Site icon

የእግዚአብሔር ልጅ መለኮታዊ ነው። 

ማቴዎስ፥ ማርቆስና ሉቃስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው ማለታቸው እርሱ ከእግዚአብሔር ጋር የቅርብ ቀንኙነት ያለው መሢሕ ነበር፤ ይሁንና ከዚህም በተጨማሪ እርሱ ራሱ መለኮት የሆነ መሢሕ ነበር ብለው መጠቆማቸውም ነበር። 

ጥያቄ፡– ሀ) ማርቆስ 1፡1-3 አንብቡ፡ ማርቆስ በቁጥር 1 ውስጥ ኢየሱስን በምን አኳኋን ገለጸው? ለ) ሚልክያስ 3፡1 አንብቡ። የእግዚአብሔር መልእክተኛ በተን ፊት ይሄዳል? ሐ) ኢሳይያስ 40፡3 አንብቡ፡ መንገድ ለማን ተዘጋጀ? መ) ርስ በምን ፃክንያት ሚልክያስ 3፡1 ኢሳይያስ 40፡3 በወንጌሉ መጀመሪያ ላይ የጠቀለ ይመስላችኋል? 

ማርቆስ በወንጌሉ መክፈቻ ላይ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን አስቀድሞ ይገልጻል። ይህን ሊጽፍስ ምን ማለቱ ነው? ማርቆስም ይህን ልንገነዘብ እንድንችል ወዲያውኑ ሚልክያስ 3፡1 እና ኢሳይያስ 40፡3ን ይጠቅላላ በሚልክያስ 9፡1 ላይ እግዚአብሔር ከራሱ ከጌታ አስቀድሞ መልእክኛውን እንደሚልክ ይናገራል። ብዙዎቹ አይሁድ ይህን ክፍል ኤልያስን የመሰለ መልእከተኛ ቀድሞ መማተ ለመሢሑ መንገድ እንደሚያዘጋጅለት አድርገው ገምተው ነበር (ማርቆስ 9፡1)። ማርቆስ፥ ሚልክያስ 3፡1ን በመጥቀስ፥ ኢየሱስ ዮሐንስ ይመጣል ብሎ መንገድ ያዘጋጅለት የነበረው መሢሕ የእግዚአብሔርም ልጅና፥ እርሱ ራሱም መለኮት እንደሆነ ይነግረናል። 

ጥያቄ፡- ማቴዎስ 14፡33 አንብቡ። ሀ) ኢየሱስ በውኃ ላይ ሄዶ የባሕሩን ሞገድ ጸጥ ካለኘው በኋላ፥ ደቀ መዛሙርት ምን ተሰማቸው? ለ) ይህ በሆነ ጊዜ ምን ብለው ጠሩት? 

ኢየሱስ በውኃው ላይ ከሄደና ጴጥሮስንም ከማዕበሉ ካዳነው በኋላ ወደ ጀልባው እንደ ወጡ፥ የባሕሩ ሞገድ ወዲያው ጸጥ አለ። በተፈጥሮ ላይ ሲፈጸም ያዩት ኃይልና ቁጥጥር፥ ስለ ኢየሱስ ማንነት በአድናቆትና በፍርሃት እንዲሞሉ አደረጋቸው። ከዚያም በጀልባው ውስጥ እያሉ ስሜታቸውን በስግደት ገለጡለት። ለእግዚአብሔር ብቻ ይሰጥ የነበረውን ክብርና ሞገለ አቀረቡለት። በሰገዱለትም ጊዜ፥ «በእርግጥ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ» አሉት። የእግዚአብሔር ልጅ የሆነው መሢሑ ኢየሱስ ከሰው በላይ እንደሆነ ማቴዎስ በዚህ ታሪክ አማካይነት ይነግረናል። እውነትም ኢየሱስ በተፈጥሮ ላይ ፍጹም የሆነ ሥልጣን ነበረው። እርሱ ራሱም መለኮት ነበር። ደቀ መዛሙርቱም ይህንን በማስተዋል፥ ለአንድ መለኮታዊ አምላክ የሚገባውን ስግደት በማቅረብ ስሜታቸውን ገለጹለት። 

ጥያቄ፡- ሉቃስ 1፡32፥ 35 አንብቡ፡ ሀ) እንደ ቁጥር 32 አባባል እግዚአብሔር ለኢየሱስ ምንን ሰጠ? ለ) እንደ ቁጥር 35 አባባል መልአኩ በምን ምክንያት ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ተብሎ ይጠራል አለ? 

መልአኩ ገብርኤል በመጀመሪያ ስለ ኢየሱስ መወለድ ለማርያም ሊያበስርላት ወደ እርሷ በመጣ ጊዜ፥ በመጀመሪያ የነገራት፥ «እርሱ ታላቅ ይሆናል፥ የልዑል እግዚአብሔርም ልጅ ይባላል፥ ጌታ አምላክ የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል» የሚል ነበር። በዚህም ኢየሱስ መሢሕ እንደሚሆን ነግሮአታል። «የልዑል እግዚአብሔር ልጅ» የሚለው መጠሪያ እርሱ በተለይ በእግዚአብሔር የተመረጠ መሢሕ መሆኑን የሚገልጥ ሌላው መንገድ ነበር። እንደዚሁም መልአኩ ገብርኤል ማርያም ድንግል መሆንዋን እንደሚያውቅ እረጋግጦላት፥ ነገር ግን ከወንድ ጋር የግብረ ሥጋ ገንኙነት ሳታደርት እንደምትፀንስና የምትፀንሰውም በመንፈስ ቅዱስ ኃይል እንደሚሆን ነግሮአታል። ማርያም በእግዚአብሔር ኃይል ስለምትፀንስ፥ የሚወለደውም ሕፃን የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል። «ይጸልልሻል» የሚለው ቃል፥ ኢየሱስ መልኩ በሚያንጸባርቅ ሁኔታ በተለወጠ ጊዜ የእግዚአብሔር በዚያ መገኘት የተገለጠበት ቃል ይህ ነው። እንደዚሁም እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን ጊዜ የነበረውን የቃል ኪዳኑን ድንኳን ሲሞላ የነበረበት ሁኔታም የተገለጸው በዚሁ ቃል ነበር። ሉቃስም እያለ ያለው የእግዚአብሔር የራሱ መገኘት የኢየሱስን መፀነስ እንደሚያከናውን ነው። የኢየሱስ መፀነስ በእግዚአብሔር በራሱ መገኘት ስለሆነ እርሱም የእግዚአብሔር ልጅ ተብሎ ይጠራል። «የእግዚአብሔር ልጅ» የሚለው መጠሪያ ኢየሱስ ከመፀነሱ ጊዜ ጀምሮ መለኮት አብሮት እንደ ነበረ ያመለክታል። 

«የእግዚአብሔር ልጅ» የሚለው የማዕረግ መጠሪያ መለኮታዊ የሆነው መሢሕ መጠሪያ መሆኑን በግልጽ የሚናገረው ክፍል ኢየሱስ በአይሁድ ሸንጎ ፊት ቀርቦ በተወነጀለ ጊዜ የቀረበው ነው። 

ጥያቄ፡– ማርቆስ 14፡61-64 አንብቡ። ኢየሱስ፥ የብሩክ እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ነኝ ብሎ በተናገረ ጊዜ፥ የካህናት አለቃው እንዴት ባለ ሁኔታ መለሰ? 

ኢየሱስ በአይሁድ ሸንጎ ፊት ቀርቦ ሲመረመር ሳለ፥ እርሱ የተቀባው መሢሕ ክርስቶስ መሆኑን እስከ ጠየቁበት ጊዜ ድረስ ምንም ዓይነት መልስ አልሰጣቸውም ነበር። በሌላ አገላለጽ መሢሕ ማለት የብሩክ እግዚአብሔር ልጅ ወይም «የእግዚአብሔር» ልጅ ተብሎ ሊተረጎም ይችላል። ወዲያውኑ ኢየሱስ ግልጽ የሆነ መልስ ሰጣቸው። እርሱ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን አስረጻቸው። በመቀጠልም የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ እንደ መሆኑ፥ አንድ ቀን በራሱ ሰአብ ቀኝ ተቀምጦ እንደሚያዩት ገለጸላቸው። በእግዚአብሔር ቀኝ እቀመጣለሁ ሲላቸው፥ የእግዚአብሔር የራሱን ክብርና ሥልጣን እኔም እቀበላለሁ ማለቱ ነበር። በሌላ አገላለጽ እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ መሢሑ በመሆኑ ራሱም መለኮት እንደሆነ እየነገራቸው ነበር። የካህናት አለቃውም ኢየሱስን በዚህ ሁኔታ እንደተረዳው የምናውቀው ወዲያው የኢየሱስን ስድብ ሰማችሁ በማለት ከሰነዘረበት ክስ ነው። ሊቀ ካህኑ ኢየሱስን ተራ ሰው እንደ ነበር ያምን ነበር። ነገር ግን የእግዚአብሔር ልጅ የሆነው መሢሕ ነኝ ብሎ መናገርና ይህን ማዕረግ የራስ አድርጎ መግለጽ መለኮት ነኝ ብሎ እንደ መደምደም ነው። ስለዚህ ኢየሱስ እንደ ተሳደበ መሰለው። ይህ ክፍለ ምንባብ በግልጽ የእግዚአብሔር ልጅ የሚለው መጠሪያ ኢየሱስ ራሱ መለኮት የሆነው መሢሕ ነው ማለት መሆኑን ያመለክታል። 

ማቴዎስ፥ ማርቆስና ሉቃስ «የሰው ልጅ» የሚለውን የማዕረግ መጠሪያ ሲጠቀሙ፥ ለመግለጽ የፈለጉት። ኢየሱስ ከእግዚአብሔር ጋር ልዩ ፍቅርና ግንኙነት ያለው ስለሆነ እግዚአብሔርን በተለየ ሁኔታ የመግለጽ ኃይል እንዳለው ነው። እንደዚሁም በዚህ የማዕረግ መጠሪያ ለመግለጽ ያሰቡት ኢየሱስ ከሰው ልጅ የበለጠና መለኮታዊ መሆኑን ጭምር ነው። 

ጥያቄ፡- አንድ ሙስሊም የሆነ ወዳጃችሁ «እናንተ ክርስቲያኖች ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው ትላላችሁ፥ እግዚአብሔር ልጅ አለው ብላችሁ ስለምታምኑ፥ እግዚአብሔርን ትሳደባላችሁ» ይላችኋል እንበል። ታዲያ በዛሬው ትምህርታችን ላይ በመመሥረት ክርስቲያኖች ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው ሲሉ ምን ማለታቸው እንደሆነ እንዴት እንደምትገልጹለት በጽሑፍ አስቀምጡ። በተቻለ መጠን ሙስሊሙን ወዳጃችሁን በማያስቀይመው መንገድ መልሱለት። 

ሙስሊሞች ክርስቲያኖች ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ያምናሉ ማለትን በሚሰሙበት ጊዜ ክርስቲያኖች እግዚአብሔር ከሴት ጋር ግብረ ሥጋ ንኙነት ከአደረገ በኋላ ኢየሱስ እንደ ተወለደ እንደሚያምኑ አድርገው ያስባሉ። ይህንንም እንደ ከባድ ስድብ እድርገው ይቆጥሩታል። ነገር ግን እንደሚታወቀው ክርስቲያኖች ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው ሲሉ፥ የሚያምኑት ይህንን አይደለም። ነገር ግን ዛሬ እንደ ተከታተልነው፥ «የሰው ልጅ» የሚለው መጠሪያ የሚያመለክተው፥ ኢየሱስ የእስራኤል መሢሕ እንደሆነና ከእግዚአብሔር ጋር ልዩ ፍቅርና አንድነት እንዳለው ነው። እርሱ ከእግዚአብሔር ጋር ልዩ ግንኙነት ስላለው ማንም ሰው ሊገልጸው በማይችለው መንገድ እግዚአብሔርን ሊገልጸው ችሏል። ልጅ አባቱን እንደሚመስል ሁሉ «የእግዚአብሔር ልጅ» የሚለው መጠሪያ ኢየሱስ ራሱ ፍጹም እግዚአብሔርን እንደሚመስል ያመለክታል። ታዲያ ሙስሊም ከሆኑ ወዳጆቻችን ጋር በምንወያይበት ወቅት ወዲያው ተቻኩለን «የእግዚአብሔር ልጅ» የሚለውን ቃል ልናነሣባቸው አይገባም። ምክንያቱም ብዙ ጊዜ ይህ የምንናገረው ነገር ያደናግራቸዋልና ነው። በዚህ ፈንታ መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስን «የእግዚአብሔር ልጅ» ብሎ በሚጠራበት ጊዜ ምን ማለቱ መሆኑን አንሥተን ብንወያይ ይሻላል። ኢየሱስ ከእግዚአብሔር ጋር ልዩ ፍቅርና አንድነት ያለው መሢሕ መሆኑንና ከዚህም የተነሣ ማንም ሰው የተባለ ሊያደርገው በማይችለው ሁኔታና መንገድ፥ እግዚአብሔርን ለሰዎች ሊገልጽ መቻሉን እንደምናምን ልንነግራቸው እንችላለን። ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ» ነው ስንል ኢየሱስ ማንም ሰው ሊያደርገው በማይችለው መንገድ እግዚአብሔር ምን እንደሚመስል አሳይቷል ማለታችን ነው።

ምንጭ፡- “አስተምህሮ ክርስቶስና ደኅንነት”፤ ጽሑፍ፣ በዶ/ር ስቲቭ ስራውስ፤ ትርጉም በኃይሉ ልመንህ

Exit mobile version