Site icon

የኢየሱስ ከድንግል መወለድ 

በዚህ ሳምንት በተከታተልነው ትምህርት ላይ ኢየሱስ ሙሉ በሙሉና ፍጹም ሰው ስለመሆኑ ተረድተናል። እርሱም ሰብዓዊ አካል፥ ነፍስና መንፈስ ነበረው። ሰብአዊ ስሜትም ነበረው። እንደ ሰዎች ሁሉ ፈተና አጋጥሞታል። ሆኖም በፈተና አልተሸነፈም። ዛሬ ደግሞ በመቀጠል ስለ ኢየሱስ ሰብአዊነትና ልደት በሌላ አቅጣጫ ቀረብ ብለን እንመለከታለን። ኢየሱስ ሌሎች ሰዎች ወደ ዓለም በመጡበት ሁኔታ ተወለደ። ነገር ግን የኢየሱስ ልደት ከማንኛውም ይልቅ የተለየ ነበር። 

2. መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ድንግል መውለድ ምን ይላል? 

ጥያቄ፡- ማቴዎስ ፡18-25 አንብቡ። ሀ) እንደ ቁጥር 18 አገላለጽ ማርያም ፀንሳ የተገኘው መቼ ነበር? ለ) በምን ኃይል ፀንሳ ተገኘች? ሐ) ዮሴፍ ማርያም መፅነሷን ባወቀ ጊዜ ምን ለማድረግ እሰበ? መ) መልአኩ ለዮሴፍ በታየው ጊዜ፥ ስለ ማርያም መፀነስ እንዴት ብሎ ገለጸለት? ሠ) መልአኩ ዮሴፍ ምን እንዲያደርግ ነገረው? ረ) ስለ ድንግል መፀነስ ማቴዎስ ተፈጸመ የሚለው የትኛውን ትንቢት ነው? ለ) በቁጥር 24 ላይ እንደ ተነገረው ዮሴፍ ምን አደረገ? ሸ) ኢየሱስ እስኪወለድ ድረስ ዮሴፍና ማርያም በምን አኳኋን አብረው ኖሩ? 

በአዲስ ኪዳን ውስጥ ድንግል ማርያም ኢየሱስን ስለ መፀነስዋ ሁለት ማስረጃ ዎች አሉ። አንደኛው በማቴዎስ ወንጌል ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፥ ታሪኩ የተነገረው ከዮሴፍ አኳያ ነው። ማቴዎስ «ሳይገናኙ በመንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኘች» ሲል ይነግረናል። ነገር ግን ዮሴፍ ማርያም ፀንሳ ባየ ጊዜ በመጀመሪያ ከሌላ ሰው ያረገዘች መስሎት ጠርጥሯት ነበር። እርሱ ስላልተገናኛት የተረገዘው ሕፃን የእርሱ አለመሆኑ ይገባው ነበር። ቢሆንም በሰዎች ፊት ሊያጋልጣት አልፈለገም። ስለሆነም ምሥጢራዊ በሆነ መንገድ የእጮኛነቱን ውል እንዴት እንደሚያፈርስ አሰበ። እንግዲህ ይህን ሲያስብ ሳለ ነው ሕልም ያየው። በዚህ ሕልም ውስጥ መልአኩ ማርያም በመንፈስ ቅዱስ ኃይል መፀነስዋን አበሰረው። ከዚያም ማርያምን በሚስትነት ለመውሰድ እንዳይሰጋ ለዮሴፍ ነገረው። ስለዚህ ዮሴፍ ለእግዚአብሔር በመታዘዝ ማርያምን በሚስትነት አገባት። ነገር ግን ኢየሱስን እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም ነበር። እዚህ ላይ ማቴዎስ በኢሳይያስ 7፡14 ላይ የተጻፈው ትንቢት መፈጸሙን ይናገራል። እርሱም ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች» የሚለው ነው። 

ኢየሱስ ያለሰብአዊ አሳት በማርያም ማኅፀን ስለ መፀነሱ ማቴዎስ በሦስት መንገድ አጽንኦት ሰጥቶ ይናገራል። በመጀመሪያ፥ ማርያም የፀነሰችው እርስዋና ዮሴፍ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ከማድረጋቸው በፊት መሆኑን ያስረዳል። ሁለተኛ፥ ማርያም ከሰው ጋር ግብረ ሥጋ ግንኙነት በማድረግ ሳይሆን፥ በመንፈስ ቅዱስ ኃይለ መፀነስዋን ሁለት ጊዜ ደጋግሞ ይነግረናል። በመጨረሻም፥ ድንግል ትፀንሳለች» ተብሎ በትንቢት የተነገረው ቃል መፈጸሙን ይገልጽልናል። ማቴዎስ «ድንግል» ለሚለው ቃል የተጠቀመበት የግሪክ ቃል ግልጽና የማያሻማ ቃል ነው። ቃሉ ኮረዳና ያላገባች «ልጃ ገረድ» ማለት ብቻም አይደለም። በማያሻማ መንገድ በፍጹም የግብረ ሥጋ ግንኙነት ያላደረገች ሴት ማለት ነው። ድንግል ማርያም ወንድ ሳታውቅ ኢየሱስን መፀነስዋን ማቴዎስ በግልጽ ይነግረናል። 43ኛ ጥያቄ፡- ሉቃስ 1፡26-38 አንብቡ። ሀ) በቁጥር 27 ላይ ማርያም እንዴት ተገለጸች? ለ) ከቁጥር 30=33 ድረስ መልአኩ ለማርያም ያበሠረላትን መልእክት ጠቅለል ባለ ይዘት አቅርቡት። ሐህ የቁጥር 34 መልእክት በማርያም አእምሮ ውስጥ ምን ጥያቄ ቀሰቀለ? መ) በቁጥር 35 ላይ መልአኩ ለማርያም ጥያቄ እንዴት ያለ መልስ ሰጠ? 

ሁለተኛ ስለ ኢየሱስ የቀረበው ማስረጃ ከማርያም አቅጣጫ ሲሆን፥ የሚገኘውም በሉቃስ ወንጌል ላይ ነው። ማቴዎስ እንደ ጻፈው ሁሉ ሉቃስም በጥንቃቄ ማርያም ገና ድንግል ሳለች መፀነሰዋን ይገልጻል። በመጀመሪያ፡ መልአኩ ወደ ማርያም በመጣ ጊዜ ድንግል እንደ ነበረች ሁለት ጊዜ ደጋግሞ ይነግረናል (ቁጥር 27)። ሁለተኛ፥ ማርያምም መልሳ ክዚህ ጊዜ በፊት ወንድ እንደማታውቅ ትናገራለች (ቁጥር 34)። ሦስተኛ፥ እርስዋ ድንግል ስለሆነች እንዴት ልትፀንስ እንደምትችል ስትጠይቀው የፀነሰችው በመንፈስ ቅዱስ ኃይል መሆኑን መልአኩ መልሶ ይነግራታል። ማቴዎስ እንደ ጻፈው ሁሉ ሉቃስም ማርያም ኢየሱስን የፀነሰችው ያለምንም ግብረ ሥጋ ግንኙነት መሆኑን ትኩረት ሰጥቶ ያስረዳል። 

1. ስለ ድንግል መውለድ ልናስወግዳቸው የሚገቡን ተቃውሞዎች ምንድን ናቸው? 

በእነዚህ ጥቅሶች ላይ የሚሰነዘሩና ልናስወግዳቸው የሚገቡን ሁለት ተቃውሞዎች አሉ። የመጀመሪያው ተቃውሞ ኢየሱስ ከግብረ ሥጋ ግንኙነት ውጭ መወለዱን የሚጠራጠር የዘመናዊ ሰው አመለካከት ነው። እንዲህ ዓይነቶቹ ሰዎች የድንግል መውለድ ሁኔታ ከሥነ ተፈጥሮ ሳይንስ እሳቤ የራቀ ነውና ሊሆን አይችልም ይላሉ። እነዚህ ሰዎች አንዳንድ ጊዜ የድንግልን መውለድ በተመለከተ ተጽፎ የሚገኘው በማቴዎስና በሉቃስ ወንጌል ውስጥ ብቻ ነው ይላሉ። ታዲያ የድንግልዋ መውለድ እርግጠኛ ቢሆን ኖሮ፥ ለምን በማርቆስና በዮሐንስ ወንጌሎች ውስጥ አልተጠቀሰም? ይላሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ ለምን አልጠቀሰውም ባይ ናቸው። ከዚህ አልፈው ይህ ታሪክ በጥንት ዘመን አማልክት በገሃዱ ዓለም ካሉ ሴቶች ጋር ግብረ ሥጋ በመፈጸም ልጆች ይወልዳሉ ከሚባለው አፈ-ታሪክ ጋር ይመሳሰላል ይላሉ። ስለዚህ የጥንት አረማውያን አፈ-ታሪክ ነው በማለት ያናንቁታል። 

እንዲህ ላሉት ተቃውሞዎችም ቢሆን በቂ የሆኑና መልስ ሊሰጡ የሚችሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃ ዎች አሉ። ይህን ተቃውሞ የሚያቀርቡ ሰዎች ችግር፥ የመጽሐፍ ቅዱስን ግልጽ የሆነ ማስረጃ ና ትምህርት አለመቀበል ነው። እንደዚሁም ከሰዎች ግንዛቤ በላይ በሆነ በመለኮት ሥራዎች ማመን አይፈልጉም። ማቴዎስና ሉቃስ ማርያም ኢየሱስ ተረግዞ በሚወለድበት ጊዜም ድንግል እንደነበረች በግልጽ ያስተምራሉ። ይህ ሁኔታ ከሥነ ሕይወት ጋር አይስማማ ይሆናል። ይሁን እንጂ እግዚአብሔር በእግዚአብሔርነቱ ከፈለገ የሥነ ሕይወትን ሂደት የሚያፋልስ ድርጊት ሊፈጽም ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል ነው ብለን ካመንን የድንግል መፀነስ የሥነ ሕይወት እሳቤን የሚቃረን ሊሆን ይችላል። ሆኖም እግዚአብሔር እግዚአብሔር ከሆነ እግዚአብሔር በተአምር ማርያም ድንግል ሳለች፥ ኢየሱስን እንድትፀንስ ማድረጉን አምነን መቀበል ይኖርብናል። ማርቆስና ዮሐንስ የድንግልን መውለድ አክለው ያልጻፉበት ምክንያት፥ ስለ ኢየሱስ በጻፉት ወንጌላቸው ውስጥ በልጅነት ታሪኩ ላይ ትኩረት ካለመስጠታቸው የተነሣ ነው። እንደዚሁም ስለ ኢየሱስ የልጅነት ታሪክ ያልጻፉት፥ ከተነሡበት የወንጌል ዓላማ ጋር እምብዛም ስለማይገጥም ነው። ሐዋርያው ጳውሎስም ቢሆን ስለ ድንግል መውለድ ያላነበት ምክንያት መልእክቶቹ ያተኮሩት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ባሉ ወቅታዊ ችግሮች ላይ ስለነበረ ነው። ከዚህም በስተቀር ስለ ድንግል መውለድ በቤተ ክርስቲያኖቹ ውስጥ የተነሣ አፍራሽ ክርክር ስላልነበረ ጳውሎስ በዚህ ጉዳይ ላይ አልጻፈም። በመጨረሻም የድንግል (መፀነስ) ሁኔታ፥ ከአረማውያን አፈ ታሪክ የተለየ ነው። የድንግል መውለድ ታሪክ ሐሰተኛ አማልክት በገሃዱ ዓለም ካሉ ሴቶች ጋር ግብረ ሥጋ አድርገው ልጆች ይወልዳሉ ከሚለው አባባልም ጋር የሚመሳሰል አይደለም። ማቴዎስና ሉቃስ በግልጽ እንደ ተናገሩት ማርያም ከወንድ ጋር ግብረ ሥጋ ሳትፈጽም በመንፈስ ቅዱስ ኃይል መፀነስዋን ያስረዳሉ። ስለዚህ ኢየሱስ በቅዱስና ኃይል በተሞላበት የእግዚአብሔር ሥራ በማርያም ማኅፀን ሊያድር ቻለ እንጂ፥ ስግብረ ሥጋ ግንኙነት አልተፀነሰም (ሉቃስ 185)። 

መጽሐፍ ቅዱስን የሚያምኑ ክርስቲያኖች የድንግል መውለድ ሊሆን አይችልም የሚሉ መናፍቃንን ማራቅ አለባቸው። እንደዚሁ ክርስቲያኖች ሊያስወግዱት የሚገባ ሁለተኛ ተቃውሞ አለ። ብዙ ክርስቲያኖች ስለ ድንግል መውለድ እነዚህ ጥቅሶች ከሚያስተምሩት መንገድ በመውጣት የራሳቸውን ሃሳብ ይጨምሩበታል። ለምሳሌ ያህል፥ ብዙ የካቶሊክና የኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ማርያም ኢየሱስን ከወለደችም በኋላ በድንግልናዋ ቀርታለች ብለው ያምናሉ። ማቴዎስም ሆነ ሉቃስ ማንኛቸውም ማርያም ድንግል ሆና ቀረች ብለው አልጻፉም። በማቴዎስ 1፡25 ላይ በተጻፈው ሁኔታ ከሆነ ኢየሱስ ከተወለደ በኋላ ማርያምና ዮሴፍ ባልና ሚስት በመሆን እንደ ማንኛውም ባለትዳር የግብረ ሥጋ ግንኙነት እየፈጸሙ አብረው መኖራቸው ይገመታል። እንደዚሁም አንዳንድ የካቶሊክና የኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ተአምራዊ በሆነ ድርጊት ኢየሱስ ስለተወለደ የማርያም ድንግልናዋ አልተነካም ይላሉ። እግዚአብሔር እንዲህ ያለውን ተአምር ሊፈጽም ቢችልም፥ እነርሱ በሚሉት ሁኔታ ኢየሱስ ተወለደ የሚል ማስረጃ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የለም። በሉቃስ 2፡1-7 ተጽፎ የሚገኘው እርግጠኛው የኢየሱስ መወለድ እንደ ማንኛውም ሰው የመወለድ ሁኔታ መሆኑን ይናገራል። መጽሐፍ ቅዱስ የኢየሱስ መፀነስ ተአምራዊ መሆኑን በግልጽ ይናገራል። ይህም እሱ ከወንድና ሴት ግብረ ሥጋ ግንኙነት ውጭ መፀነሱ ነው። እንደዚሁም ማርያም ኢየሱስን እስከወለደችበት ጊዜ ድረስ ድንግል ሆና መቆየቷን መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያስረዳል። ነገር ግን ማርያም ኢየሱስን ከወለደች በኋላ ድንግል ሆና ቀረች ብሎ አያስተምርም። 

አንዳንድ ሰዎች ማርያም ኢየሱስን ከወለደች በኋላም ድንግል ሆና ኖራለች እያሉ ለምን ይከራከራሉ? ይህ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ዘግየት ብሎ የተነሣ አሳብ በሁለት ግምቶች ላይ የተመሠረተ ነበር። የመጀመሪያው ሁኔታ አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ማርያም ከኃጢአት ነፃ ናት ብለው ማስተማር ጀመሩ። ኢየሱስ ያለ ኃጢአት የሚወለድ ከሆነ (ትክክል ነው) ማርያምም ኃጢአት የሌለባት መሆን ይገባታል (ትክክለኛ ያልሆነ) ብለው አሰቡ። ሁለተኛ፡ እነዚሁ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በጋብቻም ቢሆን ግብረ ሥጋ ግንኙነት መፈጸም ኃጢአት ነው ብለው ያስቡ ነበር። ስለዚህ ማርያም ኃጢአት የሌለባት ንጽሕት ከሆነች ድንግልም መሆን ይኖርባታል ብለው አመኑ። ዳሩ ግን መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ እንደሚናገረው በጋብቻ ጥምረት የሚፈጸም የግብረ ሥጋ ገንኙነት ኃጢአት አይደለም። እግዚአብሔር በጋብቻ ላይ የሚፈጸመውን ቀብረ ሥጋ ግንኙነት ያከብረዋል (ዘፍጥረት 1፡28፤ 2፡24)። የሚያከብረውም ለሕዝቡ ካለው ዋነኛ ፍቅር ጋር ተምሳሌታዊ በማድረግ (መኀልየ መኀልይ፥ ኤፌሶን 5፡25) ነው። ማርያም ከባልዋ ዮሴፍ ጋር በትዳር መካከል የሚፈጸመውን የግብረ ሥጋ ግንኙነት አድርጋለች ያሉ ሰዎች የማርያም ጠላት መሆናቸው አይደለም። ኢየሱስ በድንግል ማርያም ተፀንሶ ተወልዶአል ነገር ግን ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስ ከሚናገረው ውጪ ማርያም ሕይወቷን ሙሉ ድንግል ሆና ቀርታለች እንዳይሉ መጠንቀቅ አለባቸው። 

1. የድንግል መውለድ ትርጉሙ ምንድን ነው? 

1.1 የድንግል መውለድ ኢየሱስ ፍጹም እግዚአብሔር ፍጹም ሰው መሆኑን ያስረዳል። 

ኢየሱስ ከድንግል ስለምን ተወለደ? ዛሬ ለአማኞች የድንግል መውለድ ምን ትርጉም አለው? ቀዳሚውና ዋንኛው ምክንያት የድንግል መውለድ ኢየሱስ ፍጹም መለኮት ደግሞም ፍጹም ሰው ለመሆኑ ማስረጃ ነው። እግዚአብሔር ኃያል ስለሆነ አምላክም ሰውም ሆኖ በቀጥታ ከሰማይ ሊመጣ ይችል ነበር። ይህም ከድንግል ሳይወለድ ፍጹም ሰው ፍጹምም መለኮት ሆኖ ማለት ነው። ነገር ግን የድንግል መውለድ ፍጹም ሊገባን በሚችል ሁኔታ የሚያሳየው የክርስቶስ ፍጹም አምላካዊነት እና ፍጹም ሰብአዊነት ያላቸውን ፍጹም አንድነት ነው። እግዚአብሔር ከሰው ሳይወለድ አምላክም ሰውም ሆኖ ከሰማይ ቢወርድ ኖሮ ሰው መሆኑ ያጠራጥር ነበር። ከአዳም ዘር ባይገኝ ኖር እንዴት ሰው ሊሆን ይችል ነበር? ከሰው በመወለድ ወደ ዓለም ባይመጣ ኖር እንዴት እንደ እኛ ሰው ሊሆን ይችል ነበር? በሌላ በኩል አምላክም ሰውም ሆኖ በወንድና ሴት በሚደረግ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ቢወለድ ኖሮ መለኮት መሆኑም ግልጽ ባልሆነ ነበር። ደግሞም በዚህ ሁኔታ የኢየሱስ ልደት ተፈጽሞ ቢሆን ኖር እንዴት አምላክ ሊሆን ይችል ነበር ዌይን ሩደም የተባለ የሥነ መለኮት ምሑር ሲናገር፥ እንዲህ ብሏል፡ 

«ዚአብሔር በጥበብ በኢየሱስ ልደት ለውና መለኮት እንዲጣመሩ አደረገ። የእርሱ ሰው መሆን በግልጽ ይታወቅ ዘንድ ከሌት ተወለደ አምላክነቱም በግልጽ ይታወቅ ዘንድ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በማርያም ማኅፀን አደረ።» ኢየሱስ ከድንግል እንዲወለድ የሆነበት የመጀመሪያ ምክንያት እርሱ ፍጹም ሰው ፍጹምም አምላክ መሆኑን ለማሳየት ነው። 

ሙስሊሞች ኢየሱስ በተወለደ ጊዜ ማርያም ድንግል ነበረች ብለው ያምናሉ። በቁራኑ ሱራ 19፡16-34 ባለው ክፍል በእግዚአብሔር ልዩ ጥበብ በማርያም ማኅፀን ተፀነሰ ይላል። እንደዚህ ይበሉ እንጂ፥ ኢየሱስ ከድንግል መወለዱ ፍጹም አምላክነቱንና ፍጹም ሰው መሆኑን የሚያስረዳ ነው ብለው አያምኑም። በእርግጥ ሙስሊሞች ኢየሱስ እግዚአብሔር መሆኑን አይቀበሉም። እነርሱ እንደሚያምኑት እግዚአብሔር አዳምን እንደ ፈጠረ ሁሉ ኢየሱስንም ፈጠረ ባይ ናቸው። ሆኖም እግዚአብሔር ኢየሱስን በማርያም ማኅፀን ውስጥ ፈጠረው ይላሉ። በዚህ ሁኔታ ሙስሊሞች ኢየሱስ ከድንግል ማርያም መወለዱን ቢቀበሉም። ይህ ልደቱ አምላክነቱንም እንደሚያሳይ ግን አያምኑም፡፡ ከሙስሊም ወዳጆቻችን ጋር ወንጌልን ስንካፈል ድንቅ የሆነውን የኢየሱስን ልደት ክገለጽንላቸው በኋላ፥ ይህ ስለ ኢየሱስ ምን እንደሚያስተምራቸው ልንጠይቃቸው እንችላለን። ይህ ግንኙነት ስለ ኢየሱስ አብረናቸው በይበልጥ እንድንወያይ ዕድል ይሰጠናል። 44ኛ ጥያቄ፡– ሙስሊም ስለሆኑ ወዳጆቻችሁ አስቡ። ስለ ድንግል መወለድ አንሥታችሁ ከእርሱ ወይም ከእርሷ ጋር እንዴት ልትወያዩ ትችላላችሁ? 

3.2 የድንግል መውለድ ኢየሱስ ያላንዳች የኃጢአት ባሕርይ መወለዱን በግልጽ ያስረዳል። 

ኢየሱስ ከድንግል የተወለደበት ሁለተኛ ምክንያት ቀልጽ የሚያደርግልን ኢየሱስ ያላንዳች የኃጢአት ባሕርይ መወለዱን ነው። ጥያቄ፡- ሉቃስ 1፡35 አንብቡ። መንፈስ ቅዱስ ኢየሱስ በማርያም ማኅፀን ውስጥ እንዲፀነስ የማድረጉ ውጤት ምን ነበር? 

ኢየሱስ ሰብአዊ አባትና እናት ኖረውትም ቢሆን እንኳን እግዚአብሔር ኃያል በመሆኑ በኃጢአት ባሕርይ እንዳይወለድ ሊያደርገው ይችል ነበር። ወንጌላዊው ሉቃስ በምዕራፍ 1፡35 ላይ እንደ ገለጸው፥ መንፈስ ቅዱስ ጌታ ኢየሱስ እንዲፀነስ የማድረጉ ውጤት ኢየሱስ ቅዱስ መሆኑን ለማስረገጥ ነበር። በመሆኑም ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ የተፀነሰ ስለሆነ ያላንዳች የኃጢአት ባሕርይ ተወልዶአል። ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ መፀነሱ ግልጽ የሚሆንበት አንዱ መንገድ ከድንግል የመወለዱ ተአምር ነው። 

ኢየሱስ የኃጢአትን ባሕርይ ከማርያም እንዴት ሊወርስ አልቻለም? አንዳንድ የኦርቶዶክስና የካቶሊክ ክርስቲያኖች፥ ማርያም ኃጢአት ስላልነበራት፥ ኢየሱስ ከድንግል በመወለዱ የኃጢአት ባሕርይ አልነኮውም ይላሉ። ነገር ግን ማርያም እንዴት ኃጢአት አልኖራትም? አንዳንዶቹ እንደሚያምኑት፥ ማርያም ራስዋ ከድንግል ስለተወለደች የኃጢአት ባሕርይ የላትም ባይ ናቸው። ሆኖም ይህ ችግሩን አንድ ትውልድ ወደ ኋላ ይመልሰዋል። ማርያም ከድንግል በመወለዱ ኃጢአት ካልኖራት እናቷስ እንዴት ልትሆን ነው? እናቷ የወረሰችውን ኃጢአት እንዴት ወደ ማርያም አላስተላለፈችም? የማርያም እናትም ከድንግል ተወልዳ ኃጢአት አልነበራትም ይሆን? ከዚህ ይልቅ የተሻለው መፍትሔ የታየው በኢየሱስ መፀነስ ላይ ነው። በዚህ ሁኔታ ኢየሱስ የማርያምን የኃጢአት ባሕርይ እንዳይወርስ መንፈስ ቅዱስ ጠብቆታል። ኢየሱስ የኃጢአት ባሕርይ ይዞ እንዳይወለድ ካደረገው አባት በመወለዱ ሳይሆን፥ የኃጢአት ባሕርይ ሳይኖርበት ንጹሕ ሆኖ እንዲፀነስ ባደረገው በመንፈስ ቅዱስ ጥበቃና እንክብካቤ ውስጥ ስለነበረ ነው። 

3.3 የድንግል መውለድ የሚያሳየን ድነት (ደኅንነት) ከላይ የሚሰጥ የእግዚአብሔር ጸጋ መሆኑን ነው። 

ኢየሱስ ከድንግል እንዲወለድ የተደረገበት ሦስተኛውና ዋንኛው ምክንያት ደኅንነታችን ሙሉ በሙሉ ከላይ የሚሰጥ የእግዚአብሔር ጸጋ መሆኑን ለዓለም ስለሚያሳይ ነው። እኛ ሥጋ ለባሾች ራሳችንን ለማዳን የምናደርገው ምንም ነገር ሊኖር አይችልም። የመድኃኒታችን ወደዚህ ዓለም መምጣት እንኳን እግዚአብሔር ያደረገው ተአምር ነው። የእግዚአብሔር ድነት (ደኅንነት) የራሱ ሥራና ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ድረስ እርሱ ለእኛ የሰጠው ስጦታ ለመሆኑ የድንግል መውለድ ማረጋገጥ ነው። 46ኛ ጥያቄ፡- ወዳጃችሁ የሆነ ለው የማርያም ጠላት ናችሁ ብሎ እንደ ከሰሳችሁ አድርጋችሁ ገምቱ። ታዲያ እንዲህ ላለው ክስ መልሳችሁን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በመመሥረት እንዴት ቅራኔ በማያስከትል ሁኔታ ልትመልሱ ትችላላችሁ? 

አማኞች ሁሉ ድንግል ማርያምን ሊያከብሯት ይገባል። እግዚአብሔር ልጁ ወደዚህ ዓለም በመጣ ጊዜ በእርሷ ማኅፀን አድሮ እንዲወለድ መርጧታል። ከዚህም በስተቀር ከድንግል ማርያም ሕይወት ስለ ታዛዥነትና ራስን ዝቅ ስለ ማድረግ ብዙ ልንማር እንችላለን። ማርያም ኃጢአት የለባትም ካሉት ጋር በምንወያይበት ጊዜ የሚከተሉትን የማርያም መልካም ባሕርያት ልንጠቅስላቸው እንችላለን። ድንግል ሆና ኢየሱስን ፀንሳለች፥ እግዚአብሔርን የምትፈራ ሴት ናት፥ ልጁ ከእርሷ ተወልዶ ወደዚህ ዓለም እንዲመጣ ለማድረግ እግዚአብሔር መርጧታል። ስለዚህ ለማርያም ትልቅ ግምት ያላቸውን ሰዎች ማስቀየም፥ አላስፈላጊ የሆነ ንትርክ መቀስቀስና ማናደድ ጥቅም የለውም።

ምንጭ፡- “አስተምህሮ ክርስቶስና ደኅንነት”፤ ጽሑፍ፣ በዶ/ር ስቲቭ ስራውስ፤ ትርጉም በኃይሉ ልመንህ

Exit mobile version