በመላው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እጅግ በጣም ጠቃሚ ከሆኑ መሪ አሳቦች መካከል አንዱ፥ ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያለው ርእሰ ጉዳይ ነው። ብዙ ሃይማኖቶች በእግዚአብሔር ያምናሉ። ይሁን እንጂ ክርስቲያናዊ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ናት ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔርን ለሰዎች የሚገልጥ፤ ሰዎች ከእግዚአብሔር ዘንድ የዘላለምን ሕይወት ሊያገኙ የሚችሉበትን መንገድና ሰውም አምላክም እንደሆነ የምታምነው። ስለዚህ የክርስቶስ አስተምህሮና እርሱ ለእኛ ያደረገው ነገር፥ ክርስትናን በዚህ ዓለም ካሉት ሌሎች ሃይማኖቶች ሁሉ የተለየ ያደርገዋል።
1ኛ ጥያቄ፡- ዕብራውያን 1:1-2 አንብቡ። ሀ) እግዚአብሔር ባለፉት ዘመናት ለሰዎች እንዴት ተናገረ? ለ) እግዚአብሔር ለእኛ በእነዚህ በመጨረሻዎቹ ቀኖች እንዴት ተናገረን?
2ኛ ጥያቄ፡- ዕብራውያን አንብቡ። ወልድ አብን እንዴት ይገልጣል?
ዕብራውያን 1፡1-3 እግዚአብሔር ለሕዝቡ በብዙ መንገዶች እንደ ተናገራቸው ያስገነዝበናል። በብሉይ ኪዳን ዘመን፥ እግዚአብሔር ለሕዝቡ የሚናገርበት ዋነኛ መንገድ በነቢያት አማካይነት ነበር። ነገር ግን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህች ምድር ከመጣ በኋላ እግዚአብሔር በአዲስና በተሻለ መንገድ ለሕዝቡ ተናገረ። በልጁ አማካይነት ተናገራቸው። ኢየሱስ እግዚአብሔርን ለሰው እጅግ በላቀ መልኩ የገለጠ የእግዚአብሔር ልጅ ነው። «እርሱ የክብሩ መነጸባረቅና የባሕርዩ ምሳሌ ሆኖ፥ . .» (ዕብ.1፡3)። ኢየሱስ እግዚአብሔር ምን እንደሚመስል በተለይም የእግዚአብሔርን ክብር ለሰዎች ያሳያል።
እግዚአብሔር ሰዎችን የፈጠረው እርሱን እንዲያውቁትና ከእርሱም ጋር ኅብረት እንዲያደርጉ ነው (ኤር. 9፡23፤ ሆሴዕ 6፡6፤ ዮሐ 17፤ ፊልጵ. 3፡7-10)። እግዚአብሔርን ለማወቅ እጅግ በጣም ጠቃሚ ከሆኑት መንገዶች አንደኛውና ዋንኛው መንገድ ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅ ነው። እርሱን በበለጠ እየተገነዘብነውና እያወቅነው ስንሄድ፥ እግዚአብሔርንም በበለጠ ልናውቀው እንችላለን። ስለዚህ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ማንነትና ሥራ ደህና አድርጎ ማጥናት ማንኛውም ክርስቲያን ሊፈጽመው የሚገባ ጠቃሚ ተግባር ነው። እግዚአብሔር የሚፈልግበትን ጠቃሚ ተግባር የሚፈጽም ክርስቲያን ለመሆን ካሻችሁ፥ ጌታ ኢየሱስን ለማወቅ ጊዜ ውሰዱ። ይህ ትምህርት ኢየሱስንና የፈጸመልንን ተግባራት በተሻለ ሁኔታ እንድታውቁ ይረዳችኋል።
ምንጭ፡- “አስተምህሮ ክርስቶስና ደኅንነት”፤ ጽሑፍ፣ በዶ/ር ስቲቭ ስራውስ፤ ትርጉም በኃይሉ ልመንህ
