1. መሢሑ የዳዊት ልጅ ደግሞም ንጉሥ ይሆናል።
ጥያቄ፡- ማቴዎስ 1፡1ና 22፡42 አንብቡ። መሢሑ የማን ልጅ ይሆናል የሚል ተስፋ ነበር?
ጥያቄ፡- ማቴዎስ 2፡2-4 አንብቡ። ሰብአ ሰገል ስለ ማን ጠየቁ? ሄሮድለ ካህናቱን ስለ ማን የትውልድ ስፍራ ጠየቃቸው?
ጥያቄ፡- ሉቃስ 23፡2 አንብቡ። የአይሁድ መሪዎች ክርስቶስ ማን ነው ብለው ነበር ለጲላጦስ የገለጹለት?
ጥያቄ፡- ማርቆስ 15፡32፤ ሉቃስ 23፡35 አንብቡ። እንደ ሕዝቡ አስተሳሰብ «በእግዚአብሔር የተመረጠ ክርስቶስ ማን ነበር?
በኢየሱስ ዘመን የነበሩ ሰዎች ከዳዊት ዘር የሚወለድ በተለይ በእግዚአብሔር የተመረጠና እግዚአብሔር የቀባው ንጉሥ እንደሚመጣላቸው በግልጽ ይጠባበቁ ነበር። ማቴዎስ በወንጌሉ በምዕራፍ 1፡1 ውስጥ ኢየሱስን ክርስቶስ ብሎ ሲገልጽ በቀጥታ የተናገረው ኢየሱስ የዳዊት ልጅ መሆኑን ነው። ኢየሱስ የሃይማኖት መሪዎችን ክርስቶስ የማን ልጅ እንደሚሆን በጠየቃቸው ጊዜ የመለሱትም እርሱ የዳዊት ልጅ እንደሆነ ነው። ሰብአ ሰገልም ወደ ንጉሥ ሄሮድስ ወደ ሃይማኖት መሪዎች ዘንድ ዘወር ብሎ ክርስቶስ የት እንደሚወለድ ጠየቃቸው። ሰብአ ሰገል ይፈልጉት የነበረው የአይሁድ ንጉሥ ሕዝቡ ይመጣል ብለው የሚጠባበቁት የተቀባው ክርስቶስ እንደሆነ ሄሮድስ ያውቅ ነበር። የአይሁድ መሪዎች ኢየሱስን በጲላጦስ ፊት የከሰሱት ራሱን ክርስቶስ ነኝ ይላል ብለው ነበር። እነርሱም ለጲላጦስ ክርስቶስ የሚለውን ቃል ትርጉም ሲያስረዱት፥ ክርስቶስ ማለት «ንጉሥ» ማለት ነው ብለው ነበር የነገሩት። ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሆኖ ያፌዙበት ሰዎች ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ አላመኑም ነበር። ምክንያቱም እነርሱ የጠበቁት ክርስቶስ የተመረጠና ንጉሥ የሚሆን ነበር። ደግሞም የተሰቀለ ማንም ሰው በእግዚአብሔር የተመረጠ ወይም ንጉሥ ሊሆን እንደማይችል ይገመት ነበር። ስለሆነም የአይሁድ ሕዝብ በልዩ ሁኔታ በእግዚአብሔር የተቀባውንና መጥቶም በንጉሥነት የሚገዛቸውን የዳዊትን ልጅ በግልጽ ይጠባበቁ ነበር።
2. ኢየሱስ መሢሑ- ንጉሥ ነው
ጥያቄ፡- ሉቃስ 1፡31-33 አንብቡ። መልአኩ ለማርያም ምን ተስፋ ሰጣት?
ጥያቄ፡- ዮሐንስ 18፡36-37 እንብቡ። ኢየሱስ በጲላጦስ ፊት በቆመ ጊዜ ማን መሆኑን ነበር የገለጸው? ደግሞስ እንዴት ያለውን መንግሥት ለመግዛት እንደ መጣ ነበር የተናገረው?
ኢየሱስ ሕዝቡ ሲጠባበቀው የነበረ መሢሕ መሆኑን አዲስ ኪዳንም ደህና አድርጎ ይገልጻል። መልአኩ ለድንግል ማርያም በተናገራት ጊዜ፥ እርሱ ተስፋ የተገባለት መሢሕ፥ የዳዊት ልጅ ነው፥ እርሱም በእስራኤላውያን ላይ ለዘላለም ይነግሣል ብሎ ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ በጲላጦስ ፊት በቆመ ጊዜ ያስታወቀው ይህ ንጉሥ እርሱ መሆኑን ነበር።
የማቴዎስ ወንጌል፥ ኢየሱስ በብሉይ ኪዳን ውስጥ ተስፋ የተሰጠበት መሢሑ ንጉሥ እንደ ነበረ በማረጋገጥ ረገድ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ጽፎአል። ማቴትስ ኢየሱስ መሢሑ ንጉሥ መሆኑን ለማረጋገጥ፥ የሰው ልጅ፥ የእግዚአብሔር ልጅ በሚሉት የማዕረግ ስሞች ተጠቅሞአል። እነዚህ ስሞች በሕዝቡ ዘንድ የሚመጣው መሢሕ መጠሪያዎች በመሆን ይታወቁ ነበር (ማቴዎስ 16፡16፥ 27-28፤ 26፡63-64)። እነዚህን ለኢየሱስ የተሰጡ የማዕረግ መጠሪያዎች በሌላ ትምህርት ላይ እናጠናቸዋለን። ነገር ግን በብሉይ ኪዳን ውስጥ ተስፋ የተሰጠበት መሢሑ- ንጉሥ፥ ኢየሱስ መሆኑን ማቴዎስ በም ስት የተለያዩ መንገዶች ያረጋግጣል።
2.1 ኢየሱስ የዳዊት ልጅ ነው።
ጥያቄ፡- ማቴዎስ 1፤ 9፡27፤ 2፡23፤ 5፡22፤ 20፡30-31፤ 21፡9 አንብቡ። በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ ኢየሱስ ማን ተብሎ ይጠራል?
ማቴዎስ በመጀመሪያ ኢየሱስ መሢሑ ንጉሥ መሆኑን የሚገልጠው፥ ኢየሱስ ሕዝቡ የሚጠብቀው የዳዊት ልጅ መሆኑን በማመልከት ነው። ማቴዎስ ራሱ የዳዊት ልጅ ብሎ ይጠራዋል። ደግሞም ብዙ ጊዜ ሰዎች በዚህ ስም ሲጠሩት እንደ ነበረ ጽፎአል። 22 ብሉይ ኪዳን፥ ኢየሱስ መሢሑ- ንጉሥ እንደ ነበረ ያረጋግጣል።
ጥያቄ፡- ማቴዎስ 2:2፣ 21፡5 አንብቡ። በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ ኢየሱስ ማን ተብሎ ይጠራል?
ማቴዎስ የሚመጣው መሢሑ ንጉሥ ኢየሱስ መሆኑን የሚያስረዳበት ሁለተኛው መንገድ እርሱ የሚመጣው መሢሑ ንጉሥ መሆኑን የሚመሰክሩ ክፍሎችን በብሉይ ኪዳን ውስጥ በመጥቀስ ነው። ሰብአ ሰገል በብሉይ ኪዳን ውስጥ ተስፋ የተሰጠበትን የአይሁድ ንጉሥ ፍለጋ መጡ። ሄሮድስም ሄደው እንዲገናኙት ወደ ቤተልሔም ላካቸው። ማቴዎስ በሚክያስ 2 ላይ መሢሑ ንጉሥ በቤተልሔም እንደሚወለድ የተነገረው የተስፋው ፍጻሜ ኢየሱስ መሆኑን በግልጽ ተረድቶአል። (ያለፈውን ሳምንት ትምህርት ተመልከቱ)። ኢየሱስ በአህያ ጀርባ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም በገባ ጊዜ በዘካርያስ 9፡9 ላይ መሢሑ ንጉሥ በአህያ ላይ ተቀምጦ እንደሚመጣ የተጻፈው ተፈጸመ ሲል ማቴዎስ ተናግሮአል። እንደዚሁም ማቴዎስ ስለ መሢሑ የሚያስረዳ ልዩ ልዩ የብሉይ ኪዳን ክፍሎችን በመጥቀስ እርሱ መሢሑ= ንጉሥ መሆኑን ለማረጋገጥ ተጠቅሞበታል (ማቴዎስ 3፡3፤ 2፡18-21 21፡5 22፡44)። 23 ኢየሱስ ስለ መንግሥቱ ሰበከ።
ጥያቄ፡- ማቴዎስ 4፡17፥ 23 9፡35 እንብቡ። ኢየሱስ ሲያስተምር በነበረበት ጊዜ መልእክቱ ስለ ምን ነበር? ማቴዎስ 10፡7 አንብቡ። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ይሰብኩ ዘንድ የሰጣቸው መልእክት ምን ነበር?
ጥያቄ፡- ማቴዎስ 5፡3፥ 10፥ 20፤ 6331 21 አንብቡ። እነዚህ ጥቅሶች እንደሚያስረዱት፥ የተራራው ስብከት ዋና ትኩረት ምን ነበር? 16ኛ ጥያቄ ማቴዎስ 13፡24፥ 31፥ 33፥ 44፥ 47! 21፡1 22፡2 አንብቡ። የኢየሱስ ምሳሌዎች ስለ ምን ነበሩ?
ሦስተኛው ማቴዎስ ኢየሱስ መሢሑ ንጉሥ መሆኑን ያሳየበት መንገድ፥ የኢየሱስ ትምህርት ዋናው ጭብጥ ስለ መንግሥት እንደ ነበረ ትኩረት ሰጥቶ መጻፉ ነው። በማቴዎስ ወንጌል መንግሥት ማለት መንግሥተ ሰማያት እንደሆነ ተገልጾአል። በሌሎች ወንጌሎች ውስጥ ግን መንግሥት የሚለው ቃል የእግዚአብሔር መንግሥት ተብሎ ተጽፎአል። እነዚህ ሁለት አገላለጾች፥ ስለ ኢየሱስ አገዛዝና ንግሥና በሁለት የተለያዩ መንገዶች የተጻፉ ናቸው። ኢየሱስ ስለ መንግሥቱ በሰበከ ጊዜ ግዛቱ አሁን በምድር እንዳለና፥ ገና ወደፊትም እንደሚመጣ ገልኦአል። በትምህርት ዘጠኝ ላይ ኢየሱስ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ስላስተማረው ትምህርት በሰፊውና በዝርዝር እንማራለን። ለዛሬው ኢየሱስ ስለ መንግሥቱ የሰጠው ትምህርት እርሱ የእስራኤል መሢሑ ንጉሥ መሆኑን ምን ያህል ግልጽ እንዳደረገልን መገንዘብ እንፈልጋለን።
ጥያቄ፡- ሉቃስ 17፡20-21፤ ዮሐንስ 18፡36-37፤ ቆላስይስ 1፡12-13 አንብቡ። በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ ምን ዓይነት መንግሥት ነው የተገለጸው፥ ደግሞስ መች ይኖራል?
ጥያቄ፡- ማቴዎስ 6፡10፤ 8፡11፤ ሉቃስ 22፡18፤ 29-30፤ 1ኛ ጢሞቴዎስ 4፡1 አንብቡ። በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ የተገለጸው ምን ዓይነት መንግሥት ነው? ደግሞስ መቼ ይኖራል?
በአዲስ ኪዳን ውስጥ በሚገኙ አንዳንድ ክፍሎች ላይ እንደተገለጸው መንግሥቱ ኢየሱስን እንደ አዳኛቸውና ጌታቸው በተቀበሉት ልብ ውስጥ አለ። በልባቸው ውስጥ ይገዛል፤ እነርሱም ገንዘቡ ናቸው። ኢየሱስ በምድር በነበረ ጊዜ አብረውት ለነበሩት፥ የእግዚአብሔር መንግሥት በመካከላቸው እንደ ነበረ ነግሮአቸዋል (ሉቃስ 17፡20-21)። ለጲላጦለም የእርሱ መንግሥት ከዚህ ምድር እንዳልነበረ ነግሮት ነበር (ዮሐንስ 18፡36-37)። እንዲሁም ጳውሎስ ለቆላስይስ ሰዎች እግዚአብሔር ወደ ልጁ መንግሥት እንዳመጣቸው ነግሮአቸዋል (ቆላስይስ 1፡12-13)።
ሆኖም፥ በአዲስ ኪዳን በሌሎች ክፍሎች ውስጥ ግን መንግሥት ሲል፥ ወደፊት ስለታቀደውና በዓይን ስለሚታየው ምድራዊ መንግሥት ማለቱ እንደሆነ ግልጽ ነው። ስለሆነም ክርስቲያኖች ይህ መንግሥት እንዲመጣ እንዲጸልዩ ተነግሮአቸዋል (ማቴዎስ 6፡1)። አይሁዳውያንና አሕዛብ ሁለቱም የዚህ መንግሥት በረከት ተካፋዮች ይሆናሉ። ሐዋርያት በዚህ መንግሥት ውስጥ ልዩ የሆነ የሥልጣን ስፍራ ይኖራቸዋል (ማቴዎስ 8፡11)። ኢየሱስም በመጨረሻው እራት ወቅት ይህን መንግሥት ገና ወደፊት እንደሚመጣ አድርጎ ይመለከተው ነበር (ሉቃስ 22፡18፥ 29-30)። ሐዋርያው ጳውሎስም ኢየሱስ በሚገለጥበት ጊዜ ማለትም በዳግም ምጽአቱ ወቅት ይጀመራል ይላል (1ኛ ጢሞ. 4፡ህ። ኢየሱስ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደዚህ ምድር በመጣበት ወቅት የንጉሥነት ግዛቱ በተወሰነ ደረጃ እንደ ተጀመረ ግልጽ ይመስላል። ይኸውም ሳመኑትና በታዘዙት ልብ አድሮ መግዛቱ ነው። ሆኖም ግዛቱ ገና በሙሉ አልተፈጸመም። ዳግም ተመልሶ ሲመጣበት ግዛቱን ይመሠርታል፤ መንግሥቱም ፍጹምና እንከን የለሽ ነው።
በኢየሱስ ጊዜ የነበሩ አይሁዶች መሢሐቸው ንጉሥ እንደሚሆን ያውቁ ነበር። እነርሱ በዚያን ጊዜ ስለ መሢሑ- ንጉሥ የነበራቸው እምነት በራሳቸው ላይ ተንሰራፍተው ይገዙዋቸው የነበሩትን የሮማውያንን ቀንበር ሰብሮ በማስወገድና እስራኤልን ወደ ቀድሞው ክብርዋና ታላቅና ኃያል መንግሥትነትዋ እንደሚመልሳት ነበር። ሆኖም ኢየሱስ እስራኤላውያንን ባስተማረበት ጊዜ አጽንዖት የሰጠው ስለ ሌላ ዓይነት መንግሥት ነበር። በመሆኑም ንስሐ እንዲገቡ፥ በገዛ ራሳቸው ጽድቅ እንዳይመኩና አምነው እንዲድኑ አስተማራቸው። በሕይወታቸው ለእርሱ መገዛት ነበረባቸው። የእርሱ መንግሥት፥ ጦር ከትቶ ከሮማውያን ጋር የሚዋጋ ምድራዊ መንግሥት አልነበረም (ዮሐንስ 18፡15)። ሕዝቡ አስገድደው የፖለቲካ አራማጅ ንጉሥ እንዲሆንላቸው የነበራቸውን ሙከራም አልተቀበለም (ዮሐንስ 6፡15)። ስለዚህ የአይሁድ ሕዝብ ከመሢሑ ንጉሣቸው የጠበቁት ምላሽ ይህ ስላልነበረ፥ ብዙዎቹ ኢየሱስን ተዉት። ሆኖም ኢየሱስ ተመልሶ መጥቶ የአይሁድንና ሌሎችንም ሕዝቦች በዚህ ምድር ላይ የሚገዛበት ጊዜ ይመጣል።
3. ኢየሱስ መጥቶ ንጉሥ ሆኖ ይገዛል።
19ኛ ጥያቄ፡- ራእይ 1፡5፤ 17፡14፣ 19፡16 አንብቡ። ሀ) ኢየሱስ የማን ንጉሥ እንደሚሆን ተነገረ? ለ) ፊልጵስዩስ 2፡11 አንብቡ። ፍጥረታት ሁሉ አንድ ቀን ምን ያደርጋሉ?
የዮሐንስ ራእይ እግዚአብሔር መንግሥቱን በኢየሱስ አማካይነት ዳግም በምድር ላይ መልሶ እንደሚያቋቁም ግልጽ አድርጎ የሚያብራራ ሥዕላዊ መጽሐፍ ነው። በዚሁ ክፍል ኢየሱስ የምድር ነገሥታት ሁሉ ንጉሥ እንደሆነና የምድርንም ሕዝቦች ሁሉ እንደሚገዛ ተጽፎአል። ስለዚህ እርሱ አንድ ቀን መንግሥቱን በቀጥታ በዚህ ምድር ላይ በመመሥረት በእርሱ ከታመኑት ጋር አብሮ ይገዛል (ራእይ 20፡4)። በዚህንም ጊዜ ፍጥረታት ሁሉ በእግዚአብሔር የተቀባውን፥ የኢየሱስን ገዢነትና ጌታነት ተቀብለው ያስተጋባሉ።
ጥያቄ፡- ኢየሱስ መሢሑ ንጉሥ እርሱ መሆኑን በተዘዋዋሪ መንገድ ይገልጽባቸው ስለነበሩት ሁኔታዎች አስቡ። ይህ በሕይወታችሁ ውስጥ ምን ልዩነትን ያስከትላል? በዚህ ሳምንት ኢየሱስን ንጉሣችሁ አድርጋችሁ በሕይወታችሁ መኖር የምትጀምሩባቸውን ሦስት ለየት ያሉ የሕይወት አቅጣጫዎችን ጻፉ።
ኢየሱስ በእግዚአብሔር የተቀባ ንጉሥ እንደ መሆኑ መጠን የእርሱ ተከታዮች ነን የምንል ሁሉ፥ በዚህ ምድር ላይ ንጉሣችን አድርገን ልንቀበለው ይገባል። ሌሎች እኛን በሚመለከቱበት ጊዜ ኢየሱስ ንጉሣቸው የሆነ ሕዝብ ናቸው ብለው የሚመሰክሩልን ሕይወት ሊኖረን ይገባል። በንግግራችንም ውስጥ ቢሆን ኢየሱስ ንጉሥ መሆኑን መግለጽ ይገባል። እርሱን ለመግለጽና ማዳኑን ለመናገር፥ እንዲሁም ለሕይወታችን የሰጠውን በረከት ለማሳወቅ ፈጣኖች መሆን አለብን። በገንዘብ አጠቃቀማችንም ሆነ በተቀረው ንብረታችን ውስጥ ኢየሱስ ንጉሥ መሆኑ ሊገለጥ ይገባል። እኛ አሥራት የምንከፍለው የገቢአችንን አሥር በመቶ ብቻ ሳይሆን፥ ያለን ንብረት ሁሉ የእርሱ መሆኑን በመገንዘብ ሊሆን ይገባል። ለእግዚአብሔር ሥራ የምናመጣው ገንዘብ የእኛ ላይሆን የሌላ ሰው ገንዘብ መሆኑን ሁልጊዜ ማስታወስ ጠቃሚ ነው። ይህም ሰው ንጉሡ ኢየሱስ ነው። ሕይወታችንን በሚመለከቱ ውሳኔዎች ላይም እንኳን ቢሆን፥ ኢየሱስ ንጉሣችን መሆኑን ማሳየት አለብን። የምንመርጠውን ሙያ ወይም የሥራ ዘርፍ፥ የምናገባውን ሰው፥ ልጆቻችንን እንዴት እንደምናሳድግ፥ የት እንደምንኖር ወይም ትርፍ ጊዜአችንን እንዴት እንደምንጠቀም ሳይቀር ኢየሱስ ንጉሣችን መሆኑን ስማስታወስ ይሁን። አንድ ቀን አንደበት ሁሉ ኢየሱስ ንጉሥ እንደሆነ ይመሰክራል። ታዲያ ዛሬ እኛም እርሱ ንጉሣችን መሆኑን በተግባር እናሳይ።
ምንጭ፡- “አስተምህሮ ክርስቶስና ደኅንነት”፤ ጽሑፍ፣ በዶ/ር ስቲቭ ስራውስ፤ ትርጉም በኃይሉ ልመንህ
