የሕይወት እንጀራ

የኢየሱስ ባሕርይ አይለዋወጥም 

ጥያቄ፡- ሀ) መዝሙር 102፡25-27 እና ሚልክያስ 3፡6 አንብቡ። እነዚህ ጥቅሶች ስለ እግዚአብሔር ምንን ያስተምሩናል? ለ) ዕብራውያን 13፡8 አንብቡ። ይህ ጥቅስ ስለ ኢየሱስ ምን ያስተምረናል? 

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እግዚአብሔር ከሚያስተምረን ትምህርት ውስጥ አንደኛው አስደናቂ ነገር እግዚአብሔር የማይለወጥ መሆኑ ነው። ሰዎች ልብሶቻቸውን እንደሚቀያይሩ፥ የፍጥረት አካል የሆነ ነገር ሁሉ ይለዋወጣል። ዳሩ ግን እግዚአብሔር አይለወጥም። ባሕርይውም ቢሆን የጸና ነው። ለዓለም ያለው ዕቅድና ዓላማም እንደነበረ ነው። ለሕዝቡ የሰጠው ተስፋም እንዲሁ የጸና ነው። 

ዕብራውያን 13፡8 ኢየሱስ እንደማይለወጥ ያረጋግጥልናል። በሚቀጥሉት ምዕራፎች ውስጥ እንደምንመለከተው ስለ ኢየሱስ አንዳንድ ነገሮች ተለውጠዋል። ለምሳሌ ያህል፥ በአንድ ወቅት እርሱ መለኮታዊ ብቻ ነበር ነገር ግን ከድንግል ማርያም ሲወለድ፥ ሰውም አምላክም ሆነ። ታዲያ ዕብራውያን 13፡8 ኢየሱስ ክርስቶስ አይለወጥም ሲል ምን ማለቱ ነው? የዚህ ጥቅስ ዓውደ ንባብ የእግዚአብሔር ፍርሃት ያለበት ክርስቲያናዊ ባሕሪ ስለሚያሳዩ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የሚናገር ነው። ስለዚህ ጥቅሱ በመሠረቱ ስለማይለወጠው የኢየሱስ ባሕርይ ያስተምረናል። የእግዚአብሔር ባሕርይ እንደማይለወጥ ሁሉ፥ የኢየሱስ ባሕርይም እንደዚሁ አይለወጥም። ይህም ኢየሱስ አምላክ ለመሆኑ ሌላው ማስረጃ ነው። | 19ኛ ጥያቄ፡- የማይለወጠው የኢየሱስ ባሕርይ እንዴት ነው የሚያጽናናችሁ? 

የኢየሱስ የማይለወጥ ባሕርይ ስንል፥ እርሱ ለእኛ ያለው አመለካከት ይለወጣል ብለን መፍራት የለብንም። ሰዎች ብዙ ጊዜ በሌሎች ያላቸውን ስሜት ይለውጣሉ። ኢየሱስ ለእኛ ያለው ፍቅር በፍጹም አይለወጥም። ኢየሱስ ተስፋውን በፍጹም አይለወጥብንም። ሰዎች ተስፋ ይሰጣሉ፤ ነገር ግን እነዚያን ተስፋዎች አይጠብቁትም። ኢየሱስ ግን የሰጠንን ተስፋ ሁሉ ይጠብቃል። ስለዚህ እርሱ ዛሬ ፍጹም፥ ጻድቅና አፍቃሪ መድኅን እንደሆነ ሁሉ፥ ነገም እንደዚሁ ስለሚሆን በእርሱ ልንታመን እንችላለን።

ምንጭ፡- “አስተምህሮ ክርስቶስና ደኅንነት”፤ ጽሑፍ፣ በዶ/ር ስቲቭ ስራውስ፤ ትርጉም በኃይሉ ልመንህ

የጌታ ጸጋ ከእርስዎ ጋር ይሁን፤ ሀሳብዎን ለመስማት ዝግጁ ነን።

Discover more from የሕይወት እንጀራ

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading