Site icon

ኢየሱስ በሞቱ በሰይጣን ላይ ታላቅ ድልን ተቀዳጅቷል – ክፍል ሁለት 

በትናንትናው ቀን ክርስቶስ በሰይጣን ላይ ስለተቀዳጀው ድል ማጥናት ጀምረን ነበር። የዚህ የድል ትንቢት የተነገረው በኤድን ገነት ውስጥ እንደ ነበረና ይህም ቀደም ብሎ በኢየሱስ አገልግሎት ውስጥ እንደ ተጀመረ እና ኋላም ክርስቶስ በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ ግቡን እንደ መታ ተገንዝበናል። በእርሱ ለሚያምኑት የክርስቶስ ድል ተጨባጭ ውጤት ምንድን ነው? በዛሬው ዕለት ኢየሱስ በሰይጣን ላይ ስለ ተቀዳጀው ድል ስለ ማሳወቅ፥ ስለ ማስፋፋትና ስለ ድሉ ፍጻሜ እናጠናለን። 

በክርስቶስ ትንሣኤ የተገኘና የተነገረ ድል 

የኢየሱስ ከሞት መነሣት በመስቀሉ በሰይጣን ላይ የተገኘውን ድል ያረጋገጠ ከመሆኑም በላይ የድሉን ውጤት ለዓለም ሁሉ አስተጋብቷል። 

ጥያቄ፡- የሐዋ. 13፡37-39 አንብቡ። የትንሣኤው ውጤት ምንድን ነው? 

ጥያቄ፡- የሐዋ. 17፡31 እንብቡ። ትንሣኤው ምንን አረጋገጠ?

ጥያቄ፡- 1ኛ ቆሮ. 15፡20፥ 23-26 አንብቡ። የኢየሱስ ትንሣኤ የሚሰጠው ዋስትና ምንድን ነው? በእነዚህ ምንባቦች ውስጥ ቢያንስ ሦስት መልሶችን ፈልጉ። 

ጥያቄ፡– ኤፌ. 1:20-21 እንብቡ። እግዚአብሔር ኢየሱስን ከሞት ባስነሣው ጊዜ ምን ተፈጸመ? 

ጥያቄ፡– ኤፌ 4፡8 አንብቡ። ኢየሱስ ወደ ሰማይ ባረገ ጊዜ ምን አደረገ? 

የክርስቶስ ትንሣኤ ለሚያምኑበት ምን ጥቅም አስገኘላቸው? በአዲስ ኪዳን ውስጥ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ያስገኘውን ድል ትንሣኤው በዋስትና አረጋገጠልን። ድሉም በዓለም ሁሉ ላይ ታወቀ። የሐዋ. 13፡37-39 እንደሚለው ኢየሱስ ከሞት በመነሣቱ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የኃጢአትን ይቅርታ ያገኛል። ይህ ይቅርታም በሙሴ ሕግ አማካይነት የሚገኝ አይደለም ይላል። ትንሣኤው እንዳረጋገጠው በኃጢአታቸው ምክንያት በሰይጣን ባርነት ሥር ያሉና ስለ ኃጢአታቸውም ቅጣትን የሚጠባበቁ በኢየሱስ ክርስቶስ በሚሆን እምነት የኃጢአታቸውን ይቅርታ አግኝተዋል። 

የሐዋ. ሥራ 17፡31 እንደሚለው ኢየሱስ አንድ ቀን በዓለም ላይ እንደሚፈርድ ትንሣኤው አረጋግጦአል። ኢየሱስ በፍጥረቱ ላይ ያለው የገዢነት ሥልጣን በሰይጣንና በአጋንንቱ ላይ ያለውንም ሥልጣን የሚጨምር መሆኑን በአዲስ ኪዳን የሚገኙ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ይናገራሉ። ኢየሱስ በፍጥረት ሁሉ ላይ ፈራጅ እንደሚሆን በትንሣኤው ተረጋግጦአል። ኤፌ። 1፡20-21 እንደሚናገረው ክርስቶስ ከሙታን ተነሥቶ ወደ ሰማይ በወጣ ጊዜ፥ እግዚአብሔር ከግዛትና ከሥልጣን፥ ከኃይልና ከጌትነት በላይ አድርጎ አስቀመጠው ይላል። ሐዋርያው ጳውሎስ «ስለ ግዛት ሥልጣን፥ ኃይልና ጌትነት» በሚናገርበት ጊዜ በተለይ ስለ ሰይጣንና ስለ ሠራዊቱ መናገሩ ነው (ኤፌ. 6፡12፤ 1ኛ ቆሮ. 15፡25 ይመልከቱ)። የኢየሱስ ትንሣኤ ገዢአቸው ለመሆኑ፥ ትክክለኛ መብት ያለው ለመሆኑ ማረጋገጥ ነው። ጳውሎስ ኢየሱስ በሰይጣን ላይ ስለተቀዳጀው ድል የበለጠ ጉልህ ማብራሪያ በኤፌ. 4፡8 ውስጥ ስለ ትንሣኤና ስለ ዕርገት በተናገረው ላይ ገልጾአል። እንደሚለውም «ወደ ላይ በወጣ ጊዜ ምርኮን ማረከ፤ ለሰዎችም ስጦታን ሰጠ» ይላል። ኢየሱስ ከሞት ተነሥተ ወደ ሰማይ ባረገበት ጊዜ ሁኔታው ልክ አንድ ጄኔራል ድል አድርጎ በወታደሮቹ ታጅቦ በጦርነት የያዘውን ምርቱ እስከትሉ ከጦር ሜዳ እንደሚመለስ ዓይነት ነበር። ይህ ድል ያደረገ ጀኔራል በሚኖርበት ከተማ የድል ሰልፍ ካደረገ በኋላ ለሠራዊቱ ስጦታ ያድላል። በጳጳውሎስ አጻጻፍ «ምርኮዎች» የተባሉት ሰይጣንና መናፍስቱ ናቸው። የኢየሱስ ሠራዊት ደግሞ ቤተ ክርስቲያን ናት። የጳውሎስ አባባል አንድ) ጄኔራል ድል አድርጎ ሲመለስ ያገኘውን ምርኮ ይዞ እንደሚገባ ሁሉ፥ ኢየሱስም በመስቀል ላይ በሰይጣንና በሠራዊቱ ላይ የተቀዳጀው ድል በትንሣኤውና በዕርገቱ ተረጋግጦአል። 

ምናልባት የክርስቶስ ትንሣኤ በሰይጣንና በሞት ላይ የተቀዳጀው ድል ማረጋገጫና ለዓለም ሁሉ ማወጂያ መሆኑን በይበልጥ የሚገልጸው ክፍል 1ኛ ቆር. 15፤ 1ኛ ቆሮ. 5፡20፥ 23-26 ይሆናል። ቃሉም፥ «የክርስቶስ ትንሣኤ ከሙታን ለሚነሡ ሁሉ በኩር ነው» ይላል። በአሥረኛው ትምህርት ውስጥ እንደተመለከትነው የክርስቶስ ትንሣኤ በእምነት የክርስቶስ ለሆኑት ሁሉ ከሙታን የሚነሡ ለመሆናቸው ዋስትና ነው። እንደዚሁም የክርስቶል ትንሣኤ ክርስቶስ ለመጨረሻ ጊዜ አንድ ቀን ሙሉ በሙሉ ሰይጣንና ሠራዊቱን ድል እንደሚመታ ማረጋገጥ ነው። ማናቸውም («ግዛት፥ ሥልጣንና ኃይልን»፥ ቁጥር 24) ክዚያም ክርስቶስ የአጽናፈ-ዓለም ፍጹም ገዥ ይሆናል። እንደዚሁም በመጨረሻው ላይ ሞት ራሱ ጨርሶ እንደሚሸነፍ የክርስቶስ ትንሣኤ ማረጋገጫ ነው። ክርስቶስ ከመስቀል ላይ በሰው ልጅ ጠላቶች ላይ ያገኘው ድል በትንሣኤው ተረጋግጦ ድሉንም አሳውቆአል። ጠላቶች የተባሉት ሰይጣንና ሠራዊቱ፥ ወይም ክፉ መናፍስቱ፥ ኃጢአትና ሞት ናቸው። 

ድሉ በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ውስጥ ተስፋፋ 

ኢየሱስ በሰይጣንና በክፉ መናፍስት (ሠራዊት) ላይ የተቀዳጀው ድል፥ በዛሬዋ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ውስጥ እየተስፋፋ ነው። የኤፌሶን መልእክት ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሞቶ በሰይጣን ላይ የተቀዳጀው ድል በትንሣኤው አማካይነት እንዴት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንደ ተስፋፋ የሚገልጽ በመሆኑ በጣም ጠቃሚ ነው። 

ጥያቄ፡– ኤፌ 1፡22–23 አንብቡ። እግዚአብሔር ኢየሱስን የሁሉ ራስ አድርጎ የሾመው ለምንድን ነው? 46ኛ ጥያቄ፡– ኤፌ 2፡6 አንብቡ። ሀ) እግዚአብሔር በክርስቶስ ያስቀመጠን የት ነው? ለ) ኤፌ 2፡10 አንብቡ። በክርስቶስ ኢየሱስ የተፈጠርነው ምን እንድንሠራ ነው? 

ጥያቄ፡– ኤፌ 4፡11 አንብቡ። ሀ) እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያን ምን ስጦታዎችን ሰጠ? ለ) ኤፌ. 4፡12-13 አንብቡ። 

ጥያቄ፡– ኤፌ 6፡10-13 አንብቡ። ሀ) አማኞች የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ከለበሱ ምን ማድረግ ይችላሉ? ለ) ኤፌ 6፡14-17 አንብቡ። አማኞች የሰይጣንን ተቃውሞ ሊከላከሉ የሚችሉት በምን ዘዴ ነው? 

ክርስቶስ በሰይጣን ላይ ያገኘው ድል በመስቀልና በትንሣኤ ብቻ ተወስኖ አልቀረም። የዚህ ድል ውጤት በዛሬይቱ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተስፋፍቷል። ኤፌ 1፡22-23፥ እግዚአብሔር ኢየሱስን የሁሉ ራስ አድርጎ በሰይጣንና በሠራዊቱም ላይ፥ ቁጥር 21) ለቤተ ክርስቲያን ሾመው። የኢየሱስ ሥልጣን በሰይጣን ላይ መኖሩ ለቤተ ክርስቲያንም ይጠቅማታል። ከኢየሱስ ሥልጣን የተነሣ ቤተ ክርስቲያን የምታገኘው ጥቅም ምንድን ነው? በተቀረው የኤፌሶን ክፍል ውስጥ ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን ከክርስቶስ ድል ጥቅም የምታገኝባቸውን ሦስት መንገዶች ያስቀምጣል። ክርስቶስ በሰይጣንና በርኩሳን መናፍስቱ ላይ ካለው ሥልጣን ቤተ ክርስቲያን የምታገኘው የመጀመሪያው ጥቅም በኤፌ 2፡6 ውስሮ ይገኛል። ጳውሎስ እንደሚነግረን እርሱ ባዳነን ጊዜ እግዚአብሔር ከክርስቶስ ጋር በሰማያዊ ስፍራ አስቀመጠን፡ ዳግም በኃጢአታችን ሙታን አንሆንም፥ ለኃጢአተኛ ተፈጥሮአችንም ባሪያዎች አንሆንም። እንደዚሁም የሰይጣን ተከታይነታችን ይቀራል (ኤፌ. 2፡1-3)። በዚህ ፈንታ በሰይጣንና በመናፍስቱ ላይ ያለው የክርስቶስ የድል አድራጊነቱ ሥልጣን ተካፋዮች እንሆናለን። ስለ ዳንና በዚህ አዲስ ቦታ ላይ ስላለን አዲስ ሕይወትን በመኖር እግዚአብሔር የፈቀደልንን መልካም ሥራ እናከናውናለን (ኤፌ 2፡10)። 

ክርስቶስ በሰይጣን ላይ ከተቀዳጀው ድል ቤተ ክርስቲያን የምታገኘው ሁለተኛው ጥቅም በኤፌ 4፡8 ውስጥ ይገኛል። ቀደም ብለን እንዳየነው ሁሉ ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቶስ በሰይጣን ላይ የተቀዳጀውን ድል በትንሣኤውና በእርገቱ እውን ካደረገ በኋላ ለተከታዮቹ ስጦታዎችን አደለ ይለናል። ለቤተ ክርስቲያን ክርስቶስ ያደላቸው ስጦታዎች በኤፌ. 4፡11 ውስጥ ተዘርዝረዋል። እነዚህም፥ ሐዋርያት፥ ነቢያት፥ ወንጌል ሰባኪዎች፥ እረኞችና አስተማሪዎች ናቸው። እነዚህ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ሰዎች አገልግሎቱን ሁሉ ራሳቸው እንዲያከናውኑ ለቤተ ክርስቲያን አልተሰጡም። በአኳያው ኤፌ 4፡12-13 ያለው ክፍል እንደሚነግረን የእነዚህ ተሰጥኦ ያላቸው ሰዎች ተግባር እርስ በርስ አንዱ ሌላውን እንዲያገለግል ማዘጋጀት፥ ማሠልጠንና ማስታጠቅ ነው። ስለዚህ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉ ሰዎች የተዘጋጁና የታጠቁ ሊሆኑና አንዱ ሌላውን ለማገልገል ሲችል ብቻ ቤተ ክርስቲያን ኅብረትን አግኝታ በብስለት ታድጋለች። ክርስቶስ በሰይጣን ላይ ከተቀዳጀው ድል የተገኘችው የተባበረችና የደረጀች ቤተ ክርስቲያን ከክርስቶስ ቀጥላ በጠቃሚነትዋ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትቀመጥ ናት። 

ሦስተኛው ጥቅም በኤፌ. 6፡10-18 ውስጥ ይገኛል። አማኞች የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር በሚለብሱበት ጊዜ፥ የሰይጣንና የሠራዊቱን ጥቃት ፊት ለፊት ሊቋቋሙ ይችላሉ። እንዴት ያለውን ጥቃት ነው ሊቋቋሙ የሚችሉት? ከቁጥር 14-20 በግልጽ እንደተብራራው አማኛች የሰይጣንን ፈተና ሁሉ ለመቋቋም ይችላሉ። 

ጥያቄ፦ በኤፌ 6፡14-17 የተጻፈውን የጦር ዕቃ ብትለብሱ፥ የሰይጣንን ጥቃት ልትን፡ሙ የምትችሉባቸውን የተለያዩ ዘዴዎች ጻፉ? 

በኤፈሶን 6፡14-17 የተጠቀሰውን ዕቃ ጦር የለበሱ አማኞች ልባቸውንና አእምሮአቸውን በእግዚአብሔር እውነት፥ በቃሉና በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ከሞሉ፥ ኃጢአት እንዲሠሩ ለመገፋፋት ሰይጣን የሚያመጣባቸውን ፈተና ሁሉ ሊቋቋሙ ይችላሉ። ሰይጣን እንዲዋሹና እውነትን እንዲደብቁ በሚፈትናቸው ጊዜ፥ እውነተኞች ለመሆንና የእግዚአብሔርንም እውነት ሊያስተጋቡ ይችላሉ። እንደዚሁም ሰይጣን እንዲረክሱ ሲፈትናቸው፥ እነርሱ ን ይህን ተቃውመው የጽድቅ ሕይወትን ሊኖሩ ይችላሉ። ሰይጣን እምነታቸውን ለሌሎች ለማካፈል እንዲፈሩም ሆነ በሌሎች ላይ እንዲቆጡ በሚፈትናቸው ጊዜ፥ ይህን ተቋቁመው ወንጌሉን ያስፋፋሉ። ደግሞም ከሌሎችም ጋር በሰላም ይኖራሉ። ሰይጣን እንዲጠራጠሩ ሲፈትናቸው፥ እነርሱ ቀን ለእግዚአብሔር ታማኞች ይሆናሉ። እርሱንም አለኝታቸው ያደርጉታል፡ የዳኑ ሰዎች መሆናቸው ይታወቃቸዋል፤ ለእግዚአብሔር ቃል በመታዘዝ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ውስጥ ይኖራሉ። ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሰይጣንን ስላሸነፈው ዛሬ አማኞች በሰይጣን ጥቃትና ፈተና ላይ ድል አላቸው። 

ክርስቶስ በመስቀል ላይ ድልን አገኘ ማለት አማኞች በቂ እምነት ብቻ ካላቸው ሁልጊዜ ከደዌዎቻቸው ይፈወሳሉ ማለት ነውን? ደግሞስ ክርስቶስ ሰይጣንን ድል በመምታቱ፥ አማኞች ከደኅንነትና ከስደት ነፃ ይሆናሉ ማለት ነው? 

ጥያቄ፡- 1ኛ ዮሐንስ 5፡18 አንብቡ። ክርስቲያኖች ከሰይጣን ራሳቸውን የሚከላከሉበት ምን ተስፋ አላቸው? 

ጥያቄ፡– 2ኛ ጢሞ. 4፡20 አንብቡ። ሀ) ሙሉላ ጥሮፊሞስን በሚሊጢን ውስጥ ትቶት በሄደ ጊዜ ሁኔታው እንዴት ነበር? ) 2ኛ ጢሞ. 3፡12 አንብቡ። በመንፈሳዊነት ለመኖር በሚፈልጉት ላይ ምን ይደርሳል? 

ጥያቄ፡- 2ኛ ቆሮ. 6፡5 አንብቡ፡፡ ጳውሎስ በወንጌል ምክንያት ምን መከራ ደረሰበት? 53ኛ ጥያቄ፡- 2ኛ ቆሮ. 12፡7-10 አንብቡ። ሀ) እግዚአብሔር ወደ ጳውሎስ ሕይወት ምን እንዲመጣ ፈቀደ? ለ) ጳውሎስ እግዚአብሔር ይህን ነገር እንዲያርቅለት በጸለየ ጊዜ እግዚአብሔር ምን መልስ ሰጠው? ሐህ ይህ በጳውሎስ ሕይወት ላይ እንዲመጣ እግዚአብሔር ለምን ፈቀደ? 

ጥያቄ፡- ሮሜ 8፡28-29፣ 35-39 አንብቡ። ሀ) እግዚአብሔር ለሚወዱትና በእርሱ ለተጠሩት ምን ሥራ ይሠራል? ለ) ከክርስቶስ ፍቅር የሚለየን ምንድን ነው? 

አዲስ ኪዳን የሰይጣንን ጥቃት እንዴት መከላከል እንደሚገባን ሁለት የተለያዩ እውነቶችን ያስተምረናል። በእነዚህ ሁለት እውነቶች መካከል ስላለው ሚዛን መገንዘቡ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ በአንድ በኩል፥ አማኞች ከሰይጣን ጋር በሚያደርጉት ጦርነት የእግዚአብሔር መከላከያ አላቸው፡ በ1ኛ ዮሐ 5፡18፤ ያ ክፉ ማለትም ሰይጣን ከእግዚአብሔር የተወለዱትን እንደማይነካ ተስፋ ተሰጥቷል፤ በኤፌ. 6፡14-18 ከሰይጣን ጥቃት ራሳችንን የምንከላከልበት ዕቃ ጦር መኖሩን ተስፋ ተሰጥቷል። በሌላ በኩል፥ አዲስ ኪዳን በግልጽ እንደሚያስተምረው እግዚአብሔር ለበጎ፥ አማኞችን ለመገሠጽና ለመምከር ሰይጣን የሚያመጣውን ሥቃይ በአማኞች ሕይወት ላይ እንዲደርስ ይፈቅዳል። አንዳንድ ጊዜ ይህ ሥቃይ በሽታን ይጨምራል። በ2ኛ ቆሮ. 12፡7 ውስጥ ሐዋርያው ጳውሎስ እግዚአብሔር ሰይጣንን «የሥጋዬ መውጊያ» በሕይወቴ ላይ እንዲያመጣብኝ ፈቀደ ይላል። ይህ እንግዲህ አንድ ዓይነት የሰውነት ችግር ሊሆን፥ ይህም በሽታ ወይም የአካል ጉድለት ሊሆን ይችላል። ይህም ሰይጣን በጳውሎስ ሕይወት ላይ ያመጣው ዓይነት ችግር ነበር። በ2ኛ ጢሞ. 4፡20 ውስጥ ሐዋርያው ጳውሎስ ኮሚሊጢን በሄደ ጊዜ ወዳጁ ጥርፊሞስ ስለ ታመመ ትተት መሄድ ነበረበት። በግልጽ እንደሚታየው ጳውሎስ ወዳጁን ጥሮፊሞስን መፈወስ ባለመቻሉ፥ እንደ ታመመ ትተት ለመሄድ ተገደደ። ሮሜ 8፡18፥ 23፥35-39 እንደሚናገረው አንዳንድ ጊዜ ሥቃይ፥ ድህነትና ስደት በክርስቲያኖች ሕይወት ላይ ይመጣል። 2ኛ ጢሞ. 3፡12 እንደሚለው በመንፈሳዊነት ‘ሚኖሩ ሁሉ የስደትን ሥቃይ ይቀበላሉ። 

እነዚህን ሁለት እውነቶች በአንድነት በምንመለከትበት ጊዜ እግዚአብሔር ንዳንድ ጊዜ ሰይጣን በሽታን፥ ድህነትን፥ ወይም ስደትን በአማኞች ሕይወት ላይ እንዲያመጣ እንደሚፈቅድ እናስተውላለን። ነገር ግን ሁኔታዎች ሁሉ ምን ጊዜም በእግዚአብሔር ቁጥጥር ውስጥ ናቸው። ምንም እንኳን ሰይጣን በሕይወታችን ላይ ችግርን፥ ድህነትን፥ ወይም ስደትን ቢያመጣም፥ እነዚህ ሁሉ ከእግዚአብሔር ፍቅርና ከቁጥጥሩ አይለዩንም። ስለሆነም ከእግዚአብሔር ፍቅር የሚለየን ምንም ነገር አይኖርም። 

እግዚአብሔር ሰይጣን በሽታ፥ ድህነት፥ ወይም ስደት በአማኞች ሕይወት ላይ እንዲያደርስ በሚፈቅድለት ጊዜ ሁሉ፥ ለእኛ ፍቅርን የተላበሰና መልካምነት ያለው ዓላማ አለው። ይህንን እኛ በእምነትና በታዛዥነት ብንቀበል፥ እግዚአብሔር ሁልጊዜ በሽታውን፥ ወይም ስደቱን ኢየሱስን ለምንመስልበት መልካም ዓላማ በማዋል ሌሎችን ሰዎች ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ለማምጣት እንድንችል ይጠቀምበታል (ሮሜ 8፡28-29)። እግዚአብሔር የሥጋ መውጊያ ወይም ሕመም በጳውሎስ ላይ ሲያመጣ ሁሉም ነገር በእርሱ ቁጥጥር ውስጥ ነበር። ጳውሎስ በዚህ የሥጋ መውጊያ ወይም ሕመም እንዲሠቃይ እግዚአብሔር በፈቀደበት ጊዜ የራሱ የሆነ መልካም ዓላማ ነበረው። መልካሙ ዓላማ ጳውሎስ እንዳይታበይና በራሱ ሳይሆን በእግዚአብሔር ኃይል እንዲታመን ለማድረግ ነበር። 

ጥያቄ፡- አንድ ሰው ክርስቶስ ሰይጣንን በመስቀል ላይ ያሸነፈ በመሆኑ ክርስቲያኖች በቂ እምነት ካላቸው ከደዌአቸው ሁሉ ይፈወሳሉ፥ ወይም ክርስቲያኖች በእምነት ከጠየቁ ማንኛውንም ቁሳዊ ንብረት ሊያገኙ ይችላሉ ቢላችሁ ምን መልስ ይኖራችኋል? 

አንዳንድ ክርስቲያኖች ክርስቶስ ሰይጣንን በመስቀል ላይ ድል በመምታቱ ክርስቲያኖች በቂ እምነት ካላቸው ከበሽታቸው ሊፈወሱ ይችላሉ፥ እንደዚሁም እግዚአብሔርን ከጠየቁ ብዙ ቁሳዊ ሀብት ሊያገኙ ይችላሉ። እንደዚሁም ክርስቲያኖች ስደት ሊደርስባቸው አይችልም ይላሉ። ቀደም ሲል እንደተነዘብነው እግዚአብሔር ክርስቲያኖች እንዲታመሙ ይፈቅዳል፥ አንዳንድም ጊዜ አይፈውሳቸውም (2ኛ ቆሮ. 12፡8፤ 2ኛ ጢሞ. 4፡20)፥ እግዚአብሔር ድህነት እንዲደርስባቸው ያደርጋል (ሮሜ 8፡3፣ 2ኛ ቆሮ. 6፡5 እንደዚሁም ፊልጵስዩስ 4፡12 ይመልከቱ)። እንደዚሁም እግዚአብሔር ክርስቲያኖች እንዲሰደዱ ይፈቅዳል (2ኛ ጢሞ. 3፡12፤ 2ኛ ቆሮ. 6፡5)። በ1ኛ ዮሐንስ 5፡18 ተስፋ ሰይጣን ሊነካን አይችልም፤ የዕቃ ጦር ተስፋ በኤፌ. 6፡10-18 በኢየሱስ ክርስቶስ የምናምን አንታመምም፥ የስደት መከራ አይደርስብንም፥ እንደዚሁም ድሃ አንሆንም ማለት አይደለም። የ1ኛ ዮሐ 5፡18 ተስፋ አሳቡ እግዚአብሔር ለሰይጣን አሳልፎ አይሰጠንም፥ ስለዚህ ሰይጣን በሕይወታችን ላይ ሙሉ በሙሉ ቁጥጥር እንዲኖረው አይፈቅድለትም፥ እንቋቋመዋለን ማለት ነው። የኤፈ. 6፡10-18 ተስፋ አሳብ ክርስቲያኖች ልባችንና አእምሮአችንን በእግዚአብሔር ቃል ብንሞላና የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ እንዲቆጣጠር ብንፈቅድ፥ ሰይጣን ኃጢአትን እንድንሠራ የሚያቀርበውን ፈተና ልንቋቋም እንችላለን። 

በዚህ ዓለም ውስጥ ክርስቲያኖች ሙሉ ጤንነት፥ ሀብትና ከስደት ነፃ ሆነው ይኖራሉ ብለው የሚያስተምሩ ሰዎች፥ መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቶስ በሰይጣን ላይ ያገኘው አሸናፊነት የሚሰጠውን ጠቃሚ ትምህርት የሳቱ ናቸው። ምንም እንኳን በመስቀል ላይ የተገኘው ድል በትንሣኤው የታወጀና የተረጋገጠ ቢሆንም፣ በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ውስጥ የተስፋፋ ነው። ይሁን እንጂ ፣ የመጨረሻው የድሉ ትሩፋት ኢየሱስ ወደ ምድር እስከሚመለስ ድረስ ሊመጣ አይችልም። በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር በሽታ፥ ድህነት፥ ስደትና ኢ-ፍትሐዊነት እንዲወገድ ያደርጋል። እስከዚያ ድረስ ለታመሙት ወዳጆቻችን መጸለይ የክርስቲያኖች ግዴታ ነው (ያዕ. 5፡13-16)። እግዚአብሔር ይህን ጸሎት አድምጦ በሚፈውስበት ጊዜ ክርስቶስ ዳግም ተመልሶ ሙሉ በሙሉ በሽታን ሁሉ፥ ድህነትን፣ ኢ-ፍትሐዊነትን፣ ጥቃትንና ሞትን የሚያሸንፍበት ሁኔታና በሰይጣን ላይ ያገኘውን የመጨረሻውን ድል እንደምንቋደስ የሚገልጥ ትንሽ ቅምሻ ነው። እስከዚያ ድረስ እግዚአብሔርን ብንታዘዝና በእርሱም ብናምን ሰይጣን በሚያጠቃን ጊዜ ይሸነፋል። በዚህን ጊዜ እግዚአብሔር የሰይጣንን ጥቃት ለእኛ ጥቅም ያውለዋል። ይህም በእግዚአብሔር ፊት ትሑታን ሊያደርገን፥ በበለጠ ኢየሱስን እንድንመስል በማድረግና ብዙ ሰዎችን በክርስቶስ ወደሚገኘው ደኅንነት እንድናመጣ በማድረግ ነው። በዚህ ሕይወት ውስጥ ሰይጣንን የምናሸንፍበት ዋናው መንገድ ይህ ነው። 

በክርስቶስ ዳግም መምጣት ድሉ ፍጻሜ ያገኛል 

ምንም እንኳን ሰይጣን በመስቀል ላይ የተሸነፈና አሁንም በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት አማካይነት መሸነፉ ቢታወቅም፥ ክርስቶስ ፍጹም የሆነ የሰላም መንግሥት፥ የተሟላ ጤናና ፍጹም የሆነ ብልጽግናን በምድር ላይ ለማስፈን ዳግም እስከሚመጣ ድረስ የመጨረሻው ሽንፈት አይሆንም። 

ጥያቄ፡- ራእይ 2፡7-11 አንብቡ። ሀ) ክርስቶስ ወደ ምድር ከመመለሱ በፊት ወደፊት በሰይጣን ላይ ምን ይደርሳል (ቁጥር 7-9)? ለ) በሰይጣን ላይ የሚደርሰው ይህ መሸነፍ ምንን ያመለክታል (ቁ 10)? 

ጥያቄ፡- ራእይ 20፡10 አንብቡ፡ ከዘላለም በፊት ጥቂት ቀደም ብሎ፥ በሰይጣን ላይ በመጨረሻው ምን ይደርስበታል? 

የራእይን መጽሐፍ ዝርዝር አሳብ ለመገንዘብ በጣም አስቸጋሪ ነው። ሆኖም አንድ ነገር ግልጽ ነው። ከራእይ 12፡7-11 ድረስ በግልጽ እንደምንመለከተው፥ ወደፊት በአንድ ወቅት ሰይጣን በሰማይ ትልቅ ሽንፈት እንደሚደርስበት ነው። ይህ መሸነፍ የሚያመለክተው ሙሉና ፍጹም የሆነ የእግዚአብሔር መንግሥት መመሥረትና የክርስቶስ አገዛዝ በምድር ላይ የቀረበ መሆኑን ነው። በራእይ 20፡10 የሰይጣንን የመጨረሻ መሸነፍ እንመለከታለን። የእግዚአብሔር ዘላለማዊና ፍጹም የሆነ አገዛዝ ከመጀመሩ በፊት ሰይጣን ወደ እሳት ባሕር ይጣላል። በዚያም ሆኖ ለዘላለም ይሠቃያል። ስለሆነም ሰይጣን በመጨረሻው ላይ ፈጽሞ ሊሸነፍ ያን ጊዜ የእግዚአብሔር መንግሥት ለዘላለም ይቋቋማል። 

የክርስቶስ በመስቀል ላይ መሞት በሰይጣን ላይ ታላቅ ድል አስገኝቷል። ኃጢአት እንዲሠሩ የሚያደርገውን የሰይጣን ፈተና በመቋቋም፥ እንዲሁም ሰይጣን በሚያመጣው ጥቃት መካከል እግዚአብሔርን በመታመንና በመታዘዝ በዚህም ክርስቶስን በመምሰል በድላቸው ፍሬ ደስ ሊለን ይችላሉ።

ምንጭ፡- “አስተምህሮ ክርስቶስና ደኅንነት”፤ ጽሑፍ፣ በዶ/ር ስቲቭ ስራውስ፤ ትርጉም በኃይሉ ልመንህ

Exit mobile version