በደኅንነታችን ውስጥ ካገኘናቸው በረከቶች መካከል በጣም የሚያስደስተንና የሚያጽናናን የእግዚአብሔር ጎልማሳ ልጆች ከመሆናችን የተነሣ ያለን የተትረፈረፈ የርስት ዋስትና ነው። በዚህ ረገድ እግዚአብሔር አዲስ ሕይወትን፥ ከክርስቶስ ጋር ኅብረትን እንዲሁም ከበደላችን ነፃ መውጣትን የሰጠን ብቻ ሳይሆን በተጨማሪም የራሱ ልጆችና የሰማያዊ ክብር ወራሾችም እንድንሆን መብት ሰጥቶናል። የእግዚአብሔር አዋቂ (ጎልማሳ) ልጆች የመሆን በረከት የ«ጉዲፈቻ የማደጎ ልጅ» መሆን ማለት ነው።
ጥያቄ፡- ኤፌ 1፡5ን አንብብ፡፡ እግዚአብሔር ምን እንድንሆን ነበር የመረጠን?
ጥያቄ፡- ገላ.4፡1-7 አንብብ፡፡ ሀ) ገና ሕፃን ወራሽ የሆነ ልጅ ሁኔታ ምን ይመስላል (ቁ. 1-2)? ለ) እኛስ በዚህ ዓይነት ሁኔታ የነበርነው መቼ ነው? (ቁ 3) ሐ) ክርስቶስ ባዳነን ጊዜ ምንን ተቀበልን (ቈ 5)? መ) አሁን የእግዚአብሔር ልጆች እንደ መሆናችን መጠን በተጫማሪ እግዚአብሔር ምን አድርጎልናል (ቈ 7)?
ጥያቄ፡- ርሜ 8፡14-17 አንብብ። ሀ) በእግዚአብሔር መንፈስ ስለሚመሩት ያለው እውነታ ምንድን ነው (ቈ 14)? ለ) ምን ዓይነት መንፈስ ነው እና ያልተቀበልነው (ቁ 15 )? ሐ) የተቀበልነውስ ምን ዓይነት መንፈስ ነው (ቁ 15)?
መ) ያ መንፈስ ምንን ይመሰክርልናል (ቁ 16)? ሠ) የእግዚአብሔር ልጆች በመሆናችን በተጨማሪ የተረጋገጠልን ምንድን ነው ( 17)?
ጥያቄ፡- ሮሜ 8፡23 አንብቡ። ምንን እንጠባበቃለን?
ስለ ልጅነት ያለውን የደኅንነት በረከት ሁኔታ ከመገንዘባችን በፊት፥ ለለ ልጅነት ወይም እንደ ራስ ልጅ አድርጎ ስለ መቀበል፥ በአዲስ ኪዳን ዘመን የነበረውን ባሕል ማወቅ ይገባናል። ዛሬ በብዙ ባሕሎች በአዲስ ቤተሰቦች ውስጥ ልጆች ለማደጎ የሚወሰዱት የራሳቸው ወላጆች ሳይኖራቸው ሲቀር ብቻ ነው። የአንድ ሕፃን አባት ወይም እናት ሲሞቱ ወይም ልጃቸውን ሲጥሉ፥ በዚህን ጊዜ ለልጁ እንደ ወላጅ የሚሆኑ አዲስ አሳዳጊዎች ልጁን ይወስዱና እንደ ወለዱት ልጅ አድርገው ያሳድጉታል። ሆኖም፥ በአዲስ ኪዳን ዘመን ሮማውያን ያልወለዱትን ልጅ ወስደው ማደጎ የሚያሳድጉበት ለየት ያለ ባሕል ነበራቸው። ይህም አንድ ሰው ልጅ ያልወለደ ከሆነ፣ የሕፃኑ ወላጆቹ በሞት ባይለዩትምና በሚገባ ቢንከባከቡትም እንኳ የሌላ ቤተሰብን ልጅ ተቀብሉ በማደጎ ደንብ እንደ ራሱ ልጅ አድርጎ ያሳድገዋል። አንድ ሮማዊ የሌላውን ቤተሰብ ልጅ በማደጎ ወስዶ የሚያሳድገው ያፈራው ሀብትና ንብረት ወራሽ እንዲሆንለት ነው። ስለዚህ በርማውያኑ ባሕል የሌላውን ልጅ ወስዶ እንደ ራሱ ልጅ አድርጎ የማሳደግ ዓላማ የሀብትና ንብረት ወራሽ እንዲሆን የቤተሰቡ አባል የማድረግ ሂደት ነበር።
1. እንደ ራስ ልጅ በማደጎ ተቀብሎ የማሳደግ ሁኔታ በኃላፊው ዘላለም ውስጥ፡ ኤፌ. 1፡5
አዲስ ኪዳን በእግዚአብሔር ቤተሰብ እንደ ልጅ የተደረግንበትን ሁኔታ በሦስት ደረጃ ዎች ይመለከተዋል። ይህ መንፈሳዊ ሂደት ሦስት መሠረታዊ ደረጃ ዎች ያሉት ሲሆን፥ እያንዳንዱ ደረጃም ልጅ የመደረግ ሂደትን የተለየ አፈጻጸም አጽንኦት ይሰጥበታል። የዚህ እንደ ልጅ ወደ እግዚአብሔር ቤተሰብ የመምጣት ሁኔታ የመጀመሪያው ደረጃ ልጅነታችንን ለማረጋገጥ እግዚአብሔር ቀደም ባለው ዘመን የፈጸመው ተግባር ነው። በኤፌ 1፡5 ላይ «ልጆቹ እንድንሆን አስቀድሞ ወሰነን» ይላል። ሰኛው ትምህርት ላይ እንደተመለከትነው፥ እግዚአብሔር አስቀድሞ ባደረገው ምርግ መሠረት የወራሽነት መብት ሊሰጠን የቤተሰቡ አካል አድርጎ በልጅነት ተቀበለን። ነገር ግን እግዚአብሔር ለውርስ የደረስን ጎልማሳ ልጆቹ አድርጎ እንዴት ይቀበለናል? ዛሬስ የቤተሰቡ አካል አድርጎ ሊቀበለን ምን አድርጎአል?
2. በአሁኑ ደኅንነታችን እንደ ማደጎ ልጅ መሆናችን፡ ገላ. 4፡1-7
ጳውሎስ በገላ. 4፡1-7 ውስጥ እንደተናገረው፥ በኋለኛው ጊዜ እግዚአብሔር እንደ ልጆቹ አድርጎ እንዴት እንደ ተቀበለን ይገልጻል። ገለጻውንም በመቀጠል አንድ ልጅ ምንም እንኳን የወራሽነት መብት ቢኖረውም፣ በሕፃንነት ዕድሜ ባለበት ጊዜ በውርሱ ላይ ሥልጣን እንደሌለውና በዚህን ጊዜ ሁሉም ነገር በሞግዚቶች እጅ እንደሚሆን ያስረዳል። ሕፃኑ በዚህ ዕድሜው በሚገኝበት ጊዜ በአመዛኙ ከባርያ የማይለይ በመሆኑ የዚቶቹ ታዛዥ ሆኖ እንደሚቆይና እንደ ባለ ሙሉ ሥልጣን ወራሽ ሆኖ እንደማይታይ ያላነዝባል። ጳውሎስ እንደሚለው ሁላችንም በእምነት ወደ ክርስቶስ ከመምጣታችን በፊት የነበርንበት ሁኔታ ያን ይመስላል። የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን ለመጠራትም ሆነ የእርሱ ወራሾች ለመሆን ምንም ዓይነት ሕጋዊ መብት አልነበረንም። እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ሕጋዊ መብት እንዳለው ልጅ ሳይሆን በባርነት ደረጃ ላይ የነበርን ሰዎች ነን። ሙሉ በሙሉ ለዓለም ሥርዓቶች የተገዛን ነበርን።
ጳውሎስ ለዓለም ሥርዓቶች የተገዛችሁ ነበራችሁ ሲል ምን ማለቱ ነው? «ከዓለም መሠረታዊ ትምህርት» ሲል በጊዜው ለዚህ ማብራሪያ በሥራ ላይ የነበረው የግሪክ ቃል የሰማይን አካላት (ክዋክብትንና፡ ፕላኔቶችን) ይቆጣጠራሉ የተባሉ የግሪክ የሐሰት አማልክትንና የዓለምን ሕዝቦች የሚያመለክት ነበር። እነዚህ የሐሰት አማልክት የፍጥረትና የሕዝቦች «መሠረታዊ ተቆጣጣሪ» ኃይላት ነበሩ። በጊዜው ግሪክኛ ይናገሩ የነበሩ አይሁዳውያንም ይህን ቃል እግዚአብሔር በእነርሱ አማካይነት ሕጉን ለሙሴ የሰጠባቸውን መላእክትና (ገላ 3፡19፤ የሐዋ. 7፡53) በዓለም ሕዝቦች ላይ ተቆጣጣሪዎች ናቸው ብለው የሚያምኑባቸውን መላእክት ለመግለጽ ይጠቀሙበት ነበር። የእስራኤል ሕዝብም ሆነ የአሕዛብ የቅርብ ተቆጣጣሪዎች ነበሩ ባይ ናቸው። በዚያን ዘመን የሰዎችን ሕይወት ይቆጣጠራሉ ተብለው የሚታወቁ መሠረታውያን የዓለም ትምህርቶች ክፉና መልካም መላእክትን የሚያጠቃልሉ ኃይላት ነበሩ። ጳውሎስ ሊል የፈለገው አንድ ጊዜ እኛ በእነዚህ መናፍስት ኃይላት ቁጥጥር ሥር ነበርን፥ ዛሬ ግን ነፃ ነን ለማለት ነው። እውነትም ከአጋንንታዊ ኃይላት ማለትም ግሪኮች ይሰግዱላቸው ከነበሩት ዓይነት ሐሰተኛ አማልክት ቁጥጥር ነፃ ነን። ደግሞም መልካም በሆኑ መላእክት ከተሰጡት ሕጎች ቁጥጥር ነፃ ነን። ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት እንዲኖረን መልካም ይሁኑ ክፉዎች የማናቸውም መናፍስት ኃይላት አማላጅነት አያስፈልገንም። ስለዚህ ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት ሊያደናቅፉብን አይችሉም። ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት እንዲኖረን እንደ ግርዛት ያሉትን የአይሁዳውያንን ሥርዓት ከመከተል ነፃ ነን።
ከእነዚህ መናፍስት ኃይላት ነፃ የሆንነው እንዴት ነው? እግዚአብሔር ጌታ ኢየሱስ ሰው ሆኖ እንዲወለድ በላከው ጊዜ፥ የሕግ ባሪያዎች ከመሆን አድኖ እንደ ልጆቹ አድርጎ በመቀበል የቤተሰቡ አካል አደረገን። እንደ ጎልማሳ ልጆች መብትን ሰጠን። ከዚያ በፊት በመናፍስት ኃይላት ቁጥጥር ሥር የነበርንና የሌላ ቤተሰብ አካል ነበርን። አይሁዳውያን በሙሴ ሕግ ሥርዓት ሥር ነበሩ። ነገር ግን ::ግዚአብሔር እኛን እንደ ራሱ ልጆች የቤተሰቡ አካል አድርጎ ተቀበለን። ለውርስ የምንበቃ ጎልማሳ ልጆቹ አድርጎ የወራሽነት መብትን ሰጠን። መንፈስ ቅዱስም በውስጣችን አድሮ እኛ የእርሱ ቤተሰብ አካል መሆናችንን እንዲያሳስበንና እንዲያረጋግጥልን አደረገ። በዚሁ መሠረት እግዚአብሔር የመለኮታዊ ውርሱ ወራሾች እንድንሆን ጎልማሳ ልጆች አደረን።
ጥያቄ፡- ሀ) በአካባቢአችሁ የሚኖሩ ሰዎች በምን አኳኋን የመናፍስት ኃይላትን አማላጅነት ይሻሉ? ለ) ይህ ክፍል ለእነዚህ ሰዎች ምን መልእክት ይሰጣቸዋል? ሐ) በእናንተ አካባቢ ያሉ ሰዎች የብሉይ ኪዳንን ሥርዓተ አምልኮ መከተል እንደሚገባቸው የሚያስቡት በምን አኳኋን ነው? መ) ይህ ክፍል ለእዚህ ሰዎች ምን ትምህርት ይሰጣቸዋል? ገላ. 3፡23-25 እና 5፡1ን አንዳንድ አሳቦችን ላለመጨበጥ ያክል ተመልከት።
ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ሰዎች በመናፍስት ኃይል ቁጥጥር ሥር ያሉ ይመስላቸዋል። ብዙ ሰዎች መንፈሳዊ ኃይላትን ማክበርና የሕይወትን በረከት ለማግኘት፥ እንደዚሁም ከሚያጋጥማቸው ሁሉ ለመጠበቅ የመንፈሳዊ ኃይላት አማላጅነት የሚያስፈልጋቸው አድርገው ያምናሉ። ሌሎች ሰዎች ደግሞ መላእክትን ማክበርና ለአማላጅነት እነርሱን ለመማጠን ወደ እነርሱ ዘንድ መቅረብ እንዳለባቸው ይሰማቸዋል። አንዳንዶቹ ደግሞ ለመናፍስት ስጦታና መሥዋዕት ማቅረብን ተግባራቸው አድርገው ይይዛሉ፡ አንዳንድ ሰዎች እንዲጠብቋቸው ወይም በረከት እንዲያገኙ ለመናፍስት ማለትም ውቃቢ ወይም ዛር ስጦታና መባ ማቅረብ እንዳለባቸው ይሰማቸዋል። እርግጥ ሰዎች ክርስቶስን እንደ መድኃኒታቸው አድርገው ከመቀበላቸው በፊት እነዚህ ክፉ መናፍስት ተጽዕኖ ሊያደርጉባቸው ችለው ይሆናል። ነገር ግን ገላ. 4፡1-7 እንደሚነግረን፥ ማንኛውም ሰው አንዴ በክርስቶስ ካመነ በኋላ በመናፍስት ቁጥጥር ሥር ሊውል አይችልም። ያመኑ ሰዎች የመላእክትንም ሆነ የሌሎች መናፍስትን አማላጅነት አይሹም። ስጦታም ሆነ መሥዋዕት ለመናፍስቱ ማቅረብ አይኖርባቸውም። እግዚአብሔር ከማንኛውም መናፍስት ባርነት ነፃ አውጥቶ የቤተሰቡ አካል አድርጎአቸዋል። እግዚአብሔር እንደ ጎልማሳ ልጆቹ በመቀበል ለተትረፈረፈ ውርሱ ወራሾች አድርጎአቸዋል። ልጆቹ መሆናቸውንም እንዲያረጋግጥላቸው መንፈስ ቅዱስን ሰጥቶአቸዋል። እግዚአብሔር እኛን እንደ ልጆቹ ተቀብሎ የቤተሰቡ አካል አደረገን ማለት በምንም ዓይነት (ከአሁን ወዲያ እኛ) በክፉ መናፍስት ቁጥጥር ሥር ልንሆን አንችልም ማለት ነው።
ዛሬም ቢሆን በኢትዮጵያ ውስጥ አንዳንድ ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር ለመቀራረብና ቤተኛ ለመሆን የብሉይ ኪዳንን ሥርዓተ አምልኮ መፈጸም ያለባቸው መስሎ ይታያቸዋል። ስለዚህ የግድ መገረዝ እንዳለባቸው ወይም አንዳንድ የምግብ ዓይነቶችን መብላት እንደሌለባቸው ያስባሉ። እነዚህን ሥርዓቶች ካልጠበቁና፡ ካልፈጸሙ በስተቀር የእግዚአብሔር ቤተሰብ አካል ሊሆኑ የማይችሉ ይመስላቸዋል። ከዚህም በስተቀር እነዚህን ሥርዓተ አምልኮዎች ካልጠበቁና ካልፈጸሙ ደኅንነትን ሊያገኙ እንደማይችሉ ይመስላቸዋል። ገላ. 4፡1-7 ያለው ቃል ግን በመላእክት አማካኝነት በተሰጠ ሕግ ቁጥጥር ሥር አለመሆናቸውን በግልጽ ይነግራቸዋል (ገላ. 3፡19)። አሁን ግን እግዚአብሔር ጎልማሳ ልጆቹ ስለ አደረገን፥ በሕግ ሞግዚትነት ሥር አይደለንም (ገላ. 3፡25)። እግዚአብሔርን ለማገልገልና እርሱን ለማክበር በመንፈስ ኃይል ባገኘነው ነጻነት የሕግ ሥርዓቶች ላያስፈልጉን – የእግዚአብሔር ቤተሰብ መሆናችንን ለሌሎች ለመመስከር ነፃ ሆነናል (ገላ. 5፡1)።
3. የዛሬው ልጅነት የወደፊቱን ተስፋ ይዟል፡- ሮሜ 8
እግዚአብሔር ቤተሰቡ አድርጎ ለተቀበላቸው ጎልማሳ ልጆቹ የሰጠው ውርስ ምንድን ነው? ይህን በሮሜ 8፡14-17 ውስጥ ጳውሎስ አብራርቶ አቅርቦታል። በዚህም ውስጥ የእግዚአብሔር ልጆች ሆኖ ከእግዚአብሔር ቤተሰብ ጋር በመቆጠር ዛሬም ሆነ ለወደፊቱ ስለሚኖረው በረከት ገልጾአል። ጳውሎስ በዚሁ በርማ 8 ውስጥ እግዚአብሔር የሰጠንን አዲስ ሕይወት ለመኖር ስለሚያስችለን መንፈስ ቅዱስ በረከት ይናገራል። የመንፈስ ቅዱስ መኖር በእርግጥ እኛ የእግዚአብሔር ልጆች ለመሆናችን አመላካች ነው። መንፈስ ቅዱስ የፍርሃት መንፈስ አይደለም። የእግዚአብሔር ፍርድ ስለሚያስከትለው ሁኔታ እንድንፈራ አያደርገንም። ከሞት በኋላም ቢሆን ስላለው ሁኔታ እንድንፈራ አያደርግም። ይልቁንም መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ የሚያደርግ መንፈስ ነው። በልጅነት መቋ እግዚአብሔር ቤተሰብ እንድንቀላቀል የሚያደርገን እርሱ መንፈስ ቅዱስ ነው። መንፈስ ቅዱስ ጎልማሳ የእግዚአብሔር ልጆች እንድንሆን ያደርገናል።
የእግዚአብሔር ልጆች በምንሆንበት ጊዜ ሁለት በረከቶችን እናገኛለን። አንዱን አሁን ሌላውን ደግሞ ወደፊት እናገኛለን። በመጀመሪያ፥ አሁን የምናገኘው በረከት፥ መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጆች ስለመሆናችን የጠለቀ ዋስትና በመስጠት እግዚአብሔርን «አባ አባታችን» ብለን እንድንጠራው ያስችለናል (ሮሜ 8፡15)። «አባ» የሚለው ቃል በጳውሎስ ጊዜ የነበሩ ትንንሽ የአይሁድ ልጆች አባቶቻቸውን የሚጠሩበት ቃል ነበር። ምንም እንኳን ጳውሎስ ይህንን መልእክት ለሮሜ ሰዎች የጻፈበት ቋንቋ ግሪክኛ ቢሆንም፥ እግዚአብሔር ርኅሩኅ አፍቃሪና ተንከባካቢ መሆኑን የበለጠ ለመግለጽ ያስችለኛል በማለት ስሜቱን በራሱ አፍ መፍቻ የዕብራይስጥ ቃል በመጠቀም ጽፎላቸዋል። እንግዲህ መንፈስ ቅዱስ ለእውነተኛ አማኞች ሁሉ ይህንን የእግዚአብሔርን የሞቀ የአባትነት የፍቅር ዋስትናን ይሰጣል። ስለዚህ ትንንሽ ልጆች አባቶቻቸውን በሚቀርቡበት ሁኔታ እርሱን መቅረብ እንችላለን። ልጆች አባቶቻቸውን በፍቅርና በመልካም ሁኔታ በእምነትና በእርግጠኝነት እንደሚቀርቡ ሁሉ፥ እኛም ወደ እግዚአብሔር አባታችን ይህንኑ በመሰለ መንፈስ ልንቀርበው ይገባናል።
የእግዚአብሔር ልጅ መሆን ሲባል እግዚአብሔር አፍቃሪና ተንከባካቢ አባት ብቻ ነው ማለትም አይደለም። እግዚአብሔር እንደ ጎልማሳ ልጆቹ ተቀብሎ የራሱ ልጆች ያደረገን በመሆናችን አንዳንድ የወደፊት በረከቶች ወራሾችም ነን። ባለፈው ሳምንት ትምህርታችን እንዳየነው፣ ከክርስቶስ ጋር የተባበርን በመሆናችን፣ የክርስቶስ የሆነውን የተትረፈረፈ ብልጽግናም ወራሾች እንደምንሆን የተረጋገጠልን ነን፡ ከእርሱ ጋር አብረን ወራሾች ነን። የምንወርሰውም የሚጠብቀንን ሰማያዊ ክብር ይሆናል። ክርስቶስ በምድር ላይ በነበረ ጊዜ እንደ ተሠቃየና የሥቃዩ ተካፋዮች እንደሆንን ሁሉ፥ የሰማያዊ ክብሩ ተካፋዮች እንሆናለን። እንደ እግዚአብሔር ጎልማሳ ልጆች መሆናችንን ሰማያዊው ክብር የሚጠብቀን ለመሆኑ ማረጋገጫ ነው። አዎ፥ በምጥ ጭንቀት ተይዞ በመቃተት ላይ ባለ የበሰበሰ ዓለም ውስጥ በመኖር ላይ ነን (ሮሜ 8፡22)። አዎ፥ ከሥቃይ የተነሣ በሚቃትት በስባሽ ምድራዊ አካል እንኖራለን (ሮሜ 8፡18 እና 23)። ነገር ግን የእግዚአብሔር ጎልማሳ ልጆቹ ስለሆንን የከበረው የሰማያዊ ውርስ ዋስትና አለን። በመሆኑም ሞትን ወይም ከሞት በኋላ ስለሚሆነው ሁሉ መፍራት አይኖርብንም። ውርሳችን «የአካላችንን መዳን» ይጨምራል (ሮሜ 8፡23)። የመጨረሻው የልጅነት ደረጃ ችን በማይሞት አካል የመነሣታችን ሁኔታ ነው። የእግዚአብሔርን ክብር ውርስ ለመካፈል በምንነሣበት ጊዜ፥ እግዚአብሔር ለልጆቹ ተስፋ የገባላቸውን ውርስ እንቀበላለን። የእግዚአብሔር ቤተሰብ አካል ሆንን ማለት ሞትን የምንፈራበት ምንም ምክንያት አይኖረንም ማለት ነው። በትንሣኤ ለዘላለም የሰማይ ክብር ተካፋዮች መሆናችን የተረጋገጠ ለመሆኑ በፍጹም እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ መድኃኒታቸው መሆኑን አምነው የተቀበሉ ሁሉ የሰማያዊውን የክብር ውርስ ተካፋዮች እንደሚሆኑ የተረጋገጠ እውነታ ነው።
ጥያቄ፡- ሀ) በአካባቢአችሁ የሚኖሩ ሰዎች እግዚአብሔርን እንደ አፍቃሪ አባት ወይም እንደ ሌላ ይመለከቱታል? ለ) በልጅነት ምክንያት የሚገኝ በረከት ለእነርሱ በሕይወታቸው ውስጥ ምን ጥቅም ይኖረዋል? ሐ) በአካባቢያችሁ ያሉ ሰዎች ስለ ሞት ምን ያስባሉ? መ) በልጅነት ምክንያት የሚገኝ በረከት ለእነርሱ በሕይወታቸው ውስጥ ምን ጥቅም ይኖረዋል?
ዛሬ ብዙ ሰዎች እግዚአብሔርን እንደ አፍቃሪ አባት አይመለከቱም። እግዚአብሔርን በሞቀ ስሜት የመቅረብ ዝንባሌና ከእርሱ ጋር ሆነው ጊዜ የማሳለፍ ምኞትና ፍላጎት የላቸውም። ይልቁንም፣ እግዚአብሔርን የሚመለከቱት በኃጢአታቸውም ሊኮንናቸው የተዘጋጀ ጨካኝ ዳኛ አድርገው ነው። እግዚአብሔርን ስለሚፈሩት በተቻላቸው መጠን ከእርሱ ርቀው ለመኖር ይሻሉ። ነገር ቀን በእግዚአብሔር የሚያምኑ ሰዎች እግዚአብሔርን የሚፈሩበት ምንም ምክንያት የላቸውም። እግዚአብሔር በልጅነት ተቀብሎ የቤተሰቡ አካል ያደረጋቸው፥ የሚንከባከባቸውና የሚራራላቸው አባት ሆኖላቸዋል። አንድ ሕፃን ልጅ የአባትዋ ፍቅርና እቅፍ ደስ እንደሚላት ሁሉ፥ አማኞችም እንደዚሁ የአባታቸው የእግዚአብሔር ፍቅርና እንክብካቤ ያስደስታቸዋል። የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ መገኘት የእግዚአብሔርን የአባትነት የፍቅር በረከት እንድናገኝና እንድንረካበት ያደርገናል።
ዛሬ ብዙ ሰዎች የራሳችውንም ሆነ የዘመዶቻቸውን ሞት ይፈራሉ። ከመቃብር ባሻገር ስላለው ሁኔታ ይጨነቃሉ። የሰማይ ክብር ተካፋዮች እንደሚሆኑ ምንም ዓይነት መተማመኛ የላቸውም። እንዲሁም ለዘላለም ሕይወት በትንሣኤ እንደሚነሡ እርግጠኞች አይደሉም። አማኞች ግን በክርስቶስ ስለሆኑ ስለ መቃብር የሚፈሩበት አንዳችም ምክንያት የላቸውም። እግዚአብሔር በልጅነት ደረጃ ተቀብሉ የቤተሰቡ አካል በማድረግ እውነተኛ ውርስን አውርሶአቸዋል። እንደዚሁም የሰማዩ ክብር ወራሾች ናቸው። ከክርስቶስ ጋር አብረው ይወርሳሉ። በትንሣኤ የክብሩ ተካፋዮች እንደሚሆኑ ከእግዚአብሔር ተስፋ ተሰጥቶአቸዋል። በልጅነት የእግዚአብሔር ቤተሰብ አካል መሆናችን የዚህ ዓለም እንዲሁም የሟች ሥጋችን ሥቃይ ከሞት በኋላ በሰማያዊ ክብር እንደሚለወጥ አስደናቂ የሆነ ዋስትናን ሰጥተናል።
ምንጭ፡- “አስተምህሮ ክርስቶስና ደኅንነት”፤ ጽሑፍ፣ በዶ/ር ስቲቭ ስራውስ፤ ትርጉም በኃይሉ ልመንህ
