ክርስቶስ ሰው የሆነበትና፥ እንደ ሰውም የኖረበት ምክንያት፥ በመስቀል ላይ ለመሞት ነበር። ምንም እንኳን የኢየሱስ ቅዱስ ሕይወት ለእኛ ምሳሌ ቢሆንም፥ ስለ መንግሥቱ የሰጠው ትምህርትም ለሕይወታችን ተስፋና መመሪያ ሆኖ ቢያገለግለንም፥ ኢየሱስ የፈጸመልን ታላቁ ተግባር ስለ እኛ መሞቱ ነው። የእርሱ መሰቀል የመላ ሕይወቱ ትኩረትና ከፍተኛው ድርጊት ነው። በዚህ መጽሐፍ ሁለተኛው አጋማሽ ላይ፥ ስለ ክርስቶስ ሞትና ለመዳናችን ስለሚያበረክተው ትርጉም በዝርዝር እንነጋገራለን። ሆኖም በኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ሰዎች ኢየሱስ በሞተ ጊዜ በእርግጥ ምን እንደሆነ ጥያቄዎች አሉዋቸው። ዛሬ ከእነዚህ ጥያቄዎች ውስጥ ጥቂቶቹን ለመመለስ እንሞክራለን። ይህ በተለይ ለኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ጠቃሚ ነው።
1. ኢየሱስ በእውነት ተሰቅሎ ነበር?
የእስልምና እምነት ተከታዮች ኢየሱስ ተሰቅሎአል የሚለውን አስተሳሰብ ፈጽመው አይቀበሉትም። እነርሱ ኢየሱስ ነቢይ መሆኑን ያምናሉ። አላህ ደግሞ ከነቢያት መካከል አንዱ የሆነውን ኢየሱስን ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ የወንጀለኛ ሞት እንዲሞት አያደርግም ይላሉ። ስለዚህ ብዙ ሙስሊሞች እግዚአብሔር ስኢየሱስ ፋንታ ሌላ ሰው በመስቀል ላይ ተክቶ እንዲሰቀል አድርጓል ባይ ናቸው። አንዳንዶቹ ደግሞ ይህ ምትክ የተሰቀለ ሰው ይሁዳ ነበር ይላሉ።
ክርስቲያኖች ሙስሊሞች ለሆኑ ወዳጆቻቸው፥ ለዚህ ታሪካዊ መረጃ ዎችን በማቅረብ ሊመልሱላቸው ይችላሉ። በመጀመሪያ፥ አራቱ ወንጌላትና ሌሎች የአዲስ ኪዳን በርካታ መጻሕፍት፥ ኢየሱስ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ስለ መሞቱ በግልጽ ያስተምራሉ። ሙስሊሞች ብዙ ጊዜ ሲናገሩ፥ ክርስቲያኖች እውነተኞችን ወንጌላት ለውጠዋል ይላሉ። ነገር ግን አብዛኛዎቹ የጥንት አዲስ ኪዳን ቅጂዎች፥ ዛሬ በእጃችን ከሚገኙት ወንጌላት ጋር ተመሳሳይና ይዘት የማይለያዩባቸው እንዲሁም ከጥንታውያን ቅዱሳት መጻሕፍት መካከል ኢየሱስ አልሞተም የሚሉ የሉም። ሁለተኛ ክርስቲያኖች ያልነበሩ ጥንታውያን የታሪክ ምሑራን ሳይቀሩ፥ ኢየሱስ መሞቱን መስክረዋል። አይሁዳዊ የታሪክ ሰው የነበረውና ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ70ኛው ዓመተ ምሕረት አካባቢ የኖረው ጆሲፈስ ኢየሱስ ታዋቂና ታሪካዊ ሰው መሆኑን ጠቅሶ፥ በጲላጦስ ትእዛዛት መሰቀሉን ጽፉአል። እንዲሁም ኢየሱስ መሢሕ መሆኑን ያልተቀበሉ አይሁድ ጸሐፊዎች የጻፉዋቸው ሌሎች መጻሕፍትም ኢየሱስ መሰቀሉን ተስማምተውበታል። ታይተስ የተባለው ሮማዊ ታሪክ ጸሐፊ፥ ጲላጦስ ኢየሱስን እንደ ሰቀለው ጽፎአል። የታሪክ ማስረጃዎች የሰጡት ምስክርነት በግልጽ የኢየሱስን መሰቀል የሚያረጋግጥ ነው።
ጥያቄ፡- ክርስቶስ ስለ መሰቀሉ፥ ሙስሊም ለሆኑ ወዳጆቻችሁ ልትገልጹላቸው የምትችሉት ምን ማስረጃ አለ?
ክርስቶስ በእርግጥ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ የሞተ መሆኑን፥ ክርስቲያኖች ለሙስሊም ወዳጆቻቸው ታሪካዊ መረጃ ዎችን በማቅረብ ሊያረጋግጡላቸው ይችላሉ። ነገር ግን እንደ እውነቱ ከሆነ ኢየሱስ መሰቀሉን ሙስሊሞች አምነው የማይቀበሉበት ምክንያት፥ ኢየሱስ የኃጢአትን ቅጣት ሊከፍል በመስቀል ላይ በመሥዋዕትነት ተሰቅሎ መሞት እንደ ነበረበት ስላልገባቸው ነው። ስለዚህ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ መሞት ያስፈለገበትን ምክንያት፥ ክርስቲያኖች ለሙስሊሞች ወዳጆቻቸው በትዕግሥትና በፍቅር ሊገልጹላቸው ይገባል። ይህንንም በዚሁ መጽሐፍ በሁለተኛው አጋማሽ ላይ እንወያይበታለን?
2. ኢየሱስ ያለ ኃጢአት ነበር። ስለዚህ መሰቀል አልነበረበትም።
ስለ ኢየሱስ ሞት መገንዘብ የሚገባን ሁለተኛው እውነታ እርሱ በሞተ ጊዜ ያለ ኃጢአት እንደ ነበር ነው። ምንም እንኳን እንደ ወንጀለኛ ተቆጥሮ በአደባባይ ተሰቅሎ ሲሞትም፥ ለሞት የሚያበቃው ወንጀል ከቶ አልፈጸመም። እንደ እውነቱ ከሆነ፥ በመላ ሕይወት ዘመኑ ምንም ዓይነት ስሕተት አልሠራም።
ጥያቄ፡- ማቴዎስ 2722-25፤ ሉቃስ 23፡4፥ 22 አንብቡ። ጲላጦስ በመጨረሻው ኢየሱስ ላይ ምን አደረገ?
ጥያቄ፡– በክፍል ሁለት ትምህርታችን ላይ፥ ኢየሱስ ኃጢአት መሥራቱን ወይም አለመሥራቱን አጥንተን ነበር። በዚያን ጊዜም ማቴዎስ 26፡59-60፤ ዮሐንስ 8፡46፤ ዕብራውያን 4፡15፤ 1ኛ ጴጥሮስ 2፡22፤ 2ኛ ቆሮንቶስ 5፡21 እና 1ኛ ዮሐንስ 35ን አንብበናል። አሁን የሰጣኋቸውን መልሶች አንብቡ። ታዲያ ኢየሱስ ኃጢአት ስለ መሥራቱ፥ ወይም ስላለመሥራቱ የእናንተ መደምደሚያ አሳብ ምንድን ነው?
ጥያቄ፡- ዘሌዋውያን 4፡3፥22 አንብቡ። ለኃጢአት ይቅርታ ምን ዓይነት መሥዋዕት ይቀርብ ነበር?
ጥያቄ፡- 1ኛ ጴጥሮስ 1፡18-19 አንብቡ። በቁጥር 19 ላይ ክርስቶስ ምን ዓይነት በጎ ተብሎ ተገለጸ?
ኢየሱስ ጲላጦስ ፊት ቀርቦ ክሱ በተሰማ ጊዜ፥ ጲላጦስ ውሳኔውን ግልጽ አድርጎት ነበር። ይኸውም ኢየሱስ ምንም ዓይነት ወንጀል አለመሥራቱ ነበር። ታዲያ ጲላጦስ የማያዳላና ጽድቅን የተከተለ ፍርድ የሚሰጥ ዳኛ ቢሆን ኖሮ፥ ኢየሱስን በነፃ ባሰናበተው ነበር። ዳሩ ግን ጲላጦስ ሕዝቡን ፈራ። ክፍርሃቱም የተነሣ፥ ኢየሱስ እንዲሰቀል አሳልፎ ሰጠው። ጲላጦስ ኢየሱስ ከምንም ዓይነት ወንጀል ነፃ ነው ብሎ ማሳወቁ፥ ስለ ኢየሱስ አጠቃላይ ሕይወት መልካም ድምጻሜ ሆኗል። በዚህ ረገድ ኢየሱስ ፈጽሞ ኃጢአት ላለመሥራቱ አዲስ ኪዳን አቋሙ ግልጽ ነው። በኢየሱስ ዘመን የነበሩ ሰዎችም፥ እርሱን የሚከሱበት አንዳችም ኃጢአት አላገኙበትም (ዮሐ. 8፡46፤ ማቴዎስ 26፡59-60)። ጴጥሮስ (1ኛ ጴጥሮስ 2፡22)፥ ጳውሎስ (2ኛ ቆሮ. 5፡20፥ ዮሐንስ (1ኛ ዮሐ 3፡5) እንደዚሁም የዕብራውያን ጸሐፊ (ዕብራውያን 4፡5)። ሁላቸውም ኢየሱስ ምንም ዓይነት ኃጢአት ላለመሥራቱ፥ በአንድ ድምፅ ይመሰክሩለታል።
ኢየሱስ ኃጢአት ያልሠራ ሰው ሆኖ ስለ መሞቱ በሚገባ መገንዘብ በጣም ጠቃሚ ነው። የብሉይ ኪዳን ሕግ እንደሚያስተምረው፥ ለኃጢአት ይቅርታ የሚቀርበው እንስሳ ንጹሕ መሆን እንደ ነበረበት ነው። ስለዚህ መሥዋዕት የሚሆነው እንስሳ ፍጹም መሆን ይጠበቅበት ነበር። የዓለምን ኃጢአት ለማስወገድ መሥዋዕት የሆነው ክርስቶስም ያላንዳች ነውር ፍጹም መሆን ነበረበት። 1ኛ ጴጥሮስ 1፡19 ኢየሱስን፥ ነውር የሌለበት ንጹሕ ስግ ሲል ይገልጸዋል። ስለሆነም ኢየሱስ ፈጽሞ ኃጢአት አላደረገም። እርሱ ሙሉ በሙሉ ፍጹም ነበር። ሮማውያን አደገኛ የሆኑ ወንጀለኞችን ስስቅላት ይቀጡዋቸው ነበር። ኢየሱስም በመስቀሉ፥ ትልቅ ወንጀል እንደ ሠራ እየተቀጣ ያለ ይመስል ነበር። ግን ኢየሱስ ከሕግ ውጭ የተሰቀለ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያስረዳል። እርሱ ከማንኛውም ወንጀል ነፃ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፥ ከምንም ዓይነት ኃጢአትም ነፃ ነበር።
3. ኢየሱስ በሞተ ጊዜ በአካሉ ላይ ምን ደረሰ?
ስቅላት በዘመናት ውስጥ ከታዩት የቅጣት ዓይነቶች ሁሉ ጭካኔ የተሞላበት አሰቃቂ የሆነ የቅጣት ድርጊት ነው። የስቅላት ቅጣት በመጀመሪያ የተጀመረበት ምክንያት ሰውን እያሠቃየ ቀስ በቀስ ወደ ሞት እንዲያደርስ ነው። የስቅላት ፍርድ የሚፈጸምባቸው ሰዎች ራቁታቸውን በመስቀሉ ላይ ተዘርግተው በምስማር በሚሰቀሉበት ግንድ ላይ ይቸነከራሉ። በእያንዳንዱ የእጅ መጋጠሚያ ላይ አንዳንድ ምስማር ይመታል። ከዚያም በሁለቱ የእግሮቹ ቁርጭምጭሚቶች ላይ አንዳንድ ምስማር ይቸነከራል። ከዚያም የመስቀያው ግንድ ብድግ ተደርጎ ጉድጓድ ውስጥ በኃይል ይተከላል። በዚህን ጊዜ የተሰቀሉት ሰዎች ጡንቻዎቻቸውና ብልቶቻቸው ከውስጥ ስለሚተረተሩ የሚያሳቅቅ ሕመም ይሰማቸዋል። ከዚህ ሕመም የተነሣ በስቅላቱ ላይ ያሉ ሰዎች ብዙ ጊዜ መጀመሪያ ላይ ራሳቸውን ይስታሉ፥ ሆኖም ብዙ ሳይቆይ አእምሮአቸው መለስ ይልሳቸዋል። ክርስቶስ በተሰቀለ ጊዜ በመስቀል ላይ ሳለ በሰውነቱ ላይ ስለደረሰበት ሁኔታ ለመግለጽ፥ ከሌላ መጽሐፍ «የክርስቶስ ሕይወት» “The Life of Christ by Frederick famar” በሚል ርእስ በፍሬድሪክ ፋረር ከተጻፈው መጽሐፍ ረጅም ክፍል ልጠቅለ እወዳለሁ፣ «ተፈጥሮአዊ ያልሆነው አቋሙ እያንዳንዱን እንቅስቃሴ አሰቃቂ ሕመም አድርጎታል፥ የተቀደዱት የደም ሥሮችና የተጨፈለቁት ጅማቶች ሳያቋርጥ የሚያሙት ቁስሎቹ፥ በመጋለጥ ያንገበግቡት፥ ቀስ በቀስም በስብሰው፥ ትልልቅ የደምሥሮች (የደም ቅዳዎች)፥ በተለይም የራሱና የሆድ ዕቃው አብጠውና በደም ግና ተሞልተው፥ እና ሁሉም ሥቃይ እየባሰ ሲሄድ የሚያንገበግብና ፈጽሞ የማይቻል የሚያቃጥል የባለ ጥም ተጨመረበት፡» በመስቀል ላይ የተሰቀለ ሰው ለመተንፈስ አየር ወደ ውስጥ በሚስብበት ጊዜ ሰውነቱ ወደ ላይ ስለሚመዘዝ በምስማር የተቸነከሩ ቁርጭምጭሚቶቹን ይጭናል። ከዚህም የተነሣ ኃይለኛ ሕመም ይሰማዋል። ጡንቻዎቹ ሁሉ ይኮማተራሉ። ከትኩሳቱ ብርታት የተሣም ራሱን ያዞረዋል። ሥቃይ እየበዛ ቢሄድም፣ ሞት ግን ቶሎ አይመጣም። አንዳንድ ሰዎች በተለይ የሚጠጣ ነገር ተሰቅለው ባሉበት ከተሰጣቸው በመስቀል ላይ ለበርካታ ቀናት በሕይወት እንደሚቆዩ ታውቋል። ስቅላት የተፈረደባቸው ሰዎች እንዴት ይሞታሉ? እንደ ልብ ለመተንፈስ ስለማይችሉና መተንፈስም በሚሞክሩበት ጊዜ ሥቃይ ስለሚሰማቸው በትንፋሽ እጥረትና በኦክስጂን እጦት ይሞታሉ። አንዳንዶቹ ሳይሞቱ ለአንድ ወይም ለሁለት ቀናት ቢቆዩም፥ በውኃ ጥም፥ በደም እልቂትና በድካም ይሞታሉ።
ኢየሱስ ግን እናንተንና እኔን ስለ ወደደ የደረሰበትን ሥቃይና ሕማም በትዕግሥት ተቀበለ።
ጥያቄ፡- ኢየሱስ ለእናንተ ሲል በመስቀል ላይ የደረሰበትን መከራ ችሎ በመቀበሉ፥ ምን ይሰማችኋል? እስቲ ይህን ስሜታችሁን በጸሎት ላኢየሱስ ግለጹ።
4. ክርስቶስ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ በነበረበት ጊዜ በመንፈሱ ላይ ምን ደረሰ?
ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሳለ የደረሰበት አሰቃቂ ሥቃይ አካላዊ ሥቃይ ብቻ አልነበረም። በዚህ ጊዜ፥ የደረሰበት አሠቃቂ ሥቃይ፥ የመንፈስ ሥቃይ ነበር። ኢየሱስ አባቱ ጽዋውን እንዲወስድለት በለመነው ጊዜ፥ እጅግ የፈራው በመስቀል ላይ ስለሚገጥመው አካላዊ ሥቃይ አልነበረም (ማቴ 26፡39)። እርሱ ሊያስወግድ የፈለገው ከአባቱ የሚለየውን መንፈሳዊ ሥቃይ ነበር።
ጥያቄ፡- ማቴ. 27፡45-46 አንብቡ። ሀ) ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሆኖ ለሦስት ሰዓታት በቀየበት ጊዜ በምድሪቱ ላይ ምን ደረሰ? ለ) ስለ ኢየሱስ ጩኸት በቁጥር 46 ላይ እንብቡ። በዚህን ጊዜ እርሱ ከእግዚአብሔር አብ ጋር ስላለው ግንኙነት ይህ ክፍል ምን ይላል?
ጥያቄ፡- 2ኛ ቆሮ. 5፡21 አንብቡ። ኢየሱስ ለእኛ ብሎ ምን ሆነ?
በስቅላቱ ጊዜ ወደ ስድስት ሰዓት ማለትም በቀኑ አጋማሽ ላይና ከቀነ ዘጠኝ ሰዓት ላይ በመስቀሉ እካባቢ ባሉ ስፍራዎች ፍጹም ጨለማ ሆነ በዚህኑ ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ ሲል ጮኸ፥ «አምላኬ፥ አምላኬ ለምን ተውከኝ»። ኢየሱስ ይህን ማለቱ የመዝሙር 22፡1 ቃል መጥቀሱ ነበር፡ በዚህን ጊዜ በግልጽ እንደታየው፥ እግዚአብሔር አብ፥ ከእግዚአብሔር ወልደ ጋር የነበረውን ዘላለማዊ ግንኙነት አቋርጦት ነበር። እግዚአብሔር አብ በምን ምክንያት ግንኙነቱን አቋረጠ? ያቋረጠበት ምክንያት በዚህን ጊዜ በመስቀል ላይ ሆኖ የሞትን ጽዋ ይቀበል በነበረው፥ ሰው በሆነው ክርስቶስ ላይ የመላው ዓለም የኃጢአት ሸክም ወድቆ ስለነበረ ነው? 2ኛ ቆሮንቶስ 5፡21 እግዚአብሔር ኢየሱስን ኃጢአት አደረገው ይላል። በወቅቱ በመስቀሉ ዙሪዬ የሰፈነው ጨለማ፥ ኢየሱስ የዓለምን ኃጢአት ለመሽከሙ እውን የሆነ ምልክት ነበር። እግዚአብሔር ከማንኛውም ኃጢአታዊ ነገር ጋር ግንኙነት ሊኖረው ስለማይችል፣ በዚህን ጊዜም ከልጁ ጋር የነበረው ግንኙነት ተቋረጠ። በምድር ላይ የታየው ጨለማ፥ አብ ከልጁ ጋር የነበረው ግንኙነት ለመቋረጡ ምልክት ነበር። የእግዚአብሔር ልጅ፥ ከዘላለም ጀምሮ በፍጹም ፍቅርና፥ በፍጹም ኅብረት ከእግዚአብሔር ጋር የነበረ ቢሆንም፥ አሁን ግን ከአባቱ ተለይቷል። በአባቱ ፍቅር በመርካትና በመደሰት ፈንታ፥ አባቱ በኃጢአት ላይ ባወረደው ቁጣ ሥቃይን ተቀበለ። ኢየሱስ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ በቆየባቸው ሰዓታት ውስጥ በታሪክ ሁሉ እያንዳንዱ ሰው የፈጸመው ዘግናኝና አስከፊ የኃጢአት ጦስ ተሰምቶት ነበር። ብዙ ጊዜ ኃጢአት በምንሠራበት ወቅት በደል ይሰማናል። ከዚህ የተነሣ ከእግዚአብሔር በመለየታችንና፥ ከእግዚአብሔርም ጋር የነበርን ግንኙነት በመቋረጡ እንከፋለን። ጌታ ኢየሱስ እንደ ነፍስ መገደል፥ አስገድዶ መድፈር፥ አመንዝራነትንና ስርቆትን የመሳሰሉትን ዘግናኝ ኃጢአቶች እንዲሁም፥ ሂትለር፥ ስታሊንና መንግሥቱን የመሰሉ ሰዎችንም አስከፊ ኃጢአት በላዩ ላይ ተሸከመው። ኢየሱስ አባቴ በማለት ፈንታ «አምላኬ» ብሎ መጮኹ፥ በዚያን ሰዓት በእርሱና በአባቱ መካከል የነበረው ግንኙነት በአንድ ወንጀለኛና በፈራጅ ዳኛ መካከል እንዳለው ግንኙነት ስለነበረ ነው። ኢየሱስ በዚያኑ ጊዜ ቢሆንም፥ አምላክም ሰውም ነበር። ሆኖም ግን ከአባቱ ጋር ባለው የቤተሰባዊ ኅብረት ሊደሰትበት አልቻለም። በመሆኑም ለሦስት ሰዓታት ከአብ ጋር የነበረው ግንኙነት፥ የኃጢአት ተሸካሚነት ግንኙነት ነበር።
ጥያቄ፡- ኢየሱስ ለዘላለም ከእግዚአብሔር ተለይታችሁ የነበራችሁበትን ያክል ሥቃይ በመስቀል ላይ በመቀበሉ ምን ይሰማችኋል? እስቲ ስሜታችሁን ለእርሱ በጸሎት ግለጹ።
5. ክርስቶስ ከሞተ በኋላ፥ ወደ ሲዖል ወርዶ ነበር?
ስለ ክርስቶስ ሞት አንዳንድ አማኞች የሚያቀርቡት ጥያቄ፥ ኢየሱስ በመስቀል ላይ ከሞተ በኋላ ምን ሆነ? የሚል ነው። አስከሬኑ በመቃብር ውስጥ መቀበሩ ግልጽ ነው። ነገር ግን መንፈሱ ምን ሆነ? የሐዋርያት የእምነት መግለጫ ክርስቶስን፥ «በተሰቀለ፥ በሞተ፥ በተቀበረ ከዚያም ወደ ሲኦል በወረደ እንደ ቅዱሳት መጻሕፍት ቃል በሦስተኛው ቀን ከሙታን በተነሣ» ይላል። ታዲያ ኢየሱስ ከሞተ በኋላ መንፈሱ ወደ ሲኦል ወርዳ ነበር?
ኢየሱስ ከሞተ በኋላ ወደ ሲኦል መውረዱን የሚደግፉ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አሉ። ይሁን እንጂ እነዚህ ጥቅሶች ግልጽ ካለመሆናቸውም በላይ ለመገንዘብ አስቸጋሪዎች ናቸው። እነዚህን ጥቅሶች ከመመልከታችን በፊት፥ ኢየሱስ ከሞተ በኋላ በመንፈሱ ላይ ምን እንደ ደረሰ በግልጽ የሚናገሩትን ጥቅሶች እንመለከታለን።
ጥያቄ፡- ሉቃስ 23፡43 አንብቡ። ሀ) ኢየሱስ ሌባው ሰው በዚያን ቀን የት ይሆናል አለ? ለ) ኢየሱስ በዚያን ቀን የት እንደሚገኝ ተናገረ?
ኢየሱስ በመስቀል ላይ በመሞት ላይ እያለ፥ በጎኑ ከተሰቀሉት ሌቦች መካከል አንደኛው፥ ኢየሱስ ንጹሕ እንደ ነበረና በእውነት እርሱ በእግዚአብሔር የተመረጠና በእርሱም በኩል ደኅንነትን ማግኘት እንደሚችል ተረዳ። ስለዚህ በመሞት ላይ በነበረው ኢየሱስ ስላመነ፥ «ኢየሱስ ሆይ፥ ወደ መንግሥትህ በምትመጣበት ጊዜ አስበኝ» አለ። በዚህ ጊዜ የኢየሱስ መልስ ፥ «ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ» የሚል ነበር። ሌባው ሰው ድኖ ከእርሱ ጋር በዚያኑ ቀን በእግዚአብሔር ፊት እንደሚሆን ኢየሱስ ተስፋ ሰጠው። ይህ የኢየሱስ አነጋገር የሚገልጽልን፥ ከሞተ በኋላ ከእግዚአብሔር ጋር እንደሚሆን ኢየሱስ ራሱ ያውቅ እንደ ነበር ነው። ኢየሱስ ከሞተ በኋላ መንፈሱ እግዚአብሔር ወደሚገኝበት ገባ እንጂ፥ ወደ ሲኦል አልወረደም።
ጥያቄ፡- ዮሐንስ 19፡30 አንብቡ። ሀ) ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት ምን ብሎ ጮኸ? ለ) ኢየሱስ በዚህ ጩኽቱ ምን ለማለት የፈለገ ይመስላችኋል?
ጥያቄ፡- ሉቃስ 23፡46 አንብቡ። ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት ሌላ ምን ብሎ ጮኸ?
ኢየሱስ ልክ ከመሞቱ አስቀድሞ፥ «ተፈጸመ» ብሎ ጮኸ። ይህ ኢየሱስ ያሰማው የጩኸት ቃል፥ አንድ ዕዳ በሙሉ ከተከፈለ በኋላ፥ ዕዳው ሰነድ ግርጌ ከሚጻፈው ቃል ጋር ተመሳሳይ ነው። የዚህ ቃል ትርጉም «በሙሉ ተከፈለ» የሚል ነው። ኢየሱስ ይል የነበረው የመላው ዓለም ሙሉ የኃጢአት ዕዳ ተከፍሏል ነው። እርሱም በመስቀል ላይ፥ የሁሉንም ዓይነት ቅጣት በመቀበል ተሠቃይቷል። ከዚህ በኋላ ላለ ኃጢአት መሠቃየት አላስፈለገውም። የእርሱ ስለ ኃጢአት መሠቃየት ተፈጽሞአል። ኢየሱስ ከሞተ በኋላ ስለ ኃጢአት ተጨማሪ ሥቃይ ለመቀበል ወደ ሲኦል አልወረደም። ስለ ኃጢአት የደረሰበት ሥቃይ ሁሉ፥ በመስቀል ላይ ሆኖ ከአባቱ ጋር በተለያየ ጊዜ ተፈጽሞአል። በተጨማሪም ኢየሱስ ልክ ከመሞቱ በፊት ነፍሱን ለእግዚአብሔር አብ አደራ ሰጥቷል። እንደገናም እግዚአብሔርን «አባቴ» ብሎ ይጠራዋል። ከእግዚአብሔር አብ ጋርም ያለው ግንኙነት ታድሏል። ስለ ኃጢአት የተቀበለው ሥቃይ እንደ ተፈጸመ ያውቃል። ስለዚህ ነፍሱ በአባቱ ፊት በራሱ በአብ መልካም አቀባበል እንደሚደረግለት የተገባ መሆኑን ገለጸ። እነዚህ ጥቅሶች የኢየሱስ ሥቃያ በመስቀል ላይ ስለ ተፈጸመ፥ በመስቀል ላይ ከሞተ በኋላ በሲኦል እንዳልተሠቃየ ያመለክታሉ።
ጥያቄ፡- የሐዋ. ሥራ 2፡26-27 አንብቡ። እግዚአብሔር የኢየሱስን ነፍ ክምን አጻናት?
ሆኖም ኢየሱስ ወደ ሲኦል ወርዷል ፡ የሚለውን አባባል ለመደገፍ አንዳንድ ጊዜ አራት ጥቅሶች ለማስረጃ ይቀርባሉ። የመጀመሪያው ጥቅስ፥ የሐዋ. ሥራ 2፡26-27፡ይህም ከመዝሙር 16፡20 ላይ የተወሰደ) ነው። ቃሉም የኢየሱስ ነፍስ በሲኦል ውስጥ አልቀረችም የሚለው ነው። የሆነ ሆኖ፥ ሲኦል ማለት ብዙ ጊዜ ገሃነም ማለት አይደለም። ብዙ ጊዜ ሲኦል ማለት፥ «መቃብር» ማለት ነው። ጴጥሮስ በዚህ ክፍል ላይ ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ ይናገር ስለነበር፥ በሐዋ. ሥራ 2፡26-27 አሳብ እግዚአብሔር ክርስቶስ ሞቶ እንዲቀር አላደረገም፥ ወይም በመቃብር ውስጥ አልተወውም፥ ይልቅስ ሕያው አደረገው ማለቱ እንደሆነ ግልጽ ነው።
ጥያቄ፡– ኤፌሶን 4፡8-10 አንብቡ። ክርስቶስ ወደ የት ወረደ?
ሁለተኛው ጥቅስ፥ ኤፌሶን 4፡9 ነው። እርሱም ኢየሱስ «ወደ ምድር ታችኛው ክፍል ወረደ» ይላል። ሆኖም የዚህ አገላለጽ፥ «ታችኛው ክፍል» ሊል ምድር ማለቱ ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቶስ ከምድር ተነሥቶ ወደ ሰማይ ስለማረጉ ያወዳድር ስለነበር (ቁጥር 10)፥ ይህ ያለጥርጥር የሚያመለክተው ክርስቶስ ወደ ታችኛው ክፍል ማለትም ምድር እንደ ወረደና ከዚያም ወደ ሰማይ ወጥቶ ለሰው ልጆች ስጦታን እንደ ሰጠ ነው። ኤፌሶን 4፡9 ኢየሱስ ወደ ገሃነም ሄደ ብሉ አያስተምርም። ግን የሚለው በመጀመሪያም ወደ ምድር እንደ መጣና ከዚያም ወደ ሰማይ እንደ አረገ ነው። እንግሊዝኛ የምታነቡ ከሆናችሁና፥ «ኒው ኢንተርናሽናል ቨርሽን–NIV» መጽሐፍ ቅዱስ የምታገኙ ከሆናችሁ፥ ኤፌሶን 4፡9 አንብቡ። ከዚያም እውነተኛውን ትርጉሙን ታገኛላችሁ። በተጨማሪም የአማርኛውን አዲሱ መደበኛ ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስን ተመልከቱ።
ጥያቄ፡- ሀ) 1ኛ ጴጥሮስ 4፡6 አንብቡ። ሀ) ወንጌል ለእነማን ተሰበከ? ለ) ዕብራውያን 9፡27 አንብቡ። ከሞት በኋላ ለሰው ልጆች ያለው ምንድን ነው?
ሦስተኛው ጥቅስ፥ 1ኛ ጴጥሮስ 4፡6 ነው። ይህም ክፍል ወንጌል ለሙታን ተሰበከ ይላል። ታዲያ ይህ ጥቅላ፥ ኢየሱስ ወደ ሲኦል ወርዶ በብሉይ ኪዳን ጊዜ የነበሩ የማያምኑ ሰዎች ወንጌልን ሰምተው ሁለተኛ ዕድል በማግኘት ወደ ሰማይ እንዲገቡ ወንጌልን ሰበከላቸው ማለት ነው? ይህ ሊሆን አይችልም። ይህማ ፍርድ ከሞት በኋላ እንደሚመጣ ከሚያስተምረው ከሀብታሙ ሰውና ከአልአዛር ታሪክ ጋር ይቃረናል (ሉቃስ 16፡19-31፤ ዕብራውያን 9፡27)። በ1ኛ ጰጥሮስ 4፡6 ላይ ያለው ሐረግ፥ በወንጌል የተሰበከው፥ «አሁን በሕይወት ላሉት» ማለት ሊሆን ይችላል። እነዚህ ሰዎች በሕይወት በነበሩ ጊዜ ወንጌል ተሰብኮላቸዋል። አሁን ግን ሞተዋል። ይህ ከዐውደ አሳቡ ጋር ይስማማል፥ ጴጥሮስም በዚህ ቃል የሚሰደዱ አማኞችን ያጽናናበታል። እንደዚሁም «ዘ ኒው ኢንተርናሽናል ቨርሽን» በእንግሊዝኛው የሚተረጉመው እንደዚሁ ነው።
የመጨረሻውና እጅግ በጣም አስቸጋሪ የሆነው ጥቅስ፥ ደግሞ ኢየሱስ በመስቀል ላይ ከሞተ በኋላ ወደ ሲኦል ወረደ በማለት አንዳንዶች አዘወትረው የሚጠቅሱት፥ 1ኛ ጴጥሮስ 3፡18-20 ላይ ያለው ክፍል ነው። “
ጥያቄ፡- 1ኛ ጴጥሮስ 3፡18-20 አንብቡ። ክርስቶስ ለእነማን ሰበከ?
1ኛ ጴጥሮስ 3፡18-20 ያለው ክፍል፥ ክርስቶስ «በመንፈስ ሄዶ በወኅኒ ሴት ለነበሩ ነፍሳት ሰበከላቸው» ይላል። እንዲህ ማለት፥ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ከሞተ በኋላ ለማያምኑ ለደኅንነት ሁለተኛ ዕድል ሊሰጣቸው ወደ ሲኦል ወርዶ ሰበከላቸው ማለት ነውን? አይደለም። ቀደም ሲል እንዳየነው፥ ከሞት በኋላ አንዳንዶች የመዳን ሁለተኛ ዕድል ተሰጣቸው የሚለው አባባል፥ ክሌሎች የቅዱሳት መጻሕፍት ክፍሎች ጋር ይቃረናል። ደግሞስ ይህ ክፍል፥ ክርስቶስ ሙታን ወዳሉበት ሄዶ የብሉይ ኪዳን ቅዱሳን ወደ መንግሥተ ሰማይ ይለቀቁ ዘንድ አወጀ ማለቱ ነው? አይደለም። ምክንያቱም ነፍሳቱ ባለመታዘዛቸው ወኅኒ የገቡ መሆናቸው ነው የተገለጸው። 1ኛ ጴጥሮስ 3፡19 20፥ ክርስቶስ በሲኦል በነበሩ በወደቁ መላእክትና አጋንንት ላይ ፍርዱን አወጀ ማለቱ ነው? ይመስላል፥ ነገር ግን እዚህ ላይ የተጠቀሰው ‹መስበክ› የሚለው ቃል፥ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ፥ «ፍርድን ማወጅ» ተብሎ በፍጹም አልተጠቀሰም። ሁልጊዜ «ወንጌልን ማወጀ» በሚለው አገላለጽ ነው የታወቀው። ምናልባት ለዚህ ጥቅስ እጅግ አሳማኝ የሚሆነው ማብራሪያ፥ ጴጥሮስ እየተናገረ ያለው ክርስቶስ በመንፈስ አማካይነት በኖኅ ጊዜ ለነበሩ ሰዎች ወንጌልን መስበኩንና እነርሱም ሳይቀበሉት መቅረታቸውን ሲሆን፥ ባለመታዘዛቸው አሁን የሚገኙት በወኅኒ መሆኑን ነው። ወኅኒ የተባለው ገሃነም ነው። የዚህ ጥቅስ ትርጉም ምን እንደሆነ ፍጹም እርግጠኞች አይደለንም። ስለዚህ ጥቅስ አንድ ነገር ግልጽ ነው። ይህ ጥቅስ ክርስቶስ በሲኦል ውስጥ ላለ መሠቃየቱ፥ ወይም በሲኦል ውስጥ ለነበሩ ሰዎች ስለ
መስበኩ አይናገርም።
ስለዚህ እንዲህ ብለን መደምደም እንችላለን፣ የክርስቶስ መንፈስ እርሱ በመሠቀል ላይ ከሞተ በኋላ፥ ለመሠቃየት ወደ ሲኦል አልወረደም። እርሱ በመስቀል ላይ በመሞቱ የኃጢአት ዕዳ ሙሉ በሙሉ ተከፍሏል (ዮሐንስ 10፡30)። በዚህ ፈንታ ነፍሱ በአባቱ ዘንድ ተቀባይነትን አገኘች (ሉቃስ 23፡46)፣ በተጨማሪም የኢየሱስ መንፈስ ወደ ገነት ገባ (ሉቃስ 23፡43፥46)።
ምንጭ፡- “አስተምህሮ ክርስቶስና ደኅንነት”፤ ጽሑፍ፣ በዶ/ር ስቲቭ ስራውስ፤ ትርጉም በኃይሉ ልመንህ
