Site icon

ኢየሱስ ፍጹም ሰው መሆኑን እንዴት እናውቃለን? 

2.1 ኢየሱስ ሰብአዊ አካል ነበረው። 

ኢየሱስ ፍጹም ሰው እንደነበረ እንዴት ልናውቅ እንችላለን? በመጀመሪያ፥ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስተምረን ኢየሱስ ሰብአዊ አካል ነበረው። 

ጥያቄ፡- ዮሐንስ 1፡1 አንብቡ። ኢየሱስ ሰው ለመሆኑ ዮሐንስ ምን ማረጋገጥ ይሰጠናል። 

ዮሐንስ በመጀመሪያው መልእክቱ በቁሳዊ ዓለም ውስጥ የሚገኝ ማንኛውም ነገር ክፉ ነው ብለው ያስተምሩ የነበሩትን ሐሰተኛ ሰዎች እየተቃወመ ነበር። ይህን የሐሰት ትምህርት ያስተምሩ የነበሩ ሰዎች በቁሳዊ ዓለም ውስጥ የሚገኝ ሁሉ ክፉ ነው ብለው ያምኑ ስለነበርና ኢየሱስም ፍጹም ስለነበር እውነተኛ ሰብአዊ አካል አልነበረውም ብለው ያምኑ ነበር። እነዚህ ሐሰተኞች መምህራን ኢየሱስ የነበረው ሰብአዊ አካል የመሰለ እንጂ እውነተኛው የሰው አካል አልነበረም ይሉ ነበር። ነገር ግን ሐዋርያው ዮሐንስ ለአንባቢያኑ እንደሚያስረዳው ከሆነ፡ የኢየሱስ አካል እውነተኛው የሰው አካል እንደነበረ ነው። እርሱም አይቶታል፤ ደግሞም ዳስሶታል። የኢየሱስ አካል እንደ ማንኛውም የሰው አካል እውነተኛ ነው ሲል ያረጋግጣል። 

ጥያቄ፡- ሉቃስ 2፡1-7 ድረስ እንብቡ። ኢየሱስ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም | እንዴት ባለ አኳኋን ተገለጠ? 

የኢየሱስን ሰብአዊነት ከሚያጎሉት ነገሮች ዋነኛው ልደቱ ነበር። በዓለም ላይ እንደ አንድ ጎልማሳ ሰው ሆኖ አልተገለጠም። ማንኛውም ሰው በሚወለድበት አኳኋን ተወለደ። በእርግጥ የኢየሱስ ልደት በዓለም ከታየው ልደት ሁሉ ዝቅ ባለና በተዋረደ ስፍራ ውስጥ ነበር። በሴት ወይም በሆስፒታል ውስጥ በመወለድ ፈንታ፥ በእንስሳት ማደሪያ ግርግም ውስጥ ተወለደ። ወንጌላዊው ሉቃስ ስለ ኢየሱስ ልደት ሰፋ አድርጎ በዝርዝር ባይጽፍም፥ «የመውለጃዋ ወራት ደረሰ» ብሎ ሊል፥ ይህ አባባሉ ማርያም ስትወልድ የሚሰማት የምጥ ስሜት የተለመደው ዓይነት እንደሆነና እንደ ማንኛውም ወላድ አምጣ እንደ ወለደች መናገሩ ነው። በዚህ ሳምንት መጨረሻ ላይ በኢየሱስ ልደት ዙሪያ ስለታዩት ታምራቶች እንወያያለን። የእርሱ ልደት ልዩ መሆኑ ግልጽ ነው። ነገር ግን ደግሞ ፍጹም ሰብአዊም ነው። 

ጥያቄ፡- ሉቃስ 2፡52 አንብቡ። ኢየሱስ እያደገ ሲመጣ በአካሉ ላይ ምን ተከሰተ? 

ወንጌል ስለ ኢየሱስ ልጅነት ሁኔታ ብዙም አይነግረንም። ስለ ልደቱና ዕድሜው አሥራ ሁለት ዓመት በሆነው ጊዜ ወደ ቤተ መቅደስ ስለ መሄዱ ከሚናገረው ሌላ፥ ስለ ኢየሱስ የልጅነት ጊዜ የሚያወሳው ይሄኛው ጥቅስ ብቻ ነው። በዚህ ሳምንት ወደዚህ ጥቅስ ደጋግመን በመመለስ እናጠናዋለን። ለዛሬው፥ «ኢየሱስ በቁመት ያድግ ነበር።» የሚለውን አስተውሉ። እንዲህ ማለት የኢየሱስ አካል ከሌላው ሰው ባልተለየ አኳኋን የእድገት ሂደቱን ጠብቆ ያድግ ነበር ማለት ነው። የኢየሱስ አካል እንደ ማንኛውም ሰው አካል ደረጃ ውን ጠብቆ ያድግ ነበር። 

ጥያቄ፡- ማቴዎስ 4፡2፤ ዮሐንስ 4፡6-7፤ ዮሐንስ 19፡28 እና ዮሐንስ 19፡34 አንብቡ። የኢየሱስ አካል የየትኛቹ ሰብአዊ ድካሞች ተሞክር ነበረው? 

የኢየሱስን አካል ያጋጠመው ድካም ልክ እኛንም የሚያጋጥመን ወይም የሚሰማን ድካም ዓይነት ነው። ኢየሱስ ለተወሰነ ጊዜ ሳይበላ ቢቆይ ይርበው ነበር። ለተወሰነ ጊዜ ውኃ ሳይጠጣ ሲቆይ ይጠማው ነበር። እንደዚሁም ለብዙ ሰዓታት በእግሩ ሲሄድ ይደክመው ነበር። እንዲሁም ሰውነቱ ከተመታ፥ ከተወጋና በመስቀል ላይ በምስማር የተቸነከረ በኋላ ሞተ። ልክ ማንኛውም ሰው ሲሞት እንደሚሆነው ሁሉ ኢየሱስም በሞተ ጊዜ የልቡ ምት ቆመ፤ ሳምባውም መተንፈሱን ተወ። እነዚህ ሰብአዊ ድካሞች በኢየሱስ ዓይነ ሕሊና የታዩ ስሜቶች አይደሉም። ከላይ የተጠቀሱት ጥቅሶች በግልጽ እንደሚያስረዱት እነዚህ ሰብአዊ ፍላጎቶች እንደ ማንኛውም ሰው እርሱንም እስፈልገውታል። ኢየሱስ ልክ እንደ እኛው አካል ነበረው። 

2.2 ኢየሱስ ሰብአዊ ነፍስና ሰብአዊ መንፈስ ነበረው። 

ኢየሱስ ሰብአዊ አካል ብቻ አልነበረውም፤ ሰብአዊ ነፍስና መንፈስም ነበረው። ባለፈው ሳምንት ለመመልከት እንደሞከርነው ኢየሱስ ራሱ እግዚአብሔር ቢሆንም እንኳ፥ እንደ ሰው ከእግዚአብሔርና ከሌሎች ሰዎች ጋር ግንኙነት ነበረው። ኢየሱስ እንደ ማንኛውም ሰው ማኅበራዊና መንፈሳዊ ሕይወት ነበረው። 

ጥያቄ፡- ሀ) ማቴዎስ 26፡38 አንብቡ። ሀ) ኢየሱስ እስከ ሞት ድረስ ያሳዘነኝ ምንድን ነው አለ? ለ) ሉቃስ 23፡46 አንብቡ። ኢየሱስ በአባቱ እጅ ያስረከበው ምንድን ነው? 

አንዳንድ ሰዎች ኢየሱስ በውስጥ እግዚአብሔር እንደሆነና በውጭ ሰው እንደ ሆነ አድርገው ይገምታሉ። ነገር ግን ኢየሱስ ከሰብአዊ አካል የበለጠ ነገርም ነበረው። ይኸውም ሰብአዊ ነፍስና መንፈስ ነበረው። ያለጥርጥር ሙሉ በሙሉ እግዚአብሔር ነበር። ነገር ግን ሰብአዊ ሥነልቡናና ስሜቶችም ነበሩት። ሰዎች ሁሉ እንደሚያደርጉት እርሱም ከሰዎች ጋር ግንኙነት ነበረው። ልክ ሰዎች እንደሚያደርጉት ዓይነት ግንኙነት እርሱም ከእግዚአብሔር ጋር ነበረው። በማቴዎስ 26፡38 ላይ ኢየሱስ ነፍሱ በጣም መጨነቋን ይገልጻል። ነገ ስለ ኢየሱስ ስሜቶች ሰፋ አድርገን እናጠናለን። ለዛሬው ኢየሱስ ሰብአዊ ነፍስ አለኝ ማለቱን አስተውሉ። በሉቃስ 23፡46 ውስጥ ሊሞት ሲል ነፍሱን አሳልፎ ለእግዚአብሔር አብ ስለማስረከቡ ይናገራል። ኢየሱስ ሲሞት ለእግዚአብሔር አብ ያስረከበው ሰብአዊ ነፍስ ነበረው። የኢየሱስ ሰብአዊነት በውጫዊው አካል ብቻ አልነበረም። በውስጣዊውም ሰብአዊ ነበር። 

ጥያቄ፡- ሉቃስ 252 እንደገና አንብቡ። ኢየሱስ ያደገው በቁመት ብቻ አልነበረም። ከዚህ ሌላ በምን መንገድ ያድግ ነበር? ኢየሱስ ከማን ፊት በሞገስ አደገ? 

ጥያቄ፡- ሀ) ማርቆስ 9፡21 አንብቡ። ኢየሱስ በምን ምክንያት ይህን ጥያቄ ጠየቀ? ለ) ማርቆስ 13።2 አንብቡ። ኢየሱስ ራሱ አላውቅም ያለው ምንን ነበር? 

ጥያቄ፡- ሉቃስ 4፡16 እና ሉቃስ 6፡12 እንብቡ። ኢየሱስ ከእግዚአብሔር አብ ጋር የነበረውን አንድነት ለማጠንከር ምን አደረገ? 

ሉቃስ 2፡52 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እጅግ በጣም አስደናቂ ከሆኑት ጥቅሶች ውስጥ አንዱ ነው። በዚህ ሕይወት እያለን ሙሉ በሙሉ የማንገነዘበው ጥቅስ ነው። ኢየሱስ በቁመት እንዴት ያድግ እንደነበረ መመልከት ቀላል ነው። እንደ ሕፃን ተወልዶ ኋላም እካሉ ስለማደጉ መረዳት አይከብደንም። ነገር ግን ይህ ጥቅስ ከኢየሱስ አካላዊ እድገት ስለሚበልጥ ነገር ይናገራል። እርሱ «በጥበብም» ያድግ ነበር ይላል። ባለፈው ሳምንት እንደተመለከትነው፥ ኢየሱስ እንደ እግዚአብሔር ሁሉን ያውቃል። ሆኖም ኢየሱስ እንደ ሰው በጥበብ እያደገ ልዩ ልዩ እውቀቶችን ይቀስም ነበር። ወላጆችና መምህራን ልጆችን በጊዜያቸው እንደሚያስተምሩ ሁሉ፥ ወላጆቹና መምህራኑ ኢየሱስን አስተማሩት። አንዳንድ የማያውቃቸውን ነገሮች ተማረ። በማርቆስ 13፡32 በምድር ላይ ሳለ የሚመለስበትን ጊዜ እንደማያውቅ ተናግሮአል። አብ ብቻ ያውቃል። እንደ እግዚአብሔር ኢየሱስ በእርግጥ የሚመላስበትን ጊዜ ያውቅ ነበር። ነገር ግን እንደ ሰው እርሱ ራሱ ያንን ጊዜ አያውቅም። በማርቆስ 9፡21 ላይ እንደ ሰው መረጃ ለማግኘት ይጠይቃል። ልጁ በአጋንንት ከተያዘ ምን ያህል ጊዜው እንደሆነ ለማወቅ አባትዬውን ጠይቋል። እንደ እግዚአብሔርነቱ ያ ልጅ በአጋንንት መቼ እንደ ተያዘ በእርግጥ ያውቃል። እንደ ሰው ግን መረጃ ለማግኘት ጥያቄ የሚያቀርብ ይመስላል። በሚመጡት ሳምንታት፥ ኢየሱስ በአንድ ጊዜ ሙሉ በሙሉ እንዴት እግዚአብሔር፥ እንዲሁም እንዴት ሰው እንደሚሆን በቅርብ እንመረምራለን። ይህ አንዳንድ ጊዜ «የተሠግዎ (ሥጋ የመልበስ) ምሥጢር» ተብሎ ይጠራል። ለዛሬው ኢየሱስ ያለ ኃጢአት ከመሆኑ በስተቀር፥ ልክ እንደ እኛው ሰው እንደ ነበረ እንመለከታለን። በጥበብም እንኳ አድጓል። 

ሉቃስ 2፡52 ኢየሱስ በጥበብና በቁመት ብቻ ያድግ ነበር አላለም፤ በእግዚአብሔርና በሰው ፊት በሞገስ ያድግ ነበር የሚል ጨምሮበታል። ኢየሱስ ከሌሎችም ጋር በነበረው ግንኙነት አደገ። ወዳጆችንም አፍርቶ ነበር። ማኅበራዊ ግንኙነትንም አዳብሯል። ከሰዎች ጋር የነበረውን ግንኙነት እያዳበረ በሄደ ቁጥር ሰዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ በይበልጥ ይወዱት ጀመር። ነገር ግን ኢየሱስ ከሰዎች ጋር በነበረው ግንኙነት ማደጉ ብቻ ሳይሆን ከእግዚአብሔር ጋር የነበረውን ግንኙነትም እያዳበረ አድጓል። ይህ ለመቀበልም ሆነ ለመገንዘብ አስቸጋሪው የኢየሱስ ስብእና ገጽታ ነው። ኢየሱስ እንደ እግዚአብሔርነቱ ከእግዚአብሔር አብ ጋር ባለው ግንኙነት እንዴት ሊያድግ ይችላል? እንደምታስታውሱት ኢየሱስ ኃጢአትን አላደረገም፣ ስለዚህ ከኃጢአተኝነት ወደ ታዛዥነት ለማደግ አይችልም። እርሱ እንደ ሰው ሕይወቱን የጀመረው ከእግዚአብሔር ጋር በቅርበት ሆኖ ነው። በመላ የሕይወት ዘመኑም በበለጠ ቅርበትን መሥርቷል። በሉቃስ 4፡16 እና በሉቃስ 6፡12 ውስጥ ኢየሱስ እግዚአብሔር አብን ማምለኩንና ወደ እርሱም መጸለዩን እናውቃለን። ምንም እንኳን እርሱ ራሱ እግዚአብሔር ቢሆንም፥ እንደ ሰው በጸሎት ከእግዚአብሔር አብ ጋር ይነጋገር ነበር። እንደ ሰውም ከእግዚአብሔር ጋር ቅርበት ኖሮት አደገ። በእግዚአብሔር ፊትም ተወዳጅ ሆኖ አደገ። 

ኢየሱስ ክርስቶስ ሙሉ በሙሉ ሰው ነበር። የሰው አካልም ነበረው። የሰው ነፍስና መንፈስ ነበረው። ከሰዎች ጋርም መልካም የማኅበራዊ ግንኙነት ነበረው። እንደዚሁም ሰብአዊ አእምሮና ሥነልቡና ነበረው። ነገ ደግሞ ሰብአዊ ስሜቶች እንደነበሩት በሰፊው እናጠናለን። ሌሎች ሰዎች ሁሉ ኃጢአት እንደሚያደርጉ፥ ኢየሱስ በፍጹም ኃጢአት አላደረገም። በተረፈ በሌላው ሁሉ ልክ እንደ እኛ ሰው ነበር። 

በኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ሰዎች ኢየሱስ ሰው ነበር የሚለውን ለመቀበል ይከብዳቸዋል። እርሱ ግን ከኃጢአት በስተቀር እንደ እኛው ሰው ነበር። ምናልባት ኢየሱስ ሰውም ነው ብሎ መናገር አምላክነቱን ያሳንሰዋል ብለው ሰግተው ይሆናል። ከሚመጣው ሳምንት ጀምሮ በተሠግዎ አማካኝነት ስለተመሠረተው የኢየሱስ ሰብአዊና መለኮታዊ ጥምረት እንወያያለን። ቢሆንም፥ ይህን ውይይት ከመጀመራችን በፊት ኢየሱስ ፍጹም ሰውና ፍጹም አምላክ መሆኑን መገንዘብ ጠቃሚ ነው። እርሱ ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ መሆኑን መረዳት ያስቸግረናል። መጽሐፍ ቅዱስ ግን ሁለቱም ትክክል መሆናቸውን በግልጽ ያስረዳል። 

ጥያቄ፡- ኢየሱስ ኃጢአት ካለማድረጉ በስተቀር ልክ እንደ እኛው ሰው ስለሆነ የምናመሰግነው እንዴት ባለ መንገድ ነው? በዚህ ረገድ እንድታመሰግኑት የሚያደርጓችሁን ምክንያቶች በማስታወሻ ደብተሮቻችሁ ላይ ጻፉ። ኢየሱስ እንደ እኛ ሰው በመሆኑ እርሱን በጸሎት የምታመሰግኑበት ጊዜ ይኑራችሁ። 

ጥያቄ፡- ሀ) የምታውቋቸው አንዳንድ ሰዎች ኢየሱስ ሰው የመሆኑን ነገር የማይቀበሉበትን አንዳንድ ምክንያቶች ጻፉ። ለ) ኢየሱስ ሙሉ በሙሉ ሰው መሆኑን ባናምን እንዴት ያሉ አደገኛ የሆኑ የሐሰት ትምህርቶች ይከሰታሉ? አንዳንድ እሳቦችን በማስታወሻ ደብተሮቻችሁ ላይ ጻፉ። 

ኢየሱስ በእኛ ላይ የደረሰውን ሁሉ ለመቀበልና ስሜታችንንም ለመጋራት ልክ እንደ እኛው ሰው በመሆኑ ልናመሰግነው ይገባል። በዚሁ አኳኋን እርሱ ስሜታችን ይገባዋል፥ ተስፋ መቁረጣችንንም ይረዳል፥ እንደዚሁም ሥጋዊ ድካማችን ይገነዘባል፥ ከሌሎችም ጋር ስላሉን ግንኙነቶች ይረዳል፥ እንደዚሁም የሚደርሱብንን ፈተናዎችም ይገነዘባል። ምክንያቱም ኢየሱስ ሰው በመሆኑ እግዚአብሔርን ለእኛ ይገልጣል፤ እንደዚሁም ሌሎች ሰዎችም እግዚአብሔርን እንዲያውቁትና ከእግዚአብሔር ጋር ቅርበት እንዲኖራቸው ሁኔታዎችን ያመቻቻል። ኢየሱስ ሰው ሳይሆን ኖሮ፥ ሰዎች ወደ እግዚአብሔር የሚመጡበት መንገድ ክፍት አይሆንላቸውም ነበር። ሰዎችም እግዚአብሔርን ባለማወቅ ጨለማ ለዘላለም በጠፉ ነበር። ምክንያቱም ኢየሱስ ሰው ስለሆነ ሰዎች እግዚአብሔርን ሊያውቁት ቻሉ።

ምንጭ፡- “አስተምህሮ ክርስቶስና ደኅንነት”፤ ጽሑፍ፣ በዶ/ር ስቲቭ ስራውስ፤ ትርጉም በኃይሉ ልመንህ

Exit mobile version