Site icon

የዘላለማዊ ዋስትና ማረጋገጫና የእግዚአብሔር ቅዱሳን ጽናት፥ ክፍል 2 

በትናቱ ዕለት ትምህርታችን ስለ አማኞች ዘላለማዊ ዋስትና ማረጋገጥ ወይም ጥበቃ ማጥናት ጀምረናል። በዚህ ትምህርት ላይም፥ አማኞች በደኅንነታቸው ረገድ ሁኔታው ዋስትና እንዳለውና የተጠበቀላቸው መሆኑን ተመልክተናል። ይህ ሊሆን የቻለበትም ምክንያት፥ ከእግዚአብሔር ጋር በመታረቃቸውና ሰላምንም በመመሥረታቸው ምክንያትና እንደዚሁም እግዚአብሔር ሁልጊዜ የጀመረውን ሥራ ስለሚፈጽም ነው። ከዚህም ጋር መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉ በመሆናቸውና ኢየሱስ ራሱ ስለሚጠብቃቸው፥ ከዚህም የተነሣ አዲስ ሰዎች ስለሆኑ ነው። ዛሬ ደግሞ አማኞች በተጨማሪም ለዘላለም የተጠበቁ የሆኑበት ምክንያት እያንዳንዳቸው የክርስቶስ አካል ክፍሎች ስለሆኑና ኃጢአት በሚሠሩበት ጊዜ ኢየሱስ ስለሚማልድላቸውም እንደሆነ እናጠናለን። እንዲሁም በርሜ ምዕራፍ 8 ውስጥ ስለ አማኞች ዘላለማዊ ዋስትና መጠበቅ ጠቃሚ የሆነ አጠቃላይ ትምህርትን በመከታተል፥ አማኞች ስለ ዘላለማዊ ዋስትናቸው መጠበቅ ስለሚኖራቸው ስሜት እናስተውላለን። 

6. አማኞች ዘላለማዊ ዋስትናቸው የተጠበቀ ነው። ምክንያቱም እያንዳንዳቸው የክርስቶስ አካል ክፍሎች ስለሆኑ ነው።

ጥያቄ፡- 1ኛ ቆሮ. 12፡27 አንብብ። እያንዳንዱ አማኝ ምን ይሆናል? 

በ17ኛው ትምህርት ውስጥ እንደ ተመለከትነው፥ በክርስቶስ በማመን መድኃኒቱ አድርጎ የተቀበለው ሁሉ፥ የክርስቶስ የአካሉ ክፍል እንደሚሆን አስተውለናል። 1ኛ ቆሮ. 12፡27 እንደሚያስገነዝበው፥ እያንዳንዱ አማኝ የአካሉ ክፍል እንደሆነና እያንዳንዶቹ አማኞችም በመሰባሰብ የክርስቶስ አካል እንደሚሆኑ ይናገራል። ስለዚህ በዚህ ምድር ላይ ስላለን ሁላችን በአንድነት የክርስቶስ አካል በመሆን፥ እርሱን ለዓለም በጉልህ ማሳየት ይገባናል። አማኞች በእውነተኛው አኳኋን ደኅንነታቸው የተረጋገጠላቸው ካልሆነ በስተቀር፥ የክርስቶስ አካል አንድ መሆኑ ቀርቶ ይከፋፈላሉ። ቀን አንድ ሰው በክርስቶስ ካመነና ለዘላለሙም የአካሉ ክፍል ከሆነ፥ ደኅንነቱም ለዘላለም ዋስትና ያለውና የተጠበቀ ይሆናል። 

7. አማኞች ኃጢአት በሚሠሩበት ጊዜ፥ ኢየሱስ ስለሚማልድላቸው፥ ለዘላለም ዋስትናቸው የተጠበቀ ነው። 

ጥያቄ፡- ሮሜ 8፡34 እንብብ። ኢየሱስ አሁኑኑ ስለ እኛ ምን እያደረገ ነው? 

ጥያቄ፡- 1ኛ ዮሐ 2፡1-2 አንብብ። ሀ) አማኞች ኃጢአት በሚያደርጉበት ጊዜ ስለ እነርሱ ሆኖ የሚናገር ማን ነው? ለ) ምልጃቸው በምን ምክንያት ውጤታማ ሊሆን ቻለ? 

ጥያቄ፡- ዕብ 7፡24-25 አንብብ። ኢየሱስ ስለ እኛ የሚያደርገው ጸሎት ውጤት ምንድን ነው? 

ብዙ ክርስቲያኖች ኃጢአት በሚሠሩበት ጊዜ እግዚአብሔር የሰጣቸውን ደኅንነት የሚቀማቸው እየመሰላቸው ይሸበራሉ። ነገር ግን በትናንትናው ትምህርታችን ውስጥ በሮማ 8፡34 እንደ ተመለከትነው፥ ኢየሱስ በእግዚአብሔር ቀኝ ሆኖ ስለ እኛ እንደሚማልድ ተገንዝበናል። በ1ኛ ዮሐ 2፡1 እኛ ኃጢአት በምናደርግበት ጊዜ ኢየሱስ ስለ እኛ እንደሚማልድ በቀልጽ ይነግረናል። ኢየሱስ ስለ እኛ የሚያቀርበው ምልጃ ውጤታማ እንደሚሆን እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን፥ ምክንያቱም እርሱ ራሱ የእግዚአብሔርን ቁጣ የሚመልስ መሥዋዕት ስለሆነ ነው። የኃጢአታችንን ቅጣት የከፈለልንና በእግዚአብሔር ቁጣ ምክንያት ስለ ኃጢአታችን የተሠቃየው እርሱ አሁንም ኃጢአት በምንሠራበት ጊዜ ይማልድልናል። ዕብራውያን 7፡24-5 ያለው ክፍል ክርስቶስ ባለማቋረጥ ስለ እኛ የሚያደርገው ምልጃ ፍጹም የሆነ ደኅንነት እንደምናገኝ ያረጋግጥልናል። በትምህርት 12 ውስጥ እንደተመለከትነው፥ እግዚአብሖር ኃጢአትን ይጠላል። በነገው ትምህርትም እንደምናጠናው የክርስቲያኖች ኃጢአት ሁልጊዜ የከፋ ውጤት ይኖረዋል። ነገር ቀን ኃጢአት በምንሠራበት ጊዜ፥ ኢየሱስ ይማልድልናል። አማኞች ደኅንነታቸውን የሚያጡበት ጊዜ ቢኖር፥ የኢየሱስ ጸሎት በማይመለስበት ጊዜ ነው። በእርግጥ ደግሞ የኢየሱስ ጸሎት ሁልጊዜ ይመለሳል። ኢየሱስ ሁልጊዜ የሚማልድላቸው በመሆኑ፥ አማኞች ደኅንነትን በማግኘታቸው ረገድ እርግጠኞች መሆናቸውን ሊገነዘቡ ይገባል። 

8. ጠቃሚ የሆነ ማጠቃለያ፡- ሮሜ 8፡31-39 

ጥያቄ፡- ሮሜ 8፡31–39 አንብብ። ሀ) እግዚአብሔር ልጁን ለእኛ የሰጠ ስለሆነ፥ ከልጁ ጋር ምንን እንደሚሰጠን እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን? (ቁጥር 32) ለ) ሐዋርያው ጳውሎስ በቁጥር 33፡34ና 35 ውስጥ ለጠየቃቸው ጥያቄዎች ውስጠ ታዋቂ ሆኖ የቀረበው መልስ ምንድን ነው? ሐ) እንደ ቁጥር 38ና 39፥ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን የሚችል ምንድን ነው? 

በሮሜ 8፡31-39 የቀረበው ቃል፥ ጳውሎስ ከሮሜ ምዕራፍ 5-8 ያቀረበው ትምህርት ማጠቃለያ ወይም የተሰባሰበ አሳብ ሲሆን፥ አሳቡም ስለ አማኛች የደኅንነት ዋስትና መረጋገጥ የሚናገር ነው። በሮሜ 8፡31-32 ውስጥ የማጠቃለያ አሳቡን በሚጀምርበት ጊዜ፥ እግዚአብሔር እስከ ዛሬ ያደረገልን ተግባር፥ ያጸድቀናል፥ መንፈስ ቅዱስን ይሰጠናል፥ ያስታርቀናል፥ የጀመረውን ሥራ ይፈጽምልናል፥ ደግሞም የዘላለም ሕይወትን ይሰጠናል በማለት ያረጋግጥልናል። ከዚያም በቁጥር 33-35 ውስጥ ጳውሎስ አማኞች ለዘላለም የጻኑ መሆናቸውን ለመግለጽ፥ ሦስት ጥያቄዎችን ይጠይቃል። በመጀመሪያም፥ የሚያቀርበው ጥያቄ፥ «በእግዚአብሔር ፊት በድፍረት ቆሞ አማኞችን በደለኞች ናቸው ብሎ በመክሰስ፥ በኃጢአታቸው ምክንያት መሠቃየት ይገባቸዋል የሚል ይኖር ይሆን?» የሚል ሲሆን፥ መልሱም «በእግዚአብሔር ፊት በድፍረት ቆሞ አማኛችን የሚከስስ ሊኖር አይችልም። ምክንያቱም እግዚአብሔር አስቀድሞ «በደለኞች አይደሉም»፣ በኢየሱስ ደም ምክንያት «ጻድቃን» ናቸው ሲል አስታውቋልና ነው። ስለዚህ እግዚአብሔር አስቀድሞ «በደለኞች አይደሉምስላለ፥ በክርስቶስ አማኛች የሆኑትን ሁሉ ተሳክቶለት ሊከስስ የሚችል ከቶ አይኖርም። 

በሁለተኛ ደረጃ ጳውሎስ በሚያቀርበው ጥያቄ፥ አማኞች በኃጢአታቸው ምክንያት እንዲቀጡ ማን ሊኮንናቸው ይችላል? የሚል ነው። ለጥያቄውም መልስ ለመስጠት ሲል ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አስቀድሞ ለአማኞች ኃጢአት ቅጣት አጸፋውን የከፈለ በመሆኑ፥ ፈራጅ በሆነው በእግዚአብሔር ፊት ቆሞ እንደሚማልድላቸው ያስታውሰናል። ሰይጣን አማኞችን በእግዚአብሔር ፊት በሚከስስበት ጊዜ፥ በአማኞች ፈንታ ለመናገር ጌታ ኢየሱስ በእዚያ ነው። እርሱም ሲናገር፥ «አዎን! ይህ ሰው ሊኮነን የሚገባው ኃጢአተኛ ነው። ነገር ግን እኔ ስለ እርሱ ኩነኔ ሥቃይን ተቀብያለሁ። ስለ ኃጢአቱም ይከፍለው የነበረውን ቅጣትም ከፍየለታለሁ። ስለዚህ የሚኮነንበት ምንም ምክንያት አይኖርም» በማለት ይመልሳል። በትምህርት 17 ውስጥ በሮሜ 8፡1 እንደተመለከትነው፥ ከክርስቶስ ጋር ኅብረት ያላቸው ሁሉ አይኮነኑም። ጳውሎስ ደግሞም ሲናገር፥ ከክርስቶስ ጋር የተባበርን እንደ መሆናችንና ኢየሱስም በእግዚአብሔር ፊት ቆሞ ስለ እኛ ስለሚማልድ፥ ኩነኔ ጨርሶ ሊኖርብን አይችልም ይላል። 

ሦስተኛው ጳውሎስ የሚያቀርበው ጥያቄ አማኞችን ማንኛውም ነገር ቢሆን፥ ከእግዚአብሔር ፍቅር የሚለያቸውና የእግዚአብሔርን ዘላለማዊ ውርስ የሚያሳጣቸው እንደሌለ ነው። በተለይም እርሱን የሚያሳስበው በአማኞች ሕይወት ውስጥ ስለሚከሰተው የሥቃይ ሁኔታ ነው። በአማኞች ሕይወት ውስጥ ሥቃይ አለ ማለት፥ የአማኞች ሕይወት ከእግዚአብሔር ፍቅር ይለያል ማለት ነውን? እንደዚሁም አማኞች በስደት፥ በረሃብ፥ በድኅነትና በጦርነት ምክንያት ሥቃይን ቢቀበሉ፥ ይህ ሁሉ ከእግዚአብሔር ፍቅር ለይቶ ዘላለማዊ ውርሳቸውን ያሳጣቸዋል ማለት ነውን? አይደለም! ጳውሎስ መዝሙር 44፡22ን በመጥቀስ፥ የእግዚአብሔር ተከታዮች ለሆኑት ሁሉ ሥቃይን መቀበል የተለመደ ክስተት በመሆኑ እንደ ቁጣ ሊታይ አይገባም ይላል። በእግዚአብሔር የሚያምኑ ሰዎች ሁሉ ሁልጊዜ እንደሚታረዱ በጎች ይቆጠራሉ። ምንም እንኳን አማኞች ሥቃይን የሚቀበሉ ቢሆኑም፥ በመጨረሻው ቀን ድልን እንደሚቀዳጁና ዘላለማዊ ውርስን እንደሚያገኙ የተረጋገጠላቸው ሐቅ ነው (ቁጥር 37)። 

በመጨረሻውም ላይ፥ በቁጥር 38 እና 39 ውስጥ ሐዋርያው ጳውሎስ ታይቶ ያልታወቀና አሁን የታየ እንግዳ ነገርም ቢሆን፥ አማኞችን ከእግዚአብሔር ፍቅር ፈጽሞ ሊለያቸው እንደማይችል በማረጋገጥ ነገሩን ይቋጫል። በዚህ ማጠቃለያ አሳቡም ላይ አማኞችን ከእግዚአብሔር ፍቅር ለመለየት የሚሞክሩ ጠላቶችን በዝርዝር ይገልጻል። እነዚህም፥ ዲያቢሎስ፥ ሞት፥ ወደፊት የሚሆነው ነገር ጥርጣሬና የመሳሰሉትን አደናቃፊዎች ከዘረዘረ በኋላ፥ ምንም ልንፈራው የሚገባን ነገር ከቶ ሊኖር እንደማይችል በማበረታታት ነገሩን ይደመድማል። የትኞቹም ዓይነት ጠላቶቻችን ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለዩን አይችሉም፡፡ 

Tያቄ፡- ሀ) ከእግዚአብሔር ሊለየን ይሆናል ብላችሁ አንዳንዴ የምትፈሩት ነገር ምንድን ነው? ለ) ይህ የተመለከታችሁት ክፍል እንዴት ሊያጽናናችሁና አለኝታ ሊሆናችሁ ይችላል? 

ሁሉም አማኞች ቢሆኑ በሕይወታቸው ውስጥ ጥርጣሬ የሚያጋጥማቸው ወቅት አለ። ይህም ሊከሰት የሚችለው ስለ መዳናቸው ተጠራጥረው ፍርሃት በሚሰማቸው ጊዜ ነው። ይህ የጥርጣሬ ስሜትም ወደ አእምሮአችን የሚገባው በሰይጣን አማካይነት ነው። ሰይጣን ስለ እግዚአብሔር ፍቅርና ስለ እርሱ እንክብካቤ እንድንጠራጠር ይፈልጋል። ስለ ዘላለማዊ ደኅንነታችንም ጥርጣሬ እንዲገባን ያደርጋል። ከዚያም ያለፈው ኃጢአታችን ፊታችን ተደቅኖ እንዲታወሰንና ጨርሶ ወደ እግዚአብሔር ፊት ለመቅረብ ብቃት የሌለን አድርጎ ያሳየናል። እኛም ምንኛ ኃጢአተኛች መሆናችንን በምናስታውስበት ጊዜ፥ ስለ ደኅንነታችን መጠራጠር እንጀምራለን። እንደዚሁም ሰይጣን የአጋንንቱን ኃይል አጉልቶ ሊያስታውሰን ይሻል። ከዚህም የተነሣ ስለ ሞትና ወደፊት ስለሚሆነው ሁሉ እንድንጠራጠር ያደርጋል። «ምን ሊሆን እንደሚችል የምታውቀው ምን ነገር አለ?» በማለት ይጠይቃል። ይቀጥልና፥ «ወደፊት ስለሚሆነው ነገር፥ ስለ ሞትና መቃብር መፍራት አለብህ። እንዲሁም የማንኛውንም አጋንንቶቼን ኃይልና አቅም መፍራት አለብህ» ይላል። ነገር ግን እግዚአብሔር በተስፋው ቃል እንዳረጋገጠው፥ በክርስቶስ የሚያምኑትን ሁሉ ኃጢአታቸውንና በደላቸውን ይቅር ብሎአቸዋል። እርግጥ ነው፥ እኛ የእግዚአብሔር ደኅንነት የማገባን ኃጢአተኞች ነን። በዚህ በኃጢአታችን ሁኔታና በክፋታችን ውስጥ ሆነን በእግዚአብሔር ፊት መቆም እንችልም። ነገር ግን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ጽድቅ ለብሰን በእዚአብሐር ፊት ልንቆም እንችላለን። ሮሜ ምዕራፍ 8 እንደሚያሳስበን ከሆነ፥ ጌታ ኢየሱስ አስቀድሞ ከፈጸመልን ተግባር የተነሣ የዘላለም ደኅንነታችን ሁኔታ ዋስትና ያለውና የተረጋገጠ መሆኑ ነው። 

አማኛች ለዘላለም ስለተረጋገጠላቸው ደኅንነት ያላቸው አመለካከት እንዴት ነው? 

አንዳንድ ሰዎች፥ አማኞች ያላቸው ደኅንነት ለዘላለም የተረጋገጠ ነው የሚለውን ትምህርት በሚሰሙበት ጊዜ ይጠራጠሩና አሳቡ ሰዎችን የበለጠ ኃጢአት እንዲሠሩ ይገፋፋቸዋል በማለት ይፈራሉ። እንዲያውም ሰዎች «በምንም ሁኔታ ደኅንነቴን አላጣውም፥ ስለዚህ ሄጄ እንዳሻኝ ኃጢአት ልሥራ፥ ወደ ሰማይ የምገባ መሆኔ አሁንም ተረጋግጦልኛል» ብለው ያስባሉ ሲሉ ያምናሉ። ነገር ቀን አዲስ ኪዳን በግልጽ እንደሚናገረው፥ ያገኘውን ደኅንነቱን የሚያጣ መሆኑ ሳይሰማሙ በድፍረት ወደ ኃጢአት ተመልሶ የሚገባ ሰው፥ ዳግም የተወለደ እውነተኛ እማኝ አይደለም። አዲስ ኪዳን እንደሚያስተምረን እውነተኛ የሆኑ አማኞች እግዚአብሔርን ለማስደሰትና ለእርሱ ለመታዘዝ ይፈጥናሉ እንጂ፥ በስሜት ተነሣሥተው ኃጢአትን ለሥራት እይጣደፉም፡: 

ጥያቄ፡- ቲቶ 2:11-13 አንብብ። የእግዚአብሔር ጸጋ ስለ ምን ያስተምረናል? የተኋላ መልስ ሰጡ። መልሳችሁም ልናደርገው ስለሚገባንና ስለማይገባን ነገር የያዘ መሆን አለበት። 

ጥያቄ፡- ሮሜ 6፡1-2 እና 15-18 አንብብ። አማኞች በእግዚአብሔር ጸጋ ሥር በመሆናቸው ኃጢአት ሊሠሩ የማይገባው- በምን ምክንያት ነው? 

በ16ኛው ትምህርታችን ውስጥ፥ ሰዎች የጻኑት በንስሐ፥ በእምነትና በመለወጥ ወደ እግዚአብሔር በመመላስ እንጂ፥ በመልካም ሥራቸው እንዳልነበረ ተመልክተናል። ሆኖም፣ አሁንም ቢሆን መልካም ሥራ በአማኞች ሕይወት ውስጥ በጣም ጠቃሚ ሆኖ ይገኛል፡ መልካም ሥራና ታዣዥነት፥ አዛኝ የሆነ እምነትና ክርስቶስን የሚከተል ደቀ መዝሙር እውነተኛ ፍሬ ምስክር ነው። መልካም ሥራና ታዛዥነት የደኅንነት ውጤቶች ናቸው። እውነተኛና ዳግም በክርስቶስ የተወለዱ አማኞች እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘትና ለእርሱም ”ታዘዝን ይወዳሉ። እንደዚሁም በእውነት ዳግም በክርስቶስ የተወለዱ አማኞች ከኃጢአት ተመልሰው፥ ከእግዚአብሔር በተቀበሉት ጸጋ ያድጋሉ። ቲቶ 2፡11-13 ያለው ክፍል የእግዚአብሔር ጸጋ የተቀበሉትን የሥጋ ምኞትና ኃጢአተኝነትን እንዲክቶ ያስተምራቸዋል ይላል። ሰዎች የእግዚአብሔርን ጸጋ ሰሚቀበሉበት ጊዜ፥ «አሁን ለዘላለም የጻንሁ በመሆኔ፥ የፈለግኩትን ያህል ኃጢአት ልሠራ እችላለሁ» በማለት ማሰብ አይጀምሩም። ከዚህ ይልቅ የእግዚአብሔር ጸጋ የሚያስተምራቸውን ማድመጥ ይጀምራሉ። ይህም ድምፅ «ኃጢአትና የሥጋ ምኛት ለእናንተ አይጠቅሙአችሁም፥ ስለዚህ ያጠፉአችኋል። አሁኑኑ ካዱዋቸው» ይላቸዋል። ሰዎች የእግዚአብሔርን ጸጋ በሚቀበሉበት ጊዜ፥ የእግዚአብሔር ጸጋ ድምፅ እንዲህ ሲል የሚያስተምራቸውን ድምፁን ያዳምጣሉ። ይህ ድምፅም፥ «እግዚአብሔርን በማወቅና እርሱን በማስደሰት በሕይወትህ ውስጥ የምታሳልፈው ጊዜ ትልቁ ጊዜ ነው። ስለዚህ ራስህን በመቆጣጠር፥ በጽድቅና እርሱን በመፍራት ጊዜህን በቁም ነገር ላይ ብታውል፥ እግዚአብሔርን ለማወቅና እርሱን ለማስደሰት ትችላለህ በማለት ያሳስባል። አማኞች እግዚአብሔርን የማስደሰትና እርሱንም የመታዘዝ ፍላጎት ያድርባቸዋል። በክርስቶስ በእውነት የሚያምኑና በእውነት ዳግም የተወለዱ አማኞች ቀድሞ የነበሩበትን ሕይወት እንዲለውጡ በእግዚአብሔር ጸጋ ይቀሰቀሳሉ። 

ጳውሎስ በሮሜ 6 ውስጥ ይህንኑ የመሰለ ትምህርት ያቀርብልናል። አንዳንድ ሰዎች፥ ጳውሎስ ስለ እግዚአብሔር ጸጋ ያስተላለፈው ትምህርት፥ ሰዎችን ወደ ኃጢአት ይመራቸዋል ይላሉ። ጳውሎስ ይህንን ለመሰለ የሐሰት ክስ ለሚያቀርቡ ሰዎች ሊመልስ፥ «የእግዚአብሔር ጸጋ በዝተልን ኃጢአታችንን በመሸፈኑ ምክንያት (ሮሜ 5፡20)፥ በኃጢአት ጸንተን እንኑርን? በምንም ዓይነት ይህ ሊሆን አይገባም» በማለት ይናገራል። ጳውሎስ የሰጠው መልስ በግሪክኛው ቋንቋ አገላለጽ ጠንከር ያለ ለማት አለው። የእግዚአብሔር አዳኝ የሆነው ጸጋ ወደ ኃጢአት ሰዎች እንዲያመሩ ያበረታታል የሚለውን የሐሰት ክስ ሐዋርያው በኃይል ይቃወማል። የእግዚአብሔርን ጸጋ የተቀበሉ ሰዎች አርጌው ሕይወታቸው የሞተ መሆኑን አበክረው ሊነዘቡት ይገባል ይላል። ለእነርሱ እግዚአብሔር አዲስ ሕይወትን ሰጥቷቸዋል። እንዴት አድርገው ወደ አለፈው አርገ ሕይወት ለመመለስ ያስባሉ? በአሮጌው ሕይወታቸው ጊዜ የኃጢአት ባርች ነበሩ ይላል ጳውሎስ በሮሜ 6፡15-18 ባለው ክፍል። አሁን ን ከኃጢአትና ከሞት ፡ ስለሆኑ የጽድቅ ሕይወትን ሊኖሩ ይችላሉ። በእውነት ይህን እግዚአብሔር በጸጋው የሚሰጠውን ሕይወት የተቀበሉ ሁሉ ጽድቅን ማገልገል እንጂ ለኃጢአት መገዛትን አይሹም ይላል። 

ጥያቄ፡- ለዘላለም ደኅንነታችሁ የተረጋገጠላችሁ መሆኑን ማወቃችሁ፥ ጌታን ለመታዘዝና እርሱን ለማገልገል እንድትፈልጉ እንዴት ሊያደርጋችሁ ይችላል? 

ለዘላለም ደኅንነታችን የተረጋገጠ መሆኑን ስንገነዘብ፥ ለእግዚአብሔር ያለን ፍቅር ያድጋል። እንዲሁም በደኅንነታችን ረገድ የሰጠንን አስደናቂ በረከት ሁሉ ማየት እንችላለን። በተጨማሪም እርሱን ለማወቅና እርሱን ለማፍቀር ፍላጎት ያድርብናል። እርሱን ለማፍቀርና እርሱን ለመውደድ ለእርሱ መታዘዝ ይጠበቅብናል። ስለዚህ ጊዜአችንን ከእርሱ ጋር ማሳለፍ አለብን። እንደዚሁም ከእርሱ ጋር የቅርብ ግንኙነት ሊኖረን ይገባል። ደኅንነታችን ለዘላለም የተረጋገጠና የተጠበቀ መሆኑን መገንዘባችን ወደ እግዚአብሔር በበለጠ እንድንቀርብ ያስችለናል። ከዚህ ጋር የዘላለማዊውን ደኅንነታችንን በረከት ስናስተውል፥ ከአሮጌው ሕይወታችን ይልቅ አዲሱ ሕይወታችን በክርስቶስ ውስጥ ጎልቶ ይታየናል። ይህ በሚሆንበት ጊዜ ወደ ቀድሞው አሮጌ ሕይወታችን ዳግም ለመመለስ ጨርሶ አናስብም። በአዲሱ ሕይወታችን ውስጥ በምናገኛቸው መንፈሳዊ ጥቅሞችና በረከቶች ደስ ተሰኝተን መኖርን እንመርጣለን። ያገኘነው ዘላለማዊ ዋስትና በተቀበልናቸው በረከቶች ረክተን በአዲስ ሕይወታችን እንድንኖር ይቀሰቅሰናል። ልክ ልጆች በወላጆቻቸው ጥበቃና እንክብካቤ ውስጥ በመሆናቸው ምክንያት ወላጆቻቸውን ለማክበርና ለመታዘዝ ፍላጎት እንደሚያድርባቸው ሁሉ፥ እኛም በፍቅሩ ጥበቃ ውስጥ መሆናችንን በምንገነዘብበት ጊዜ፥ እግዚአብሔርን ለማክበርም ሆነ ለመታዘዝ በጣም እንፈልጋለን። 

ምንጭ፡- “አስተምህሮ ክርስቶስና ደኅንነት”፤ ጽሑፍ፣ በዶ/ር ስቲቭ ስራውስ፤ ትርጉም በኃይሉ ልመንህ

Exit mobile version