Site icon

ስለ ተሠገዎ በዕብራውያን ምዕራፍ 2 

ዛሬ በዕብራውያን 2፡5-18 ያለውን ስለ ተሠገዎ የሚያስተምረውን ሦስተኛውን ቁልፍ ክፍለ ምንባብ እንመለከታለን። ይህ ክፍል ኢየሱስ እግዚአብሔር ሆኖ እያለ በምን ምክንያት ፍጹም ሰው ለመሆን እንዳስፈለገው እንድንገነዘብ ይረዳናል። 

1. እኛ ፍጥረታትን እንድንገዛ፥ ኢየሱስ ሰው ሆነ 

ጥያቄ፡- ዕብራውያን 2፡5-8 እንብቡ። ሀ) እግዚአብሔር የሚመጣውን ዓለም ለማን ነው የማይሰጠው? ለ) የሚመጣውን ዓለም ለማን ይሰጣል? ሐ) እኛስ ገና | ያላየነው ምንድን ነው? 

ጥያቄ፡- ዕብራውያን 2፡9 ኣንብቡ። ምንን እናያለን? 

ጥያቄ፡- ይህን ክፍል ከአነበባችሁ በኋላ ኢየሱስ ሰው እንዲሆን ያስፈለገበትን ምክንያት ለማሰላሰል ጊዜ እንዲኖራችሁ አድርጉ። ከዚያም ስታሰላስሉ የቆያችሁትን አሳብ በማስታወሻ ደብተር ጻፉ። 

ዕብራውያን 2፡5-18 ለሰው ልጆች በተሰጠ አስደናቂ የተስፋ ቃል ይጀምራል። ጸሐፊው በዕብራውያን 2፡1-4 ውስጥ አንባቢዎቹ ለወደፊቱ ስላሚጠብቃቸው የደኅንነት ፍስሐ በማብሰር ይናገራል። ይህ ደኅንነት የሚመጣውን አስደናቂ ዓለም ይጨምራል ይላል። ነገር ግን ይህ መጪው ዓለም ለመላእክት አይደለም። ታዲያ የእግዚአብሔር ዓላማ መጪውን ዓለም ለማን ለመስጠት ነው? ደራሲው ለዚህ መልስ ለመስጠት መዝሙር 8፡4-6 ይጠቅሳል። ምንም እንኳን የሰው ልጆች ከመላእክት ጥቂት ቢያንሱም፥ በመጪው ዓለም ግን የክብርና የምስጋና ዘውድን ይቀዳጃሉ። ሰዎች በመጪው ዓለም የእግዚአብሔርን ፍጥረተ ዓለም ሁሉ (ዩኒቨርስን) ይገዛሉ። እኛ አማኞች ከሚኖሩን ታላቅ የደኅንነት በረከቶች አንድ ቀን እግዚአብሔር በፈጠረው ሁሉ ላይ ገዥዎች የመሆናችን እውነታ ነው። 

ነገር ግን ይህን አስደናቂ በረከት ገና አልተቀበልንም። አሁን ባለንበት ሕይወት ሰብአዊ ፍጡር በፍጥረታት ላይ ያለውን የአገዛዝ ሥልጣን ገና አላየነውም። እነዚህን በረከቶች አንድ ቀን እንደምንቀበል እንዴት ልናውቅ እንችላለን? ይህን የወደፊት በረከት የሚያረጋግጡልን አንዳንድ ነገሮችን እናያለን። በአንድ ወቅት ሰው በመሆን ዝቅ ብሎ የውርደትንና የትሕትናን ሕይወት የኖረው ኢየሱስ ከፍ ከፍ ሲል አይተናል። ኢየሱስ ልክ እንደ እኛው ሰው ሆነ። ለእኛ ሊሞት ብሎ ሥጋን ለበሰ። ይህ ከእኛ እንደ አንዱ ሆኖ የኖረው ኢየሱስ አሁን በሰማይ ከፍ ከፍ ብሎ ይገኛል። መላ ፍጥረተ ዓለምን (ዩኒቨርስን) የመግዛት ክብር፥ ሞገስና ገናናነት ያለው ኢየሱስ ብቻ ነው። ነገር ግን ኢየሱስም ሰው ስለነበረና በዚህ ባሕርይ ስለምንዛመደው እኛም የዚህ አገዛዝ ተካፋዮች የመሆን ባለ መብት ነን። 

አንድ ሰው የአገሩ ፕሬዚዳንት ሆኖ በሚመረጥበት ጊዜ፥ እርሱ ብቻውን የሥልጣንና የማንኛውም ክብር ባለቤት ሆኖ በቤተ መንግሥቱ ውስጥ አይኖርም። ባለቤቱና ልጆቹ በቤተ መንግሥቱ ውስጥ አብረውት በመሆን ክብር የተመላበትን ሕይወት ይጋራሉ። በዚሁ መሠረት እኛም ከኢየሱስ ጋር ባለን ተዛምዶ ከእርሱ ጋር ሆነን በኣዲሱ ዓለም ክብርና ደስታ የተሞላበትን ሕይወት እንኖራለን። ጌታ ኢየሱስ ሰው ሆኖ ተሠቃይቶ ከሞተልን በኋላ በሰማይ ከፍ ብሎ ስላለ፥ የደኅንነት በረከቶቻችንን እንደምናገኝ እርግጠኞች ነን። ምክንያቱም እግዚአብሔር ሰውም-ኣምላክም የሆነውን ኢየሱስን ከሁሉም በላይ ከፍ ከፍ ስላደረገው፥ ተስፋውን ጠብቆ ልጆቹ ፍጥረታትን እንዲገዙ ከፍ ከፍ እንደሚያደርጋቸው እናውቃለን። 

ከኢየሱስ ጋር እንዴት ልንዛመድ ቻልን? ምክንያቱም እርሱ ፍጹም ሰው ሆኖ እስከ ሞት ድረስ ሥቃይን ስለተቀበለ ዝምድና ልንመሠርት ችለናል። ኢየሱስ የሰው ልጆች እውነተኛ አለኝታ ሆኖ ክብር የተሞላበትን ደኅንነት ለሰዎች ለመስጠት የእርሱ ሰብአዊነትና ሰብአዊ ሥቃይ አስፈላጊዎች ነበሩ። ደግሞም የኢየሱስ ሰብአዊነት ለመጪው ደኅንነታችን እውነተኛ ዋስትናችን ነው። የወደፊቱን የክብር ወራሽነት እንድናገኝ ኢየሱስ ፍጹም ሰው መሆን ነበረበት። 2. ኢየሱስ ከእኛ ጋር አንድ ቤተሰብ ሆኖ ደኅንነትን ለመስጠት ሰው ሆኖአል። 

ጥያቄ፡- ዕብራውያን 2፡10 አንብቡ። እግዚአብሔር (ብዙ ልጆችን ወደ ክብር ለማምጣት ብሉ) በደኅንነት ራስ (ኢየሱስ) ላይ ምን አደረገ? 

ጥያቄ፡- ዕብራውያን 2፡11-13 አንብቡ። ሀ) ሌሎችን ሊቀድስ የሚችል እርሱ ማን ነው? ለ) የተቀደሱት እነማን ናቸው? ሐ) የሚቀድሰውና የሚቀደሱት ሁሉ ከአንድ ናቸውና ይላል። «ከአንድ ናቸውና» ሲል ምን ማለቱ ነው? 

ጥያቄ፡- በቁጥር 11-13 ላይ ኢየሱስ የሰው ልጆችን ምን ብሎ ይጠራቸዋል? ቢያንስ ሁለት መልሶችን ፈልግ። 

እነዚህ ጥቅሶች ስለ ኢየሱስ ሰብአዊነት ጠለቅ ያለ ግንዛቤ ይሰጡናል። በመጀመሪያ ደረጃ ኢየሱስን የደኅንነታችን «ራስ» ሲሉ ይገልጹታል። «ራስ» ተብሎ ከግሪክኛው የተተረጎመው ቃል፥ ከሁሉ ቀድሞ ወደ አዲስ አገር ደርሶ ሌሎች እንዲከተሉት መንገድ የሚከፍት ማለት ነው። ከኃጢአት በስተቀር ኢየሱስ በሁሉም ረገድ እንደ እኛው ሆኖ ብዙ ልጆች በክብር ደኅንነቱ ደስ እንዲላቸው መንገዱን ከፈተላቸው። ነገር ግን ይህን ለማድረግ የሞትን ሥቃይ ተቀብሎ ፍጹም መሆን ነበረበት። ስለዚህ ኢየሱስ ተሠቃይቶ ባይሞት ኖሮ ፍጹም ሰው ሊሆን ባልቻለ ነበር። እንደዚሁም ሥቃይን ተቀብሎ ባይሞት ኖሮ ፍጹም መድኅን ባልሆነም ነበር። ኢየሱስ በሥቃዩና በሞቱ ጊዜ እንኳን ፍጹም ሰው ነበር። ምክንያቱም እርሱ በሥቃዩና በሞቱ ፍጹም ሰው ስለነበረ፥ የእግዚአብሔርን ልጆች ክብር ወጻለው ደኅንነት ለማምጣት የሚችል መድኅን ነበር። 

ለመሆኑ ኢየሱስ ሙሉ በሙሉ ሰው ነው? ጸሐፊው ኢየሱስ ሰብኣዊ ከሆነ ቤተሰብ የተገኘ ፍጹም ሰው መሆኑን ለማስረዳት ከብሉይ ኪዳን ጥቅሶችን ያቀርባል። የሚቀድሰው ኢየሱስ ራሱ ነው። የሚቀደሱት ደግሞ ሁሉም አማኞች ናቸው። «ከአንድ ናቸውና» ወይም «ከአንድ አባት ናቸውና» ይህን ሊል ከአንድ ቤተሰብ ናቸው ማለቱ ነው። ኢየሱስና የሰው ልጆች አንድ ቤተሰብ ናቸው። ይህን ለማረጋገጥ መሢሑ የተቀሩትን የሰው ልጆች «ወንድሞቼ» ሲል የተናገረውን መዝሙር 22፡22 በመጀመሪያ ይጠቅሳል። ሰዎች የኢየሱስ ወንድሞችና እኅቶች ከሆኑ፥ እርሱ ራሱ ሰው ነው ማለት ነው። በምድር መሢሑ፥ ሌሎች እግዚአብሔርን ሲቃወሙ እግዚአብሔርን ከሚያምኑ የእግዚአብሔር ሰዎች ጋር ራሱን ያመሳሰለበትን በሁለተኛነት ኢሳይያስ 8፡17 ይጠቅሳል። ልክ ሌሎች ሰዎች በእግዚአብሔር እንደሚተማመኑ ሁሉ፥ እርሱም በእግዚአብሔር ይተማመን ነበር። በምድር በነበረበት ጊዜ ፍላጎቱን እግዚአብሔር እንዲያሟላለት በፍጹም ሰብአዊነቱ በእግዚአብሔር ይተማመን ነበር። በመጨረሻውም ላይ፥ መሢሑ ሕዝቡን «ልጆቼ» ብሎ የተናገረበትን ኢሳይያስ 8፡18 ይጠቅሳል። ምክንያቱም መሢሑ ሰዎች የሆኑ ተከታዮቹን ወንድሞቼና ልጆቼ ብሎ ስለሚጠራቸው እርሱ ሰው መሆኑን በዚህም እንረዳለን። በእርግጥም ኢየሱስ ብዙ ልጆችን ክብርን ወደ ተጎናጸፈ ደኅንነት ለማምጣት ፍጹም ሰው ሆኖአል። 

3. ኢየሱስ በሞቱ ሰይጣንን ለማሸነፍ ሰው ሆኖአል። 

ጥያቄ፡- ዕብራውያን 2፡14-15 አንብቡ። ሀ) ቀደም ሲል በሞት ላይ ሥልጣን የነበረው ማን ነው? ለ) ይህ ምን ማለት ነው? ሐ) ኢየሱስ ስለዚህ ምን አደረገ? መ) ኢየሱስ በሞት ፍርሃት ባርነት ውስጥ ላሉት ምን አደረገ? ሀ) ኢየሱስ ሥጋና ደምን ለምን ተዋሃደ? 

ጥያቄ፡- ዕብራውያን 2፡18 ኢየሱስ የሚረዳው ማንን ነው? 

ኢየሱስ ሙሉ በሙሉ ሰው የሆነበትን ምክንያት ደራሲው በሰፊው መግለጹን አሁንም ይቀጥልበታል። ኢየሱስ፥ ሰይጣን በሰዎች ላይ ያለውን የሞት ሥልጣን ለመሻርና እርሱን ለማሸነፍ ኢየሱስ ፍጹም ሰው መሆን ነበረበት። ደራሲው ሰይጣን የሞት ሥልጣን በሰዎች ላይ አለው ሲል፥ ምን ማለቱ ነው? ይህን ሲል፥ ሰይጣን ሰዎችን የመግደል ሥልጣን አለው፥ ወይም ኢየሱስ በተሰቀለ ጊዜ ለሰይጣን የሞት ካሳ ከፈለው ማለት አይደለም። ሰይጣን ሰሞት ላይ ያለው ሥልጣን፥ ሰዎች ኃጢአት እንዲሠሩ መፈተን ነው። ሰዎች ኃጢኣትን በሚያደርጉበት ጊዜ፥ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ስለሚጥሱ በሥጋም በመንፈስም እንዲሞቱ ይፈረድባቸዋል። ስለዚህ ፍጥረተ ዓለማትን (ዩኒቨርስን) ለመግዛት የተመረጥን የሰው ልጆች ከኃጢአታችን የተነሣ የሞትና የሰይጣን ባሪያዎች እንሆናለን። 

ጥያቄ፡- ሞትን በመፍራታቸው ስለምታውቋቸው ሰዎች እስቲ አስቡ። ስማስታወሻ ደበተራችሁ ውስጥ ከሁለት እስከ ሦስት ሰዎች ጻፉ። እነዚህ ሰዎች በምን ምክንያት ሞትን ይፈራሉ? 

ሰዎች በሞት ፍርሃት ምክንያት በባርነት ውስጥ መኖራቸውን በቀላሉ ልንገነዘብ እንችላለን። እስቲ በቅርቡ ስለተገኛችሁበት በክርስቶስ የማያምኑ ሰዎች ልቅሶ አስቡ። የሞቱ ወላጆቻቸውና ወዳጆቻቸው ከሞት በኋላ ምን እንደሚሆኑ እርግጠኞች ባለመሆናቸው ተስፋ በቆረጠ ስሜት ያለቅሳሉ። ሰዎች ሁሉ ኃጢአተኞች መሆናቸውን በልባቸው ያውቃሉ። እንደዚሁም በኃጢአታቸው ምክንያት ቅጣት እንደሚገባቸውም ያውቃሉ። ስለዚህ ሰዎች ራሳቸውም ሆኑ ወዳጆቻቸው በሚሞቱበት ጊዜ ቅጣታቸውን የሚቀበሉ መሆናቸውን ስለሚረዱ ሞትን በጣም ይፈሩታል። ሰይጣን ኃጢአትን እንድንሠራ ስለሚያደርገንና ኃጢአታችንም ለቅጣት አሳልፎ ስለሚሰጠን፥ ሰዎች የሞት ፍርሃት ባሪያዎች እንሆ ለልን። 

ነገር ግን ኢየሱስ በሞተ ጊዜ ሰይጣን በሞት ላይ የነበረውን ኃይል ደምስሶ ሰዎችን ከሞት ፍርሃት ውስጥ ነፃ አውጥቶአቸዋል።

ጥያቄ፡- ቆላስይስ 2፡13-5 አንብቡ። ሀ) ኢየሱስ በሞተ ጊዜ ይኮንኑን ስለነበሩት ሕጎች ወይም የዕዳ ጽሑፎች ምን ኣደረገ? ለ) ይህ አለቅነትንና ሥልጣናትን ምን አደረጋቸው? 

ቆላስይስ 2፡13-15 ኢየሱስ በሞተ ጊዜ የተጻፈውን ጽሕፈት ማለትም የእግዚአብሔርን ሕግ በመስቀል ላይ በሚስማር ጠርቆታል ይላል። በጥንቱ ዓለም፥ አንድ ሰው በሚሰቀልበት ጊዜ፥ በግለሰቡ የስቅላት ቅጣት የደረሰበትን ምክንያት የሚያስረዳ ጽሑፍ እዚያው አጠገቡ በመስቀሉ ላይ በሚስማር ይመታ ነበር። ይህ ጥቅስ የሚነግረን፥ ኢየሱስ በተሰቀለ ጊዜ የእርሱ ቅጣት እኛ የእግዚአብሔርን ሕግ መጠበቅ አለመቻላችን መሆኑን ነው። ስለዚህ የእግዚአብሔርን ሕግ በመጣሳችን ልንከፍል የነበረውን የሞት ዕዳ ኢየሱስ ስለ ከፈለልን፥ እግዚአብሔር ዕዳችንን ሰርዞልናል። እነሆ፣ ዕዳችን ስለ ተከፈለልን፥ ሰይጣንና ጭፍሮቹ በእኛ ላይ የነበራቸው ኃይል ተወግዷል። ስለሆነም ኢየሱስ በሞቱ በእኛ ላይ ይሠለጥን የነበረውን የሰይጣንን ኃይል ደምስሶታል። 

ኢየሱስ በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ፥ ለእግዚአብሔር መክፈል የነበረብንን የኃጢአት ቅጣት ዕዳ እርሱ ከፈለልን። የክርስቶስን ሞት ለኃጢአታቸው የተከፈለ ቤዛ አድርገው የሚቀበሉ ሁሉ፥ ለኃጢአታቸው ዋጋ ለመካፈሉ ዋስትና አላቸው። ስለዚህ ምንም ጊዜ ሞትን የሚፈሩበት ምክንያት የላቸውም። ከእንግዲህ ወዲያ የኃጢአት ቅጣት አያስፈራቸውም፤ ምክንያቱም ኢየሱስ በሥቃዩ ቅጣታቸውን ተቀብሎላቸዋልና። ሰይጣን ለምን ጊዜውም ቢሆን የፍርሃት ባሪያ ሊያደርጋቸው አይችልም፤ ምክንያቱም ኢየሱስ ሰው ሆኖ መጥቶ ለኃጢአታቸው ሞቶላቸዋልና። ኢየሱስ የሰው ልጆች ሊሞቱ የሚገባቸውን ሞት ሊሞትላቸው፥ ሥጋና ደምን ወስዶ ሙሉ በሙሉ ሰው ሆነ። ክርስቶስ ይህን ሞት በሞተ ጊዜ ሰይጣንን ድል አድርጎ ከሞት ፍርሃት ነፃ አወጣን። መላእክት ይህን የመሰለ አርነት አይሹም፡ ምክንያቱም ንጹሐን የሆኑት መላእክት ኃጢኣት ኣላደረጉም። ሰዎች ግን ኃጢአትን ፈጽመዋል። ስለዚህ ኢየሱስ በአብርሃም እምነት ውስጥ ያሉትን የሰው ልጆች ከሞት ፍርሃት አርነት ለማውጣት ራሱ ሰው ሆነ። 

ጥያቄ፡- በ33ኛው ጥያቄ ላይ ስሞቻቸውን ስለ ጻፋችኋቸው ሰዎች እለሱ። ስለ ኢየሱስ ሰብአዊነት ከሚናገረው ከዚህ ምንባብ ውስጥ ለእነርሱ ማበረታቻ የሚሆን የትኛውን አብራችኋቸው ትካፈላላችሁ? 

የተሠገዎ ምሥጢር ኢየሱስ ከኃጢአት በስተቀር ሰብኣዊነትን ተላብሶ፥ እኛን ከሞት ፍርሃት ነፃ ማውጣቱ ነው። የሞት ፍርሃት አለባችሁ? በክርስቶስ ፍጹም ሰብኣዊነት ደስ ይበላችሁ። ኢየሱስ ሙሉ በሙሉ ሰው መሆኑን የምታምኑ ከሆናችሁ፥ ሞትን ከቶ ልትፈሩ አይገባችሁም። ሞትን የሚፈሩ የምታውቋቸው ሰዎች አሉ? ካሉ ስለ ክርስቶስ ሙሉ ሰብኣዊነት ያለውን እውነት አብራችኋቸው ተካፈሉ። እርሱ ሙሉ በሙሉ ሰው ስለሆነ፥ ሞትን ጨርሶ ሊፈሩ አይገባቸውም። 

4. ኢየሱስ ፍጹም ካህናችን ሊሆን ሰው ሆነ። 

ጥያቄ፡- ዕብራውያን 2፡17-18 አንብቡ። ኢየሱስ ለብአዊ ካህን እንዲሆን ለምን አስፈለገ? ከእነዚህ ሁለት ጥቅሶች በመነሣት ሁለት ምክንያቶችን ጻፉ። 

ጸሐፊው ኢየሱስ በምን ምክንያት ሰው እንዲሆን እንዳስፈለገ ገለጻውን ለማጠቃለል እንደ ሰብአዊ ካህን የፈጸማቸውን ሁለት ተግባራት ያብራራል። ኢየሱስ በማንኛውም መንገድ እንደ ወንድሞቹ መሆን ነበረበት ይለናል። እንደዚህ ማለት ኢየሱስ ሙሉ በሙሉ ሰው መሆን ነበረበት ማለት ነው። እንደ ሰብኣዊ ወንድሞቹና እኅቶቹ እርሱም ሰው መሆኑ ለምን አስፈለገ? ያስፈለገበት ምክንያት ፍጹም ካህናቸው እንዲሆን ነው። ስለዚህ ኢየሱስ በፍጹም ሰብአዊነቱ የሚያከናውናቸው ሁለት ተግባራት አሉ። በመጀመሪያ፡ ኢየሱስ የሰው ልጆችን ኃጢአት ያስተሰርይ ዘንድ ፍጹም ሰብኣዊ ካህን መሆን ነበረበት። ደራሲው ይህንን ዘርዘር አድርጎ በዕብራውያን 7-10 ይገልጽልናል። በሚቀጥለው ትምህርት ውስጥ ስለ ኃጢአት ኢየሱስ የከፈለውን መሥዋዕትነት አንሥተን እንወያያለን። እዚህ ላይ ደራሲው የሚነግረን፥ እርሱ ፍጹም ሰብኣዊ ካህን በመሆኑ ፍጹም የሆነ መሥዋዕትን ለእግዚኣብሔር ሊያቀርብ እንደ ቻለ ነው። 

ኢየሱስ ፍጹም ሰብአዊ ካህን እንዲሆን ያስፈለገበት ሁለተኛው ምክንያት እርሱ በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች ይገነዘብልን ዘንድና ፈተናዎቹንም እንድንቋቋማቸው ያበረታታን ዘንድ ነው። ደራሲው እንደ ገና በሚቀጥለው ትምህርት ይህን በዕብራውያን 4፡14-5፡1ዐ በበለጠ ዘርዘር አድርጎ ይገልጸዋል። እኛም በሚቀጥለው ትምህርት ውስጥ ስለ ኢየሱስ ካህንነት ተመልሰን እንወያያለን። ነገር ግን ከተሠገዎ ምሥጢር የተነሣ፥ ኢየሱስ ፍጹም ሰብአዊነትን ተላብሶ ፍጹም ርኅሩኅ ካህን በመሆን ሊያገለግል ችሏል። 

ዕብራውያን 2፡5-18 እንደሚያብራራው፥ በተሠገዎ ምሥጢር ውስጥ ኢየሱስ ፍጹም ሰው ሆነ። እንዲያውም ሰብአዊነቱ በሥቃይ ሞቱ የተሟላ ሆኖአል። ለወደፊቱ ከእርሱ ጋር ሆነን በእግዚአብሔር መንግሥት መግዛት የምንችልበትን በረከት ሊያረጋግጥልን የቻለው ፍጹም ሰው በመሆኑ ብቻ ነው። እርሱ ሙሉ በሙሉ ሰው በመሆኑ ብቻ ነው እኛም የእርሱ ቤተሰብ አካል ልንሆን የቻልነው። ሙሉ በሙሉ ሰው ከመሆኑ የተነሣ ብቻ ሰይጣንን ድል አድርጎ ከጣለብን የሞት ፍርሃት ነፃ አውጥቶናል። ለእኛ ፍጹም የሆነ ካህን ሊሆን የቻለውም ሙሉ በሙሉ ሰው ስለሆነ ብቻ ነው። ዕብራውያን 2፡5-18 እንደሚያስተምረን የኢየሱስ ፍጹም ሰብኣዊነት የእኛን ፍጹም ደኅንነት ያረጋግጥልናል። 

ጥያቄ፡– በዚህ ትምህርት ውስጥ ለእግዚአብሔር ምስጋና እንድታቀርቡ የሚያደርጋችሁ ምን ቁም ነገር ተማራችሁ? በደብተራችሁ ውስጥ ጻፉትና ጊዜ ወስዳችሁ ጸሎት አድርጉ። ኢየሱስንም ሰው በመሆኑ አመስግኑት። 

ጥያቄ፡- ሞትን ከሚፈራ አንድ ሰው ጋር ኢየሱስ እንዴት ሰው እንደ ሆነ፥ እንደ ሞተና እንደ ተነሣ፥ ከዚህ ፍርሃትም ነፃ ሊያወጣው እንደሚችል አብራችሁ | ተወያዩ። በዚህ ረገድ ያላችሁን ተሞክሮ ፍሬ አሳቡን በማስታወሻ ደብተራችሁ ውስጥ ጻፉ።

ምንጭ፡- “አስተምህሮ ክርስቶስና ደኅንነት”፤ ጽሑፍ፣ በዶ/ር ስቲቭ ስራውስ፤ ትርጉም በኃይሉ ልመንህ

Exit mobile version