Site icon

መሢሑ እንደ ካህን 

ምንም እንኳን አይሁዶች ንጉሥ የሚሆናቸውን መሢሕ እየፈለጉ ቢሆንም፥ አንዳንድ የብሉይ ኪዳን ትንቢቶች ግን መሢሑ ከንጉሥ የበለጠ እንደሚሆን ያመለክቱ ነበር። አንዳንዶቹ ትንቢቶች ደግሞ መሢሑ ካህን እንደሚሆን ሲናገሩ፥ ሌሎቹ ትንቢቶች ደግሞ ነቢይ እንደሚሆን ይጠቁሙ ነበር። ስለሆነም መሢሑ ካህንም እንደሚሆን ስለተነገሩ ትንቢቶች ፍጻሜ ዛሬ አብረን እናጠናለን። 

1. ብሉይ ኪዳን ዓይነተኛ ካህን እንደሚመጣ ተንብዮ ነበር። 

ባለፈው ሳምንት መዝሙር 110ን አጥንተን ነበር። በብሉይ ኪዳን የነበሩ አማኞች ይህ መዝሙር ስለሚመጣውና በእግዚአብሔር ስለተቀባው መሢሕ በግልጽ እንደሚናገር ግንዛቤ ነበራቸው። እንደ ተከታተልነው ሁሉ በኢየሱስ ጊዜ የነበሩ የአይሁድ ሰዎችም በመዝሙር 110 ላይ «ጌታ» የሚለውን የዳዊት ልጅ የሆነው መሢሕ- ንጉሥ ነው ብለው ተቀብለዋል (ማቴዎስ 22፡44)። ነገር ግን መዝሙር 110 መሢሑ «በመልከ ጼዴቅ ሥርዓት የመጣ የዘላለም ካህን ነው» ይላል። ግን በኢየሱስ ዘመን የነበሩ የአይሁድ ሕዝብ መሢሑ ካህንም ንጉሥም ሊሆን የሚችልበት ሁኔታ አልገባቸውም። በብሉይ ኪዳን ውስጥ ካህናት ነገሥታት አልነበሩም፥ ነገሥታትም ካህናት የነበሩበት ጊዜ አይታወቅም። ያም ሆኖ ግን መዝሙር 110 መሢሐዊ ካህን ይመጣል የሚል ተስፋ በሕዝቡ ዘንድ እንዲኖር አደረገ። ስለሆነም በተለይ እግዚአብሔር ራሱ የቀባውን ዓይነተኛ ካህን ይልክ ነበር። 

ሆኖም ደግሞ በብሉይ ኪዳን ውስጥ ዓይነተኛ ካህን እንደሚመጣ ተስፋን ያሰፈነ ሌላ ክፍልም ነበር። 

ጥያቄ፡- 1ኛ ሳሙኤል 2፡35 አንብቡ። ስሙ ያልተጠቀሰው ነቢይ ለዔሊ ምን ትንቢት ነገረው? 22ኛ ጥያቄ፡- 1ኛ ነገሥት 2፡27፥ 35 አንብቡ። ይህ ትንቢት እንዴት ተፈጸመ? 

1ኛ ሳሙኤል ምዕራፍ 2 በሴሎ የነበረውን የመገናኛ ድንኳን ያገለግል የነበረውን የእግዚአብሔር ካህን፥ የዔሊ ቤተሰብ ኃጢአት አሳዛኝ ሁኔታ ይተርክልናል። ስለዚህ የዔሊን ልጆች ኃጢአት እንዲያወግዝ (1ኛ ሳሙኤል 2፡27)፥ በዚያውም ልጆቹ ኃጢአት ስለሠሩ እግዚአብሔር በኃጢአታቸው ምክንያት እንደሚገድላቸውና ዳግም ከእርሱ ዘር ካህን እንደማይወጣ እንዲያረዳው አንድ ስሙ ያልተጠቀሰ ነቢይን ወደ ዔሊ ዘንድ ላከው (1ኛ ሳሙኤል 2፡34፥ 36)። ከዚያም ትንቢቱ እንዲህ በማለት በተስፋ ይፈጸማል፥ «ለእኔም ለአንተም ምትክ ታማኝ የሆነና እኔ የምወደውን ሁሉ የሚያደርግ ሌላ ካህን እመርጣለሁ፤ ለእርሱም እኔ በምመርጠው ንጉሥ ፊት ካህናት ሆነው የሚያገለግሉ ዘሮችን እሰጠዋለሁ» (1ኛ ሳሙኤል 2፡35)። የትንቢቱ የመጀመሪያ ክፍል በ1ኛ ሳሙኤል 4 ላይ እንደተጻፈው የዔሊ ልጆች በጦርነት ላይ በሞቱ ጊዜ በአስደናቂ ሁኔታ ተፈጽሞአል። የትንቢቱ ሁለተኛው ክፍል ደግሞ በ2ኛ ነገሥት 2፡27፥ 35 ከዔሊ ዝርያ የነበረው የአቢያታር ሊቀ ክህነት በንጉሥ ሰሎሞን ዘመን ለሳዶቅ በተሰጠ ጊዜ ተፈጽሞአል። ይህን ትንቢት በመጀመሪያ ደረጃ ው በመፈጸም በተቀቡ ነገሥታቱ በዳዊትና በሰሎሞን ፊት ካህን ሆኖ እንዲያገለግል እግዚአብሔር ሳዶቅን አስነሣው (2ኛ ሳሙኤል 8፡17፤ 5፡24፥ 35፤ 20፡25)። የሳዶቅ ቤተሰብ ከእርሱ ሞት በኋላም በክህነቱ አገልግሎት በመቀጠል በታማኝነት የይሁዳ ካህናት ሆነው የዳዊትን ቤተሰብ ሲያገለግሉ ቆይተዋል (1ኛ ነገሥት 4፡1፤ 1ኛ ዜና 6፡11-5)። ከዚያም እስራኤላውያን ከባቢሎን ምርኮ እስከ ተመለሱበት ጊዜ ድረስ ቀጥለዋል (ዕዝራ 7፡1-2)። ሆኖም በብሉይና በአዲስ ኪዳን ጊዜ መካከል ማለትም ለ160 ዓመታት አንቲዮኩስ ኤፒፋነስ የተባለ የሶሪያ ንጉሥ ሥልጣነ ክህነቱን ከሳዶቅ ቤተሰብ ነጥቆ ለሌላ ሰው ሰጠ። ከዚህን ጊዜ ጀምሮ ሊቀ ካህናት በፖለቲካና በሌላም ዓለማዊ ሥራዎች ውስጥ መሳተፍ ጀመሩ። ከዚያም ልክ እንደ ሀብታም የተንደላቀቀ ኑሮ መኖር ቀጠሉ። በኢየሱስ ጊዜ የነበሩ ብዙ ተራ አይሁዶች በ1ኛ ሳሙኤል 2 እና በመዝሙር 110 ውስጥ የተጻፈውን ትንቢት ተስፋ በማድረግ፥ በእግዚአብሔር በልዩ ሁኔታ የሚመረጠው ካህን አንድ ቀን መጥቶ የሊቀ ክህነቱን ስፍራ የሚወስድበትን ቀን ይናፍቁ ነበር። ንጹሕ ሕይወት የሚኖር፥ እግዚአብሔርን የሚፈራና የሊቀ ክህነቱንም ማዕረግና መንፈሳዊ 

መንበር የሚያደርግ ዓይነተኛ መሢሕ ይመጣል ብለው ይጠባበቁ ነበር። 

2. ኢየሱስ ሁሉን የሚያሟላ፥ ተስፋ የተሰጠበት ካህን ነው። ስለዚህ ፍጹምነት ባለው ክህነቱ ፍጹም የሆነ መሥዋዕት ያቀረበ ፍጹም ካህን ነው። 

ባለፈው ሳምንት እንደተማርነው፥ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ኢየሱሪ የመዝሙር 110 ፍጻሜ መሆኑን የሚያመለክቱ ክፍሎች እንዳሉ ተገንዝበናል (ማቴዎስ 22፡44፤ የሐዋ. ሥራ 2፡32-34 አንብቡ)። በተለይም የዕብራውያ መልእክት ኢየሱስ እንዴት የመዝሙር 110 ፍጻሜ እንደሆነና እንዴት እግዚአብሔር በልዩ ሁኔታ የሾመው መ ሐዊ ካህን ሆኖ እንደ መጣ ሰፋ 

አድርጎ ያስረዳል። 2.1 ኢየሱስ አንድ ፍጹም የሆነ ሊቀ ካህን የሚፈለግበትን መሥፈርት ሁላ ያሟላል። 

ጥያቄ፡- ዕብራውያን 5፡1-4 አንብቡ። ከአንድ ሊቀ ካህን የሚጠበቅ መሥፈርት ወይም ብቃት ምንድን ነው? 

ጥያቄ፡- ዕብራውያን 5፡6-10 አንብቡ። ኢየሱስ እነዚህን መሥፈርቶች ወይም ብቃቶች እንዴት አሟላ? 

ጥያቄ፡- ዕብራውያን 4፡14-16 አንብቡ። እነዚህን መሥፈርቶች ሁሉ የሚያሟላ ሊቀ ካህን ስላለን የእኛ አመለካከት ምን መሆን አለበት? 

ዕብራውያን 4፡14-5፡10 ክርስቶስ አንድ ሊቀ ካህን ሊያሟላ የሚገባውን መሥፈርት ወይም ብቃት ሊያሟላ እንደሚችል ይገልጻል። ሐዋርያው በመጀመሪያ ይህንን ሊቀ ካህን እንዴት ልንመለከተው እንደሚገባን ይነግረንና ቀጥሎም ክርስቶስ በእርግጥ ሊቀ ካህናችን እንደሆነ እንዴት ማረጋገጥ እንደምንችል ያስረዳናል። ሐዋርያው በዕብራውያን 5፡1-4 ውስጥ ከሁሉም ሊቀ ካህናት የሚፈለገውን መሥፈርት ያስቀምጣል። በመጀመሪያ፥ ሰዎችን ወክለው ወደ እግዚአብሔር እንዲቀርቡ የተሾሙ መሆን አለባቸው። ሁለተኛ፥ እነርሱም ሰዎች ስለሆኑና ሁሉም ሰው እንደሚፈተን ስለሚፈተኑ ኃጢአት የሚሠሩትን በርኅራኄ መቀበል ይችላሉ። ሦስተኛ፥ በእግዚአብሔር ካልተሾሙ በስተቀር ራሳቸውን ካህናት አድርገው ሊሾሙ አይችሉም፥ ዕብራውያን 5፡5-10 ያለው ክፍልም ክርስቶስ ይህንን የሊቀ ካህንነት መሥፈርት እንዴት እንደሚያሟላ ይናገራል። በመጀመሪያ ጸሐፊው መዝሙር 2፡7 እና መዝሙር 10፡4ን ጠቅሶ ክርስቶስ የሊቀ ካህንነቱን ማዕረግ ራሱ የወሰደ ሳይሆን፥ በእግዚአብሔር የተሰጠው ሹመት መሆኑን ያረጋግጣል። ባለፈው ሳምንት ያጠናናቸው እነዚህ ሁለት ክፍሎች ስለ መሢሑ መምጣት የተተነበዩ ናቸው። ጸሐፊው የጠቀሳቸው ክርስቶስ መሢሕ ሆኖ መሾሙ ሊቀ ካህን ሆኖ መሾሙን ጭምር እንደሚያጠቃልል ለማረጋገጥ ነው። ሁለተኛ፥ ክርስቶስ የተፈተነና ፈተናን ድል ያደረገ ሰው ነበር። ቁጥር 7 ኢየሱስ በጌቴሴማኒ የአትክልት ስፍራ በነበረ ጊዜ ያጋጠመውን ፈተና ይገልጻል። በዚህም ምንም እንኳን መታዘዝ የዓለምን ኃጢአት ተሸክሞ እስከ ሞት ድረስ አሰቃቂ ሥቃይና መከራ መቀበል ማለት ቢሆንም፥ የአብን ፈቃድ ለመፈጸም እራሱን አለ። ኢየሱስ ማንም ሰው ከተሠቃየው በላይ ተሠቃይቷል፥ ቢሆንም ግን ለአብ ታማኝና ታዛዥ ነበር። ኢየሱስ በጣም አስቸጋሪ በሆነ ጊዜ እንኳን ለአብ መታዘዝን መምረጥ ምን እንደሚመስል ከልምድ ያውቃል። ስለዚህ ኢየሱስ መፈተን ምን ማለት እንደሆነ ስለሚገነዘብ ልክ እንደ ሌሎች ካህናት እርሱም በሚያጋጥመን ፈተና ላይ ተገኝተ ያጽናናናል፤ በርኅራኄም ይቀበለናል። ጸሐፊው ኢየሱስ «ፍጹም» ሆነ ሲል ኢየሱስ ኃጢአት አድርጎ ነበር ማለቱ አይደለም። በዚህ ፈንታ ኢየሱስ ፍጹም ሰው መሆኑ አስፈላጊውን ሁሉ አድርጓል ማለቱ ነው። ለአብ እንዳይታዘዝ የሚገፋፋ ፈተና እንደ ማንኛውም ሰው ደርሶበታል። ነገር ግን እርሱ ሁልጊዜ ለአብ ፈቃድ መታዘዝን መረጠ። እርሱ ካህን እንዲሆን በእግዚአብሔር በመመረጡ ምክንያት እና ለአብ ፈቃድ እንዳይታዘዝ ፈተና የደረሰበት ሰው በመሆኑ ኢየሱስ በእግዚአብሔር ፊት እኛን ወክሎ ሊቀ ካህናችን ሆኖ ለመቆም ብቃት አግኝቷል። 

ታዲያ ለእኛ የሚራራልን ሊቀ ካህናት ስላለን አቋማችን ምን ሊሆን ይገባል? ዕብራውያን 4፡14-16 ሁለት መልሶች ይሰጠናል። «በሰማያት ያለፈ ትልቅ ሊቀ ካህናት የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ስላለን፥ ጸንተን ሃይማኖታችንን እንጠብቅ።» በመጀመሪያ፥ እምነታችንን አጥብቀን መያዝ ይገባናል። እንዲህ ማለትም በምናደርገውና በምንናገረው ሁሉ በክርስቶስ ላይ ያለን አቋም ግልጽና የጠነከረ መሆን አለበት ማለት ነው። ምንም ያህል አስቸጋሪ ቢሆንም እንኳ፥ ክርስቶስን የምንከተል መሆናችንን ለሌሎች ሰዎች መመስከር ይገባናል። ምንም እንኳን እንደማያምኑ ሰዎች ለመኖር ብንፈተንም፥ እንደ ክርስቶስ ተከታዮች ሆነን መኖር አለብን። 

ጥያቄ፡- እንደ ክርስቶስ ተከታዮች በተለይ ለመናገርም ሆነ ለመኖር አስቸጋሪ የሚሆንባችሁ መቼ ነው? 

አማኞች ሁሉ በክርስቶስ ጸንተው ለመቆም የሚያቅታቸው ጊዜ አለ። አንዳንድ ጊዜ ለክርስቶስ በመቆማችን ልንሰደድ ወይም ሰዎች ሊያፌዙብን ይችላሉ። አንዳንዴም ለክርስቶስ መቆም፥ ከሥራ መውጣትን ወይም ሌሎች ጥሩ የሆኑ ዕድሎችን ማጣት መሆን ይችላል። አንዳንድ ጊዜም ለክርስቶስ መቆም ለወዳጆች የመራቅ ምክንያት ሊሆን ይችላል። እንደዚሁም ለክርስቶስ መቆም ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያመጣ ይሆናል። ግን በእነዚህ ፈተናዎች ሁሉ ውስጥ ለእርሱ መታዘዝ አስቸጋሪ መሆኑን ክርስተስ ያውቃል። ምክንያቱም እርሱም ለአብ ፈቃድ ታዛዥ እንዳይሆን ተፈትኖ ነበርና ነው። እንደ ክርስቶስ ተከታዮች ለመናገርም ሆነ ለመሥራት አስቸጋሪ ስሚሆንብን ጊዜ ማስተዋል ያለብን ኢየሱስ ይህንን ስሜታችንን በትክክል እንደሚነዘብልን ነው። 

ነገር ግን እንደሚገነዘብ ከማስታወስ ያለፈ ነገር ማድረግ ይኖርብናል። ሁለተኛ መልሳችን ክርስቶስን በእውነት ርኅሩኅ የሆነ ሊቀ ካህናችን ነው የምንልበት «እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ» (ዕብራውያን 4፡16) የሚል ቃል ስላለን ነው። አንድ ጊዜ ክርስቶስ ርኅሩኅ የሆነ ሊቀ ካህናችን መሆኑን ከተገነዘብን ፈተናን ለመቋቋም ለእርሱ በመቆም እንድንታዘዘውና እርዳታው እንዳይለየን እግዚአብሔር እንድንጸልይ ይፈልጋል። ለመቆጣት ፈተና ሲገጥመን፥ ሞኞች ሲፈትኑን፥ ሰዎችን የመስቀል ስሜት ሲያድርብን፥ ስንጨነቅ ወይም ስንዋሽ፥ ስለ ፈተናው ለእርሱ መንገርና ለመታዘዝ የሚያስችለውን የእርሱን ጸጋና ብርታት መለመን ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነ እንድናስታውስ ክርስቶስ ይፈልጋል። ምናልባትም ለክርስቶስ ለመቆም ስንሻ ስደትና መከራ ቢደርስብን ወይም ያለንን ብናጣ ክርስቶስ ለመታዘዝና የእርሱን ምሕረትና ብርታት መለመን ምንኛ አስቸጋሪ እንደሆነ እንድናስታውስ ይፈልጋል። ብቸኝነት ሲይዘን፥ የሥራ ጫና፥ ሕመምና የመሳሰሉ ሁኔታዎች ሲያጋጥመን እንዲህ ባሉ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ሆኖ ለእግዚአብሔር ታማኝ መሆን። ለመታመንም የሚያስችለውን የእርሱ ጸጋና ኃይል መጠየቅ አስቸጋሪ መሆኑን እንደሚገነዘብ እንድናስታውስ ይፈልጋል። 

ጥያቄ፡- አሁኑኑ ጀምራችሁ ጥቂት የጸሎት ጊዜ አድርጉ። ኢየሱስ እውነተኛና ርኅሩኅ ሊቀ ካህን በመሆኑ አመስግኑት። ከዚያም በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በምትሆኑበት ጊዜ በተግባርና በቃል ጭምር ለክርስቶስ ለመቆም የሚያስችላችሁን 

ምሕረቱን፥ ጸጋውንና ኃይሉን እንዲለጣችሁ ጠይቁ። 

2.2 የኢየሱስ ክህነት ፍጹም የሆነ ክህነት ነው። 

ጥያቄ፡- ዕብራውያን 7፡23-28 አንብቡ። የኢየሱስ መልከ ጼዴቃዊ ክህነት ከአሮን ክህነት የበለጠ ስለመሆኑ፥ ከዚህ ክፍለ ምንባብ ቢያንስ ሁለት ምክንያቶችን ጻፉ። 

ባለፈው ሳምንት ትምህርቶቻችን ላይ ዕብራውያን 7፡11-22ን ስንመለከት፥ የመልከ ጼዴቅን መሥመር የተከተለ የኢየሱስ አዲሱ ክህነት ከአሮጌው ከአሮን የክህነት አመጣጥ የበለጠ መሆኑን ተገንዝበናል። ዕብራውያን 7፡23 28 ለምን የበለጠ እንደሆነ ይነግረናል። በመጀመሪያ፥ ጥንታውያኑ ካህናት በየጊዜው ስለሚሞቱ በዚያው መጠን ያለማቋረጥ ምትክ የሚሆኑ ብዙ ካህናት ያስፈልጉ ነበር። ኢየሱስ ግን ለዘላለም ይኖራል። ስለዚህ ፍጹም ምትክ የማያስፈልገው አንድ ካህን ብቻ አለን። የማይለወጥ አንድ ካህን ለሁል ጊዜ ስላለን፥ እርሱ ስለ እኛ ይማልዳል፤ ደግሞም ፈጽሞ ያድነናል (ወደ ኋላ ላይ ኢየሱስ ለእኛ ስለሚያደርገው ምልጃ እንማራለንህ። ሁለተኛ፥ የጥንቱ ካህናት ስለ ኃጢአታቸው መሥዋዕት ማቅረብ ነበረባቸው። እነርሱ ራሳቸው ፍጹማን ስላልነበሩ፥ በእግዚአብሔር ፊት ፍጹም የሆኑ አማላጆች አልነበሩም። ኢየሱስ ግን በፍጹም ኃጢአት አልሠራም። ስለዚህ እርሱ ቅዱስ፥ ነውር የሌለበትና ንጹሕ ነው። «ቅዱስና ያለ ተንኮል ነውርም የሌለበት ከኃጢአተኞችም የተለየ ከሰማያትም ከፍ ከፍ ያለ፥ እንደዚህ ያለ ሊቀ ካህናት ይገባናል» እንግዲህ የሚያስፈልገንን የሚያዘጋጅልን ሊቀ ካህናችን ኢየሱስ ነው፤ እርሱ «ቅዱስ የሆነ፥ ያለነቀፋ የሆነ፥ ንጹሕ የሆነ ከኃጢአተኞች የተለየ ከሰማያት በላይ ከፍ ያለ ነው» (ዕብራውያን 7፡26)። ኢየሱስ ፍጹም ንጹሕ በመሆኑ ለኃጢአቱ መሥዋዕት ማቅረብ አልነበረበትም። መሥዋዕት የማያስፈልገው የራሱ ኃጢአት የሌለው በመሆኑ ራሱን ለሌሎች ኃጢአት አሳልፎ የመስጠት ብቃት ተቀዳጀ። እንዲሁም ተፈተነ እንጂ ኃጢአትን ያላደረገ ስለሆነ ክርስቶስ ፍጹም ካህን ሊሆን ችሏል። 

2.3 የኢየሱስ የካህንነት መሥዋዕት፥ ፍጹምነት ያለው ለኃጢአት የቀረበ መሥዋዕት ነው። 

ጥያቄ፡- ዕብራውያን 9፡11-15፥ 24፡26 አንብቡ። ሀ) ኢየሱስ ለኃጢአት መሥዋዕት ለማቅረብ ወዴት ገባ? ለ) ክርስቶስ ያቀረበው መሥዋዕት ምን ነበር? ሐ) ክርስቶስ መሥዋዕቱን ለማቅረብ ስንት ጊዜ ይገባ ነበር? መ) የክርስቶስ መሥዋዕት ውጤቶች ምን ነበሩ? 

ክርስቶስ በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ፥ ፍጹም የሆነ መሥዋዕትን ለመላው ዓለም ያቀረበ ሊቀ ካህናት ሆነ። በብሉይ ኪዳን ሊቀ ካህናት እንስሳውን አቅርቦ በመሠዊያው ላይ 5ሠዋ በኋላ የእንስሳውን ደም ይዞ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ ይገባ ነበር (ዘሌዋውያን 16)። ቅድስተ ቅዱሳኑ እግዚአብሔር በዚያ ስፍራ ለመገኘቱ ምልክት ነበር። ክርስቶስ የመሥዋዕትነቱን ደም ይዞ ወደ ምድራዊ መገናኛ ድንኳን ወይም ቤተ መቅደስ አልገባም። እርሱ የገባው ከማንኛውም ፍጥረት ጨርሶ ወደ ተለየ ስፍራ የእግዚአብሔር ማደሪያ ወደሆነው ወደ ሰማይ ነው። የእርሱ መሥዋዕት የእንስሳ ደም ሳይሆን፥ ነገር ግን የራሱ ደም ነበር። እርሱ ኃጢአት የሌለበት በመሆኑ፥ ደሙ ከኃጢአት ፈጽሞ የማንጻት ኃይል እለው። በብሉይ ኪዳን ውስጥ የሚደረጉ የእንስሳት መሥዋዕቶች የብሉይ ኪዳንን አማኞች በእውነት ከኃጢአታቸው እያነጹዋቸውም ነበር። መሥዋዕቶቹ ያደርጉላቸው የነበረው ውጪአዊ ሥነ ሥርዓታዊ ማንጻት ብቻ ነበር። ለኃጢአታቸው ጊዜያዊ የሆነ ሽፋን ብቻ ይሰጡዋቸው ነበር እንጂ ከኃጢአታቸው ፍጹም አያነጹአቸውም ነበር። ነገር ግን የክርስቶስ ደም በብሉይ ኪዳን ዘመን ለነበሩትም ሆነ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ላሉት እውነተኛ አማኞች ሁሉ ሙሉና ብቁ፥ ፍጹም የኃጢአት መንጻትን ይሰጣቸዋል። ክርስቶስ ያቀረበው መሥዋዕት ፍጹምነት ያለው መሥዋዕት በመሆኑ ምክንያት እግዚአብሔር ወደሚገኝበት ደጋግሞ እየገባ በየጊዜው ለኃጢአት ሥርየት መሥዋዕት ማቅረብ አያስፈልገውም። እርሱ በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ፊት ቀርቦ ለሚያምኑት ሁሉ የኃጢአታቸውን ዋጋ ለአንዴና ለመጨረሻ ው ከፍሎአል። 

ጥያቄ፡- ዕብራውያን 10፡19-22 አንብቡ። ሀ) አማኞች እንዴት ባለ ሁኔታ ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ሊጎቡ ይችላሉ? ለ) ኢየሱስ የእኛ ሊቀ ካህናት በመሆኑ አቋማችን ምን መሆን አለበት? 

ዕብራውያን 10፡19-22 ያለው ክፍል ኢየሱስ ራሱን ለኃጢአት ፍጹም መሥዋዕት አድርጎ ስላቀረበ አማኞች ሁሉ እግዚአብሔር ወዳለበት ይገቡ ዘንድ በሩን እንደ ከፈተላቸው ይነግረናል። ኢየሱስ በተሰቀለ ጊዜ በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ውስጥ የነበረውን ቅድስተ ቅዱሳኑን ከሌላው የመቅደሱ ክፍል የሚለየው መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ተቀደደ (ሉቃስ 23፡45)። ይህ እንግዲህ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ስለ ሞተ ወደ እርሱ የሚወስደው መንገድ ክፍት መሆኑን እግዚአብሔር የገለጸበት አንዱ መንገድ ነው። ክርስቶስ ፍጹም የሆነ መሥዋዕት ከማቅረቡ የተነሣ የእኛ ሊቀ ካህናት በመሆኑ አማኞች ሁሉ በቀጥታ እግዚአብሔር ወዳለበት እንዲገቡ በሩን ከፍቶላቸዋል። ታዲያ አማኞች ይህንን ለመሰለው መብት ምላሻቸው ምንድን ነው? ሁላችንም ኃጢአታቸው ይቅር እንደ ተባለላቸው ሰዎች ወደ እግዚአብሔር በመቅረብ በዚህ ዕድል ልንጠቀም ይገባል። ወደ እግዚአብሔር ሕልውና ውስጥ ዘወትር በመግባት ልናመልከውና ልንሰግድለት ይገባል። እንደዚሁም የሚያሳስቡንን ነገሮች ወደ እርሱ ዘወትር ይዘን በመቅረብ መፍትሔው ከእርሱ ዘንድ መሆኑንና እኛ አቅም የሌለን መሆናችንን እንንገረው። ኃጢአት በምንሠራበት ጊዜ ከበደለኝነትና ከፍርሃት የተነሣ ከእግዚአብሔር መራቅ እንደሚገባን አይሰማን። ይልቁንም ወደ እርሱ ቀርበን ኃጢአታችንን በመናዘዝ እንደገና ከእርሱ ጋር በመሆንና ለኃጢአታችንም ይቅርታን በመቀበል በእርሱ ልንደሰት ይገባል። 

ጥያቄ፡– አንድ ወዳጃችሁ በሠራው ኃጢአት በጣም እያዘነና እግዚአብሔርም የሠራውን ኃጢአት ይቅር እንደማይለው እያሰበ በፍርሃት ተይዞ ወደ እናንተ ዘንድ ይመጣል እንበል። ይህ ወዳጃችሁ እግዚአብሔርን ስለፈራው እርሱን ለማምለክም ሆነ ወደ እርሱ ለመጸለይ ብቁ እንዳልሆነ ተሰምቶታል። ታዲያ በዚህ በዕብራውያን መልእክት ውስጥ ካነበባችሁት ቃል ምን ማበረታቻ ልትነግሩት ትችላላችሁ? 

ክርስቶስ እግዚአብሔር በሚገኝበት በሰማይ ደሙን ፍጹም መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበ እውነተኛ ሊቀ ካህናት ነው። በክርስቶስ የሚያምኑ ሁሉ ኃጢአታቸው ይቅር የማይባልላቸው መስሎ ሊሰማቸው አይገባም። ምክንያቱም የክርስቶስ ደም ፍጹም የሆነ ማንጻትን ያደርጋልና። በክርስቶስ የሚያምኑ ደኅንነታቸው በከፊል የሚሆን ሊመስላቸው አያስፈልግም፥ ክርስቶስ የሚያድነው ሙሉ በሙሉ ነው። እንደዚሁም በክርስቶስ የሚያምኑ ምእመናን፥ ክርስቶስ ይቅር የሚለውን የከፋ ኃጢአት ሠራን ብለው ሊፈሩ አይገባም። የክርስቶስ ደም ውጪአችንን ብቻ ሳይሆን ውስጣችንንም የማንጻት ኃይል አለው። አንድ ሰው ክርስቶስን አምኖ እንደ መድኅኑ ሊቀበለውና ኃጢአቱን ሲናዘዝ፥ ያኔ ከኃጢአቱ ይነጻል። ሰዎች ክርስቶስን ካልተቀበሉ በደለኛ መሆናቸው እየተሰማቸው ለሠሩት ኃጢአት ይቅርታ እንደማያገኙ በማሰብ ፍርሃት ያድርባቸዋል። ነገር ግን በክርስቶስ አምነው ኃጢአታቸውን ሲናዘዙ ፍጹም በሆነ ደሙ ከኃጢአታቸው እንደሚያነጻቸው ተስፋ ይሰጣቸዋል። እግዚአብሔር ኃጢአተኞች ሁሉ በክርስቶስ ደም አማካይነት ወደ እርሱ መጥተው፥ ኃጢአታቸውን እንዲናዘዙና እንዲያመልኩት፥ ከእርሱም ጋር አንድነት እንዲኖራቸው ይፈልጋል። 

የዕብራውያን መልእክት ኢየሱስ መሢሑ– ንጉሥ ብቻ መሆኑን የሚያመለክት ሳይሆን፥ መሢሐዊ– ካህን መሆኑንም ይናገራል። እርሱ ፍጹም የሆነ ሊቀ ካህናችን በመሆኑ፥ ፍጹም የሆነ የኃጢአት ይቅርታን ይሰጠናል። እንደዚሁም እርሱ ስለሚራራልን የኃጢአት ፈተናን የምናሸንፍበትን ምሕረቱንና ኃይሉን ይሰጠናል። 

ምንጭ፡- “አስተምህሮ ክርስቶስና ደኅንነት”፤ ጽሑፍ፣ በዶ/ር ስቲቭ ስራውስ፤ ትርጉም በኃይሉ ልመንህ

Exit mobile version