ኢየሱስ ሁሉን አዋቂ ነው 

ጥያቄ፡- ሀ) መዝሙር 139፡1-4፥ 17-18፥22-23 እንብቡ። እግዚአብሔር ከሚያውቃቸው ነገሮች አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው? ለ) ማርቆስ 2፡8፤ ዮሐንስ 1፡48} 6፡64፤ 16፡30፤ 21፡17 እንብቡ። ኢየሱስ የሚያውቃቸው ነገሮች አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው? 

እግዚአብሔር ሁሉንም ያውቃል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እጅግ ከሚወደዱ ክፍለ ምንባቦች ውስጥ መዝሙር 139 አንዱ ነው። ይህ ምዕራፍ እግዚአብሔር ከሚያውቃቸው ነገሮች መካከል ጥቂት ምሳሌዎችን (ናሙናዎችን) ይፈነጥቃል። ይህ መዝሙር እግዚአብሔር ስለ እኛ ሁሉንም እንደሚያውቅ ይነግረናል። እርሱ አሳባችንን፥ ሥራችንን፥ የምንናገራቸውን ቃላት ገና ሳንናገራቸው አስቀድሞ ያውቃል። እግዚአብሔር ስለ እኛ ያለው እውቀት ፍጹም ምሉዕ ነው። 

ጌታ ኢየሱስ ይህን ስለ ሰዎች ያለውን ፍጹም እውቀት በምድር ላይ ላለ ገልጾታል። እርሱ ሽባውን ሰው ከመፈወሱ አስቀድሞ ፈሪሳውያን ምን እንደሚያስቡ ያውቅ ነበር። ናትናኤል ከእርሱ ጋር ከመገናኘቱ በፊት፥ የት እንደነበረ ያውቅ ነበር። እንደዚሁም ይሁዳ ራሱ ከማወቁ አስቀድሞ፥ አሳልፎ እንደሚሰጠው እርሱ ያውቅ ነበር። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንደ እግዚአብሔር ሁሉን ነገር እንደሚያውቅ ይገነዘቡ ነበር (ዮሐንስ 16፡30፤ 21፡17)። ኢየሱስ ሁሉን ነገር፥ በተለይም የሰዎችን አስተሳሰብ ማወቁ፥ እርሱ እግዚአብሔር ለመሆኑ ሌላው ማረጋገጫ ነው። 

ጥያቄ፡- ሀ) ኢየሱስ ስለ እናንተ ሙሉ በሙሉ ማወቁ እንዴት መጽናናትን ይሰጣችኋል? ቢያንስ በሁለት መንገዶች ለጹ። ለ) ኢየሱስ ስለ እናንተ ሙሉ በሙሉ ማወቁ የበደለኛነት ስሜት የሚያሳድርባችሁ ወይም የሚያስፈራችሁ እንዴት ነው? ቢያንስ በሁለት መንገዶች አስረዱ። 

ኢየሱስ ስለ እኛ ያለው ፍጹም እውቀት ሊያጽናናንም የበደለኝነት ስሜት ሊያሳድርብንም ይችላል። የሚያጋጥመንን ሕመማችንና ሥቃያችንን ኢየሱስ የሚያውቅ መሆኑን መረዳታችን ያጽናናል። እንዲሁም ኢየሱስ ፍጹም በሆነ እውቀቱ፥ በተመሰቃቀለ ሕይወት ውስጥ የሚመራን መሆኑን ማወቃችን ያጽናናል። ኢየሱስ ለእኛ የሚበጀንን ማወቁ ያጽናናናል። ነገር ግን ኢየሱስ አሳባችንን፥ ስሜታችንንና የልባችንን እውነተኛ መነሣሣት ማወቁን መገንዘባችን የበደለኝነት ስሜት እንዲያድርብንም ያደርጋል። በአንድ ሰው ላይ ስንቆጣ፥ ወይም ስለ ማንነታችን በምስጢር ስንኮራ ወይም የሌላውን ሰው ስንመኝ ኢየሱስ የሚያውቅ መሆኑ ያሳስበናል። ስለሆነም የኢየሱስ ፍጹም እውቀት ያጽናናናል፤ ደግሞም ድርጊታችንን በመግለጥ ይወቅሰናል።

ምንጭ፡- “አስተምህሮ ክርስቶስና ደኅንነት”፤ ጽሑፍ፣ በዶ/ር ስቲቭ ስራውስ፤ ትርጉም በኃይሉ ልመንህ

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading