Site icon

ክርስቶስ «አንድ ባሕርይ» አለው የሚለው አስተምህሮ በኢትዮጵያ

ትናንትና ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን ስለ ኢየሱስ ባሕርያት የነበራትን ግንዛቤ እንዴት እያሳደገች እንደ መጣች ማጥናት የጀመርነውን ትምህርት አጠናቅቀናል። በዚህ ትምህርታችን መጨረሻ ላይ ክርስቶስ «አንድ ባሕርይ» አለው የሚለው አስተምህሮ በኢትዮጵያ ውስጥ ተለይቶ ተቀባይነትን በማግኘት ብሔራዊ እምነት ለመሆን የቻለበትን ሁኔታ እናጠናለን። 

ከዘጠኙ ቅዱሳን በኋላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ለአንድ ሺህ ዓመታት ስትስፋፋ ቆይታለች። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን ታሪክ በሙሉ አንሥተን ለመወያየት አንችልም። ነገር ግን ቤተ ክርስቲያኒቱ በታሪኳ ውስጥ በክርስቶስ ባሕርያት ላይ ያላትን የአስተምህሮዋ አቋም መገንዘብ እንፈልጋለን። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በዚህ የአንድ ሺህ ዓመታት ታሪኳ ውስጥ የኢየሱስ ሰብኣዊና መለኮታዊ ባሕርያት በተሠገዎ በአንድ ባሕርይ ተዋህደዋል በሚለው አስተምህሮዋ ጸንታ ቆይታለች። ከዚህ የተነሣ በኬልቄዶኑ ጉባዔ ላይ ኢየሱስ መለኮታዊና ሰብአዊ የሆኑ ሁለት ባሕርያት አሉት የሚለውን ኣስተምህሮ ሲቃወሙት ቆይተዋል። አንዳንዶቹ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ የኢየሱስ አካል መለኮታዊና የማይሞት ነው የሚል ትምህርትም ያራምዱ የነበረ ይመስላል። የክርስቶስ ሰብኣዊነት ከተቀሩት የሰው ልጆች ሰብአዊነት የተለየ ነው ብለውም ያምናሉ። ይሁን እንጂ ሌሎች ደግሞ ኢየሱስ ያለ ኃጢአት ከመሆኑ በስተቀር ፍጹም አምላክ ፍጹምም ሰው ነው ሲሉ ይቀበላሉ። ሁሉም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መሪዎችና አስተማሪዎች የአቡነ ሌዎ አስተምህሮ የሆነውን ማንኛውንም ትምህርትና የኢየሱስን ሁለት ባሕርያት ኣስተምህሮ በጥብቅ ይቃወሙት ነበር። 

ጥያቄ፡– ከዘጠኙ ቅዱሳን በኋላ በነበረው አንድ ሺህ ዓመታት ውስጥ፥ ስለ ክርስቶስ ሁለት ባሕርያት የኬልቄዶኑ ጉባዔ ባስተላለፈው ውሳኔ ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እንዴት ያለ አቋም ስትወስድ ቆየች? 

የካቶሊካውያን ሚሲዮኖች መምጣት 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከ500-1509 ዓ.ም ድረስ፥ ለአንድ ሺህ ዓመታት ኢየሱስ መለኮታዊና ሰብአዊ የሆኑ ሁለት ባሕርያት አሉት የሚለውን የኬልቄዶኑ ጉባዔ ተቀብሎ ያጸደቀውን አስተምህሮ ስትቃወም ቆይታለች። በእነዚህ ዓመታት በአብዛኛው አረቦች ሰሜን አፍሪካንና ዐረቢያን ላለ ያዙ፥ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ጋር የነበራት ግንኙነትም ያነሰ ሆኖ ቆይቷል። ነገር ግን በ500 እና በ1600 ዓመታት ላይ በቁጥር ጥቂት የሆኑ የካቶሊክ ሚሲዮናውያን ከአውሮፓ ወደ ኢትዮጵያ መጡ። እነዚህ ሚሲዮናውያን ይዘውት የነበረው አስተምህሮ በኬልቄዶኑ ጉባዔ ላይ ተቀባይነትን ያገኘው ኢየሱስ ሁለት ባሕርያት አሉት የሚለውን ነበር። ታዲያ የእነዚህ ሚሲዮናውያን መምጣትና ይህን ትምህርት ለማስፋፋት መሞከር በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ትልቅ ነውጥን አስከተለ። 

የመጀመሪያዎቹ ሚሲዮናውያን አመጣጥ መሐመድ ግራኝ ባስከተለው ወረራ ምክንያት ነበር። ስለሆነም መሐመድ ግራኝ የአፄ ልብነ ድንግልን መንግሥት በወረረ ጊዜ፥ ንጉሡ በጊዜው ወዳጃቸው ከነበረው ከፖርቹጋሉ መንግሥት የጦር እርዳታ ጠየቁ። ከዚያም የፖርቹጋል መንግሥት ኣራት መቶ ወታደሮችን ከጥቂት የካቶሊክ ሚሲዮናውያን ጋር አድርጎ ወደ ኢትዮጵያ ላከ። እነዚህ ወታደሮች ከፖርቹጋል ተልከው ኢትዮጵያ በደረሱበት ጊዜ አፄ ልብነ ድንግል ሞተው ቆዩኣቸው። ሆኖም ልጃቸው አፄ ገላውዲዮስ ነግሠው ዙፋኑን ወርሰው ነበር። ከዚያም የፖርቹጋል ሠራዊት ከአፄ ገላውዴዎስ ወታደሮች ጋር በመሆን መሐመድ ግራኝንና ሠራዊቱን ገጥመው በማሸነፍ ግራኝን ገደሉ። ከዚህ በኋላ አብዛኛዎቹ የፖርቱጋል ወታደሮች በኢትዮጵያ ነዋሪ ሆነው ቀሩ። ኋላም ብዙ ካቶሊክ ሚሲዮናውያን መጡላቸው። ከዚህ በኋላ ሚሲዮናውያኑ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ አማኞች ካቶሊኮች እንዲሆኑ ለማሳመን በጣም ጣሩ። በጊዜው ከመሪዎቹ ጋር ክርክር ከገጠሙባቸው አስተምህሮዎች ውስጥ አንዱ የክርስቶስ ባሕርያት ነበር። ካቶሊካውያኑ ኢየሱስ ሁለት ባሕርያት ነበሩት፥ እነርሱም አንዱ መለኮታዊ ሌላው ሰብአዊ ሲሆን፥ ሁለቱም በአንድ አካል ውስጥ የተጣመሩ ናቸው የሚለውን አስተምህሮአቸውን ለማሳመን ጣሩ። ኦርቶዶክሳውያኑም ኢየሱስ መለኮታዊና ሰብአዊ ባሕርያት እንዳሉት ቢያምኑም፥ ሁለት ባሕርያት አሉት የሚለውን ኣስተምህሮ አልተቀበሉትም። ይህ አስተምህሮ ኢየሱስን ይከፋፍለዋል አሉ። በመጨረሻም፥ ክርክሩ በኣፄ ገላውዴዎስና በአንደኛው የካቶሊክ ካህን መካከል ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደረሰ። ከዚያም አፄ ገላውዴዎስ ክርክሩን አሸነፉ። በመሆኑም ከኢትዮጵያውያን መካከል ካቶሊካዊነትን እምነት የተቀበሉ ጥቂቶች ነበሩ። 

ጥያቄ፡– የመጀመሪያዎቹ የፖርቹጋል ካቶሊክ ሚሲዮናውያን በምን ምክንያት ወደ ኢትዮጵያ መጡ? 

ጥያቄ፡- የክርስቶስን ባሕርያት በሚመለከት በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንና በፖርቹጋል ካቶሊካዊያን ሚሲዮናውያን መካከል የነበረው ልዩነት ምን ነበር? 

ጥያቄ፡– ካቶሊካውያን ሚሲዮናውያኑ ኢትዮጵያውያኑ የካቶሊክን እምነት እንዲቀበሉ ጥረት ባደረጉበት ጊዜ ኦርቶዶክሳውያኑ ምን አቋም አላዩ? 

እንደሚታወሰው የመጀመሪያዎቹ የካቶሊክ ሚሲዮናውያን ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ግራኝ መሐመድን ለመዋጋት ከመጡት ወታደሮች ጋር ነበር። እነዚህ ሚሲዮናውያንም ኦርቶዶክሳውያኑን አማኒያን ካቶሊካዊውን እምነት እንዲቀበሉ ብዙ ጥረት አድርገዋል። ነገር ግን በሁለቱ መካከል ትልቅ ልዩነት ነበር። ያም ካቶሊካውያን ኢየሱስ ሁለት ባሕርያት አሉት ሲሉ፥ ኦርቶዶክሳውያን ደግሞ አንድ ባሕርይ ብቻ አለው ይሉ ነበር። አብዛኛዎቹ ካቶሊካውያን ሚሲዮናውያን ሕይወታቸውን በሙሉ እዚሁ ሲያገለግሉ ቆይተው እዚሁ በኢትዮጵያ ውስጥ አርፈዋል። ጠንካራው ጥረታቸው ብዙ ፍሬም ባያፈራ፥ ጥቂት ኢትዮጵያውያን ካቶሊኮች ሊሆኑ ችለዋል። 

ይሁን እንጂ የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ጥረትዋን እንደገና አድሳ ብትቀጥል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን አሳምና ወደ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን እንደምታመጣ በመተማመን ትምህርቱን ቀጠለች። ከዚህ የተነሣ ከፖርቹጋል ተጨማሪ ሚሲዮናውያንን ወደ ኢትዮጵያ መላክ ቀጠለች። ከአፄ ገላውዴዎስ ጋር ከተካሄደው ክርክር ከሃምሳ ዓመት ገደማ በኋላ፥ ፒያዝ የተባለ ሚሲዮናዊ ወደ ኢትዮጵያ መጣ። ይህ ፒያዝ የተባለ ሰው ትሑት ሰው ከመሆኑም በላይ፥ ትምህርት ቤት ከፍቶ እምነቱን አድምጠው ለሚቀበሉት የካቶሊካውያንን አስተምህሮ መስበክ ጀመረ። በመጨረሻውም ላይ አፄ ዘድንግል ስለ ፒያዝ ትምህርት ሰምተው አድናቆት ስላደረባቸው ወደ ቤተ መንግሥታቸው አስጠሩት። ፒያዝም ሲናገር በሰሙት ጊዜ፥ በትምህርቱ ተመስጠው የክርስቶስን የሁለት ባሕርያት አስተምህሮ በመቀበል ካቶሊክ ሆኑ። ይሁን እንጂ ይህ በመላው መንግሥታቸው ውስጥ ዓመፅን ቀስቅሶ እርሳቸውም ወዲያው ተገደሉ። ከዘድንግል ቀጥለው የነገሡት ሱስንዮስ ነበሩ። አፄ ሱስንዮስም ቢሆኑ ለካቶሊክ አስተምህሮ ኣድናቆትና ፍላጎት ነበራቸው። ሆኖም ከዘድንግል በበለጠ ጥንቃቄ አደረጉ። ለብዙ ዓመታትም ከቆዩ በኋላ ከታላላቅ የኢትዮጵያ ልዑላን ዘንድ ድጋፍ አገኙ። ከዚያም ኢየሱስ ሁለት ባሕርያት አሉት የሚለውን የካቶሊክ እምነት የሚቀበሉ መሆናቸውን በይፋ አሳወቁ። አሁንም እንደገና ዓመፅ ተቀሰቀሰ። ስለዚህ አፄ ሱስንዮስ የካቶሊክን ሃይማኖት በኢትዮጵያ ለማቆየት ከገዛ ሕዝባቸው ጋር መዋጋት ነበረባቸው። 

በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ፒየዝ ሞቶ ነበር። ስለዚህ ሜንዴዝ የተባለ ሚሲዮናዊ ዱካውን ተከትሎ መሥራት ጀመረ። ሜንዴዝ ከፒያዝ የተለየ ኃይለኛ ቁጡ ሰው ነበር። በመሆኑም ኢትዮጵያውያን የካቶሊክን እምነት ይቀበሉ ተብሎ ሳይወሰን አልፎ ተርፎ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በምትከተለው መንገድ እንደገና መጠመቅ አለባቸው አለ። በቤተ ክርስቲያናቸውም ውስጥ የግዕዙን ቋንቋ ትተው በላቲን መጠቀም አለባቸው፥ ካህናቱም ቢሆኑ በካቶሊክ ሥርዓትና እምነት ሊቀድሱ ይገባል ኣለ። ታዲያ ይህ የሜንዴዝ አሳብ ኢትዮጵያውያኑን ክፉኛ አናደዳቸው። ይህ የሜንዴዝ አባባል ኦርቶዶክሳውያን የቆዩበትን የአምልኮ ሥርዓትና ባሕል ዝቅ ያደረገና ለመጪው እምነት የበለጠ ስፍራ የሰጠ ሆኖ ተሰማቸው። ከዚህ አሜንዴዝ ጠንካራ አቋምና አስተሳሰብ የተነሣ የካቶሊክ እምነት በኢትዮጵያውያን ዘንድ ተቀባይነት እንደሌለው ብዙ ኢትዮጵያውያን አረጋገጡ። ከዚያም ስእ፤ ሱስንዮስ ላይ የተቀሰቀሰው ዓመፅ የበለጠ ጠነከረ። 

በኋላም አፄ ሱስንዮስ አገራቸው እንድትከፋፈል ምክንያት በመሆናቸው ተስፋ ቆርጠው በ1632 ዓም ዙፋናቸውን ለልጃቸው ለፋሲለደስ ለቀቁላት። አፄ ሱስንዮስም ይህ ከሆነ ከኣንድ ዓመት በኋላ ሞቱ። አፄ ፋሲለደስ የኣደረጉት የመጀመሪያው ተግባር ካቶሊክ ሚሲዮናውያንን ከአገር ማባረርና አገሪቱን ወደ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መመለስ ነበር። ሚሲዮናውያኑንም ከአገር በሚያባርሩበት ጊዜ አፄ ፋሲለደስ፥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች የሁለት ባሕርያትን ትምህርት እንደማይቀበሉና ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም አምላክ ፍጹምም ሰው መሆኑን እንደሚያምኑ በመንገር ነበር። ለሕዝቡም አክለው ሲናገሩ፥ «አሁን ኢትዮጵያ ከምዕራባውያን ጅቦች አምልጣለች» ብለዋል። 

የካቶሊክ ሚሲዮናውያን መምጣትና የአፄ ሱስንዮስ መንግሥት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ክርስቶስ አንድ ባሕርይ አለው የሚለውን እምነቷን በበለጠ እንድታጠናክር ረዳት። በአንጻሩ ክርስቶስ ሁለት ባሕርያት አሉት የሚለውን አስተምህሮ እንደ ባዕድ- አመጣሽ አስተምህሮ በመቁጠር፥ ይህን መሰል አስተምህሮ በእውነተኞች ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ዘንድ ተቀባይነት የሌለው ነው በማለት በነቀፋ ወሰዱት። በቀጣዮቹ ሁለት መቶ ዓመታት ውስጥ የውጭ አገር ተወላጅ የሆነ ሰው ወደ ኢትዮጵያ በመጣ ቁጥር እምነቱ በኢየሱስ ሁላት ወይም አንድ ባሕርይ እንደሆነ ይጠየቅ ነበር። እኔ የማምነው በሁለት ባሕርያት ነው ካለ ተቀባይነት አያገኝም። የአንድ ባሕርይ አማኝ ሆኖ ከተገኘ ግን ተቀባይነትን ያገኛል። 

ጥያቄ፡- ዘድንግልንና ሱስንዮስን የካቶሊክን እምነት እንዲቀበሉ ፒያዝ እንዴት ሊያግባባ ቻለ? 

ጥያቄ፡- ሀ) ሜንዴዝ ከፒያዝ እንዴት ይለያል? ለ) ሜንዴዝ በተለይ የኢትዮጵያን ክርስቲያኖች የሚያስቀይም ምን ተግባር ፈጸመ? 

ጥያቄ፡– የሱስንዮስ ወደ ካቶሊክነት መግባት ውጤቱ ምን ሆነ? 

ጥያቄ፡- ንጉሥ ፋሲለደለ ወደ ዙፋን ከመጡ በኋላ ምን አደረጉ? 

ጥያቄ፡- ሀ) ካቶሊኮች ከመጡ በኋላ ክርስቶስ ሁለት ባሕርያት አሉት ብለው ሲያስተምሩ፥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ተቃውሞዋን እንዴት ገለጸች? ለ) ሱስንዮለ ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ ያላቸው ዝና እንዴት ያለ ነው? 

ጥያቄ፡– ዛሬ የቤተ ክርስቲያናቸውን ታሪክ ደህና አድርገው የሚያውቁ የተማሩ ኦርቶዶክስ ኢትዮጵያውያን ክርስቶስ ሁለት ባሕርያት አሉት ለሚላቸው ሰው መልሳቸው ምን ይሆናል ብላችሁ ታስባላችሁ? 

ዘዴ በታከለበትና በሚስብ የትምህርት አቀራረብ ፒያዝ አፄ ዘድንግልንና አፄ ሱስንዮስን ክርስቶስ መለኮታዊና፥ ሰብአዊ ባሕርያት እንዳሉት በማሳመን የካቶሊክን እምነት እንዲቀበሉ አድርጓል። በኣንጻሩ ግን ሜንዴዝ በነበረው ኃይለኛ ባሕርይና ለሕዝቡ እንግዳ የሆነ ሥርዓትን ለማስተዋወቅ በመጣሩ ብዙ ኢትዮጵያውያን ኦርቶዶክሶችን አስቀይሟል። እንዲሁም አፄ ሱስንዮስ የካቶሊክን አምነት በመቀበላቸው ምክንያት ጦርነት በአገሪቱ ውስጥ ከመነሣቱም ሌላ ኢትዮጵያም እንድትከፋፈል አድርጓል። አፄ ፋሲለደስ ከነገሡ በኋላ፥ ካቶሊኮችን አስወጥተው በፈንታው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ እምነት ወደ ስፍራው እንዲመለስ አድርገዋል። የዚህ ሁሉ ውጤት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ክርስቶስ ሁለት ባሕርያት አሉት የሚለውን አስተምህሮ እንደ ባዕድ እምነት እንድታየዉና እንድትቃወመው አድርጓል። ስለሆነም በኢየሱስ ሁለቱ ባሕርያት የሚያምኑ ምዕራባውያን ኣብያተ ክርስቲያናት እንደሚያጠፉ ጅቦች ተቆጥረዋል። ዛሬም እንኳ አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያውያን ድርጊታቸው አገሪቱን አሳልፎ ስለ ሰጠና ስለ ከፋፈለ ስለ አፄ ሱስንዮስ መልካም አመለካከት የላቸውም። ዛሬም ቢሆን ስለ ክርስቶስ ሁለት ባሕርያት የሚያስተምሩ የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች እንደ ሌላው ሱስንዮስ ተቆጥረው ክስ ሊመሠረትባቸው ይችላል። ምክንያቱም እንዲህ ያሉት ክርስቲያኖች እውነተኛ ክርስቲያኖች ተብለው ተቀባይነት ስለማያገኙ ነው። ብዙዎች የተማሩ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች፥ የካቶሊክ ሚሲዮናውያን በአገሪቱ ውስጥ ቀስቅሰውት የነበረውን ችግርና መለያየት ስለሚያስቡ ስለ ሁለት ባሕርያት የሚናገር ወይም የሚያስተምር ሰው ሲሰሙ ትዝ የሚላቸው የያኔው ተግባር ነው። 

በተዋሕዶ፥ በቅባትና በሦስት ልደት መካከል የነበረ ክርክር 

ከአፄ ሱስንዮስ ግዛት በኋላ በነበሩት ዓመታት፥ የክርስቶስ መቀባትን በተመለከተ፥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በተለያየ አስተሳሰብ ሥር ተከፋፈለች። በዚህ ነጥብ ላይ በመጀመሪያ የተነሡት ሁለት ቡድኖች ተዋሕዶና ቅባቶች ነበሩ። ተዋሕዶዎች ክርስቶስ ከመወለዱ በፊት ሰብአዊና መለኮታዊው ባሕርይ በአንድ አካል ውስጥ ሲጣመሩ በአዳም ውድቀት ምክንያት ጠፍቶ የነበረውን ራሱን ቀብቷል፤ ይህ ቅባት ወደ ክርስቶስ ሰብአዊነት በመመለስ ፍጹም ሰው አድርጎታል ብለው ያምናሉ። ቅባቶች ደግሞ፥ ክርስቶስ በአባቱ ተቀብቶኣል፥ ይህ ቅባትም ሁለቱ ባሕርያት በአንድ ባሕርይ እንዲጣመር አድርጓል ይላሉ። እንደዚሁም ሁለቱ ባሕርያት ሲጣመሩ፥ የክርስቶስ መለኮታዊ ባሕርይ ሰብኣዊውን ባሕርይ ይውጠዋል የሚል ትምህርትም ያስፋፉ ይመስላል። ዘግየት ብሎ ሌሎቹ በሦስተኛ ደረጃ የሚጠቀሱት የሦስት ልደት ኣማኞች ተነሡ። ይህ ቡድን ደግሞ ክርስቶስ ሦስት ጊዜ ተወልዷል የሚሉ ነበሩ። ይኸውም ለዘላለም ከእግዚአብሔር ኣብ፥ በሥጋ ደግሞ ከድንግል ማርያም ማኅፀንና በዮርዳኖስ ወንዝ በተጠመቀበት ጊዜ ደግሞ እንደ ጸጋ ልጅ ተወልዷል ብለው ያምናሉ። 

ወደ ኋላ ላይ በሚመጣው ትምህርት ስለ እነዚህ አሳቦች በዝርዝር እናጠናለን። ለዛሬው በዚህ ትምህርት ላይ ለመመልከት የምንፈልገው እያንዳንዱ ቡድን በየፊናው ትምህርታችን ክርስቶስ አንድ ባሕርይ እንደ ነበረውና እውነተኛ አምላክም እውነተኛ ሰውም መሆኑን ያስተጋባል በማለት የየግል አቋሙን እንዴት እንደሚከላከል ነው። ተዋሕዶዎች ስለ ቅባቶች ሲናገሩ፥ ክርስቶስ በአብ የተቀባ በማለት የክርስቶስን ክብር ዝቅ አድርገዋል፤ ይህም የሚያሳየው፥ ክርስቶስ ሙሉ በሙሉ እግዚአብሔር አይደለም ማለታቸው ነው ሊሉ ይተቿቸዋል። ቅባቶች ደግሞ በበኩላቸው ተዋሕዶዎችን፥ ተዋሕዶዎች ክርስቶስ በተቀባ ጊዜ ቅባቱ ሰብኣዊ ባሕርይውን አንጽቶታል ብለው ስለሚያምኑ፥ ባለ ሁለት ባሕርያት ያደርጉታል ባይ ናቸው። ታዲያ እነዚህ ሁለት ቡድኖች በየፊናቸው ደግሞ የሦስት ልደት አማኞችን በብርቱ ይቃወማሉ። የሚያቀርቡትም ምክንያት በእውነተኛ ውሕደት አያምኑም የሚል ነው። በመጨረሻውም የተዋሕዶ እምነት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ይፋዊ አስተምህሮ ሊሆን ችሏል። 

ጥያቄ፡- ሀ) ስለ ክርስቶስ መቀባት ተዋሕዶዎች ምን ያምኑ ነበር? ለአቋማቸው የክርስቶስን እውነተኛ ሰብአዊነትና አምላክነት ያስጠብቃል ብለው ያመኑት ለምን ነበር? 

ጥያቄ፡- ሀ) ቅባቶች ስለ ክርስቶስ መቀባት የነበራቸው እምነት ምንድን ነው? ለ) ቅባቶች አቋማችን ከማንም ይበልጥ የክርስቶስን አሃዳዊ ባሕርይ ያስጠብቃል ብለው ያመኑት ለምን ነበር? 21ኛ ጥያቄ፡- ተዋሕዶዎችና ቅባቶች በምን ምክንያት ሦስት ልደት አማኞችን አወገዙ? 

ስለ ክርስቶስ መቀባት ይካሄድ የነበረው ክርክር ትኩረት ሊሰጥበት የሚገባው አንደኛው ምክንያት፥ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የነበሩ የተለያዩ ቡድኖች ስለ ክርስቶስ አንድ ባሕርይ ምን ያህል ጠንካራ አቋም እንደነበራቸው ስለሚያመለክት ነው። ተዋሕዶዎች ክርስቶስ በአብ ተቀባ የሚለውን አስተምህሮ አይቀበሉም። ምክንያቱም ይህን እምነት የክርስቶስን እውነተኛ አምላክነት የሚክድ አድርገው ስለሚቆጥሩት ነው። ይህም ክርስቶስ መለኮታዊና ሰብአዊ የሚሆን አንድ ባሕርይ የለውም እንደ ማለት ስለሆነ ነው። ቅባቶች ደግሞ ተዋሕዶዎች፥ የክርስቶስ መቀባት ሰብአዊ ባሕርይውን መልሶለታል የሚለውን አቋም አይቀበሉም። ምክንያቱም፥ ይህ አቋም ክርስቶስ ሁለት ባሕርያት አሉት የሚለውን ስለሚያመለክት ነው። ይሁን እንጂ እነዚህ ሁለት ቡድኖች በበኩላቸው የሦስት ልደት አማኞችን ያወግዛሉ። ምክንያታቸው ባለ ሦስት ልደቶቹ ክርስቶስ የሁለት ባሕርያት ውሕደት መሆኑን አይቀበሉም የሚል ነው። ይህ የእርስ በርስ የአስተምህሮ ክርክርና አለመግባባት የኢትዮጵያ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን ለሦስት መቶ ዓመታት ከፋፍሏት ቆይቷል። ስለ ክርስቶስ መቀባት አስተምህሮ በሌላ ትምህርታችን ላይ እናጠናለን። ሆኖም የክርስቶስ ሁለት ባሕርያት በአንድ መለኮታዊና ሰብአዊ ባሕርይ ውስጥ ፍጹም መዋሐዳቸውን የማመኑ ጉዳይ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በጣም ጠቃሚ እንደሆነ በእነዚህ ቡድኖች መካከል የተካሄደው ክርክር ያስገነዝባል። 

ምንጭ፡- “አስተምህሮ ክርስቶስና ደኅንነት”፤ ጽሑፍ፣ በዶ/ር ስቲቭ ስራውስ፤ ትርጉም በኃይሉ ልመንህ

Exit mobile version