በትምህርት አንድ ላይ፥ መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ሙሉ በሙሉና ፍጹም እግዚአብሔር መሆኑን እንደሚያስተምር ተገንዝበናል። እንደዚሁም መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ሙሉ በሙሉና ፍጹም ሰው መሆኑን ያስተምራል። ኢየሱስ በልደቱ ኃጢአት የሌለበትና ኃጢአትም ያላደረገ ንጹሕ ካመሆኑ በስተቀር ልክ እንደ እኛው ሰው ነበር። በዚህ ሳምንት በመቀጠል የክርስቶስን ስብእና በተመለከተ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ማብራሪያ የሚሰጡንን ትምህርቶች እናጠናለን።
የኢየሱስ ፍጹም ሰብአዊነት
ዛሬ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰብአዊነት የሚያስረዳንን ትምህርት ማጥናት እንጀምራለን። አዲስ ኪዳን ኢየሱስ በተፈጥሮ ኃጢአት የሌለበትና ኃጢአትም ያላደረገ ንጹሕ ከመሆኑ በስተቀር፥ ልክ እንደ እኛ ሰው እንደነበረ በግልጽ ያስተምረናል። እንግዲህ በዛሬውና በነገው ትምህርታችን ላይ ስለ ኢየሱስ ሰብአዊነት የቀረቡ ልዩ ልዩ የማረጋገጫ ትምህርቶችን እንማራለን። በዚህ ሳምንት ቆየት ብለን ደግሞ ስለ ክርስቶስ ሰብአዊነት የሚናገሩ ልዩ ምክንያቶችን የምንመለከት ሲሆን፥ እነርሱም በፈተና ወቅት ምንም ኃጢአት ስላለማድረጉና ከድንግል ስለ መወለዱ ናቸው።
1. ኢየሱስ ሰው እንዲሆን ለምን አስፈለገ?
1.1 ኢየሱስ ሰው እንዲሆን ያስፈለገበት ምክንያት የሰው ልጆች በሞት ላይ ድልን እንዲቀዳጁ ለማድረግ የዘላለም ሕይወትን
ለመስጠት ነው።
የኢየሱስ ፍጹም ሰብአዊነት አማኞች ሊያውቁት የሚገባቸው በጣም ጠቃሚ የሆነ ትምህርት ነው። ጌታ ኢየሱስ ሰው እንዲሆን ያስፈለገበት የተለያዩ ምክንያቶች ነበሩ።
ጥያቄ፡- ዕብራውያን 2፡14-15 እና 1ኛ ቆሮንቶስ ኢየሱስ ሰው እንዲሆን በምን ምክንያት አስፈለገ?
ዕብራውያን 2፡14-5 ያለው ክፍል ኢየሱስ ሰው እንዲሆን በምን ምክንያት እንዳስፈለገ ይነግረናል። ኢየሱስ ወደ እዚህ ምድር የመጣበት አንዱና ዋናው ምክንያት ሰይጣንና በሰው ልጆች ላይ የነበረውን የበላይነት ለመደምሰስ ነው። ከእነዚህ ካነበብናቸው ጥቅሶች እንደምንረዳው ሰይጣን በሰው ልጆች ላይ ከነበረው ሥልጣን የሞት ኃይል በእጁ መሆኑ አንደኛው ገጽታ ነው። ያ ማለት ሰይጣን ከእግዚአብሔር ፈቃድ ውጭ ሰዎችን ለመግደል ኃይል አለው፥ ወይም ኢየሱስ የሞተው ለሰይጣን ብድራቱን ሊከፍል ነው ማለት አይደለም። ሰይጣን በሞት ላይ ያለው ሥልጣን እኛ ኃጢአት እንድንሠራ መፈተን ነው። እኛ ደግሞ ኃጢአት ስናደርግ የእግዚአብሔርን ሕግ ስለምንተላለፍ በሥጋም በመንፈስም እንድንሞት ይፈረድብናል። ስለዚህ ከኃጢአታችን የተነሣ የሞትና የሰይጣን ባሪያዎች እንሆናለን። እንግዲህ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው እንዲሆን ያስፈለገበት
ምክንያት ሰይጣን በእኛ ላይ ያለውን ሥልጣን እንዲያስወግድ ነው። ስለዚህ ጌታ ኢየሱስ በሞቱ የሰይጣንን ኃይል ሽሮታል። እርሱም በሞተ ጊዜ እኛ ልንሞተው የሚገባንን ሞት ሞተልን። በዚህም ሞቱ የኃጢአታችንን ቅጣት ከፈለልን። በመሆኑም ክርስቲያኖች ስለ ኃጢአታቸው ዋጋ ስለተከፈለላቸው መፍራት የለባቸውም። ዘላለማዊ ሞት ይደርስብናል ብለው ሊሰጉ አይገባም። ኢየሱስ ሰው የሆነው ስለ ሰው ልጆች ኃጢአት በሞቱ ቅጣታቸውን ሊቀበልና ሊከፍል ነው። እርሱ ለው ባይሆን ኖሮ ሊሞትና የሰው ልጆችን ኃጢአት ሊከፍል ባልቻለም ነበር።
ጥያቄ፡- ብዙ ጊዜ ሰዎች በቀብር ላይ ተስፋ በቆረጠና በሚያስፈራ ሁኔታ ሊያለቅሱ ይታያሉ። የክርስቶስ ሰው መሆንና ከሞት መነሣት ፍርሃትንና የሞትን ተስፋ የማስቀረጥ ሁኔታ እንዴት አስወገደ?
1ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 5 እንደሚያስተምረን፥ ክርስቲያኖች ካሉን ታላላቅ ተስፋዎች መካከል ትንሣኤ ሙታን አንዱ ነው። ስለዚህ እያንዳንዱ አማኝ ከሞቱ በኋላ ከክርስቶስ ጋር ለዘላለም አብሮ ለመኖር በአዲስና ክብርን በተሞላ አካል ከሙታን ይነሣል። ታዲያ ክርስቲያኖች ይህን አስደናቂ የትንሣኤ ዋስትና እንዴት ተቀበሉት? በ1ኛ ቆሮንቶስ 15፡21 ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያኖች በትንሣኤ የሚነሡት ኢየሱስ ሰው ሆኖ በመሞቱ፥ ኋላም ከሙታን በመነሣቱ መሆኑን ያስረዳል። ስለዚህ ክርስቲያኖች በሞት ላይ ድልን እንዲቀዳጁ ክርስቶስ ራሱ መሞትና እንደ ሰው ከሙታን መነሣት ነበረበት። ማንኛውም ክርስቲያን ሞትን በፍርሃትና ተስፋ በመቁረጥ ስሜት ሊመለከተው አይገባም። ምክንያቱም ሁላችንም ስለ ትንሣኤ ሙታንና ስለ ዘላለም ሕይወት እርግጠኞች ነንና። ለክርስቲያኖች የተሰጠ ትንሣኤና ዘላለማዊ ሕይወት የተገኘው ኢየሱስ ልክ እንደ እኛው ሰው በመሆኑ ነው።
1.2 በድካማችን እንዲራራልንና በኃጢአት ስንፈተን እንዲረዳን ኢየሱስ ሰው መሆን ነበረበት።
ጥያቄ፡- ዕብራውያን 4፡5-16 ያሉትን ጥቅሶች አንብቡ። ሀ) ኢየሱስ ሰው እንዲሆን ለምን አስፈለገ? ለ) ኢየሱስ ክእኛ ከሰው ልጆች የሚለይበት አንድ መንገድ ምንድን ነው?
ጥያቄ፡- ያዕቆብ 1፡13 አንብቡ። ሊፈትን ወይም ሊፈተን የማይችል ማን ነው?
ዕብራውያን 4፡2-6 ያለው ክፍል ኢየሱስ ሰው እንዲሆን ያስፈለገበትን ሁለተኛ ምክንያት ያቀርባል። ይህ ክፍል ኢየሱስ ሰው በመሆን ራሱን በኃጢአት እንዲፈተን መፍቀዱን ይገልጻል። ይህን ክፍል ያቀረበልን ጸሐፊ ኢየሱስ ይፈተን እንጂ ምንም ዓይነት ኃጢአት ያልፈጸመ መሆኑን በጥንቃቄ ያስገነዝባል። ስለሆነም እርሱ በእርግጥ ቢፈተንም በአጋጠመው ፈተና ተሸንፎ ኃጢአት አልሠራም። በዚህ ሳምንት በሌላ ትምህርት ላይ መለስ ብለን ኢየሱስ ኃጢአትን እንዲያደርግ ስለደረሰበት ፈተና እንወያያለን። በዛሬው ትምህርታችን ላይ ማስተዋል ያለብን ኢየሱስ ሰው በመሆኑ ኃጢአትን እንዲፈጽም ስለ መፈተኑ ይሆናል። ያዕቆብ 1፡13 እንደሚያስረዳን፥ እግዚአብሔር ኃጢአትን እንዲፈጽም ሊፈተን አይችልም፡፡ ስሕተትንም የመፈጸም ባሕርይ የለውም። ይሁን እንጂ እግዚአብሔር የሰው ልጆችን ፈተና ለመገንዘብና የሚፈተኑትንም ሊረዳቸው ሲል ራሱ ሰው ሆነ። ስለዚህ ኢየሱስ ራሱ እግዚአብሔር ሆኖ ሳለ የእኛ ፈተና እንዲሰማውና እንዲፈተንም ሰው ሆነ፡ ጌታ ኢየሱስ ራሱ የተፈተነ በመሆኑ በምንፈተንበት ጊዜ ከጎናችን ሆኖ ያበረታታል።
ጥያቄ፡- ሀ) ዘወትር የምትፈተኑባቸውን ሁለት መንገዶች ጻፉ። ኢየሱስ የእኛ ፈተና የሚሰማው መሆኑን መገንዘባችን ምን ያህል ያጽናናናል?
ሰዎች ሁሉ በኢየሱስ ክርስቶስ ካመኑ በኋላም እንኳን ቢሆን ፈተናዎች ያጋጥሟቸዋል። ነገር ግን ኢየሱስ ራሱ በተፈተነ ጊዜ ፈተናውን መቋቋሙን በመረዳት ልንጽናና እንችላለን። ኢየሱስ ፈተናዎችን መቋቋም ምን ያህል አስቸጋሪ መሆኑን ያውቃል፤ ፈተናዎች በሚያጋጥሙን ጊዜ ለእግዚአብሔር የምንታዘዝበትን ኃይል ይሰጠናል።
1.3 ኢየሱስ እግዚአብሔርን ለእኛ ለመግለጽ ሰው መሆን ነበረበት።
ጥያቄ፡- ዕብራውያን 1፡1-3 አንብቡ። የእግዚአብሔር ዋና ነጸብራቅ (ምሳሌ) ማን ነበር?
ባለፈው ሳምንት የክርስቶስ የመለኮቱ መገለጫ ማረጋገጫ የሆነውን ዕብራውያን 1፡1-3 አጥንተን ነበር። ይህ ክፍል የኢየሱስ ሰብእዊነት በምን ምክንያት እንዳስፈለገ እንድንገነዘብ ረድቶናል። ዕብራውያን 1፡1-3 እርሱ ፍጹም የእግዚአብሔር ነጸብራቅ መሆኑን ይነግረናል። እግዚአብሔር ራሱን ከሰው ልጆች ጋር ሊያስተዋውቅበት የፈለገው ዋናው መንገድ ራሱን ሰው ማድረግ ነበር። እግዚአብሔር ራሱን ሰው በማድረጉ ብቻ ሰዎች በሚገባቸው መንገድ ሊያውቁትና ሊገነዘቡት ቻሉ። ኢየሱስ እግዚአብሔርን ለሰዎች ሊገልጥ የሚችለው ራሱ ሰው በመሆን ስለነበረ የእርሱ ሰብአዊነት በጣም አስፈላጊ ነበር። እኛ እግዚአብሔርን ልናውቀው የምንችልበት ብቸኛ መንገድ የኢየሱስን ሕይወት በማጥናት ነው።
የኢየሱስ ሰብአዊነት ስለምን አስፈላጊ ሆነ? ኢየሱስ ከኃጢአታችንና የኃጢአታችን ቅጣት ከሆነው ከሞት ሊያድነን የሚችለው ሰው በመሆን ብቻ ስለነበረ ነው። ኢየሱስ ኃጢአትን እንድናደርግ በምንፈተንበት ጊዜ ከጎናችን ሆኖ ሊያበረታን የሚችለው ሰው ሲሆን ብቻ ነው። ኢየሱስ እግዚአብሔርን በሚገባ ሊገልጥልን የሚችለው ሰው በመሆን ብቻ ነው፡፡
ምንጭ፡- “አስተምህሮ ክርስቶስና ደኅንነት”፤ ጽሑፍ፣ በዶ/ር ስቲቭ ስራውስ፤ ትርጉም በኃይሉ ልመንህ
