በዛሬው ትምህርታችን ውስጥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ስለ ክርስቶስ ተሠገዎ ስላላት ምሥጢረ እምነት አስተምህሮ እናጠናለን። እናንተም ብትሆኑ አብዛኛዎቹ የኦርቶዶክስ ምእመን ስለ ክርስቶስ ባሕርያት ያላቸውን አመለካከት ለማወቅ በተለይ ከሚቀርቡዋችሁ ከአንዳንዶቹ ጋር ልትወያዩ ትችላላችሁ። የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች የየትኛውም ቤተ ክርስቲያን አባሎች ይሁኑ የሚናገሩትን ነገር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አማንያን በምን ዓይነት መንገድ እንደሚገነዘቡት ማወቅ አለባቸው። ስለ ተሠገዎ ምሥጢር በምናስተምርበት ጊዜ፥ የምናቀርበው ትምህርት የመጽሐፍ ቅዱስን ትክክለኛ አሳብ በመልእክቱ ውስጥ የሚያስተላልፍ ሊሆን ይገባል። አንዳንድ ጊዜ ምዕራባውያን ስለ ክርስቶስ ፍጹም አምላካዊነትና ፍጹም ሰብአዊነት ባሕርይ ለመግለጽ የሚጠቀሙባቸው ቃላት ወደ አማርኛ ቋንቋ በሚተረጉሙበት ጊዜ ትክክለኛውን መልእክት ይዘው ለኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ላይደርሱዋቸው ይችሉ ይሆናል። ለመሆኑ ዛሬ ኦርቶዶክሳውያን ስለ ተሠገዎ ምሥጢር እምነታቸው ምንድን ነው?
ቤተ ክርስቲያኒቱ ስለ ተሠገዎ ምሥጢር ያላትን የእምነት አቋም «በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት፥ ሥርዓተ አምልኮትና የውጭ ግንኙነት» ብላ ሐምሌ 1988 ዓ.ም ባሳተመችው መጽሐፍ በገጽ 27 ላይ እንዲህ ብላለች፡
«መለኮት ከሥጋ ሥጋ ከመለኮት ጋር ያለ መለወጥ፥ ያለ መቀላቀል፥ ያለ መለያየትና ያለ መከፈል በተዋሕዶ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ሆነ። ሰው ከመሆኑ አስቀድሞ ሰውም ከሆነ በኋላ አንድ ወልድ አንድ ክርስቶስ ነው። (ቄርሎስ ሃይ. አበ. ምዕ. 78 ክፍ. 48 ቁ 9-18)። ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙም) በተዋሕዶ ሰው የሆነ አምላክ አምላክም የሆነ ሰው እርሱ ብቻ ነው ብሎኣል። ሀ. ኢ ምዕ. 61 ክፍል 4 ቁጥር 23. ሥጋም በተዋሕዶተ ቃል እንደ ከበረ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ‹በሥጋ የነበረ እንዴት በተዋሕዶተ ቃል ጠፋ። የቃል ክብር ለሥጋ በተዋሕዶ ገንዘቡ ሆነ› ብሎአል። (ዮሐ. አፈ. ሃይ/አ/ምዕ. 66. ክፍ. 9. ቁጥ. 18-19)።
ከተወለደም በኋላ ከኃጢአት በቀር ሰው የሚሠራውን ሥራ ሁሉ እየሠራ አደገ በዚህም ዓለም 33 ዓመት ከሦስት ወር ኖሮና አስተምሮ ስለ እኛ የሞት ፍርድን ተቀበለ፤ በመስቀል ተሰቅሎ ሞተ፤ በሞቱም ሞትን አጠፋ፤ ዓለምን አዳነ፤ ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በከርሰ መቃብር አድሮ ተነሣ» ይላል። በዚሁ መጽሐፍ ውስጥ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ስለ ተሠገዎ ምሥጢር እምነትዋ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተጻፈው እንዲህ ይላል፡
«ክርስቶስ ቃል የሆነው የእግዚአብሔር አንድ ባሕርይ ነው። ከባሕርያቱ ውሕደት በኋላ ክርስቶስ ሁለት ባሕርያት አለው ብሎ መናገር አይቻልም። ባሕርያቱ በተሠዎ አንድ ባሕርይ ሆነዋል፥ ስለዚህ ባሕርያቱ ያለመለወጥ፥ ያለመቀላቀል፥ ያለ መለያየትና ያለ መከፋፈል በተዋሕዶ አንድ አካል፥ አንድ ባሕርይ ሆነዋል። ባሕርይ ከባሕርይ ሳይቀላቀል መለኮት ቃል ከሥጋ ሥጋ ከመለኮት ቃል በተዋሕዶ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ሆነ… እርሱም በአምላክነቱ ከእግዚአብሔር አብ ጋር እኩል ነው። ከእኛም ጋር አንድ ሆነ አንድነቱም ከባሕርይው ውሕደት ነው። ቃል ሥጋ ሆነ የሚለው የተፈጸመው በድንግል ማርያም ማኅፀን ውስጥ በመፅነሱ ነው»።
ከዚህ በላይ ከተመለከትናቸው ነጥቦች ብዙ ሁኔታዎች ግልጽ ሆነዋል፡
1) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን፥ ስለ ክርስቶስ አምላክነትና ሰብአዊነት ታስተምራለች። እርሱም በአምላክነቱ ከእግዚአብሔር አብ ጋር እንድ በሰብአዊነቱም ከኃጢአት በስተቀር ከእኛ ጋር አንድ ነው። ከኃጢአት በቀር ሰው የሚሠራውን ሥራ ሁሉ ሠርቷል።
2) የክርስቶስን ባሕርይ ኣሃዳዊነት ለመጠበቅ ቤተ ክርስቲያኒቱ የክርስቶስ አምላክነትና ሰብአዊነት በተዋሕዶ አንድ ባሕርይ ሆኖአል። ክርስቶስ ከተሠገዎ በኋላ ሁለት ባሕርያት አለው የሚለውን አስተምህሮ አጥብቀው ይቃወማሉ። ወልድን በተዋሕዶ አሃዳዊነት ይሠራ ነበር ስለሚሉ ሰው በሆነው የእግዚአብሔር ልጅ ውሕደት ኣጥብቀው ያምናሉ።
3) የአምላክነትና የሰብአዊነት ውሕደት፥ የክርስቶስን ሰብአዊነት ከሌሎች ሰዎች ሰብአዊነት ይለይ አይለይ እንደሆነ አስተምህሮዋ ላይ ግራ መጋባት ይታያል። በአንድ በኩል ቤተ ክርስቲያኒቱ «ያለመቀላቀል፥ ያለመከፋፈል» ክርስቶስ እንድ አካል አንድ ባሕርይ ሆነ ትላለች። በሌላ በኩል ደግሞ «በሥጋ የነበረ እንዴት በተዋሕዶተ ቃል ጠፋ፥ የቃል ክብር ለሥጋ በተዋሕዶ ገንዘቡ ሆነ» እንደዚሁም፥ «ቃል የሆነው የመለኮት ባሕርይ ከሥጋ፥ ሥጋ ቃል ከሆነው ከመለኮት ባሕርይ ጋር አንድ ነው።» በማለት ታስተምራለች። እንዲህ ማለት የክርስቶስ አካል ሌሎች ሰዎች ያለባቸው ድክመቶች የሉትም፥ እንደዚሁም መለኮታዊው ባሕርይ ሥጋዊውን ባሕርይ ሲነካው ሥጋዊው ባሕርይ ተለውጦአል የሚል ይመስላል። ኢየሱስ ሰው የሆነው የእግዚአብሔር ልጅ ብቻ አይደለም፥ «በተዋሕዶ ሰው የሆነ አምላክ አምላክም የሆነ ሰው እርሱ ብቻ ነው፡፡» ይህ አገላለጽ የክርስቶስ ሰብአዊነት መለኮታዊ ሰብአዊነት ነበር የሚል ይመስላል። ሌሎች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ደራሲያን፥ የክርስቶስ አምላካዊና ሰብአዊ ባሕርያት በአንድ ባሕርይ እንደ ተዋሐዱና ክርስቶስም አንድም በአምላካዊነት አልያም በሰብአዊነት ባሕርይው እንደሚሠራ አድርገው ትኩረት በመስጠት ጽፈዋል። ብዙዎቹም ክርስቶስ በሥጋው ብቻ አልሞተም፥ በመለኮታዊና በሰብአዊ አምላክነት ጭምር ነው ሲሉ አበክረው ይገልጻሉ።
ጥያቄ፡- የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ስለ ክርስቶስ ባሕርይ በምታካሂደው ግልጽ ትምህርት አጽንኦት የምትሰጣቸው ሦስት ነጥቦች ምንድን ናቸው?
ጥያቄ፡- ሀ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ አስተምህሮ ከኬልቄዶኑ ጉባዔ አስተምህሮ እንዴት ይመሳሰላል? ለ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ትምህርት ከኬልቄዶኑ ጉባዔ አስተምህሮ ጋር በምን ይለያል?
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በምትሰጠው ግልጽ ትምህርት በሚከተሉት ነጥቦች አጽንኦት ታደርጋለች፡
1) ኢየሱስ ክርስቶስ ሰውም አምላክም መሆኑን፥
2) የክርስቶስ መለኮታዊነትና ሰብአዊነት በአንድ ባሕርይ እንደ ተዋሐዱ፥ በተናጠል እንደ አምላክ ወይም እንደ ሰው እንዳልሠራና ነገር ግን ሁልጊዜም የተዋሐደ ሰበ – አምላክ ሆኖ እንደ ሠራ፥
3) የክርስቶስ መለኮታዊነትና ሰብኣዊነት ፍጹም ከመዋሐዱ የተነሣ በሆነ መንገድ መለኮቱ ሰብአዊ ክፍሉን በመንካቱ ከሌሎች የተለየ ዓይነት መለኮታዊ– ሰብኣዊነት አድርጎታል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ልክ እንደ ኬልቄዶኑ ጉባዔ ኢየሱስ ክርስቶስ ኣምላክም ሰውም መሆኑን ታስተምራለች። እንደዚሁም ልክ እንደ ኬልቄዶኑ ጉባዔ የክርስቶስ ሰብኣዊ ባሕርይ ከመለኮታዊው ባሕርይ ጋር አይቀላቀልም በማለት በአንዳንድ ስፍራ ታስተምራለች። ይሁን እንጂ ቤተ ክርስቲያኒቱ፥ የክርስቶስ ሰብአዊና መለኮታዊ ባሕርይ በኣንድ ተዋሕደዋል በማለት በምትሰጠው ትምህርት ከኬልቄዶኑ ጉባዔ ትለያለች። ደግሞ ኢየሱስ በሰብኣዊ ባሕርይው ወይም በመለኮታዊው ባሕርይው በተናጠል ምንም ነገር አላከናወነም ከማለቷም ሌላ በሞተም ጊዜ በተዋሐደ አንድ ሰበ-ኣምላካዊ ባሕርይ ነው የሞተው ትላለች። በመጨረሻም አንዳንድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ የክርስቶስ ሰብአዊነት መለኮታዊ ሰብአዊነት ስለሆነ የእርሱ ሰብአዊነት እንደ ተቀረው የሰው ልጅ ሰብአዊነት እንዳልሆነ ተደርጎ ይቀርባል።
ጥያቄ፡- ባሕርይና ጠባይ ስለሚሉት ቃላት አስቡ። አካል ስለሚለውም ቃል አስቡ። ባሕርይ ወይም ጠባይ ሳይኖር አካል ሊኖር ይችላል? በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንና በምዕራባውያን መካከል ያለው የቋንቋ ልዩነት በምሥጢረ ተሠገዎ ግንዛቤአቸው እንዴት ያለ ተጽዕኖ ሊያሳድር ቻለ?
በርካታ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ደራሲያን፥ የኬልቄዶኑ ጉባዔ ክርስቶስ ሁለት ባሕርያትና አንድ አካል እንዳለው አድርገው የተሳሳተ ትምህርት በማቅረባቸው የእነርሱ የሃይማኖት መግለጫ በኢትዮጵያ ውስጥ ተቀባይነት የለውም ይላሉ። ለምሳሌ ያህል፥ ብርሃኑ ጎበና «አምደ ሃይማኖት» በሚለው መጽሐፉ ላይ፥ «አካል ያለ ባሕርይ፥ ወይም ባሕርይ ያለ አካል ዋጋ የለውም። ሁለት ባሕርያት ካሉ፥ ሁለት አካላት ሊኖሩ ይገባል» ብሏል።
የኬልቄዶኑን ጉባዔ ሃሳብ በአማርኛ ቋንቋ አገላለጽ ለመገንዘብ ሙከራ በሚደረግበት ጊዜ ግልጽ የሆነውን አሳብ ማግኘት የሚያስቸግር ይመስላል። በኬልቄዶኑ ጉባዔ ላይ የተገኙ የቤተ ክርስቲያን አባቶች የሃይማኖት መግለጫውን በጻፉበት ጊዜ፥ ሁለት ባሕርይ በኣንድ አካል በማለት ሊገልጹት የፈለጉት አሳብ የተካተተ ኢየሱስ በአንድ አካል ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው መሆኑን ለማሳየት ነበር። ይህን የኬልቄዶኑን የሃይማኖት መግለጫ አንድ ሰው በአማርኛ ቋንቋ ወስዶ ክርስቶስ ሁለት ባሕርያት ኣለው ብሎ ቢያስተምርህ፥ ብዙ ጊዜ የተምታታ አሳብ መስሎ ይታያል። እንደዚሁም አንድ ሰው ክርስቶስ ሁለት ባሕርያት አለው ብሎ ቢያስተምር፥ ይህ ሰው በሚሰጠው ትምህርት አንዳንድ ሰዎች ክርስቶስ በራሱ የተከፋፈለ ነው የሚል የተዛባ ግንዛቤ ሊወስዱ ይችላሉ።
በመሠረቱ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉ ብዙ ምእመናን ስለ ክርስቶስ ማንነት የተለያየ አስተሳሰብ አላቸው። ይህን በክርስቶስ ምሥጢረ ተሠገዎ ላይ የጀመርነውን ትምህርት ከማጠቃለላችን በፊት ለየት ያለ የተግባር ትምህርት ታከናውናላችሁ። ስለዚህ መጻሕፍቶቻችሁን ታስቀምጡና ለምታውቁዋቸው የኦርቶዶክስ ምእመናን ቃለ መጠይቅ ታደርጋላችሁ። ቃለ መጠይቅ እንድታደርጉላቸው ፈቃደኛ የሆኑትን ሦስት ሰዎች ምረጡ። ቃለ መጠይቅ እንድታደርጉላቸውም ፈቃደኞች ይሆኑ ዘንድ ስለ ሃይማኖት በመማር ላይ መሆናችሁን ግለጹላቸው። ከዚያም የእናንተ ሥራ እነዚህ ሦስት ሰዎች ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ማንነት ስላላቸው ግንዛቤ መጠየቅ ይሆናል። ቃለ መጠየቁን የምታቀርቡላቸው ሦስት ሰዎች አንዱ ወንድ፥ አንዲት ሴትና አንድ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ (ማለትም ቄስ፥ ዲያቆን፥ ደብተራ፥ ወይም መነኩሴ) ሊሆን ይችላል። ምናልባት የሚጠየቅ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ባታገኙ፥ አንድ ስለ ሃይማኖቱ ጠለቅ ያለ ትምህርት ያለውን የኦርቶዶክስ ሰው ልትጠይቁ ትችላላችሁ። ቃለ መጠይቁን ስታደርጉ፥ መልሱን ቃል በቃል ኣትጻፉት፥ አሳቡን ደህና አድርጋችሁ በማስታወሻ ያዙት።
ጥያቄ፡- ለቃለ መጠይቆቻችሁ የምትጠቀሙባቸው ጥያቄዎች የሚከተሉት ናቸው፡
1) በምድር ላይ በነበረ ጊዜ ኢየሱስ ክርስቶስ ማን ነበር?
2) ክርስቶስ በምድር ላይ በነበረ ጊዜ ስለነበረው ባሕርይ ዘርዝር።
3) ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ በነበረ ጊዜ አምላክ ነበር? ሰው ነበር? ወይስ ሁለቱንም ማለትም እግዚአብሔርም ሰውም? (መላሾቹ፥ እርሱ እግዚአብሔርም ሰውም ነበር ካሉ፥ ይህን ጥያቄ ቀጥላችሁ አቅርቡ)፡ ሰብአዊውና ኣምላካዊው ባሕርያቱ የተጣመሩበትን ሁኔታ ግለጽ።
4) አሁን ኢየሱስ ወደ ሰማይ አርጓል። ታዲያ እርሱ አምላክ ነው? ሰው ነው? ወይስ አምላክም ሰውም ነው?
5) አንድ ሰው ወደ ኣንተ ዘንድ ቢመጣና ኢየሱስ ሁለት ባሕርያት አሉት፥ እነርሱም መለኮታዊና ሰብአዊ ባሕርያት ናቸው ቢል፥ መልስህ ምን ይሆን?
6) ኢየሱስ አማላጅ መሆኑን ታምናለህ?
7) ስለ ኢየሱስ ሕይወት ዋና ቁም ነገር ነው የምትለው ምንድን ነው?)
የዛሬ ተግባራችሁ በሚቀራችሁ ጊዜ እነዚህን ቃለ መጠይቆች ማቅረብ ነው። ጠይቃችሁ የምታገኙዋቸውንም መልሶች በማስታወሻ ደብተሮቻችሁ ውስጥ ጻፉዋቸው።
ምንጭ፡- “አስተምህሮ ክርስቶስና ደኅንነት”፤ ጽሑፍ፣ በዶ/ር ስቲቭ ስራውስ፤ ትርጉም በኃይሉ ልመንህ
