄ፦ 2ኛ ሳሙኤል 2፡15 አንብቡ፡ ሀ) እግዚአብሔር በኤሊ ልጆች ላይ ምን ሊያደር ፈልጎ ነበር? ለ) ኦሪት ዘዳግም 28፡63ን አንብቡ፡ እስራኤላውያን እግዚአብሔርን በማይታዘዙበት ጊዜ፥ ምን ሊያደርግባቸው ይፈቅድ ነበር? 

እግዚአብሔር ሰውን ሁሉ ለማዳን ፈቃዱ መሆኑን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተለያዩ ክፍሎች እናነባለን። በ2ኛ ጴጥሮስ 3፡9 ውስጥ ሰዎች ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲመጡ ፈቃዱ ነው ይላል። በ1ኛ ጢሞቴዎስ 2፡3-4 ደግሞ እግዚአብሔር ሰዎችን ሁሉ ለማዳን ይፈልጋል ይላል። እንዲሁም በሕዝቅኤል 18፡23 ውስጥ እግዚአብሔር ክፉዎችን በመቅጣት እንደማይደሰትና ሰዎች ከክፉ መንገዳቸው ተመልሰው ንስሐ ሊገቡ ደስ እንደሚለው ይናገራል። እንግዲህ እግዚአብሔር ሰው ሁሉ እንዲድን ከፈለገ ጥቂቶች ብቻ ወደ ደኅንነቱ እንዲመጡ ይመርጣቸዋል እንዴት ይባላል? መጽሐፍ ቅዱስ «ስለ እግዚአብሔር ፈቃድ» በሁለት መንገዶች ይናገራል። አንዳንድ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እግዚአብሔር ፈቃድ ሲናገር በትእዛዛቱ ውስጥ እንደተገለጠው ለፍጥረቱ ስላለው ፍቅራዊ ምኞት ነው። እግዚአብሔር ፍጥረቱን ሁሉ ያፈቅራል። ስለዚህ ሕይወታቸው የተቃና ይሆን ዘንድ ሊያደርጉ የሚገባቸውን አካፍሎአቸዋል። እነዚህ ነገሮችም ለሕይወታቸው ሕጎቹ ወይም ፈቃዱ ናቸው። በሌላ ጊዜ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እግዚአብሔር ፈቃድ ሲናገር የሚናገረው ለፍጥረቱ ስላለው ቁጥጥር ወይም ዕቅድ ነው። እግዚአብሔር በሥነ ተፈጥሮው ውስጥ ያለውን ሁሉ ፍጹምነት ባለው ሁኔታ ይቆጣጠራል፤ እንዲሁም ለእግዚአብሔር ዕቅዱን ለመፈጸም ስሥነ ፍጥረቱ ላይ ያለው ቁጥጥር «ፈቃዱ» ተብሎ ይጠራል። ይህን የእግዚአብሔር ፈቃድ አጠቃቀም በ1ኛ ጴጥሮስ ውስጥ እንመለከታለን። በ1ኛ ጴጥሮስ 2፡15 42 ውስጥ የ«እግዚአብሔር ፈቃድየሚለው አገላለጽ የእግዚአብሔር ምኞት ወይም የእግዚአብሔር ትእዛዛት የሚል ትርጉም አለው፡ የእግዚአብሔር ምኞትና ፈቃድ መልካም ነገርን እንድናደርግ ነው (1ኛ ጴጥሮስ 2፡15)። 

የእርሱ ፍላጎት ክፉ ምኞትን በመፈጸም እንድንኖር ሳይሆን፣ ፈቃዱን በማድረግ እንድንኖር ነው (1ኛ ጴጥሮስ 4፡2)። ነገር ግን በ1ኛ ጴጥሮስ 3፡17 እና 4፡19 ውስጥ፣ «የእግዚአብሔር ፈቃድ» የሚለው አገላለጽ የእግዚአብሔር ቁጥጥርና ዕቅድ የሚል ትርጉምን ይይዛል። ስለዚህ ክርስቲያኖች ለሃይማኖታቸው እንዲሠቃዩ የእግዚአብሔር ዕቅድ ሊሆን ይችላል (1ኛ ጴጥሮስ 3፡17፤ 4፡19)። 

የእግዚአብሔር ፍቅራዊ ምኞትና ፈቃድ ብዙ ጊዜ እንደ ቁጥጥሩና እንደ ዕቅዱ ሊሆን አይችልም። ብዙ ጊዜ ሰዎች እግዚአብሔር የሚያቀርብላቸውን የደኅንነት ስጦታ ተገንዝበው ወደ እርሱ ይመጡ ዘንድ የእርሱ ፈቃድና ምኞት ነው። በመሆኑም እግዚአብሔር ክፉ ሰዎችን የመቅጣት ፍላጎት የለውም። ነገር ግን እግዚአብሔር ጻድቅና ቅዱስ በመሆኑ ኃጢአትን መቅጣት አለበት። ይህ የእግዚአብሔር ጻድቅነትና ቅድስና ባሕርይ የኤሊን ልጆች በኃጢአታቸው እንዲቀጡ አደረገ። እንደዚሁም እስራኤላውያን ለሕጉ ሳይታዘዙ በቀሩበት ጊዜ ይኸው የእግዚአብሔር የጻድቅነትና የቅድስና ባሕርይ መቀጣታቸውን አስፈላጊ ሆኖ አገኘው። በመሠረቱ እግዚአብሔር ለሁልጊዜውም ቢሆን የእርሱ ፈቃድና ፍላጎት ሰዎችን ከኃጢአታቸው ማዳን እንጂ በማንም ላይ ሞትን ማምጣት አይደለም። ግን ሰዎች በኃጢአታቸው ተናዝዘው ንስሐ ሳይገቡ በሚቀሩበት ጊዜ የእግዚአብሔር የጽድቅና የቅድስና ባሕርይ እንዲሁም የሰማይና የምድር ገዥነቱ ዕቅድ የኃጢአተኞችንም ቅጣት ያጠቃልላል። እንግዲህ «የእግዚአብሔር ፈቃድ» የሚለውን አገላለጽ የእግዚአብሔር ፍላጎት የሚል ትርጉም ብንሰጠው፣ ይህ ከሆነ ሁልጊዜ የእግዚአብሔርን ፈቃድና ፍላጎት ሰዎችን ማዳን ነው ማለት እንችላለን። እንደዚሁም «የእግዚአብሔር ፈቃድ» የሚለውን አሳብ የእግዚአብሔር ቁጥጥርና ዕቅድ ብለን ብናብራራው፣ ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱን ንቀው ወይም ችላ ብለው የሚሄዱትን ሁሉ የሚደርስባቸውንም ቅጣት ይጨምራል። 

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እግዚአብሔር ፈቃድ በሁለት ልዩ ልዩ መንገዶች የሚያቀርባቸው አሳቦች እንደሚከተለው ምሳሌ ተብራርተዋል። አንድ የአገራችን ፕሬዚዳንት የቅርብ ወዳጅ በአገሩ ላይ የክደት ሥራ ሠራ እንበል። ይህ በአገራችን ላይ የክደት ተግባር የሠራ ሰው ተይዞ ሕግ ፊት ከቀረበ በኋላ ይሙት በቃ ተፈረደበት እንበል። ግን የይሙት በቃውን የመጨረሻ ፍርድ የሚያጸናው ፕሬዚዳንቱ ስለሆነ ጉዳዩ ለፊርማ ወደ እርሱ ዘንድ ይቀርባል። ይህን ጊዜ የአገር ጉዳይ ስለሆነ ፕሬዚዳንቱ በኀዘን እያነባ ወንጀለኛው በሞት እንዲቀጣ ፍርዱን በፊርማ ያጸድቀዋል። ፍትሕ ይህ ወንጀለኛ ወዳጁ በወንጀሉ መቀጣት እንደሚያስፈልገው ማስገደዱን ያውቃል። እንደዚሁም በዚህ ወንጀለኛ ላይ የተበተነውን የሞት ቅጣት ካላጸና በስተቀር ሌሎችም እንደዚሁ ተነሥተው የክደት ሥራ ስለሚሠሩ፥ አገሪቱ አደጋ ላይ እንደምትወድቅ ያውቃል። በግሉ ወዳጁን ከሞት ሊያድነው በወደደ ነበር፡ ቀን ፍትሕ፥ ለአገሩ ባለው ዕቅድ ውስጥ የባልንጀራው ቅጣት እንዲጠቃለል ያስገድደዋል፡፡ (ይህ የጠቀስነው ምሳሌ ከሁለት መቶ ዓመታት በፊት በአሜሪካ ውስጥ በእውን ተፈጽሞአል። በዚያን ጊዜ የአሜሪካ የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት ጆርጅ ዋሽንግተን አንድ በአገሩ ላይ የክደት ሥራ በሠራ የቅርብ ወዳጃቸው ላይ የይሙት ፍርድ አጽንተውበት ሰውየው ቅጣቱን ተቀብሏል።) 

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እግዚአብሔር ምርጫ የሚያቀርበው አሳብ እስልምና አስቀድሞ ስለ መመረጥ ከሚሰጠው አስተሳሰብ በምን ይለያል? 

አብዛኛዎቹ ሙስሊሞች አላህ አንድ ቀን የሚድኑትንና የማይድኑትን ይመርጣል ብለው ያምናሉ። በዚህ ምርጫ ላይ እግዚአብሔር ለሙስሊሞች እንደሚያደላ ቢናገሩም፥ አላህ ምርጫውን በፈለገው መንገድ እንደሚፈጽም ያምናሉ። አላህ ሉዓላዊና ሁሉን ቻይ አምላክ ስለሆነ ደስ ባለው ጊዜ የፈለገውን ሊሠራ ይችላል ይላሉ። እንደዚሁም ሙስሊሞች በዓለም ላይ የሚሆነው ነገር ሁሉ በአላህ ፈቃድ በመሆኑ ሰዎች ሕይወታቸውን የሚመሩበት አማራጭ የላቸውም፡፡ የሚፈጽሟቸው ተግባራት ሁሉ አስቀድመው በአላህ የተወሰኑ ናቸው ብለው ያምናሉ። 

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እግዚአብሔር ምርጫና ስለ እግዚአብሔር ጥሪ የሚሰጠው ትምህርት ሙስሊሞች ካላቸው አስተሳሰብ በአምስት መንገዶች ይለያል፦ 

1. ሮሜ ምዕራፍ 9 ውስጥ እንደተከታተልነው እግዚአብሔር ሁሉን ስለሚገዛና ስለሚቆጣጠር ብቻ ምርጫውን አሻሚ በሆነ መንገድ አይፈጽምም። ሁልጊዜ የእርሱ ምርጫዎች የተመሠረቱት በፍቅሩ፥ በጥበቡና በጽድቁ ላይ ነው። እግዚአብሔር ሰዎችን ሁሉ ያፈቅራል። ስለዚህ አንዱን ከሌላው እያበላለጠ ባለመሆኑ ሰዎች ሁሉ ወደ እርሱ ዘንድ እንዲመጡ ፈቃዱ ነው። የእግዚአብሔርን ምርጫና ጥሪ ባንገነዘብም፥ በእርሱ ጽድቅና በእርሱ ፍቅር ላይ የተመሠረቱ በመሆናቸው በምንም ሁኔታ እሻሚ በሆነ አኳኋን አይተገበሩም። 

2. የእግዚአብሔር ምርጫና የእግዚአብሔር ጥሪ በሆነ ምሥጢራዊ መንገድ ከሰዎች ነፃ ፈቃድና ኃላፊነት ጋር ሊቃረን አይችልም። እግዚአብሔር ከጊዜ በላይና ከጊዜ ውጪ ነው። በመሆኑም ከእርሱ አስተሳሰብና አተገባበር አቅጣጫ ማንኛውም የተፈጸመና ገናም የሚፈጸም ነገር ሁሉ በእርሱ አእምሮ ውስጥ ቀደም ብሎ በተግባር ላይ ውሎ ከፍጻሜ የደረሰ ነው፥ ስለዚህ ይህ በእርሱ ሙሉ በሙሉ የተፈጸመ ነገር ሁሉ ምንም ጊዜ በእርሱ ቁጥጥር ውስጥ ነው። እንደዚሁም እግዚአብሔር ለአንዳንድ ሰዎች የሚሰጣቸው የምሕረት ትሩፋት በእግዚአብሔር አስተሳሰብ ውስጥ ከጊዜ ውብ የሆነ ነገር ነው። ግን እኛ የሰው ልጆች ያለነው በጊዜ ውስጥ ነው። ስለዚህ በጊዜ ወሰናችን ውስጥ ለምናደርገው ማንኛውም ነገር ሙሉ በሙሉ ተጠያቂዎች ነን። ለምሳሌ ያህል፥ አንድ የቤት መኪና ሹፌር ግድየለሽ ቢሆንና ይህ ጠባዩ ለመኪና አደጋ ቢያደርሰው፥ ይህ ሹፌር እግዚአብሔርን በማማረር፥ «ይህ አደጋ በእግዚአብሔር ፈቃድ ደረሰብኝ። ብሉ ሊወቅሰው አይችልም። ሹፌሩ ለፈጸመው ጥፋት ኃላፊ ነው። ሾፌሩ የበለጠ ጥንቃቄ ቢኖረው ኖሮ አደጋ ባልደረሰበትም ነበር። በተመሳሳይ መንገድ በጊዜ ወሰን ውስጥ እኛም ሰዎች የሆንን ሁሉ እግዚአብሔርን ልንቀበለው ወይም ላንቀበለው ነጻነት አለን። ሆኖም በአንጻሩ ደግሞ በምናደርገው ተግባር ሙሉ በሙሉ ተጠያቂዎች ነን። በጊዜ ውስጥ የእግዚአብሔር ሉዓላዊ ምርግ ነጻነታችንን ወይም ተጠያቂነታችንን አይገፍብንም፥ በዚህ ፈንታ እግዚአብሔር ነፃ ምርግችን በሉዓላዊው ዕቅዱ ውስጥ እንዲገባ ያደርጋል። 

3. እግዚአብሔር ማንም ሰው እንዲቀበለው ወይም እንዲተወው አያስገድድም። ይልቅስ የእርሱ ምርጫና የእርሱ ጥሪ ሰዎች በእምነትና በንስሐ ወደ እርሱ ዘንድ መጥተው በነፃ እንዲቀበሉት ያደርጋል። ቀደም ሲል በዚህ ሳምንት ውስጥ እንደተመለከትነው፥ እግዚአብሔርን ያልተቀበሉ ሰዎች በነህ ፈቃዳቸው ሳይቀበሉት ቀርተዋል (ማቴዎስ 23፡37፤ ዮሐንስ 5፡40፤ 8፡44፤ ሮሜ 1፡20፥25)። የኮምፒውተር መሣሪያን ተመልክታችሁ ከሆነ፥ ኮምፒውተሩ የሚፈጽመው ተግባር የተሰጠውን ፕሮግራም ብቻ ነው። ሰዎች ቀን እንደ ኮምፒውተር ተደርገው ሊታሰቡ አይገባም። ስለዚህ ሰዎች እንደ ኮምፒውተር ታዘው በፕርግራም የሚሠሩ አይደሉም። እንዲሁም ሰዎች እንደ ተንቀሳቃሽ አሻንጉሊቶች (ፓፔትስ) የሚያንቀሳቅሳቸው ሰው የሚያዛቸውን ተግባር የሚፈጽሙ አይደሉም። ስለሆነም ሰዎች ነፃ ስእግዚአብሔር የተመረጡና በነጻነታቸው ውስጥ የተጠሩ ሥራዎቹ ናቸው። 

4. ቀደም ሲል በዚህ ሳምንት እንደ ተመለከትነው እግዚአብሔር ለሌሎች ምሕረቱን ለመስጠት በነፃ ምርግ ለመጠቀም ሁልጊዜ ይሠራል። ማንም ሰው እግዚአብሔርን ላለመቀበል እምቢተኝነትን በሚያሳይበት ጊዜ፥ እግዚአብሔር ሁልጊዜ ይህን የሰዎችን እምቢተኝነት ሌሎችን ወደ እርሱ ለመሳብ ዓላማ ይጠቀምበታል። 

ጥያቄ፦ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እግዚአብሔር ምርግና ጥሪ የሚሰጠው ትምህርት ምን ያህል ለእናንተ መጽናናትንና ብርታትን ይሰጣችኋል? 

5. መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እግዚአብሔር ምርጫና ጥሪ ስለሚሰጠው ትምህርት ማስታወስ ያለብን እጅግ በጣም ጠቃሚ የሆነው ነገር በተግባር ላይ ውሉ የሚታይ መሆኑ ነው። ቀደም ሲል እንደተመለከትነው፥ የእግዚአብሔር ርግና ጥሪ በፊቱ ትሑታን እንድንሆን በማድረግ በደኅንነት ላይ ያለንን ትዕቢት ያስወግደዋል። (ሮሜ 9፡8፥11፤ በተጨማሪም ሮሜ 3፡7 ተመልከቱ።) የእዚአብሐር ምርግና ጥሪ ለጠፉት ሰዎች እንድንጸልይላቸው ያሳስበናል። የጸሎታችንም ምክንያት እግዚአብሔር ወደ ራሱ ይስባቸው ዘንድ ነው። (ሮሜ 8፡15-16፤ በተጨማሪም ሮሜ 10፡1 ተመልከቱ።) እንደዚሁም የእግዚአብሔር ምርጫና ጥሪ በክርስትና ሕይወታችን እንዲያድግ በማበረታታት የእግዚአብሔር ሥራ በእኛ ሕይወት አማካይነት ለሌሎች ሊገለጽ እንዲችል ያደርጋል (2ኛ ጴጥሮስ 1፡10)። የእግዚአብሔር ምርግና ጥሪ ዘላለማዊ ደኅንነታችንን ያረጋግጥልናል (ሮሜ 8፡29-30)። እንደዚሁም የእግዚአብሔር ምርግና ጥሪ በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ወንጌልን ለማዳረስ ያነቃቃል። እዚህ ላይ እግዚአብሔር ወደ እርሱ ሊያመጣቸው በውስጣቸው የራሱን ሥራ እንደሚሠራ እርግጠኞች ልንሆን ይገባል (የሐዋርያት ሥራ 18፡10)።

ምንጭ፡- “አስተምህሮ ክርስቶስና ደኅንነት”፤ ጽሑፍ፣ በዶ/ር ስቲቭ ስራውስ፤ ትርጉም በኃይሉ ልመንህ

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading