ሰዎች ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ አዳኛቸው አምነው በሚቀበሉበት ጊዜ፥ እግዚአብሔር አስደናቂና የተትረፈረፉ የደኅነት በረከቶችን በላያቸው ላይ ያፈስሳል። በዚህም አዲስ ሕይወትን ይሰጣቸዋል፥ ከክርስቶስ ጋር ኅብረት እንዲኖራቸው በማድረግ፥ ኃጢአታቸውንም ይቅር ይላቸዋል፣ ከዚያም ከእርሱ ጋር መታረቃቸውን በማሳወቅ፥ የቤተሰቡ አካል ያደርጋቸውና በፊቱ ቅዱሳን ሆነው እንዲገኙ በሕይወታቸው ውስጥ ይሠራል። ሆኖም፣ እያንዳንዱን አማኝ ወደፊት የሚጠብቀው በረከት አለ፣ ይህም የክብር በረከት ነው። ስለሆነም ከዚህ ሕይወት ፍጻሜ በኋላ፥ አማኞች ሁሉ ዘላለማዊ የሆነ የክብር ሕይወት እንደሚያገኙ የተረጋገጠላቸው እውነታ ነው። ከዚህ በመነሣት በዚህ ሳምንት ስለሚመጣው የክብር በረከትና አማኞች ይህን የክብር በረከት የሚያገኙ ስለመሆናቸው ስላለው ዋስትና አብረን እናጠናለን።
መጀመሪያ ቀን – ክብር
በዚህ ዓለም ውስጥ ያሉትን በሽታዎችና የተለያዩ ሥቃዮችን በመመልከት፥ «ይህ ዓለም የከፋ ስፍራ ነው» ብላችሁ ያሰባችሁበት ጊዜ ይኖር ይሆን? «እርግጥ በዚህ ዓለም ውስጥ ብዙ የተዛነፉ ሁኔታዎች ሲከሰቱ እንመለከታለን። ልንገራችሁና የራሴም ሕይወት ቢሆን ችግር አለበት። ስለዚህ አካሌ በሕመም ምክንያት ኃይለኛ ስሜት የሚያመጣብኝ ጊዜ አለ። ላደርንው የማልፈልገውን ነገር ሳደርግ እገኛለሁ። የከፉ የኃጢአት ድርጊቶችንም እፈጽማለሁ። በዚህ ዓለም ላይ የእኔም ሕይወት ሆነ የዓለም ሁኔታ በትክክለኛው መንገድ እንደ ተመራ ቢኖር በጣም ደስ ባለኝ ነበር!» ሕይወታችንንም ሆነ፥ ይህን ዓለም በሚመለከት ብዙ የተበላሹ ነገሮች አሉ። የእግዚአብሔር የማዳን በረከቶች ግን እኛን ከእርሱ ጋር ለማስታረቅ በሂደት ላይ ናቸው። እግዚአብሔር በበረከቱ ሕይወትን ይሰጠናል፥ ከዚያም ከእርሱ ጋር መታረቃችንን በይፋ ይገልጥልናል። ቀጥሎም የቤተሰቡ አካል ያደርገናል፥ እንዲሁም በቅድስና ጎዳና ላይ ይመራናል። ይህም ሆኖ፥ ሥቃይና ክፋት በሰፈነበት ዓለም ውስጥ እንኖራለን። ሰውነታችንም በኃጢአት የተሞላ ርኩሰት ያሸነፈው በመሆኑ፥ ብዙ ጊዜ ከሥቃይ የራቀ አይደለም። ይህን እንጂ ክርስቲያኖች ሁሉ፥ ከዚህ ሕይወት በኋላ በሚመጣው ሕይወት፥ የክብር በረከቶችን እንደሚቀበሉ የተረጋገጠላቸው እውነታ ነው። መክበር የሚባለው፥ በመጨረሻው ጊዜ በሕይወታችንና በአካላችን ላይ ያለውን የኃጢአት መርገም የሚያስወግድልን የደኅንነት በረከት ነው። እንዲሁም መክበር፥ ሕይወታችንና አካላችንን እግዚአብሔር ወዳዘጋጀው የፍጹምነት ደረጃ የሚያደርስ የደኅንነት በረከት ነው።
1. እንከብራለን ሲባል ምን ማለት ነው?
1.1 መክብር (ክብር) ማለት ፍጹማንና ንጹሐን እንሆናለን ማለት ነው፡፡
ጥያቄ፡- 1ኛ ቆሮ. 1፡8 አንብብ። እግዚአብሔር ለአማኞች ምን ተስፋን ይሰጣል?
ጥያቄ፡– ኤፌ 5፡25-27 አንብብ፡ ቤተ ክርስቲያን በእግዚአብሔር ፊት እንዴት ሆና ትቀርባለች?
ጥያቄ፡- ቆላ. 1፡22 እንብብ። እግዚአብሔር እኛን ከራሱ ጋር የማስታረቁ ውጤት ምንድን ነው?
ጥያቄ፡- ይሁዳ 24 አንብብ። እግዚአብሔር ምን ያደርግልናል?
ጥያቄ፡- 1ኛ ተሰ. 5:23-24 አንብብ። እግዚአብሔር ታማኝ የሆነው ምን ሊያደርግልን ነው?
በምንከብርበት ጊዜ በመጀመሪያ የምንቀበለው በረከት፥ ያለነውር፥ ፍጹምና ንጹሕ መሆንን ነው። 1ኛ ቆሮ. 1፡8 ላይ እግዚአብሔር እስከ መጨረሻው ቀን ጠብቆ፥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እስክመለስበት ቀን ያላነቀፋ ሆነን እንድንገኝ ያደርገናል ይላል። ይህ የጌታችን የኢየሱስ ቀን የተባለው እርሱ ተመልሶ የሚመጣበት ቀን ነው፡ በዚህ ምድር ላይም ክርስቶስን አምነው እንደ አዳኛቸው ተቀብለው ያሉትን ክርስቲያኖች እግዚአብሔር በሰጣቸው ተስፋ መሠረት ኢየሱስ እስኪመለስ ድረስ በእምነታቸው የጸኑና የጠከሩ፥ ከነውርም ሁሉ የጸዱ አድርጎ ይጠብቃቸዋል። ከኃጢአት ሁሉም የነጹ ይሆናሉ። በኤፌ. 5፡25-27 ውስጥ ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን ወደ ክርስቶስ ፊት የመቅረብዋን ሁኔታ፥ በሠርጋቸው ቀን ሙሽሪት ወደ ሙሽራው በምትቀርብበት አኳኋን መስሎ ጽፎታል። እንደሚታወቀው ሁሉ ሙሽሮች በሠርጋቸው ቀን ቆንጆ ልብስ ይለብሳሉ፥ ባማረ ሁኔታም ያጌጣሉ። በዚህን ዕለት ሙሽሪት በሁለመናዋ ያማረችና የደቀች ሆና በሙሽራው ዓይን ትታያለች። ታዲያ ቤተ ክርስቲያን፥ በጌታ ኢየሱስ ፊት በምትቀርብበት ጊዜ፥ ፍጹም ለመሆን በመጣር ብቻ አትቀርብም፥ ነገር ግን እጅግ በጣም ፍጹምና እንከን የለሽ ሆና ትቀርባለች። ማለትም ያላንዳች ኃጢአት፥ እንከንና ነውር ሆና ፊቱ ትቀርባለች። እናም ፍጹም የሆነ ቅድስናን ትጎናጸፋለች። በቆላ 1፡22 ላይም፥ እግዚአብሔር ከራሱ ጋር ስለ አስታረቀን፥ ቅዱሳንና ንጹሐን፥ ነቀፋም የሌለብን አድርጎ በፊቱ አቆሙን ይላል። በምንከብርበት ወይም ክብርን በምንጎናጸፍበት ጊዜ፥ ከኃጢአት ፈጽመን ለምን ጊዜውም እንነጻለን። ከዚህ በኋላ ማንም ሰው ቢሆን በኃጢአት ወይም በስሕተት አሳብቦ ሊከስሰን አይችልም። በይሁዳ 24 ላይ እግዚአብሔር በደኅንነቱ ውስጥ እንደሚጠብቀንና በፊቱም ያላንዳች ነውር እንደምንም ተስፋ ይሰጠናል። በ1ኛ ተሰ. 5፡23-24 እዚአብሐር ያላንዳች ነውር ጠብቆ ክርስተስ ተመልሶ እስከሚመጣ ድረስ እንደሚያቆየን ያረጋግጥልናል።
ጥያቄ፦ በቅርቡ ኃጢአት የሠራችሁበትን ጊዜ አለቡ። ስለዚህ ኃጢአት ለእግዚአብሔር ከተናዘዛችሁ በኋላ እንኳን ምን ተሰማችሁ?
አንዳንድ ጊዜ ሰይጣን ወደ እኛ ዘንድ ይመጣና ስለ ሠራናቸው ብዙ ኃጢአቶች ያስታውሰናል። ይህን በመሰለ ሁኔታ ወደ እኛ ይጠጋና በደላችንን እያጎላ፥ ፈጽሞ ስእግዚአብሔር ፊት መቆም የማይገባን ኃጢአተኞች መሆናችንን እየነገረ ያስፈራራናል። ኃጢአታችንን በእግዚአብሔር ፊት የተናዘዝን ሆነን ሳለን እንኳን ቢሆን፥ ወደ እኛ ቀርቦ የኃጢአታችን ሸክም የከበደ መሆኑን እየወተወተ ማስፈራራቱን ይቀጥልበታል። ሰይጣን ይህን ያድርብን እንጂ እግዚአብሔር እንደሚሰጠን ተስፋ ከሆነ፥ ጌታ ኢየሱስ በመስቀል ላይ በከፈለው መሥዋዕትነት ኃጢአታችንን ይቅር በማለቱ፥ ከዚህ ሕይወት በኋላ የሥነ ተፈጥሮ ኃጢአት ጨርሶ ሊኖር እንደማይችልና፥ ከዚህም በስተቀር ኃጢአት የሚኖርበት ሥራ እንደማይሠራ ያረጋግጥልናል። በሁለመናችንም ፍጹማን ስለምንሆን፥ ሰይጣን ከዚያ ወዲያ እኛን የሚከስስበት ምክንያት ጨርሶ አይኖረውም። ክብርን በምንጎናጽፍበት ጊዜ፥ ካኃጢአት፥ ከበደልና ከክስ ነፃ እንሆናለን።
1.2 መክበር (ክብርን መጎናጸፍ) ማለት የአካላችን ወደ ፍጹምነት መታደስ ማለት ነው።
ጥያቄ፡- 1ኛ ቆሮ. 15፡20፥ 42-44፥ 49-57 ቀን አንብብ። ሀ) ሐዋርያው ጳውሎስ እካላችን አሁን ምን ይመስላል አለ? ሐዋርያው ወደፊትስ አካላችን ምን ይመስላል አለ?
ያቄ፦ 2ኛ ቆሮ 5፡1 አንብብ። ሀ) ሐዋርያው ጳውሎስ ያሁኑን አካላችንን ከምን ጋር ያመሳስለዋል? ለ) ደግሞስ በሞታችን ጊዜ የምንለብሰውን አካል ከምን ጋር ያመሳስለዋል?
ጥያቄ፡- ፊልጵ. 3፡21 አንብብ። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም በሚመጣበት ጊዜ፥ ይህን የተዋረደውን ሰውነታችንን ወደ ምን ይለወጣል?
ይህ የለበስነው አካላችን ወደፊት በሚመጣው የክብር አካል እንደሚተካው ከሚያስተምሩት እጅግ ግልጽ ከሆኑት ክፍሎች አንዱ የኛ ቆሮ. ምዕራፍ 15 ነው። በ10ኛው ትምህርት ላይ እንደተከታተልነው፣ የክርስቶስ ትንሣኤ እርሱን እንደ አዳኛቸው አምነው ለተቀበሉት ሁሉ የመጀመሪያው ፍሬ ወይም በኵር ነው። የእርሱ ትንሣኤ የእኛን መጪውን ትንሣኤ ያረጋግጥልናል። እንዲሁም የክርስቶስ የተነሣው አካል፥ ለመጪው ለሚነሣው አካላችን ምሳሌ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚናገረው፥ በምንሞትበት ጊዜ የሚቀበረው አካላችን ጠፊ፥ ደካማ፥ ተፈጥሮአዊና ክብር የለሽ ነው። ነገር ን ከሙታን በምንነሣበት ጊዜ፥ የማይጠፋና ሕያው፥ ክብርን የተጎናጸፈ፥ ኃይልና መንፈሳዊነትን የተሞላ አካል ይኖረናል። ጌታ ኢየሱስ ከሙታን በተነሣ ጊዜ እንደ ነበረው ያለ የተሟላ የሰው አካል ይኖረናል። ያሁኑ አካላችን , ከአፈር የተሠራውን የአጻምን አካል የሚመስል ነው፡ ነገር ን አካላችን ክብርን ሲለብስ ወይም ሲከብር፥ ከሰማይ የመጣውን የኢየሱስን አካል ይመስላል። ሐዋርያው ጳውሎስ “የማይጠፋ፥ ሕያው’ ብሎ ሊላ፥ በፍጹም የማይሞት አካል ይኖረናል ማለቱ ነው። የሰዎች የመጨረሻው ጠላት የሆነው ሞት ፈጽሞ ድል ይሆናል። የደኅንነት የክብር በረከት፥ የማይታመም፥ የማይደክምና የማይሞት አካልን ይሰጠናል። ጳውሎስ በፊልጵ. 3፡21 ውስጥ፥ እርሱ ይህን የተዋረደውን ሰውነታችንን በመለወጥ የእርሱን ክብሩ ሰውነት እንዲመስል ያደርገዋል” ይላል።
በ2ኛ ቆሮ. 5፡1 ውስጥ ጳውሎስ ይህን ሥጋችንን በድንኳን፥ ክብርን የሚጎናጸፈውን አካላችንን ደግሞ በእግዚአብሔር በታነጻ ዘላለማዊ መኖሪያ ይመስለዋል። ይህ ያለንበት አካላችን ጊዜያዊ ቤታችን ነው። ከዚህም የተኑግ ነው የሚያረጀው፥ የሚደከመውና ለሥቃይም በቀላሉ የሚጋለጠው ነገር ተን ይህ ሕይወት ካለፈ በኋላ፥ ከምንኖርበት፡ የተደረተ ጊዘያዊ ድንኳን ወደ አማረና ለዘላለም ወደማያረጀው ቤታችን እንዛወራለን። እዚህ ላይ ጳውሎስ፥ ይህ አካላችን ከፈረሰ በኋላ፥ ነዋሪ ወደ ሆነው ዘላለማዊ ቤታችን እንገባለን ብሎ የተናገረውን ሰጥሞና አስቡ። አማኞች የሆኑ ሁሉ ከዚህ ዓለም በሞት በሚያልፉበት ጊዜ፥ ወዲያውኑ የክብር በረከት የተሞላበትን አካል ይለብሳሉ። የተለምዶ ስለሆነ፥ ቤተሰቦቻችን ወይም ወዳጆቻችን በሞት በሚለዩን ጊዜ እናዝናለን ነገር ቀን በሞት ምክንያት ከምንወዳቸው ሰዎች የመለየት ሁኔታ እንዲሁ የተለምዶ ነው ማለት አንችልም። ሞት የኀዘን ወቅት ቢሆንም በተለይ በጌታ ኢየሱስ የሚያምኑ ሰዎች በሚሞቱበት ጊዘ የኀዘናቸው ጊዜ ሆኖ ሊወሰድ አይገባም። ምክንያቱም በክርስቶስ ለሚያምኑት በሚሞቱበት ጊዘ ወቅቱ አርጌና ጊዜያዊ ከሆነው የመኖሪያ ድንኳናቸው ወደ አማረውና ዘላለማዊ ወደ ሆነው ቤታቸው የሚዛወሩበት ጊዜ ስለሆነ ነው። ስለዚህ እንዲህ ላሉት አማኒያን በማንሳት ፈንታ፥ በደስታ ልንሸኛቸው ይገባናል!
ጥያቄ፡- 2ኛ ቆሮ. 4፡16-18 አንብብ። በክርስቶስ አማኝ የሆኑ ሰዎች ዛሬ ባሉበት ሁኔታ በአካላቸው ላይ ሥቃይ በሚደርስባቸው ጊዜ ስሜታቸው እንዴት ሊሆን ይገባል?
ጥያቄ፡- ሀ) እስቲ አሁን በቅርቡ ታምማችሁ ወይም ተሠቃይታችሁ ስለነበረበት ሁኔታ አስቡ። የሚመጣው የክብር ተስፋ እንዴት መጽናኛ ሊሆናችሁ ይችላል? ለ) አሁን በቅርቡ ለለ ሞተ ስላምታውቁት ሰው ለማሰብ ሞክሩ። ለአማኞች ሁሉ የተሰጠው የክብር ተስፋ እንዴት መጽናኛ ይሆናችኋል?
አካላችን በክብር የመነሣቱ ተስፋ ከደኅንነት በረከቶች መካከል እጅግ በጣም አስደናቂው ነው። ዛሬ አመም ሲያደርገን፥ ወይም ሥቃይ ሲደርስብን፥ ከዕለታት አንድ ቀን በቅርቡ ጨርሶ ሥቃይ የሌለበት አካል እንደሚኖረን እናምናለን፡ ምንም እንኳን እርሱ በዚህ ሕይወት ሁልጊዜ ከሚደርስብን ሕመም ሳይፈውሰን፥ ወይም ከሚሰማን ሥቃይ ሳያወጣን ቢዘገይም፥ ይህ ሕይወት ካለፈ በኋላ ነዋሪውን አካል በምንለብስበት ጊዜ፥ በሽታና ሥቃይ ጨርሶ የማይኖርበትን ሕይወት በመኖር እንደምንደሰት ያረጋግጥልናል። እንደዚሁ፥ ክርስቶስን እንደ ግል መድኃኒታቸው ተቀብለው የነበሩ ወዳጆቻችን ወይም የቤተሰብ አባላት ሲሞቱ፥ በሕይወታቸው ሳሉ ያደኅንነትን የክብር በረከት ያገኙ በመሆናቸው ደስ ልንሰኝ ይገባናል። እንዲያውም የእነርሱ ሁኔታ ከእኛ ይልቅ የተሻለ ነው። ምክንያቱም ወደ ዘላለማዊው ቤታቸው ገብተዋልና ነው! ስለዚህ፣ በማንኛውም ጊዜ ሥቃይ በሚደርስብን ጊዜ፥ ስለ ደረሰብን ሥቃይ ከማሰብና ከመጨነቅ ይልቅ፥ ዓይናችንን በሚመጣው ክብር ላይ ተክለን መላ አሳባችን ሁሉ በእርሱ ላይ ሊያርፍ ይገባል። ዛሬ የሚደርስብን ሥቃይቶ ሊመጣ ያለው የእግዚአብሔር አስደናቂ የክብር በረከት መምጫ መንገድ ነው።
1.3 ክብር (መክበር) ማለት ፍጹም የሆነ እውቀት ይኖረናል ማለት ነው።
ጥያቄ፡- 1ኛ ቆሮ. 13፡12 አንብብ። በዚያን ጊዜ ወደፊት እንዴት እናውቃለን?
በ1ኛ ቆሮ. 13፡12 ውስጥ ሐዋርያው ጳውሎስ አስደናቂ የሆነ ተስፋ ይሰጣል። ስለዚህም ሊገልጥ ሐዋርያው፥ በዚህ ሕይወት ላለን ስለ መንፈሳዊ እውነታ የምናውቀው በጣም ጥቂት መሆኑን ይነግረናል። ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ መንፈሳዊ ስጦታዎች ማወቅ ስለ እግዚአብሔር አንዳንድ ነገሮችን ያስተምረናል። ነገር ገን፣ በዚህ ሕይወት እያለን ስለ እግዚአብሔር የምናውቀው ድንቀዝቀዝ ባለ በመስተዋት እንደምናየው ዓይነት ነው። እንዲሁም ዛሬ ባለንበት ሕይወት ስለ እግዚአብሔር የምናውቀው፥ የሕፃንን እውቀት ያህል ነው። ጳውሎስ እንደሚለው፣ ክርስቶስ ተመልሶ ሲመጣ፥ ያን ጊዜ ፍጹም የሆነ እውቀት ይኖረናል። እዚህ ላይ ጳውሎስ የሚናገረው እኛ ስለ እግዚአብሔርና ስለ እውነተኛው መንፈስ ያለንን እውቀት ነው። እነሆ፥ እኛ በማናውቀውና በማንጓዘበው ምሥጢራዊ መንገድ ስለ እግዚአብሔር የሚኖረን እውቀትና የደኅንነታችን ምሥጢር በምንከብርበት ጊዜ ፍጻሜ ያገኛሉ። ኢየሱስን የማወቃችንና እርሱም ያደረገልንን ሁሉ የመገንዘባችን ሁኔታ እኛ የተፈጠርንለትን ዓላማ በፍጹምነት የሚያሟላ ሂደት ነው። በምንከብርበት ጊዜ ያኔ እግዚአብሔር እኛ እንድናውቀው ባቀደልን መንገድ ልናውቀው እንችላለን።
ጥያቄ፡- 1ኛ ዮሐ 3፡2 አንብብ። ጌታ ኢየሱስ ተመልሶ በሚመጣበት ጊዜ ማንን እንመስላለን?
ምናልባት የክብር በረከት በእያንዳንዳችን ሕይወት ውስጥ ስላለው ሁኔታ ማጠቃለል ብንፈል፦
መክበር ማለት እኛ ኢየሱስን እንመስላለን ማለት ነው!
እዚህ ላይ ኢየሱስን እንመስላለን ሲባል፥ እኛ ራሳችን የኢየሱስን መለኮታዊ ባሕርያትን ሁሉ እንበላለን ማለት አለመሆኑን መገንዘብ ያሻል። እግዚአብሔር ብቻ አምላክ ስለሆነ ወደ ሰማይ በምንሄድበት ጊዜ እና እግዚአብሔርን መሆን አንችልም። ነገር ን ኢየሱስን በሰብአዊ ፍጹምነቱ ልንመስል እንችላለን፡ ኢየሱስ ያላንዳች ነውር ፍጹም እንደ ነበረ ሁሉ፥ ንጹሕ እንደሆነ እንዲሁም ቅዱስ እንደ መሆኑ ሁሉ፥ እኛም ነውር የሌለብን፥ ንጹሐንና ቅዱሳን እንሆናላን፡ በዚሁ ሁኔታ፥ ጌታ ኢየሱስ ከትንሣኤው በኋላ በሙሉ አካል እንደተገለጠው ሁሉ እኛም በትንሣኤ ሙሉ አካል ይኖረናል። እንደዚሁም ጌታ ኢየሱስ ከአባቱ ጋር ፍጹም የሆነ እውቀት ያለበት ግንኙነት እንደ ነበረው ሁሉ፥ እኛም እንደ እርሱ ፍጹም እውቀት ያለበት ግንኙነት ከእግዚአብሔር ጋር ይኖረናል። ስለሆነም መከበር ሲባል እኛ ኢየሱስን እንመስላለን ማለት ነው!
2. የእኛ መከበር በተቀሩት ፍጥረታት ላይ ምን ውጤት ይኖረዋል?
14ኛ ጥያቄ፡- ሮሜ 8፡18-23ን አንብብ። የእኛ በተቀሩት ፍጥረታት ላይ ምን ውጤት ይኖረዋል?
ጌታ ኢየሱስ ዳግም ተመልሶ በሚመጣበትና በእርሱም የሚያምኑ ሁሉ በሚከብሩበት ጊዜ፥ የመክበራችን ውጤት በተቀረው ፍጥረት ላይ ይፈስሳል። በሮሜ 8፡18-23 ጳውሎስ ሲናገር፣ የሰው ልጆች ካመጡበት የኃጢአት መርገም የተነሣ ፍጥረት ሁሉ እንዲሠቃይ ሆኖአል ይላል። ስለዚህ ከኃጢአት ውጤት የተነሣ በምንሠቃይበት ጊዜ ፍጥረት ሁሉ አብሮን ይሠቃያል። በአንጻሩ፥ የምንጎናጸፈው ክብር አሁን ያለብንን ሥቃይ ጠርጎ ስለሚያስወግደው፥ እንደዚሁ ሁሉ፥ የእኛ ክብርን መላበስ የፍጥረታት ሥቃይ ሁሉ እንዲያበቃ ያደርጋል። ስለዚህ ፍጥረት በመላው፥ እኛ ክብርን አግኝተን የኃጢአት ውጤት ሁሉ የሚወገድበትን ጊዜ በናፍቆት ይጠባበቃል። የምናገኘው ክብር አካላችንን የሚያድሰው ብቻ ሳይሆን፥ በዙሪያችን ያለውን ሥነ ተፈጥሮአዊ ዓለምንም አዲስ ያደርገዋል።
3. እንደምንከብር (ክብርን እንደምንጎናጸፍ) እንዴት እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን?
ጥያቄ፡- ቲቶ 1፡2 አንብብ። የማይዋሸው አምላክ፥ በእርሱ ለተመረጡት የሰጠው ተስፋ ምን ነበር? 16ኛ ጥያቄ፡- ዕብ 11፡16፥ 39-40 አንብብ። የእምነት አርበኞች ከእኛ ጋር ምንን ያገኛሉ?
ጥያቄ፡- ያዕቆብ 2፡25 አንብብ። እግዚአብሔር በእምነት ለበለጸጉትና ለሚወዱት ምንን ሊሰጣቸው ተስፋ አደረገ?
ጥያቄ፡- ሮሜ 8፡30 አንብብ። አስቀድሞ የወሰናቸው፥ ደግሞም የጠራቸውና ያጸደቃቸው ምን ይሆናሉ?
በመላው የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ እግዚአብሔር በተደጋጋሚ ጊዜያት በሰጠው ተስፋ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ወደ እርሱ ዘንድ የሚመጡት ሁሉ ክብርን እንደሚጎናጸፉ እርግጠኞች ሊሆኑ እንደሚገባ ገልጧል። በቲቶ 1፡2 ሐዋርያው ጳውሎስም እንደተናገረው፣ «የማይዋሸው አምላክ ይህን ሕይወት ሊሰጠን ከዘመናት በፊት ቃል ገባልን» ይላል። በዕብ 11፡39-40ም ያለው ቃል የብሉይ ኪዳን የእምነት አርበኞች ከአዲስ ኪዳን አማኞች ጋር በአንድነት ሰማያዊት ከተማ የሆነችውን ፍጹማዊት ውርስን ይወርሳሉ ይላል። በዚህ ዓለም ውስጥ ምንም እንኳን ድሆች ብንሆንም፥ ሐዋርያው ያዕቆብ በመልእክቱ ምዕራፍ 2፡5 ላይ እግዚአብሔር የሚወዱትን የመንግሥቱ ወራሾች እንዲሆኑ የመረጣቸው መሆኑን ይናገራል። በሮሜ 8፡30 እግዚአብሔር አስቀድሞ የመረጣቸው እንዲሁም የጠራቸውና ያጸደቃቸው እንደሚከብሩ ይገልጻል። ጌታ ኢየሱስን እንደ መድኃኒታቸው አድርገው ያወቁት ሁሉ ከዚህ ሕይወት በኋላ የደኅንነትን የከብር በረከት ይቀበላሉ።
ጥያቄ፦ እስቲ ለመጨረሻ ጊዜ ከሞት በኋላ ምን እንደሚደርስባችሁ የፈራችሁበትን ወቅት አስቡ። ከሆነ፥ የዛሬው ትምህርት በምን አኳኋን ሊያጽናናችሁ ይችላል?
ጌታ ኢየሱስን እንደ አዳኛቸው አድርገው ያመኑትና ከእርሱም ጋር መታረቃቸው የተነገረላቸው ሁሉ፥ የዘላለምን ደኅንነት ክብር ያላንዳች ጥርጥር ያገኛሉ። እግዚአብሔር ከዚህ የተሻለ ምን ተስፋን ሊሰጥ ይችላል? ከሞት በኋላ ምን ይደርስብን ይሆን ብላችሁ ፍርሃት በሚሰማችሁ ጊዜ፥ ዛሬ ወደ ተማርነው ክፍል መለስ በማለት እግዚአብሔር የሰጣችሁን አስደናቂውን የደኅንነት ክብር በረከት ተስፋ አስቡ።
ክርስቶስን እንደ አዳኝ አምነው የተቀበሉትን እግዚአብሔር የማክበሩ ነገር፥ አማኞች ይህ ያገኙት ደኅንነት አስተማማኝ መሆኑ ብዙ ጥያቄዎችን አስከትሏል። ስለዚህ በዚህ ሳምንት ውስጥ በቀሪው ክፍለ ጊዜ የእነዚህ እውነተኛ አማኞች ዘላለማዊው ደኅንነት የተረጋገጠላቸው ስለ መሆኑና ስላለመሆኑ፥ እንዲሁም እነዚህ እውነተኞች አማኞች ለእግዚአብሔር ታማኛች በመሆን በዚሁ የሚቀጥሉ ስለ መሆናቸው እናጠናለን።
ምንጭ፡- “አስተምህሮ ክርስቶስና ደኅንነት”፤ ጽሑፍ፣ በዶ/ር ስቲቭ ስራውስ፤ ትርጉም በኃይሉ ልመንህ
