Site icon

የእግዚአብሔር ቅዱስነት የኃጢአትን መሥዋዕት ይሻል፡- የብሉይ ኪዳን ምሳሌ 

የኃጢአት ይቅርታ ለማስገኘት አንድ ሰው እንዲሞት ለምን አስፈለገ? ብዙ ሙስሊሞች፥ ያላንዳች መሥዋዕት አቅርቦት እግዚአብሔር ኃጢአትን ይቅር ይላል ብለው ያምናሉ። እግዚአብሔር ሉዓላዊ ሥልጣን ያለውና የዓለም ገዥ በመሆኑ ኃጢአታችሁ ይቅር ተብሏል ብሎ በቀላሉ ለመናገር ኃይልም ሥልጣንም አለው ይላሉ። ስለዚህ ስለ ኃጢአት ቅጣት ሊከፈል አያስፈልግም፥ ምክንያቱም እግዚአብሔር ኃጢአት ይቅርታ እንዲያገኝ በቀላሉ ሊያዝ ይችላል ብለው ያምናሉ። ሌሎች ሰዎች ደግሞ ስለሌላው ኃጢአት ሌላው ሰው መሞት አለበት ብሎ መናገር ስሕተት ነው ባይ ናቸው። አንዱ ሰው ሌላውን ቢበድለው፥ ለዚያ ኃጢአት ካሣ ለመክፈል ሌላው መሞት አይገባውም ይላሉ። ስለዚህ የተበደለው ሰው ለበዳዩ ሰው በቀላሉ ይቅርታ ሊያደርግለት ይችላል ይላሉ። ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ብሉ በመስቀል ላይ ስለ መሞቱ የምናምነው በምን ምክንያት ነው? 

ጥያቄ፡- ዘሌዋውያን 11፡45፤ 20፡26 አንብቡ። ሀ) በእነዚህ ጥቅሶች አማካይነት፥ እግዚአብሔር ራሱን በምን አኳኋን ይገልጻል? ለ) እግዚአብሔር በዚህ አኳኋን ሲገልጽ የእግዚአብሔር ሰዎችስ ምን ሊያደርጉ ይገባቸዋል? 

ጥያቄ፡- ኢሳይያስ 6፡1፥ 5-7 አንብቡ። ሀ) በኢሳይያስ ራእይ ውስጥ እግዚአብሔር በምን ሁኔታ ተገለጸ? ለ) ኢሳይያስ ስለታየው የእዚአብሐር ራእይ ስሜቱና አስተያየቱ እንዴት ነበር? ሐ) መልአኩ ለኢሳይያስ ምን አደረገ? መ) የመልአኩ ተግባር ውጤት ምን ነበር? 

ጥያቄ፡– ዘፀአት 3፡5 አንብቡ። ሙሴ አድርግና አታድርግ ተብሉ የታዘዘው ምን ነበር? 

ጥያቄ፡- ዘሌዋውያን 10፡1-3 አንብቡ። ሀ) ናጻብና አብዩድ በምን ምክንያት ሞቱ? ለ) ዘሌዋውያን 16፡2 አንብቡ። የአሮን ሁለቱ ወንዶች ልጆቹ ተራና ያልተቀደሰ እሳት ይዘው በእግዚአብሔር ፊት በመቅረባቸው ተቀስፈው ከሞቱ በኋላ፥ እግዚአብሔር አሮንን ምን አዘዘው? 

ጥያቄ፡- 1ኛ ዮሐንስ 1፡5ና ዕብራውያን 12፡17 አንብቡ። በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ እግዚአብሔር በምን መልክ ተገልግል? 

ጥያቄ፡- ዘሌዋውያን 18፡25 አንብቡ። ሀ) እግዚአብሔር ከነዓናውያንን በምን ምክንያት ከምድራቸው አስወጥቶ አባረራቸው? እግዚአብሔር ከነዓናውያንን ከምድሩ አስወጥቶ እንዴት እንዳባረራቸው ጥቅሱ በምን አኳኋን ይገልጸዋል? ለ) ዘሌዋውያን 20፡22-23 አንብቡ። እስራኤላውያን የከነዓናውያንን ተግባር ቢከተሉ ኖሮ ምን ይደርስባቸው ነበር? 

ክርስቶስ ለእኛ ኃጢአት ሲል በምን ምክንያት እንደ ሞተ ለመገንዘብ፥ በመጀመሪያ የእግዚአብሔርን ቅድስናና የሰውን ልጅ ኃጢአተኝነት ማወቅ ያሻል፡ እግዚአብሔር «ቅዱስ» ነው በምንልበት ጊዜ፥ እርሱ ከማንኛውም ተራ ከሆነ ነገር ሁሉ፥ በተለይም ከኃጢአት ፈጽሞ የተለየ ነው ማለታችን ነው። ዘሌዋውያን 1፡45ና 20፡26 እንደሚያስታውሰን እግዚአብሔር ቅዱስና ከኃጢአት የነፃ ፍጹም እንደሆነ ሁሉ፣ ሕዝቡም ቅዱስና ከኃጢአትም ንጹሐን እንዲሆኑ መፈለጉን ይናገራል። የእግዚአብሔር ሕዝብ ራሳቸው ቅዱስና ከኃጢአትም የተለዩ ካልሆኑ በስተቀር በእርሱ ጸንተው ሊቆዩ አይችሉም። 

እግዚአብሔር ቅዱስ ስለ መሆኑ፥ ከኃጢአት ምን ያህል የራቀ እንደሆነና ኃጢአት በእርሱ ዘንድ የረከሰ ላለ መሆኑ፥ መጽሐፍ ቅዱስ እፍታቶ ለእኛ ለመግለጽ በተለያዩ ምስሎች ይጠቀማል። በመጀመሪያ፣ መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ከፍጥረታቱ ሁሉ በላይ ከፍ ብሎ እንደሚገኝ ይናገራል። ኢሳይያስ ስለ እግዚአብሔር ዙፋን ሊገልጽ፥ ከፍ ከፍ ያለና ከሁሉም በላይ የከበረ የላቀ መሆኑን ያስረዳል። እግዚአብሔር ምን ያህል ከፍ ያለና ቅዱስ እንደሆነ በተመለከተ ጊዜ በመጀመሪያ ያረጋገጠው እርሱ ምን ያህል ኃጢአተኛ እንደ ነበረ ነው። ከዚያም ኢሳይያስ በእግዚአብሔር ፊት ጸንተ ሊቆም ይችል ዘንድ መልአኩ ከኃጢአቱ ሊያነጻው ብሎ በምድጃ ው ላይ ከነበረው ፍም በጉጠት ወስዶ ከንፈሩን ዳሰሰው። ከንፈሮቹ በእሳት መዳሰሳቸው ብቻ ኢሳይያስን ከኃጢአቱ ሊያጠራው አይችልም ነበር። ስለዚህ በእሳት የተዳሰሰው የኢሳይያስ ከንፈር ኃጢአት በእግዚአብሔር ፊት ሊኖር እንደማይችልና ኃጢአተኞች ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ከመቅረባቸው አስቀድሞ ከኃጢአታቸው መንጻት እንዳለባቸው የሚያስገነዝብ ሥዕላዊ መግለጫ ነው። እንዲሁም ሙሴ ይቃጠል የነበረውን ቁጥቋጦ በቀረበ ጊዜ እግዚአብሔር ወደ ቁጥቋጦው እንዳይቀርብ፥ ጫማውንም እንዲያወልቅ አዘዘው። ይህ እንግዲህ እንደ ሙሴ ያለ ተራና ኃጢአተኛ ሰው፥ ቅዱስ ወደሆነው እግዚአብሔር ፊት ሊቀርብ እንደማይችል ማስጠንቀቂያ ነበር። በብሉይ ኪዳን ውስጥ ወደ ነበረው የኪዳኑ ድንኳን፥ ተራው ሕዝብ ሊቀርብ አይችልም ነበር። በኪዳኑ ድንኳን ውስጥ ያገለግሉ የነበሩት ካህናቱ ብቻ ነበሩ። ስለሆነም ናዳብና አብዩድ ያልተቀደሰ ተራ ፍም ይዘው በእግዚአብሔር ፊት በቀረቡ ጊዜ እግዚአብሔር ስለ ቀሰፋቸው ሞቱ። ከዚያም እግዚአብሔር ለአሮን፥ እርሱ በማይፈቅድበት ጊዜ፥ ማንም ሰው ሊቀ ካህናትም ቢሆኑ ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ ሊቀርቡ እንደማይችሉ አዝዞታል። የእግዚአብሔር ቅድስና ማለት እርሱ ከፍጥረቱ ሁሉ በላይ ነው ማለት ነው። በተለይም የእግዚአብሔር ቅድስና ማለት እርሱ ኃጢአተኛ ከሆነው ከሕዝቡ ሁሉ የተለየ ነው ማለት ነው። 

ሁለተኛ፥ መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔርን እንደ እሳትና ብርሃን አድርጎ ይገልጸዋል። በ1ኛ ዮሐንስ 1፡5 ውስጥ እግዚአብሔር የኃጢአትን ጨለማ የሚገልጥ ብርሃን ነው ይላል። በዕብራውያን መልእክት 12፡18 እግዚአብሔር የኃጢአትን ርኩሰት ሁሉ የሚያቃጥል እሳት ነው ይላል። እግዚአብሔር ንጹሕና እጅግ በጣም የደመቀ ብርሃን ስለሆነ፥ እርሱ እጅግ ሞቃትና የሚንበለበል እሳት በመሆኑ እግዚአብሔርና ኃጢአት አብረው ሊኖሩ አይችሉም። 

ምናልባት እግዚአብሔር ከኃጢአት ነፃ የሆነና የተቀደሰ ስለ መሆኑ ግልጽ በሆነ ምሳሌ የተናገረው «ትፋት» በሚለው ቃል መግለጫነት ነው። በዘሌዋውያን 18፡5 ውስጥ እግዚአብሔር ሲናገር፥ የከነዓንን ሰዎች ከኃጢአታቸው የተነሣ ምድሪቱ ልትተፋቸው ነው ይላል፡፡ በዘሌዋውያን 20፡22-23 ደግሞ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ እስራኤላውያንም በክፋታቸው ቢቀጥሉ →ምድሪቱ እንዲሁ ታደርጋቸዋለች፥ ከምድራቸውም ትተፋቸዋለች። ትፋት ወይም ትውከት የሚከሰተው አንድ ሰው ጨጓራው የማይፈጨውንና ሰውነቱን የሚመርዝ ምግብ ሲመገብ ነው። እንደዚሁም ኃጢአት መርዝ ስለሆነ፥ እግዚአብሔርን በምንም መልኩ «ሊዋሃደው» አይችልም። ስለዚህ ኃጢአት የሚሠሩትንም ሰዎች እግዚአብሔር ይተፋቸዋል። 

እግዚአብሔር በፍጹም ከኃጢአት የተለየ ቅዱስ ነው። እግዚአብሔር ቅዱስ ስለሆነ፥ ልጆቹም እንደዚሁ ቅዱሳን ሊሆኑ ይገባል። ወንዶችም ሴቶችም ቅዱሳን ካልሆኑ የእግዚአብሔር ልጆች መሆን አይችሉም። ነገር ግን ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ እንደ ተከታተልነው በምድር ላይ ያሉ ሰዎች ሁሉ ኃጢአተኞች ናቸው። ሁላችንም ኃጢአተኛች ከመሆናችን የተነሣ፥ ራሳችንን የእግዚአብሔር ጠላቶች (ሮሜ 8፡9፤ ቆላስይስ 1፡21፤ ያዕቆብ 4፡4)። የሰይጣን አገልጋዮች (ኤፌሶን 2፡2)፥ የኃጢአት ባሪያዎች (ዮሐንስ 8፡34)። የእግዚአብሔር የጽድቅ ቁጣ የሚፈጽምባቸው አድርገናል (ኤርምያስ 4፡4፤ ሮሜ 1፡18)። 

እግዚአብሔር ሉዓላዊ የሆነ የፍጥረታት ገዥ እስከሆነ ድረስ ኃጢአታችንን በቀላሉ ይቅር ሊለን የማይችለው ለምንድን ነው? እግዚአብሔር እጅግ ፍጹምና ጻድቅ ስለሆነና እኛም ራሳችንን ኃጢአተኛ ጠላቶቹ ከማድረጋችን የተነሣ እግዚአብሔር እንዲህ በቀላሉ ኃጢአታችንን ይቅር አይለንም። ይቅርታ ከማግኘታችን በፊት ኃጢአታችን መቀጣት አለበት። እንዲሁም ይቅርታ ከመቀበላችን እስቀድሞ የበደላችንና የኃጢአታችን ቅጣት ሊከፈል ይገባል። ይቅርታ ከማግኘታችን በፊት የእግዚአብሔር የጽድቅ ቁጣ ሊፈጸም ይሻል። ይቅርታ ከመቀበላችን አስቀድመን የእግዚአብሔር ወዳጆች ልንሆን ይገባል። ይቅር ከመባላችን በፊት ከኃጢአት ባርነትና ከሰይጣን አገልግሎት ልንድን ይገባል። እግዚአብሔር ቅዱስና ንጹሕ በአንጻሩ እኛ ደግሞ ኃጢአተኞች በመሆናችን፥ የእኛ ኃጢአት ሊቀጣ ያስፈልጋል። 

ጥያቄ፡- ዘሌዋውያን 16፡1-34 አንብቡ። በምታነቡበት ጊዜም መሥዋዕቱና የአቅርቦቱ ሥነ ሥርዓት ለኃጢአታችን «ስርየትን» እንደሚሰጥ እግዚአብሖር ስንት ጊዜ እንደ ተናገረ ቁጠሩ። 

ጥያቄ፡- ዘሌዋውያን 4፡27-35 አንብቡ። ሀ) በብሉይ ኪዳን ጊዜ የነበሩ እስራኤላውያን ኃጢአት በሚሠሩበት ጊዜ ምን ማድረግ ነበረባቸው? ይህን በራሳችሁ ቃል በአጭር መግለጫ ጻፉ። ለ) ውጠቶቹ ምን ይሆናሉ (ቁጥር 31ና 5)? 

ጥያቄ፡- ዕብራውያን 10፡3-4 አንብቡ። ሀ) እነዚህ የብሉይ ኪዳን መሥዋዕቶች በእውነት የብሉይ ኪዳን እስራኤላውያንን ኃጢአት ያስወግዱ ነበር? ለ) ዕብራውያን 9፡13 አንብቡ። ሰዎች በእምነት ያቀርቡዋቸው የነበሩ የብሉይ ኪዳን መሥዋዕቶች ምን ይጠቅሟቸው ነበር? ሐ) ሮሜ 3፡25 እንብቡ። እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን ጊዜ ስለተፈጸሙ ኃጢአቶች ምን አደረገ? 

ጥያቄ፡- ኢሳይያስ 53፡4-6 አንብቡ። ከዚያም የሚሠቃየው ባሪያ፥ በእውነት በመጨረሻው የኃጢአትን ቅጣት እንደሚሸክም የሚያመለክቱ ሐረጉችን ጻፉ። 

በብሉይ ኪዳን ዘመን እግዚአብሔር ለሕዝቡ ለኃጢአት የሚቀርቡ መሥዋዕቶችን በተመለከተ መመሪያ ሰጥቶ ነበር። መመሪያው በስርየት ቀን ይጀመር ነበር። ይህ ሥርዓት በዓመት አንድ ጊዜ ይፈጸም ነበር። ይህ የስርየት ቀን መላው ሕዝብ የኃጢአት መንጻት ስርየት የሚያገኝበት ነበር። በዘሌዋውያን 16 ውስጥ እግዚአብሔር አሥራ ስድስት ጊዜ በዚያን ቀን የሚቀርቡለት መሥዋዕቶች የኃጢአት ስርየትን እንደሚያስገኙ ይናገራል። በዚህ ለመላው ሕዝብ ስርየት የሚቀርበውን መሥዋዕት መሠረት በማድረግ እያንዳንዱ እስራኤላዊ በበኩሉ የኃጢአት ይቅርታ የሚያገኝበትን መሥዋዕት ያቀርብ ነበር። በዘሌዋውያን 4 የተነገረው የኃጢአት ይቅርታ መሥዋዕት አንዱ ምሳሌ ነው። ሊቀ ካህኑ መሥዋዕት ላመጡት ግለሰቦች ስርየት የሚያሰጥ አንድ በሬ በመሠዊያው ላይ ይሠዋ ነበር፡፡

ነገር ግን እነዚህ የብሉይ ኪዳን መሥዋዕቶች፥ መሥዋዕቶቹን ላመጡት ግለሰቦች በእርግጥ ኃጢአታቸውንና በደላቸውን አያስቀሩላቸውም ነበር። በዕብራውያን 10፡3-4 የበሬና የፍየል ደም ኃጢአትን ሊያስወግድ አልቻለም ይላል። የመሥዋዕቱ ደም ሙሉና የመጨረሻውን ይቅርታ በመስጠት ፈንታ፥ ኃጢአታቸውን ይሸፍን ነበር። በዚህም የውጪአዊ ነገር ሆኖ በእግዚአብሔር ፊት ሊቆሙ እንዲችሉ በሃይማኖት ሥነ ሥርዓት ንጹሐን ሆኑ፡፡ ዕብራውያን 9፡13 ደግሞ እነዚህ መሥዋዕቶች ውጫዊውን ሥጋ በሃይማኖታዊ ሥርዓት ለማንጻት የሚቀድሱ ናቸው ይላል። የሚቀርቡት መሥዋዕቶች፥ እግዚአብሔር ሕዝቡን ይቅር እንደሚለው በሰጠው ተስፋ መሠረት ይቅር እንዲላቸው እምነታቸውን የሚገልጹበት ሁኔታ ነው። እንደዚሁም በሮሜ 3፡25 እግዚአብሔር በመላው የብሉይ ኪዳን ዘመን፥ ለእነዚህ ኃጢአቶች ሁሉ ይቅርታን ለመስጠት በትዕግሥት ቆየ ይላል። ስለዚህ እውነተኛ ይቅርታ ፍጹም የሆነ ሥዋዕት ለኃጢአት እስኪቀርብ ድረስ ይጠብቃል። ኢሳይያስም ይህንኑ በምዕራፍ 8 ውስጥ ገልጾታል። በስድስተኛው ክፍለ ትምህርታችን ውስጥ ስለ ኢሳይያስ 53 ተልዕኮ በዝርዝር ተምረናል። ከቁጥር 4-5 ያለው ጥቅስ ሥቃይን የሚቀበለው ባሪያ እርሱ በመጨረሻ ኃጢአታቸውን የሚሸከም መሆኑን ለእስራኤላውያን ገልጾላቸዋል። እርሱ በእኛ ፈንታ ኃጢአታችንን ስለ ተሸክመ እኛ የምንሸከመው ነገር አይኖርም። እርሱም ስለ መተላለፋችን ቆሰለ፥ ስለ በደላችንም ደቀቀ። ከእግዚአብሔር ጋር ሰላምን የሚሰጠንን ቅጣት እርሱ ተሸክመ። ጌታ የእግዚአብሔርን ሕዝብ በደል ሁሉ በእርሱ ላይ አኖረበት። የብሉይ ኪዳን መሥዋዕቶች እውነተኛውን ይቅርታ የሚሰጡ ሳይሆኑ፥ ኢየሱስ ከመጣ በኋላ የተፈጸመው እውነተኛ መሥዋዕት ምሳሌ ነበር። ስለዚህ የኢየሱስ ሞት፥ ለበደልና ለኃጢአት ቅጣት ለዘላለም የተካፈለ ፍጹም የሆነ የእግዚአብሔር መሥዋዕት ነበር። 

በብሉይ ኪዳን ውስጥ እንስሳ በሰው ምትክ መሥዋዕት መደረጉን የሚያሳይ ሌላ ምሳሌ አለ። 

ጥያቄ፡– ዘፀአት 12፡1-13 አንብቡ። ሀ) ምን ዓይነት እንስሳት ለመሥዋዕት ይቀርቡ ነበር (ቁጥር 5)? ለነ እንስሳቱ ከተሠዉ በኋላ በደማቸው ምን ይደረግ ነበር (ቁጥር ? ሐ) ይህ እስራኤላውያንን እንዴት ይጠብቃቸው ነበር (ቁጥር 12-13)? 

ጥያቄ፡- 1ኛ ቆሮንቶስ 5፡7 አንብቡ። የአማኙ የፋሲካ በግ ማን ነው? 

የፋሲካ ታሪክ በእናንተ ዘንድ የታወቀ ነው። እግዚአብሔር በግብፅ ሕዝብ ላይ ዘጠኝ መቅሠፍቶችን ከላከ በኋላ እስራኤላውያን ሰነፃ እንዲሄዱ በሚያደርግ በአሥረኛው የመጨረሻ መቅሠፍት ገብፃውያንን እንደሚመታ ለሙሴ ነገረው። ከዚያ በኋላ የእግዚአብሔር ዕቅድ በግብፅ ውስጥ ማለፍና የግብፃውያንን በኩር ወንዶች ልጆችን መግደል ነበር (ዘፀአት 11፡15)። ነገር ግን የእስራኤላውያን በኩር ልጆች እንዳይሞቱ እግዚአብሔር ምትከን ሰጠ። ከዚያም እስራኤላውያን ጉድለት የሌለበት የአንድ ዓመት ጠቦት በግ መምረጥ ነበረባቸው። ይህ በግ የአካል ጉድለት የሌለበት ስለመሆኑ ለአሥራ አራት ቀናት ሲመረምሩ ከቆዩ በኋላ፥ አርደው ደሙን በመዝጊያው መቃን ጎንና ጎን እንዲሁም በመቃኑ ላይ ደሙን መቀባት ነበረባቸው። እግዚአብሔርም ይህ ደም በተቀባባቸው ቤት የሚኖሩትን በኩራት ሳይገድል እንደሚያልፍ ቃል ገብቶ ነበር። በጉ በበኩሩ ልጅ ፈንታ መሥዋዕት የሚሆን ነበር። 1ኛ ቆሮንቶስ 5፡7 «ክርስቶስ ለአማኞች ሁሉ የፋሲካ በግ ነው» ይላል። በተመሳሳይ ሁኔታ የዘፀአት በግ፥ በኩር የሆኑ ወንዶች ልጆች ከሞት እንዲተርፉ ሞተ። እኛ በደልንና የኃጢአታችንን ቅጣት እንዳንሸከም ክርስቶስ በደላችንንና የኃጢአት ቅጣታችንን ተሸከመልን። የፋሲካው በግ በኩር ለሆኑ ወንዶች ልጆች መሥዋዕትና ምትክ እንደሆነ ሁሉ፣ ክርስቶስም ለሚያምኑት ሁሉ መሥዋዕትና ምትክ ነው። 

እግዚአብሔር ቅዱስ ስለሆነ የኃጢአት ድርሻ ሊኖረው አይችልም። እግዚአብሔር በፍጹም ከኃጢአት የራቀና የተለየ ነው። ነገር ግን ሰዎች ሁሉ ኃጢአተኞች ናቸው። ስለዚህ እግዚአብሔር ራሱ በደልንና የኃጢአት ቅጣትን የሚሸከም ምትክ ሊሆን የሚችል መሥዋዕት ማቅረብ ነበረበት። በብሉይ ኪዳን ውስጥ እግዚአብሔር ጊዜያዊ የኃጢአት መሸፈኛ ወይም መክደኛ የሆነ የመሥዋዕት ሥርዓት ነበረው። እንደዚሁም ለእስራኤል በኩሮች ምትክ የሚሆን የፋሲካ በግ መሥዋዕትም መሥርቶ ነበር። ነገር ግን ይህ ሁሉ የብሉይ ኪዳን የመሥዋዕት ዓይነት፥ ምሉዕና እውነተኛውን የኃጢአት ይቅርታ ሊያሰጥ አልቻለም። እነዚህ ሁሉ ፍጹም መሥዋዕትና የኃጢአት ቤዛ ለሚሆነው ምስሎች ብቻ ነበሩ። በነገው ትምህርታችን ውስጥ ኢየሱስ ክርስቶስ የብሉይ ኪዳን ምስሎች እውን ፍጻሜ መሆኑን እናጠናለን። 

የዛሬውን ትምህርታችንን ከመደምደማችን በፊት ግን፥ እግዚአብሔር ኃጢአትን ምን ያህል እንደሚጠላና የኃጢአት ድርሻ ሊኖረው እንደማይችል ጥቂት አከል አድርገን ማሰብ ይኖርብናል። 

ጥያቄ፡– ራእይ 3፡16 አንብቡ፡፡ የሎዶቂያ ክርስቲያኖች ቀዝቃዛ ወይም ሙቅ ባለመሆናቸው ክርስቶስ ምን እንደሚያደርጋቸው አስጠነቀቀ? 

ኢየሱስ በራእይ ምዕራፍ 3፡16 ውስጥ በሎዶቂያ ላለችው ቤተ ክርስቲያን ይናገራል። በዚህ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚያመልኩ ምእመናን በጌታ ያመኑ አድርገው ራሳቸውን ቢቆጥሩም፥ በአኳያው ደግሞ ከመካከላቸው ብዙዎች በክርስቶስ ዳግም የተወለዱ አማኞች አልነበሩም። ስለዚህ ኢየሱስ በመንፈስ እሳትና ኃይል ሙቆች አለመሆናቸውን ወይም በሚያድስ መንፈስና መጽናናት ቀዝቃዞች እንዳልሆኑ በማሳሰብ ይናገራቸዋል። እነዚህ ክርስቲያኖች ከኃጢአታቸው የተነሣ የመንፈስ ድሆች ስለ መሆናቸው አልተገነዘቡም ነበር። እንደዚሁም በኃጢአታቸው ምክንያት በመንፈስ የታወሩ እንደ ነበሩ አልገባቸውም ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ከኃጢአታቸው የተነሣ በመንፈሳዊ ረገድ የተራቆቱ መሆናቸው አይሰማቸውም ነበር። ታዲያ እነዚህ ሰዎች ራሳቸውን ፍጹም ክርስቲያኖች አድርገው ቆጥረው ስለነበረ፥ በመንፈሳዊ ረገድ ከእግዚአብሔር ጋር የተስተካከለ ግንኙነት እንዳላቸው ራሳቸውን አድርገው ይቆጥሩ ነበር። ነገር ግን እንደ እርሱ ፈቃድ አይመላለሱም ነበር። በኃጢአት ውስጥ የነበረው ሕይወታቸው ከእግዚአብሔር ጋር የማይስማሙና እንደ ፈቃዱም እንደማይመላለሱ የሚያረጋግጥ ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ ሲያስጠነቅቃቸው ከአፉ አውጥቶ እንደሚተፋቸው ተናገረ። «አውጥቶ መትፋት» በቀድሞው የቋንቋ አባባል «ማስታወክ» ማለት ነው። እነዚህ ራሳቸውን አማኝ ክርስቲያኖች አድርገው ያስቡ የነበሩ ምእመናን፥ ስለ ደኅንነታቸው በእውነት በክርስቶስ አላመኑም ነበር። በመሆኑም። በኃጢአት የተሞላ ሕይወታቸው፥ በክርስቶስ በእውነት ዳግሞ የተወለዱ አማኞች እንዳልሆኑ ይመሰክር ነበር። ኢየሱስ ያመጣውን ደኅንነት ባለማግኘታቸው በኃጢአታቸውም ውስጥ ይኖሩ ስለነበር እግዚአብሔር ከአፉ አውጥቶ እንደሚተፋቸው ተናገረ። 

ጥያቄ፡- እናንተለ ኃጢአታችሁን ለኢየሱስ በመናዘዝና እርሱም የግላ አዳኛችሁ መሆኑን በማመን፥ ዘላለማዊ ደኅንነታችሁን አረጋግጣችኋልን? ራሳችሁን ፍጹም ክርስቲያኖች እድርጋችሁ ሳላችሁ በአኳያው ደግሞ ሕይወታችሁ በኃጢአት የተሞላ ከሆነ፥ ኢየሱስን የሕይወታችሁ ጌታ አድርጋችሁ አልተቀበላችሁትም ማለት ነው። ሁኔታው እንዲህ ከሆነ ጊዜ ወስዳችሁ ራሳችሁን አሁኑኑ መርምሩ። ከዚያም ኃጢአታችሁን በመናዘዝ ኢየሱስ መድኃኒታችሁና የሕይወታችሁ ጌታ እንደሆነ እመኑ። 

ጥያቄ፡- ራሳቸውን የተሰጡ ክርስቲያኖች አድርገው የሚቆጥሩ፥ ከእግዚአብሔርም ጋር በቅርብ የሚኖሩ የሚመስላቸው ነገር ግን ሕይወታቸው በኃጢአት የተሞላና ኢየሱስ መድኅናቸውና ጌታቸው መሆኑን ያልተቀበሉ፥ የምታውቋቸው ሰዎች አሉ? ካሉ በማስታወሻ ደብተራችሁ ውስጥ የሁለቱን ወይም የሦስቱን ሰዎች ስም ጻፉ። ከዚያም ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዴት አድርጋችሁ ልትነግሯቸው እንደምትችሉ ጥቂት ጊዜ ወስዳችሁ ጸልዩ። 

ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ አብዛኛዎቹ ሰዎች በክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ የተወለዱ ናቸው። ምናልባት የተጠመቁና ክርስቲያን ነኝ በሚል እሳቤ ብቻ አድገው ይሆናል። ደግሞም በቤተ ክርስቲያን ቆርበው ሰይጣንን ለመካድ ቃል ገብተውም ይሆናል። በመሆኑም ከእግዚአብሔር ጋር በሁሉም ረገድ ተስማምተው የሚኖሩ ይመስላቸው ይሆናል። ነገር ግን በኃጢአት ያለው ሕይወታቸው፥ እንደ እግዚአብሔር ልጆች በእርግጥ ዳግም ያልተወለዱ መሆናቸውን ይመሰክራል። እነዚህ ሰዎች ኢየሱስን ተቀብለው ጌታቸውና መድኃኒታቸው መሆኑን አረጋግጠው ካላመኑበት በስተቀር ኢየሱስ ከአፉ አውጥቶ እንደሚተፋቸው ይናገራል።

ምንጭ፡- “አስተምህሮ ክርስቶስና ደኅንነት”፤ ጽሑፍ፣ በዶ/ር ስቲቭ ስራውስ፤ ትርጉም በኃይሉ ልመንህ

Exit mobile version