Site icon

በጥንታዊቷ ቤተ ክርስቲያን የተሠገዎ ታሪክ፣ ኖስቲካዊነት

ኢቢዮናውያን ተነሥተው ኢየሱስ ሰው ብቻ ነበር ብለው ባስተማሩበት በዚያው ጊዜ ከኢቢዮናውያን ለየት ያለ ትምህርት ይዘው የተነሡት ደግሞ ኖስቲካውያን ነበሩ። እነዚህ ኖስቲካውያን በትምህርታቸው ውስጥ በተፈጥሮ የተገኘውና ማንኛውም አካላዊ ነገር ሁሉ ክፉ ነው ብለው። ያምኑ ነበር። ማንኛውም ተፈጥሮአዊ ነገር ወይም ቁስ አካል ክፉ በመሆኑ ምክንያት ኢየሱስ ሰው መሆኑ እውነት ሊሆን አይችልም ብለው ያስተምሩ ነበር። መንፈስ ብቻ መልካም ነው ብለው ያምኑ ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ እውነተኛ የሰው አካል ያለው እውነተኛ ሰው ሳይሆን እውነተኛ የሰው አካል ያለው መስሎ የተገለጠ ነው ይሉ ነበር። በእርግጥ ኢየሱስን ድንግል ማርያም አላረገዘችውም፥ ነገር ግን በውስጧ ብቻ አለፈ ብለው ያምኑ ነበር። እንደዚሁም ኖስቲካውያን ወደ ደኅንነት ሊደረስ የሚቻለው በእውቀት ነው ብለው የሚያምኑ ነበሩ። ሰው የበለጠ መንፈሳዊ ምሥጢራትን ባወቀ መጠን ክፉ ከሆነው ከቁስ አካላዊ ዓለም ይርቅና መልካም ወደሆነው መንፈሳዊ ዓለም ይቀርባል ባይ ናቸው። የጥንት ቤተ ክርስቲያን መሪዎች በእነዚህ በኖስቲካውያን ትምህርት ውስጥ ብዙ ጉድለቶችን ሊመለከቱ ችለዋል። – በመጀመሪያ፥ ኢየሱስ በድንግል ማርያም ተፀንሶ የተወለደ፥ እውነተኛ ሰው መሆኑን ይክዳሉ። ሁለተኛ፥ ቁስ አካላዊው ዓለም በራሱና ከራሱ ክፉ ነው ይላሉ። በመጨረሻም፥ ደኅንነት በመሠረቱ የሚገኘው ጥልቅ በሆነ መንፈሳዊ እውቀት ነው ይሉ ነበር። ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን ኖስቲካውያንን በዚህ ሐሳዊ ትምህርታቸው የተነሣ አውግዛቸዋለች፤ ነገር ግን ትምህርታቸው ቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስን የበለጠ መርምራ ወደ ትክክለኛው ግንዛቤ እንድትደርስ በማድረግ ረገድ ረድቷታል። በመጀመሪያ፥ ኢየሱስ በሰው ተመስሎ ብቻ አልታየም፤ ኃጢአት አላደረገም እንጂ በማንኛውም ሁኔታ እርግጠኛ ሰው ነበር። ሁለተኛ፥ ቁስ አካላዊው ዓለም በራሱ ክፉ ኣይደለም። እግዚአብሔር መልካም አድርጎ ፈጥሮታል። ቁስ አካላዊውም ሆነ መንፈሳዊው ዓለም ከኃጢኣት የተነሣ ክፉዎች ናቸው። ሰዎች ኃጢአትን ወደ ቁስ አካላዊው ዓለም ሲያመጡ ብቻ ክፉ ይሆናል። በመጨረሻም፥ ደኅንነት መንፈሳዊ ምሥጢርን ከመገንዘብ በላይ ነው። ስለሆነም ደኅንነት ማለት በክርስቶስ አምኖ በልብ መለወጥ ነው። ደኅንነት ክርስቶስ በመስቀል ላይ በፈጸመልን ተግባር ላይና ፈቃዳችንን ለእግዚአብሔር አሳልፈን በመስጠታችን ላይ የተመሠረተ ነው። 

ጥያቄ፡- ሀ) ኖስቲካውያን ስለ ኢየሱስ ማንነት የሚያምኑት ምን ነበር? ለ) ኖስቲካውያን ስለዚህ ስለተፈጠረው ቁሳዊ ዓለም ምን ያምኑ ነበር? ሐ) ኖስቲካውያን ሰው በምን መንገድ ደኅንነትን ያገኛል ይላሉ? መ) ኖስቲካውያን ከአቢዮናውያን እንዴት ይለያሉ? ሠ) ከእነርሱ የሐሰት ትምህርት የተነሣ ስለ ኢየሱስ ምን ግንዛቤ እየጠራ ግልጽ እየሆነ ሄደ? 

ጥያቄ፡- ሀ) ከኃጢአት በስተቀር፥ ኢየሱስ ሙሉ በሙሉ ሰው ነው የሚለውን እውነታ በመቀበል ረገድ ችግር ያለባቸው የምታውቃቸው ሰዎች ኣሉ? ለ) ስለ እነርሱ የምታውቁትን ጻፉ። ሐህ ክርስቶስ በእውነት ሰው መሆኑን የሚያስተምሩ የትኞቹን ክፍለ ምንባቦች አቅርባችሁ አብራችኋቸው ትወያያላችሁ? 

ጥያቄ፡- ሀ) በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ውስጥ ከሁሉ የበለጠው ነገር መንፈሳዊ ምሥጢራትን መገንዘብ ነው ብለው የሚያምኑ፥ የምታውቁዋቸው ሰዎች አሉ? ለ) ስለ እነዚህ ሰዎች የምታውቁትን ጻፉ። ሐ) በዓለም ያለው ቁስ አካል ሁሉ ክፉ ነው ብለው የሚያምኑ የምታውቋቸው ሰዎች አሉ? ስለ እነዚህ ስዎች ያላችሁን ተሞክሮ ጻፉ። 

ኖስቲካውያን ይህ ቁሳዊ ዓለም ክፉ በመሆኑ ኢየሱስ እውነተኛ ሰው ሊሆን አይችልም ብለው አመኑ። እንደዚሁም ወደ ደኅንነት የሚያደርሰው መንገድ በመንፈሳዊ ምሥጢራት ግንዛቤ ነው አሉ። ዛሬም በኅብረተሰቦቻችን ውስጥ የዚህ ዓይነት ተመሳሳይ እምነት ያላቸው ሰዎች ኣሉ። እንዳንድ ክርስቲያኖች መሆናቸውን እየተናገሩ ኢየሱስ እውነተኛ ስብእና እንዳለው አያምኑም። እነዚህ ወገኖች ኢየሱስ ሥጋ የለበሰ ኣምላክ ነወ ቢሉም፥ እንደ እኛ ሰው እንደ ነበረና ሰብአዊ ነፍስና ሰብአዊ መንፈስ እንደ ነበረው ይክዳሉ። ነገር ግን በዮሐንስ ምዕራፍ 1፥ በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 2፥ እንደዚሁም በዕብራውያን ምዕራፍ 2 እና በሌሎችም ክፍለ ምንባቦች ላይ እንደተነዘብነው ኢየሱስ ከኃጢአት በስተቀር እንደ እኛው ሰው መሆኑን ተምረናል። እኛን ለማዳን ሲል ሰው መሆን እንዳስፈለገውም ተመልክተናል። ራሳቸውን ክርስቲያኖች ብለው የሚበሩ በኅብረተሰቦቻችን መካከል የሚገኙ አንዳንድ ሰዎች ጥልቅ የመንፈሳዊ ምሥጢራት ግንዛቤ ካላቸውና መንፈሳዊ ቃላትንም ካወቁ መንፈሳዊ ኃይልና ደኅንነትን የሚያገኙ ይመስላቸዋል። ነገር ግን በሚቀጥለው ትምህርታችን ላይ ደኅንነት በዕውቀት ወይም በልዩ ግንዛቤ የሚገኝ አለመሆኑን እንማራለን። ደኅንነት ፈቃድንና ልብን በመለወጥ ይመጣል።

ምንጭ፡- “አስተምህሮ ክርስቶስና ደኅንነት”፤ ጽሑፍ፣ በዶ/ር ስቲቭ ስራውስ፤ ትርጉም በኃይሉ ልመንህ

Exit mobile version