Site icon

ኃጢአት አልባው የኢየሱስ ሰብአዊነት 

በዚህ ክፍል በሙሉ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ስብእና እናጠናለን። እርሱ እንደ እኛ ሰው ስለመሆኑ አይተናል። ነገር ግን ሳምንቱን በተማርነው ትምህርት ከኃጢአት ነፃ ነው ስንል ቆይተናል። ዛሬ ኢየሱስ ኃጢአት ያላደረገ ስለመሆኑ፥ ሰፋ አድርገን እናጠናለን። እንደዚሁም የሚከተለውን ጥያቄ ልናነሣ እንችላለን፡ «ኢየሱስ ፈጽሞ ኃጢአት ባይሠራም፥ ኃጢአትን ሊፈጽም ይችል ነበር?» 

ኢየሱስ በፍጹም ኃጢአትን ላደረገም 

ጥያቄ፡- ዕብራውያን 4፡5 አንብቡ። ሀ) ስለ ኢየሱስ መፈተን ይህ ጥቅስ ምን ይላል? ለህ እንደዚሁም ይህ ጥቅስ ኢየሱስ ኃጢአት ስለ መሥራቱና ስለ አለመሥራቱ ምን ይላል? 

ጥያቄ፡- ሀ) ዮሐንስ 8፡46 አንብቡ። ኢየሱስ ለጠየቀው ጥያቄ መልሱ ምንድን ነው? ለ) ማቴዎስ 26፡59-60 አንብቡ። ኢየሱስ በሸንጎው ፊት በቀረበ ጊዜ በኃጢአት ምክንያት ወይም በወንጀል የከሰሰው ሰው ነበር? 

ጥያቄ፡- 1ኛ ጴጥሮስ 2፡22 አንብቡ። እዚህ ላይ ጴጥሮስ ስለ መሢሑ ከኢሳይያስ መጽሐፍ ይጠቅሳል። ስለ ክርስቶስ ምን ይላል? 

ጥያቄ፡- 2ኛ ቆሮንቶስ 5፡21 አንብቡ። ይህ ጥቅስ ስለ ክርስቶስ ምን ይላል? 

ጥያቄ፡- 1ኛ ዮሐንስ 3፡5 አንብብ። ክርስቶስ ለምን ኃጢአታችንን ሊያስወግድልን ቻለ? 

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ በነበረ ጊዜ፥ ምንም ዓይነት ኃጢአት አለማድረጉን አዲስ ኪዳን በግልጽ ያቀርበዋል። እርሱም በምድር ላይ በነበረ ጊዜ በአንዳች ኃጢአት የሚከሰው ካለ እንዲያቀርብ ይቃወሙት ለነበሩ ይነግራቸው ነበር። እንደዚሁም በሚያነጋግራቸው ጊዜ አንዳችም ኃጢአት ያላዩበት ከመሆናቸውም በላይ ከሰሰው በሸንጎ ፊት ባቀረቡትም ጊዜ አንዳች ኃጢአት አላገኙበትም። ምንም እንኳን ወንጀል የሚፈልጉበት ቢሆኑም፥ የሐሰት ምስክሮችም ቀርበው የሐሰት ክስ ሊያቀርቡበት ቢፈልጉም፥ በምንም ኃጢአት ሊወነጅሉት አልቻሉም። ስለ ኢየሱስ ምድራዊ ሕይወት ያለው ምስክርነት ግልጽ ነው፡ እርሱ ኃጢአት አልሠራም። 

በአዲስ ኪዳን ውስጥ የሚገኙ መልእክቶች ኢየሱስ ኃጢአት አለመፈጸሙን በተመሳሳይ ሁኔታ ግልጽ አድርገውታል። በ1ኛ ጴጥሮስ 2፡22 ውስጥ ጴጥሮስ ከኢሳይያስ 53፡9 ላይ ጠቅሶ፥ ክርስቶስ ምንም ኃጢአት አለማድረጉን ያስረዳል። ኢየሱስ ኃጢአት አለመፈጸሙ ብቻ ሳይሆን፥ ኃጢአታዊ ባሕርይ አልነበረውም። የኃጢአት ቅድመ- ዝንባሌም አልነበረውም። 2ኛ ቆሮንቶስ 5፡21፥ «ኃጢአት ያላወቀውን» ሲል ስለ ኢየሱስ ይመሰክራል። እርሱ በአድራጎትም ሆነ በባሕርይ ኃጢአት አልነበረበትም። 1ኛ ዮሐንስ 3፡5፥ «በእርሱም ኃጢአት የለም» ይላል። በእነዚህ በሁለቱም ጥቅሶች የተነገረው ኢየሱስ ኃጢአትን እንዳላደረገና ኃጢአትንም የመፈጸም ዝንባሌ እንዳልነበረው ነው። ስለሆነም በምንም ዓይነት መልኩ ኢየሱስ ኃጢአትን አያውቀውም። ከዚህም በስተቀር የኃጢአት ባሕርይ አልነበረውም። ኢየሱስ ከግል ኃጢአት ነፃ ሲሆን፥ የሰው ልጆች ሁሉ የወረሱትን የኃጢአት ባሕርይ እርሱ አልወረሰም። 

ኢየሱስ ኃጢአትን እንዲያደርግ በእውነት ተፈትኖአል 

ምንም እንኳን ኢየሱስ ኃጢአት ባያደርግም፥ ኃጢአት እንዲሠራ መፈተኑን መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያስረዳል። ዕብራውያን 4፡15 በሰብአዊ አእምሮአችን ውስጥ ሁለት ተቃራኒ አሳቦችን የሚጨምር ጠቃሚ ጥቅስ ነው። አንድ ሰው በሚፈተንበት ሁኔታ ኢየሱስም ተፈትኖአል። ይህ ማለት ሰዎችን ያጋጠማቸው የፈተና ዓይነት ሁሉ እርሱንም አጋጥሞታል ማለት ነው። በሥጋ ፍላጎት ተፈትኖአል። በዓይን አምሮትም ተፈትኖአል። እንደዚሁም በኑሮ ትምክህትም ተፈትኖአል (1ኛ ዮሐንስ 2፡16)። ኃጢአትን ለመሥራት መፈተን ማለት በፈተና መሸነፍ ማለት አይደለም። መፈተን ራሱ ኃጢአት አይደለም። ስፈተና መሸነፍ ግን ኃጢአት ነው። ምንም እንኳን ኢየሱስ ኃጢአትን እንዲያደርግ ቢፈተንም፥ በፈተና አልተሸነፈም። ኃጢአትም አላደረገም። 

አንዳንድ ጊዜ እኛ አማኞችም ፈተና ያጋጥመናል፥ ነገር ግን ግን በዚህ ፈተና እንወድቃለን ማለት አይደለም። በቁጣ፥ አንዳችን ነገር በመስረቅ፥ በመመኘት፥ ወይም በውሸት እንፈተን ይሆናል። በዚህ ፈተና እንሸነፋለን ማለት አይደለም። ነገር ግን ሰይጣን ይመጣና ስለተፈተንን ብቻ ጸጸት ውስጥ እንድንገባ ያደርጋል። ስለሆነም በመፈተን ብቻ የሚመጣ ጸጸት የሰይጣን የሆነ ሐሰተኛ ጸጸት ነው። ኢየሱስም ቢሆን ተፈትኖአል። መፈተን ደግሞ ክፋት የለውም። ችግሩ ወደ ፈተና ገብቶ ኃጢአትን መሥራቱ ላይ ነው። 

ኢየሱስ በሕይወቱ ሙሉ ፈተና ሊደርስበት፥ ያንን ፈተና እንዴት እንደ ተወጣው ሁሉንም አናውቅም። ነገር ግን ኢየሱስ በምድረ በዳ ያጋጠመውን ፈተና እንዴት እንደ ተጋፈጠው መጽሐፍ ቅዱስ ዝርዝር ሁኔታውን ያስረዳናል። ይህን ማስረጃ በማጥናት ኢየሱስ እንደ ሰው ያጋጠመውን ፈተና ሁሉ እንዴት ባለ መንገድ እንደ ተወጣው በብዙ ልንማር እንችላለን። 

ጥያቄ፡- ሀ) ዘፍጥረት 3፡6 አንብቡ። ሔዋን በየትኞቹ ሦስት መንገዶች ተፈተነች? ለ) 1ኛ ዮሐንስ 2፡16 እንብቡ። እኛስ በየትኛቹ ሦስት መንገዶች ነው የምንፈተነው? 

ጥያቄ፡- ሉቃስ 4፡1-13 እና ማቴዎስ 4፡1-1 አንብቡ። ሀ) ኢየሱስን ስላጋጠሙት ሦስት ፈተናዎች ጻፉ። ለ) ኢየሱስ ድንጋዩን ወደ ዳቦ ለውጦት ቢሆን ኖሮ ስሕተቱ ምን ላይ ይመስላችኋል? ሐ) ኢየሱስ ከቤተ መቅደስ ጫፍ ላይ ቢዘል [ ኖሮ ስሕተት ይሆን የነበረው ለምን ይመስላችኋል? መ) ኢየሱስ እንዴት እነዚህን ፈተናዎች ተቃወመ? ሠ) የኢየሱስ ፈተናዎች ከአዳምና ከሔዋን ፈተናዎች የሚመሳሰለው እንዴት ነው? ልዩነታቸውስ ምኑ ላይ ነበር? 

ሉቃስ የኢየሱስን የፈተና ታሪክ በጻፈ ጊዜ ኢየሱስን ከአዳምና ከሔዋን ጋር እንድናነጻጽር የፈለገ ይመስላል። ኢየሱስ ባጋጠመው ፈተና ላይ ድልን የተቀዳጀ ሲሆን፥ በአንጻሩ አዳምና ሔዋንን በፈተናው መሸነፋቸውን ልብ እንድንል የፈለገ ይመስላል። ሉቃስ ስለ ኢየሱስ ፈተና ታሪክ ከመናገሩ በፊት ስለ ዘር ሐረጉ ይዘረዝርና ከአዳም ዘር ሲወርድ ሲዋረድ ስለመምጣቱ ያወሳል። ይህ እንግዲህ አእምሮአችንን አዳምና ሔዋን ወደነበሩበት ወደ ኤድን ገነት መልሶ ይወስደዋል። ከዚያም አዳምና ሔዋንን የሥጋ ምኞት፥ የዓይን አምሮትና የኑሮ ትምክህት ፈተና (ዘፍጥ. 3፡6) እንዳጋጠማቸው ሁሉ፥ ኢየሱስንም የሥጋ ፈተና፥ ድንጋዩን ወደ ዳቦ የመለወጥ እንዲሁም የዓይን አምሮት ፈተና፥ የዓለምን መንግሥታት በሙሉ የማግኘት እና የሕይወት ትምክህት ፈተና (በሕዝቡ ዘንድ ለመታወቅ ራስን ከቤተ መቅደሱ ወደ ታች የመወርወር) ፈተና እንዳጋጠመው ይገልጽልናል። ነገር ግን በኢየሱስ፥ በአዳምና በሔዋን መካከል፥ አንዳንድ ልዩነቶች ነበሩ። ኢየሱስ በምድረ በዳ ውስጥ ተፈተነ። አዳምና ሔዋን ግን በኤድን ገነት ውስጥ ተፈተኑ። ኢየሱስ በረሃብ በደከመ ጊዜ ተፈተነ፥ አዳምና ሔዋን ግን በምግብ ተከብበው ተፈተኑ። አዳምና ሔዋን ፈተናውን መቋቋም አቅቷቸው ወደቁ፥ ኢየሱስ ግን እነርሱ የወደቁበትን ፈተና አሸነፈ። 

ሰይጣንን የማምለክ ፈተና ኃጢአት መሆኑን መገንዘብ ቀላል ነው። ምን ጊዜም ቢሆን በእግዚአብሔር ፈንታ ለማንም ለምንም መስገድ ኃጢአት ነው። ነገር ግን የተቀሩት የሰይጣን ፈተናዎች ኃጢአት ስለመሆናቸው መገንዘብ ያዳግታል። ለምሳሌ ያህል፥ ኢየሱስ ድንጋዩን ወደ ዳቦ መለወጡ ኃጢአት ይሆንበት ነበር? ኢየሱስ ኋላ ላይ ውኃውን ወደ ወይን ለውጦአል። ጥቂቱን ዳቦና ጥቂቱን ዓሣ አብዝቶአል። በዚህን ጊዜ ምግብን ማዘጋጀት ኃጢአት የሚሆነው ለምንድን ነው? መልሱ ኢየሱስ መለኮታዊ ኃይሉን ለሥጋዊ ፍላጎቶቹ ማዋሉ የአብ ፈቃድ ስላልነበረ ነው። ምንም እንኳን ኢየሱስ ሙሉ በሙሉ እግዚአብሔር ቢሆንም እንደ ሰብዓዊ ፍጡር እንዲኖር የእግዚአብሔር ፈቃድ ነበር። ኢየሱስ መለኮታዊ ኃይሉን ያሳይ የነበረው አብ እንዲያሳይ ፈቃዱ ሲሆን ብቻ ነበር። ኢየሱስ ከዘዳግም 8፡3 ጠቅሶ ለሰይጣን ሲመልስ፥ «ሰው በእግዚአብሔር ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም» አለው። ይህ ጥቅስ ሙሴ በምድረ ባዳ ለእስራኤል ልጆች ከተናገረው ቃል የተገኘ ነው። የዕለታዊ ምግባቸውንም እንኳ የሚሰጣቸው እርሱ መሆኑን የእስራኤል ልጆች እንዲያምኑ ሙሴ እግዚአብሔር መና እንደ ላከላቸው ነገራቸው። በኦሪት ዘዳግም እንደተጻፈው ለእስራኤል ልጆች እግዚአብሔር የዕለት ምግባቸውን እንደሚሰጣቶው ማመን እንዳለባቸው ሁሉ፥ ኢየሱስም ለዕለት ምግቡ እንዲተማመን የእግዚአብሔር ፈቃድ ነበር። ኢየሱስ ለዕለት ምግቡ እግዚአብሔርን በማመን ፈንታ በራሱ ታምኖ ቢሆን ኖሮ ኃጢአት በሆነ ነበር። 

ጥያቄ፡- ሀ) በራሳችሁ እንድትታመኑ የሚጋብዙአችሁ አንዳንድ ቀላል ነገሮች ምንድን ናቸው? ለ) ለእነዚያ ነገሮች እግዚአብሔር እንድትታመኑበት የሚፈልግባችሁ እንዴት ነው? 

አንዳንድ ጊዜ ቀላል ለሆኑ ነገሮች በራሳችን የመታመን ፈተ ያጋጥመናል። በቂ ምግብ በቤታችን ውስጥ በሚኖረን ጊዜ ለዕለት ምግባች በእግዚአብሔር መተማመን እንዳለብን ረስተን፥ በራሳችን መታመ’ እንጀምራለን። ሥራ አግኝተን ደመወዛችን ከፍ ያለ ሆኖ የምንፈልገው ሁሉ ስንገዛ ይህንን በሰጠን አምላክ መተማመን ትተን በራሳችን መታመ እንጀምራለን። የሚወዱን ወዳጆችና ቤተሰብ ሲኖሩን እግዚአብሔር ማመስገን ትተን በራሳችን መታመን እንቀጥላለን፥ እንደዚሁም ጤናማዎች ጠንካሮች በምንሆንበት ጊዜ ይህን በአደረገልን አምላክ መተማመን ትተን ክብሩን ለራሳችን እንሰጣለን። እግዚአብሔር ግን ይህን ሁሉ የለገሰን እርሰ መሆኑን እንድናስታውስ ይፈልጋል፥ እናም እነዚያን ጥቃቅን የሆነ ፍላጎቶቻችንን ለወደፊቱም ቢሆን እንዲያሟላልን በእርሱ መታመ’ አለብን። 

ኢየሱስ ከቤተ መቅደስ ጫፍ ራሱን ወደ ታች ቢወረወር፥ ለሕተት የሚሆነው ለምንድን ነው? ኢየሱስ ራሱን ከቤተ መቅደስ ጫፍ ቁልቁል ወርውሮ ቢሆን ኖሮ እግዚአብሔር በተአምር እንዲያተርፈው ባስገደደወ ነበር። ኢየሱስ ይህን በማድረጉ አብ በሕይወት ላይ የነበረውን ሥልጣ በካደ ነበር። ኢየሱስ ታምራትን የሚያደርግበትን ጊዜና ስፍራ አብ የሚወስንበትን ሥልጣን በካደ ነበር። ኢየሱስ ሰይጣን ለአቀረበለት ጥያላ ኦሪት ዘዳግም 6፡16 ጠቅሶ እንዲህ ሲል መልሶለታል፥ «እግዚአብሔር እምላክህን አትፈታተን።» ይህ ጥቅስም ሙሴ በምድረ በዳ ለእስራኤል ልጆች ከተናገረው ቃል የተወሰደ ነው። እግዚአብሔር ውኃ በተአምር እስካልሰጠን ድረስ አልተንከባከበንም ማለት ነው ብለው በእርሱ ላይ መቆጣታቸውና ማጉረምረማቸው ኃጢአት መሆኑን ሙሴ ይነግራቸዋል፡ በዚሁ ረገድ ኢየሱስም አባቱን ተአምር በመሥራት ከጉዳት እንዲጠብቀወ አስገድዶት ቢሆን ኖሮ ኃጢአት በሆነበት ነበር። ምንም ጊዜ ቢሆ እግዚአብሔር እኛን ለመርዳት ተአምር አላዳረገም ብሎ ማጉረምረም ኃጢአት ነው። 

ጥያቄ፡- ሀ) እግዚአብሔር አልተንከባከበኝም ብላችሁ ያማረራችሁት መላ ነበር? ለ) እግዚአብሔር ተአምር አላደረገም ብላችሁ የተበላጫችሁትስ መቼ ነበር ሐ) እግዚአብሔር እንዲህ ባሉት ሁኔታዎች እንዴት ያለ ምላሽ እንድትሰጡት ይፈልግ ነበር? 

አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር እኛ በፈለግነው መንገድ ነገሮችን ሳያደርግልን ሊቀር እንቆጣለን። ለምሳሌ፥ ታመን ወይም ጉዳት ደርሶብን ሳንድን ለረጅም ጊዜ ብንቆይ፥ እግዚአብሔር አልፈወሰንም ብለን በቀላላ እናማርረዋለን። የምንወደው ሰው ሲታመም ወይም ሲሞት እግዚአብሔርን ማማረር የተለመደ ነው። እንደዚሁም በፈተና ስንወድቅም ሆነ ከሥሪ ስንወጣ እግዚአብሔርን ማማረር ይቀልለናል። በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች ብናማርረውም እግዚአብሔር ከእኛ የሚፈልገው ተግባራችን ሁሉ ፍሬ እንዲያፈራ፥ እርሱም ሊንከባከበን እንዲችል እኛ በእርሱ ብቻ እንድንተማመንና እንድንደገፍ ነው። እግዚአብሔርን በይሁንልኝ ጥያቄ ልንጎተጉተው አይገባም። እኛ ማድረግ ያለብን እርሱ በፈቀደው መንገድ ፍላጎታችንን እንዲያሟላልን በእርሱ ብቻ መተማመን ነው። 

ኢየሱስ የዓለምን መንግሥታት ክብር ለማግኘት ብሎ ለሰይጣን ወድቆ ሲሰግድለት ኖሮ፥ ድርጊቱ ኃጢአት ሊሆን መቻሉን መገንዘብ አያዳግትም። ለዚህም መልስ ለመስጠት ዘዳግም 6፡13 ጠቅሶ ለሰይጣን እንዲህ ብሏል፤ «ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ»። ይህም ጥቅስ የእስራኤል ልጆች ለወርቁ ጥጃ በሰገዱ ጊዜ ሙሴ ከተናገረው ማሳሰቢያ የተወሰደ ነው። የእስራኤል ልጆች ያላንዳች ችግርና ፈተና ወደ ተስፋይቱ ምድር የሚያስገባቸውን አምላክ ይፈልጉ ነበር። ሰይጣንም ለኢየሱስ ያቀረበለት ፈተና፥ ምንም ዓይነት ችግር ሳይደርስበትና በመስቀልም ላይ መሞት ሳይኖርበት፥ የመላው ዓለም ንጉሥ የሚሆንበትን ፈተና ነበር። የዚህ ዓለም አማልክት ሁልጊዜ የሚያቀርቡልን የምንፈልገውን ነገር በቀላሉ የምናገኝበትን ሁኔታ ነው። ነገር ግን እነርሱን መከተል ከእግዚአብሔር የተለየ ነገር ማምለክ ነው። ከእግዚአብሔር የተለየ ሌላ ነገርን ማምለክ ወይም መስገድ ደግሞ ምንጊዜም ቢሆን ኃጢአት ነው። 

ጥያቄ፡- ሀ) በአሁኑ ሰዓት በሕይወታችሁ ውስጥ ምን ዓይነት ዓላማና ምኞት አላችሁ? ስለ ትምህርት፥ ስለ አገልግሎታችሁ ስለምትገዟቸው ነገሮች፥ እንዲሁም ይጠቅሙናል ስለምትሏቸው ግንኙነቶች አስቡ። ስለዚህ አሁን በሕይወታችሁ ስላሉ ቢያንስ ሦስት ዓላማዎችና ምኞቶች ጻፉ። ለ) ሰይጣን እነዚህን ዓላማዎችና ምኞቶች የእግዚአብሔር ፈቃድ ባልሆነ መንገድ እንድታገኙ ለማድረግ እንዴት እየተፈታተናችሁ ነው? ሐ) እነዚህን ግቦችና ምኞቶች በተግባር ላይ እንድታውሉ የእግዚአብሔር መንገድ ምንድን ነው? 

ብዙ ጊዜ ሰይጣን ግባችንን የእግዚአብሔር ፈቃድ ባልሆነ መንገድ እንድንደርስበት ይፈትነናል። ፈተና አጭበርብረን በማለፍ ወደ ትምህርት ግባችን እንድንደርስ ይፈታተነናል። የተጭበረበረ የሥራ ማመልከቻ በማቅረብ ወደ ሥራ ግባችን እንድንደርስ ይፈታተነናል። ከሌሎች ሰዎች ጋር እንዲኖረን ለምንፈልገው ጥሩ ግንኙነት ባሕርያችን በኃጢአት እንዲደፈርስ ያደርጋል። እንዲኖረን የምንፈልገውን ንብረት ለማግኘት ማስተዋል በጎደለው ሁኔታ ገንዘብ እንድንበደር ወይም እንድንሰርቅ ያበረታታናል። የእግዚአብሔር ፈቃድ የሕይወታችንን ግብ እንደ እግዚአብሔር ትእዛዛት እንደ ቃሉ መመሪያ እንድናደርገው ነው። 

ሰይጣን ለኢየሱስ ለአቀረበለት ፈተና ሁሉ፥ ኢየሱስ ተገቢውን መልስ የሰጠው ቅዱሳት መጻሕፍትን በመጥቀስ መሆኑን ልብ በሉ። ጌታ ኢየሱስ መጽሐፍ ቅዱስን በሚገባ ያውቅ ስለ ነበር፥ ሰይጣን ለአቀረበለት ለእያንዳንዱ ፈተና ተገቢውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ እየጠቀሰ መልስ ሰጠ። ለክርስቲያኖች በፈተና ላይ ድልን የመቀዳጀት አንዱና በጣም ጠቃሚው ዘዴ የእግዚአብሔርን ቃል ማጥናትና በቃል ይዞ ማስታወስ ነው። በዚህ ሁኔታ አእምሮአችን በእግዚአብሔር ቃል ሊሞላ፥ ሰይጣን ፈተናውን ይዞ በሚቀርበን ጊዜ ወዲያው ከእግዚአብሔር ቃል ተገቢውን መልስ መስጠት እንችላለን። 

ጥያቄ፡- ኢየሱስ ሰይጣን ለአቀረባቸው ጥያቄዎች ከመላሳቸው ጥቅሶች መካከል አንዱን መርጣችሁ አሁን በቃል አጥኑ። 

ኢየሱስ ምንም ዓይነት ኃጢአት አለመፈጸሙን በግልጽ ተምረናል። ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ኢየሱስ ኃጢአት ሊሠራ ይችል ነበር? ብለው ይጠይቃሉ። ኢየሱስ አንዳችም ኃጢአት አለመሥራቱ ቢታወቅም ኃጢአት መሥራት ግን ይቻለው ነበር? በዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ጥርት ያለ መልስ አይሰጠንም። ኢየሱስ ኃጢአት ሊሠራ ይችላል ወይም አይችልም ብሎ በግልጽ የሚነግረን ጥቅስ የለም። ነገር ግን ሆኖም እንዲህ ላለው ጥያቄ መልስ ሊሆኑ የሚችሉ ጥቂት ጥቅሶች ይኖራሉ። በመጀመሪያ፥ ኢየሱስ ሰው መሆኑን እናውቃለን። ዕብራውያን 2፡18 እና 4፡5 ኢየሱስ እንደ እኛው ሰው በመሆኑ ያለ ጥርጥር እንደ ተፈተነ ይነግረናል። ኢየሱስ ልክ እንደ እኛው ኃጢአት የመፈጸም ፍላጎት ነበረበት። ሁለተኛው፥ ነገር ግን ነገር ኢየሱስ እግዚአብሔርም ነበረ። ያዕቆብ 1፡13 በግልጽ እንደሚነግረን እግዚአብሔር ኃጢአትን ለመሥራት ጨርሶ አይፈተንም ይላል። ኢየሱስ ሰው ብቻ ቢሆን ኖሮ፥ ኃጢአት ባደረገ ነበር። በአንጻሩም ኢየሱስ እግዚአብሔር ብቻ ቢሆን ኖሮ ደግሞ፥ ኃጢአትን የመሥራት ስሜት ባላደረበት ነበር። ነገር ግን ኢየሱስ ፍጹም ሰው ብቻ ወይም ፍጹም አምላክም ብቻ አልነበረም። እርሱ ሰውም አምላክም ነበር። ታዲያ እርሱ ሰው ስለነበረ ኃጢአትን የመሥራት ስሜት ነበረበት። ደግሞም እግዚአብሔር ስለነበረ ኃጢአትን አይሠራም ነበር። ግን ሰውም አምላክም በመሆኑ፥ የኃጢአት ፈተና ቢያጋጥመውም ኃጢአትን የመሥራት ባሕርይ ሊኖረው አይችልም። ሆኖም ኢየሱስ የሰይጣንን ፈተና ያሸነፈው በአባቱ ፈቃድ በመታመን መሆኑን ተመልክተናል። እርሱ አምላክ ሆኖ ሳለ በመለኮታዊ ባሕርይውና በኃይሉ ሳይጠቀም ፈተናውን ሊቋቋም ችሎአል። በእርግጥ የፈተናው ጽናት ተሰምቶታል። ያጋጠመውንም ፈተና ለማሸነፍ በእግዚአብሔር ኃይል ታምኖአል። ደግሞም መታዘዝን ተምሮአል (ዕብራውያን 5፡8)። 

ሉቃስ 4፡1-18 እና ማቴዎስ 4፡1-11 በትክክል ኢየሱስን ፈተና እንዳጋጠመው ሲነግሩን፥ በፈተናው ተሸንፎ ኃጢአት አለመሥራቱንም በግልጽ ያስረዱናል። ዕብራውያን 2፡18 እና 4፡5 ኢየሱስ እንደ እኛ የተፈተነ እና ተፈትኖም ኃጢአትን ያላደረገ በመሆኑ፥ እኛንም ፈተና በሚያጋጥመን ጊዜ ሊራራልንና ሊረዳን ዝግጁ መሆኑን ይገልጽልናል። 41ኛ ጥያቄ፡- በዚህ ሳምንት ምን ፈተና አጋጥሞአችኋል? በየትኞቹ ፈተናዎች ተሸንፋችሁ ኃጢአት ሠራችሁ? ኢየሱስ ስለ እናንተ ስላለው ርኅራኄ የቆይታ ጊዜ አድርጋችሁ ጸልዩ። እርሱ እኛ ከኃጢአት ጋር የምናደርገውን ትግል ይገነዘባል። ኢየሱስን ለለ ርኅራኄው አመላኑት። በዚህ ሳምንት በፈተና ላይ ድልን እንድትቀዳጁ እርሱ ይረዳችሁ ዘንድ ኃይልም ይሰጣችሁ ዘንድ ጸልዩ።

ምንጭ፡- “አስተምህሮ ክርስቶስና ደኅንነት”፤ ጽሑፍ፣ በዶ/ር ስቲቭ ስራውስ፤ ትርጉም በኃይሉ ልመንህ

Exit mobile version